Saturday, 30 November 2013 10:35

ኢትዮጵያ በሴካፋ ላይ…

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው አስቀድሞ ከ2004 እሰከ 2006 እኤአ ብሄራዊ ቡድኑን በዋና

አሰልጣኝነት ሲመሩ በ5 ዓመት ውስጥ 3 የሴካፋን ዋንጫዎችን  ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋር ለማግኘት በቅተዋል፡፡

በ2005 እ.ኤ.አ በሩዋንዳ ላይ እንዲሁም በ2004 እ.ኤ.አ ደግሞ አዲስ አበባ ላይ ሁለት የሴካፋ ዋንጫዎችን በዋና

አሰልጣኝነት ያሸነፉት ሰውነት በ2001 እ.ኤ.አ በረዳት አሰልጣኝነት ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር የሴካፋን ዋንጫ ሩዋንዳ ላይ

እንዳገኙ ይታወቃል፡


በኬንያ አስተናጋጅነት ከተጀመረ አራተኛ ቀኑን በያዘው 37ኛው የምስራቅ እና መካከለኛው የእግር ኳስ ሻምፒዮና በተስፋ

ቡድኗ የምትሳተፈው ኢትዮጵያ ከምድቡ ለማለፍ ዛሬ ከዛንዚባር ጋር በምታደርገው ወሳኝ ጨዋታ ማሸነፍ

ይጠበቅበታል፡፡ የምድብ 1 የመጀመርያ ግጥሚያዎች ባለፈው ረቡዕ  ተደርገው በከፍተኛ ጉጉት የተጠበቀው የአዘጋጇ

ኬንያ እና ኢትዮጵያ ጨዋታ ያለንምንም ግብ 0ለ0 ሲጠናቀቅ፤ በሌላ የምድቡ ጨዋታ ደግሞ ዛንዚባር 2ለ0 ደቡብ

ሱዳንን አሸንፋለች፡፡ በሻምፒዮናው የምድብ 1 ሁለተኛ ዙር ጨዋታዎች ዛሬ ሲቀጥሉ ኢትዮጵያ ከዛንዚባር ፤ ኬንያ ደግሞ

ከደቡብ ሱዳን ጋር ይጫወታሉ፡፡ ኢትዮጵያን የወከለው ተስፋ ቡድን ከምድብ 1 የማለፍ እድሉን ለመወሰን ከዛንዚባር

ጋር በሚያደርገው ጨዋታ ማሸነፍ ብቸኛው አማራጩ ሲሆን ካልቀናው ሰኞ ከደቡብ ሱዳን ጋር የሚያደርገው የምድቡ

የመጨረሻ ጨዋታ መርሃግብሩን ለመጨረስ የሚካሂደው ይሆናል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በ2005 እኤአ ላይ

ለአራተኛ ጊዜ የዞኑ ሻምፒዮን ለመሆን ከበቃ ወዲህ ያን ያህል ጠንካራ ውጤት ሊያስመዘግብ አዳግቶታል፡፡ በዘንድሮው

የሴካፋ ውድድር ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ዓመታት ለአፍሪካ ዋንጫ በማለፍ፤ ለዓለም ዋንጫ የመጨረሻ ጥሎ ማለፍ

ምእራፍ በመድረስ እና የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮንሺፕ ተሳትፎውን ያረጋገጠውን ዋና ቡድኗን ባለማሰለፏ ከዋንጫው

ግምት ውጭ ያደረጋት ሲሆን የተስፋው ቡድን ከሩብ ፍፃሜ ለማለፍ እንኳን ከባድ ፈተና እንደሚገጥመው እየተገለፀ

ነው፡፡ ባለፈው ረቡዕ የተስፋ ቡድኑ ከኬንያ ጋር 0ለ0 አቻ ከተለያየ በኋላ አስተያየታቸውን ለሱፕር ስፖርት የሰጡት

አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው የሴካፋው ተሳትፎ ብሄራዊ ቡድናቸው ለቻን ውድድር ጠቃሚ ልምድ ሊያገኝበት አስቦ

የሚወዳደረው መሆኑን ገልፀው፤ ለውድድሩ ከአራት ቀናት ያነሰ ዝግጅት ማድረጋቸው ለምድቡ የመጀመርያ ጨዋታ በቂ

ሁኔታ አልነበረምም ብለዋል፡፡ ፡ ኢትዮጵያ ከኬንያ ጋር በናያዮ ስታድዬም ያደረገችውን ግጥሚያ በርካታ ተመልካች

የታደመው ሲሆን በተለይ በተከላካይ መስመር ተሰልፈው የነበሩት የቅዱስ ጊዮርጊሱ ሳላዲን በርጌቾ እና የኢትዮጵያ

ቡናው ቶክ ጀምስ ምርጥ ብቃት ማሳየታቸውን ሱፕር ስፖርት ዘግቦታል፡፡ ከምድብ 1 የመጀመርያ ጨዋታዎች በኋላ ወደ

ቀጣዩ ምዕራፍ ለመሸጋገር እድል አላቸው ከተባሉት ኬንያና ኢትዮጵያ ይልቅ ዛንዚባር ሁኔታዎች ተመቻችተውላታል፡፡  

ቀድሞ የታንዛኒያ ብሄራዊ ቡድን ተጨዋች በነበሩት ሳሉ ሙናሽሮ የሚሰለጥነው የዛንዚባር ብሄራዊ ቡድን በፊፋ እውቅና

ያላገኘ ሲሆን የተመዘገበው በታንዛኒያ ቡድን አካል ሆኖ ነው፡፡ ዛንዚባር በሴካፋ የረጅም ጊዜ ተሳትፎ ታሪኳ በ1995

እኤአ ላይ ብቸኛውን የዋንጫ ድል አስመዝግባለች፡፡ የ37ኛው የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ሻምፒዮና  አዘጋጅ

የሆነችው ኬንያ በውድድሩ ሻምፒዮን ከሆነች 11 ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ኬንያ በሴካፋ ሻምፒዮና ለአምስት ጊዜ

ዋንጫውን በማንሳትና 6 ጊዜ ሁለተኛ ደረጃ በማግኘት በምንጊዜም የውጤት ደረጃ ሁለተኛ ስትሆን በፊፋ የእግር ኳስ

ደረጃዋ 118ኛ ነው፡፡ ነፃነቷን ካገኘች በኋላ በሴካፋ ዞን ውድድር ስትሳተፍ ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜዋ የሚሆነው ደቡብ

ሱዳን የባንግላዴሽ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ በነበሩት ዞራን ዶርዴቪች ትመራለች፡፡ ደቡብ ሱዳን በፊፋ የእግር ኳስ ደረጃ

የመጨረሻውን 205ኛ ደረጃን ይዛለች፡፡
የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ የእግር ኳስ ሻምፒዮና ከተጀመረ ከ87 ዓመታት በላይ ማስቆጠሩ የዓለማችን

አንጋፋው የእግር ኳስ ውድድር ያደርገዋል፡፡ የእግር ኳስ ሻምፒዮናው በ1926 እኤአ ላይ ተጀምሮ 1983 እስከ 1966

እኤአ ድረስ በዊልያም ጎሴጅ የሳሙና ፋብሪካ ስፖንሰርነት ሲካሄድ ጎሴጅ ካፕ ተብሎ ለ37 ጊዜያት የተከናወነ ነበር፡፡

ከ1967 እስከ 1971 እኤአ ለአምስት ጊዜያት የዞኑ የእግር ኳስ ሻምፒዮና ፓልሜሬስ ካፕ ተብሎም ተካሂዷል፡፡ በጎሴጅ

እና ፓልሜሬስ ካፕ ተሳታፊ የነበሩት አገራት ኬንያ፤ ኡጋንዳ፤ ታንጋኒካ እና ዛንዚባር ናቸው፡፡
በሴካፋ ምክርቤት ስር የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ሻምፒዮና ‹‹ሲኒዬርስ ቻሌንጅ ካፕ ተብሎ ››መካሄድ

የተጀመረው በ1973 እኤአ  ላይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ የተሳተፈችው ደግሞ በ1983 እኤአ ላይ በኬንያ

ሲካሄድ ነበር፡፡ በወቅቱ በምድብ 1 ከኬንያ፤ ከኡጋንዳ፤ ከሱዳንና ከታንዛኒያ ጋር ተደለደለች፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን

በመጀመርያ ጨዋታ ከታንዛኒያ አንድ እኩል አቻ ከተለያየ በኋላ፤ በኬንያ 2ለ0፤ በሱዳን 2ለ0 እንዲሁም በኡጋንዳ 2ለ1

ተሸንፎ በ1 ነጥብ የምድቡን የመጨረሻ ደረጃ በመያዝ ተሰናብቷል፡፡ ከዚሁ የመጀመርያ ተሳትፎ በኋላ 3 የምስራቅ እና

መካከለኛው አፍሪካ ሻምፒዮና ውድድሮች ያመለጣት ኢትዮጵያ በ1987 እኤአ ላይ ውድድሩን በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ

የማስተናገድ እድል አገኘች፡፡ በአዲስ አበባ ስታድዬም በተደረገው በዚሁ 15ኛው የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ የእግር

ኳስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ በምድብ 1 የተደለደለችው ከዛንዚባር፤ ከኬንያ እና ከታንዛኒያ ጋር ነበር፡፡ በመጀመርያዎቹ

የምድቡ ሁለት ጨዋታዎች የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከታንዚያ እና ከዛንዚባር ጋር ያለምንም ግብ 0ለ0 በሆነ ተመሳሳይ

ውጤት ነበር የተለያየው፡፡ በመጨረሻ ጨዋታ ኬንያን 2ለ1 ካሸነፈ በኋላ ግን በ4 ነጥብ በምድቡ ሁለተኛ ደረጃ ይዞ

በመጨረስ ወደ ግማሽ ፍፃሜ ገባ፡፡ በግማሽ ፍፃሜው የተገናኘው ከኡጋንዳ ጋር ሲሆን 3ለ0 አሸነፈ፡፡ ኢትዮጵያ

ለመጀመርያ ጊዜ ባስተናገደችው የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ሻምፒዮና ላይ ብሄራዊ ቡድኑ ለመጀመርያው የዋንጫ

ጨዋታው ሲቀርብ የተገናኘው ከደቡብ አፍሪካ በተጋባዥነት ከተሳተፈችው ዚምባቡዌ ጋር ነበር፡፡ በመደበኛው የጨዋታ

ክፍለ ጊዜ 1 እኩል አቻ ሆኑ፡፡ አሸናፊውን ለመለየት በተሰጡ የመለያ ምቶች ኢትዮጵያ 4ለ3 ዚምባቡዌን በማሸነፍ

የመጀመርያውን  የሻምፒዮናነት ክብር ለማሳካት በቃች፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በቀጣይ ሻምፒዮናነቱን ለማስጠበቅ የተሳተፈበት የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ሻምፒዮና

በ1988 እኤአ ላይ በማላዊ የተካሄደው ነበር፡፡ ኢትዮጵያ በምድብ 2 ከዛምቢያ፤ ከዚምባቡዌ እና ከኡጋንዳ ጋር ነበረች፡፡

ከዛምቢያ ጋር 0ለ0 የተለያየው የኢትዮጵያ ቡድን በሁለተኛ ጨዋታው ኡጋንዳን 2ለ1 ቢያሸንፍም በመጨረሻ በዚምባቡዌ

2ለ1 በመረታተቱ በ3 ነጥብ የምድቡን 3ኛ ደረጃ ይዞ በጊዜ ሻምፒዮናነቱን ሳያስጠበቅ ተሰናብቷል፡፡
ኢትዮጵያ በ1989 እኤአ በኬንያ፤ በ1990 እኤአ በዛንዚባር እና በ1991 እኤአ ላይ በኡጋንዳ በተካሄዱት ሶስት የምስራቅ

እና መካከለኛው አፍሪካ ሻምፒዮናዎች ሳትሳተፍ ቀረች፡፡ በ1992 እኤአ ላይ ውድድሩ በታንዚያ ሲካሄድ ኢትዮጵያ

ተመልሳ ወደውድድሩ በመቀላቀል ከማላዊ፤ ከዛምቢያ፤ ከታንዛኒያ እና ከዛንዚባር ጋር በምድብ 2 ተመደበች፡፡ ዛንዚባርን

3ለ0 በማሸነፍ ጥሩ አጀማመር አሳይቶ የነበረው ቡድኑ በዛምቢያ 3ለ2፤ በታንዛኒያ 2ለ1 እንዲሁም በማላዊ 2ለ1

ተደራራቢ ሽንፈት ደርሶበት በ2 ነጥብ ከምድብ ሳያልፍ ቀረ፡፡ በቀጣይ በ1994 እኤአ ላይ ውድድሩን ኬንያ ስታስተናግድ

ኢትዮጵያ አልነበረችም፡፡ በ1995 እኤአ ላይ ውድድሩ በኡጋንዳ ሲዘጋጅ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ገብቶ በምድብ 2

ከኡጋንዳ ቢ፤ ከታንዛኒያ እና ከሶማሊያ ተገናኘ፡፡ ከታንዛኒያ ጋር 2 እኩል አቻ በመለያየት የምድብ ፉክክሩን የጀመረው

ቡድኑ የኡጋንዳ ቢ ቡድንን 1ለ0 ከዚያም ሶማሊያን 3ለ0 አሸንፎ በ7 ነጥብ የምድቡ መሪ ሆኖ አለፈ፡፡ በግማሽ ፍፃሜ

የተገናኘው  ከዛንቢያ ጋር ሲሆን በመደበኛው እና በተጨማሪዎቹ የጨዋታ ክፍለ ጊዜዎች 1 እኩል ከተለያየ በኋላ

አሸናፊውን ለመለየት በተደረጉ የመለያ ምቶች ተሸነፈ፡፡ በመቀጠል ለደረጃ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከኬንያ ጋር

ተጫውቶ 2ለ1 በማሸነፍ በሶስተኛ ደረጃ ተሳትፎውን ደምድሞታል፡፡ በ1996 እኤአ  ሱዳን ላይ እንደሚካሄድ ተወስኖ

የነበረውና በ1997 እኤአ አዘጋጅ አገር ባለመመረጡ ሁለት የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ሻምፒዮናዎች

አልተካሄዱም፡፡  በ1998 እኤአ ላይ በሩዋንዳ ውድድሩ ሊካሄድ ታቅዶ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን በሴካፋ

ምክርቤት ላይ እግድ በመጣሉ እና ከ1998ቱ የዓለም ዋንጫ በፊት በፊፋ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ከመደረጉ ጋር በተያያዘ

ሻምፒዮናው በድጋሚ ሳይካሄድ ተሰርዟል፡፡ በዚህ ውድድር ለመሳተፍ ፍላጎት የነበራት ኢትዮጵያ በምድብ 1 ከሩዋንዳ፤

ከኡጋንዳና ከብሩንዲ ጋር ተደልድላ ነበር፡፡ የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ሻምፒዮና ለ4 ዓመታት ሳይካሄድ

ውጣውረድ ከቆየ በኋላ በ1999 እኤአ ላይ የተዘጋጀው በሩዋንዳ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ በምድብ 3 ከሱዳንና ዛንዚባር ጋር

ተመደበች፡፡  ዛንዚባርን 2ለ0 ያሸነፈው ቡድን ከሱዳን ጋር ለ0 አቻ ተለያይቶ በ4 ነጥብ የምድቡ መሪ ሆኖ አለፈ፡፡

በሩብ ፍፃሜ ምእራፍ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የተገናኘው ከሩዋንዳ ቢ ቡድን ጋር ቢሆንም 1ለ0 ተሸንፎ ከውድድሩ

ውጭ ሆኗል፡፡
በ2000 እኤአ ላይ አዘጋጇ ኡጋንዳ ነበረች፡፡ ኢትዮጵያ በምድብ 1 ከኡጋንዳ፤ ከብሩንዲ፤ ከጅቡቲ እና ከሶማሊያ ጋር

ተደለደለች፡፡ በመጀመርያ ጨዋታ ከኡጋንዳ ጋር 2ለ2 አቻ ስትለያይ ለኢትዮጵያ ጎሎቹን ያስቆጠሩት ስንታየሁ ጌታቸው

እና ሁሴን ሰማን ነበሩ፡፡ ሶማሊያን 2ለ1 ስታሸንፍ ደግሞ ግቦቹን ስንታየሁ ጌታቸው እና ሁሴን ሰማን አስቆጥረዋል፡፡

በምድቡ 3ኛ ጨዋታ ላይ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ጅቡቲን 4ለ2 ያሸነፈ ሲሆን ጎሎቹን ሁለቱን እስማኤል አቡበከር፤

እንዲሁም ስንታየሁ ጌታቸውና እና ጌቱ ተሾመ የተቀሩትን አስመዝግበዋል፡፡ በምድቡ የመጨረሻ ጨዋታ ቡድኑ ብሩንዲን

1ለ0 ሲያሸንፍ ጎሏን ያስመዘገበው እስማኤል አቡበከር ነበር፡፡ በምድብ ጨዋታ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከፍተኛ

ብቃቱን ያስመዘገበበት አቋም ለዋንጫው ግምት ያሳደረ ነበር፡፡ ምድቡን በ10 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበልጦ በሁለተኛ ደረጃ

የጨረሰው ቡድኑ በግማሽ ፍፃሜ የተገናኘው ከኡጋንዳ ጋር ሲሆን ሳይጠበቅ 1ለ0 ተሸንፎ ለደረጃ መጫወት ግድ

ሆነበት፡፡ ለደረጃ በተደረገው ጨዋታ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የተገናኘው ከሩዋንዳ ሲሆን 1ለ1 አቻ ተያይዞ ቢቆይም

በመለያ ምቶች 4ለ2 ተሸንፎ በ4ኛ ደረጃ ጨርሷል፡፡
በ2001 እኤአ ላይ ሱዳን አዘጋጃለሁ ብላ የሰረዘችውን ሻምፒዮና በምትክነት ያስተናገደችው ሩዋንዳ ነበረች፡፡ ኢትዮጵያ

በምድብ 3 ከሩዋንዳ ቢ ቡድንና ዛንዚባር ጋር ተመደበች፡፡ ዛንዚባርን በመጀመርያ ጨዋታ 5ለ0 ስታሸንፍ ይልማ፤

አፈወርቅ፤ ዮርዳኖስ ፤ ፈቃዱ እና ባዩ ሙሉ ጎሎቹን ከመረብ አዋህደዋል፡፡ በመቀጠል ከሩዋንዳ ቢ ቡድን ጋር 1ለ1 አቻ

ስትለያይ ጎሎን ያገባው ባዩ ሙሉ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ በ4 ነጥብ የምድቡ መሪ ሆና አለፈች፡፡ በሩብ ፍፃሜ ከብሩንዲ ጋር

የተገናኘው ቡድኑ በጨዋታ ክፍለ ጊዜ 2ለ2 አቻ ተለያየየ፡፡ ጎሎቹ የዮርዳኖስ አባይና ባዩ ሙሉ ናቸው፡፡ አሸናፊውን

ለማወቅ መለያ ምቶች ተሰጥተው ኢትዮጵያ 5ለ4 ብሩንዲን አሸንፋ ግማሽ ፍፃሜ ገባች፡፡ በግማሽ ፍፃሜው ሩዋንዳን

ስታሸንፍ ብቸኛዋን የማሸነፊያ ጎል ያስመዘገበው ባዩ ሙሉ ነበር፡፡ በመጨረሻም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ለዋንጫ

ጨዋታ ከኡጋንዳ ጋር ተገናኘ፡፡ ማሞዓለም ሻንቆ እና ዮርዳኖስ አባይ ባስቆጠሯቸው  ጎሎች 2ለ1 በማሸነፍ የኢትዮጵያ

ብሄራዊ ቡድን ለሁለተኛ ጊዜ የሴካፋ ሻምፒዮን ለመሆን በቃ፡፡ ይህ የዋንጫ ድል ከአገር ውጭ የተገኘ በመሆኑ

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ  አበይት ስኬት ሆኖ ለመጠቀስ የበቃ ነበር፡፡ በ2002 እኤአ  የምስራቅ እና መካከለኛው

አፍሪካ ሻምፒዮናን ያስተናገደችው ታንዛኒያ ነበረች፡፡ ኢትዮጵያ በምድብ 2 ከኡጋንዳ፤ ሩዋንዳ እና ዛንዚባር ጋር

ተደለደለች፡፡ ከዛንዚባር ጋር 0ለ0 የተለያየው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በኡጋንዳ 3ለ0 ሲሸነፍ አንተነህ አላምረው

በራሱ ላይ አግብቶ ነበር፡፡ በ3ኛው የምድቡ ጨዋታ ሻምፒዮናነቱን ያስጠብቃል ተብሎ የነበረው ቡድኑ ባልተገመተ

ሁኔታ በሶማሊያ 1ለ0 ተሸነፈ፡፡ ከዚያም በምድቡ የመጨረሻ ጨዋታ በድጋሚ በሩዋንዳ 1ለ0 ተረትቶ ሻምፒዮናነቱን

ሊያስጠብቅ ሳይችል በ1 ነጥብ የምድቡ መጨረሻ ደረጃ ይዞ ውድድሩ ተሰናብቷል፡፡ በ2003 እኤአ ላይ  የምስራቅ እና

መካከለኛው አፍሪካ ሻምፒዮናን ሱዳን ስታዘጋጅ ኢትዮጵያ በምድብ 2 ከኬንያ፤ ኡጋንዳ እና ኤርትራ ጋር ተደልድላ

የነበረ ቢሆንም ሳትሳተፍ ቀረች፡፡
በ2004 እኤአ ላይ ክቡር ሼህ መሃመድ አላሙዲ የሴካፋ ውድድርን ስፖንሰር በማድረጋቸው የእግር ኳስ ሻምፒዮናው

በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በታሪክ ለሁለተኛ ጊዜ ሊካሄድ በቃ፡፡ በአዲስ አበባ ስታድዬም በተደረገው በዚሁ ውድድር

ኢትዮጵያ በምድብ 1 ከብሩንዲ፤ ከሩዋንዳ፤ ከዛንዚባር እና ታንዛኒያ ጋር ነበር የተመደበችው፡፡ በመጀመርያው ጨዋታ

ሰብስቤ ሸገሬ እና ፍቅሩ ተፈራ ባስቆጠሯቸው ጎሎች ብሩንዲን 2ለ1 ያሸነፈው ቡድኑ በመቀጠል ከሩዋንዳ ጋር 0ለ0 አቻ

ተለያየ፡፡ በሶስተኛው የምድቡ ጨዋታ ታንዛኒያን 2ለ0 ድል ማድረግ የተቻለው በአንተነህ አላምረው እና በታፈሰ ተስፋዬ

ጎሎች ነበር፡፡ በምድቡ የመጨረሻ ጨዋታ ላይ ደግሞ የኢትዮጵያ ቡድን ዛንዚባርን 3ለ0 ሲያሸንፍ ጎሎቹን ፍቅሩ ተፈራ፤

አሸናፊ ግርማ እና ሃይደር መንሱር አግብተዋል፡፡ በዚህ መሰረት የኢትዮጵያ ቡድን ምድቡን በ10 ነጥብ በመምራት ግማሽ

ፍፃሜ ገባ፡፡ በግማሽ ፍፃሜው  ከኬንያ ጋር የተገናኘው ቡድኑ አንተነህ አላምረው እና ታፈሰ ተስፋዬ ባስቆጠሯቸው

ጎሎች ሁለት እኩል አቻ ከተለያየ በኋላ በመለያ ምት አሸናፊው ሲለይ 5ለ4 ረትቶ ለሶስተኛ ጊዜ በሴካፋ ሻምፒዮና

የዋንጫ ጨዋታ ላይ ቀረበ፡፡ በዋንጫ ጨዋታው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ብሩንዲን በአንዷለም ንጉሴ፤ በታፈሰ ተስፋዬ

እና በአንተነህ አላምረው ጎሎች 3ለ0 በማሸነፍ በታሪክ ለሶስተኛ ጊዜ የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ሻምፒዮና

ዋንጫን ተጎናፀፈ፡፡
በ2005 እኤአ ላይ የውድድሩ አዘጋጅ የሆነችው ሩዋንዳ ነበረች፡፡ ኢትዮጵያ ሻምፒዮንነቷን ለማስጠበቅ ተስፋ አድርጋ

በምድብ 2 ከኡጋንዳ፤ ከሱዳን፤ ከሶማሊያ እና ከጅቡቲ ጋር ተመደበች፡፡ በመጀመርያው ጨዋታ ከኡጋንዳ ጋር 0ለ0

ከተለያየች በኋላ በሁለተኛው ግጥሚያ ሱዳንን 3ለ1 የረታችው በሰብስቤ ሸገሬ ሃትሪክ ነበር፡፡ በቀጣይ የኢትዮጵያ

ብሄራዊ ቡድን ጅቡቲን 6ለ0 እንዲሁም ሶማሊያን 3ለ1 በማሸነፍ በ10 ነጥብ የምድቡን ሁለተኛ ደረጃ ይዞ አለፈ፡፡

በግማሽ ፍፃሜ ቡድኑ ዛንዚባርን 4ለ0 ሲያሸንፍ ፍቅሩ ተፈራ ሃትሪክ የሰራ ሲሆን አንደኛዋን ጎል ደግሞ አሸናፊ ግርማ

አስመዝግቧታል፡፡ በዋንጫ ጨዋታው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የተገናኘው ከሩዋንዳ ጋር ሲሆን በጨዋታው

የማሸነፊያዋን ብቸኛ ጎል ያገባው በቀይ ካርድ የወጣው አንዱዓለም ንጉሴ ነበር፡፡ በዚህም ውጤት የኢትዮጵያ ብሄራዊ

ቡድን በተከታታይ ዓመት የውድድሩ አሸናፊ ሆኖ ሻምፒዮናነቱን ከማስጠበቅ ባሻገር በተሳትፎ ታሪኩ አራተኛውን ዋንጫ

ለማግኘት ችሏል፡፡
በ2006 እኤአ ላይ የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ሻምፒዮና ውድድርን ለአራተኛ ጊዜ የማስተናገድ እድሉን ያገኘችው

የአራት ግዜ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ ነበረች፡፡ በምድብ 1 ከታንዛኒያ፤ ከማላዊ እና ከጅቡቲ ጋር ተመድባ ነበር፡፡

በመጀመርያው ጨዋታ በታንዛኒያ 2ለ1 ስትሸነፍ የማፅናኛዋን ጎል ያስመዘገበው ቢኒያም ታፈሰ ነበር፡፡ በመቀጠል ጅቡቲን

በዳዊት መብራቱ፤ ታፈሰ ተስፋዬ፤ ባህይሉ ደመቀና ብዙነህ ወርቁ ጎሎች 4ለ0 የረታው የኢትዮጵያ ቡድን ማላዊን

በዳዊት መብራቱ ጎል 1ለ0 በማሸነፍ ለሩብ ፍፃሜው የበቃው በ6 ነጥብ የምድቡ ሁለተኛ ሆኖ ነበር፡፡ በሩብ ፍፃሜው

በሜዳው እና በደጋፊው የተጫወተው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በዛምቢያ 1ለ0 ተሸንፎ ከውድድሩ ውጭ ሆነ፡፡ በአዲስ

አበባ ተደርጎ የነበረውን የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ሻምፒዮና ዋንጫንዛምቢያ ሱዳንን በመለያ ምቶች 11ለ 10  

በማሸነፍ ወስዳለች፡፡ በ2007 እኤአ ላይ የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ሻምፒዮና  በታንዛኒያ አዘጋጅነት ሲካሄድ

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በምድብ 3 ከዛንዚባር እና ሱዳን ጋር ተደልድሎ ነበር፡፡ በምድቡ የመጀመርያ ጨዋታ

በዛንዚባር 3ለ1 የተሸነፈው ቡድኑ ከሱዳን ጋር ያለምንም ግብ አቻ ከተለያየ በኋላ በ1 ነጥብ መጨረሻ ደረጃ ይዞ

ከውድድሩ የምድብ ምእራፍ ተሰናብቷል፡፡ ሻምፒዮናው በ2008 እኤአ መካሄድ ሲቀጥል አጋጇ ኡጋንዳ የነበረች ሲሆን

ኢትዮጵያ አልተሳተፈችበትም ነበር፡፡ በ2009 እኤአ ላይ የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ሻምፒዮና የተካሄደው ኬንያ

ላይ ነው፡፡ በዚሁ ውድድር ኢትዮጵያ በምድብ 1 ከዛምቢያ፤ ከኬንያ እና ከጅቡቲ ጋር ተደልድላለች፡፡ በመጀመርያ

ጨዋታ ጅቡቲን 5ለ0 ላሸነፈው የኢትዮጵያ ቡድን ጎሎቹን ያስቆጠሩት ሁለቱን ኡመድ ኡክሪ እንዲሁም ሌሎቹን አየነው

አክሊሉ፤ አዳነ ግርማና ታፈሰ ተስፋዬ ናቸው፡፡ በቀጣይ በተደረጉት የምድብ ጨዋታዎች የኢትዮጵያ ቡድን በዛምቢያ

1ለ0 እንዲሁም በኬንያ 2ለ0 በመሸነፉ ከውድድሩ በጊዜ መሰናበት ግድ ሆኖበታል፡፡
በ2010 እና በ2011 እኤአ ላይ ሻምፒዮናው የተስተናገደው የሴካፋ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሊዮዳር ቴንጋ አገር በሆነችው

ታንዛኒያ ውስጥ ነበር፡፡  በ2010 እኤአ ላይ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በምድብ 3 ከኡጋንዳ ፤ ከኬንያ እና ከማላዊ

ተደልድሎ ነበር፡፡  በመጀመርያው ጨዋታ ቡድኑ በኡጋንዳ 2ለ1 ቢሸነፍም በቀጣይ ኬንያን 2ለ1 በመርታት እንዲሁም

ከማላዊ 1ለ1 አቻ በመለያየት ከምድቡ ማለፉን አረጋገጠ፡፡ በሩብ ፍፃሜ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዛምቢያን 2ለ1 አሸንፎ

በግማሽ ፍፃሜ ከአይቬሪኮስት በመገናኘት 1ለ0 ተሸንፎ ውድድሩን በ4ኛ ደረጃ አገባድዷል፡፡በ2011 እኤአ ላይ ሴካፋው

በታንዛኒያ በድጋሚ ሲደረግ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን  የገባው ለዋንጫው ግምት አግኝቶ ነበር ፡፡ በወቅቱ በምድብ 3

ከማላዊ፤ ከሱዳንና ከኬንያ ጋር ተደልድሏል፡፡ በመጀመርያው ጨዋታ ከሱዳን ጋር አቻ ሲለያይ ጎል ያገባው ጌታነህ ከበደ

ነበር፡፡ ከዚያም በኬንያ 2ለ0 ተሸነፈ እና በመጨረሻው ጨዋታ አሁንም በጌታነህ ከበደ ጎል 1 እኩል  ከማሊ ጋር አቻ

ወጥቶ ከምድብ ማጣርያው ውድድሩን ተሰናብቶታል፡፡ በ2012 እኤአ ላይ ውድድሩ  በኡጋንዳ ነበር የተዘጋጀው፡፡

ኢትዮጵያ በምድብ 1 ከዩጋንዳ ከደቡብ ሱዳንና ከኬንያ ጋር ነበረች፡፡ በመጀመርያው ጨዋታ ደቡብ ሱዳንን 1ለ0

ያሸነፈው ቡድኑ በዩጋንዳ 1ለ0 እንዲሁም በኬንያ 3ለ1 ቢሸነፍም በአወዛጋቢ ሁኔታ በምድብ ምርጥ ሶስተኛነት ወደ

ቀጣይ ምዕራፍ ሊሸጋገር በቅቷል፡፡ ይሁንና ሩብ ፍፃሜ ላይ 2ለ0 በኡጋንዳ ተሸንፎ ተሳትፎውን ጨርሷል፡፡ በወቅቱ  

በሴካፋው የተሳተፈው የኢትዮጵያ ቡድን በወቅቱ ለአፍሪካ ዋንጫ ላለፈው ዋና ብሄራዊ ቡድን ‹‹ሻዶው ቲም›› ተብሎ

የብሄራዊ ቡድኑ ረዳት አሰልጣኝ በነበሩት በስዩም ከበደ የሚመራ ነበር፡፡

Read 3742 times