Saturday, 19 October 2013 12:31

“ኢየሱስ ክርስቶስ በኢትዮጵያ” የጮኸውን ያህል የማይናገር መጽሐፍ

Written by  ሎሞን አበበ ቸኮል saache43@yahoo.com solomonabebe.s5@facebbok.com
Rate this item
(2 votes)

             በአሜሪካዊ የሃይማኖት ሰባኪ እና ጥናታዊ ፊልም ሠሪ ጂም ራንኪን “ጂሰስ ኢን ኢትዮጵያ” በሚል ርእስ በአሜሪካ ውስጥ የታተመ መጽሐፍ ነው፡፡ በ2005 ዓ.ም ተተርጉመው በአማርኛ ከቀረቡ መጽሐፎችም አንዱ ነው፡፡
ብዙ አንባቢዎች የትርጉም ሥራዎችን ያለማንበብ አቋም የያዙትን ምክንያት በሚገባ ማሳየት የሚችል ከመኾኑም በላይ፤ በሀገራችን መጽሐፍን የማሳተም ሥራን በያዙት ሰዎችም የሚፈፀመውን ጥፋት አጉልቶ የሚያሳይ የትርጉም ሥራ ነው፡፡ “ኢየሱስ ክርስቶስ በኢትዮጵያ” በሚል ጯኺው ርእሱም ጭምር በብዙው ተገዝቶ ሳይነበብ አልቀረም፡፡ አሁንም በብር 40.00 እየተሸጠ ይገኛል፡፡
ይህን መጽሐፍ የግድ መመልከት ያስፈለገበት ምክንያት ቢጠየቅ “የታለ“ኢየሱስ ክርስቶስ በኢትዮጵያ የተባለው?” ለማለት ነው፡፡
አንድ አንባቢ በመጨረሻ ይህን ካልጠየቀ፣ ራንኪን በድፍረት የተናገረውን እና “ይኼ ነው ይህን የሚገልፀው ጥንታዊ የብራና መጽሐፍ” ተብሎ የተጠቆመውን በመጻፉ ብቻ በቂ ነው ብሎ ተቀብሎታል ማለት ነው፡፡ አሊያም ደግሞ፣ ለአሜሪካዊው ፀሐፊ የመንፈስ መገለጥ ብቻ አሳምኖታል ማለትም ይሆናል፡፡
በሌላ በኩል የቤተክርስትያን ሰባኪው ገና ከመነሻው ጀምሮ ሲገለጥለትና ሲገጣጠምበት የነበረውን የመንፈስ መገለጥ ምክንያት፣ ልክ ለራሱም እንደሆነለት አድርጐ በድፍኑ አምኖ ተቀብሎታል ከማለት ሌላ ምንም አይታሰብም፡፡
ራንኪንም ቢሆን ኢየሱስ ክርስቶስ በኢትዮጵያ ደርሶ እንደነበር ያሳመነው፣ በአስጐብኚው ተተርጉሞ ኢየሱስ ክርስቶስ በዚያ የጣና ደሴት ገዳም ውስጥ እንደጸለየ የተነገረው እና ይሄንኑ ከሚተርከው ጥንታዊ ብራና ላይ በሞባይሉ ፎቶ ያነሳቸው የጥቂት መስመሮች ትርጉም ብቻ ይመስላል፡፡ በፎቶ ያነሳትን የግእዝ ጽሑፍ አሜሪካ ውስጥ ሊያገኛቸው ለቻሉት አንድ ካህን አሳይቶ በድፍኑ ልትተረጐምለት በቃች። በመጽሐፉ ላይ እንደጠቀሰው፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ከእናቱ ጋር ኢትዮጵያ ስለመግባቱ የሚናገር እንደሆነ ነው የነገሩት፡፡ እንግዲህ በነዚህ ብቻ ነው መግባቱን ራሱም ነው ከማለት ይልቅ በውስጣዊ መንፈሱ ሹክ እንደተባለም ሲገልፀው የነበረው፡፡ ምናልባት እሱ በቀጥታ ባይናገረው “የመንፈስ መገለጡ” ብቻ ሊሆን ይችላል ከማለት ውጭ በጭራሽ አይታሰብም፡፡
ራንኪን ኢየሱስ ከእናቱ ጋር ኢትዮጵያ መግባቱንና መቀመጡን እንዴት “ሊያውቅ” እንደቻለ የሚተርክባቸውን ገጾችና ሌሎች ተያያዥ የጉዞ ታሪኮችን እንመልከት፡፡
ጂም ራንኪን የቦብ ኮርኑክ አሣሽ ቡድን አባል ሆኖ ነው ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት የቻለው፡፡ቦብ ኮርኑክን እማናውቅ ካለን ወይም እማናስታውሰው ከሆነ፣ በኢትዮጵያ፣ አክሱም ውስጥ ታቦተ ሙሴ መኖር አለመኖሩን “በገዛ ራሴው መንገድ ላረጋግጥ” ብሎ የተነሳ ነበር፡፡ በአክሱም ጽዮን የነበረውን የቤክርስቲያን ቅርስ ጥበቃና ምዝገባ ኃላፊ ዲያቆንና ሌሎች ሁለት መነኮሳትን በረብጣ ዶላር ደልሎ፣ ጽላቱ በምሥጢር በሚቀመጥበት ገብተው እንዲመለከቱ የሞከረ ነበር፡፡ ሙከራው በሚያስደነግጥ አደጋ ተፈፀመ፡፡
ኮርኑክ ኤድዊን ፋውንዴሽን ሥራ አስኪያጅ ነው። ይህ ፋውንዴሽን የአክሱሙን እና ከዚህ በፊትም ትክክለኛዋ ሲና የት እንደነበረች ያሰሰ ድርጅት ነው፡፡
ፋውንዴሽኑ በአፖሎ ፕሮጀክት ጨረቃ ላይ በእግራቸው የቆሙና የተራመዱ ከተባሉት አንዱ የሆነው ኤድዊን፤ ከጨረቃ ጉዞው እንደተመለሰ የመሠረተው ድርጅት ነው፡፡ ጨረቃ ላይ እግሩን እንዳሳረፈ በኅዋው ውስጥ ሽቅብ አንጋጥጦ ይቺን ምድር ባያት ጊዜ “አንዲት በቀላሉ ፍርክስ የምትል ተሰባሪ ነገር” መስላ ታየችው፡፡ ወዲያውኑ ወደ ምድር ሲመለስ ምን ዓይነት ሥራ መሥራት እንዳለበት ወሰነ፤ ኤድዊን፡፡ ድሮ ከወላጆቹ ጋር ሳለ ሲያነብበው በነበረው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጻፉ ቦታዎችንና ቅርሶችን የማሰስና የመፈለግ ሥራ፣ ይህንንም የሚሠራ ድርጅት ማቋቋም፡፡ በዚሁ መሠረት ፋውንዴሽኑን መሥርቶ ሥራውን ሲጀምር፣ በተለይም ቀዳሚው ተፈላጊ አድርጐ ያሰበውን የኖኅ መርከብ ፍለጋውን ለማካሄድ ሲነሣ የሚረዳውን ሰው ፈለገ፡፡ ትላልቅ ተራሮች ላይ ተንጠላጥሎ መውጣትን እንዲያሰለጥነውና ለደህንቱም ጠባቂው እንዲሆን በማሰብ የኮሎራዶ ፖሊስ እና ወንጀል መርማሪ የነበረውን ይህንን መቶ አለቃ ኮርኑክን ቀጠረ፡፡ እያሰለጠነው ሳለ ግን የአሠሣው ሥራም ላይ ተሳታፊ እንዲሆን ወሰነ፡፡
የኖኅ መርከብን ፍለጋው የቱርክ መንግሥት፣ አሳሾችን እንደ ሰላይ ቆጥሮ በማሰሩ ቀረ፡፡ ቀጣዩ ፕሮጀክት ሙሴ ጽላቶችን የተቀበለበት የሲናን ተራራ የት እንደሚገኝ መፈለግ ሆነ፡፡ በዚህም ላይ ኮርኑክ ከዋነኞቹ ፈላጊዎቹ አንዱ ነበር፡፡
የሲናን ፍለጋ ሥራው ካበቃ በኋላ የፋውንዴሽኑ ባለቤትና መሪ ኤድዊን ሞተ፡፡ ከዚህም የተነሳ ኮርኑክ የፋውንዴሽኑን ሥራ አስኪያጅነት ተረከበ። ታቦቱ የተሰጠበትን ሲናን እንዳገኟት፣ ያው ታቦት የት እንደደረሰ ማወቁ ደግሞ በኮርኒክ ታሰበ፡፡ እናም በቀጥታ ይገኝባታል ወደተባለችው ወደ ኢትዮጵያ ሊዘምት ተነሣ፡፡
ከዚህ በፊት እንዲሁ ስለታቦተ ሙሴ በአክሱም መገኘት፣ የታሪክ ፈለግን እየተከተለ በመመርመርና በማጥናት አክሱም ጽዮን በር ድረስ እያስረገጠ የተጓዘው ግርሃም ሃንኩክ ያቀረበውን ዘ ሳይን ኤንድ ዘ ሲል ኮርኑክ አንብቧል፡፡ “ግን አላረካኝም፣” ይል እና “ራሴ በራሴ መንገድ መፈለግ አለብኝ” ብሎ ይነሳል፡፡
ምናልባት ሃንኩክ የቃል ኪዳኑ ታቦትን ከርሱ በኋላ ለመፈለግ የሚነሳ ከመጣ፣ “እኔ ከደረስኩበት ላይ ተነስቶ አንድ ዕርምጃን ይራመድ፣” እንዳለው፣ እርሱ ከደረሰበት የሚቀጥለውን ርምጃ መራመዱ ነው ልንለው የምንችለው ዓይነት ጉዞ ነበር የተጓዘው፡፡ በገንዘብ ኃይል የመፈለግን መንገድ ነበር የመረጠው። ከዚህ ውጭ ያን ያህል የተሻለ የምርምርና የጥናት ሥራ አላደረገም፡፡
እንግዲህ፣ በዚህ ሥራ ላይ በነበረበት ጊዜ ነበር የ”ኢየሱስ በኢትዮጵያ” ጸሓፊ ኮርኑክን ያወቀው። በዚሁ የአሠሣ ሥራው በአንዱ የአሜሪካ ቲቪ ለኮርኑክ ቃለ መጠይቅ ሲደረግለት ዓይቶ ደወለለት፡፡ በመሰል ጉዳዮች ፍለጋና ዘጋቢ ፊልም በመሥራት ላይ እንደሚገኝ ገልጾ ይተዋወቃሉ፡፡
ኮርኑክ ለመጨረሻ ጊዜ የቃልኪዳን ታቦቱን ጉዳይ የሚፈጽምበትን ጉዞ ለማድረግ ሲነሳ ለጂም ራን ኪን ደውሎ፣ በዚያ ጉዞው ወደ ኢትዮጵያ ከሚጓዙት አንዱ እንዲሆን የመረጠው መሆኑን ነገረው፡፡ ሌሎች ከዚያ በፊት ይዟቸው ያልነበሩ ባለሞያዎችን ያካተተ ቡድን ወደ ኢትዮጵያ ገባ፡፡
ይህ የኮርኑክ የመጨረሻ ጉዞ የፋውንዴሽኑ ባለቤት የኤድዊን መበለትም አብራ የመጣችበትና ለኢትዮጵያ መንግስት ፕሬዚዳንትም ጨረቃ ደርሳ ተመለሰች የተባለች የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማን በይፋ ማስረከብ የቻለችበት ነበር፡፡ (ያኔ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ነበሩ ፕሬዚዳንቱ)
ለኮርኑክ የመጨረሻ በሆነው በዚህ ጉዞ፣ አክሱም ላይ ለአክሱም ጽዮን የቅርስ ምዝገባና ጥበቃ ኃላፊ ሆኖ የተሾመው ወጣት በተቀበለው ረብጣ ዶላር፣ ጽላቱ ወደሚቀመጥበት ቦታ መነኮሳት እንዲገቡና እንዲመለከቱ ቢያደርግም አልተሳካለትም፡፡ አንደኛው መነኩሴ ወዲያው ሲሞት ሌላው ደግሞ ሊሞት ሲያጣጥር ነበር የቀጠሮ ቀን ደርሶ ኮርኑክ ከነቡድኑ የገባው፡፡ ኮርኑክ የሚያጣጥረውን መነኩሴ ለማግኘት ተጣደፈ፡፡ አግኝቶ አነጋገረው፡፡ በኋላ ያም መነኩሴ ሞተ፡፡ ኮርኑክ የቃል ኪዳኑ ታቦት በአክሱም መኖሩን በዚህም አረጋግጦ ነበር፡፡ ቡድኑን ይዞ ለተጨማሪ ሥራ ወደ ጣና ሐይቅ ገዳሞችም ያመራው፡፡
ጣና ከመግባታቸው በፊት ወደ ቅማንቶች በመግባት ከአንዲት ቤተ እስራኤላዊት ድድ ዘሯን በክሮሞዞም የሚመረምሩበትን ናሙና ወስደዋል። በጣና ቂርቆስ ገዳም ውስጥ ከቤተክርስትያኑ ሕንፃ አጠገብ ከሚገኙ መቃብሮች የአንዱን አጽም በቁፋሮ ከፍተው፣ ከአጥንቱ ናሙና ለመውሰድም ጠይቀዋል፡፡ የኛን የተቀበሩትን ሰው ዘር የሚያውቁበትን ምርመራ ለማድረግ የፈለጉትን ናሙና ግን አላገኙም፡፡ በቦታው የዚያ ገዳም መሥራች እንደነበሩ የሚታወቁት መነኩሴ እንደተቀበሩበት ያውቃሉ፡፡ ነገር ግን ይህ አስቀያሚ ጥያቄአቸው በአበ ምኔቱ ሊፈቀድላቸው አልቻለም፡፡
አስጐብኚው ግን እንቢታቸውን እንዲያስለውጥላቸው በነገሩት መሠረት፣ አበ ምኔቱን አጥብቆ ይጠይቃቸዋል፡፡ አበ ምኔቱ በምንም ዓይነት እንደማይቻል በመግለፃቸው እንዳሰቡት ሳይሆንላቸው ቀረ፡፡
ከዚያ በጣና ቂርቆስ ውስጥ ያሉትን የተለያዩ ቦታዎችና አለቶች ይጐበኛሉ፡፡ በርከት ካሉት የቡድኑ አባላት ፈንገጥ እያለ፣ መንፈሱ አንድ ነገር እንደጐደለ እና እንዲፈልግ እንደሚገፋፋው አድርጐ በሚያቀርበው ገለጻው ሣር ቅጠሉን እየጠራረገ፣ በአራት እግሩ እየዳኸ፣ በአንድ ቋጥኝ ጠፍጣፋ አናት ላይ ሲያነፈንፍ የነበረው ራንኪን፤ ሳያውቀው ከደሴቱ ጫፍ ደርሶ ዥው ብሎ ሐይቁ ውስጥ ሊወድቅ እንደነበረ ገልጿል፡፡ ለጥቂት የተረፈ መሆኑን ራሱው “ኢየሱስ ክርስቶስ በኢትዮጵያ” ባለው መጽሐፉ ጽፎታል፡፡ ቋጥኙን ቧጥጦ ከሥር ውሃው ውስጥ የሚርመሰመሱት አዞዎች ቀለብ ከመሆን ዳነ፡፡
ሌሎቹ ጉብኝታቸውን ጨርሰው በመጨረሻ ከገዳሙ ከመውጣታቸው በፊት የሚያዩአቸውን ጥንታዊ ንዋያትና ቅርሶች በያዘች ያረጀች ትንሽዬ ታዛ ወርደው፣ መነኩሴው ቁልፍ ይዘውላቸው እስኪመጡ ቆመው ሲጠብቁ ጂም ራንኪን ወደ ኋላ ቀረ፡፡ አንዳች የቀረ ነገር እንዳለ ይሰማኛል” በማለት ያንን እንዲገልጽለት እዚያው ባገኘው ጠፍጣፋ ዓለት ላይ ተደፍቶ ይጸልይ ገባ፡፡
ከቤተክርስትያኑ መግቢያ አጠገብ ቆሞ እሱን ይጠብቀው ለነበረው ኢትዮጵያዊው አስጐብኚ አንድ ቄስ ይኼ ሰው የሚጸልይበት ላይ ኢየሱስም እዚህ ሳለ ይጸልይ እንደነበረ ነገረው፡፡ አስጐብኚው ይሄንኑ ለራንኪን ጮክ ብሎ ይነግረዋል፡፡ በቃ! ራንኪን የሚሆነውን ያጣል፡፡ የቀረው ነገር እንደሆነ ይሰማው የነበረውም ይኼው እንደነበረ ቅንጣት አልተጠራጠረም፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ገዳም ተቀምጦ ነው እርሱ በፀለየበት ዓለት ላይ ዘወትር “ከአባቱ ከእግዚአብሔር አብ ጋር ይነጋገር የነበረው፡፡” እንዲያውም እሱ እንደገለጸው፤ “ኢየሱስ ከእግዚአብሔር አብ መመርያን ይቀበል ነበር፡፡”
በዚህ ነገር ራንኪን በኃይለኛ ስሜት ውስጥ ገብቶ ሳለ፤ ይኼን በዝርዝር የሚናገረውን መጽሐፍ ደግሞ እታች እንደሚያገኙ አስጐብኚው በነገረው መሠረት ወደዚያው ተጣድፎ ይወርዳል፤ ሌሎቹ አባላቱ ቆመው በሚገኙበት፡፡
ካህኑ ይዘውት በመጡት መክፈቻ በከፈቷት ትንሽዬ ደሳሳ አሮጌ ቤት ውስጥ በኦሪት ዘመን መስዋዕት ይቀርብባቸው የነበሩ ንዋያት፣ ካህኑ ይለብሱት የነበረው፣ እንዲሁም ሁለት መለከቶችን ጭምር ያሳዩአቸዋል፡፡
አስቀድሞ ለጉብኝት ካናዳ ሄዶ በነበረበት ጊዜ፣ ከአንድ ጌጣጌጥ መደብር ለመገብየት ገብቶ ሳለ፣ ሻጭቱ “ለአንተ የሚሆን ልዩ ዕቃ ና ላሳይህ” ብላ ወደ ሌላ ክፍል ወስዳው ከብር የተሰራ የእሥራኤላውያን ቀንደ መለከት ሥል የተንጠለጠለበት ጌጥ፣ ከታቦቱ ጋር የማይጠፋ እንደነበር ገልጻለት፣ እንዲገዛ አድርጋው ነበር፡፡
ጂም ራንኪን በዚህ የጌጣጌጥ መደብር ውስጥ ይህን ከገዛበት ዕለት በፊት በነበረው ሌሊት ነው በእንቅልፉ ውስጥ ሳለ፣ የቃልኪዳኑን ታቦት ለምን እንደማይፈልገው የተጠየቀው፤ እሱ እንደተረከው። ደንግጦ ባነነ፣ ያ ጥያቄ ሲያስጨንቀው ቆየ፡፡ ጧት ተነሳ፣ ከውሎው ተመልሶ ጌጣጌጥ ሊገበይ በገባበት ነበር፣ ያ የቀንደ መለከቱን የብር ጌጥ የገዛው፡፡ በጣና ቂርቆስ ገዳም ከነዚያ ንዋያት በተጨማሪ ኢየሱስ ከእናቱ ጋር እዚያ እንደተቀመጠ የሚተርከውን መጽሐፍም አሳዩአቸው፡፡ ራንኪን ጥቂት ገጾችን ፎቶ አነሳ፡፡
በዚሁ የኢትዮጵያ ቆይታቸው አብቅቶ አሜሪካ ሲገቡ፣ ያን በፎቶ የያዙትን የግእዝ ቃል ተርጓሚ ፈለጉ፡፡ ያገኟቸው ኢትዮጵያዊ ቄስ አስቀድሞ እንደተገለፀው ያንኑ ታሪክ የሚናገር መሆኑን ገለፁለት፡፡
አበቃ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በኢትዮጵያ የቱ ጋ ነው ያለው?
ይሄን ሾላ በድፍን የተወበትን መጽሐፍ ነው “ኢየሱስ ክርስቶስ በኢትዮጵያ” ሲል የሰየመው። መጽሐፉ ከዚህ ይልቅ ሌሎች ዓላማዎች የያዘ ይመስላል፡፡ በአክሱምና በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች ወንጌልን የመስበክ ፕሮጀክት አብረው ከተጓዙት ጋር ሲነድፉ ይገኛሉ፡፡ ከሁሉ ሁሉ የሚያስገርመው ግን ኢትዮጵያውያንን ለመስደብ እና ለመንቀፍ የመቸኮሉ ነገር ነው፡፡ በስንቱ መጽሐፍ ተጽፎ፣ በየጊዜው እየተገለፀ የሚገኘውን ይህን ጉዳይ፣ “ለምንድነው የሚደብቁት” እያለ በተደጋጋሚ ይቆጣል፡፡
ይሄም ሳያንሰው እግዚአብሔር እንዴት “በዚች ውኃዎቿ ሁሉ በበሽታ የተበከለ…” አገር የቃል ኪዳን ታቦቱን የመሰለውን ሊደብቅባት ቻለ? በማለት ሕዝቡንና ሀገሪቱን ይሰድባል፡፡
ምናልባት የዚህ መጽሐፍ አንድ ጥቅም ተደርጐ ሊወሰድ የሚችለው፣ ፀሐፊው በደርዘን ፓንቶችና ካልሲዎች ሳይቀር ወሻሽቆ በሻንጣው ደብቆ ያወጣቸውን ዓይነቶች የቅርሶች ዝርፊያ እንደሚፈፀም እና ጥበቃው ምን ያህል ልል እንደሆነ ማሳየቱ ብቻ ይመስለኛል፡፡
ሌሎች መፅሃፉን ያነበቡ ሰዎች ግን “ቢያንስ ኢየሱስ ክርስቶስ በኢትዮጵያ” እንደነበረ መገለጹን እንደ አንድ ጥቅም ቆጥረውታል፡፡
ግና የታለና እሱ?

 

Read 3753 times