Saturday, 02 November 2013 11:51

ፍልስፍና ስታፅናና!

Written by  ደረጀ ኅብስቱ - derejehibistu@gmail.com
Rate this item
(1 Vote)

            ቦያቴየስ /Boethius/ የተባለው የሮማ ፈላስፋ ከ470-524 አካባቢ እንደኖረ ይገመታል። በፍልስፍናው ዓለም በጣም ከሚጠቀሱለት ሥራዎቹ ውስጥ “Consolation of Philosophy” (መጽናኛ ፍልስፍና እንደ ማለት) የተሰኘው በእስር ቤት ውስጥ ሆኖ የፃፈው ድርሳን ይገኝበታል፡፡ ንግስት ኤልሳቤጥ ቀዳማዊትን የሚያካክሉ ሰዎች በሥራው ተመስጠው ወደ እንግሊዝኛ እስከ መተርጎም ደርሰዋል፡፡ መቼም ጠንካራና አቋሙን በፅናት የሚያስጠብቅ ሰው ሁሌም መገኛው፤ በአምባገነኖች እስር ቤት ውስጥ ነውና ቦያቴስየም በዘመኑ ንጉስ መፈንቅለ መንግስት ተጠርጥሮና ብዙ የሃሰት ማስረጃዎች ተፈልፍለው ዘብጥያ ወረደ፡፡ በዛሬው ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትር “Master of offices” እንደምንለው ያለ ትልቅ ስልጣን በሮማ ምድር እንዳልነበረው ሁሉ፤ ሞት ተፈርዶበት እስር ቤት ተወረወረ፡፡
ይኼኔ ፍልስፍና ልታጽናናው ዘርፋፋ ቀሚሷን እየጎተተች እስር ቤት ትመጣለች፤ ከምድር ወገብ ሰማይ የተዘረጋውን መሰላል ይዛ፡፡ ይሄኔ እሱም በእርጋታ ወደ ላይ ሽቅብ ያርጋል፡፡ ፍልስፍና በጨለማ ውስጥ ትነግሳለች፡፡ ጭንቅ፣ መከራ፣ ግራ መጋባት፣ መፋለስና ምስቅልቅል ወዘተ ሲከሰት ወይዘሮ ፍልስፍና ከተፍ ትላለች፡፡ ለቦያቴየስም በእስር ቤት ከራሱ ጋር በሚጣላበት በሌሎችም በተኮነነበት ሥፍራ ከተፍ አለችለት፡፡ ያውም መሰላል ይዛ፤ የሐሳቡና የተግባሩ መታረቂያ ምልክት እንዲሆነው፡፡ የመሰላሉ ቋሚ፣ ሐልዮትን ይወክላል፡፡ አግዳሚው ደግሞ ተግባርን፡፡ የጥበብ/እውነት አፍቃሪው ፍቅሩን በጽናትና በሕይወት ተርጉሞ እንዲገልጽላት ስታመላክተው መሰላል ይዛለት መጣች፡፡ የኛም አባቶች እኮ “… በዚያም እለት እመቤታችን ትመጣለች፡፡ የብርሃን ምንጣፍ ይነጠፋል፤ የብርሃን ድንኳን ይዘረጋል፤ የብርሃን ዙፋን ይዘጋጃል፡፡ አመስግነኝ ወዳጄ ኤፍሬም ትለዋለች…” ይሉናል፡፡ ከዚያማ የብርሃን ዓለም እየጐበኙ፣ በብርሃን ሰረገላ ተጭነው፣ የብርሃን መንገድ መጓዝ ነዋ፡፡
ምንም እንኳን ክፉዎች በስልጣን ላይ ቢሆኑም፤ እራሱን በሚወቅስበትም ሰዓት ፍልስፍናዊ ማሳመኛዎችን እያነሳሳ “ሁሉም ነገር ለበጎ ነው” ይል ነበር፤ እስር ቤት ሆኖ፡፡ ስለ ምን ግን የዋሃን በጅምላ ፍትህ አልበኝነት ይጎዳሉ? እነ እከሌ፣ እነ እከሊት ስለምን በማይረቡ ከዳተኛ ጓደኞቻቸው ክስ ምክንያት በእስር ይከረቸማሉ? ወይዘሮ ፍልስፍና ትመልሳለች፤ የረሳውን ነገር እያስታወሰችው “ማወቅ ያለብህ ነገር ዝና፤ ሥልጣንና ሃብት ለመልካም ነገር መጠቀሚያ እስካላደረግሃቸው ድረስ ለጥበብ ሕይወትህ ትርኪምርኪና ትርፍ ነገሮች ናቸው፡፡” ቦያቴየስ ፈላስፋ ነውና በቀላሉ ይመሰጣል፤ እራሱንም ያጽናናል፡፡ ገንዘብን ስለ ገንዘብነቱ ሳይሆን በገንዘብ ስለምተገብራቸው መልካም ጉዳዮች ስል ብቻ ነው መውደድ ያለብኝ፤ ዝናንም ዝነኛ ለመሆን ብቻ ሳይሆን ዝነኛ ብሆን ምን መልካም ነገር እሰራበታለሁ የሚለውን ከመለስኩ ነው ዝናን መውደድ ያለብኝ፡፡ አቶ ሥልጣንንም እንዲሁ፡፡ በሥልጣኔ ምን በጎ ስራ ሠራሁ የሚለው ቁልፍ ጉዳይ ነው፤ ለወይዘሮ ፍልስፍና፡፡ ያለበለዚያ ሁሉም ከንቱ የከንቱ ከንቱ ነው፡፡ ቢወፍሩም የምስጥ ቀለብ ለመሆን ነው፡፡ ሌላ ትርፍ የለውም፤ ራዕይም ከምስጥ አያድንም፡፡
ቦያቴየስና ወይዘሮ ፍልስፍና ውይይታቸውን ቀጥለዋል፡፡ ሁሉም ነገር ደረጀ በደረጃ ነው የሚከወነው፤ አንድ ሐኪም የሚያውቀውን መድሃኒት በሙሉ በአንድ ጊዜ ለታካሚው እንደማያዝ ሁሉ ፍልስፍናም በደረጃ ነው፡፡ ይህ ስቃይ የበዛበት የሥጋ ዓለም ለነፍሳችን መከራን እንጅ ሌላ ነገር አያለብሳትም፡፡ ዘላለማዊት ነፍሳችን ሰላም የምታገኘው በወይዘሮ ፍልስፍና መጽናኛ ነው፡፡ መከራ ሲበዛ አዕምሮ በሙሉ አቅሙ ለመስራት ይቸገራልና ደረጃ በደረጃ መንፈሳችንን ማጽዳት ያስፈልገናል፡፡ የማይቀል ነገር የለም፤ ሁሉም ይቀየራል፤ የአጋንንት ሴራም ቢሆን፡፡ የኛም አባቶች እኮ በመጽሐፎቻቸው በከይሲ ምክር የምድር ግዞተኛ የሆኑትን አዳምንና ሔዋንን ዲያብሎስ የጨለማ መጋረጃ ጋርዶ፣ ሥቃይ አጽንቶባቸው ሳለ ሥቃዩን እንዳቀልላችሁ “እኛ አዳምና ሔዋን የዲያብሎስ አገልጋዮች ነን የሚል ደብዳቤ ጽፋችሁ ስጡኝ” ብሏቸው ነበር፤ በመሲሁ ግን የእዳ ደብዳቤያቸው ተቀደደላቸው ይሉናል፡፡ በንፋስ አውታር በእሳት ዛንዛር አስሮ የሚያስለፈልፈውን ልጁን አንድዬ ልኮላቸው፡፡ ቦያቴየስና ፍልስፍናም ይሄው ነው ግንኙነታቸው፤ ከመከራው፣ ከስቃዩ ፍልስፍና እያጽናናች ወደ መልካም መንፈስ ትመልሰዋለች፡፡
ዛሬም የእስር ቤት ድንበሩ ሰፍቶ ነው የተቸገርነው፤ አማራጭ ሐሳብ የሚያቀርቡ ሰዎች መንፈሳቸው ቀጭጯል፣ አንደበታቸው ይንተባተባል፡፡ የክስ ወሬ፣ የእስር ወሬ በብዙሃን መገናኛው በብዛት ይወራል፡፡ ከዚህ ጨለምተኝነት ወደ ብርሃናዊው መንፈስ የምታሳርገን ወይዘሮ ፍልስፍና ታስፈልገናለች፡፡ መቀየር የምንችለው ሁኔታ ሁሉ ጨለምተኝነት እንዳያመጣብን አቅማችንን አሟጥጠን መሞከር፤ ከአቅም በላይ የሆኑ ነገሮችን ግን ድብታ ውስጥ እንዳይከትቱን እንደ መደበኛ ጉዳዮች መቀበል ወሳኝ እርምጃ ነው ይለናል ቦያቴየስ፡፡ ከመጻፍ፣ ከመመራመር፣ ከመፈላሰፍ የሚከለክለው ነገር እስኪመጣ ድረስ፡፡ የሰው ልጆች ድሮም የጠፈር ህግጋት ተገልጦላቸው፣ አምዕሮዋቸው በዚያ መሰረት እስኪገዛላቸው ድረስ ደስታን ማጣጣም አይችሉምና፡፡ ደረጃ በደረጃ ሐሳቡ ከፍ እያለ በመሰላሉ ላይ ይረማመዳል ቦያቴየስ፡፡
ልዕለ ደገኛ/መልካምነት ማለት ምን ማለት ነው? ከርሱ በላይ ሌላ ማሰብ የማንችለው ጉዳይ ማለት ነው፡፡ ጥሩ፣ ደገኛ፣ መልካም የምንላቸው ጥቃቅን ነገሮች ሞልተውናል፤ ሁሉም ግን ሄደው ሄደው ማሰሪያቸው አንድ ልዕለ ደገኛነት ላይ ነው፡፡ የተበጣጠሰ ደስተኝነት ሳይሆን አንድ ፍጻሜ ደስታ ግን ህልው ነው፡፡ ይህ አንድ ፍጻሜ መመሪያውን፣ መገዣውን ህግጋት ለእውነት ፍለጋ ብናውለው አንድ ልዕለ እውነት እናገኛለን፡፡ ይህ ልዕለ እውነት ደግሞ ሁላችንም እንዳንፈረካከስ አንድ አድርጐ መያዝ የሚችል ኃይል አለው፡፡ የህዋ ከዋክብት እርስ በርስ እንዳይፈረካከሱ አንድ አድርጐ የሚይዛቸው አንዳች መለኮታዊ ህግ አላቸው፤ ሁሉንም ነገር አንድ አርጐ መያዝ የሚችለው ይህ ህግ ነው ፈጣሪ ማለት ይለናል፡፡ ፈጣሪ ማለት በራሱ ህልው የሆነ ማለት ነው፤ ለህልውናው አስገኝ ምክንያት የማያስፈልገው፡፡ ክፋት ማለት ደግሞ የህላዌ ጐዶሎነት ማለት ነው፤ ምንምነት፣ በህልውና መዋቅር ውስጥ ዝቃጩ ማለት ነው፡፡
ይሄው ነው እንግዲህ ይደርስብናል ብለን የምንፈራው ክፋት፤ ቦያቴየስ አብጠርጥሮ ያሳየናል የክፋትን ምንነት፡፡ ሁሌም መልካም ማድረግ ነው አንድን ሰው፣ ሰው ሆኖ በሰውነት ማሰሪያ አንድ አድርጐ ይዞ እንዳይፈረካከስ የሚጠብቀው እንጅ፤ የክፋት ውጤቱ መፈረካከስ ነው፤ ልጋግን አለመሰብሰብ፣ መዝረክረክ፣ በቁም መፍረስ፡፡ የፍጥረት ሁሉ ዝቃጭ መሆን፣ ሞተንም ቀብራችን የማያምር፣ ተቀብረንም መሬት የማትቀበለን መሆን ማለት ነው ክፉ መሆን ማለት፡፡ በችጋር ቀጥቼ ባሪያ አድርጌ አላልካቸዋለሁ የምትለዋ የገዢዎቻችን መንፈስ፤ ዛሬም ቢሆን ስትፈራገጥ እያየናት ነው፤ ቀባሪዎቿ መሆናችንን ግን ታሪክ ይመሰክራል፡፡ ስንቱን ቀብረን ፈውስ እንደምናገኝ ግን “እርሱ” ይወቀው፡፡ ክፋትን በመልካምነት ነጽቶ መዋጋት ያስፈልጋል፤ ክፋትን በክፋት መመከት አይቻልም፡፡ ተያይዞ ዝቃጭ መሆን ነውና ፍጻሜው፡፡ የኢትዮጵያ መንፈስ “ሰው” ያስነሳል፤ የዲያብሎስንም ሴራ ይበጣጥሳል፡፡
እርሱ መኪና እያሽከረከረ ጫማ በቀየረ ጓደኛው የሚቀናን ሰው ምን ይሉታል? የክፋት ዛር ውላጅ ካልሆነ በስተቀር፡፡ ህዝብ ከበላ ከጠጣ፣ ኑሮ ከተመቸው ሥልጣኔን ይጋፋኛል የሚል ፖለቲከኛንስ ምን ይሉታል? የክፋት አለቃ ካልሆነ በስተቀር፡፡ መለያየትን፣ መፍረስን የሚሰብኩ ሁሉ ከህላዌ ህግጋት ውጭ የሆኑ፣ ባዶነት የተሞሉና ስንኩል ፍጡራን ናቸው፡፡ እድል እጣፈንታ እንዳይገዛን በደገኝነትና በንጽህና ማበብ ይኖርብናል፡፡ ወደታችኛው የህላዌ መዋቅር፣ ወደ ዝቃጭነት በወረድን ቁጥር፣ ከልዕለ መልካምነት እርቀናልና የእጣፈንታ መጫወቻ እንሆናለን፡፡ የመንፈስ ልእልና ያስፈልገናል፡፡ ሌባ ሆኖ ሌብነትን ማውገዝ አይቻልም፡፡ ጨቋኝ ሆኖ ስለ ጭቆና መታገል፤ ማውራት አይቻልም፡፡ ሰዎችን ከመመዘናችን በፊት በያዝነው ሚዛን እራሳችንን መመዘን አለብን፡፡ በመልካምነት ባደግን ቁጥር ከልዕለ ደስታ፣ ከፍጻሜ እውነት፣ ከአንድዬ ጋር አንድ እየሆንን እንመጣለን እና የክፋትን ሰንሰለት በጣጥሰን ደስተኞች እንሆናለን፡፡
የመንግስትንም የተቃዋሚንም ዋሾ፣ አስመሳይና ተንኮለኛ ፖለቲካን አሜን አሜን በማለት ሳይሆን ውሸቱን መግለጥ፣ አስመሳይነቱን ማሳበቅ እና ክፋቱን በመልካምነት መዋጋት ያስፈልገናል፤ ይገባናልም፡፡ ታሪክ የሚደልዘውን፣ ሴራ የሚሸርበውን ማፋጠጥና ማስተማርም ያስፈልጋል፡፡ አለበለዚያ የፍጥረት ሁሉ እንቅርጣጭ፣ ነኳታ መሆን ነው ትርፉ፡፡
“መሬት ስንቆፍር ድንገት የተቀበረ ሃብት ብናገኝ የእድል ጉዳይ ነው” ይለናል አርስጣጣሊስ፣ ቦያቴየስ ግን ይህን አይቀበልም፡፡ ጉድጓዱን እንድንቆፍር የሚያነሳሳን አንዳች መለኮታዊ ኃይል አለ፡፡ ይህ መለኮታዊ ኃይል ወደርሱ በመልካም ግብራችን በቀረብነው ቁጥር ደረጃ በደረጃ ተጠቃሚ የምሆንባቸውን ሁነቶች ያመቻቻልና ነው፡፡ እንኳን ማስፈራሪያ እና እስር፤ መተትና አጋንንት የማይረቱት ብርቱ መንፈስ መታጠቅ ያስፈልገናል፡፡ እራስን ከመንፈስ እስረኝነት ነጻ ለማውጣት፡፡
በደካሞች ላለመገዛት ሲባል ፈላስፋው መሪ መሆን አለበት ይለናል አፍላጦን፤ ቦያቴየስ በዚህ ሃሳብ እጅግ አድርጐ ስለሚስማማ፣ የፍልስፍና ድርሳናቱና የህይወቱ መመሪያ አድርጐታል፡፡ እንዲህ አይነት ቅኔም ይቀኝለታል፡-
O happy race of men,
If like heaven your hearts
Were ruled by love!
ፈላስፋ የምንለው ጥበበኛውን ነው፡፡ እውቀት፣ እውነት፣ ፍትህ፣ ፍቅር፣ ውበት፣ መልካምነት ወዘተ አማናዊ፣ ደገኛ፣ አልፋ ኦሜጋ፣ ቀዋሚ ባህሪያት ያሉዋቸው ነገሮች አብጠርጥሮ የሚያውቀውን፡፡ ክፋት፣ መመሳሰል፣ ቅዠት፣ ጥላ፣ ብዥታ፣ ጊዜያዊነት ወዘተ የሚባል ነገር ሁሉ ከንቱ መሆኑን የተረዳውን ነው ቦየቴየስ ፈላስፋ የሚለው፡፡ የመልካምነት አባቷ ፈጣሪ ብቻ ነው፡፡ ሰዎች መልካም በሆኑ ቁጥር ደቂቀ መለኮት ይሆናሉ ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ምንም እንኳን መለኮት አንድ ቢሆንም መልካምነቱን ግን ለብዙዎች ለማካፈል የሚያግደው ነገር የለምና ነው፡፡ ከመለኮት መልካምነትን የተካፈለ ሰው ደግሞ መሪ ለመሆን ሁሉንም እኩል በፍትህ ለማስተዳደር ተወዳዳሪ አይኖረውም፡፡ ወይዘሮ ፍልስፍና ቦያቴየስን እንዲህ ታጨዋውተዋለች፤ እርሱም ማማረሩን እረስቶ ቅልጥ ያለ ፍልስፍና ይጽፋል፡፡
ሰው እጅ እግሩ እንጅ የሚታሰረው መንፈሱና ሃሳቡ አይታሰርም፤ እስር ቤትም ተሁኖ እንዲህ ይጻፋል፡፡ ሰው በስጋ እንጅ በስጋት መንፈስ መሞት የለበትም፤ ስለ እውነት ያለስጋት የሚጽፉት፤ ከአንድ ሺህ ስድስት መቶ ዓመት በኋላም እንዲህ እንደ ቦያቴየስ እንደመምበታለን፡፡ ቦያቴየስ ኢትዮጵያዊ ደብተራ ቢሆን ኖሮ፣ “ስለ ታሰሩ ሰዎች እንማልዳለን” ብሎ ጽሑፉን ይዘጋው ነበር፡፡

Read 2567 times