Saturday, 02 November 2013 11:49

“ማዕዶት”ስለግጥማችን የተፃፈ ግጥም

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(2 votes)

ለሥነ - ጽሑፍ ሥራዎች ስኬት፣ ውበትና ምልዐት እባህሩ ውስጥ መኖር፣ የማህበረሰቡን የየዕለት ትንፋሽ መጐንጨት፣ ሕልሙ ውስጥ ማደር፣ ተስፋውን ማቀፍ የግድ ነው ይላሉ - ምሁራን፡፡ እኛም በዚሁ ሃሳብ እንስማማለን፡፡ ደራሲው ከሕዝቡ ተገንጥሎ የልቡን ትርታ እንዴት ሊያዳምጥ ይችላል? ካልቻለስ እንዴት ይጽፋል? የሩሲያው ደራሲ ኢቫን ቱርጌኔቭም ከሀገሬ ከተለየሁ ከባህር የወጣሁ ዓሣ ነኝ” ያለው ለዚህ መሠለኝ፡፡
በርግጥም ለሥነ ጽሑፍ ለዛ፣ ለጣፋጭ ቋንቋ አጠቃቀም ከተደራሲው ሕዝብ ጋር መኖር ወሳኝ ሲሆን በተለየ ከገጠሬው ጋር ሕይወት መጋራት የበለጠ ውጤት አለው፡፡ ይሁን እንጂ ይህንን ሃይል አልፈው የቦታን ርቀት ሰብረው፣ በንባብ ከሕዝቡ ጋር የሚቀላቀሉ፣ ጆሮ ሰጥተው የተለያዩ መገናኛ ብዙሀን የሚከታተሉ መሠናክሉን ሊያልፉት ይችላሉ፡፡ ዛሬ ወደዚህ ሃሳብ ያመጣኝ አንድ ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ ለሃያ ሦስት ዓመታት ካናዳ እየኖረ በአማርኛ ቋንቋ ባልተንሻፈፉ ቃላት የግጥም መጽሐፍ አሳትሞ ለአንባቢ አቅርቧል፡፡
ከሁሉ የገረመኝም ይሄ ነው፡፡ “ማዕዶት” በሚል ርዕስ መጽሐፍ ማሳተሙ ብቻ ሳይሆን የሀገራችንን ሥነ ጽሑፍ ለማሳደግ ባለበት ሀገር ሆኖ መትጋቱ ያስደንቃል፡፡ በብዙዎች ዘንድ “የቆሎ ተማሪ” በሚል የብዕር ስሙ የሚታወቀው ማናዬ በቀለ፤ ስለ ሀገራችን ግጥም መቆርቆሩን የሚያሳይ ግጥም ጽፏል። አፍንጫው ምን ያህል ረዝሞ ውበትን ማሽተት እንደቻለ ሳስብ ገርሞኛል፡፡ ከውቅያኖስ ማዶ ሆኖ ሀገር ቤት የሚነድድ ምድጃ ዳር መሞቅ፣ ስናነጥስ አብሮ መርገፍገፍ ደስ ይላል፡፡ እስቲ “መለከት” የሚለውን ግጥሙን እንይለት፡፡
ግጥም ታወከ፣ በጠና ታመመ፤
ልቡ ደከመ፣ ምቱ ዘገመ፤
ድምፁ ሰለለ፣ ቤቱ ዘመመ፤
ፊደል ገደፈ፣ ግቱ ነጠፈ፣
በንዳድ ተመታ፣ አበባው ረገፈ፡፡
ዘር አባከነ፣ አፈርም ተሻማ፣
ድካምም ፀነሰ፣ ሽንፈትን አሰማ፤
ልምሻ አላሸቀው፣ ስር ግንዱ ቀጨጨ፤
ደዌም አደቀቀው፣ ጐበጠና ጫጨ፣
ትንፋሹም አጠረ፣ ነፍሱም ጣራ ሞት፣
ኤሎሄ አበዛ፣ አጥብቆ ቃተተ፡፡
የግጥም ቤተኞች፣ ስራስሩን ማሱ፤
ጥሞናም ያዙና፣ በድኑን አስነሱ፣
ወይም ገንዙና፣ አፈሩን መልሱ፡፡
ገጣሚው በዚህ ግጥሙ፤ ግጥም በሀገራችን ሕያው አይደለም፤ ሙት ተብሎም አልተቀበረም፡፡ ታምሞ ጣዕረ ሞት ላይ ነው፤ ወይም “ኤሎሄ”
ላይ ደርሷል እያለ ነው፡፡ ታዲያ ኤሎሄውን የሰማችሁ ወዳጆቹ፤ ከሁለት አንዱ አድርጉለት፣ ለበድኑ እስትንፋስ ስጡ፣ ካልሆነም ቀብራችሁ ገላግሉን እያለ ነው፡፡
በትክክለኛ ጊዜ የተፃፈ፣ ትክክለኛ ግጥም ነው። ስለግጥማችን ግጥም መፃፍም አለበት፡፡ ቀለም እየለቀለቅን ወረቀት አዥጐርጉረን ግጥማችንን ወዳጅ ባናሳጣው ደግ ነበር፡፡ አሁን አሁን በተለይ ብዙዎች የግጥም ነገር “በቃን” ያሉ ይመስላል፡፡ ጀርባቸውን ሰጥተውታል፡፡ ነፍስ ያላቸውን ከሙታን መካከል እንኳ የመምረጥ ትዕግስት አጥተዋል፡፡ የግጥምን ስም አታንሱብን በሚል ጆሮ ከልክለዋል፡፡ ለዚህ ነው ገጣሚው ግጥም የገጠመው፡፡
ከማናዬ ግጥሞች “ዕጣ ፈንታ” የሚለው ደግሞ እንይለት
ካንድ ኩሬ ተቀድቶ፣
ካንድ አፈር ተቦክቶ፣
ባንድ እጅ ለስልሶ፣
ባንድ እሳት ተጠብሶ፣
ቅርፁና መጠኑ፣ ስለተቀየረ፣
ጢስ እየጠገበ፣ ኩሽና እየኖረ፣
ማብሰያ እንዲሆን ለእሳት ተፈጠረ፡፡
እደጅ እየዋለ፣ እቤት እያደረ
ዞሮ እየገባ፣ በጀርባ እየኖረ፡፡
እንስራው ወንድሙ፣ ለውሃ ተዳረ፡፡
ይላል፡፡ ሕይወት እንዲህ ናት፡፡ ምናልባትም ተምሣሌታዊ አድርገን ልንወስደው እንችላለን። ከአፈር የተሰራ ሰው ዕድልና አጋጣሚ የተለያየ መልክና ቦታ ይሰጠዋል ልንል እንችላለን፡፡ አንዱ ዕድሜ ልኩን እየተጠበሰና እየተቃጠለ ሲኖር፤ አንዱ ደግሞ በተረጋጋ ሕይወት ሊኖር ይችላል፡፡ ሕይወት አንዱ በሣቅ እየተፍለቀለቀ፣ ሌላው በእምባ እየነደደ የሚኖርባትም መድረክ ናት፡፡ ብቻ በተለያየ ቦይ ለሚፈስሱ ሁሉ ግጥሙ ትልም ያበጀ ይመስላል፡፡ እሳት ወይስ አበባ? ይሏል እንዲህ ነው፡፡
ሌላው “መንቶ” ግጥምም ልቤን ነካክቶታል፡፡ እንዲህ እያለ :-
“አልተኛሁም”፡፡ ይላል፤ በኑሮ አመካኝቶ፣
እንቅልፉን በእንጀራው፣ እምሽክ አርጐ በልቶ፡፡
ይህቺ ግጥም ወደ ዳያስፖራው ሕይወት ይዛኝ ሮጣለች፡፡ በሥራ ብዛት በጊዜ ማጣት እንቅልፍ የራበው ስደተኛ፣ ኑሮውን በእንቅልፍ መለወጡን በእንጀራው እንቅልፉ መብላቱን ይነግረናል፡፡ እንጀራ ደግሞ ለመብላት - ከዳቦ ይልቅ ይመቻል። ጠቅለል አድርጐ መጉረስ ነው፡፡ ግን “እንጀራ” የሚለው ባለሺህ አይኖቹን ፈጣጣ አይደለም፡፡ የምንኖርበትን መንገድ ነው፡፡ የመኖርን መንፈስ፤ የመኖርን ድርሻ!
“ለጋን ውስጥ መብራቶች” በሚል ርዕስ የተፃፈው ሌላ ግጥምም አንዳች ውስጥን የሚሰረስር፣ ሃሳብን የሚያሻግር ነገር አለው፡፡
እናንተ መብራቶች፣ ለብቻ ምትበሩ፣
ለኛም እንዲታየን፣ ጋኖቹ ሰበሩ፡፡
ይህ ግጥም ለኔ የገባኝ፤ “መብራት የሆናችሁ ሕያዋን፣ በእኛና በእናንተ መካከል ያለው የልዩነት ግድግዳ ይፍረስ፤ ብርናችሁ ይብራ” በሚል ነው። ብቻችሁን በርታችሁ ብርሃንና ሙቀታችሁን አታባክኑ፤ ይልቅስ በብርሃናችሁ ብርሃን እንዳናገኝ የከለከለንን ግርዶሽ አስወግዱ ነው የሚለው፡፡ ግጥሙ ብዙ ዘርፍ አለው፡፡ ብዙ ያሳያል፡፡ ጋኖቹ እነማን ናቸው? ባህል፣ እምነት፣ ቋንቋ? እሱን ዓውዱ ይፈታዋል፡፡ ግና የግጥሙ ሃሳብ፣ የብርሃን ጥማት የማወቅ ናፍቆት ይመስላል፡፡ ለጋኖቹ ከሳሳችሁ ግን ብርሃኖች ለራሳቸው ነድደው፤ ብቻቸውን አመድ ሆነው ይረግፋሉ፤ ይለናል ገጣሚው፡፡
“የሁለት እናት ልጅ” በሚል ርዕስ የተቋጠሩት ስንኞችም ባህርማዶ ያሉ የሀገር ልጆችን ሕይወት የሚዳስስ ይመስላል፡፡
ልቧን ለቸረች እናቱ፣
እቅፏን ላሰፋች ሞግዚቱ፣
እሱነቱን እየገማመካ፤
እንባውና ላቡን፣ ሁሌ ያፈስበት፣
ላይሞላለት ነገር፣ ሰርክ እየዳከረ፣
“ኮብላዩ” ወገኔ ባንዲራ መስቀያ፣
ሰንደቅ ሆኖ ቀረ፡፡
ግጥሙ፤ እንባና ላብ ስለሚያፈስስ ገፀ ባህሪ ሕይወት ያወጋል፡፡ እንባና ላብ ለምን ተጣመሩ ብለን ስንጠይቅ፣ እንባው ብሦት፣ ላቡ ለእንጀራ የሚደረግ ድካም ነው የሚል መልስ ይታየናል፤ ወይም እኔ ታይቶኛል፡፡
የእንባው መፍሰስም ላይሞላለት ነገር መዳከሩ፣ ምናልባትም ልቡ ሁለት ቦታ ሆኖበት ይሆናል። እንጀራ ፍለጋ ተሰድዶ፣ ደግሞ ሀገርን ናፍቆ ማልቀስ፣ በሰቀቀን መብሰልሰል፡፡ “ሀገር” የሚለውን ክር ባለመበጠሱ፣ ልቡን ቆርሶ በመስጠቱ፣ ለሀገር ልጅነቱ ምስክሩ ባንዲራው ብቻ በመሆኑ፣ “ባንዲራ መስቀያ ሰንደቅ ሆኖ ቀረ” ብሎታል፡፡ ናፍቆት የሚያውለበልበው ዘንግ!
“ማሪዶት” ብዙ ግጥሞቹን በዜማ ስብራት ያጣ ግን ደግሞ ብዙ ጥሩ ሃሳቦች ያሉት፤ ሙዚቃው ጨፍግጐ የውበት ሣቆቹን የነጠቀው መድበል ነው እኔም ልዳስሰው የፈለግሁበት ዋና ምክንያት፤ በባዕድ ሀገር ሆኖ ቋንቋውን ሳይጥል፣ ለጥበብ ለደከመው ያገር ልጅ ክብር ለመስጠት ነው፡፡ በዚያ ላይ የሀገራችንን መጽሐፍት አሳድዶ በመፈለግ እየተረከ ለንባብ ባህላችን ከፍተኛ ዋጋ ከፍሏል፡፡ ገጣሚ ማናዬ፤ የባህር ማዶ የሀገራችን ሥነ ጽሑፍ አምባሳደር በመሆኑም ሊከበር ይገባዋል እላለሁ፡፡

Read 4946 times