Saturday, 19 October 2013 11:12

“ኔክስት ዲዛይኒንግ” ከሌሎች ሀገራት ተማሪ ለመቀበል አስቧል

Written by  መልካሙ ተክሌ
Rate this item
(1 Vote)

          በቅርቡ “ኢንተርናሽናል ስታር ፎር ኳሊቲ” የሚል ሽልማት የተሸለመው ኔክስት ዲዛይኒንግ ኢንስቲትዩት ከሌሎች ሀገራት በተለይም ከአፍሪካ ሀገራት የዲዛይኒንግ ተማሪዎች ተቀብዬ ለማስተማር አቅጃለሁ አለ፡፡ ሽልማቱ ዓለም አቀፍ ዕውቅናዬን ይጨምርልኛል ብሏል-ተቋሙ፡፡
ኔክስት ዲዛይኒንግ ኢንስቲትዩት በ1996 ዓ.ም ማስተማር የጀመረ ሲሆን በልብስ ቅድ፣ በልብስ ስፌት፣ በፋሽን እና በተያያዥ ሙያዎች በኮሌጅ ደረጃ እያስተማረ ይገኛል፡፡ ጄኔቭ የሚገኘው ቢድ ቢዝነስ ኢኒሸቲቭ፤ ኔክስት ዲዛይኒንግን የሸለመው ሰባት የጥራት መመዘኛ መርሆዎችን መመዘኛ አድርጐ ሲሆን ከነዚህም አንዱ የደንበኛን ፍላጐት እና ግምት ማርካት ነው፡፡ በርካታ የፋሽን ትርዒቶች በማቅረብም የሚታወቀው ኔክስት ዲዛይኒንግ፤ ተመራቂ ተማሪዎቹን እያወዳደረ ለአጫጭር ኮርስ ሕንድ የሚልክ ሲሆን ገንዘብ ከፍለው መማር ላልቻሉ ወገኖችም የነፃ ትምሕርት ዕድል በማመቻቸት 165 ተማሪዎች እንዳስመረቀ ከኮሌጁ የወጣው መግለጫ ያመለክታል፡፡
የትምህርት ቤቱ ባለቤት እና ሥራ አስኪያጅ ሞዴልና ዲዛይነር ወ/ሮ ሳራ መሐመድ ኦስማን በቅርቡ መሸለማቸውን አስመልክቶ “ሽልማቱ በማበረታታት ለውጥ እንድናመጣ ያደርጋል። ከሌላው ዓለም ጋርም ተወዳዳሪ ያደርገናል። ከኢትዮጵያ ውጪ ተማሪዎች እንድንቀበል ያስችለናል፡፡” ብለዋል፡፡

Read 2002 times