Saturday, 12 October 2013 13:17

“ጠበሳ 3” ለገበያ ቀረበ

Written by  መልካሙ ተክሌ
Rate this item
(38 votes)

“ወረፋ” እና “የጋብቻ ችግሮችና መፍት ሔዎቻቸው” ተመረቁ
በመምህር ታዴዎስ ግርማ የተዘጋጀው “የጋብቻ ችግሮችና መፍትሔዎቻቸው” መጽሐፍ ባለፈው ረቡዕ ምሽት በቅድስት ሥላሴ ደብር ተመረቀ፡፡ “አማኑኤል ናና” በሚለው መዝሙሩ ይበልጥ የሚታወቀው የነገረመለኮት ምሩቅ መምሕር ታዴዎስ ግርማ፣ ያሁኑን ጨምሮ ሦስት መጻሕፍትን ለንባብ አብቅቷል፡፡ በምረቃው እለት የቤተክርስቲያኒቱ ጳጳሳት ለመምሕር ግርማ “ጸሐፌ ትዕዛዝ” የሚል መጠርያ ማእረግ እንደሰጡት ለማወቅ ተችሏል፡፡ 115 ገፆች ያሉት “የጋብቻ ችግሮችና መፍትሔዎቻቸው”፣ ለሀገር ውስጥ በ25 ብር፣ ለውጭ አገራት በ12 ዶላር ለገበያ ቀርቧል፡፡
በውስጥ ደዌ ስፔሻሊስቱ በዶ/ር ኤልያስ ሳሙኤል ማቲዎስ የተዘጋጀው “ወረፋ” የግጥም መድበል ከትናንት ወዲያ ምሽት ቦሌ አካባቢ በሚገኘው ፍሬንድሺፕ ኢንተርናሽናል ሆቴል ተመረቀ፡፡

በግጥም መጽሐፉ 145 የአማርኛና ሰባት የእንግሊዝኛ ግጥሞች ተካትተዋል፡፡ ሊትማን ጀነራል ትሬዲንግ የሚያከፋፍለው የግጥም መድበል፣ ለሀገር ውስጥ በ30 ብር፣ ለውጭ ሀገራት ደግሞ በ5 ዶላር እየተሸጠ ነው፡፡
በሌላ በኩል በጥቁማስት የተዘጋጀው “ጠባሳ ፫ የማማለል ጥበብ” ሰሞኑን ለገበያ ቀረበ፡፡ በኤች ዋይ ማተሚያ ድርጅት የታተመው ባለ 142 ገፆች መጽሐፍ በ35 ብር ይሸጣል፡፡ የኢትዮጵያ ሴት ደራስያን ማሕበር አባል በሆነችው ገጣሚ ሙሉብርሃን ሞላ የተዘጋጀው “በስተርጅና ሙሽርና” የግጥም መድበልም በሩስያ ሳይንስና ባሕል ማእከል የተመረቀው ባለፈው ሳምንት ነበር። 64 ገፆች ያሉት የግጥም መጽሐፉ፤ በ15 ብር እየተሸጠ ይገኛል፡፡

Read 13270 times