Saturday, 19 October 2013 12:39

ቢትወደድ መኮንን እንዳልካቸው

Written by  ወልደመድህን ብርሃነ መስቀል
Rate this item
(5 votes)

በ”የሕልም ሩጫ” ሲታወሱ
በ1895 ዓ.ም በ12 ዓመቴ ከአዲስጌ አዲስ አበባ መጥቼ ከዚህ ዓለም እሽቅድምድም ገባሁ። አንዱ ሲሾም ሌላው ሲሻር፣ አንዱ ሲታሰር ሌላው ሲፈታ፣ አንዱ ሲሞት ሌላው ሲተካ በማየት የዚህን ዓለም እሽቅድምድም ትግል አጠና ነበር፡፡ በ1895 ዓ.ም የምኒልክ ትምህርት ቤት ሲከፈት (ትምህርት ቤቱ 4 ኪሎ ከመምጣቱ በፊት ፒያሳ በአልፍሬድ ኤግል መኖሪያ ቤት እያለ ማለታቸው ይሆናል) ደጃዝማች ተፈሪ መኮንን፣ ልጅ ብሩ ሃብተማርያም፣ እምሩ ኃይለሥላሴ፣ ዘውዴ ጐበና፣ አስፋው በንቲ፣ እኔና ሌሎች ልጆችም አብረን ነበርን፡፡
የአጐቴ ሞት ጥልቅ ሀዘን ላይ ስለጣለኝ 5 ዓመት በጽሞናና በብቸኝነት ተቀመጥኩ፡፡

“ፍላጐትህን ስታባርረው ተመልሶ እየጋለ ይመጣል” እንደሚባለው እሽቅድምድሙን ዓለም ተመልሼ ተቀላቀልኩ፡፡ በዚያ ዘመን ተወዳዳሪን ለማሸነፍ የቤተ - መንግስትን ሥርዓት ማወቅ ያስፈልግ ነበር፡፡ ባለማዕረግ አባት የሞተበት ልጅ በቀላሉ ወደ ስልጣን ይወጣል፡፡ እኔ አባቴ በልጅነቴ ስለሞተ ውድድሩን በጥረቴ ማሸነፍ ነበረብኝ፡፡ አፄ ምኒልክ ከሞቱ በኋላ ከልጅ ኢያሱ ጋር መግባባት ስላልቻልን ይኸም ተጨማሪ መከራ ሆነብኝ፡፡ ባለመሾሜ እኔ ብቻ ሳልሆን ወዳጆቼም ሀዘን ገባቸው፡፡ አለቃ ገብረሚካኤል ለሚባሉ አባት ጭንቀቴን ስነግራቸው:-
“አንድ ወዳጅህ የሆነ ሰው ምሳ ቢጋብዝህ ቁርስ ለመብላት ትሄዳለህን ወይስ ለራት ቢጋብዝህ ለምሳ ትሄዳለህ? እንደዚሁም ሁሉ እግዚብሔር በዚህ ዓለም ለሥራ የመረጠውን ሰው አንዳንዱ በጠዋት፣ አንዳንዱን በእኩለ ቀን፣ ሌላውንም በማታ ነው የሚጠራው፡፡ ምናልባት አንተ ለእኩለ ቀን ወይም ለማታ ተጠርተህ እንደሆን፤ ለጠዋት ካልሆነህ ብለህ በከንቱ ታዝናለህን?” አሉኝ፡፡ ምክራቸው ልቤን ነካኝ፡፡ እኔም ደጅ ጥናቱን ትቼ ቤቴ ተቀመጥኩ፡፡
በምኒልክ ትምህርት ቤት አብረውኝ የተማሩት ልጅ፤ አልጋ ወራሽ ሲሆኑ አለቃ ገብረሚካኤል የሰጡኝ ምክር ትዝ አለኝ፡፡ በወዳጄ ዘመነ መንግስት ከአስር የማያንሱ የስልጣን ማዕረጐችን አገኘሁ፡፡ በአገር ውስጥና ከአገር ውጭም በተለያዩ ኃላፊነቶች እየተሾምኩ አገለግልኩ፡፡ በ1921 ዓ.ም በለንደን ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሆንኩ፡፡ በማይጨው ጦርነት ከንጉሱ ጋር አብሬያቸው ነበርኩ፡፡ ሚያዝያ 24 ቀን 1928 ዓ.ም ከኦጋዴን ጦር ሜዳ በጅቡቲ በኩል ወደ አውሮፓ ሲሄዱም በቅርብ ነበርኩ፡፡
በ1907 ዓ.ም የራስ ቢትወድድ መንገሻን ልጅ ዘውዲቱን አግብቼ ሰላምና ደስታ የሞላበት ትዳር ነበረኝ፡፡ ከጃንሆይ ጋር ወደ ውጭ በሄድኩበት ወቅት ታምማ አልጋ ላይ ነበረች፡፡ ዳግመኛ መገናኘት አልቻልንም፡፡ ሁለተኛው ትዳሬን የመሠረትኩት በኢየሩሳሌም ሲሆን ልዕልት የሻሽ ወርቅ ይልማን ነው ያገባሁት፡፡ በስደት ላይ እያለንም የንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት ተወካይ ሆኜ ወደተለያዩ አገር ባለስልጣናት እየሄድኩ ጉዳይ አስፈጽሜያለሁ ጠላት በተባረረ ማግስት በ1934 ዓ.ም የአገር ግዛት ሚኒስቴር ሚኒስትር ሰብሳቢ ሆንኩ፡፡ በኢሊባቡር ጐሬ ተሹሜም ሠርቻለሁ፡፡ መፃሕፍትን መፃፍ የጀመርኩት እንደትርፍ ጊዜ ሥራ ነበር፡፡ ይህን “የሕልም ሩጫ” ብዬ የሰየምኩትን መጽሐፍ ያዘጋጀሁበት ምክንያት ሰው በነፍሱ አፈጣጠር ከፍ ያለ መሆኑን፤ በሥጋዊ አፈጣጠሩ ብልሹ መሆኑን ለማሳየት ነው፡፡
እግዚአብሔር ባንዱ እጁ አንዱን ዘመን ሲያጠፋ፣ በሁለተኛ እጁ ሌላውን ዘመን ያበራል። እድሜና ዘመን ከመሄድ አያቋርጡም፡፡ ሰውም የጊዜው ተገዢ በመሆኑ በሰከንድ፣ በደቂቃ፣ በሰዓት፣ በቀን፣ በወርና ባመት ላይ ተቀምጦ ይገሰግሳል፡፡ ማንም ባለስልጣን ሰው ቢሆን ነገን ጠልቸዋለሁና ልለፈው፤ ትላንትን ወድጄዋለሁና ልመልሰው ለማለት አይችልም፡፡ ስለዚህ በራስ ሃሳብና ምኞት መጣደፍ የሕልም ሩጫ፣ የማይጨበጥ አረፋ ይሆናል፡፡
የሰው ልጅ እንዳትክልት በሕፃንነቱ ለምልሞ፣ በወጣትነቱ አብቦ፣ በጐልማሳነቱ አፍርቶ ሲታይ ደስ እንደሚል እንደዚሁ በዕድሜ ጠውልጐ፣ በእርጅና ደርቆ፣ በሞት ሲቆረጥ የሰውን የመጨረሻ ዕድሉን ስናስበው በጣም ያስገርማል፡፡ ይህ ሲታይ ሰው በዚህ ዓለም ላይ ለጥቅምና ለክብር የሚደክመውና የሚሮጠው ሁሉ የሕልም ሩጫን ይመስላል፡፡
በስደት ላይ ሳለን ሥዕሎችንም እስል ነበር፡፡ ነፃነት ተመልሶ በአገራችን መኖር ስንጀምር ባለቤቴ ልዕልት የሻሽወርቅ ይልማ ሕፃናት መርጃ የበጐ አድራጐት ድርጅት መሥርታ ነበር፡፡ ስዕሎቼን በ2ሺህ 800 ብር ሸጨው ለበጐ አድራጐት ሥራው ውሏል፡፡ ከፃፍኳቸው መፃሕፍት አንዳንዶቹ ለቴአትር ጨዋታ ተጠንተው በመድረክ ሲቀርቡ በተገኘው ገንዘብ ሕዝብ ሲጠቀምበት ማየቴ የመንፈስ ደስታ ሰጥቶኛል፡፡ ለጃንሆይ 25ተኛ ኢዮቤልዩ በዓል፤በሥማቸው የተሰየመው ቴአትር ቤት ተመርቆ ሲከፈት የእኔ ቴአትር (ዳዊትና ኦርዮን) ተመርጦ በመቅረቡ ላቅ ያለ የመንፈስ ከፍታ ተሰምቶኛል፡፡
መጽሐፍ ከመድረስ፣ ሥዕል ከመሳል፣ የቴአትር ጽሑፎችን ከማዘጋጀቴም ባሻገር ለፎቶግራፍ ጥበብ ልዩ ፍቅርና አክብሮት አለኝ፡፡ በ “የሕልም ሩጫ” መጽሐፌ ውስጥ በርካታ ፎቶግራፎችን ያስገባሁት በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ፎቶግራፍ ለአገርና ለሕዝብ ታላላቅ ተግባራትን አከናውነው ያለፉ ባለታሪኮችን ምስል የሚያኖርልን ሙያና ጥበብ ስለሆነ ሌሎች ሰዎችም ፎቶግራፎችን እንዲያስቀምጡ አደራ እላለሁ፡፡
ሕፃን ከእናቱ ማህፀን በኩል ወደዚህ ዓለም ላይ የሚመጣው ለመልካም ወይም ለክፉ መልዕክት እንደሆነ የታወቀ በመሆኑ፤ ፓስካል (Pascal) የሚባል የፈረንሳይ ሊቅ አንድ ሕፃን አልጋው ላይ ተኝቶ ሲንፈራገጥ ባየ ጊዜ፣ ባርኔጣውን አውልቆ “አንተ ሕፃን ለእንዴት ያለ ሥራ ተልከህ መጥተህ ይሆን?” ብሎ እጅ ነስቶት ያልፍ ነበር ይባላል፡፡
በምድር ሕይወት እንደምንመለከተው ራሱን በመጥላት፣ ወንድሙን በመውደድ፤ ገንዘቡንም ሕይወቱንም ለሀገሩ መስዋዕት በማድረግ የምግባር አርበኛ የሚሆን አለ፡፡ ሕዝብን በሰላም በመምራት በሕዝብ ልብ ውስጥ የሚነግስ የአገር መሪ ይኖራል፡፡ ጥቅሙን ሁሉ ለራሱ ሰብስቦ ወንድሙ የእሱ ለማኝ እንዲሆን የሚመኝና በዚህ ክፉ ሥራው የሚደሰትም አለ፡፡ ለዓለምና ለሰው ልጆች ጠቃሚ የሆኑ የጥበብ ሥራዎችን የሚፈለስፉ ምሁራን አሉ፡፡ የሰው ልጅ በዚህ መልኩ ለልዩ ልዩ ዓይነት ተግባር የተፈጠረ መሆኑ ይታያል፡፡
የሰው ልጅ ከመቃብሩ አፈር በላይ የሚቀር ታሪካዊ ሥራ ሳይሰራ መቶ ዓመት ቢቀመጥ ትርፉ ምንድነው? ሰው ከዕድሉ ጋር እስኪናገኝ ግን በከንቱ መድከም አይኖርበትም፡፡ ጥረትና ድካም ከዕድል ጋር ሲገናኙ ምን እንደሚመስሉ “የሕልም ሩጫ” ብዬ በሰየምኩት መጽሐፍ ባሰፈርኩት ጽሑፍና በአንድነት ካቀረብኳቸው ፎቶግራፎች፣ ከእኔ ሕይወትና ሥራ መማር ይቻላል፡፡
* * *
የቢትወደድ መኮንን እንዳልካቸው የሕይወትና የሥራ ታሪክን የያዘው “የሕልም ሩጫ” መጽሐፍ በሁለት ሦስተኛ ገፆቹ የሰበሰባቸው ፎቶግራፎችም መረጃ ሰጪ ብቻ ሳይሆኑ ታሪክም ይናገራሉ፡፡ የአፄ ቴዎድሮስ፣ ዮሐንስ፣ ምኒልክ፣ የንግሥት ዘውዲቱና የእቴጌ ጣይቱ ምስሎችን ይዟል፡፡
የመጽሐፉ ባለታሪክ በልጅነታቸው በአሊያንስ ኢትዮ ፍራንሲስ ከነበሩትበት ዘመን አንስቶ በወጣትነት፣ በአርበኛነት፣ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎችና ከኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ዲግሪያቸውን በተቀበሉበት ወቅት የተነሱትን ፎቶግራፎችንም አቅርቧል፡፡ አፄ ኃይለሥላሴ በአልጋ ወራሽነት የስልጣን ዘመናቸው ከፈረንሳይ መንግስት የተሰጣቸው የ”ቪላ ካሚስትራ” ሕንፃ፤ አልጋ ወራሹ አውሮፓን ዞረው በጐበኙባቸው ወቅት የነበረው ሁኔታ ምን እንደሚመስል ታሪክ የሚናገሩ ብዙ ፎቶዎችም አሉት፡፡
የባለታሪኩ ባለቤት ልዕልት የሻሽወርቅ ይልማ ላቋቋሙት የሕፃናት በጐ አድራጐት ድርጅት መርጃ ከሆኑትና 2ሺህ 800ብር ከተሸጡት ስዕሎች የተወሰኑት ፎቶግራፍ ተነስተው የመጽሐፉ አካል ሆነዋል፡፡ በዘይት ቀለም ቅብ ከሳሏቸው መካከል የኢየሱስ ክርስቶስ ምስል፣ የጐንደር ግንብ፣ የምጽዋ ድልድይ…ስዕሎች ይገኙበታል፡፡ በ1930 ዓ.ም በኢየሩሳሌም የሳሉትና እግዚአብሔር አንዱን ዘመን እያጠፋ ሌላውን ሲያበራ የሚያሳየው ስዕል በተለየ ሁኔታ ያስደምማል፡፡
ረጲ አካባቢ ይገኝ በነበረው መኖሪያ ቤታቸው ግቢ “የዓለም መታሰቢያ” የሚል ሐውልት ያሰሩት ቢትወደድ መኮንን እንዳልካቸው፤ መጽሐፋቸው ሊያስተላልፉ የፈለጉትን መልዕክት ቀደም ብለው በሐውልቱ ላይ ያመለከቱ ይመስላል፡፡ በሐውልቱ አንድ ሽማግሌ ዓለምን ተሸክሞ ይታያል፡፡
ዓለምን በሚወክለው የድንጋይ ሉል ላይ “ኃጢአት ሸክምሽ የከበደ፤ ሌቦችና ቀማኞች የሚካፈሉሽ ዓለም ሆይ!” የሚል ጥቅስ ተጽፏል፡፡ በመኖሪያ ቤታቸው አፄ ኃይለሥላሴን ጨምሮ የዩጐዝላቪያ መሪ የነበሩት ፕሬዘዳንት ቲቶን መሰል ታላላቅ ሰዎችን ያስተናግዱ እንደነበር የሚያሳዩ ፎቶግራፎችም አሉ፡፡
“ላንድ ሕዝብ ነፃነት ማግኘት ብቻ የሚበቃ ነገር አይደለም፡፡ ነገር ግን ተቀባዩ ሕዝብ የነፃነትን ትርጉም ምን እንደሆነ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡
ቮልቴር የሚባል የፈረንሳይ ሊቅ “ነፃነት ለሰው ሁሉ የሚገባው መብቱ ሲሆን የወገኑን ኑሮ ሳያበላሽና መብቱን ሳያስደፍር በጥንቃቄ እንዲሰራበት ያስፈልጋል’ ይላል፡፡” በማለት በአንድ ወቅት በቤተመንግሥት ተገኝተው ንግግር የደረጉት ቢትወደድ መኮንን እንዳልካቸው፤ ከንባብ፣ ከትምህርትና ከሥራ ልምድ ያገኙትን ዕውቀት በተለያዩ መፃሕፍት እያዘጋጁ በማሳተም ይታወቁ ነበር፡፡

Read 2499 times