Saturday, 14 December 2013 12:35

የመዲናችን ገመናዎች በ‹‹ሮዛ›› መጽሐፍ ውስጥ ሲቃኙ

Written by  እንድሪያስ ቢ.
Rate this item
(72 votes)

ባለፈው ሳምንት በዚሁ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ “በመዲናዋ ምስጢራዊ የወሲብ ገበያ ደርቷል” በሚል ርእስ በመታሰቢያ ካሳዬ የተጻፈውና በህብረተሰብ አምድ ላይ የተስተናገደው ጽሁፍ፣ ከሰሞኑ ከመጻሕፍት አዟሪዎች ደረት ላይ የማይጠፋውንና በማህበራዊ ድረ ገጾች ትኩስ መነጋገሪያ የሆነውን “ሮዛ” የተሰኘ መጽሀፍ አስታወሰኝ። ሁለቱም ጸሀፍት ለአብዛኞቻችን አዲስ አበቤዎች እንግዳ የሆኑና የማናውቃቸውን የመዲናችንን አስገራሚ ድብቅ እውነታዎች አስቃኝተውናል፡፡ የዛሬ ጽሁፌ አቢይ ትኩረት ግን “ሮዛ” በሚል ርእስ ለህትመት የበቃውን የሮዛ ይድነቃቸው የእለት ማስታወሻዎች ስብስብ መጽሀፍ ላይ ሂሳዊ ምልከታን ማቅረብ ነው፡፡
የእለት ማስታወሻዎች ተሰብስበው በመጽሀፍ መቅረባቸው በኢትዮጵያ ስነ-ጽሁፍ ውስጥ የተለመደ አይደለም፤ በቅርብ አመታት ውስጥ ለህትመት የበቁ የስመ-ጥር ኢትዮጵያውያን ግለ-ታሪክ መጻህፍት ከእለት ማስታወሻዎች ስለመጠናቀራቸው እስካሁን ያገኘሁት ተጨባጭ ፍንጭ የለም፡፡

ጎምቱው ደራሲ ተስፋዬ ገብረአብ ማንኛውንም የተለየ ቅጽበት ባስተዋለ ቁጥር ማስታወሻ ደብተሩን ከኪሱ አውጥቶ የመሰጠውን ቅጽበት፣ ሃሳብ ወይም ክስተት በዝርዝር የመጻፍ ቋሚ ልምድ እንደነበረው የቀድሞ የስራ ባልደረቦቹና ወዳጆቹ በአንድ አጋጣሚ አጫውተውኛል፡፡ ከነስህተትና ድብቅ አጀንዳቸውም ቢሆን ከነዚህ ማስታወሻዎች ተነስቶ “የጋዜጠኛው ማስታወሻ”፣”የደራሲው ማስታወሻ” እና “የስደተኛው ማስታወሻ” የተሰኙትን መጻህፍት ለህትመት እንዳበቃ ራሱ በስደተኛው ማስታወሻ ላይ ይገልጻል፡፡ ዛሬ ለዳሰሳ የመረጥኩት “ሮዛ” የሚል ስያሜ የተሰጠው መፅሐፍም ሮዛ በምትባል ኢትዮጵያዊት ኮማሪት የተጻፈ የግል ማስታወሻ ነው፡፡ ምንም እንኳ የግል ማስታወሻዎቿ አርታኢ እጅ ላይ ወድቀው መጠነኛ የይዘትና የቅርጽ ለውጦች ቢደረጉባቸውም የግል ማስታወሻዎችን ወደ መፅሐፍ ቀይሮ በማሳተም ረገድ ምናልባትም ቀዳሚ ስራ ነው ለማለት ያስደፍራል፡፡
ከዚህ የስነ ጽሁፍ ዘውግ ጋ ለመጀመሪያ ጊዜ በውል የተዋወቅነው አዶኒስ ከአመታት በፊት ወደ አማርኛ ተርጉሞ ባቀረበልን “The Diary of Ana Frank” (የአና ፍራንክ ማስታወሻ) በሚለው መጽሀፍ ይመስለኛል፡፡ አና እነዚህን በመላው አለም በበርካታ ቋንቋዎች ተተርጉመው በሚሊዮኖች ኮፒ የተሸጡላትን የእለት ማስታወሻዎች የከተበችው በሁለተኛው የአለም ጦርነት ወቅት በሆላንድ ርእሰ መዲና አምስተርዳም ከናዚዎች በተደበቀችባት ክፍል ውስጥ ነበር፡፡ በድርሰት ስራቸው የተደመምንባቸው በርካታ የአውሮፓ እና የአሜሪካ ደራሲያን ስራዎች ከደራሲያኑ የእለት ማስታወሻዎች የተወለዱ ነበሩ፡፡ ለአስረጅነት የቨርጂንያ ዉልፍን፣ አዳም ረታ በ”እቴ ሜቴ ሎሚ ሽታ” ድርሰቱ ውስጥ የሚያነሳትን ዝነኛዋ የኢሮቲክ ልቦለዶች ደራሲ የሆነችውን አናይስ ኒንን፣ ለየት ባሉት አጫጭር ልቦለዶቹ የሚታወቀውን ፍራንዝ ካፍካን፣ የዝነኞቹን አሜሪካዊያን የኢሮቲክና ሮማንቲክ ልቦለድ ደራሲዎቹን የኤሪካ ዮንግንና የሳንድራ ብራውንን ስራዎች ማንሳት እንችላለን፡፡
አናይስ ኒን “የኔም ሆነ የሌሎች እውነተኛ ማንነት በአንዳች አይነት የስሜት ጡዘት ወይም ቀውስ ውስጥ ስለሆነ እነዚህ ቅጽበቶች በምንም ሁኔታ እንዲያመልጡኝ አልፈቅድም፤ በፍጥነት አንዳች ሳላስቀር በእለት ማስታወሻዎቼ ላይ አሰፍራቸዋለሁ” ብላ ነበር፡፡ ፍራንዝ ካፍካ  “በህይወታችን የተለያዩ ምእራፎች ያሳለፍናቸውን የደስታና የሀዘን፣የጭንቀትና የፈንጠዝያ፣የድሎትና የውጣ-ውረድ ጊዜያት በእለት ማስታወሻዎቻችን በኩል መለስ ብለን ስንመለከታቸው በርግጥም መኖራችንን፣ ከመኖርም አልፈን የኖርነውን በጽሁፍ ለዘለቄታው ማስቀመጣችንን በውል እንገነዘባለን፤ ከእለት ማስታወሻችን በተሻለ የኖርነውን ህይወት፣ ቅጽበታዊ ስሜቶቻችንን ሳይቀር በግልጽነትና በታማኝነት የሚዘግብልን ድርሳን የለም” ይላል፡፡ ስመ - ጥሩ ደራሲ ዴቪድ ሴዳሪስ በበኩሉ “የእለት ማስታወሻዎቻችን ቢያንስ በሁለት  ምክንያቶች ይጠቅሙናል፤ ባለፈ ብስጭታችን፣ ስቃያችን፣ ስህተታችን፣ ድክመታችን፣ እንጭጭነታችንና ውጣ ውረዳችን ዘና እያልን እንዳንደግማቸው ትምህርት እንወስዳለን፤ ‘መጋቢት 3 ቀን 1998 ላይ እኮ እንዲህ ብለህ ነበር’ ብለን ክርክር በመጀመር ሙግት እንረታበታለን” ሲል ተናግሯል፡፡
ሮዛ ራሷም ለዳሰሳ በመረጥኩት ማስታወሻዋ ውስጥ እንደምትገልጸው ኮሌጅ የበጠሰች ሴተኛ አዳሪ ናት። ለሮዛ ዳዬሪዋ (የእለት ማስታወሻዋ) ብቸኛ የሚስጥር ጓደኛዋ የሆናት ይመስላል፤ ይህን የግል ማስታወሻዋን ነው እንግዲህ አደባባይ ያሰጣችው፡፡ በዚህች ምድር ላይ ገሚስ አድሜን ያሳለፈች የአገር ልጅ ለነገ ሳትል ጥብቅ ሚስጢሯን ሁሉ በመጸሐፍ መልክ ድንገት ስትዘከዝክ “ለምን?” ማለታችን አይቀርም፡፡ እኔም ለምን ብዬ ደጋግሜ ጠየቅኩ፡፡ መላምት እንጂ መልስ አላገኘሁም፡፡ ምናልባት ከብዙዎቹ ሴተኛ አዳሪዎች በተለየ ኮሌጅ መበጠሷ ህይወቷን ለሌሎች በማሳየት ማህበረሰባዊ ግዴታዋን ለመወጣት አስባ ይሆን?ምናልባት ሲሶ እድሜዋን የኖረችበትንና እሷ እምብዛም የማትቆጭበትን የቡና ቤት ህይወት በመተረክ ርካሽ ዝናን በአቋራጭ ለማግኘት አቅዳስ ይሆን? ነው ወይንስ ሙአመር ጋዳፊን ማግኘቷን እንደ ታላቅ ስኬት በመቁጠር እዩልኝ ስሙልኝ እያለችን ይሆን? እነዚህን ሁሉ መላምቶች ለመሰንዘር የተገደድኩት መጽሀፏ ውስጥ ምንም አይነት አስረጅ ባለማግኘቴ ነው፡፡ በመጸሐፉ የመጀመርያዎቹ ጥቂት ገጾች መረዳት የቻልኩት ሮዛ  ከያንዳንዱ የ ‹‹ሾርት›› እና የ‹‹አዳር›› ቢዝነስ በኃላ የዕለት ማስታወሻ የመያዝ ልምድ እንዳላት ብቻ ነው፡፡ ምናልባት መጸሐፉ የራሱ መግቢያ ተበጅቶለት ቢሆን ኖሮ እኛም ከመላምት በዳንንና ስለ ጸሐፊዋ ግብና ተልእኮ ብዙ መረዳት በቻልን ነበር እላለሁ፡፡ “ከሾፌር፣ ከሴተኛ አዳሪ፣ ከዘበኛና ከቤት ሰራተኛ የምታመልጥ አንዳችም የአለም ሚስጥር የለችም” በሚል መሪ ቃል ሽፋኑን ያደመቀው ይህ መጸሐፍ፤ ደራሲዋ የሙአመር ጋዳፊ ድንኳን ውስጥ የዘለቀች ‹‹ጀግና›› መሆኗን ገልጾ የልብ ምታችንን ያፈጥንብናል፡፡
በእርግጥ ይህ መጽሀፍ እስካሁን ካነበብኳቸውና ተመሳሳይ ይዘት ካላቸው መጻህፍት በብዙ መልኩ እንደተለየብኝ አልክድም፡፡ መጽሀፉ በርካታ አመታትን በዲፕሎማቶችና ከፍ ባለው ማህበረሰብ ዙርያ በሴተኛ አዳሪነት ህይወት ውስጥ ባሳለፈች፣ ከአንድም ሁለት ሶስት ዓለምአቀፍ ቋንቋ በምትናገር የተማረችና፣ ሯሷን በንባብ የገራች ኮማሪት መጻፉ ብቻ አይደለም ልዩ የሚያደርገው። አጻጻፏ በራሱ አንባቢ ላይ በግድ ቅጽበታዊ ስሜትን የማጋባት ባህሪ አለው፡፡ ስታዝን ይከፋናል፣ስትደሰት እንስቃለን፣ስትበግን እንንገበገባለን፣ ስትስቅ ፈገግ እንላለን…በማያገባን እያስገባችን ስሜታችንን ትሾፍረዋለች፡፡ እለታዊ ማስታወሻዋ የእንቶ ፈንቶ ጉዳይ ቢመስልም የዘመናችንን ማህበራዊ፣ፖለቲካዊ፣፣ባህላዊ፣ሃይማኖታዊና ስነልቦናዊ እውነታዎች በማስታወሻዎቿ በኩል በግርድፉ ታሳየናለች። ይህንን ደግሞ ከአንዲት ኮማሪት የምንጠብቀው ስላይደለ እንገረማለን፡፡ የቡና ቤት ሴት ሆናም የኛን የሞራልና መንፈሳዊ ዝቅጠታችንን ጥልቀት ስትነግረን እንድንሸማቀቅ አድርጋ ነው፡፡ በዕለት ማስታወሻዋ የመኝታ ገድሎቿን እየተረከችልን እሷን ሳይሆን እኛን እንድንታዘብ የሚያደርግ ስሜትን ትረጭብናለች፡፡ ይህንን ማድረግ የቻለችው ከልቧ በፍጹም የተቆርቋሪነት ስሜት ስለምትጽፍ ይሆናል፡፡ ከኪነ-ጥበብ ስራ በላይ ዘመንን ቅልብጭ አድርጎ የሚያሳይ ነገር ያለ አይመስለኝም ነበር፤ የፈጠራ ስራ ባልሆኑት የሮዛ የግል ማስታወሻዎች ውስጥ ይህንን ሁለንተናዊ የዘመን መንፈስ መመልከቴ ሳያስገርመኝ አልቀረም፡፡
“ሮዛ” እንደ “መሀልዬ መሀልይ ዘ ምናምን” እያሉ ከተድባበ ጥላሁን ቱባ ስራ በኋላ የልብ ካውያ እንደሆኑብን ገበያ ተኮር መጻህፍት የገድለ ወሲብ ጥርቅም አይደለም፤ ወይም ደግሞ ከጋዜጣ ወደ መጽሐፍ እንደተገለበጡት ስራዎች የቡና ቤት ሴቶችን ግልብ ቃለመጠይቅ ወደ ጽሁፍ ቀይሮ ለንባብ ያበቃም አይደለም፡፡ በእርግጥ እነዚህ መጻህፍትም ቢሆን ይብዛም ይነስ በተለያየ ዘመን እና ቦታ የተኖረን ህይወት ለዘለቄታው ለመጪዎቹ ትውልዶች የሚያስተላልፉ ቋሚ ሰነዶች እንደመሆናቸው ሚናቸውንና ጠቀሜታቸውን እያሳነስኩ እንዳልሆነ ይታወቅልኝ። የስብሀት ገብረ እግዚአብሄር “ሌቱም አይነጋልኝ” መጽሀፍ ባይኖር በንጉሱ ዘመን በውቤ በረሀ የተኖረውን ህይወትና የዘመን መንፈስ እንዴት ማወቅ ይቻለን ነበር?የአለማየሁ ገላጋይ “አጥቢያ” ልቦለድ ባይኖር አሁን ሙሉ በሙሉ በፈረሰችው አራት ኪሎ ውስጥ የተኖረውን ህይወት፣የነበረውን ማህበራዊ መስተጋብር መጪዎቹ ትውልዶች እንዴት ሊያውቁ ይችላሉ? በማህበረሰብ ጥናት ዘርፍ የተሰማሩ ምሁራንስ ከተጻፉ መዛግብት በላይ ምን አይነት ተጨባጭ መነሻ ይኖራቸዋል?
ከላይ ከተጠቀሱት መጻህፍት በተለየ የሮዛ ህይወት በአንድ ሰፈር የተገደበ አይደለም፤የስራዋ ባህሪ ሆኖ መላው አዲስ አበባን ያካልላል፡፡ የሮዛ ህይወት ከድብቅ (ህቡእ)የመዲናችን የአስረሽ ምቺው ቪላዎች እስከ ሼራተን ቪላ እና የሊቢያው መሪ የጋዳፊ ድንኳን ድረስ ይዘልቃል፡፡ ጋዳፊ የአፍሪካ ህብረት አመታዊ ስብሰባን አስታከው የሀበሻ ቆነጃጅትን ለገዙት ‹‹ኤር አፍሪክ›› አየር መንገድ በሆስቴስነት ሲመለምሉ ሮዛ እንዳገኘቻቸው ትገልጻለች፡፡ ከሳቸው ጋርም ባረፉበት ሼራተን ቪላና በድንኳናቸው ውስጥአጭር ሆኖም አስገራሚ ቆይታ ማድረጓንም ትተርክልናለች፡፡ ሮዛ በመጸሕፏ እንደነገረችን ከሆነ ጋዳፊ በርግጥም ወፈፌ ነበሩ። ይህን ቆይታዋን “ከጋዳፊ ጋር ድንኳን መጋፈፍ” በሚለው የመጽሀፉ ሰፊ ምእራፍ ውስጥ በዝርዝር ገልጻዋለች፡፡ ከአመታት በፊት እዚሁ አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ጋዳፊ በሼራተን ስላካሄዱት የሆስቴስ ምልመላ አጠቃላይ ሂደት በስፋት ማንበቤ ትዝ ይለኛል፡፡ምናልባት ሮዛ በዚሁ ምልመላ ወቅት አንዷ ታዳሚ መሆኗን መገመት ይቻላል፡፡
በ”ሮዛ”ውስጥ 29 በቀላሉ ከአእምሮ የማይጠፉ ታሪኮች አሉ፡፡ እንደገመትኩት አርታኢው በታሪኮቹ መረጣ ላይ ዋናውን ሚና ሳይወጣ አልቀረም፡፡ ምክንያቱም ለአመታት ከጻፈቻቸው በርካታ የእለት ማስታወሻዎች ውስጥ በሰው ዘንድ ልዩ ስሜት የሚፈጥሩትን ታሪኮች ለማወቅ ሙያዊ ትኩረትና ክህሎት ይፈልጋል፡፡
በ”ሮዛ” ውስጥ በመጀመሪያ ላይ የምናገኘው ታሪክ “ኮሌጅ በጠስን” የሚለውን ነው፡፡ ሮዛ በዚህ ታሪክ ውስጥ የትምህርት ፖሊሲያችን የደረሰበትን ዝቅጠት፣ የራሷንና የኮሌጅ ጓደኞቿን ህይወት በማውሳት ታሳያለች፤
…ኮሌጅ የበጠሱ የኔ “ባቾች” እንዳሁን ዘመን ተመራቂዎች ሁሉም ኮብልስቶን አንጣፊ አልሆኑም፡፡ በባለ አምስት ኮከብ ሆቴሎች ውስጥ አልጋ አንጣፊ የሆኑም አሉ፡፡ እንደኔ እና እንደወይንሸት የተማረ ሸሌ ሆነው የቀሩም አሉ፡፡ እንደ መዲና፣እንደ ራሄል፣እንደ ሂዊ፣እንደ ፎዚያ፣ እንደ ጠይባ አረብ አገር ለግርድና የሄዱም አሉ፡፡ እንደ አብዱልሰመድ(ወሎዬው) በአካውንቲንግ ተመርቀው የመን አገር ፍየል ለማገድ የተሰደዱም አሉ፡፡እንደ ምስኪኑ ሀብትሽ ሰፈር ውስጥ ጸጉር አስተካካይ የሆኑም አሉ፡፡ ሀብትሽ “ አታካብዱ ያው ነው፣ድሮም በጭንቅላቴ ነበር የምሸመድደው አሁንም ጭንቅላት ነው የምከረክመው፤አሁንም ድሮም ከአንገት በላይ ስፔሻሊስት ነኝ!” እያለ ራሱ ላይ ይቀልዳል፡፡ የክላስ ልጆችን ሳስብ እንደ ሀብትሽ አንጀቴን የሚበላኝ ሰው የለም፡፡ ሀብትሽ ለአራት አመት “ስፔስ” እየተመላለሰ፣አይኑ እየተጨናበሰ፣እንቅልፍ እንዳያሸንፈው እግሩን በሳፋ እየዘፈዘፈ፣ ሌት-ተቀን ትምህርቱን ሲሸመድድ ቢኖርም ያቺ ቆሽማዳ ህይወቱ ፈቀቅ አላለችም…(ገጽ-5)
በመጽሀፉ ውስጥ “ዋለልኝ” በሚለው ታሪክ ውስጥ አቸኖ የተባለውን የቺቺንያ ለማኝ እናገኛለን፤ዋለልኝ እንግሊዝ ለንደን ውስጥ በሚገኝ አንድ ግዙፍ ኩባንያ ውስጥ በስራ አስኪያጅነት የሚሰራና በርካታ ሺህ ፓውንድ ደሞዝ የሚከፈለው የቀድሞ የኢህአፓ አባል ነው፡፡ በኢህአፓ ትግል ወቅት በደረሰበት ስነ ልቦናዊ ችግር ምክንያት ወሲብ መፈጸም አይችልም፡፡ የሴት ገላ አቅፎ ለመተኛትም የቻለው በእንግሊዝ ቆይታው ረጅም ጊዜ በወሰደ የስነ ልቦና ህክምና ነው፡፡ በዚህ ቅንጭብ ታሪክ ውስጥ ሮዛ ተራ የህይወት ትዝብቷን እንዴት ከዘመናችን ማህበረ ፖለቲካ ጉዳዮች ጋር አቆራኝታ እንደምትመለከታቸው እንረዳለን፡፡ የሮዛ አንዳንድ ትዝብቶች አጥንታችን ድረስ ዘልቀው የሚሰሙን ናቸው፡፡ ለማሳያ ያህል የአቸኖን ቅንጭብ ታሪክ እንመልከት፡-
ሰኒና ወገቧን ያቀፋት ወጣት ኮንትራት ታክሲ ውስጥ ሊገቡ ሲሉ የእግር አልባው ለማኝ የአቸኖ ድምፅ ገታቸው። ከኋላቸው ስለነበርኩ ለማኙ ምን እንደሚላቸው እየተከታተልኩ ነበር፡፡ አቸኖ ሁሌም እንደሚያደርገው የሌሊቱን ብርድ ለመቋቋም በርካታ አረቄዎችን እንደተጋተ የድምጹ ቅላጼ ያሳብቃል፡፡
“አባቱ!እስቲ ብር ልቀቂብኝ!”
ወጣቱ ምንም ምጽዋት ሳይሰጠው ሰኒን እንዳቀፈ ወደ ታክሲው አመራ፡፡ አቸኖ ከመቅጽበት እሳት ለበሰ፤ሁልጊዜ ነው እንዲህ የሚሆነው፡፡ ሰው ሳይመጸውተው እንዳላየው ሆኖ ለማለፍ ሲሞክር ክፉ ይናገራል፤አቸኖ ሰኒን ያቀፈውን ወጣት ምን ሊለው እንደሚችል እየጠበቅኩ ነበር፡፡
“ትሰማኛለህ ወንድሜ!አንተ እንደዚህ በሰላም አየር የሴት ወገብ እንድታቅፍ እኮ ነው እኔ ባድመ ላይ በሻእቢያ ፈንጂ ሁለት እግሮቼን ያጣሁት! ተጸይፈኸኝ ነው ዞረህ እንኳን ልታየኝ ያልፈለግከው?”አለው፡፡
አቸኖ ምጽዋት ሲጠይቅ ለመላው ቺቺንያ በሚሰማ አስገምጋሚ ድምጽ እያንባረቀ ስለሆነ ያስፈራል…(ገጽ 111-112)
ሮዛ “የተከበሩ ማዳም ኤልዛቤጥ” በሚለው ታሪክ ውስጥ የማዳም ኤልዛቤጥ ግዙፍ የመስቀል ፍላወር ቪላ የሚሰጠውን ህቡእ የወሲብ አገልግሎትና በዚያም የሚደርሰውን አሰቃቂ አጋጣሚ በዕለት ማስታወሻዋ ታስቃኘናለች፡፡ ማዳም ኤልዛቤጥ የእድሜያቸውን ሲሶ በፈረንሳይ ያሳለፉ እመቤት ናቸው፡፡ ከዚህ ታሪክ በርግጥም በመዲናችን ውስጥ በርካታ የማናውቃቸው ገመናዎች መኖራቸውን እንረዳለን። ”ፍቅርተን ማን ገደላት?ባሏ” በሚለው አሳዛኝ ታሪክ ውስጥ ሮዛ የአፍ ወለምታ ህይወትን የሚያክል ውድ ነገር የሚያስቀስፍበትን ገጠመኝ ትነግረናለች፡፡
“ጥኡም ወዲ አስመራ” በሚለው ማስታወሻዋ ውስጥ አባትና ልጅ በአንድ ምሽት ሳያስቡት ከሷ ጋር ለመተኛት በሚያደርጉት ትግል ድንገት ግንባር ለግንባር መገጣጠማቸውን በመተረክ፣ የዘመናችንን እውነታ ፍንትው አድርጋ ታሳየናለች፡፡ ይህንን ታሪክ አንብቦ አለመደንገጥ ይከብዳል፡፡ “የቤዛ አልፋና ኦሜጋ” በሚለው ታሪክ ውስጥ ደግሞ ወንድም ከቡና ቤት ሴት ጋር እየቀበጠ ከበርካታ አመታት በፊት ከቤት ወጥታ የቀረች እህቱን፣ በዚያው ሆቴል ውስጥ በሴተኛ አዳሪነት ስትሰራ እንደሚያገኛት እንመለከታልን፡፡
የሮዛ የስራ ጸባይ በራሱ በየእለቱ ከተለያዩ የህይወት ጽንፍ የሚመጡ በርካታ ሰዎችን እንደሚያገናኛት ከመጽሀፉ እንረዳለን፡፡ በማስታወሻዎቿ ውስጥ ሮዛ ስለራሷ ገመና ብቻ አይደለም የምትተርክልን፡፡ ስለ ቡና ቤት ሴት ጓደኞቿ(የስራ ባልደረቦቿ)፣አብረዋት ስለተማሩ ወንዶችና ሴቶች፣ ስለፓይለትና ፕሮፌሰር ደምበኞቿ፣ በስካር ነብዘው በተንቋረረ ድምጻቸው “ከኛ በላይ ላሳር” ስለሚሉ ትምክህተኛ ምሁራን፣ስለአፍሪካ ዲፕሎማቶችና ሴሰኝነታቸው፣ራሳቸውን ከፓሪሱ “ኤፍል ታወር” በላይ ቆልለው ስለሚያዩ ዳያስፖራዎች…እያሳቀችን ትተርክልናለች። ደግሞ ማሳቅ ትችላለች፡፡ የስነ-ጽሁፍ አንዱ ግብ አንባቢን ማዝናናት መሆኑ ይታወቃል፡፡
”Usman The Pimp” በሚለው ታሪክ ውስጥ ብዙ አለም-አቀፍ ቋንቋዎችን አቀላጥፎ የሚናገረውን መልከ-መልካሙን አስጎበኚ ኡስማን እናገኛለን። ኡስማን በቅልጥፍናው በርካታ ሀበሻ ቆነጃጅትን ከአረቦች፣ከነጮች፣ከአፍሪካውያንና፣ከእስያውያን ቱሪስቶች ጋ ያገናኛል፤ሁሌም ባተሌና እረፍት አልባ ነው። የውጭ ዜጎቹን ከሀበሻ ቆነጃጅቱ ጋ የሚያገኛኝበት ህቡእ መረብ ስፋትና ጥልቀት በተለይ በአለም-አቀፍ ስብሰባዎች ወቅት አስገራሚ ነው፡፡ እኛ የዓለም ሶስተኛዋ የዲፕሎማሲ ዋና ከተማ እያልን የምናንቆለጳጵሳት መዲናችን፣ በእያንዳንዱ አለማቀፍ ስብሰባዎች ምሽት ታላቅ የወሲብ ንግድ እንደሚካሄድ የምንረዳው በዚሁ የኡስማን ዘ ፒምፕ ታሪክ ውስጥ ነው፡፡ የሴት ደላላ ሆኖ የተነገረን የኡስማን ታሪክ “ተወልጄ እድሜዬን ሁሉ በኖርኩባት አዲስ አበባ እንዴት ይሄ ሁሉ ጉድ መኖሩን እስካሁን አላወቅኩም?” ብዬ እንድጠይቅ አድርጎኛል፡፡ ሮዛ ከጋዳፊ የፕሮቶኮል ሀላፊ እና ከራሳቸው ከሊቢያው መሪ ጋር እንድትገናኝ አስፈላጊውን ሁኔታ ያመቻቸውም ይኸው ሴት አቅራቢ ኡስማን ዘ ፒምፕ ነው፡፡ ሮዛ ኢትዮጵያዊያን ሴት እህቶቻችን አረብ አገር ብቻ ሳይሆን እዚሁ በአገራችን ለወሲብ ገበያ በስፋት እንደሚቀርቡ ትነግረናለች፡፡ ሴቶቻችንን ለአረቦች በረብጣ ሪያል በመሸጥ ሀብት ንብረት ያፈሩ ሰዎችን ለማሳየትም ይህንኑ ዝናው በከተማዋ ቆነጃጅት ዘንድ የናኘውን ኡስማን ዘ ፒምፕን ታሪክ ታቀርብልናለች፡፡
“ራቁት ጭፈራ ቤቱ ተዘጋ” በሚለው ታሪክ ውስጥ ሮዛ ደምበል ህንጻ ስር ስለነበረው ’ኢን ኤንድ አውት’ ስለተባለውና ከበርካታ ዓመታት በፊት በፖሊስ አሰሳ ስለተዘጋው ራቁት ቤት ቆይታዋ ታወጋናለች፡፡ ይህ የራቁት ቤት በአሰሳ መልክ ሲዘጋ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን ጨምሮ በበርካታ የአገራችን ሚዲያዎች በስፋት መዘገቡ ይታወሳል፡፡ በወቅቱ ጥቂት ስመጥር ምሁራንና አርቲስቶች በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው እንደነበር ይታወሳል። ሮዛ የቤቱ ታዳሚዎች እነማን እንደነበሩ ብቻ ሳይሆን በዚሁ ህንጻ ውስጥ በሚገኝ ሊፍት ውስጥ ብዙ የወሲብ ገድሎች ይፈጸሙ እንደነበረ በምልሰት ትተርካለች፡፡ እንደምሳሌም ‹‹የሊፍት ቴክኒሻኑ ፈሌ›› በሚለው ንዑስ ርዕስ ስር ይሆናል ብለን የማናስበውን ድብቅ የሊፍት ውስጥ የቤርጎ አገልግሎት እናገኛለን፡፡
ከታሪክ ታሪክ የሮዛን ስሜት እየተጋራሁ ነው መጽሀፉን የጨረስኩት፡፡ ማስታወሻዎቹ በቀልድና በጨዋታ የተዋዙ ስለሆኑ አዝናንተውኛል፡፡ በየታሪኮቹ ጣልቃ በማህበረሰባችን ሁኔታ ያዘንኩባቸውና የደነገጥኩባቸው ቅጽበቶችም ነበሩ፡፡ 29ኙም ታሪኮች ስሜት ይነካሉ ማለት ይቻላል፡፡ የማስታወሻዎቹ ስነ-ጽሁፋዊ ውበትም ማለፊያ ነው፡፡የሮዛ ለየት ያሉ የህይወት ትዝብቶች፣ ምልከታዎችና ለማንኛውም ነገር ያላት በሳል አስተሳሰብ ይማርካል። አንዳንዶቹ ማስታወሻዎች የተጻፉበት ቀን ተገልጿል፤ በርካቶቹ መቼ እንደተጻፉ ግን አልተገለጸም፡፡ቀኑ ቢገለጽ በጊዜው ስለነበረው አጠቃላይ ሁኔታ እንድናውቅና ሌሎች ተዛማች ክስተቶችን እንድናሰላስል ይጋብዘን ነበር፡፡
ሮዛ ታሪኩን በስራ ቦታዋና በስራ ባልደረቦችዋ ቋንቋ በማቅረብዋ አልወቅሳትም፡፡ ግልጽነቷንና ታማኝነቷን አበረታታለሁ፡፡ መሸፋፈኑና መደባበቁ ነው ክፉኛ የጎዳን፡፡ ቃላት የሚጠበቅባቸውን ነገሮችን የመግለጽ ሚና በአግባቡ እስከተወጡ ድረስ ነውር አይሆኑም ብዬ አምናለሁ። ሮዛ “ሩካቤ ስጋ”፣”ግብረ ስጋ”፣”ተራክቦ ስጋ”፣”የጭን ገረድ”፣”የከንፈር ወዳጅ”፣”እቁባት” ወዘተ የሚሉ በስራ ገበታዋ ላይ ፍጹም የማትጠቀማቸውን ማለዘቢያና ማሽሞንሞኛ ቃላትን በማስታሻዎቿ ውስጥ ብትጠቀም ኖሮ አስመሳይ ትሆንብኝ ነበር። አርታኢዋም ይህን ነጻነቷን ስላልነፈጋት ምስጋናዬ ይድረሰው፡፡ ስለቡና ቤት ህይወት እየተወራ ቃላትን ማሽሞንሞን የመጽሀፉን ጠቅላላ መንፈስ የሚያውከው ይመስለኛል፡፡
ሮዛ የአዋቂ መጽሀፍ ነው፤እድሜያቸው ከ18 አመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች እንዳያነቡት በሽፋኑ ላይ ተገልጿል። እንደ አደገኛ መድሀኒት ህጻናትና ታዳጊ ወጣቶች ከማይደርሱበት ቦታ መቀመጥ ይኖርበታል፡፡ ሆኖም ግን ይህ በሽፋኑ ላይ መገለጡ አደጋውን ሙሉ በሙሉ ያስወግዳል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ሁላችንም እንደምንረዳው፣ የእለት ማስታወሻዎች በባህሪያቸው ቅጽበታዊ ስሜቶች በትኩስ ስሜት፣ በማያመዛዝን ህሊና እና በጥድፊያ ወደ ጽሁፍነት የሚቀየሩ ሰዋዊ ትዝብቶች እንደመሆናቸው፣ ‹‹ሮዛ›› በዚህ ስሜት ውስጥ ሆና የከተበቻቸው ማስታወሻዎች በአፍላ እድሜ ላሉ ወጣቶች የሚያስተላልፉት መልዕክት አደጋው የትየሌሌ የሚሆንበት አጋጣሚ የሰፋ ነው። በመሆኑም በኔ ግምት የአርታኢው ሚና መሆን የነበረበት እነዚህን ስሜት ያናወጣቸው የግል ማስታወሻዎችን ማለዘብና ማስከን ብሎም ለአንባቢ የማይጎረብጡ፣ በማንኛውም ጊዜና ሁኔታ መነበብ የሚችሉ እንዲሆኑ ማድረግ ነው፡፡ ይህንን አርታኢው አሳክቶታል ብዬ አላምንም፡፡
ምክንያቱም የመፅሐፉ ስሜት አንባቢ ዘንድ ሲደርስም ቢሆን የልብ ምትን የሚያፈጥን፣ የቡና ቤት ሁካታው የሚሰማ፣ ፈንጠዚያው ያልበረደለት ሆኖ ነው፡፡  መጽሀፉ ውስጥ በርካታ የፊደል፣የቃላትና የሀሳብ አለመጣጣም ስህተቶች አሉ፡፡አርታኢው “ሮዛ በተለያየ አይነት ስሜት ውስጥ ሆና በተለያየ ቅጽበትና ጊዜ የጻፈቻቸው ማስታወሻዎች ስለሆኑ እንደፈለገች በመዘባረቅ መጻፏንና ያም ከነስህተቱ ማለፉን አንባቢዎች ይወዱታል፤ይረዱታል” የሚል አቋም ቢይዝ እንኳን መሰረታዊዎቹን ስህተቶች ማረም ነበረበት፡፡ ለምሳሌ “ሊሊ ቂጦ” በሚለው ታሪክ ውስጥ ሊሊን አንዳንድ ቦታ ላይ ሚሚ ሆና እናገኛታለን፡፡”የቤዛ አልፋና ኦሜጋ” በሚለው ታሪክ ውስጥ ታሪኩ የሚከወንበት  ኦሜጋ ሆቴል አንድ ቦታ ላይ ኦሜድላ ሆቴል ተብሎ እናገኘዋለን፡፡” የሚልኪና የሹገር ማሚዎቹ አጭር የህይወት ታሪክ” በሚለው ታሪክ ውስጥ ወይዘሮ ሳሮን በምን አስማት ቲና እንደምትሆን ግልጽ አይደለም፡፡ ምናልባት እነዚህ ስህተቶች አርታኢውን ሰነፍ ያስብሉት ይሆን እንጂ ጸሐፊዋን ክፉኛ የሚያስተቹ ናቸው ለማለት አልደፍርም፡፡
 በተለያየ ውጥንቅጥ ስሜት ውስጥ ሆነን ክስተቱን ለማስቀረት ብቻ እንዳሻን ስለምንጽፍ (ዲያሪ የመጻፍ ልምድ ካለን)በሌላ ጊዜ በተረጋጋ ስሜት ውስጥ ሆነን ስንመለከታቸው እንዲህ አይነት ተራ፣አስቂኝና አዝናኝ ስህተቶችን እንደምንፈጽም ባልዘነጋውም አርታኢው የሮዛን ስህተቶች ማለፍ አልነበረበትም ባይ ነኝ፡፡ አርታኢው “የእለት ማስታወሻ ከነስህተቱ ነው የሚያምረው፤አለበለዚያ ለዛውንና ወጥነቱን ያጣል” የሚል አቋም ያለው አይመስለኝም፡፡ መጽሀፍ ላይ ሁሉም አይነት ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል፡፡በቀጣይ እትሞች ላይ እነዚህ ስህተቶች እንደሚታረሙ እምነቴ የፀና ነው፡፡

Read 46390 times