Monday, 25 November 2013 10:51

በቀን 30ሺ ሊትር ነዳጅ ሸጠው ማደያ የተሸለሙ ኢትዮጵያዊ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ፤
Rate this item
(4 votes)

አራቱ ትልልቅ የነዳጅ ኩባንያዎች ይፎካከሩባቸው ነበር
የበርካታ ቤተ - ክርስቲያናት ሊቀ ካህን ሆነው አገልግለዋል
በ84 ዓመት እድሜያቸው ያለመነፅር በፍጥነት ያነባሉ
63ኛ ዓመት የጋብቻ በዓላቸውን በድምቀት አክብረዋል

አለቃ ገ/እግዚአብሔር ገብረየሱስ ይባላሉ፡፡ በአድዋ አውራጃ ማሪያም ሸዊት በምትባል ቦታ በ1922 ዓ.ም እንደተወለዱ ይናገራሉ፡፡ የ84 አመቱ አዛውንት በትውልድ አካባቢያቸው የቤተ - ክህነት ትምህርታቸውን ከተከታተሉ በኋላ፣ በ1943 ዓ.ም ከአቡነ ይስሃቅ ሊቀ ካህን በሚል ማዕረግ ተሰይመው ለአመታት አገልግለዋል፡፡
ዘመናዊ ትምህርታቸውን እስከ ስድስተኛ ክፍል የተማሩት አለቃ ገ/እግዚአብሔር፤ እስከ 1949 ዓ.ም በማሪያም ሸዊት ገዳምና በአባ ገሪማ ገዳም ውስጥ በሚገኙ ቤተክርስቲያናት በካህንነት ያገለገሉ ሲሆን በ1951 ወደ አዲስ አበባ ከመጡ በኋላ፤ የዘመዳቸው ድርጅት በሆነው አምቦ ጠበል ፋብሪካ፣ በራስ ሆቴል እና በብሔራዊ ባንክ ተቀጥረው ሲሰሩ ቆይተው፣ ትንሽ ሱቅ በመክፈት ነዳጅ እና የሞተር ዘይቶች መቸርቸር ይጀምራሉ፡፡  ይህንን ስራቸውን በጥረት በማሳደግ ከሞቢል፣ ከአጂፕ፣ ከሼልና ቶታል ኩባንያዎች ነዳጅ በቅናሽ በመውሰድ የለየላቸው ነዳጅ አከፋፋይ በመሆን በቀን 30ሺህ ሊትር እስከመሸጥና ከሞቢል ኩባንያ ነዳጅ ማደያ እስከ መሸለም በቅተዋል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ አዲሱ ገበያ በሚገኘው የመኖሪያ ቤታቸው ተገኝታ ስለ ንግድ ስራቸው፣ ስለ ትዳር ህይወታቸው፣ ስለ ቀድሞው እና ስለአሁኑ አጠቃላይ የህይወት ሁኔታና በመሰል ጉዳዮች ዙሪያ ከአዛውንቱ ጋር ቀጣዩን አድርጋለች፡፡


ትውልድና እድገትዎ የት ነው?
ትግራይ ውስጥ አድዋ አውራጃ፣ ማሪያም ሸዊት በሚባል ቦታ ነው ተወልጄ ያደግሁት፡፡ ወደዚህ ምድር የመጣሁት በ1922 ዓ.ም ነው፡፡
ከትውልድ ስፍራዎ እንዴት ወደ አዲስ አበባ መጡ? መቼስ ነው የመጡት?
ወደዚህ የመጣሁት በ1951 ዓ.ም ነው፡፡ አመጣጤ ገጠርና ጠባብ ከተማ ውስጥ ከመኖር ሰፊ በሆነው አዲስ አበባ ብኖር ይሻለኛል ብዬ ነው፡፡
በትውልድ አካባቢዎ የቀለም ትምህርት ቀስመው ነበር እንዴ?
በአብዛኛው በደንብ የተማርኩት የቤተ - ክህነት ትምህርት ነው፡፡ ነገር ግን ዘመናዊ ትምህርትም እስከ ስድስተኛ ክፍል ተምሬ ነበር፡፡
ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ ማን ተቀበለዎት? ዘመዶች ነበሩዎት?
የተፈሪ ሻረው እናት ዘመዴ ነበረች፤ እርሷ ናት የተቀበለችኝ፡፡
ተፈሪ ሻረው ማን ናቸው?
የአምቦ ጠበል ፋብሪካ ባለቤት ነበር ተፈሪ ሻረው፤ እናቱ የቅርብ ዘመዴ ናት፡፡
ብቻዎትን ነው ወደ አዲስ አበባ የመጡት?
ታናሽ እህቴንም ይዣት ነው የመጣሁት፡፡ ለምን ብትይ… ገና ትንሽ ሆና ሊድሯት ነበር፡፡ ልጅቱን ስጡን ጥንድ በሬ እንሰጣችኋለን እያሉ ሲነጋገሩ ሰምቼ፣ አሁን ከምታገባ በጉልበቷ ሰርታ ትበላለች ብዬ ይዣት መጣሁ፡፡ ሂሩት ገ/የሱስ ትባለለች፡፡ ያን ጊዜ አውቶቡስ አምጥቶ ጊዮርጊስ አካባቢ ጣለን፡፡ አሜሪካ ጊቢ አንድ እህት ነበረችኝ፡፡ መጀመሪያ እሷ ጋር አረፍኩ፡፡ ከዚያ በኋላ አድዋ ማሪያም ሸዊት የተወለዱ የአገር ሰዎች ነበሩ፡፡ “አለቃ መጥተዋል ተቀበሏቸው” ብለው መኝታው፣ ጮማው ተይው… ጥሩ አቀባበል ተደረገልኝ እልሻለሁ፤ እነዚህ ሰዎች ለመሬት ሙግት ከአዲስ አበባ ወደ አድዋ ሲመጡ እኔም ጥሩ አቀባበልና መስተንግዶ አድርጌላቸው ነበር፡፡ የተፈሪ ሻረው እናት ወ/ሮ አዛለችም ጥሩ አቀባበል አድርጋልኛለች፡፡
እንግድነትዎን ጨርሰው ምን ስራ ላይ ተሰማሩ?
በወቅቱ የአምቦ ጠበል ባለቤት አቶ ተፈሪ ወደ ውጭ ይሄድ ነበር እና ሌላ ስምንት ሰው ጨምሬ አምቦ በመሄድ እዛው ፋብሪካው ውስጥ ካቦ ሆኜ መስራት ጀመርኩ፡፡
በስንት ብር ደሞዝ ተቀጠሩ?
በሳምንት ስምንት ብር፣ በወር 40 ብር አካባቢ ነው፡፡ ያኔ ብዙ ብር ነው ለእኔ፡፡ እዛ እስከ 1954 ዓ.ም ከሰራሁ በኋላ ጥየው መጣሁ፡፡
አዲስ አበባ ከመምጣትዎ በፊት ትዳርና ልጆች እንደነበሩዎት ሰምቻለሁ፡፡ እስኪ ይንገሩኝ …
በ1942 ነው የአሁኗን ባለቤቴን ሙሉ ግደይን ያገባሁት፡፡ እዚህ ከመምጣቴ በፊት ሁለት ልጆቼን እዛው ማሪያም ሸዊት ነው የወለድኩት፡፡ እዚህ በመጣሁ በሁለት አመቴ ሚስቴንና ልጆቼን አባቴ ይዘውልኝ መጡ፡፡ አምቦ ሆኜ ተቀበልኳት፡፡ ከዚያ… በኋላ ስድስት ልጆች ጨመርን፡፡ አንዱ ሲሞት ሰባቱ አሉ፡፡ የልጅ ልጅም፣ የልጅ ልጅ ልጅም አሳይተውኛል፤ ቅድመ አያት ሆኛለሁ፡፡
ስንት የልጅ ልጆችና የልጅ ልጅ ልጆች አሉዎት?
ሀያ የልጅ ልጆች፣ ሁለት የልጅ ልጅ ልጆች አሉኝ፡፡
ከአምቦ ወደ አዲስ አበባ ከመጡ በኋላ ምን አይነት ስራ ጀመሩ?
ከአምቦ እንደመጣሁ ራስ ሆቴል ውስጥ ተቀጠርኩኝ፡፡ መጀመሪያ የሰራሁት አራት ኪሎ ዩኒቨርስቲ ውስጥ በካፍቴሪያ ውስጥ ነው፡፡ በወቅቱ ዩኒቨርስቲው በታህሳስ ግርግር ተዘግቶ ነበር፡፡ ራስ ሆቴል የዩኒቨርስቲውን ካፍቴሪያ ኮንትራት ይዞ ይሰራበት ስለነበር እዛ መስራት ጀመርኩኝ፡፡ ከታህሳስ ግርግር በኋላ ጃንሆይ ቤተ-መንግስታቸውን ለዩኒቨርስቲነት ሰጥቻለሁ ብለው ቃል ሲገቡ (የአሁኑን አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ማለት ነው) ወደ ዩኒቨርስቲው ተዛወርኩና ሰራሁ። ይህ በ1956 ነው። በ1957 ደግሞ ብሄራዊ ባንክ ተቀጠርኩ፡፡ ባንክ እየሰራሁ ነው በበርሜል ነዳጅ መሸጥ የጀመርኩት፡፡
ነዳጅ መሸጡን እንዴት አሰቡት?
እንዴ! ስራ መፍጠር አለብኛ ምን ማለትሽ ነው? (ኮስተር አሉ) ተቀጥሮ በመንግስት ቤት ብቻ መስራት እኮ ፅድቅ አይደለም! ጠዋት ወደ ባንክ ከመግባቴ በፊት ነዳጅ የሚወስድ ነጋዴ ስፈላልግ አረፍዳለሁ፡፡ እንዲህ እንዲህ እያልኩ ከአራቱም ኩባንያዎች ማለትም ከቶታል፣ ከአጂፕ፣ ከሼልና ከሞቢል ነዳጅ በቅናሽ እየወሰድኩ እሸጥ ጀመር፡፡
እንዴት ከአራቱም እየወሰዱ ያከፋፍላሉ? ኩባንያዎቹ ተፎካካሪዎች አይደሉም እንዴ? አሁን ጊዮርጊስ ቢራ የሚያከፋፍሉ ቢሆን ሌሎች ቢራዎችን ዞር ብለው እንዲያዩ አይፈቀድም?
እኔ በወቅቱ ያለ ምንም አድልዎ የአራቱንም ኩባንያዎች በበርሜል እየወሰድኩ በየክፍለ ሀገሩ አከፋፍል ነበር፡፡ እርግጥ የእኛን በደንብ ውሰድ፣ የእኛን በብዛት ሽጥ እያሉ ይጫረቱ ነበር፡፡ የሆነ ሆኖ እኔን ለማበረታታት ነዳጁ ላይ ቅናሽ አድርገውልኝ ነበር፡፡ እንዲህ እንዲህ እያልኩ በስራው ገፋሁበት፡፡
ሞቢል የካ አካባቢ ማደያ ሸልሞዎት ነበር፡፡ እንዴት ሊሸልምዎት እንደቻለ ቢነግሩኝ?
ሞቢል የሸለመኝ አንደኛ በአንድ ቀን 150 በርሜል (30 ሺህ ሊትር) ነዳጅ በመሸጤ ነው፡፡ ሁለትም እነ አጂፕ ሼልና ቶታል ጀነራል ማናጀሮቹ እየጠሩኝ ከእኛ ግዛ፣ ከእኛ ጋ ስራ ማለት ሲያበዙ፣ ቀድሞ እኔን ለመያዝ ነው ሞቢል ማደያውን የሸለመኝ፡፡ ረጅም ጊዜ ሰርቼበታለሁ፡፡
አሁንም ማደያው እየሰራ ነው ወይስ …?
ለራሳቸው መልሼላቸዋለሁ፡፡
በምን ምክንያት?
እዛው ማደያው ላይ ስሰራ የመኪና አደጋ ደርሶብኝ እግሬ ተጐዳ (አደጋው ያደረሰውን ረጅም ጠባሳ ቱታቸውን ሰብስበው አሳዩኝ፤ የከፋ አደጋ እንደነበር ይጠቁማል) በአደጋው ለአንድ አመት ያህል ምኒሊክ ሆስፒታል ተኛሁ፡፡ (ከ1963-64 ዓ.ም) መሆኑ ነው፡፡ በወቅቱ ወንድሜና ዘመዶቼ እንዲሰሩ ሃላፊነት ሰጥቻቸው ነበረ፡፡ ሆኖም በአግባቡ ሊሰሩ ስላልቻሉ ለኩባንያው መለስኩለት። ነገር ግን መጀመሪያ የከፈትኩት የሞተር ዘይት መቸርቸሪያ ሱቅ ስለነበረ እሱ ስራውን ቀጠለ። የሞተር ዘይት ብቻ ሳይሆን በበርሜልም ነዳጅ አከፋፍል ነበር፡፡ ማደያውን ከመለስኩ በኋላ ማለት ነው፡፡ መጀመሪያም የጀመርኩት በሱቅ ነበር፡፡
ነዳጅ በወቅቱ በሊትር ስንት ነበረ?
ይታይሽ… ከጅቡቲ የታሸገው በርሜል ነዳጅ በ15 ብር ነው የሚመጣልን፡፡ በ15 ብር ተረክበን ነው የምንሸጠው (በጣም እየሳቁ) በሊትር 15 ሳንቲም ይሁን አስር ሳንቲም… ብቻ ከዚህ አይበልጥም ነበር፡፡
እርስዎ ነዳጅ መሸጥ ሲያቆሙ ነዳጅ በሊትር ስንት ነበር? እስኪ ያስታውሱ?
ውይ እሱን አላስታውስም… ብቻ እኔ ሳቆም በሊትር አንድ ብር የገባ አይመስለኝም፡፡
እስኪ ስለ ትዳርዎ እናውራ፡፡ አሁን ወ/ሮ ሙሉ ግዴይ የት አሉ? እድሜያቸውስ ስንት ሆነ?
አለች ጓዳ ውስጥ ስራ ላይ ናት፤ እድሜዋ ከእኔ በአምስት አመት ያንሳል፡፡ ከተጋበን 63 አመታችን ነው፡፡ በቅርቡ 63ኛ ዓመት የጋብቻ በዓላችንን ልጆቻችን ድል ባለ ድግስ አክብረውልናል፡፡ ተዓምር የሆነ ድግስ ነው፡፡ ልጄ ቢኖር በፊልም የተቀዳውን ያሳይሽ ነበር፡፡
ነዳጅና የሞተር ዘይት ያከፋፍሉበት የነበረው ሱቅ አሁን ምን ሆነ?
አለ ይሰራል፡፡ ነገር ግን ነዳጅ ሳይሆን የህትመት ወረቀት አስመጪ ድርጅት ነው የሆነው፡፡ ልጄ ዘካሪያስ ውክልና ወስዶ እየሰራበት ነው፤ ያው ከንግዱ አልወጣሁም፡፡
በትውልድ አካባቢዎ ለካህንነት ለተሾሙበት ማሪያም ሸዊት እርዳታ እንዳደረጉም ሰምቻለሁ፡፡ እስኪ ይንገሩኝ?
ለማሪያም ሸዊት መብራት አብርቼለታለሁ፡፡
አብርቼላታለሁ ሲሉ ምን ማለትዎ ነው?
መብራት ከመብራት ሃይል ጠልፌ በገንዘቤ አስገብቼ፣ የመብራት ተጠቃሚ አድርጌያለሁ። ከቤተ ክርስቲያኑ እየወሰደ የአካባቢውም ሰው መብራት ይጠቀማል፡፡ በተጨማሪም ለቤተ - ክርስቲያኗ አራት ወፍጮ ተክዬ በገቢው እየተጠቀመች ትገኛለች፡፡ ይህን ያደረግሁበት ከደርግ ውድቀት በኋላ ነው፡፡
ለመጨረሻ ጊዜ አድዋ የሄዱት መቼ ነው?
እስከ ቅርብ ጊዜ እሄድ ነበር፡፡ እስከ 2000 ዓ.ም። ከዚያ በኋላ አልሄድኩም፤ ትንሽ እያመመኝ ነው፤ እዛ መኖሪያ ትልቅ ቤት ሰርቻለሁ፡፡ ልጄ ዘካሪያስም ቤት አለው፤ ማሪያም ሸዊት ከአድዋ ከተማ 10 ኪሎ ሜትር ነው የሚርቀው፡፡ ይሄ ገዳም ይገርምሻል በ1945 ተቃጥሎ ነበር፤ እንደገና ነው የተሰራው። ደጃች ሀጐስ ተሰማ የተባሉ ዘመዳችን ሄደው ፕላን አንስተው ከመጡ በኋላ፣ ለጃንሆይ ነግረው ነው መልሶ የተሰራው፡፡ በዚህ የቤተክርስቲያን ስራ ውስጥ አባቴም ትልቅ አስተዋፅኦ ነበራቸው፡፡ እስካሁንም ለቤተክርስቲያኗ ፍቅር አለኝ፡፡ አሁንም ለህዳር ማሪያም ለአመቱ ቢኒያምን (ልጃቸው ነው) ካባና ፅናፅል ግዛ ብዬዋለሁ፡፡ አሁን ድምፅ ማጉያም ያስፈልጋል፤ እሱንም ልጄን ግዛ ብዬዋለሁ፡፡
አሁንስ ወደ አድዋ የመሄድ ፍላጐት አለዎት?
በደንብ ፍላጐት አለኝ፤ ትንሽ ይሻለኝና እሄዳለሁ። የፈጣሪ ፈቃድ ይሁን… ትንሽ እግሬ ያስቸግረኛል፡፡
አባባ አዲስ አበባ ከመጡ በኋላ በትምህርትዎ እንዴት አልገፋም?
ከዚያ በኋላማ ልጆች መጡ፤ እነሱን ወደማስተማሩ ነው የሄድኩት፡፡ ምክንያቱም ከአድዋ ባለቤቴ ሁለት ልጆቼን ይዛ መጣች፡፡ እዚህም ተጨማሪ ልጆች አፈራን፡፡ ከዚያ “ትምህርት ለምርት” በሚል መርሆ ለልጆች ቅድሚያ ሰጥተን ማስተማርና ማሳደግ ስንጀምር የእኔን ትምህርት ዘነጋሁት፡፡
ባንክ ቤት የሰሩት በስድስተኛ ክፍል የትምህርት ደረጃዎት ነው?
አዎ በዛው ነው፤ ግን በደንብ እውቀት ነበረኝ። በወቅቱ ትምህርቱም በደንብ ነበር የሚሰጠው፡፡
አሁን ነዳጅ በሊትር ስንት እንደገባ ያውቃሉ?
ውይ አሁንማ በጣም በጣም ውድ ሆኗል። መቼም ጊዜ ሲለወጥ ሁሉም ይለወጣልና ምን ይደረግ፡፡
እስቲ የቀድሞውንና የአሁኑን ትውልድ ያነፃጽሩልኝ?
አሁን ጊዜው ወርቅ ነው፡፡ ወጣቱም ጐበዝ ሆኗል፡፡ ቴክኖሎጂው ሁሉ ድካም እየቀነሰ ነው፡፡ አሁን ድሃ ሃብታም የለም፤ ሁሉም መማር ይችላል። ዋናው የራስ ጥረት ነው እንጂ ለመስራትም ለመማርም እድሉ አለ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ቀጣፊ ቦታ የለውም፡፡
እንደሚባለው ቀጣፊ፣ ሙሰኛ፣ አጭበርባሪው የበዛው አሁን ነው፡፡ የድሮ ሰዎች ፈሪሃ እግዚአብሔር ያላቸው ናቸው ይባላል፡፡ እውነት ነው?
እርግጥ ሙሰኛ ሌባ ሙሉ በሙሉ የለም ማለት አይደለም፡፡ ይሄው እየተጋለጡ ወህኒ እየወረዱ ነው። ሌባ ሁሌ አይቀናውም፤ የሚሰርቅ ሁሉ እየተጋለጠ ነው፡፡ አሁን ጊዜው ትውልዱ በእኔ እምነት ደስ የሚልና የሰለጠነ፣ የሚሰራና የሚማር ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን ወጣቶች አገራቸውን መውደድ አለባቸው፡፡ በአገራቸው መስራት አለባቸው፣ ስደት መጥፎ ነው፤ ከስደት መቆጠብ አለባቸው፡፡ አሁን እዛ የማይረባ አረብ አገር ሄደው ለሞትና ለውርደት ነው የተዳረጉት፡፡
ግን እኮ ኢትዮጵያውያን የሚሰደዱት ወደው ሳይሆን ስራ በማጣት ነው እየተባለ ነው?
ነገርኩሽ! እኔ እኮ ስራ ፈጠርኩ፤ ባንክ ቤት እየሰራሁ፣ ጠዋት 12 ሰዓት ወጥቼ በርሜል ይዘው ነዳጅ ለመውሰድ የሚመጡ ነጋዴዎች የሚያድሩበትን ቦታ በጐን እፈልግ ነበር፡፡ ከባንክ የማገኘው ደሞዜ ይበቃኛል ብዬ እጄን አጣጥፌ አልቀመጥኩም። ምንም ቢሆን አገር ይሻላል፡፡ ስራ መፍጠር፣ የተገኘውን መስራት የግድ ነው፡፡ እሰው አገር ሄዶ ከመሞትና ከመዋረድ ራስን መጠበቅ አስፈላጊ ነው። ዋናው ስራ ሳይንቁ ሰርቶ መለወጥ ነው፡፡ ፍላጐቱ ካለ ስራ አይጠፋም፡፡ ስራ አጣሁ ብሎ ራስን ወደ ሞት አገር ማሰደድ እብደት ነው እላለሁ፡፡
አዲስ አበባ ከመጡ በኋላ መንፈሳዊ ህይወትዎ ምን ይመስላል?
እዚህም ራጉኤል ቤተ ክርስቲያን ነበርኩ፡፡ ቤተ ክርስቲያኑ መፅሐፍ ቅዱስ ሁሉ ሸልሞኛል፤ ከዚያ አልጠፋም ነበር፡፡ ያው እድገቴም ቤተ - ክህነት ስለሆነ ቤተክርስቲያን እወዳለሁ፡፡ መንፈሳዊ ህይወቴ ጥብቅ ነው፡፡ የቤተ - ክርስቲያን በርካታ መጽሐፍት አሉኝ። ይሄ የምታይው ዳዊት ነው (ወደ የቤታቸው ስንገባ ይደግሙት የነበረውን ቀይ ሽፋን ያለው መዝሙረ ዳዊት እያሳዩኝ) ስንት መጽሐፍ አለኝ መሰለሽ
አሁን እድሜዎት 84 ዓመት ደርሷል፡፡ መዝሙረ ዳዊት ሲያነቡ ያገኘሁዎት ያለመነጽር ነው፡፡ አይንዎት እንዴት ነው?
ኦ…ኦ…አይኔ ግሩም ነው፤ በደንብ አያለሁ፣ በደንብ አነባለሁ፤ ጆሮዬ በደንብ ይሰማል፡፡ ምንም ችግር የለብኝም፡፡
አይኔ መነጽር አጥልቆ አያውቅም። ወደፊትም አልፈልግም፡፡ እስቲ ላንብብልሽ፡፡ (ግዕዙ ባይገባኝም እርሳቸው ግን በፍጥነት አንበለበሉት)
አሁን ኑሮ እንዴት ነው? ልጆችዎት በደንብ ይንከባከቡዎታል?
በጣም በጣም ልጆቼ ይወዱኛል፡፡ ወልደሽ ልጅ ሲባረክልሽ ጥሩ ነው፡፡ ልጆቼ በደንብ ይዘውኛል። እኔ እንኳን አድዋ እቀመጣለሁ ብዬ ነበር፤ ግን እግዚአብሔር ፈቅዶ እዚሁ እየፀለይኩ ነው፡፡ ሸዋ እንደሆነ ብሩክ አገር ነው እኔም ባለቤቴ ሙሉ ግደይም ተወደን ተከብረን በደንብ እየኖርን ነው፡፡ አነባለሁ እፀልያለሁ፡፡ ይገርምሻል… ብራና መጽሐፍ ሁሉ አለኝ… ላሳይሽ (ከዘራቸውን ድጋፍ አድርገው ከሳሎን ወጥተው በርካታ መጽሐፍ ይዘው መጡ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ብራና መጽሐፍ ማየቴና መንካቴ ነው)
ከየት አመጡት? ይህን አይነት ብራና መጽሐፍ አሁን በግለሰቦች እጅ አይገኝም ብዬ ነው?
ልክ ነሽ አሁን አሁን እንኳን በግለሰብ እጅ በቤተ - ክህነትና በገዳማት ብዙ ያለ አይመስለኝም። ዱሮ ጠጅ ለመጠጣት፣ ጮማ ለመቁረጥ ገዳም ሰፈር እንመጣ ነበር፡፡ ታዲያ ያኔ አሁን ሴትዮዋ ሞተዋል፡፡ ባላቸው ዳኛ ነበሩ፡፡ “ይህን መጽሐፍ ቱሪስት ከሚወስደው እርሶ ይግዙት ቅርስ ነው” ብለው በ15 ብር ሸጡልኝ። ይሄው ቅርስ ሆኖ እኔም አንብቤው ተቀምጧል፡፡ ሌላም በርካታ መጽሐፍት አሉኝ፡፡ (የብራና መጽሐፉን አሰራርና ከምን እንደተሰራ እያገላበጡ አሳዩኝ፤ ከመጽሐፉ አንድ ምዕራፍ ያህል በፍጥነት አነበቡልኝ)
አሁን ፎቶ ላነሳዎት ነው ይዘጋጁ…
እንደዚህ የቤት ልብስ ለብሼማ አይሆንም። ባይሆን ትንሽ ታገሺኝ፤ ከወገቤ በላይ ሌላ ልብስ ልልበስ፡፡ ጋዜጣሽን እንዳላበለሻብሽ (አሁንም በከዘራቸው ድጋፍ ወደ መኝታ ቤት ገብተው ሽሮ መልክ ያለው ንፁህ ሸሚዝና ግራጫ ቀለም ያለው ኮት ደርበው ተመለሱ) አሁን እንግዲህ እንደፈለግሽ አንሺኝ፡፡
አበባ ገ/እግዚአብሔር፤ በጣም እግዚአብሔር ይስጥልኝ፡፡ ስለ ትብብርዎ አመሰግናለሁ…
እኔ ላመስግን እንጂ… እኔን ፈልገሽ ቁም ነገር ለመስማት የመጣሽው አንቺ ተባረኪ የኔ ልጅ፤ አመሰናግለሁ፡፡

Read 3029 times