Saturday, 12 October 2013 12:59

ኢትዮጵያዊቷ ፋሽን ዲዛይነር በላስ ቬጋስ

Written by  አበባየሁ ገበያው
Rate this item
(30 votes)

ከሁለት ወር በፊት ለአንድ ሳምንት ሥልጠና ወደ አሜሪካ ተጉዤ ነበር፡፡ ስልጠናዬን እንዳጠናቀቅሁ ወደ አገሬ አልተመለስኩም፡፡ ወዳጅ ዘመድ እየተቀበላለ ሲጋብዘኝና አስደናቂ ቦታዎችን ሲያስጎበኝ ለሁለት ወራት ያህል ቆይቻለሁ፡፡
አንድ ምሽት ሁለት ዘመዶቼ በላስ ቬጋስ ታዋቂ ወደሆነው “ግሪን ቫሊ ካዚኖ” ይዘውኝ ሄዱ - እራት ሊጋብዙኝ፡፡ የተንጣለለ የምግብ አዳራሽና ደረጃውን የጠበቀ የመኝታ ክፍል ያለው ነው፤ ካዚኖ ቤቱ፡፡ አሁን በህይወት የሌለው የፖፕ ሙዚቃ ንጉስ ማይክል ጃክሰን ሆቴሉን ያዘወትረው እንደነበር ሰምቻለሁ፡፡ የእራት ቡፌው ርዝመት እንኳን በእግር በአይን ዓይቶ ለመጨረስ ይደክማል። በተንቆጠቆጠው የምግብ አዳራሽ ውስጥ ከዘመዶቼ ጋር እራት እየበላን፤ እኔ ስለ አገር ቤት፣ እነሱ ስለ አሜሪካና በተለይ የቱሪስቶች ከተማ ተብላ ስለምትጠራው ቬጋስ እያወጋን ሳለ ድንገት ዓይኔ አዳራሹን አቋርጠው የሚያልፉ ዘናጭ ወጣት ሴቶች ላይ አረፈ፡፡ እንኳንስ ወንድን ሴትንም የሚያፈዙ እንስቶች ናቸው፡፡ ሞዴሎች እንደሆኑ መገመት አላቃተኝም፡፡ ወዴት እንደሚሄዱ ለማወቅ ጓጓሁ። እራቴን አቋረጥኩና ዘመዶቼን ይቅርታ ጠይቄ ተከተልኳቸው፡፡ ለካስ የፋሽን ትርኢት የሚያሳዩ ሞዴሎች ናቸው፤ ቆነጃጅቱ፡፡ በአንድ መለስተኛ አዳራሽ ውስጥ ታዳሚው ጥቅጥቅ ብሎ ውበትና ፋሽንን ይኮመኩማል፡፡ ይሄን የፋሽን ትርኢት ለየት የሚያደርገው በፋሽን ዲዛይነር የ4ኛ ዓመት ተመራቂዎች የተዘጋጀ መሆኑ ነው፡፡ መድረኩ ላይ ዲዛይነሮች በተራቀቁበት አልባሳት ተውበው፣ ሰበር ሰካ የሚሉትን ሞዴሎች ፈዝዤ ስመለከት፣ የአበሻ ሴት ስም ሲጠራ የሰማሁ መሰለኝ፡፡ በዙሪያዬ ግን አንድም የአበሻ ፊት ያላት ሴት አላየሁም። “ፍሬ ህይወት ተክሌ ወንዳፍራሽ” ---- ስሙ በድጋሚ ተጠራ፡፡ አልተሳሳትኩም፣ በ20ዎቹ ዕድሜ መጨረሻ ግድም ያለች ወጣት ወደ መድረኩ ስትወጣ ተመለከትኩ፡፡ ሞዴሎቹ ከተዋቡበት አልባሳት መካከል ጥቂቶቹ በእሷ ዲዛይን የተደረጉ ናቸው፡፡ ከመድረኩ ስትወርድ ጠብቄ አነጋገርኳት፡፡
ከኢትዮጵያ ነው የመጣሁት፡፡ አዲስ አድማስ የሚባል ጋዜጣ ታውቂያለሽ? እዛ ነው የምሰራው። ፈቃደኛ ከሆንሽ ቃለመጠይቅ ላደርግልሽ እፈልጋለሁ …
አዲስ አድማስ! ኦ ማይ ጋድ! (ባለማመን ስሜት)…ከአገሬ.. ከኢትዮጵያ! … ያውም በደስታዬ ቀን! የሚገርም ነው… …ኦ.. ምን ልበልሽ … በኔ ቦታ ብትሆኝ ሊሰማሽ የሚችለውን አላውቅም … በጣም ነው ደስ ያለኝ … ይታይሽ ቬጋስ ውስጥ በአማርኛ ኢንተርቪው ስትደረጊ፤ ያውም አገር ቤት እያለሁ በጣም በምወደው ጋዜጣ..ኦ አምላኬ..እንዴት ትወደኛለህ!!
የፋሽን ዲዛይን ተመራቂዎች መሆናችሁን ሰምቻለሁ….
ትክክል ነሽ፡፡ ከአስራ አምስቱ ተማሪዎች እኔ ብቻ ነኝ ኢትዮጵያዊ፡፡ ስራዎቼን መድረክ ላይ/ራንዌይ/ ሳያቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ነው (በደስታ ዓይኗ እንባ እያቀረረ) እንደምታይው ሁላችንም ተመራቂዎች ነን፡፡ በትርኢቱ ልቆና ጎልቶ የታየው ስራ ግን የእኔ ነው… ሞዴሎች የኔን ስራ ለብሰው ሲወጡ ከፍተኛ ጭብጨባና አድናቆት አግኝተዋል። እባክሽ አንድ ደቂቃ ስጪኝ..አንዳንድ ነገሮቼን ልጨርስና እራት እየበላን እናውራ..
(ፋሽን ዲዛይነሯ ፍሬሕይወት ተክሌ፤ ነገሮቿን እስክትጨርስ እኔም ከዘመዶቼ ጋር የጀመርኩትን እራት በልቼ ከአንድ ሰዓት በኋላ ለመገናኘት ተስማማን፡፡)
ከአንድ ሰዓት በኋላ ተገናኝተንም ወጋችንን እንዲህ ቀጠልን-
ፋሽን ዲዛይነር የመሆን ፍላጐት ያደረብሽ መቼ ነው?
የልጅነት ህልሜ ነው፡፡ አሁን ያንን ህልሜን በአንድ ደረጃ አሳድጌዋለሁ፡፡ በሙያው ሰልጥኜ የመመረቂያ ስራዬን ነው ዛሬ ያቀረብኩት፡፡ ስራዎቼን ታዋቂ ሞዴሎች ለብሰውት ስመለከት የተሰማኝን ደስታ አልነግርሽም…
ስራዎችሽ ለቀጫጭንና ለረጃጅም ሴቶች የታለሙ ይመስላሉ …
/ሳቅ/ የልብስን ውበት ማየት የሚቻለው እኮ ቀጭን ሰው ላይ ነው ይባላል፡፡ እንዳየሽው ዲዛይን የማደርጋቸው አልባሳት ወገባቸው ቀጭን፣ ጎናቸው ሰፋና ወጣ ያለ፣ እግራቸው ደግሞ ጠባብ (ቫጊ ስታይል) ነው፡፡ ጨርቆቹ የመልክአ ምድር ቅርፅ አላቸው… ላንድስኬፕ ይመስላሉ፡፡ ቀለማቸው ኧርዝ ወይም የመሬት ውበት አይነት ነው፡፡ እሱን እሱን አንድ ላይ ቀላቅዬ ነው ኮሌክሽኑን የሰራሁት፡፡ የሳመር ልብሶች በጣም ይማርኩኛል፡፡ በቃ ማራኪና ሳቢ ግን ሲምፕል (ቀለል ያለ) ነገር ይመስጠኛል…
በዛሬ ቀን ታዲያ ምነው ብቻሽን ሆንሽ?
/ሳቅ/ ይኼው አንቺን ጣለልኝ..ጓደኛዬም አለ፡፡ አስተማሪዬንም አይተሻታል አይደል? በስራዬ በጣም ኮርታብኛለች፡፡ ከሁሉም በላይ ግን ተመልካቾች በስራዎቼ እንዴት እንደተሳቡና እንደተመሰጡ አልነግርሽም፡፡ አይተሻቸው የለ!
በቀጥታ ወደ ፋሽን ዲዛይን ትምህርት ነው የገባሽው ወይስ ሌላ ትምህርት ተምረሻል?
እዚህ ደረጃ ላይ ለመድረስ ብዙ ፈተናዎችን አልፌአለሁ፡፡ ፍቅሩ ሳይኖር ዝም ብለሽ አትዳክሪም። ኢትዮጵያ ሳለሁ አካውንቲንግ ተምሬአለሁ፡፡ ሳላውቀው መስመሬን ስቼ ነበር። ወደ አሜሪካ ከመጣሁ በኋላ ነው በምፈልገው አቅጣጫ መጓዝ የጀመርኩት፡፡ ልጅ እያለሁ ያገኘሁትን ጨርቅ እያነሳሁ ስሰራ፣ ስቦጭቅ ስጥል ነበር የምውለው፡፡ ይሄ የምታይው ጠባሳ (ቀሚሷን ገልጣ ጭኗን እያሳየችኝ) የሆነ ጫማ በእኔ እግር ልክ ለመስራት በምላጭ ስቀድ ነው እንደዚህ ሰውነቴን የቆራረጥኩት፡፡ አምስተኛ ክፍል እያለሁ እናቴ ከቤት ወጣ ስትልልኝ ጣሪያ ላይ ቦንዳ አየሁና ለምን ለጸጉሬ ጌጥ (ቲያራ) አልሰራም ብዬ ቦንዳውን አውርጄ በጭንቅላቴ ለክቼ ቆረጥኩት፡፡ ከዚያም እናቴ የምትለብሰውን ውድ ከፋይ ቀሚስ ቀድጄ ቦንዳው ላይ ቆንጆ አድርጌ ሰፋሁት፣ ለጌጥ ፅጌሬዳ ከእላዩ ላይ አደረግሁበት፡፡ እናም ቆንጆ ቲያራ ሰራሁ። ትምህርት ቤት ጓደኞቼ ሲያዩት ተረባረቡበት። “ቲያራሽ ሲያምር…ከየት ሃገር መጥቶልሽ ነው›” አሉኝ፡፡ ራሴ እንደሰራሁት ስነግራቸው በጣም ተደነቁብኝ፡፡ ለዚህ ሁሉ ግን መሰረቱ እናቴ ናት። ዘናጭ ነበረች፤ ፋሽን ተከታይ፡፡ እሷ ናት ለፋሽን ዓይኔን የገለጠችልኝ፡፡
እናትሽ አልተቆጡም---- ቀሚሳቸውን ቀደሽባቸው?
ያን ግዜ ምንም አልተባልኩም፡፡ የሚገርምሽ እናቴ ስራዬን አድንቃ ይሁን እንዳላየች ሆና አልፋኝ አላውቅም … ምንም አላለችኝም፡፡ ግን ለምን ዝም እንዳለችኝም ጠይቄያት አላውቅም፡፡ ያውም እኮ የምትለብሰው ቀሚስ ነበር፡፡ ከፋይነቱና ልስላሴው ዛሬም ድረስ ከህሊናዬ አልጠፋም፡፡
አገር ቤት አካውንቲንግ መማርሽን ነግረሽኛል፡፡ ሰራሽበት ወይስ ውሃ በላው?
ሃሃሃሃ--- (ሳቅ) እውነትም ውሃ በላው፡፡ 12ኛ ክፍል ውጤት ስላልመጣልኝ ነበር ቤተሰብ ተፈሪ መኮንን ት/ቤት ገብቼ እንድማር የገፋፋኝ። ይሁንና በአካውንቲንግ ተመርቄ ከወጣሁ በኋላ አልሰራሁበትም፡፡ አንድ ቀን ከጓደኛዬ ጋር ከቡልጋሪያ የሙሽራ ልብስ እያመጣች የምታከራይ ቡልጋሪያዊት ቤት ሄደን፣ ከጂንስ ሱሪዬ የሰራሁትን ቦርሳ እጄ ላይ አየችው፡፡ ጫማም ሰርቼለት ነበር። ቡልጋሪያዊቷ በጣም አድንቃ እንድሰራላት ጠየቀችኝ፡፡
ሰራሽላት?
ያኔ እኔ መስፋት አልችልም ነበር፡፡ ዲዛይኑን በእጄ ከሰራሁ በኋላ ልብስ ሰፊ ቤት ወስጄ ስሩልኝ እላቸዋለሁ፡፡ እሷ ስራዬን ካየች በኋላ ‹‹በኤሌክትሪክ እና በማንዋል የሚሰራ የልብስ ስፌት ማሽን ስላለኝ አሳይሻለሁ›› አለችኝ፡፡ እናም ስፌት እስዋ ጋ ተማርኩ፡፡ ከዛ ላይፍ (ህይወት) ተቀየረ፡፡ ያኔ ሲመሽ እንኳን አይጨንቀኝም ነበር፤ ለብሩ አይደለም የምሰራው፣ ለደስታዬ ነው፡፡ አንድ ቀን ለሙከራ ብላ አንድ የሙሽራ ልብስ ስሪ ብላ ሰጠችኝ፡፡ ቬሎ ያለው የሚጎተት የሙሽራ ልብስ ነው፡፡ “እኔ ሞክሬ አቅቶኛል” ብላ ሰጥታኝ ሄደች፡፡ ከሄደችበት ስትመለስ ሰርቼ ጨርሻለሁ፡፡ በጣም ተገረመችና ወዲያው እሷ ጋ ቀጠረችኝ፡፡
ከእሷ ጋ ምን ያህል ጊዜ ሰራሽ?
ለአንድ ዓመት ያህል ነው የሰራሁት … ግን ጊዜ አገኘሁ --- .ከራሴ ፍላጐትና ውስጣዊ ስሜት ጋር ተዋወቅሁ፣ የምወደውን ነገር በቅጡ መረመርኩ። ለጓደኞቼ ቦርሳ እየሰራሁ ሁሉ እሰጥ ነበር፡፡ ለህፃናት ለየት ያሉ ልብሶችን እሰራለሁ፡፡ በቃ ህይወት እየጣፈጠኝ መጣ፡፡ ደስተኛ ሆንኩ። ሊገርምሽ ይችላል..ለጓደኞቼ ቦርሳ ስሰራ አንድም ቀን አስከፍያቸው አላውቅም፡፡ በቃ የሰራሁትን ይዘውት ሳይ ደስ ይለኝ ነበር፡፡
እንዴት ነው ወደ አሜሪካ የመጣሽው?
ዲቪ ደርሶኝ ነው፡፡ አገሩን እስካውቀው፣ ስራ እስክጀምርና ሁኔታዎችን እስከማስተካክል ሶስት ዓመት ፈጀብኝ፡፡ ስራ ከጀመርኩ በኋላ በህልሜም በውኔም የሚያባንነኝን፣ ከልቤ የማፈቅረውን የፋሽን ዲዛይኒንግ ሙያ ለመማር ዩኒቨርስቲ ገባሁ። አራት አመት ተምሬ ይኼው በድግሪ ለመመረቅ በቃሁ፡፡
የዲቪ እድሉን ስታገኚ..የፋሽን ዲዛይን እማራለሁ ብለሽ ወስነሽ ነበር?
መቶ በመቶ ነዋ! ኢትዮጵያ እያለሁ አሜሪካ ውስጥ የሙሽራ ልብስ ዲዛይነር ስለሆነችው አምሳለ በሬድዮ ሰምቼ ነበር፡፡ መፅሄት ላይም ታሪኳን አንብቤያለሁ፡፡ ከዚያ በኋላ ዲቪውም ሳይደርሰኝ “በአገሬ ላይ በዚሁ ሞያ ትልቅ እሆናለሁ”› የሚል ህልም ነበረኝ፡፡ ዲቪውን ስሞላም “አሜሪካ ሄጄ ፋሺን ዲዛይን እማራለሁ፡፡ የፋሽን አገር በሆነችው ኒው ዮርክም በትልቅ ኩባንያ ውስጥ እሰራለሁ” ብዬ ለራሴ ቃል ገብቼ ነበር፡፡ ይኼው አሁን ስመጥር በሆነ ኩባንያ ውስጥ ተቀጥሬ ወደ ኒው ዮርክ ልሄድ ነው፡፡
ለአራት ዓመት እየሰሩ መማሩ አልከበደሽም?
“አይኤዲቲ ኢንተርናሽናል አካዳሚ ኦፍ ዲዛይኒንግ ቴክኖሎጂ” ነው የተማርኩት፡፡ ትምህርቱ ከስራ ጋር በጣም ፈትኖኛል፤ እንቅልፍ አልነበረኝም። ትምህርቱ የማታ ስለነበር ክላስ ሆኜ እኩለ ሌሊት ያልፋል፡፡ ከዛ ደግሞ በሌሊት ስራ መግባት አለብኝ። የማስረክባቸው ፕሮጀክቶች ነበሩ፤ ልብስ መስፋት፣ ዲዛይን ማድረግ፣ የገበያ ጥናት፣ የገበያ ዕቅድ …ብዙ ነው፡፡ የጊዜ ገደብ ደግሞ አለ እናም ሳልተኛ ለንቃት ቡናዬን እጠጣና ወደ ስራ ሩጫ ነው፡፡ አየሽ… እዚህ እንደ ኢትዮጵያ የፈለግሽውን ለማድረግ ጊዜ የለሽም። ብቻ ብዙ ፈተና አልፌ ነው ለዚህ የበቃሁት፡፡
ወደ ቬጋስ እንደመጣሽ፣ ስራሽ ምን ነበር?
ቀኑን ሙሉ ቆሜ ነው የምውለው፤ ካሸር ነበርኩ፡፡ ግን አንድ ቀን ሁኔታዎች እንደሚስተካከሉ ስለማስብ እንቅልፍ ማጣቱና ድካሙ ምንም አይመስለኝም ነበር፡፡
ፋሺን ዲዛይነርነት ስትማሪ በልምድ ከምታውቂው የተለየ ምን አዲስ ነገር አገኘሽበት?
ፋሺን ዲዛይነር ለመሆን ስዕል መቻል ይጠበቅብሻል፡፡ በአንድ ነገር ኢንስፓየርድ (መነሸጥ) መሆንም አለብሽ፤ ይሄን ሁሉ አላውቅም ነበር፡፡ ት/ቤት ስገባ ግን “ስዕል መሳል አለብሽ፤ መጀመሪያ ዲዛይን ካላደረግሽው እንዴት ይሰራል?” አሉኝ፡፡ ትምህርት ስጀምር አስተማሪው ለትምህርቱ ተብሎ ከተዘጋጀው መጽሄት ውስጥ የወደዳችሁትን ስዕል መርጣችሁ አምጡ አለን፡፡ ከዚያ የመረጥነውን “መልሳቸው ሳሉት” ተባልን፡፡ “እኔ ስዕል ስዬ አላውቅም፤ አራት በአራት የሆነ ጠረጴዛ እንኳን የሳልኩበትን ጊዜ አላስታውስም” አልኩት፡፡ እንደምንም እንድስል ገፋፋኝ፡፡ በኋላ የሳልኩትን ሲያይ ተገረመ፡፡ አንዳንዴ ተሰጥኦዋችንን አናውቀውም፤ እስክንሞክረው ድረስ፡፡ እናም ይህን ማወቄ ለህይወቴ አንድ ነገር ጨመረልኝ፡፡
ምን ዓይነት ልብሶች፣ ቦርሳ … ትመርጪያለሽ?
እኔ የማምነው በብራንድ አይደለም፣ በኳሊቲ (ጥራት) ነው፡፡ ለምሳሌ ጫማ --- ከቆዳ የተሰራ ብገዛ እመርጣለሁ፤ ለረጅም ጊዜ እጠቀምበታሁ፤ ሲታይም ደስ ይላል፡፡ ብዙ ሰው ግን ብራንድ ላይ ያተኩራል፡፡
የሰዎችን አለባበስ ስታይ “ምነው እንደዚህ በለበሰች ኖሮ…”ትያለሽ?
በጣም እላለሁ፡፡ ላስቬጋስ ግን ይሄን ያህል የሚነሽጥሽ (ኢንስፓየር የሚያደርግሽ) ሰው የለም፡፡ ኒው ዮርክ ሰብ ዌይ ባቡር ውስጥ ስትገቢ አፍሽን ከፍተሽ ነው የምትቀሪው፤ ድንቅ አገር ነው፡፡ ሴቶቹ በጣም ዘናጮች ናቸው፡፡ አንዳንዴ ፈዝዤ ሳያቸው እብድ ልመስልሽ ሁሉ ይችላል፡፡ በቃ አይኔ እነሱ ላይ ይንከራተታል፡፡ ፋሽን በጣም አደንቃለሁ፤ ሁሌም ጭንቅላቴ በውበት ይሞላል፡፡
በወንዶች ነው በሴቶች ፋሽን የምትማረኪው?
በሴቶች ነው፡፡ ስንማር እርሳስና ወረቀት ከእጃችሁ አይለይ ይሉን ነበር፡፡ ሀሳብ መቼ እንደሚመጣ አታውቂም..ኒውዮርክ አለባበሳቸው..ያማልልሻል.. የፋሽን አገር ነው፡፡ ከተፈጥሮ ጋር ተናበው ነው የሚለብሱት፡፡ ይሄ ኢንስፓይሬሽናል ቦርድ ይባላል፡፡ (ትልቅ የክብር መዝገብ የሚመስል ጥራዝ አውጥታ እያሳየችኝ) ዛፉ፣ ሳሩ፣ ..አሁን ይሄ አይማርክም ? ሳሩ እንደመድረቅ ቢልም ውስጥ ውስጡ አረንጓዴ ነገር አለ፡፡ አበባው የመከር ወራት ሲሆን እንዲህ ያለ ቀለም ይይዛል፡፡ መልክአ ምድሩ፣ ሰማዩ፣ አፈሩ፣ ወፎች ክንፍ ዘርግተው ሲበሩ ክንፋቸው ውስጥ የሚፈጠረው ዚግዛግ… የልብስ ዲዛይኖችን ከእነዚህ ነው የምፈጥረው፤ ኢንስፓየር ያደርጉኛል፡፡
ምን ዓይነት ቀለም ያለው ልብስ ትወጂያለሽ? ዝም ያለ ወይስ ደማቅ (የሚጮህ) ቀለም?
ዝም ያለ ልብስ አልወድም፤ የሆነ ነገር መናገር አለበት፡፡ ብራይት (የፈኩ) ቀለሞች ... በተለይ ሎሚ ቀለም … ነፍሴ ነው፡፡ በአጠቃላይ አይን የሚገቡ ቀለሞችን እወዳለሁ፡፡
“ሲዝን ፋሽን ከለር” የሚባል እንዳለ ሰምቻለሁ…
አዎ-- በየዓመቱ የፋሽን ከለር አለ፡፡ 2013 ዓ.ም ፋሽኑ ኤምሮን ግሪን (ጥቁር አረንጓዴ) ቀለም ነበር፡፡ 2014 ዓ.ም የወፍ ከለር ነው፤ ማለቴ ላይት ግሪን (ፈዘዝ ያለ አረንጓዴ) … ሎሚ ቀለም፡፡
ኒው ዮርክ ልሄድ ነው ብለሽኛል ... ሥራ አግኝተሽ ነው?
አዎ፤ “ላቭኤብል ሎላ” አዲስ የልጆች ልብስና የአሻንጉሊቶች ኩባንያ ውስጥ ነው ስራ የምጀምረው፡፡ የስራ ልምምድ (ኢንተርንሺፕ) የወጣሁትም ኒው ዮርክ ነው፡፡ ‹‹ሜጊኖሪስ ኩትር›› እና “አታር ኒው ዮርክ” ኩባንያዎች ውስጥ በተለማማጅነት ሰርቻሁ፡፡ አስተማሪዬ የምትተማመኝባት ተማሪ ላኪ ስትባል እኔን ላከችኝ፡፡ የዲዛይን ኮርስ ውጤቴ “ኤ ፕላስ” ነው። በክፍል ውስጥ ባለኝ ተሳትፎና ችሎታ ነው ወደ ኒው ዮርክ ተጉዤ በርካታ ልምዶችን ለመቅሰም የቻልኩት፡፡ ኩባንያዎቹ ለታዋቂ ሰዎችና ለሃይ ኢንድ (ለታዋቂ ብራንዶች) ሳምፕል የሚሰሩ ናቸው። ወደፊት በግሌ ፋሽን ሾው ማቅረብ እፈልጋለሁ። ይህ የሚሆነው ግን የራሴን ብራንድ ፈጥሬ ነው፡፡
አሁን ተቀጥሬ ስሰራ፣ እንዴት ነው ኢንዱስትሪው “ራን” የሚያደርገው? የሚለውን አጠናለሁ፡፡ አንድ ቀን የራሴን ቢዝነስና ብራንድ እንደምፈጥር እተማመናለሁ፡፡ ሌላ ጊዜ ከአንቺ ጋር ስገናኝ ብዙ የራሴን ነገሮች ጀምሬ ታገኝኛለሽ፡፡ የሚገርምሽ የኒውዮርኩን የስራ እድል ያገኘሁትም በአስተማሪዬ አማካኝነት ነው፡፡ አንድ ቀን ደወለችልኝና “ስራ አገኘሁልሽ” አለችኝ
“የት ነው?” አልኳት፡፡
“”ቬጋስ”
”እኔ የምፈልገው ኒው ዮርክ ነው”
‹‹ኒው ዮርክ ሰው ታውቂያለሽ?››
“አላውቅም፤ ግን እዛ ነው የምፈልገው” አልኳት። በድፍረቴ ተገረመች፡፡
ከሳምንት በኋላ አገኘችኝና “ኒውዮርክ ሰው ይፈለጋል፤ ትሄጃለሽ?” አለችኝ፡፡ የተመኘሁትን አገኘሁ፡፡ ይሄ እድል ቀላል እንዳይመስልሽ፡፡ ከአለማቀፍ እውቅ ዲዛይነሮች ሲቪ ጋር ነው ሲቪዬ (ብቃትና ችሎታዬ) የተመዘነው፡፡ ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፌ አሁን አገሬን በአለማቀፍ መድረክ ለማስጠራት ጉዞ ጀምሬአለሁ፡፡ በኩባንያው ውስጥ ኢትዮጵያዊ እኔ ብቻ እንደሆንኩ ተነግሮኛል፡፡
ደሞዙ እንዴት ነው?
በሰዓት 15 ዶላር (300 ብር ገደማ) ነው፡፡ ጀማሪ ስለሆንኩ በጣም ጥሩ ደሞዝ ነው፡፡ ያው የኒው ዮርክ ኑሮ ግን ከባድ ነው፤ እጅግ በጣም ከባድ! እኔ ግን ነገን ስለማስብ አያስጨንቀኝም፡፡
የራስሽን ቢዝነስ የመጀመር ዕቅድ እንዳለሽ አውግተሽኛል፡፡ ትኩረትሽ በአበሻ ልብስ ላይ ነው? ወይስ …
የአበሻ ቀሚስ አይደለም፤ ዘመናዊ ልብስ፣ በቃ ሁልጊዜ የሚለበስ ነው የማስበው፡፡ የምታገለውና በጣጥሼ ለመውጣት የምጥረው በዘመናዊ ዲዛይን ነው፡፡
ምናልባት ወደፊት የአበሻ ልብሶች እሰራ ይሆናል፡፡ ታያለሽ --- የራሴን ቢዝነስ ለማቋቋም ከአሁን በኋላ ሁለት ዓመት ቢፈጅብኝ ነው፡፡
በፋሽን ኢንዱስትሪው ምን ያህል ኢትዮጵያውያን ሴቶች አሉ?
ብዙ የሉም፡፡ እዚህ በደንብ የምትታወቀው ኢትዮጵያዊ ዲዛይነር አምሳለ ናት፡፡ ህልሜ እንደሷ ታዋቂ ዲዛይነር መሆን ነው፡፡ በርትተሽ ከሰራሽ ያለምሽበት ትደርሻለሽ፡፡ ስኬታማ ሆኜ የሴት ወንድ ሆና ያሳደገችኝን እናቴን ማስደሰት እፈልጋለሁ፡፡ በሚቀጥለው ስትመጪ ታይኛለሽ---የት እንደምደርስ፡፡
(ፋሺን ዲዛይነሯ ፍሬህይወት አሜሪካ ከገባች ሰባት ዓመቷ ነው)

Read 10105 times