Saturday, 11 January 2014 11:05

“የእኔን መመረጥ የተቃወሙት ከሦስት አይበልጡም”

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(4 votes)

አንድነትን ለመሰለል ኢህአዴግ ጊዜ የሚያጠፋ አይመስለኝም
ፓርቲው ኢንጂነር ግዛቸውን በመምረጡ አትርፏል ባይ ነኝ…
አንድነት ፓርቲ በቅርቡ መንግሥት ሆኖ እቺን አገር ይመራል…
በሲቪል ምህንድስና የመጀመሪያ ድግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የተቀበሉት ኢንጂነር ዘለቀ ረዲ፤ ወደ ፖለቲካው የገቡት የመኢአድ ፓርቲ የጂማ አስተባባሪ በመሆን ነበር፡፡ በ2000 ዓ.ም የተመሠረተው ብርሃን ለአንድነትና ለፍትህ ፓርቲ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት በመሆንም አገልግለዋል፡፡ የዛሬ ሁለት ዓመት ፓርቲው ከአንድነት ፓርቲ ጋር ውህደት ከፈጠረም በኋላ የድርጅት ጉዳይ ሃላፊ ሆነው የሰሩት ኢንጂነር ዘለቀ፤ ከፓርቲው አመራሮች ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ራሳቸውን ከሃላፊነት አግልለው እንደነበር ይታወሳል፡፡ በቅርቡ የፓርቲው ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡት ኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው፤ ኢንጂነር ዘለቀን የውጭ ግንኙነት ሃላፊ አድርገው ሾመዋቸዋል፡፡ ሹመታቸውን ተከትሎም በአንዳንድ አመራሮች ተቃውሞ እንደተነሳ ሲገለፅ ሰንብቷል፡፡ የኢንጂነር ዘለቀ ምን ይላሉ? አዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ኢንጂነር ዘለቀ ረዲን በአዲሱ ሹመታቸውና በፖለቲካ ህይወታቸው ዙሪያ አነጋግራቸዋለች፡፡

 ጥያቄዬን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው በሰሩበት “ብርሃን ለአንድነት ለዲሞክራሲ” ፓርቲ ልጀምርና ፓርቲው መቼ ተቋቋመ? እንዴትስ በምክትል ተቀዳሚ ፕሬዚዳንትነት ተመረጡ? ብርሃን ለአንድነት ለዴሞክራሲ (ብርሃን) ፓርቲ የተመሰረተው በ2000 ዓ.ም ነው፡፡ ምርጫ ሲካሄድም እንዳልሽው ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት አድርገው መርጠውኛል፡፡ በእርግጥ በወቅቱ ከነበረብኝ የስራ ጫና የተነሳ ሃላፊነቱን ለመቀበል ፈቃደኛ አልነበርኩም፡፡ ነገር ግን “መስራት አለብህ” የሚል ጫና ስለመጣ በሃላፊነት መስራት ጀመርኩኝ። በአንድ ፓርቲ ውስጥ ምክትል ተቀዳሚ ፕሬዚዳንት ሆኖ ለመመረጥ በፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ልምድ ያካበተ መሆንን የሚጠይቅ ይመስለኛል፡፡ እስቲ ስለፖለቲካ ልምድዎ ትንሽ ያጫውቱኝ? ከብርሃን በፊት በመላው አማራ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ውስጥ ተሳትፎ ነበረኝ፡፡ ከዚያም በተጨማሪ በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) ውስጥም ጅማ ውስጥ እሰራ ስለነበረ በፖለቲካው ልምድ ስላለኝ ነው የተመረጥኩት። ምንም እንኳ ሃላፊነቱን በጫና ብቀበልም ብርሃን ብዙ የተማርኩበት ፓርቲ ነው ማለት እችላለሁ፡፡ ከአንድነት ፓርቲ ጋር ከሁለት አመት በፊት በዲአፍሪክ ሆቴል ውህደት መፍጠራችሁ ይታወቃል፡፡ ውህደቱ ያስፈለገው ለምንድን ነው? በፓርቲያችን እና በእኛም አመራሮቹ ፓርቲዎች ተበታትነው መስራታቸው ውጤት አያመጣም የሚል እምነት ስለነበረ፣ ተነሳሽነቱን ወስደን የእንዋሀድ ጥያቄ አቀረብን፡፡ በደብዳቤ ከጠየቅናቸው በርካታ ፓርቲዎች ውስጥ አንድነትና መኢአድ ጥያቄውን ተቀበሉ፡፡

ከዚህ በኋላ የሶስትዮሽ ውይይት ማድረግ ጀመርን፡ በዚህ ሂደት ላይ መኢአድ፤ አንድነት ከመድረክ አባልነቱ ከወጣ እንደሚዋሃድ አስታወቀ፡፡ በወቅቱ የመኢአድ ጥያቄ የውህደትን ፋይዳ የሚቃረን እንደሆነ አመንን፡፡ የተነሳንበት አላማ የተበታተነ ሃይል፣ እውቀት፣ አባል… ይዘን ከምንታገል እውቀታችንን፣ ገንዘባችንንና አባላትን በአንድ አደራጅተን የተሻለ አቅም እንፍጠር የሚል ስለነበር የመኢአድን “አንድነት ከመድረክ ይውጣ” ጥያቄ ውድቅ በማድረግ፣ ከአንድነት ጋር ውህደቱን ልንፈጽም ችለናል፡፡ ከአንድነት ጋር ውህደት በፈፀማችሁበት ዕለት ፓርቲው አዲስ ፕሬዚዳንት ለመምረጥ ባደረገው ምርጫ ከዶ/ር ነጋሶ ጋር ተፎካክረው ነበር፡፡ አሸንፋለሁ የሚል እምነት ነበርዎ? በወቅቱ ሁለቱ ፓርቲዎች ሲዋሀዱ “ለፕሬዚዳንትነት መወዳደር እፈልጋለሁ የሚል ራሱን በእጩነት ያቅርብ፣ በጥቆማ መሆኑ ይቅር” የሚል ነገር ነበር፡፡

እኔ በብርሃን በኩል ራሴን አቀረብኩኝ፡፡ በእርግጥ ከልምድም ከምንም አኳያ ፕሬዚዳንት ሆኜ ፓርቲውን ለመምራት አቅሙ አልነበረኝም፡፡ ታዲያ ለምን በውድድሩ ተሳተፉ? ምርጫውን ዲሞክራሲያዊ ለማድረግ ነው የተወዳደርኩት፡፡ በወቅቱ ሰዎች በዴሞክራሲያዊ መንገድ ተወዳድረው ማሸነፍ ባይችሉም እንኳን በዚያ ውድድር መውደቅ ማለት ራሱ ማሸነፍ እንደሆነ ለማሳየት ነበር የተወዳደርኩት፡፡ ለፕሬዚዳንትነት ተወዳድረው በዶ/ር ነጋሶ ከተሸነፉ በኋላ በፓርቲው ውስጥ የተሰጥዎ ሃላፊነትዎት ምን ነበር? የአንድነት ፓርቲ የድርጅት ጉዳይ ሃላፊ ሆኜ ተመረጥኩ፡፡ በዚህም ሃላፊነት ከአንድ አመት በላይ ሰርቻለሁ፡፡ ነገር ግን ከዚህ ሃላፊነት በተጨማሪ በፓርቲው ውስጥ አዳዲስ የአሰራር ስልቶችን አምጥቻለሁ፡፡ ለምሳሌ? በተለይ በአንድነት አባላት ዘንድ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ ሰርቼአለሁ፡፡ ለምሳሌ ፓርቲው የፋይናንስ ችግር ነበረበት፡፡

ገንዘብ የለኝም ብሎ በቀጥታ ከመናገርና እጅን አጣጥፎ ከመቀመጥ የአንድነትን የአምስት አመቱን ስትራቴጂክ እቅድ ለአባላት ለማሳወቅ፣ ከየክልሉና ከየገጠሩ የሚመጡ አባላት ዶ/ር ነጋሶን ጨምሮ በቢሮ ውስጥ ሰሌን አንጥፈን በመተኛት፣ አባላት ስለፓርቲው እውቀትና ግንዛቤ እንዲኖራቸው በጣም ሰርተናል፡፡ እነዚህ አባላት በራሳቸው አበል መጡ፤ እኛም የተወሰነ ድጐማ አደረግንና በትንሽ ወጪ በርካታ ስራ ሰራን። አስቢው ለአባላት አበል እንክፈል፣ አልቤርጐ እንከራይ ብንል ፓርቲው ገንዘብ የለውም፡፡ ግን ገንዘብ የለም ብሎ ከመቀመጥ በእነዚህ ስልቶች አባላትን በማሳወቅና በማንቃት የተሻለ የትግል ውጤት ማምጣት ይቻላል በሚል ይህን ሰርቻለሁ፡፡ በዚህ በእርስዎ ስልት ምን ውጤት መጣ? እውነት ለመናገር በፊት ሳይከፈለን አንሰራም የሚሉ ሰዎች ወደየመጡበት ከተመለሱ በኋላ በራሳቸው ተነሳሽነት፣ በራሳቸው ገንዘብ እየተንቀሳቀሱ፣ በየክልሉ ከ27 በላይ ቢሮዎች እስከመክፈት ደርሰው ነበር፡፡ ይህ ትልቅ ውጤት ይመስለኛል፡፡ በዚሁ ሃላፊነት ላይ እያሉ ከፓርቲው አመራሮች ጋር ተጋጭተው በርካታ ችግሮች መከሰታቸው ይታወሳል፡፡ በየጋዜጣው እስከመወቃቀስና እስከ መዘላለፍ ደርሳችሁ ነበር፡፡ የግጭቱ መንስኤ ምን ነበር? እውነት ለመናገር ያ ያለፈ ጉዳይ ስለሆነ አሁን ላለንበት ጊዜ ጠቃሚ አይደለም፡፡ መንስኤው ላልሽው በወቅቱ አንዳንድ ችግሮች ነበሩ፡፡ አንዳንድ ሰዎች እኔ የመስራት አቅም እንደሌለኝ ይናገሩ ነበር፡፡ እኔ ደግሞ በዛን ወቅት የመስራት አቅም እንዳለኝ ለማሳየት ሞክሬአለሁ፡፡ በእርግጥ አንዳንድ ግለሰቦችና በፓርቲው ውስጥ ያሉ የሚዲያ አካላት ነገሩን ወደ ሌላ ለማዞርና ሌሎች ሰዎችን ለማጥቃት በሞከሩበት ስልት ሊያጠቁኝ ሞክረው ነበር፡፡ ሊሳካላቸው አልቻለም እንጂ፡፡ “ሌሎችን ለማጥቃት በሞከሩበት ስልት” ያሉትን ሊያብራሩት ይችላሉ? ለምሳሌ “እገሌ ኢህአዴግ ነው” በሚል ታፔላ እየለጠፉ ብዙ ለዚህች አገር ጠቃሚ የሆኑ ሰዎች ባልዋሉበት እየዋሉ፣ አንዳንዶቹ ተሰብረው አንዳንዶቹ ደግሞ “አልሰበርም” ብለው እየተለመጡና እየጐበጡ ትግላቸውን የቀጠሉ አሉ፡፡ ለምሳሌ አንቺ ጋዜጠኛ ነሽ፤ አንዱ ተነስቶ ኢህአዴግ ናት ቢልሽ በየሄድሽበት ሁሉ ስራሽ ላይ እንቅፋት ይፈጠራል፡፡ “ይቺማ በቃ ኢህአዴግ ናት፤ አቃጣሪ ናት” እየተባልሽ ስራሽንና አካሄድሽን ያበላሹብኛል፡፡ እኔም በዚህ መንገድ ነው ጥቃት የተቃጣብኝ፡፡

ግን እኔ ኢህአዴግ ሆንኩም አልሆንኩም ያንን ስም ሲሰጡኝ መነሻቸው ምንድነው? በእንቅስቃሴሽ፣ በጥንካሬሽና በአካሄድሽ የምትበልጫቸውና እነሱን የምትሸፍኛቸው ሲመስላቸው ከመሬት ተነስተው ስም ይሰጡሻል። በእኛም ፓርቲ ውስጥ ራሳቸውን ጋዜጠኞች ነን ብለው የሰየሙ ሁለት ግለሰቦች፣ እኔን “ኢህአዴግ ነው” እስከማለትና ፌስ ቡክ ላይ እስከ መለጠፍ ሙከራ አድርገዋል፡፡ ነገር ግን ህዝቡ አልተቀበላቸውም፡፡ አንደኛ አሁን በፖለቲካው ህዝቡ በጣም እየነቃ ያለበት ጊዜ በመሆኑ፣ እንዲህ አይነቱ ፍረጃና አካሄድ ውጤት አልባ መሆኑን የተረዱት ይመስለኛል፡፡ በእኔ በኩል ደግሞ እነዛን ሰዎች ከሃላፊነቴ ሳልለቅ ውስጥ ሆኜ የበለጠ መታገል እችል እንደነበር የተማርኩበት ነው፡፡ በወቅቱ እኔ ከሚባለው ውንጀላ ንፁህ መሆኔን ለማሳየት ብዙ ጥሬያለሁ፡፡ አንዳንዶች ደግሞ እኔን እዚያው አፍነው ለማስቀረት ጥረው ነበር፡፡ ከጥረታቸው መካከል ለጋዜጠኞች እየደወሉ “ዘለቀን ኢንተርቪው አታድርጉ” የሚለው ይገኝበታል፡፡

ነገር ግን በተለያዩ ጋዜጦች ላይ የሚሰሩ ጋዜጠኞች፣ የእነዚህን ግለሰቦች ጥያቄ ውድቅ በማድረግ የተፈጠረውን ነገር እንድናገርና እውነቱ እንዲወጣ እድል ሰጥተውኛል፤ አመሰግናቸዋለሁ፡፡ በወቅቱ በተነሳው አለመግባባት እርስዎ በፈቃዴ ሃላፊነቴን ለቅቄያለሁ ቢሉም የፓርቲው አመራሮች ግን በዲሲፒሊን ጉድለት እንዳሰናበቱዎት የሚያሳይ ደብዳቤ እስከማቅረብ ደርሰዋል፡፡ የትኛውን እንመን? አንቺ የምትይውን ደብዳቤ እኔ አላየሁትም፤ አልደረሰኝምም፡፡ ከተሰናበትኩ መቼም ደብዳቤው መድረስ ያለበት ለእኔና ለእኔ ብቻ ነው፡፡ አንድ ሰው ደግሞ ደብዳቤ ሲቀበል ፈርሞ ነው፡፡ ነገር ግን ደብዳቤውን አላየሁትም፤ አልደረሰኝም፡፡ ባላየሁት ደብዳቤ ላይ ከዚህ በላይ መልስ መስጠት አልችልም፡፡ እርግጥ ከሁለቱም ወገን ራስን ለማዳን የሚደረጉ ጥረቶች ነበሩ፡፡ ራስን ለማዳን ሲሉ? ከፓርቲው ወገን ግለሰቦቹ ራሳቸው ትክክል እንደሆኑ ለማሳየት በርካታ ጥረት አድርገዋል። በእኔም በኩል ትክክል መሆኔን ለማሳየት ጥረት አድርጌያለሁ፡፡ መጨረሻ ላይ አሸናፊውን የምታይው ነው፡፡ ግን እኮ ለዚህ ሁሉ ግጭት መንስኤ የሆነውን አስኳል ጉዳይ በግልፅ አልነገሩኝም፡፡ “ስራዬ ከአቅም በላይ ስለሆነባቸው ፈረጁኝ” ብቻ ነው ያሉኝ… ለምን መሰለሽ ያልነገርኩሽ… አሁን ላይ ስለማይጠቅም ነው፡፡ ነገሩ አለፈና የግለሰቦች ሃሳብ የግለሰቦች ሆኖ ቀረ፡፡ የአንድነት ፓርቲ አባላት ደግሞ በአሁኑ ምርጫ ፍትሀዊ ውሳኔ ሰጥተውበታል።

ስለዚህ ወደኋላ ተመልሶ ነገር ማነቃነቁ አላስፈለገኝም፡፡ ይህ ለማንም አይጠቅምም፡፡ ህዝቡ የማወቅ መብት ያለው አይመስልዎትም? ጠቃሚ ነገር ስለሌለው ምንም አይሰራም። አሁን ከእነዛ ግለሰቦችና ከእኔ የትኛው ትክክል እንደሆነ የፓርቲው አባላት ፍርድ ስለሰጡበት ማንሳት ጠቃሚ አይደለም፡፡ የፓርቲው አባላት ነገሩን በሰከነ ሁኔታ ይከታተሉ ነበር፣ ያጤኑ ነበር፣ ያነብቡ ነበር፡፡ አባላት እድሉን ሲያገኙ በምርጫው ወቅት ማን ትክክል እንደሆነ አውቀው፣ አሁን ፋይሉ ተዘግቶ ወደ መዝገብ ቤት ተመልሷል፡፡ ይሄ ደግሞ ይግባኝ የለውም፡፡ እርስዎ ላይ ከሚቀርቡ ቅሬታዎች አንዱ ቀደም ሲል እርስዎ እንደገለፁት “የፖለቲካ ብስለት የለውም” የሚል ሲሆን ሁለተኛው “አንድነትን ተጠቅሞ የራሱን ቢዝነስ ያጧጡፋል፤ ከፓርቲው ምስጢሮችን ለኢህአዴግ ያሾልካል፣ በአጠቃላይ ኢ/ር ዘለቀ ኢህአዴግ አንድነትን እንዲሰልል የላከው ነው” የሚሉ ናቸው፡፡ በእነዚህ ውንጀላዎች ዙርያ የእርስዎ ምላሽ ምንድን ነው? ዌል… ይህንን ያልሽውን ሁሉ ግለሰቦች ሚሊዮን ጊዜ ሊያወሩ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን በመረጃ አስደግፎ የሚያቀርብ የለም፡፡ አንደኛ እኔ ኢህአዴግ ለመሆን በአንድነት ፓርቲ በኩል ማለፍ አያስፈልገኝም፡፡ ኢህአዴግ ለመሆን የተዘጋ በር ያለ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም ከእኛ ጋር የነበሩ በእውቀትም በችሎታም ከእኛ በታች የነበሩ ናቸው ኢህአዴግ ሆነው እላይ ተሰቅለው ያሉት፡፡

ሌላው አንድነት ምን የሚሰለል ምስጢር አለው? እስቲ ንገሪኝ... አንድነት እኮ ግልጽ ፓርቲ ነው፤ ዲሞክራት ነው፡፡ እያንዳንዱን እንቅስቃሴውን በግልፅ የሚያከናውን ፓርቲ ነው፡፡ ይህንን ፓርቲ ለመሰለል ኢህአዴግም ጊዜ የሚያጠፋ አይመስለኝም፡፡ ይህንን እንደተልዕኮ ተቀብሎ ጊዜውን የሚያጠፋ የዋህ ያለ አይመስለኝም፡፡ የሚሰለለው እኮ መሳሪያ ታጥቆ በጦርነት የሚታገል ሲሆን ነው፡፡ ዛሬ ይህን አወድማለሁ፣ ነገ እዚህ ቦታ ላይ ጥቃት እሰነዝራለሁ፣ መንግስትን በማሸበር ስልጣን እነጥቃለሁ፤ የሚል ፓርቲ ሲሆን ነው የሚሰለለው፡፡ አንድነት በሰላማዊ ትግል የሚጓዝ፣ በግልጽ የሚንቀሳቀስ ፓርቲ ነው፡፡ ምን ምስጢር አለውና ይሰለላል? እርስዎ ይህን ይበሉ እንጂ አንዳንድ ወገኖች ግን “መንግስት በተለያዩ ፓርቲዎች ውስጥ ሰላዮችን በመመደብ ተቃዋሚዎች ኢህአዴግን ለመታገል የሚነድፏቸውን ምርጥ ምርጥ ስልቶች ቀድሞ በማወቅ እነዛን ስልቶች ያደናቅፋል፣ መንገድ ይዘጋል” በማለት ይከራከራሉ፡፡ እርስዎ በዚህ ይስማማሉ? የትግል ስልቶች ይነደፋሉ፤ ልክ ነው፡፡ ግን በምስጢር የሚያዙ አይደሉም፡፡ አንድነት በጋዜጣ ይጽፈዋል ብሮሸር ይበትናል፣ ለአባላት በተለያዩ መንገዶች እንዲደርሳቸው ይደረጋል፣ ለተለያዩ ሚዲያዎች በጋዜጣዊ መግለጫና በቃለ ምልልስ ይፋ ያደርጋል፡፡ ስለዚህ ምንም የሚደበቅና ለስለላ የሚያበቃ ነገር የለም፡፡ ምንም አይነት ድርጅታዊ ምስጢር የለም እያሉኝ ነው? ምንም ምስጢር የለም፤ ሁሉም ግልጽና ክፍት ነው፡፡ ለምሳሌ ፓርቲው የአምስት አመት እቅድና ስትራቴጂ አለው፡፡ ይህንን በመጽሐፍ መልክ አውጥተን ሸጠነዋል፡፡ ለአባላት በትነናል። አደረጃጀታችን ከማንም የተሰወረ አይደለም። አባላት መታወቂያ ተሰጥቷቸው በግልጽ በአንድነት አባልነታቸው ይንቀሳቀሳሉ፡፡ ድሮ አባላት አባልነታቸውን ይደብቁ ነበር፤ አሁን ያ ነገር የለም፡፡

አንድነት እኮ በቀጣይ መንግስት ሊሆን የሚችል ነው። ስለዚህ ዛሬ ትንንሽ ነገሮችን ደብቆ የሚንቀሳቀስ ትንሽ ፓርቲ ሊሆን አይችልም፡፡ ከሳምንት በፊት ስለተካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ እና ምርጫ ከማንሳታችን በፊት ከፓርቲው ለምን ያህል ጊዜ ተገልለው ቆዩ? ከፓርቲው እንቅስቃሴ ለአንድም ቀን ገለል ብዬ አላውቅም፡፡ ምክንያቱም የብሔራዊ ምክር ቤቱ አባል ነኝ፡፡ በወቅቱ ራሴን ያገለልኩት ሊቀመንበሩ ከሰጡኝ ሃላፊነት እንጂ ህዝቡ ከሰጠኝ ስልጣን ራሴን ላገልል አልችልም፡፡ ከዚህ አንፃር ለአንድ ቀንም ቢሆን አልተገለልኩም፡፡ ለምሳሌ በቅርቡ “የሚሊዮኖች ድምጽ ለነፃነት” የሚል ንቅናቄ ፓርቲው ሲያካሂድ፣ በጥሬ ገንዘብ 15ሺህ ብር፣ መኪናዬንና ሹፌሬን በመስጠት፣ እንዲሁም ለንቅናቄው ለሚሄዱት ሰዎች አበል እና መሰል ድጋፎችን በማድረግ ከአዲስ አበባ እስከ ባሌ ድረስ ንቅናቄናው እንዲካሄድና ሰላማዊ ሰልፉ እንዲደረግ አስተዋጽኦ አድርጌያለሁ፡፡ በብሔራዊ ምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባኤና ወርሃዊ ጉባኤ ላይ እገኛለሁ፣ በመዋጮ እሳተፋለሁ፣ ፓርቲዬን በተመለከተ በጋዜጣ ላይ እጽፋለሁ፡፡ ይህን ሁሉ ስታይው አንድም ቀን ከአባልነት ሃላፊነቴ ገሸሽ ብዬ አላውቅም፡፡ የኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው የፓርቲው ፕሬዚደንት ሆኖ መመረጥ ብዙዎችን እያነጋገረ ነው፡፡ ከሚደመጡት አስተያየቶች መካከል “ፓርቲው ኢ/ሩን መምረጡ ኪሳራ ነው” የሚለው ጐላ ይላል፡፡ የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው? በመጀመሪያ የኢ/ር ግዛቸውን መመረጥ ኪሳራ ነው የሚል ካለ ትርፍና ኪሳራን የማያውቅ ነው ብዬ እደመድማለሁ፡፡ እንደውም አንድነት ፓርቲ ኢ/ሩን በመምረጡ አትርፏል ባይ ነኝ፡፡ የአንድነት አባላት እውነት ለመናገር ሁሉን የሚያውቁ ሚዛኖች ናቸው፡፡ ምን ማድረግ እንዳለባቸው እና በምን ጊዜ ማንን መምረጥ እንዳለባቸው ያውቃሉ፡፡ ለምሳሌ ከሁለት አመት በፊት እኔ ተወዳድሬ ነበረ፡፡

በዛን ወቅት እኔ በነበረኝ አቅም አንድነትን መሸከም እንደማልችል ጠንቅቀው ያውቁ ነበር፡፡ ስለዚህ ዶ/ር ነጋሶን መረጡ፡፡ በጣም ትክክል ነበሩ፡፡ በአሁኑ ወቅትም ሶስት ተወዳዳሪዎች ነበሩ፡፡ ኢ/ር ግዛቸው፣ አቶ ግርማ ሰይፉና አቶ ተክሌ ማለት ነው፡፡ አቶ ተክሌ ኢ/ር ግዛቸው ለውድድር መቅረባቸውን ሲያውቅ ራሱን አገለለ፡፡ ይህን ያደረገው በፖለቲካ ልምድ፣ በትምህርት፣ በእድሜና በአጠቃላይ ብቃት እርሳቸው ፓርቲውን ቢመሩ ይሻላል በሚል ነው። ከዚያ በኋላ በኢ/ር እና በአቶ ግርማ መካከል ፉክክሩ ተካሄደ፡፡ አቶ ግርማ ወጣት የሚባል ባይሆንም እድሜው ከኢ/ር ግዛቸው በታች ነው፡፡ ነገር ግን ያገኘውን ድምጽ ስትመለከቺ ኢ/ር ግዛቸው ካገኙት ጋር በጣም የተራራቀ ነው፡፡ ይህ የሆነው ህዝቡ ፓርቲውን በአሁኑ ሰዓት ማን የመምራት ብቃት አለው የሚለውን መዝኖ በሰጠው ውሳኔ ነው፡፡ ትክክለኛ ውሳኔና ፍትሀዊ ምርጫ ነው። ኢህአዴግም ልክ እንደ አንድነት ለህዝቡ እድል ቢሰጠው የሚመራውን በትክክል ይመርጥ ነበር፡፡

በበኩሌ ኢህአዴግ ከአንድነት መማር ያለበት ነገር አለ ብዬ አምናለሁ፡፡ ኢ/ር ግዛቸው የመረጧቸው የካቢኔ አባላት ለቦታው ይመጥናሉ ብለው ያምናሉ? በትክክል! አንዳቸውም የካቢኔ አባላት ያለቦታቸው አልተቀመጡም፡፡ ልብ ብለሽ ከሆነ ኢ/ሩ የመረጧቸው የካቢኔ አባላት እኛም ወጣት የምንባል ከሆነ አብዛኞቹ ወጣቶች ናቸው፣ የበፊቶቹን አብዛኞቹን አባላት አልመረጧቸውም፡፡ ይህን ስትመለከቺ በአሁኑ ሰዓት አንድነት አትርፏል ትያለሽ፡፡ በእርግጥ ይህን ኪሳራ ብለው የሚያስወሩ ከሁለት የማይበልጡ አባላት ይኖራሉ፡፡ አንደኛ ትርፍና ኪሳራን በውል ለይተው የማያውቁ ናቸው፡፡ ሁለተኛው አንድነት አሁን ያለበት ሁኔታ በእርግጥም ያስፈራል፡፡ ለምን ብትይ… ብዙ የተንኮል ፖለቲከኞች የሌሉበት፣ ለስራ ብቻ የሚተጉ የተመረጡበት በመሆኑ ወቅቱ የአንድነት ትንሳኤ ነው፡፡ ትንሽ የሚያሳስበኝ ኢ/ር ግዛቸው አሁን ከመረጧቸው ሰዎች ጋር እኩል ሮጠው ይችላሉ ወይ የሚለው ነው። ለምን? ከእርሳቸው በዕድሜ በጣም የሚያንሱትን መርጠዋልና እነርሱ በጣም የፈጠኑባቸው እንደሆነ፣ እኩል ለመሮጥ ዝግጁ ናቸው ወይ? ስል አስባለሁ፡፡ በእርግጥ ኢ/ር የማስተባበር ብቃትና ልምድ ያላቸው በመሆኑ ያን ያህል ችግር አይገጥማቸውም የሚል እምነትም አለኝ፡፡ ኢ/ር ግዛቸው በመረጡት ካቢኔ ውስጥ እመረጣለሁ ብለው ጠብቀው ነበር፡፡ ከተመረጡስ በኋላ ምን ተሰማዎት? እውነት ለመናገር አልጠበቅሁም ነበር፡፡ በመጀመሪያ አንድ ነገር ልንገርሽ፡፡ አንዳንድ ግለሰቦች ከዚህ ትምህርት ይወስዳሉ ብዬ አስባለሁ፡፡ እዚህ በቅርብ ያሉ የአንድነት አባላት “ዘለቀ አንድነትን ተሳድቧል” ብለው አጋነው ለማቅረብ ሞክረዋል። አባላቱ ግን እኔ አንድነትን እንዳልተሳደብኩ፣ ችግሩ ከግለሰቦች ጋር ብቻ እንደነበር የገለጽኩትን በትክክል ተረድተውታል፡፡ ወደ ብሔራዊ ም/ቤት የምትገቢው በውድድር ተመርጠሽ እንጂ በፍላጐት ብቻ አይደለም፡፡ እኔ በመጀመሪያ ተመዝግቤ ተወዳድሬያለሁ፡፡ ነገር ግን ስራ አስፈፃሚ እሆናለሁ ብዬ ሳይሆን ለብሔራዊ ም/ቤት አባልነት ነው የተወዳደርኩት፡፡ 17ኛው ወይም 18ኛ ተራ ቁጥር ላይ ነበር ስሜ የተመዘገበው፡፡

አባላቱ ግን ዘጠነኛ ቁጥር ላይ ነው ያመጡኝ፡፡ 217 ድምጽ ነው ያገኘሁት፡፡ ያኔ እኔ አንድነትን ማገልገል እንደምችል አባላቱ እምነት ጣሉብኝ ማለት ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ኢ/ር የውጭ ግንኙነት ሃላፊ አድርገው መረጡኝ፡፡ ትምህርትዎ ሲቪል ምህንድስና ይመስለኛል፡፡ አሁን ከተሰጠዎት ሃላፊነት ጋር ግንኙነት የለውም። ትንሽ አይከብድም? በአሁኑ ሰዓት በዓለም አቀፍ ጥናትና የውጭ ግንኙነት ሳይንስ ትምህርቴን በማጠናቀቄ ከተሰጠኝ ሃላፊነት ጋር በቀጥታ ይገናኛል፡፡ በዚሁ ትምህርት ውስጥ ዲፕሎማሲ ላይ የሚያተኩር ኮርስም ስለወሰድኩ ለቦታው እመጥናለሁ ብዬ አስባለሁ። አብዛኛው የውጭ ግንኙነት ስራዎች በሳይንሳዊ መንገድ ስለሚሰሩና በዘርፉም ስለተማርኩ ውጤታማ ስራ እሰራለሁ ብዬ አምናለሁ፡፡ በምርጫው ወቅት የነበረው ድባብ ምን ይመስላል? በተለይ እርሶ የካቢኔ አባል ሆነው ሲመረጡ ተቃውሞ እንደነበር ሰምቼአለሁ… ከጠቅላላው ጉባኤው ልጀምርልሽ፡፡ እኔ ወደ ስብሰባው ስገባ “አንተን በማየታችን ደስተኞች ነን” ብለውኛል፡፡ አንዳንዶቹ መድረክ ላይ ንግግር እየተደረገ ሁሉ ያንን ጥሰው መጥተው ሰላምታ ሲሰጡኝ ነበር፡፡ ያኔ የአንድነት አባላት አሁንም ከጐኔ መሆናቸውን ተገነዘብኩ፡፡ ወደ ምክር ቤት ስንመጣ ግን ከሶስት ያልበለጡ ሰዎች አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ አንደኛው “ዘለቀ ልምድ ስለሌለው ስራውን አይችለውም” የሚል አስተያየት ሰጡ፡፡ አንዳንድ ሰዎች ልምድ እድሜ የሚመስላቸው አሉ።

እንዲህ አይነት አስተያየት የሚሰጡ ትልልቅ ሰዎች ግን በእድሜ እንጂ በስራ ልምድ አይበልጡኝም፡፡ እኔ ስለ ሥራ ልምዴ ልንገርሽ፣ በአበባ አምራችነቱ ሁለተኛ የሆነውንና ዝዋይ የሚገኘውን የሆላንዱን “ሼር” የተባለ አበባ አምራች ድርጅት በአለም አቀፍ ደረጃ ተሸላሚ አድርጌዋለሁ፡፡ በዚህ ድርጅት ውስጥ ለአራት አመታት ከሰባት ሺህ በላይ ሰራተኛ ስመራ፣ አንድ ሰራተኛ ለአንድም ቀን ፍርድ ቤት ክስ አቅርቦ አያውቅም፡፡ ለዚህም ድርጅቱ ዝዋይ ላይ በስሜ ትምህርት ቤት ሰርቷል፡፡ በአስተማሪነት በሰራሁበት ጊዜም ዩኒት መሪ ሆኜ ስሰራ፣ በአመራር ብቃት የወርቅ ተሸላሚ ሆኜ ነው የወጣሁት፡፡ ይህን “ሊሙ ገነት አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት” ሄዶ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ጅማም በካቶሊክ ትምህርት ቤት አስተምሬያለሁ፡፡ በጅማ ዩኒቨርስቲ ኮሙዩኒቲ ስኩልም አስተምሬያለሁ፡፡ በየሰራሁባቸው ቦታዎች ሁሉ በጥሩ የአመራር ብቃት ተሸልሜ ነው የምወጣው፡፡ እንደነገርኩሽ ዝዋይ ያለው የ”ሼር ኢትዮጵያ” ት/ቤት በስሜ ነው የሚጠራው - “ዘለቀ ት/ቤት” ይባላል፡፡ ይሄ ትልቅ ሽልማት ነው፡፡ ነገር ግን ይሄንን ብዙ አውርቼው አላውቅም፡፡ ለምን ያልሽ እንደሆነ ሰው አሁን እየሰራ ባለው እንጂ ድሮ በሰራው ብቻ መመዘን አለበት ብዬ ስለማላምን ነው። እንግዲህ ተቃውሞ የተባለው አንድ ሶስት ሰዎች ሊቃወሙ ሞክረዋል፤ ግን የተቀበላቸው የለም፡፡ ነገር ግን በርካታ የአንድነት አባላት በእርስዎ የሃላፊነት ሹመት ደስተኞች እንዳልሆኑ በስፋት እየተነገረ ነው… ብዙ ተቃውሞ አለ የሚባለው ሃሰት ነው፤ ከሶስት አይበልጡም፡፡ አንዱ ተቃዋሚ ከዚህ በፊት የኔን ገጽታ ለማበላሸት ሞክሮ ያልተሳካለት ስለነበር፣ አሁን ሃላፊነት ላይ ስቀመጥ በድንጋጤ የተናገረው ነው፡፡ እውነታው ይሄው ነው፡፡ ከዚህ በተረፈ ሌላውን አባላትን አነጋግረሽ ድረሽበት፡፡ በሚቀጥለው አመት አገራዊ ምርጫ ይካሄዳል፡፡

ፓርቲው ለመወዳደር ሃሳብ ያለው ይመስልዎታል? ሃሳብ ያለው ይመስልዎታል ሳይሆን በደንብ ይሳተፋል፡፡ አንድነት በትክክል ይሳተፋል፡፡ እርስዎ በፖለቲካው ውስጥ እያሉ አንድነት ፓርቲ በምርጫ አሸንፎ የመንግስት ሥልጣን የሚይዝ ይመስልዎታል? በትክክል! በምርጫው የምንወዳደረውም እኮ ለማሸነፍና አገር ለመምራት ነው፡፡ ደግሞም እሩቅ ሳትሄጂ አንድነት በቅርቡ መንግስት ሆኖ ይህቺን አገር ይመራል፡፡ በውስጥ አደረጃጀት፣ በአባላት ጥንካሬና በአጠቃላይ ሁኔታ በጥሩ አቋም ላይ በመሆኑ መንግስት መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ በመጨረሻ? በመጨረሻ የአንድነት አባላት በእኔ እምነት ጥለው ድምፃቸውን ስለሰጡኝ እንዲሁም የፓርቲው ሊቀመንበር ችሎታና ብቃት አለው ብለው ሃላፊነት ስለሰጡኝ በጣም አመሰግናለሁ፡፡ እኔም ሃላፊነቴን በብቃት ለመወጣት ከወዲሁ በትጋት ስራዬን ጀምሬያለሁ፡፡ አመሰግናለሁ፡፡

Read 3986 times