Saturday, 11 January 2014 11:59

ከአውሮጳነት ወጥቶ ራስን መሆን!

Written by  ደረጀ ኅብስቱ derejehibistu@gmail.com
Rate this item
(3 votes)

      ዛሬ በህይወታችን ውስጥ የአውሮጳ አስተሳሰብና ቁሳቁስ በፈቃዳችንም ይሁን ያለፈቃዳችን ወሳኝ አካላት ስለመሆናቸው የማንክደው እና የማናስተባብለው ደረቅ እውነታ ነው። ምንም እንኳ ሳይንሱ እንደሚለው የሰው ዘር መገኛው እኛ ብንሆንም መንግስታዊ ሥርዓትን በመጀመር ታሪካዊ ቅድሚያ ቢኖረንም ይህንን የበላይነት የአስተሳሰብ ብልጫ በማሳየት በዓለም ላይ ማንጸባረቅ ተስኖናል። ምናልባትም ለቁጥር የሚታክቱ ሰበቦችን መደርደር እንችል ይሆናል፤ ላለንበት ድቀት እና የበታችነት ሥርየት ባይሆኑንም እንኳ። በተቃራኒው ደግሞ በጣም ተንቀርፍፈው ከኋላችን የተነሱ የዓለም ማህበረሰቦች በተለይም ደግሞ አውሮጳዊያን የዓለም የበላይነታቸውን በአስተሳሰብ ብልጫ በማሳየት ማስከበር ችለዋል። ዛሬ እያወቅነውም ይሁን ሳናውቀው እኛ በድንጋይ እና በኀልዎተ እግዚአብሔር ስንጠበብ ዋሻ ውስጥ ይኖሩ በነበሩት በአውሮጳ የአስተሳሰብ ተጽዕኖ ስር ወድቀናል። ዛሬ ላለንበት ሁኔታ ከምናቀርባቸው ሰበቦች መካከል ደግሞ አውሮጳውያን በፍልስፍናው ዘርፍ የሰሩብንን ስውር ደባ ነው። የሰው፣ ያስተሳሰብ፣ የስልጣኔ እናም የሌሎች መሰረታዊ ጉዳዮች ሁሉ መለኪያ አውሮጳ እንደሆነች እራሳቸውን በማሳመናቸው ምክንያት የኛ እውነት አልታያቸው ብሎ እውነትን ሊያስተዋውቁን “በእውነታ ውስጥ የጠፋ እውነታ” አለ ብለው በቅኝ ግዛት ዘመቱብን።እንጭጩን እና ከብት ከብት የሚሸተውን ሰብዕናችንን ሊያድሱልን እነዚያ የዘመነ አብርሆት ጥሙቃን የብርሃን ካባቸውን ተጎናጽፈው በሰይፍ ከታተፉን፣ በታንክ ደፈጠጡን፣ በመርዝ ጋዝ አጠነዘሉን።

አውሮጳዊ የትምህርት ሥርዓትን በመቅረጽ ከማንነታችን ጋር ፊትና ጀርባ እንድንሆን የአውሮጳ ልሂቃን ላባቸውን ጠብ አድርገው ሰርተውልናል። ዘመናዊነት (አውሮጳን መምሰል) ጥንት በፍጥረተ ዓለም ተሰደን እንደ ወጣንባት ገነት ሆና እንድትናፍቀን እናም የራሳችን ባህል በስደት እንደምንኖርባት የእሾህ አሜኬላዋ ምድር እንድትሆንብን የትምህርት ሥርዓታችን እረፍት የለሽ ውጊያ አካሂዶብናል። ዛሬ የቤት እቃዎቻችን፣ የመንግስታችን መልክ፣ ልብሶቻችን፣ ቋንቋችን እና ገጸ−መልካችንም አውሮጳዊ እየሆነ ብቻ ሳይሆን እራሷን አውሮጳን በልጦ ለመታየት እየኳተነ ነው። እንጭጭነታችንን፣ ሰው ለመሆን ብዙ ዑደት እንደሚቀረን እናም ከሰው ይልቅ ለዝንጀሮ የቅርብ ዘመድ እንደሆንን በትምህርት ሥርዓታችን በኩል ደጋግመው ስለነገሩን እራሳችንን ጥለናል። እናም ለሃገራችን ልማት የምንቀርጻቸው መንግስታዊ መመሪያዎችና ደንቦች ሃገሬውን ሳይሆን አውሮጳን ለማስደሰት የታለሙ ናቸው። ሬዲዮኖቻቸው፣ ቴሌቪዥናቸው፣ ሁለመናቸውም በየሰዓቱ የበታችንነታችንን እንድንቀበልና ከተቀበልነውም እንዳንረሳው ሳያሰልሱ ይሰብካሉ።

በሃገረ አሜሪካን እነ ማይክል ጃክሰን የቆዳ ቀለማቸውን ቀይረው ነጭ ላስቲክ እስኪያስለጥፉ ድረስ ህሊናቸው ተቀጥቅጧል፤ ቀሪዎቻችንም የቆዳ ማገርጫ ቀለሞችን፣ የጸጉር ማልወስወሻ ቅባቶችን ቋሚ ሸማች ከሆንን ከራርመናል። ይህ ሁሉ የሚሆነው እራስን ጥሎ አውሮጳን ለመምሰል ነው። ምክንያቱም አውሮጳ የሁሉም ነገር መለኪያ መሆኗን አጠንክራ አስተምራናለችና ነው። ቤታችንን ሸጠን ቪዛ ገዝተን አውሮጳ መኪና ጠባቂ እንሆናለን፣ዶክትሬታችንን ማስያዥያ ሰጠተን ዲቪ ሞልተን የፈረንጅ መጸዳጃ ቤት ጠባቂ እንሆናለን ምክንያቱም ከራሳችን ማንነት ይልቅ የአውሮጳዊነትን ትልቅነት ጠንቅቀን ተምረናልና። ደብተራ ዘነብን አሊያም አባ ገብረሃናን አሊያም ሸህ ሁሴንን እንደ ሐሳብ ማደርጃ ከምንጠቅስ ይልቅ የማርክስን ዲያሌክቲካል ማቴሪያሊዝም ስናንበለብለው ለአፋችን ይቀለናል። ጆን ስትዋርት ሚልን አሊያም ጆን ሎክን እየጠቀስን የፖለቲካ ቅስቀሳ ካላደረግን በዘራያዕቆብ አሊያም በምኒልክ አሊያም በንግስተ ሳባ የፖለቲካ አስተሳሰብ አገራችንን የምንጠቅማት አይመስለንም። ለመሆኑ የፍትሐ ነገስታችን(ምንም እንኳን ከውጭ የተቀዳ ነው ቢባልም) ፖለቲካዊ ፍልስፍና ምንድን ነው? የአውሮጳ የህገ መንግስት ቅርጽ ላይ ከመንጠልጠላችን በፊት ፍትሐ ነገስታችንን አጥብቀን መርምረነዋል ወይ? የአውሮጳ የእኩልነት የነጻነት እና የአንድነት ጥያቄዎችን መልስ ለመስጠት ተብለው የተሸመኑ የፖለቲካ አልባሳት ለኢትዮጵያ ልኳ ሊሆኗት ይችላሉ? በጥቁሩ አይናችን የምናየው በፈረንጆች ሰማያዊ አይን የተቀረጸልንን ምስል ነው፤የእኛው ዓይን የሚቀርጽልንን ምስል ከአዕምሯችን ማዋሃድ ከተሳነን ዘመናት አልፈዋል።

የአውሮጳ ፈላስፎች በራሳቸው አስተሳሰብ ፍቅር ታውረው ቀሪውን ዓለም መረዳት እንደተሳናቸው የሐበሻ ፈላስፋው ፀናይ ሠረቀ ብርሃን The critique of Euro-centrism and the practice of African philosophy በተባለ ድርሳኑ አሳይቶናል። “የአውሮጳ አዙሪት/Eurocentrism/ እንደው ዝም ብሎ አውሮጳን የዩኒቨርሳችን የባህል አውራ የማድረግ የምዕራቡን ዓለም የማንገሥ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን አስተሳሰብን የመቆጣጠር ጉዳይ ዋነኛ ተልዕኮው ነው።” ይለናል ፀናይ። የአውሮጳ አዙሪት ወረራው ረቂቅ በመሆኑ የተነሳም የአዙሪቱ ጡዘት ውስጥ እየገባን እንኳን ከራሳችን ጋር መጠፋፋታችን ምንም ሳይታወቀን ይኸው ሃገርና ማንነት አለን እያልን በኩራት እናወራለን። በአውሮጳዊ የአስተሳሰብ ቅኝት አገራችንን እንመረምራለን፤ ችግራችንን እንገነዘባለን እናም አውሮጳዊ መድኃኒት ለሃገራችን እናዝዛለን፤ትርፉ ግን በበሽታ ላይ በሽታ መጨመር ብቻ። አጥፍቶ ጠፊ ይመስል እራስንም ሌላውንም ለማውደም የአውሮጳን አመለካከት እና ኀልዮት እያጋበስን እራሳችንንም አገራችንንም ማምከን የዛሬ ህይወታችን ፈሊጥ ሆኗል። የገንዘብ አጠቃቀም፣ የሃብት ማጋበስ፣እርካታ ማጣት እናም ሌሎች በሽታዎች ህሊናችንን ካሳቱን እና ካገር ይልቅ እራስን ማስቀደምን ከተካንንበት/ከቀሰስንበት ሰነባብተናል። እኛ ዛሬ ላይ እራሳችንን መሆን ተስኖናል። ግለኝነትና እርስ በእርስ መጠላለፍ እንደ ባቡር መንገድ ዝርጋታችን ዙሪያችንን በሙሉ በገደል እንድንዋጥ አድርገውናል። የሻይ ቤት፣የትምህርት ቤት፣የልጆቻችን ስሞችን እኛን እኛን አይመስሉም እያልን እየመላለስን ባደባባይ ስንተቻቸው ነበር።

አግባብነት ያለው ትችት ነው። ስለራሳችን ታሪክ እኛው እራሳችን የጻፍነውን ሳይሆን ፈረንጆች ስለኛ የጻፉልንን የበለጠ እናምነዋለን። የላቲን ኤቢሲዲ ድግምት አንብዞን፣ የገዛ ሐገራችንን መረዳት ተሳነን። ስለ አውሮጳ አዙሪት የሚሰብከው የአፍሪካ ፍልስፍና ምሁሩ ፀናይ እንኳን የአውሮጳን አዙሪት መቋቋም ተስኖት ኢትዮጵያዊነቱን ጥያቄ ውስጥ አስገብቶታል። አውሮጳ በፍልስፍናዋ የሰራችብንን ደባ መለስ ብለን ማጤን አለብን እያለ እኛን እየመከረ እርሱ ግን ኢትዮጵያ ላይ የተፈጸመውን የአውሮጳዊያን ደባ መመርመር አልፈቀደም። አውሮጳ በትምህርቷ፣ በባህሏ እናም በስፖርቷ ከተቆጣጠረችን ዘመናት አልፈዋል። አንድ የተማረ ኢትዮጵያዊ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ያመልጠኛል ብሎ ኃላፊነቱን ቸል ሲል እብደት እንጅ ምን ይሉታል። አንፈልጋችሁም የኛን አትንኩብን እንኳን ቢሉን ለምነንም ሆነ ከፍለን ወደ አዙሪታችን እንደምንመለስ ግልጽ ነው። በአንድ ወቅት በኮሞሮስ (ምናልባትም ሲሸልስ) ደሴቶች ላይ የወታደር መኮንኖች አምጸው መንግስቱን ከሥልጣን ካወረዱ በኋላ የቀድሞ ቅኝ ገዣቸው ፈረንሳይን እንድታስተዳድራቸው መጥራታቸውን አስታውሳለሁ። ይህ ነው እንግዲህ በአውሮጳ አዙሪት ውስጥ መጦዝ ማለት። በእሽክርክሪቱ ውስጥ ገብተን ስንከንፍ ማገናዘቢያችን ሁሉ ይከዳንና ለምነንም ከፍለንም እራሳችንን ለባርነት እናቀርባለን። አንዳንዶቻችን ኢትዮጵያ ውስጥ ሰው ከመሆን የፈረንጅ ውሻ መሆን ይሻለኛል እያልን ደረታችንን ነፍተን እናወራለን። አንዳንዶቻችንም በፈረንጅ ሐገር በረዶ ጠራጊ ሆነን ያሳለፍነው ህይወት የገነት አጸድ ተንከባካቢ የሆንን ያክል ክንፋችንን ዘርግተን በኩራት እንተርካለን። ከባድ መጋኛ ነው ይህ የአውሮጳ አዙሪት። ቋንቋችን ቀለሙን ቀይሮ አውሮጳን ለመምሰል ከገረጣ እና በባቡር መክነፍ ከጀመረ ከራርሟል።

እንግሊዝኛን ቀጥታ ካማርኛችን ጋር እየቀላቀልነው እንደሆነ ብዙ ግዜ ትችት ሲሰጥ አድምጠናል። ለምሳሌ እነ ኦፍ ኮርስ፣ኦኬ፣የስ፣ራይት ወዘተ ከአፋችን አይጠፉም። ከዚህ ባለፈም ግን የአማርኛችን ሰዋሰውና አስተሳሰባችን እንግሊዝኛ እንግሊዝኛ እየመሰለ ሄዷል። ለምሳሌ “ተረጅዎችን ለመድረስ” ብለን የእንግሊዝኛውን to reach the needy ሐሳብ እንደ ወረደ ባማርኛ ቃላት እንለዋለን። “ዝምታው ይሰበር” የሚለው አማርኛችን የእንግሊዝኛው break the silence ሐሳብ ዲቃላ እንጅ በዘሩ አማርኛ አይደለም፤ ምክንያቱም ባማርኛው የዝምታ ሐሳብ የሚጀመርና የሚያበቃ ጉዳይ እንጅ እንደ ጠርሙስ የሚሰባበር ዝምታ የለምና። ከዚህም የሚከፋው አማርኛ ደግሞ “ያልተወለዱ ህጻናትን እንጠብቅ” የሚለው ይመስለኛል፤ በእንግሊዝኛው let us save the unborn child የሚለው ሐሳብ በቀጥታ ወዳማርኛ ተቀድቶ ያልተወለዱ ህጻናት የሚባል ጉድ ወለደ። ህጻን የሚባለው እኮ የተወለደው ነው፤ ካልተወለደ ግን ጽንስ ነው የሚለው አማርኛችን። እነ “ባለድርሻ አካላት” stake holders፣ እነ “የአንበሳውን ድርሻ” lion’s share፣ እነ “በወፍ በረር” Bird’s eye view እማ ጎጃምኛ ከመሰሉን ሰነባብተዋል። ጉዳዩ እንግሊዝኛ መሆኑ አይደለም ቁምነገሩ አስተሳሰባችንን መንጠቁ እንጅ። የአውሮጳ አዙሪት እንዲህ ነው ቋንቋችንን ብቻ ሳይሆን አስተሳሰባችንንም ነው የሚነጥቀን። ሰከን ማለትን የልብን ትርታ ማድመጥን የጸጉር እንቅስቃሴን ማጤንን የሚጠይቅ ዘመን ላይ የደረስን ይመስላል።

ከዛሬ ሰላሳ ስድስት ዓመት ግድም አቤ ጉበኛ የማርክሳዊ ምሁራንን ቋንቋ አጠቃቀም ለመተቸት ያነሳው ሐሳብ ዛሬ ካለንበት የቋንቋ ጠኔ አንጻር ሲታይ ገለባ ሐሳብ ይመስላል። እንዲህ ይላል “ደግሞ በሌላ በኩል ሁለት ቋንቋዎችን በማጋጨት ለማንም ሊገቡ የማይችሉ ጉድ ቃላትን እየፈጠርሁ ወገኖቼን አላደናገርሁም።……የኛ ሊቃውንት ደግሞ ሁለቱን ቤተ−ዘመድ ቋንቋዎች፤ግዕዝና አማርኛን እያዳቀሉ የሚፈጥሯቸው ቃላት ለጆሮም ለአእምሮም ጉዶች የሆኑ ማጭበርበሪያዎች ናቸው። ይህ ነገር ጠቃሚ ቢመስለኝ እኔም ብገባበት እችል ነበር።……ግን ስንት ሥራ ሞልቶ የማያስፈልጉ ቃላት ለመፍጠር ሁለት ቋንቋዎችን ሲያሣርሩ{ሲያዳቅሉ} መዋል በአዲስ ዘመኑ ቋንቋ ለመጠቀም ʽከፍተኛ የፖለቲካ አሻጥርʽ መሰለኝ።” ይለናል አቤ ጉበኛ የዚያን ዘመኑን ምሬት ለመግለጽ። ዛሬ ላይ በጉድ {ተፈጥሯቸው የተበላሸ} ቃላት አይደለም የተቸገርነው በጉድ ሐሳቦች እንጅ። ቃላትን ሰባበረ ብሎ ከትውልዱ ጋር የተጣላው አቤ ዛሬ ሐሳብ ፍርክስክሱ ሲወጣ ቢኖር እራሱን በገመድ ሰቅሎ እንደሚያጠፋ ጥርጥር የለውም ነበር። ዛሬ እግር ከወርች ጠፍንጎ የያዘንን የሐሳብ ባርነት ለመበጣጠስ ያቤ ጉበኛን “ከፍተኛ የፖለቲካ አሻጥር” ቀለል አድርገን እንድናየው የሚያስገድድ ዘመን ነው። ግእዝና አማርኛን እያዳቀሉ አዳዲስ ቃላትን መፍጠሩ አንቱ የሚያስብልና የፕሮፌሰርነት ማዕረግ የሚያሰጥ ሙያ መሆኑ የተለመድ ጉዳይ ሆኗል (አንዳንዶቻችንም ድፋኔ (definition)፣ምየላ (mailing) እያልን መንገዱን ሸርሽረን አንቱታን ተጎናጽፈናል።) የመጣንበትን መንገድ መለስ ብለን አብጠርጥረን ስናስበው አሽቀንጥረን መጣል ያለብን ብዙ የአውሮጳ ግሳንግስ እንዳለ እናስተውላለን ይኧንን ባናደርግ ግን አባቶቻችን ድል ያደረጓት የቅኝ ገዥዋ አውሮጳ የነተበ አስተሳሰብ ተገዥ ከመሆን ውጭ ምንም የሚቀርብን ነገር የለም ማለት ነው። ፀናይ ሠረቀ ብርሃን የሐሳብ “ከፍተኛ አሻጥር” ተሰርቶብናል ብሎ ያምናልና የተማርነውን ነገር ወደ “አለ−መማር” መለወጥ እንዳለብን እንዲህ ያሳስበናል “ዛሬ በዚህ በድኅረ−ቅኝ ግዛት ዘመን ከመቸውም በላይ ስውር ጭቆና በአውሮጳና አሜሪካ ባህል ቀመስ በሆኑት በኛው ሰዎች እየተፈጸመብን ነው።

እኛው አውሮጳ ቀመሶች ለሃገራችን እምቁን ትሩፋት ለማምጣት አሊያም የአውሮጳን ግልባጭ ለመሆን ሥልጣኑን ተቆጣጥረነዋል።” ሰው በአካሉ ባርነት ቢገዛ በትግል ነጻነትን መጎናጸፍ ይችላል፤ በሐሳብ ባርነት ቢገዛ ግን በባርነት በተያዘ ሐሳቡ ለነጻነት ለመታገል ሱሪ ባንገት ይሆንበታል። ግን አማራጭ የለም፤ ሱሪያችንን መቅደድ ሊኖርብን ይችላል። የተማርን የሚመስለንን ሐሳብ ማጥፋት ሊኖርብን ይችላል ማለት ነው (unlearning the learned)። ስህተት የሆነን ነገር የተማረ ሰው፤ ከስህተት ህይወቱ ለመውጣት የተማረውን ነገር ሁሉ ማጥፋት ይጠበቅበታል። ሰው ከመንፈሳዊ ህይወቱ ህፀጾች ለመንጻት ወደ መንፈሳዊ መሪዎቹ እየቀረበ ምክርና ኑዛዜ እየተቀበለ የመንጻት እድልን እንደየኃይማኖቱ ተጎናጽፏል። ከአውሮጳ/ከሐሳብ ህጸጾች ለመንጻት ግን የሐሳብ አባት የለውምና እንደኔ እንደኔ ከሆነ እራሱን በራሱ ማናዘዝ ግድ ሳይሆንበት አይቀርም። ከአውሮጳ ለመላቀቅ እራሳችንን በራሳችን ቀኖና መስጠት ይጠበቅብን ይሆናል። ከአውሮጳ አንዳች የምናተርፈው ነገር የለም ብሎ መደምደም ከባድ ስህተት ውስጥ የሚከት ጉዳይ ነው። በአውሮጳዊው ሰው የተፈተሹ ምርምሮች ለጥቁር አፍሪቃዊውም የሚረባ አንዳች ነገር አይታጣላቸውምና። ነገር ግን አውሮጳ በምርምሩና በሐሳቡ ጥልቀትም ቀድማን ሄዳለችና የእርሷን መንገድ መከተል አለብን ማለትም ከድጡ ወደ ማጡ ማሽቆልቆል ይሆናል። ሰከን ማለትን፤ ወደኋላ መመለስን የሚጠይቅ ዘመን ላይ እንደ ደረስን ውስጤ ይጎተጉተኛል። በእርግጥ ግን ላሊበላን እንዴት እንዳነጽነው መልስ የሚሰጠን ማን ነው? የአክሱምንስ ሃውልት እንዴት እንደጠረብነውና እንዳቆምነው መልስ መስጠት የተሳነን ስለ ምንድን ነው? የኛ የሳይንስ ትምህርት ለዚህ መልስ ካልሰጠ ፋይዳው ከቶ ምን ይሆን? ማንነትን ማሰስ እና ማብጠርጠር አስገዳጅ እርምጃዎች የሚሆኑበት ዘመን ይመስላል ዘመናችን። የኢትዮጵያን ዳግም ልደት ለማየት ያብቃን።

Read 2820 times