Saturday, 30 November 2013 11:22

የሐሜት ዙር

Written by  ኦርዮን ወ/ዳዊት
Rate this item
(10 votes)

ድርጊቱን  ያየሁት ከ15 ቀን በፊት ነው፤ ቦታው ሻላ አዳራሽ። በቦታው የመገኘታችን ምክንያት ደግሞ የአንድ ጐረቤታችን

ልጅ ሰርግ ነበር፡፡
ከሰርጉ ቦታ የደረስነው ትንሽ ዘግይተን ስለነበር፣ አብዛኛው ቦታ እንደ እኛ በተጋበዙ እንግዶች ተሞልቷል፡፡ ለትንሽ ጊዜ

ያልተያዙ ወንበሮችን ስናፈላልግ ቆየንና፣ በመካከለኛ እድሜ ላይ የሚገኙ ሁለት ሰዎች ብቻ ያሉበት ቦታ አግኝተን

ተቀላቀልናቸው፡፡ የአጋጣሚ ነገር እኛም ሁለት ነን።
የተቀላቀልናቸው ሰዎች (ከወሬያቸው እንደሰማነው) አንዱ “ከድር” የሚባል ሲሆን ሌላኛው ደግሞ “ሥዩም” እንደሚባል

ተረድተናል። ከድር ሲናገር ረጋ ብሎ ነው፤ በተቃራኒው ሥዩም ግን ክልፍልፍ ቢጤ፣ መናገሩን እንጂ መደመጡን ልብ

ማለት የማያሻ፡፡ ግን ደግሞ ሁለቱንም አንድ የሚያረጋቸው ባህርይ እንደ አላቸው ተገንዝቤያለሁ፤ ሰውን መቦጨቅ፡፡
በአጋጣሚ የተቀመጥነው ለሁለት በተከፈለው የወንበር ሥርዓት በአንደኛው ዳር ነበርና አላፊ አግዳሚውን ቁልጭ

አድርጐ ያሳያል፡፡ አላፊ አግዳሚው ሁሉ ታዲያ በከድርና በሥዩም የተለያየ ታርጋ ይለጠፍበትና (ባይሰማም) መዘባበቻ

ይሆናል፡፡
ከሰርጉ ቦታ የደረስነው ከሙሽሮች ቀድመን ነበርና የእነ ከድር ጨዋታ ቀልባችንን እንደ ጥሩ ልብወለድ ሰቅዞ በመያዝ

በንቃት እናዳምጣቸው ጀመር፡፡ ለነገሩ የሚስቁበትን ምክንያት ባንረዳውም ገና ወደ እነሱ ስናመራ ከልባቸው እየሳቁ

ነበር፡፡
“መጣችልህ ደሞ…” አለ ሥዩም፤ አጭር ቀሚስ ለብሳ ተረከዙ ረጅም የሆነ ጫማ የተጫማች ቀጭን ረጅም ሴት አይቶ፡፡
“በለው” ከድር አደነቀለት፤ ግን ምኗ እንዳስደነቃቸው አልገባንም፡፡
“እስኪ ተመልከታት፤ እግር አለኝ መስሏት ነው በእግዚአብሔር… እንዲህ ሰጐን መስላ የመጣችው” ሥዩም ተናግሮ

ሳይጨርስ ከድር በሳቅ አጀበው፡፡
የከድርና የሥዩም አባባል እየገረመን ወደሚጠቋቆሙባት ሴት ዘወር ስንል እውነትም ቀጭን፣ ረጅም፣ ከመሆኗም በላይ

አፍንጫዋና ከንፈርዋ ወደፊት ሾለው ሲታዩ ጀማሪ ሰዓሊ የተጫወተባት ልዩ ፍጡር መስላ ታየችን፡፡
“እያማረ መጣልህ! ተመልከት ከእሷ ኋላ ያለችውን የማር አቁማዳ” ከድር ሲናገር ሁላችንም በሳቅ አጀብነው፡፡ ከጭኗ

እና ረጅሟ ሴት ኋላ የገባችው ደሞ በተቃራኒው አጭር ከመሆኗም ሌላ በጣም ወፍራም ስለሆነች፣ በተራመደች ቁጥር

ከሆዷ ላይ የተንጠለጠለው ስጋ ለብቻው ይንቀጠቀጣል፡፡
“አሁን እነዚህን አቅፈሃቸው ተኛ ብትባል ምን ትሆናለህ?” ሥዩም ጠየቀ፡፡
“ማ? እኔ ከድር?”
“አዎ አንተን!” ሥዩም መለሰለት፡፡
“ኧረ በአላህ ይዠሃለሁ፤ ከሁለቱ ቀርቶ ከአንዷ ጋር እንኳ ተኛ ከምባል ለአንድ ወር ያህል ወንዝ ወርደህ ውሃ እየቀዳህ

ማህበረሰቡን አገልግል ብባል ይሻለኛል”
“ለምን?”
“ያችኛዋ…” ወደ ረጅሟ እየተመለከተ “እስዋን ከማቅፍ አጋም እሾህ ላይ ተኛ ብባል ይሻለኛል። ባዶ አጥንት እኮ ናት!

ምኗን ታቅፈዋለህ? በሌላ በኩል ይች ዝተቷ በአንድ በኩል ስታቅፋት ሌላው ይዘረገፍብሃል፡፡ ወይ ደሞ መጀመሪያ

ቦርጯን ሰብስበህ በገመድ ጥፍር አርገህ ታስርና ትንሽ አካል የሚመስል ነገር ካገኘህ መሞከር ነው፤ ኧረ ሁሉም

ይቅሩብኝ” ከድር የተወሰነበት ያህል እያንገሸገሸው ሲመልስ ሁላችንንም አሳቀን፡፡
“ይልቅስ ተመልከት” ከድር ሥዩምን ወደ ሌላ ሴት ጠቆመው፡፡
የተጠቆመችው ሴት አጠር ያለ የባህል ቀሚስ ለብሳ፣ በአገር ባህል መዋቢያዎች የደመቀች ናት፤ አምባሯ፣ አልቦዋ፣ ጨረቃ

ጣልሰሟና ጉትቻዋ ሁሉ ባህላዊ ናቸው፡፡
“ምንም አትል፤ ግን ህዳሴ ቂጥ ናት” እንደታዘዝን ሁሉ ሁላችንም አንዴ በሳቅ አወካን፡፡
“ህዳሴ ቂጥ ማለት ምን ማለት ነው?” የሁለቱን ጨዋታ በአርምሞ ሲከታተል የቆየው ጓደኛዬ ጠየቀ።
“ህዳሴማ የተዝረከረከ ማለት ነው፤ ቅርጽ የሌለው” ሥዩም በልበ ሙሉነት መለሰ፡፡ “እውነቴንኮ ነው ሞፈር ታውቃለህ?

የኔ ወንድም!”
ጓደኛዬ በአንገቱ ንቅናቄ ብቻ ስለ ሞፈር እንደሚያውቅ ለሥዩም መለሰለት፡፡
“እንደዚያ ማለት ናት፤ እግዜር ሲሰራት ሞፈር ሊያረጋት አስቦ ነበር ማለት ነው፤ ሙልጭ አርጐ የጠረባት”
“ቢሆንም ከቅድሟ ድሪቶ እሷ ትሻላለች” ከድር የሥዩምን ሃሳብ የሚቃወም መልስ ሰጠ፡፡ በመሃል ከሙዚቃ ተጫዋቾች

አንዱ ወደ መድረክ ወጣና “ወለቤ፣ ወለቤ፣ የዓባይ ዳር ጉማሬ፣ ወጥቶ አደረ ዛሬ” የሚለውን የአበበ ተሰማ ዘፈን

ይዘፍን ጀመር፡፡ የሁላችንም ሃሳብ ወደ ዘፋኙ እንደ ዞረ:-
“የአባይ ዳር ጉማሬ? የምን የዓባይ ዳር ነው? የሻላ ጉማሬ አይልም? ለራሱ ነው የሚዘፍነው፤ አፉ፣ አፍንጫው፣

ውፍረቱ፣ ቀለሙ በአጠቃላይ የዓባይም ሆነ የጫሞና የሻላ ሃይቆች ጉማሬ ማለት ራሱ ነው” ሥዩም ሲናገር ከድር

አጨበጨበለት፡፡
ወዲያው አንዲት የፈረደባት አጭርና ቀጭን ሴት ወንበር ፍለጋ በአጠገባችን አለፈች፡፡ እሷም ከእነ ከድር ሽሙጥ

አላመለጠችም “ይች አሁን ሰው ናት ወይስ ከአፍ የወደቀች ጥሬ?” ሥዩም ከድርን ጠየቀው፡፡
“ሰው ተሳስቶ ሳያላምጥ የዋጣት ሽንብራ ከዘጠኝ ወር በኋላ ሰው ሆና ወጣች” ከድር የሥዩምን ሃሳብ አዳበረለት፡፡
“ይችንም ሴት ብሎ እንደኔ ያለው አንዱ መከረኛ ያገባት ይሆናል”
“እሱማ ምን ችግር አለው?” ሥዩም ጠየቀው፡፡
“እንደ ቻሌንጀር እጭኑ ላይ ፈንድታ እዳ ውስጥ ታስገባዋለቻ! ምን ነካህ ሥዩሜ! ከዚች የሚወለደውን ልጅም አስበው፤

ሰው ነው ወይስ የሳሎን ውሻ ከዚች ሊወለድ የሚችለው?” ሁለቱ ሲሳሳቁ እኛ ግን ከልብ ደነገጥን፡፡
“ይህንን ሁሉ ጉድ ብትሰማ ምን ይሰማት ይሆን?” ለመጀመሪያ ጊዜ ጠየቅሁአቸው፡፡
“ምን ይሰማታል? ከእኛ በላይ ታውቀዋለች፤ ምን ጣጣ አለው?” ሥዩም ፈጠን ብሎ መለሰልኝ፡፡
“አ…ይ የመብት፣ የሰብአዊነት ጉዳይ…” ሥዩም አላስጨረሰኝም “ከሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ነው የመጣኸው ወንድም!

ለነገሩ እንኳንም ከሂውማን ራይትስዎች አልሆንህ እንጂ ችግር የለውም፡፡ እሱም ቢሆን ኢትዮጵያን የሚመለከታት

በአንተ ዓይን ነው”
“ማለት?” ሃሳቡ ስላልገባኝና የጨዋታውን ርዕስም ያስቀየርሁት ስለመሰለኝ ጥያቄውን አራዘምሁለት፡፡
“ሲጀመር ድሃ አገር ውስጥ እየኖርህ ስለሰብአዊ መብት ልታወራ አትችልም፤ ቅድሚያ ሆድህን ሞልተህ ማደር አለብህ፡፡

የውይይታችን መነሻ የሆነችው ሴትም የድህነት ውጤት ናት”
“የድህነት ውጤት ናት ስትል?”
“የድሃ ልጅ ስለሆነች ነዋ እንዲህ የሽንብራ እሸት አክላ የቀረችው፤ የሃብታም ልጅ ብትሆን ኖሮ ምን አይነት መለሎ

ትሆን ነበር መሰለህ” ሥዩም ሲናገር በሰው ዘር ጥናት የተረቀቀ እውቀት ያለው መስሎ ነው፡፡
“የሩቅ ምስራቅ አገር ሰዎች፤ ለምሳሌ ቻይናውያን፣ ጃፓኖች፣ ኮርያዎች…በጣም አጭሮች ናቸው፤ ድሃዎች ናቸው ማለት

ነው?”
“እኔ የማወራህ ስለ አፍሪካ ድሃዎች ነው፤ አንተ የጠቀስሃቸው ሰዎችም ቢሆኑ ችጋራሞች ነበሩ፤ ከቁመታቸው በፊት

ኢኮኖሚያቸውን ስላሳደጉ ነው፡፡ ምን አለ በለኝ ቁመታቸው ከዚህ በኋላ ያድጋል” ሁላችንም ሳቅንበት፤ ወዲያው ከድር

አቋረጠን፡፡
“ተመልከት ሥዩሜ! ኩንታል ሙሉ የበቆሎ ዱቄት በአካሏ ላይ ገልብጣ መጣችልህ” አለ ከአንድ ጐልማሳ ጋር ወደ

አዳራሹ በመግባት ላይ ወደነበረች ሴት በአገጩ እያመለከተ፡፡
“አብሯት ያለው ሰውየስ የወፍጮ ቤት ሰራተኛ መሆኑ ነው” ሥዩም እየሳቀ ጠየቀው፡፡
“ወይም በአንዱ ጐረምሳ እያስቀናችው ጆንያ አንስቶ ገልብጦባት ይሆናል፤ መቼም ሰው በጤናው አጌጣለሁ ብሎ እንዲህ

ያልተጠረገ ቋት መስሎ ሰርግ ቤት አይሄድም” ከድር ሃሳቡን አገዘፈለት፡፡
ከመሃል “ሙሽሮች እየደረሱ ስለሆነ ሁላችንም ብድግ ብለን በእልልታና በጭብጨባ እንቀበላቸው” የሚል ድምጽ

ከመድረክ አስተጋባ።
“እናጨበጭባለን እንጂ! ሥራችን ማጨብጨብ አይደል፤ ቀበሌ ጭብጨባ፣ ለስብሰባ በተጠራንበት ቦታ ሁሉ ጭብጨባ፣

ወያላ ሲሰድበን ጭብጨባ፣ ፖሊስ ሲደበድበን ጭብጨባ፣ ቺኮቻችን ሲያዋርዱን ጭብጨባ፣ በቃ ለጭብጨባ የተፈጠርን

አጨብጫቢዎች” ሥዩም በራሱ ንግግር ተበሳጨ፡፡
በጭብጨባና በእልልታ ታጅበው ሙሽሮቹ ቦታቸውን ያዙ፤
“ይች ናት እንዴ ሙሽራዋ” ከድር ሳቅ እያፈነው ጠየቀ፡፡
“የለም ተመሳሳይዋ ናት” ሥዩምም ሳቀ፡፡
“እየቀለድሁ አይደለም ሥዩሜ… እስኪ ተመልከታት፤ የራበው አዞኮ ነው የምትመስል”
“ጨዋታችሁን ሳዳምጥ ሴቶቹን ብቻ ነው የምትተቹ፤ ወንዶች ምንም ችግር የለባቸውም ማለት ነው?” ጓደኛዬ ለሁለተኛ

ጊዜ ጠየቀ፡፡
“እንደ ሴቱ አይሆኑም እንጂ ግራ የገባቸው ወንዶች ሞልተዋል፤ ግን የእኔ ወንድም በሰርግ ቀን ሴቶችን ልብ ብለህ

አስተውለሃል? ፊተ ሾጣጣ፣ ጥርሰ ገጣጣ፣ ቂጠ ሞጥሟጣ፣ ዓይነበልጣጣ ሆዷ የተዘረገፈ፣ ለምቦጯ እንደ እበት

የተጠፈጠፈ፣ ኧረ ስንቱን ቆጥሬ እገፋዋለሁ? ልብሳቸው፣ መዋቢያቸው፣ ጠቅላላ ሁኔታቸው ሁሉ ጅራቷን የተቆረጠች

እንሽላሊት ነው የሚመስሉት፤ መልሰው ሰው ሲሆኑ ይገርመኛል…” ከድር መለሰለት፡፡
የሥዩምንና የከድርን ሃሜታዊ ወግ እያዳመጥን አልፎ አልፎም እየጠየቅን ቆይተን ምሳ ለማምጣት ወደ ብፌው ቦታ

አመራን፤ ቀልባችን የወደደውን መራርጠን ከተመለስን በኋላ ምግቡም ሃሜቱም ቀጠለ፡፡
“ለዚህ ነው እንዴ ደጅ ስንጠና የዋልነው?” ሥዩም እየተመገበ፤ ግን ደግሞ የሚመገበውን ቁርጥ ያናንቅ ጀመር፡፡
“ይኸ ለውሻ አይሰጥም እንኳን በክብር ለተጠራ እንግዳ፤ እውነቴን ነው፡፡ የእነ ጐሹ ሰርግ እለት የቀረበውን ጮማ አየህ

አይደል ከድሬ!” ሥዩም ምግቡንም ከሃሜቱ ጋር እየቀላቀለ ያቀላጥፈዋል፡፡
“ካልወደድኸው መጀመሪያ ለምን ተሸከምህ? አሁንስ ማን አስገድዶህ ትበላለህ?”ልለው አማረኝና “ከነገረኛ ሰው ስንቅ

አይደባልቁም” የሚለው ብሂል ትዝ ስላለኝ ተውሁት፡፡
ከድር ስለምግቡ ምንም አስተያየት ሳይሰጥ ተመገበና እጁን በለስላሳ ወረቀት ጠራርጐ ወደ መታጠቢያ ቤት አመራ፡፡
“የዚህ ሰውዬ ነገር በጣም ይገርመኛል፤ አሁን ይኸ እስላም ነው ክርስቲያን? ብቻ ሆዱ ይሙላ እንጂ ያገኘውን ሁሉ

ጥር… ግ ነው” ሥዩም ጓደኛውን እንኳ የማይምር መሆኑን ሳውቅ ተፈጥሮው አስገረመኝ፡፡
የሐሜቱ ድር ዞሮ ዞሮ ከሃሜተኞች ጋ መድረሱም በእጅጉ አስደነቀኝ፡፡
“የእኔ ወንድም የሌለ ድንበር እናበጃለን እንጂ ሙስሊም ወይም ክርስቲያን በሬ በዓለማችን የለም” ብየው ጓደኛዬን

አስነሳሁና ወደ ሰፈራችን ተጓዝን፤ ዘወር ስንልለት ጥሬ ስጋችንን እንደሚበላው ግን እርግጠኞች ነበርን፡፡ 

Read 6440 times