Saturday, 05 October 2013 11:16

የዋልያዎቹና ንስሮቹ ፍጥጫ ማነጋገሩን ቀጥሏል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(11 votes)

                       ኢትዮጵያና ናይጀርያ ከሳምንት በኋላ በአዲስ አበባ ስታድዬም የሚያደርጉት የዓለም ዋንጫ ጥሎ ማለፍ የመጀመርያ ጨዋታ በከፍተኛ ደረጃ አነጋጋሪ ሆኖ ቀጥሏል፡፡ ዋልያዎቹ ብራዚል በምታዘጋጀው 20ኛው የዓለም ዋንጫ በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ለመሳተፍ ሲያነጣጥሩ ንስሮቹ አምስተኛ ተሳትፏቸውን አቅደዋል፡፡ ሱፕር ስፖርት ከትናንት በስቲያ በሰራው ዘገባ ዋልያዎቹ በሜዳቸውና በደጋፊያቸው ፊት ናይጄርያን ለማንበርከክ ላለፉት ሁለት ሳምንታት በዝግጅት ላይ ነበሩ፡፡ ሙሉ ዝግጅቱን ነገ የሚጀምረው የናይጄርያ ብሄራዊ ቡድን በተለይ የአዲስ አበባ የአየር ሁኔታ ሊደርስ በሚችለው ጫና ተጨናንቆ ሰንብቷል፡፡

የሁለቱን ቡድኖች ጨዋታ ለመምራት አራት ካሜሮናዊያን ዳኞች መመደባቸውን የገለፀው ፊፋ ፤የጨዋታው ኮሚሽነር ከዚምባቡዌ እንዲሁም በፊፋ ታዛቢነት የሚሰሩ ስዊዘርላንዳዊ እንደሆኑ የሴካፋ ምክር ቤት ዋና ፀሃፊ የሆኑት ኬንያዊው ኒኮላስ ሙንሶኜ በሴክሩቲ ኦፊሰርነት መመደባቸውም ታውቋል፡፡
ዋልያዎቹ ያለ የወዳጅነት ጨዋታ እየተዘጋጁ ናቸው፤ ምን ብለዋል?
ዋና አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው በመጨረሻ ምርጫቸው የሚይዟቸውን 23 ተጨዋቾችን እስከትናት በስቲያ አላሳወቁም፡፡ እስከ ነገ ድረስ ከተለያዩ የውጭ አገራት የሚቀላቀሉትን ጨምሮ 30 ተጨዋቾች ዝግጅታቸውን ይቀጥላሉ፡፡ ለናይጄርያ ጨዋታ የሚሰለፉ 23 ተጨዋቾች ስም ዝርዝርን ሰኞ መገለፁ ይጠበቃል፡፡ በጊዜያዊነት የተመረጡት 28 ተጫዋቾች 10 ከቅዱስ ጊዮርጊስ፣ 4 ከደደቢት ሲሆኑ፣ ሦስት ሦስት ያስመረጡት ደግሞ ኢትዮጵያ ቡናና የጎንደሩ ዳሽን ቢራ ናቸው፡፡ አርባ ምንጭ ሁለት ሲያስመርጥ፣ ሲዳማ ቡናና መከላከያ አንድ አንድ አስመርጠዋል፡፡ ሳምሶን አሰፋ፣ ደጉ ደበበ፣ ቢያድግልኝ ኤሊያስ፣ ሳላዲን በርጌቾ፣ አበባው ቡጣቆ፣ ምንያህል ተሾመ፣ በኃይሉ አሰፋ፣ ምንተስኖት አዳነ፣ አዳነ ግርማ እና ዑመድ ኡክሪ ክቅዱስ ጊዮርጊስ ፤ ሲሳይ ባንጫ፣ ብርሃኑ ቦጋለ፣ ሥዩም ተስፋዬና ዳዊት ፈቃዱ ከደደቢት፤ ጀማል ጣሰው፣ ቶክ ጀምስና ፋሲካ አስፋው ከኢትዮጵያ ቡና፤ ደረጀ ዓለሙ፣ ዓይናለም ኃይሉና አሥራት መገርሳ ከዳሸን ቢራ፤ ሙሉዓለም መስፍንና ገብረ ሚካኤል ያዕቆብ ከአርባምንጭ፤መድኃኔ ታደሰ ከመከላከያ፤ ሞገስ ታደሰ ከሲዳማ ቡና ከአገር ውስጥ የተመለመሉት ናቸው፡፡ ፤ ሳላዲን ሰይድ ከግብፁ ዋዲ ደጋላ፤ ጌታነህ ከበደ ከደቡብ አፍሪካ ቢድቪስት ዊትስ ፤ ሺመልስ በቀለ ከሊቢያው አልኢትሃድ እንዲሁም ፤ አዲስ ሕንፃ ከሱዳኑ አልሂላል እስከ ሰኞ ከቡድኑ ጋር እንደሚቀላቀሉ ነው፡፡

 አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ቡድናቸው ወደ የዓለም ዋንጫ ጥሎ ለማለፍ በሜዳው ለሚጀምረው የጥሎ ማለፍ ትንቅንቅ ላለፉት ሁለት ሳምንታት ሲዘጋጁ ቢቆዩም በዚሁ ጊዜ የወዳጅነት ጨዋታ በማድረግ አቋማቸውን አለመፈተሻቸው መጠነኛ ስጋት ፈጥሯል፡፡ ናይጄሪያን ከመግጠሙ በፊት ከጋና ወይም ከካሜሮን ብሔራዊ ቡድን ጋር የአቋም መለኪያ ጨዋታ ለማድረግ ታስቦ ነበር፡፡ ሁለቱም የምእራብ አፍሪካዎቹ አገራት ፕሮፌሽናል ተጨዋቾቻውን ማሳተፉ ስለከበደ ቢቀር ያሏቸው የወዳጅነት ጨዋታዎች ናቸው፡፡ ፌዴሬሽኑና ዋናው አሠልጣኝ አቶ ሰውነት ቢሻው ለዓለም ዋንጫው ጥሎ ማለፍ ከደረሱት ቡድኖች ጋር የወዳጅነት ጨዋታ እንዲደረግ ስምምነት ላይ በመድረሳቸው ነበር፡፡ በዚህም ከምስራቅ አፍሪካ ቡድኖች ጋር በወዳጅነት ጨዋታዎች ያለው እድልን ለመጠቀም አልተቻለም፡፡ ግብፅ ወጭ ችላ በካይሮ ለመጫወት ያቀረበችው ጥያቄም ተቀባይነት አልነበረውም፡፡

ከጋና እና ካሜሮን ውጭ ለሌሎች ስድስት አገራት ደብዳቤ ተፅፎም ምላሽ አልተገኘም፡፡ የወዳጅነት ጨዋታ ለማድረግ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ባይሳካለትም ናይጄርያም በአውሮፓ የሚገኙ ተጨዋቾቿን ቶሎ ለማሰባሰብ ስላዳገተ ትተዋለች። በአንፃሩ ግብፅ ከሴራሊዮንና ከኡጋንዳ ጋር፤ ጋና ከጃፓን ጋር እንዲሁም ቡርኪናፋሶ ደግሞ ከቦትስዋና ጋር የወዳጅነት ጨዋታዎቻቸውን በማድረግ አቋማቸውን ፈትሸዋል፡፡ ዋሊያዎቹ ከንስሮቹ ጋር የሚያደርጉት ጨዋታ ከቀረው የ1 ሳምንት ጊዜ አኳያ ዛሬ እና ነገ ካልሆነ በቀር በሚቀጥለው ሰሞን በየትኛውም ቀን የወዳጅነት ጨዋታ ማድረጋቸው አይጠቅምም፡፡ ተጨዋቾችን ለአላስፈላጊ ጉዳት እና የጨዋታ መደራረብ ስለሚፈጥር ነው፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ወሳኝ ተጨዋቾች ከናይጄርያ ጋር ስለሚደረገው የዓለም ዋንጫ የጥሎ ማለፍ ትንቅንቅ በተለይ ለደቡብ አፍሪካው ሱፕር ስፖርት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ንስሮቹ በአዲስ አበባ ቀላል ተጋጣሚ እንደሚጠብቃቸው ማሰባቸው አግባብ እንዳልሆነ ያስጠነቀቀው በሊቢያው ክለብ አልኢትሃድ የሚጫወተው አማካዩ ሽመልስ በቀለ ነው፡፡ ‹‹በማይጠብቁት ሁኔታ እንፎካከራቸዋለን፡፡ ዋናው የጥንካሬያችን ምስጥር በቡድን ስራ የሚገለፅ ነው፡፡ እያንዳንዱ ተጨዋች ለዓለም ዋንጫ ለመድረስ ፤ ወደ ብራዚል የመጓዝ ህልም አለው፡፡ በናይጄርያው ጨዋታ መቶ በመቶ ብቃቴን ለማሳየት ዝግጁ ነኝ›› ብሏል። አጥቂው ሳላዲን ሰኢድም ናይጄርያውያን ከኢትዮጵያ ጋር ስለተደለደሉ ደስተኛ መሆናቸውን አጣጣጥሎታል።‹‹ ውጤቱ በሜዳ ላይ የሚወሰን ነው፡፡ ናይጄርያውያን ከእኛ ጋር መጫወትን በመናፋሻ ውስጥ እንደመንሸራሸር ከቆጠሩት ልክ አይደለም፡፡ ኢትዮጵይያ ለዓለም ዋንጫ መቼም ቢሆን በቅርብ ርቀት አልነበረችም፡፡ በጥሎ ማለፉ እስከመጨረሻው ደቂቃዎች በመፋለም እንጫወታለን› በማለት ተናግሯል፡፡

ሳላዲን ከሁለት ዓመት በፊት ጋር በአዲስ አበባ በተደረገ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታ በናይጄርያ ላይ ሁለት ጎሎች ማግባቱ የሚታወስ ነው፡፡ ይህም በናይጄርያ መገናኛ ብዙሃናት በከፍተኛ ደረጃ እንዲፈራ አድርጎታል፡፡ ከሳምንት በኋላ በሚደረገው የዓለም ዋንጫ ጥሎ ማለፍ የመጀመርያ ጨዋታም ጎል እንዳያገባብን ሳላዲን ሰኢድ ይያዝ ብለው ጥሪ ያቀረቡ አሉ ፡፡ ሁለቱ ብሄራዊ ቡድኖች በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ደቡብ አፍሪካ ላይ በተገናኙበት ወቅትም አስጨንቆ ነበር፡፡ ያኔ ደግሞ በግብ ጠባቂው ቪንሰንት ኢኒዬማ ላይ ከተሞከሩት ሶስት የግብ እድሎች ሁለቱን በአደገኛ ሁኔታ የሞከረው እሱ ነበር፡፡በደቡብ አፍሪካው ክለብ ዊትስ መጫወት ከጀመረ ሶስተኛ ወሩን የያዘው ጌታነህ ከበደም ከጉዳቱ በቂ ጊዜ ወስዶ በማገገም ከናይጄርያ ጋር በአዲስ አበባ የሚደረገውን ጨዋታ በጉጉት እየተጠባበቀ መሆኑን ለሱፕር ስፖርት ገልጿል፡፡ ከሴንተራል አፍሪካ ጋር በዓለም ዋንጫ የመጨረሻ የምድብ ማጣርያ የተደረገው ጨዋታ ስላመለጠው የቆጨው ጌታነህ ‹‹የአፍሪካን ሻምፒዮን እንደምንገጥም የታወቀ ነው፡፡

በቡድናችን ባለው የአንድነት መንፈስ ወደ ዓለምን ዋንጫ ለማለፍ የያዘነውን ህልም እናሳካለን› ብሏል፡፡ ሱፕር ስፖርት እንደዘገበው ጌታነህ ከበደ ከጉዳቱ በማገገም ለሳምንቱ ጨዋታ ይደርሳል። በደቡብ አፍሪካው ክለብ ቢድቪስት ዊትስ 6 ጨዋታ አድርጎ አራት ጎሎች ማግባቱ ግብ የማደን ብቃቱን ወቅታዊ እንደሚያሳይ ጠቅሶ በናይጄርያ ላይ ጫና በመፍጠር ለኢትዮጵያ ቡድን ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ብሎ ግምት ሰጥቶታል፡፡ ጌታነህ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በተሰለፈባቸው 19 ጨዋታዎች 7 ጎሎችን ከመረብ ያሳረፈ ነው፡፡ በአፍሪካ ዋንጫ በሰራናቸው ሁለት ስህተቶች ናይጄርያውያን ሁለት ፍፁም ቅጣት ምቶች አግኝተው ማሸነፋቸውንና በቀይ ካርድ መሰናበቱን ያስታወሰው ግብ ጠባቂው ሲሳይ ባንጫ ነው፡፡
‹‹ስህተቶችን አንደግምም ናይጄርያን ለመበቀል በሜዳችን ከምናገኘው አጋጣሚ የተሻለ ሁኔታ የለም፡፡ በደጋፊያችን ፊት በአፈራችን ላይ ነው የምንጫወተው፡፡በደንብ እናሸንፋቸዋለን።›› ብሎም ለሱፕርስፖርት ተናግሯል፡፡ ዚስዴይ የተባለ የናይጄርያ ጋዜጣ የዘገበው ምን ያህል ተሾመ ለአዲስ ጉዳይ መፅሄት የሰጠውን አስተያየት ጠቅሶ ነው ፡፡ ተጨዋቹ ለመጀመርያ ጊዜ በዓለም ዋንጫ ተሳትፎ ለማግኘት ናይጄርያ እንቅፋት አይሆንብንም እኛ የምናስበው ከናይጄርያም በላይ ነው፡፡ ዓለም ዋንጫ ገብተን ከስፔንና ከአርጀንቲና ጋር ባንድ ሜዳ መሰለፍን ተስፋ እናደርጋለን ማለቱን በማውሳት፡፡
ዋልያዎቹን ጥሎ ለማለፍ የጓጉት ንስሮቹና አጨናናቂ አጀንዳዎቻቸው
የናይጄርያ ብሄራዊ ቡድን በዓለም ዋንጫ ጥሎ ማለፍ ከኢትዮጵያ ቡድን ጋር መደልደሉን ካረጋገጠ ወዲህ አጠቃላይ ዝግጅቱ በአጨናናቂ አጀንዳዎች ተወጥሮ ሰንብቷል፡፡ የመጀመርያው በየጨዋታው በሚከፈለው የሽልማት ገንዘብ የተፈጠረው አተካራ ነበር፡፡ ለነገሩ ከወሳኝ ፍልሚያዎች በፊት ቡድን ለማነሳሳት ይጠቅማል ተብሎ ጥሪ በማሰማት መስራት የተለመደ አሰራር ሆኗል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾች በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ለዓለም ዋንጫ ካለፉ ለእያንዳንዳቸው የመኪና ሽልማት እንደሚሰጣቸው ቃል ተገብቶላቸዋል፡፡ በአንዳንድ አገራት እንደውም ለብሄራዊ ቡድኖቻቸው ተጨዋቾች በይፋ በሚገለፅ ሁኔታ በየጨዋታው በሚያስመዘግቡት ድል መሰረት የቦነስ ክፍያ የመስጠት አሰራር አላቸው። ከዚሁ ጋር ተያይዞ በናይጄርያ ብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾች እና በፌደሬሽኑ መካከል በየጨዋታው በሚገኝ የቦነስ ክፍያ መጠን የተፈጠረው አተካራ የሚነሳ ነው፡፡ ባለፈው ወር የናይጄርያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ባለበት የገንዘብ ችግር ሳቢያ የብሄራዊ ቡድኑ ተጨዋቾች በየጨዋታው በነፍስ ወከፍ የሚያገኙትን የቦነስ ክፍያ በ50 በመቶ ለመቀነስ ወስኖ ነበር፡፡ በየጨዋታው በነፍስ ወከፍ 5ሺ ዶላር ነው፡፡ ውሳኔው ለዓለም ዋንጫ ለማለፍ ከኢትዮጵያ ጋር በሚደርገው ግጥሚያ ላይ ተፅእኖ እንዳይፈጥር በሚል ስጋት ለመቀየር ታስቦ አስቀድሞ እንደነበረው በነፍስ ወከፍ 10ሺ ዶላር ሊደረግ ይችላል እየተባለም ነበር፡፡ ከትናንት በስቲያ የናይጄርያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት የቦነስ ክፍያውን ለመቀነስ የታሰበው ስፖንሰሮች ቃል የገቡትን ገንዘብ በቶሎ ባለመስጠታቸው እንደሆነ ገልፆ ለኢትዮጵያው ጨዋታ የተለየ የቦነስ ሽልማት አልተዘጋጀም ብሎ አተካራውን ዘግቶታል፡፡
ንስሮቹን ወጥሮ የያዘው ሌላ አሳሳቢ ጉዳይ በአዲስ አበባ ከፍተኛ አልቲትዩድ ሳቢያ በቡድኑ ላይ ሊፈጠር የሚችለው ጫና ነው፡፡ የናይጄርያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ብሄራዊ ቡድኑ ምንም አይነት የወዳጅነት ጨዋታ ሳይኖረው ቢያንስ በአቡጃ ተሰባስቦ ለአራት ቀናት ዝግጅት አድርጎ ለኢትዮጵያ ጨዋታ በዋዜማው ለመድረስ እቅድ እንዳለው አስታውቆ ነበር፡፡ በመጨረሻም በጨዋታው ዋዜማ ከመግባት ሁለት ቀን ቀደም ብሎ ለመገኘት ተወስኗል፡፡ ኢትዮጵያውያን አየራችን ለናይጄርያ ይከብዳል ብለው መዘናጋታቸው ለውጤት ይጠቅመናል ያሉም አሉ፡፡ ከፍተኛ አልቲትዩድ ባላቸው አገራት ስንጫወት የመጀመርያ አይደለም ያሉት የናይጄርያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የቴክኒክ አማካሪ ናቸው፡፡ አየሩን ለመላመድ ቢያንስ 10 ቀናት በኢትዮጵያ ለመቆየት ካልሆነልን በጨዋታው የዋዜማ ቀናት አዲስ አበባ በመግባት መጋጠማችን ተፅእኖ አይኖረውም ብለዋል፡፡ አንዳንድ የናይጄርያ መገናኛ ብዙሃናት ከሳምንት በኋላ በአዲስ አበባ የሚደረገውን ጨዋታ ከሜዳ ውጭ በአስተማማኝ ሁኔታ አሸንፎ መመለስ በመልሱ በሜዳ ጥሎ ለማለፍ እንደሚያበቃ እየመከሩ ናቸው፡፡
የናይጄርያ ቡድን በኢትዮጵያ አቻው በመጀመርያ ጨዋታ የሚሸነፍ ከሆነ በመልሱ ከባድ ፈተና ውስጥ መግባቱ አይቀርም በማለትም ስጋታቸውን ይገልፃሉ፡፡ በአሰልጣኝ ስቴፈን ኬሺ ለናይጄርያ ቡድን የተመረጡት 23 ተጨዋቾች የታወቁት ከሳምንት በፊት ነው፡፡ 18 ያህሉ በተለያዩ የአውሮፓ ሊጎች የሚጫወቱ ናቸው፡፡ በተለያዩ የአውሮፓ ሊጎች የሚጫወቱ ናይጄርያውያኑ ባለፈው አንድ ወር በየክለቦቻቸው ወሳኝ ሚና በመጫወት እና ጎሎችን ማግባታቸው ለኢትዮጵያ ጨዋታ እንደሚጠቅም ወቅታዊ ብቃት ተቆጥሯል። አምበልነቱ በግብ ጠባቂው ቪንሰንት ኢንዬማና ጆሴፍ ዮቦ መካከል እየዋለለ ነው፡፡

ይህ ፉክክርም ሌላው ንስሮችን የወጠረ ጉዳይ ነው፡፡ ጆሴፍ ዮቦ ቡድኑን በአምበልነት እንዲመራ እና ባለው ልምድ የተከላካይ መስመሩን እንዲያጠናክር በርካታ ግፊት እየተደረገ ነው፡፡ የእረፍት ግዜውን ከቤተሰቡ ጋር ለማሳለፍ ወደ አሜሪካ ተጉዞ የነበረው ስቴፈን ኬሺ በአቡጃ ከናይጄርያ የእግር ኳስ ፌደሬሽን ባለስልጣናት ጋር ስብስባ ነበረው ፡፡ በአቡጃ ቡድኑ በአገር ውስጥ በሚገኙ ተጨዋቾች ነገ ዝግጅቱን ሲጀምር በውጭ የሚገኙ ፕሮፌሽናሎች እስከሰኞ ይቀላቀላሉ ተብሎም ይጠበቃል፡፡ ስቴፈን ኬሺ የተመረጡ 23 ተጨዋቾች እስከ ፊታችን ሰኞ ሙሉ ለሙሉ ወደ ካምፕ ተጠቃለው እንዲገቡ ቀነ ገደብ ሰጥቶ ለ4 ቀናት ጠንከር ያለ ዝግጅት ለማድረግ መወሰኑ ታውቋል፡፡
ባለፉት ሶስት ሳምንታት በናይጄሪያ በርካታ መገናኛ ብዙሃናት ለኢትዮጵያ ጨዋታ ሰፊ ትኩረት እንደሰጡት ናቸው፡፡ ዘ ጋርድያን የተባለ አንድ የናይጄርያ ጋዜጣ የኢትዮጵያ የዓለም ዋንጫው ጥሎ ማለፍ እቅድን ደርሼበታለሁ ብሎ ባቀረበው ሰፊ ሃተታ ዋልያዎቹ በሜዳቸው የሚያደርጉትን ጨዋታ በማንኛውም ሁኔታ ድል አድርገው በመልሱ ጨዋታ ከሜዳቸው ውጭ አቻ በመውጣት የደርሶ መልስ ትንቅንቁን በስኬት ለመጨረስ ያስባሉ ብሏል፡፡ አሁን የማላዊ ሰልጣኝ የሆኑት እና በፊት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን ያሰለጠኑት ቤልጅማዊው ቶም ሴንትፌት የናይጄርያ ተከላካዮች ከኢትዮጵያ አጥቂዎች ከባድ ፈተና እንደሚገጥማቸው አስጠንቅቀዋል።

የናይጄርያ ቡድን በመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ብዙ ይቸገራል ያሉት ሴንትፌት ኢትዮጵያውያን ይህን ተገንዝበው ግብ ሊያስቆጥሩ ገልፀው እንደ ሳላዲን አይነት አጥቂዎች በዚህ አጨዋወት በቀላሉ ግብ ማስቆጠር እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን ደጋፊዎች በሜዳቸው የሚያሳዩት ትእይንት ለንስሮቹ ያን ያህል አያስጨንቅም ያሉት የናይጄርያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ዋና ፀሃፊ ናቸው፡፡ በደቡብ አፍሪካው የአፍሪካ ዋንጫ የነበረው ድጋፍ አሰጣጣቸውን እንደሚያስታውሱ አብራርተው በደጋፊ ብቻ ጨዋታን ማሸነፍ አይቻልም ብለዋል። ከኪክኦፍናይጄርያ መፅሄት ጋር ቪክተር ሞሰስ ባደረገው ቃለምልልስ የኢትዮጵያ ቡድን ለማሸነፍ የሚያስቸግር እና የሚከበር ነው ሲል ተናግሮ ‹‹በአፍሪካ ዋንጫ ያደረግነው ጨዋታን አስታውሳለሁ፡፡
ከባድ ፈተና ሰጥተውናል፡፡ እድለኞች ሆነን ባለቀ ሰዓት እኔ ላይ በፈፀሟቸው ሁለት ፋውሎች የተገኙት ኢሊጎሬዎችን አስቆጥሬ ነው አሸንፈን የወጣነው፡፡ በደንብ የተደራጀ፤ የአካል ብቃታቸው የጠነከረ፤ በማጥቃት አጨዋወታቸው አደገኛ እና ፈጣኖች ናቸው›› በማለት ምስክርነቱን ሰጥቷል፡፡
ለቱርኩ ክለብ ፌነርባቼ የሚጫወተው ግዙፉ አጥቂ ኤምኒኬ ለኤምቲኤን ፉትቦል ድረገፅ በሰጠው ልዩ ቃለምልልስ የናይጄርያ ቡድን ባለበት የስኬት ደረጃ ምንም መጠራጠር እንደሌለበት ተናግሮ ብራዚል እንደሚጓዙ ሙሉ እምነት እንዳለው አስገንዝቧል፡፡ ዴቪድ ማርክ የተባሉ ሴናተር መላው ናይጄርያዊ ከኢትዮጵያ ጋር የሚደረገውን ጨዋታ ለማሸነፍ እንዲያበረታታ በካቶሊክ አማኞች ለ9 ቀናት የሚዘልቅ የፀሎት ስነስርዓት እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ሴናተሩ ናይጄርያ በምንም አይነት ሁኔታ የብራዚል ዓከለም ዋንጫ ሊያመልጣት አይገባም ብለዋል፡፡ የቀድሞው የናይጄርያ አሰልጣኝ ሳምሶን ሲያ ሲያ ‹ከኢትዮጵያ ጋር በፊት ተጫውተናል፡፡ በተለይ በሜዳቸው አዲስ አበባ በጣም አስቸግረውናል፡፡ ቀላል ቡድን ብሎ ኢትዮጵያን መናቅ ለብስጭት ይዳርጋል፡፡ ከሜዳ ውጭ የሚደረገው ጨዋታ በጣም ወሳኝ ቢሆንም በሜዳም ለማሸነፍ በትኩረት መዘጋጀት ያስፈልጋል።› በማለት ምክሩን ለንስሮቹ አድርሷል፡፡
ከዓለም ዋንጫ ማግስት በኬንያ ሴካፋና በደቡብ አፍሪካ ቻን
ዋልያዎቹ በሚቀጥሉት ሳምንታት በዓለም ዋንጫ ጥሎ ማለፍ ከናይጄርያ ከሚያደርጉት የደርሶ መልስ ትንቅንቅ በኋላ በሌሎች ሁለት ዞናዊ እና አህጉራዊ ውድድሮች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል፡፡ ሰሞኑን በመካከለኛው እና ምስራቅ አፍሪካ የእግር ኳስ ምክርቤት ወይም ሴካፋ የሚዘጋጀው የ2013 ሴካፋ ሲኒዬር ቻሌንጅ ካፕ በህዳር ወር አጋማሽ በተያዘው ፕሮግራም እንደሚካሄድ ዋና ፀሃፊው ኒኮላስ ሙንሶኜ አሳውቀዋል፡፡
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ኢሳ ሃያቱ የውድድሩ የክብር እንግዳ እንደሚሆኑ የኬንያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ገልጿል፡፡ ካፍ ለውድድሩ አስፈላጊውን የቴክኒክ ድጋፍ ያደርጋል የተባለ ሲሆን ከኦክቶበር 27 እስከ ኖቬምበር 12 የሚደረገውን ውድድር ኬንያ በአራት ስታድዬሞች ለማስተናገድ ዝግጅቷን አጠናቅቃለች፡፡

በኬንያ አስተናጋጅነት በሚካሄደው የሴካፋ አገራት ሻምፒዮና ላይ ለመካፈል 12 የዞኑ አባል አገራት ማረጋገጫ ሰጥተዋል፡፡ ከማላዊ፤ ዛምቢያ፤ ዚምባቡዌ ወይም ኮትዲቯር መካከል ሁለት ተጋባዥ አገራት እንደሚኖሩ ይጠበቃል፡፡
በሌላ በኩል በደቡብ አፍሪካ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው ለ3ኛው የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮንሺፕ (ቻን) ውድድር ከሁለት ሳምንት በፊት የምድብ ድልድል ወጥቷል፡፡ በቻን ውድድር ለመጀመርያ ጊዜ የምትሳተፈው ኢትዮጵያ በምድብ 3 ከሊቢያ፤ ከጋና እና ከኮንጎ ብራዛቪል የተደለደለች ሲሆን በብሎምፎንቴይን በሚገኘው የፍሪ ስቴት ስታድዬም የምድብ ጨዋታዎቿን እንደምታደርግ ታውቋል። ጋና በቻን ውድድር ለሶስተኛ ጊዜ የምትሳተፍ ሲሆን በ2009 እኤአ የመጀመርያውን ዋንጫ ስትወስድ በ2011 እኤአ ደግሞ ሁለተኛ ደረጃ አግኝታለች። ሊቢያ ለሁለተኛ ጊዜ በቻን ስትሳተፍ ኮንጎ እና ኢትዮጵያ የመጀመርያ ተሳተፏቸው ነው፡፡ በምድብ1 አዘጋጇ ደቡብ አፍሪካ፤ ማሊ፤ ናይጄርያ እና ሞዛምቢክ፤ በምድብ 2 ዚምባቡዌ፤ ኡጋንዳ፤ ቡርኪናፋሶ እና ሞሮኮ እንዲሁም በምድብ 4 ዲሞክራቲክ ሪፖብሊክ ኮንጎ፤ ጋቦን፤ ቡርንዲና ሞውሪታንያ ተመድበዋል፡፡

 

Read 5761 times