Saturday, 09 November 2013 09:59

በመኪና የተገጨ ያለህክምና በፖሊስ ጣቢያ መሞቱን ቤተሰቦቹ ገለፁ

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(5 votes)

      ፖሊስ ተጐጂው ወደ ጣቢያ ሲመጣም ህይወቱ አልፎ እንደነበር ተናግሯል “በወቅቱ የመኪና ችግር ስለነበረብን ሟችን ወደ ሆስፒታል መውሰድ አልቻልንም” - መርማሪ ፖሊስ

         በኦሮሚያ ክልል በሰበታ ከተማ አስተዳደር ቀበሌ 03 ወለቴ ቴሌ ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ ባለፈው እሁድ ምሽት የመኪና ግጭት አደጋ የደረሰበት ወጣት የህክምና እርዳታ ሳያገኝ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ተወስዶ በጣቢያው ውስጥ ህይወቱ ማለፉን ቤተሰቦቹ ገለፁ። ፖሊስ ተጐጂው ወደ ፖሊስ ጣቢያ ሲመጣም ህይወቱ አልፎ ነበር ብሏል፡፡ በእለቱ ዳማስ የተባለች መኪና እና አይሱዙ የጭነት መኪና ተጋጭተው በደረሰው አደጋ የዳማሱ አሽከርካሪ ወጣት ግርማ ያደሳ ህይወቱ አልፏል፡፡ ሟች አደጋው ከደረሰበት ሥፍራ በቀጥታ ወደ ሆስፒታል መወሰድ ሲገባው ወደ ፖሊስ ጣቢያ እንዲሄድ በመደረጉ፣ ደሙ ፈሶ በማለቁ ህይወቱ እንዳለፈ ቤተሰቦቹ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡

ወጣቱ በዕለቱ የሽምግልና ጉዳይ አለብኝ ብሎ ከቤት የወጣው የምሣ ሰዓት ከመድረሱ በፊት እንደነበር የገለፀችው እህቱ ወ/ሪት ሣራ (እታለም) ያደሣ፤ ወንድሟ እስከ ምሽት ድረስ ወደቤቱ ባለመመለሱ ሃሳብ ገብቷቸው በሞባይል ስልኩ ላይ ደጋግመው ቢደውሉም ምላሽ አለማግኘታቸውን ተናግራለች፡፡ ሁኔታው ያልተለመደ በመሆኑ እጅግ ያሳሰባቸው የሟች ቤተሰቦች፤ ይገኝበታል ወዳሉት ቦታ ሁሉ እየደዋወሉ ቢሞክሩም እንዳልተሳካላቸው ገልፀዋል፡፡ ንጋት ላይ ሟች አደጋ ደርሶበት ምኒሊክ ሆስፒታል መወሰዱ ተነግሯቸው ወደ ሆስፒታሉ ቢሄዱም ለሰዓታት ሊያገኙት አለመቻላቸውንና ተስፋ ቆርጠው ባሉበት ሁኔታ የሟቹ አስከሬን ከፖሊስ ጣቢያ ሲመጣ እዛው ሆስፒታሉ ውስጥ ሆነው ማየታቸውን ተናግረዋል፡፡ በወቅቱ አደጋው በደረሰበት ቦታ ላይ ከነበሩ የዓይን እማኞች ያገኘነው መረጃ ነው በማለት የሟች ቤተሰቦች ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፤ ሟች ከአደጋው ሥፍራ ተነስቶ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ሲወሰድ ህይወቱ አላለፈችም ነበር፡፡

በመጀመሪያ የህክምና እርዳታ የሚፈሰውን ደም ለማቆም ጥረት ቢደረግ ኖሮ ከሞት ለመትረፍ ይችል እንደነበርም ቤተሰቦቹ ተናግረዋል፡፡ አደጋውን ያደረሰው አይሱዙ መኪና ጉዳዩ በምርመራ ሳይጣራ ከቦታው ላይ እንዲነሣና የያዘውን ጭነት እንዲያራግፍ መደረጉም አግባብ አይደለም ሲሉ የሟች ቤተሰቦች ተቃውመዋል፡፡ በሰበታ ከተማ አስተዳደር ክፍለከተማ 3 ፖሊስ ጣቢያ፤ በጉዳዩ ላይ ምርመራ ሲያካሂድ የነበረ ቢሆንም የሟች ቤተሰቦች ምርመራው ወደ ሰበታ ከተማ አስተዳደር እንዲዛወርላቸው ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት ምርመራው ወደዚያው መዛወሩ ታውቋል፡፡ ምርመራውን የያዙት ኢንስፔክተር ደበሬ ሞቲን ስለጉዳዩ ጠይቀናቸው፤ አደጋው በደረሰበት ሥፍራና ጊዜ እንዳልነበሩ ገልፀው፤ በሥፍራው ከነበሩ አባላቶች እንደተረዱት ግን ሟች ወደ ፖሊስ ጣቢያው ሲመጣም ህይወቱ አልፎ ነበር ብለዋል። አደጋ የደረሰበት ሰው በህይወት ኖረም አልኖረም ወደ ሆስፒታል መሄድ ሲገባው እንዴት ወደ ፖሊስ ጣቢያ ሊወሰድ ቻለ? በሚል ላቀረብንላቸው ጥያቄም፤ በወቅቱ የመኪና ችግር ስለነበረብን ሟችን ወደ ሆስፒታል መውሰድ አልቻልንም ብለዋል፡፡

የአይሱዙው አሽከርካሪና ረዳቱ አደጋው እንደደረሰ እጃቸውን ሰጥተው በፖሊስ ቁጥጥር ሥር እንደሚገኙ የገለፁት ኢንስፔክተሩ፤ ምርመራው ቀጣይ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን እንዲሰጡን የጠየቅናቸው የመድን ፈንድ አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ይሥሃቅ አበራ እንደገለፁልን ከ 3 አመታት በፊት ፀድቆ ተግባራዊ መሆን በጀመረው የ3ኛ ወገን መድን ፈንድ አዋጅ መሰረት ማንኛውም የመኪና አደጋ የደረሰበት ሰው በተቻለ ፍጥነት ወደ ሕክምና ተቋም በመሄድ ሕክምና ማግኘት እንደሚገባው ገልጸው ይኸንኑ ማድረግ የሚያስችልና በሥፍራው በተገኘው የትራፊክ ፖሊስ ተሞልቶ ከተጎጂው ጋር የሚላክ ቅፅ በቢሮው ተዘጋጅቶ ወደሚመለከታቸው አካላት መተላለፉን ተናግረዋል›› አደጋ የደረሰበት ሰው በሕይወት ይኑርም አይኑርም መሔድ የሚኖርበት ወደ ጤና ተቋማት እንጂ ወደ ፖሊስ ጣቢያ አይደለም ያሉት አቶ ይስሐቅ ይህ ከሕጋዊው አሰራር ውጪ ነው ብለዋል።

Read 2826 times