Monday, 25 November 2013 10:58

አለምን አሳምሮ፣ ነፍስን ዘርቶ ክብርን የሚያጐናጽፍ ብርቅ ሰዓሊ

Written by  ዮሐንስ ሰ.
Rate this item
(3 votes)

           ከአስራ ሁለት ዓመት በፊት ነበር ለመጀመሪያ ጊዜ የመዝገቡ ተሰማ ስዕሎችን የማየት እድል ያገኘሁት፡፡ በህይወት ከምናያቸው ማራኪ መናፈሻ ስፍራዎች ሁሉ ያማረና የለምለም ድንቅ መስክን በምናባችሁ አስቡ፡፡ አድማስ ድረስ የሚዘልቅ የሚመስልና መንፈስን የሚያዝናና አረንጓዴ መስኩ ላይ ደግሞ፤ በአካል ከምናያቸው ውብ ቆነጃጅት ሁሉ የላቀች ለግላጋ ወጣት! ከመቅጽበት በፍቅር የምትማርክና ልብን የምታንጠለጥል ይህችው የውበት ልዕልት፣ ለምለሙ ሳር ላይ ጋደም ብላ በጉጉት እና በናፍቆት ስሜት… የሷም ልብ ተንጠልጥሎ ፍቅርን ትጠብቃለች…
ለመጀመሪያ ጊዜ ያየሁትን የመዝገቡ ስዕል በቃላት ለመግለጽ እየሞከርኩ እንደሆነ ተረዱልኝ።  አይኔን መንቀል ፈተና እስኪሆንብኝ ድረስ ተደነቅሁ። ግን ሌሎቹን ድንቅ ስዕሎቹንም ማየት ነበረብኝ፡፡ በየእለቱ ከምናየው ወይም ከምናውቀው ውበትና ማራኪነት ሁሉ የላቀ ውበትን በእውን ሰርቶ እያሳየ፣ እኛው ከፍ እና ላቅ አድርገን እንድናስብ የሚያደርግ ድንቅ ሰዓሊ ነው መዝገቡ፡፡ በእለት ተእለት የኑሮ ሩጫም ሆነ በቸልታ ጥቃቅን ነገሮች ላይ ስናተኩር ትልልቅና ቁልፍ የህይወት ቁም ነገሮችን መመልከት ይሳነን የለ? ነገር አለሙ ሁሉ ይደበዝዝብናል ወይም ብዥ ይልብናል፡፡ የህይወትን አልማዞችና ወርቆችን እያጠራና እያነጠረ አጉልቶ ያሳየናል - በስዕሎቹ ነፍስ እየዘራባቸው፡፡ እናም “ለካ እንዲህ አይነት ውበትም አለ” እንድንል የሚያደርግ ብርቅ ሰዓሊ ነው - መዝገቡ፡፡
በአጭሩ ከመዝገቡ የሰው ልጅ መንፈሳዊ ፍላጐቶችን የሚያሟላ፣ የህይወት ማዕድ የሚያሰናዳ ጥበበኛ ነው፡፡ ለዚህም ይመስላል፤ ስዕሎቹን የተመለከቱ በርካታ ሰዎች “አይኖችህ የተባረኩ፣ እጆችህ  የተቀደሱ፣ ሥራዎችህ የመጠቁ ናቸው” ሲሉ የሚደመጡት፡፡ የመጀመሪያው መንፈሳዊ ፍላጐት፣ በተለምዶ “አለምን የማወቅ ጉጉት” እንለዋለን፡፡ ተፈጥሮን አጥርቶና አንጥሮ ማየት ይቻላል የሚል የአእምሮ አለኝታነትን የሚያረጋግጥ መንፈስ ያላብሰናል፡፡
የመዝገቡ ተሰማ ስዕሎች ላይም የጠራ የነጠረ አለምን ነው የምናየው፡፡ የነጠረና የተመረጠ አለምን እንጅ የቅራቅንቦ ስብስብ ምስቅልቅልን አያቀርብልንም፡፡ የጠራ የጐላ አለምን ይጋብዘናል እንጂ በብዥታ የተጋረደ ሌጣና ኦና አለምን አይግተንም፡፡ ሁለተኛው መንፈሳዊ ፍላጐት፤ በለምዶ ራዕይ ወይም ፍቅር ብለን እንጠራዋለን። ወደ ከፍታ የመምጠቅ ጉጉትን የሚያገናኝ፣ እውቀትንና ስኬትን የሚያስተሳስር፣ አእምሮንና አላማን የሚያዛምድ ነው፡፡
ሦስተኛው መንፈሳዊ ፍላጐት - የላቀ ብቃትንና የላቀ ስብዕናን መቀዳጀት የምችል ሰው ነኝ የሚል የእኔነት ክብር፡፡ መዝገቡ ተሰማ አረንጔዴ ስፍራ ሲስል፤ ከተለመደው ሁሉ የላቀ ልምላሜን ያላብሰዋል፡፡ ሴቶችን ሲስል ከለግላጋ ማራኪነት የላቀ ፍቅርን የሚጓጉ፣ ከፍ ያለ ደስታን የሚናፍቁ አድርጐ ይቀርፃቸዋል፡፡ የተራራ አናት ላይ ያወጣቸዋል፡፡ ወደፊት ወደ ላይ እየተንጠራሩ ለመብረር እንዲያኮበኩቡ ያደርጋቸዋል፡፡  
እናም የመዝገቡን ስዕሎች ያየሁ ጊዜ፣ “ከዚህ የበለጠ ድንቅ ስራ ከወዴት ይመጣል” ብዬ ተደነቅሁ። በእርግጥም የበለጠ ነገር አላየሁም፡፡ ማለቴ ለጊዜው አላየሁም፡፡ መዝገቡ ተሰማ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ በ1996 ዓ.ም በአሊያንስ ኢትዮ ፍራንሲስ፣ አዳዲስ የስዕል ስራዎቹን ለእይታ ያቀረበ ጊዜም፤ ከቀድሞ ድንቅ ስራዎቹ ጋር የሚመጣጠኑ ፈጠራዎችን ለማየት ተስፋ በማድረግ ነበር የሄድኩት፡፡
ግን እንደጠበቅኩት አልሆነም፡፡ ከቀድሞ ስራዎቹ የሚበልጡና የሚልቁ ድንቅ ስዕሎችን ነው ያቀረበው፡፡
በአዳራሹ አንድ ወገን፣ የማታውን ጨለማ ለመግፈፍና ለማባረር የተፈጠረ፣ ፍም የመሰለ የንጋት ብርሃን አየሁ - በትልቅ ሸራ ላይ የተሰራ ስዕል ነው፤ የህይወት ሃያል የማለዳ ብርሃን፡፡ ከወዲያ ማዶ ደግሞ፤ የዚያኑ ያህል የአዳራሹን ግድግዳ የሚሸፍን ስዕል ይታየል - ቀኑን ተሰማርተው የዋሉና የሚያምሩ ከብቶች… ከላሚቱ አጠገብ እመር የምትል ጥጃ፣ በግርማ ሞገስ የሚራመዱ ኮርማዎችና በሬዎች … በየራሳቸው መልክና ቀለም፣ አመሻሽ ላይ እያዘገሙ እየተመለሱ ይመስላሉ፡፡ በእለት ተእለት ከምናያቸው ከብቶች ሁሉ ይበልጥ የሚማርኩ፣ በየአጋጣሚ ከምናየው የከብቶች ስምሪት ሁሉ የሚያምሩ ትዕይንቶችን ከበርካታ የመዝገቡ ተሰማ ስዕሎች ላይ እንመለከታለን፡፡
ከዚሁ አጠገብ የነበሩት ሁለት ግዙፍ ስእሎችም ድንቅ ናቸው፡፡ ከግራ በኩል የነበረው ስዕል አረንጓዴ መናፈሻ ይመስላል፡፡ እርግት ያለው ልምላሜ ፍፁም ሰላም የሰፈነበት ከመሆኑ የተነሳ፣ ምናልባት “ገነት” የሚባለው ስፍራ  እንዲህ ይሆን እንዴ? ያስብላል፡፡ ሁለት እምቦቃቅላ ጨቅላዎች ከመስኩ መሃል ምቹ መኝታ ላይ፤ ከራስጌና ከግርጌ ተጠጋግተው አንቀላፍተዋል፡፡  ሌላኛው ግዙፍ ስዕል፤ ተራራ ላይ ከሚገኝ ጨለምለም ያለ ሰፊ ዋሻ ውስጥ ቁልቁል እስከ አድማስ ጥግ በብርሃን የተጥለቀለቀ ዛፍና ቅጠሉን፣ መስክና ጐጆውን፣ ኮረብታና ሸንተረሩን ሁሉ የሚያሳይ ነው፡፡ ፎቅ ላይ ወይም ሌላ ከፍተኛ ቦታ ላይ ስትወጡና ወደታች ስትመለከቱ የሚፈጠረው ስሜት ታውቁት የለ? ይህንን የመዝገቡ ስዕል ስትመለከቱም ተመሳሳይ ስሜት ጐብኝት ያደርጋችኋል፡፡  ከስዕሉ የቅንብር ጥበብ የመነጨ ውጤት ነው፡፡
የቁልቁለት የዳገቱ፣ የኩርባ የገደሉ፣ የማሳ የመንደሩ ምስል ንጥር -ጥርት ያለ ቢሆንም አቀማመጥና ቅንብሩ የአሽከርካሪት ባህርይ አለው። ከከፍታ ቦታ ሆነን ስንመለከት የሚፈጠርብን አይነት ስሜት፡፡ መዝገቡ ተሰማ፣ በቀለም አዋቂነቱ የላቀ ድንቅ ሰዓሊ መሆኑ ባያከራክርም በቅንብር ችሎታውም ወደር የሚገኝለት አይመስልም፡፡ በዚያን ወቅት በ1996 ዓ.ም በኤግዚቢሽኑ ካቀረባቸው ስዕሎች መካከል፣ “አድባር” የሚል ርዕስ የሰጠው ስዕልም የመዝገቡን የቅንብር ችሎታ ይመሰክራል፡፡
እንደሰማይ የራቀ የተራራ ጫፍን አጉልቶ እያሳየ፣ በዚያው መጠን ከታች አረንጓዴ የእርሻ ማሳና መኖሪያ መንደሮችን አስፍቶ ያሳያል ስዕሉ፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፡፡ ከተራራው ጫፍ ወደ ጐን ገፍቶ የወጣ ቀጭን አለት ላይ አንዲት መልከ መልካም ወይዘሪት  ቆማለች - ከምድር ብዙ ኪሎ ሜትሮችን ርቃ፡፡ ዘና ብላ ነው አፋፍ ላይ የቆመችው፡፡ ውቧ እና ማራኪዋ “አድባር” የትኛውም ከፍታ ላይ መውጣት ትችላለች፡፡ የማይቻላት ነገር፤ የማትደርስበት ከፍታ የለም፡፡ የተራራ አናት አፋፍ ላይ የቆመችን ሴት አጉልቶ፤ ወደ ታች ለማሳየት ድንቅ የቅንብር ጥበብን ይጠይቃል፡፡
ሰማይ ጠቀስ የተራራ አናት ላይ ዘና ብላ የቆመችን ሴት አጉልቶ፣ በጣም ታች ታች ያለው መንደሮችና ማሳዎችንም አስፍቶ ለማሳየት፤ ልዩ የቅንብር ጥበብን ይጠይቃል - በሌላ አነጋገር የመዝገቡን አይነት የቅንብር ጥበብ መካን ያስፈልጋል፡፡  
መዝገቡ ከከፍታ ጋር ልዩ ፍቅር ያለው ይመስላል፡፡ ባለፈው ሳምንት በተከፈተው ኤግዚቢሽን ያቀረባቸው ስዕሎችም፤ “ከፍታ”ን እና “ልቀት”ን አጉልተው የሚያሳዩ ናቸው፡፡
“ላየን ኪንግ” የተሰኘውን ድንቅ ፊልም ታስታውሱት ይሆናል፡፡ የጫካው ንጉስ ታላቁ አንበሳ፤ በከፍታ ገንኖ ከሚታይ አለት ጫፍ ላይ ወጥቶ፣ በነጐድጓድ ድምጽ እያገሳ፣ ህልውናውን ለመላው አለም ሲያውጅ የሚታይበት ቦታ አለ፡፡ ያንን አይነት ስሜት የሚያሳድር ነው አንዱ የመዝገቡ ስዕል፤ “ከፍታ” የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡
“ህልመኛ” በሚል ርዕስ ያቀረበው ሌላኛው ግዙፍ ስዕልም እንዲሁ፤ “ከፍታ”ን አቅርቦ የሚያሳይ ነው፡፡ በአስገራሚ ሁኔታ የተደራረበና የተነባበረ አለት፣ በሃይቅ ዳርቻ ላይ ያንዣበበ ይመስላል፡፡ ከታች የሃይቁ ውሃ ያንፀባርቃል፡፡ ከላይ ከፍታው አናት ላይ ደግሞ፣ ልብስ ያላደረገ ልጅ ይታያል። በኤግዚቢሽኑ ከቀረቡት 15 ስዕሎች፤ በጣም ትንሿ በአንድ ሜትር  ሸራ የቀረበችው ስዕል ናት፡፡ በሳር መስክ የተከበበችና ሸብረክ ብላ የተቀመጠች ብቸኛ ግልገል! መዝገቡ የራሱን ችሎታ ለመፈተን የሰራው የሚመስለው “ላል” የተሰኘውን ስዕል ጨምሮ ስዕሎቹ በሙሉ ድንቅ የጥበብ ውጤቶች ናቸው፡፡ ነገር ግን ተለይተው ሊጠቀሱ ይገባቸዋል የምላቸውን አምስት ስዕሎች አይቻለሁ፡፡
ወደ አዳራሹ ሲገባ በስተግራ የምናገኘው የመጀመሪያው ስዕል፤ “ግለት” የተሰኘና የእሳተ ጐመራ ስፍራ የሚመስል ስዕል ነው፡፡ “እንዲህ አይነት እቶን እና ፍም ታይቶ ይታወቃል?” ያሰኛል፡፡ እውነትም “ግለት” ይሉሃል ይሄ ነው፡፡ ሌላኛው ደግሞ “ምቹ ቦታ” የሚል ርዕስ የተሰጠው ስዕል ነው፡፡
ከቅርበትና በስፋት ጐልቶ ከሚታየው ሜዳና ተራራው፣ ጋራና ሸንተረሩ ባሻገር፣ ከተራራ ጀርባ ሌላ የተራራ ሰንሰለት፤ ከዚያ ጀርባ ደግሞ ሌላ ተራራ… ለአይን እስኪያስቸግር ድረስ በተዘረጋው በዚያ ቦታ ላይ በአካል መገኘትን የሚያስመኝ ስዕል ነው፡፡
ሌሎቹ ሦስት ስዕሎች ለብቻቸው ልዩና የላቀ ደረጃ ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ ለምን ቢባል፣  “የተዘረጋ” እና “እሷና ሌሎች” በሚል ስያሜ የቀረቡት ሥራዎች፣ የስዕል ጥበብ ላይ ተጠቃሽ እመርታን የሚያስመዘግቡ ናቸው፡፡ ከቀለም፣ ከብርሃንና ከቅንብር ጥበቦች በተጨማሪ፣ አዳዲስ ጥበቦችን በመጠቀም ለምስሎቹ ልዩ ጥልቀትንና ግዝፈትን አጐናጽፏቸዋል፡፡ ሸራው ጠፍጣፋ ነው፡፡ ምስሎቹ ግን፣ ከሸራው ጀርባ ብዙ ኪሎሜትሮችን ጠልቀውና ሰፍተው የሚዘረጉ፣ ከሸራው ፊትም ተመልካችን ለመንካት የሚመዘዙ ይመስላሉ፡፡ የስዕልን “3D” ባህርይ እንዲህ አጉልቶ ያወጣ የአገራችን ሰዓሊ የለም፡፡
“ንግሥ” የተሰኘው ስዕል ደግሞ፤ የኤግዚቢሽኑ ንጉስ ነው ማለት ይቻላል፡፡ 5 ሜትር በ2 ሜትር ስፋት ላይ የቀረበውና ከ160 በላይ የሰው ገፀ ባህርያትን ገልጦ የሚያሳየው ይሄው ስዕል፣ ግርማ ሞገስን፣ አክብሮትን፣ ስነ ሥርዓትን፣ በአጠቃላይ የሰው ልጅ ለትልቅነት ወይም ለቅድስና ያለውን ጉጉት የሚያሳይ ታላቅ ሥራ ነው - እጅግ ታላቅ ሥራ፡፡   

Read 4165 times