Monday, 27 January 2014 08:38

ጥልፍ ለመማር ጐንደር የመጣው ፈረንሳዊ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(3 votes)

             ሰሞኑን በጐንደር ከጥምቀት በዓል ጋር ተያይዞ የተለያዩ ዝግጅቶች ተካሂደዋል፡፡ ዓመታዊው “የባህል ሳምንት” አካል የሆነው የባዛር ዝግጅት ተጠቃሽ ነው፡፡
ባዛሩን ስጐበኝ ነበር የጐንደር እህት ከተማ ከሆነችው የፈረንሳይዋ ቬንሰን ከተማ ጥልፍ ለመማር የመጣውን  የ21 ዓመት ፈረንሳዊ ወጣት ያገኘሁት፡፡ እድሪያን ይባላል፡፡ እንዴት ወደ ጐንደር እንደመጣ፣ የጥልፍ ሙያ ለመማር  ምን እንዳነሳሳውና ሌሎች ጉዳዮችን አንስተን ተጨዋውተናል፡፡ እነሆ:-
መቼ ነው የመጣኸው?
ሶስት ሳምንት ሆኖኛል፡፡
የመጣህበት ዋና ጉዳይ ምንድን ነው?
በዋናነነት የመጣሁት ጥልፍ ለመማር ነው፤ ነገር ግን ብዙ ጊዜ እንደሰማሁት ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ የሚጐበኙ ነገሮች አሉ፡፡ በተለይ ጐንደር ውስጥ የፋሲል ግንብና ሌሎች ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ቦታዎች እንዳሉ ሰምቻለሁ፡፡ በተለይ ቬንሰን የጐንደር እህት ከተማ ከሆነች በኋላ ስለጐንደር ብዙ ሲባል ሰምቻለሁ፡፡ እግረ መንገዴን ለጉብኝትም ጭምር ነው የመጣሁት፤ በዋናነት ግን ጥልፍ ለመማር ነው፡፡
አሁን ያገኘሁህ ጥልፍ እየተለማመድክ ነው …. መቼ ጀመርክ?
ጥልፍ በራሴ መንገድ መለማመድ የጀመርኩት ፈረንሳይ እያለሁ ከአንድ አመት በፊት ነው፡፡ በአገሬ የዲዛይን ስራዎችን መስራት ከጀመርኩ በኋላ ማለት ነው፡፡ በተለያዩ ጅንስ ሱሪዎች እና ሸሚዞች ላይ የተወሰኑ የጥልፍ ዲዛይኖችን እሰራለሁ፡፡ ለምሳሌ የመስቀል ዲዛይን ለመስራት ሁሌ ነጥቦችን በክብ በክብ እሰራና እሱን እጠልፈዋለሁ፡፡ ግን ሁሌ አንድ አይነት ነው፡፡ በክብ ብቻ ነው መስቀል የምሰራው፡፡
ጥልፍን ለመማር የመረጥክበት ዋናው ምክንያት ዲዛይነር ስለሆንክ ነዋ?
አዎ! በተለይ ኢትዮጵያ ውስጥ ከመጣሁ በኋላ ያየሁት የጥልፍ አይነት ብዙ አይነትና የተለያየ ዲዛይን ያለው ነው፡፡ ለምሳሌ ይህን መስቀል ተመልከቺው (የአበሻ ልብስ ላይ እየጠለፈ ያለውን መስቀል እያሳየኝ) በተለያየ መልክ የመስቀል ቅርጽ መጥለፍ ይቻላል… ይህን በማወቄ ያስደስተኛል። አሁን ጥሩ እየለመድኩ ነው፡፡ ወደ አገሬ ስመለስ ይህን ባህላዊ ጥልፍ ዘመናዊ ልብሶች ላይ በመጥለፍ ትልቅ ባለሙያ የመሆን እቅድ አለኝ፡፡ ፕሮጀክት ነድፌ ስራዎቼንም በኤግዚቢሽን መልክ አቀርባለሁ ብዬ አስባለሁ፡፡ አስተማሪዬ ጐበዝ ሴት ናት፤ በደንብ እያስተማረችኝ ነው፡፡
የመጀመሪያ ሙያህ ምን ነበር?
የመጀመሪያ ሙያዬ ሙያ ከተባለ ማክዶናልድና ሳንዱች አብሳይ ነበርኩኝ፡፡
ይሄን ሙያህን አልወደድከውም?
ምን መሰለሽ? ሳንዱች ማብሰል፣ ማክዶናልድ መስራት …. በቃ ሌላ አዲስ ነገር የለም፤ ሁሌም ተደጋጋሚና አሰልቺ ነው፡፡ በመጀመሪያ የምወደው ስራም አልነበረም፡፡ አሁን ያለሁት መስራት የምፈልገው ሙያ ጅማሮ ላይ ነው፡፡ በዚያ አሰልቺ ህይወት ውስጥ መቆየት አልፈልግም፡፡
በሳንዱችና በማክዶናልድ አዘጋጅነትህ የተዋጣልህ ነበርክ?
በጣም ጐበዝ ነበርኩኝ፤ ስራውን ባልወደውም።
አንተና አስተማሪህ በምን ቋንቋ ትግባባላችሁ?
እኔ “ትንሽ” ፣ “ትልቅ”፣ “አመሰግናለሁ”፣ “እሺ”… የሚሉትን ለመግባቢያ የሚሆኑ የአማርኛ ቃላትን እናገራለሁ፤ አስተማሪዬም ትንሽ ትንሽ እንግሊዝኛ ትችላለች፡፡ አንዳንዴ ሲያቅተን በምልክትም እንግባባለን፤ በአብዛኛው በተግባር የምታስተምረኝ ይበልጣል፤ እስካሁን ለመግባባት አልተቸገርንም፡፡
ከዚህ በፊት ወደ ኢትዮጵያ መጥተህ ታውቃለህ?
አልመጣሁም፡፡ ኢትዮጵያም ጐንደርም ስመጣ የመጀመሪያዬ ነው፡፡
ከጥልፍ አስተማሪህ ጋር እንዴት ተገናኛችሁ?
ብዙ ጥልፍ የሚጠልፉ ሰዎችን አየሁና እሷ ጋር ሄጄ ጥልፍ ታስተምረኝ እንደሆነ ጠየቅኋት፤ እሺ አለችኝ፡፡ ሳያት ከሌሎቹ እሷ ጐበዝ ናት፤ በደንብ ትጠልፋለች፡፡ በዚህ መልኩ ጀመርኩኝ …፡፡
ወደ አገርህ ስትመለስ ለራስህ በልብሶች ላይ ከመጥለፍ ባሻገር እውቀትህን ለሌሎች ለማስተላለፍ አላሰብክም?
ጐንደር ውስጥ በሚኖረኝ ቀሪ ሶስት ሳምንት፣ ጐበዝ የጥልፍ ባለሙያ እሆናለሁ ብዬ አስባለሁ። ቅድም እነደ ነገርኩሽ ዘመናዊና ባህላዊ ልብሶችን በጥልፍ የማሳመር እቅድ አለኝ፡፡ ከዚያ በተረፈ በማቀርበው ኤግዚቢሽንና በስራዬ የሚመሰጥ ካለ እውቀቴን አካፍለዋለሁ፡፡ የራሴ ከተማ ቮንሰን ውስጥ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም አገሮች ግንኙነቶችና ትውውቆች  ስላሉኝ ሙያውን የማስፋፋት እቅድ አለኝ፡፡ ለምሳሌ እንደነ ቬትናም ባሉ አገሮች የማውቃቸው ሰዎች አሉ በእነሱ አማካኝነት ሙያውን የማስተዋወቅና የማስተማር ፍላጐት አለኝ፡፡
የፋሲልን ግንብ ጐበኘህ?
በደንብ ጐብኝቻለሁ፡፡
እንዴት አገኘኸው?
በጣም አሪፍ ነው፡፡ በወሬ ከምሰማውም በላይ ነው የሆነብኝ፡፡ የተገነባበት ዘመን ረጅም እንደመሆኑ ያለው አጠቃላይ የሥነ ህንጻ ዲዛይን አስገርሞኛል፡፡
ኢትዮጵያ እንደመጣህ መጀመሪያ የበላኸው ምግብ ምንድነው?
ፍርፍር ዳቦ
ዳቦ ፍርፍር ማለትህ ነው?
እኔ ያልኩትና አንቺ ያልሽው ልዩነት አለው እንዴ?
የለውም ግን አጠራሩ እኔ ባልኩት መንገድ ይሻላል ብዬ ነው፡፡
ሶሪ… ምግቡ ግን አንድ ነው አይደለ?
አዎ፤ አንድ ነው፡፡ ሽሮ ወጥ፣ ዶሮ፣ ክትፎ… እኒህን ባህላዊ ምግቦችሽ አልቀመስክም?
ያልሻቸውን ምግቦች ቀምሻለሁ፤ ኧረ ፊልተር የሚባል ባህላዊ መጠጥም ጠጥቻለሁ፡፡ የአትክልት ሾርባችሁን ወድጄዋለሁ፡፡ ብቻ ሰውም አገሩም ጥሩ ነው፤ ደስ ይላል፡፡
አየሩስ ተስማምቶሃል?
እስካሁን ያስቸገረኝ ነገር የለም፤ እንደምታይኝ በጥሩ ሁኔታ ላይ ነው ያለሁት፡፡
ከዚህ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰህ የምትመጣ ይመስልሃል?
በተደጋጋሚ የምመጣ ይመስለኛል፡፡ የአሁኑ አመጣጤ ቀጥታ ጐንደር ነው፤ ለጥልፉ ትምህርት።  ነገር ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ የሚጐበኙ ማራኪ ቦታዎች እንዳሉ ሰምቻለሁ፡፡ መጐብኘት እፈልጋለሁ፡፡

Read 3093 times