Saturday, 28 September 2013 13:51

“የኢሬቻ በአል ሃይማኖታዊ መሠረት ያለው ነው” - ጉላ ቀነአ ለሚ

Written by  በአለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(12 votes)

በ የአመቱ መስከረም ወር ላይ የሚከበረው የኢሬቻ በአል በነገው እለት በቢሾፍቱ ሆራ አርሰዲ በደማቅ ስነስርአት ይከበራል፡፡ ይህ ክብረ በአል በኦሮሚያ ክልላዊ አስተዳደርም ትኩረት ከተሠጣቸው ህዝባዊ በአላት አንዱ ሆኗል፡፡ የብሄረሰቡ መገለጫ ባህላዊ ስርአት እንደሆነም በስፋት ትምህርት እየተሠጠበት ነው፡፡ በአንድ በኩል ባህላዊ ስርአት ብቻ ስለሆነ ሃይማኖት ሣይለይ ሁሉን ያሣትፋል የሚሉ ወገኖች ሲኖሩ በሌላ በኩል ደግሞ ሃይማኖታዊ መሠረት ያለው በአል ነው የሚሉ አሉ - ባህላዊ ስርአት ብቻ አለመሆኑን በመግለፅ፡፡
ሃይማኖታዊ መሠረት ያለው በአል ነው ነገር ግን በሂደት ከሌሎች ዘልማዳዊ ባህሎች ጋር ተቀላቅሎ ይከወናል ከሚሉትና ይህን አካሄድ ለማረምና ለማቃናት ከሚጥሩ የእምነት ተቋማት መካከል “አለማቀፍ የዋቄፈና ሃይማኖት ማህበር” በሚል የሚጠራው ይገኝበታል፡፡ ከተቋቋመ አምስት አመት ገደማ የሞላው ማህበሩ ሃይማኖታዊ መሠረት ያለው በአል ነው ብሎ ይከራከራል፡፡ የማህበሩ ሊቀመንበር የሆኑት ጉላ ቀነአ ለሚ ኢሬቻ ከዋቄፈና ሃይማኖት አንፃር ያለውን አንድምታ፣ የአከባበር ሂደቱንና ስርአቱን በተመለከተ ማብራሪያ ለዝግጅት ክፍላችን ሠጥተዋል፡፡ በአሉ በሃገር አቀፍ ደረጃ የሚከበርበት የቢሾፍቱ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ አቶ ጫላ ሶሪ በበኩላቸው ኢሬቻ ከሃይማኖታዊነቱ ይልቅ ባህላዊነቱ ያመዝናል” ከሚለው ሃሣባቸው ተነስተው ስለበአሉ የበኩላቸውን ማብራሪያ ሠጥተውናል፡፡


“የኢሬቻ በአል ሃይማኖታዊ መሠረት ያለው ነው” - ጉላ ቀነአ ለሚ
የኢሬቻ በአል አሁን ከሚንፀባረቀው የተለየ ነው እያሉን ነው …
ኢሬቻ ማለት ማምለክ እና ማመስገን ማለት ነው፡፡ ይሄን ስላደረግህልኝ፣ ከክረምት ወደ በጋ (ብራ) ስላሸጋገርከኝ አመሠግናለሁ እየተባለ ፈጣሪ የሚመሰገንበት ነው፡፡ ኢሬቻ ሠፊ አገልግሎቶች አሉት፡፡ መነሻውም በጣም የራቀ ነው፡፡ ሠው ማምለክ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የመጣ ነው። መጀመሪያ እንደውም አምልኮ የተጀመረው በኢሬቻ ነው፡፡ በተለይ የኦሮሞን ብሔር ጨምሮ በኩሽቲክ የቋንቋ ክፍል ውስጥ የሚጠቃለሉ ብሄሮች ሃይማኖቶች ከመምጣታቸው በፊት ኢሬቻ (እርጥብ ሣር) ይዘው ነው ፈጣሪያቸውን የሚለማመኑት፡፡ ኢሬቻ በእርጥብ ሣር ይወከላል፡፡
ለጋብቻ ጥያቄ በራሱ (ኢሬቻ) እርጥብ ሣር አገልግል ውስጥ ተጨምሮ ነው የሚላከው፡፡ እንግዲህ እነዚህን ነገሮች በምናይበት ጊዜ ኢሬቻ ሃይማኖታዊ ዳራ ያለው መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ ድሮ ሠዎች መልዕክተኛ ሲልኩ እርጥብ ሣር ቆርጠው በመስጠት፣ “አደራህን በፈጣሪ ስም ይህን መልዕክት አድርስልኝ” ብለው ይልኩታል፡፡ እንግዲህ ቃል በቃል ሲገለፅ፤ ኢሬቻ ሣር ወይም የተመረጡ ዛፎች ቅጠል ማለት ነው፡፡
ኢሬቻ በአመት ሁለት ጊዜ ነው የሚደረገው የመጀመሪያው ከነሐሴ መጨረሻ ጀምሮ እስከ ጥቅምት መጨረሻ ይካሄዳል፤ ሁለተኛው ደግሞ በበልግ ወራቶች ግንቦትና ሠኔ ውስጥ የሚደረግ ነው፡፡ ሁለተኛው ግን አሁን እየተረሣና እየተዳከመ ነው ያለው፡፡ ሠዎች መገንዘብ ያለባቸው ኢሬቻ ሃይማኖት አይደለም ነገር ግን ሃይማኖታዊ ክብረ በአል ነው፡፡ ለምሣሌ ጥምቀት ሃይማኖታዊ በአል ነው እንጂ ሃይማኖት አይደለም፡፡ ኢሬቻም እንዲሁ ነው፡፡
እምነቱ ምንድን ነው?
የሃይማኖቱ ስም ዋቄፈና ነው፡፡ የእምነቱ ተከታይ ዋቄፈታ ነው የሚባለው፡፡ ከዋቄፈና ሃይማኖታዊ በአላት አንዱ ኢሬቻ ነው፤ ሌሎችም ብዙ በአላት አሉ፡፡ ሌላው ከዚህ ሃይማኖታዊ በአል ጋር በልማድ አብሮ ተቀላቅሎ የሚከወን ነገር አለ፡፡ ለምሣሌ ቡና ማፍላት፣ ዛፍ ቅቤ መቀባት፣ ስለት ማግባት፣ ሽቶ ውሃ ውስጥ መወርወር የመሣሠሉ አሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ ልማዶች ናቸው እንጂ የሃይማኖቱ መርሆች የሚያዛቸው አይደሉም፡፡ ቅቤ መቀባት ግን “ሙዳ” ከሚባለው ስርአት ጋር ይያያዛል፡፡ አንድ ንጉስ ሣይቀባ እንደማይነግስ ሁሉ አንድ የማምለኪያ ቦታም ተቀብቶ እውቅና ሊያገኝ ይገባዋል፡፡ ነገር ግን አሁን እየተደረገ እንዳለው በየጊዜው ሣይሆን አንድ ጊዜ ብቻ ነው ይህ ስርአት ተፈፃሚ የሚሆነው። አንድ ንጉስ በየጊዜው እንደማይቀባ ሁሉ አንድ የተመረጠ የማምለኪያ ስፍራም በየጊዜው ሊቀባ አይገባም፡፡ ቀቢውም ማንኛውም ሠው ሣይሆን የተመረጠ መሆን አለበት፡፡
የኦሮሞ ህዝብ የተለያዩ ሃይማኖቶች ተከታይ ነው፡፡ በክርስትናውም በእስልምናውም ሃይማኖት ውስጥ ያሉ አሉ፡፡ እነዚህ እንዴት ነው የዚህ በአል ተሣታፊ የሚሆኑት?
በምሣሌ ልንገርህ፡- እኔ ክርስቲያን አይደለሁም፤ ዋቄፈታ ነኝ፡፡ ነገር ግን የመስቀል ደመራ ስነስርአትና የጥምቀት በአል ላይ እገኛለሁ፡፡ ለኔ ይሄ ባህሌ ነው፡፡ ስለዚህ ክርስቲያን ለሆኑ ኦሮሞዎች፣ ይሄ ሃይማኖታቸውን ሣይለቁ ባህላቸው መሆኑን ተረድተው ተሣታፊ ሊሆኑበት ይችላሉ ማለት ነው። ለእነሡ ባህል ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ባህል ነው እንጂ ሃይማኖታዊ መሠረት የለውም ማለት የለባቸውም፡፡ ኢሬቻ ሃይማኖታዊ መሠረት ያለው በአል ነው፡፡ የማንኛውም ሃይማኖት ተከታይና ፍላጐቱ ያለው ሁሉ የመሣተፍ መብቱ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የእሬቻ በአል ከዋቄፈና ሃይማኖት በአላት አንዱ መሆኑን መካድ የለበትም ወይም አቅጣጫውን እንዲስት መደረግ የለበትም፡፡
የበአሉ አከባበር ምን ይመስላል?
የኦሮሞ ህዝብ በየቦታው ያለና ሠፊ ስለሆነ የበአሉ ትውፊታዊ አከባበር ወጥነት የለውም፡፡ የተለያዩ ክዋኔዎች ይንፀባረቃሉ፡፡ በአከባበርም ይለያያሉ፡፡ መሠረታዊ ስርአቱ ግን እሬቻ (እርጥብ ሣር) ይይዛሉ፣ በእለቱ የሚዘመሩ መዝሙሮች ይኖራሉ ነገር ግን እነዚህ መዝሙሮች በቱለማ፣ በሜሜ እንዲሁም በቦረና የተለያዩ ናቸው፡፡ ዋናው ነገር ግን መዝሙሩን እየዘመሩ ወደ “መልካ” (ወንዝ) ይሄዳሉ፡፡ እዚያም ሲደርሡ “በክረምት ወቅት ያሉትን ተግዳሮቶች አሣልፈህ ለዚህ ላደረስከን በጣም እናመሠግናለን” ይላሉ፡፡ በዚያው ቀንም ግለሠቦች ኢሬቻውን ይዘው የጐደለባቸውን ለፈጣሪያቸው በፀሎት እየነገሩ መለመን ይችላሉ፡፡ መልካው (ወንዙ) ምልክትነቱ ከዚህ በኋላ በጋ ሆኗል፣ ወንዙም ጐድሏል፤ ዘመድ ከዘመድ ወንዝ እየተሻገረ መጠየቅ ይችላል ብሎ የሚገልፅ ነው፡፡ በእለቱ ሽማግሌዎች ሃይማኖታዊ ንግግሮች ያደርጉና በድሮው ባህል እርድ ይኖራል፣ ያ ይበላ ይጠጣና ፈጣሪን በተለያዩ ጨዋታዎች እያመሠገኑ ወደየመጡበት ይመለሣሉ ማለት ነው፡፡
ሃይማኖቱን የሚመሩት እነማን ናቸው?
ምዕመናኑ “ሚሤንሣ” ይባላሉ፡፡ በገልማ (ቤተ-አምልኮ) ውስጥ በዝማሬ አገልግሎት የሚሠጡት ዋዩ ይባላሉ፡፡ አባ ከኩ የሚባሉት ደግሞ ፀሎት አድራሽ ናቸው፡፡ ሉባ የሚባለው የተለያዩ የአስተዳደር አመራር ቦታዎችን የሚያከፋፍል ነው፡፡ ቀጥሎ የሚመጣው ጉላ ነው፡፡ ጉላ ከተጠቀሡት በላይ ሆኖ በማዕከላዊ ደረጃ ሃይማኖቱን የሚመራ ነው፣ ይህ ግለሠብ በሃይማኖቱ ላይ ከ13 አመት በላይ ያገለገለ መሆን ይኖርበታል፡፡ በሌላ በኩል በገዳ ባህላዊ አስተዳደራዊ ስርአት በኩልም የሚመጣ የጐላ ደረጃ አለ፡፡ የመጨረሻው ደረጃ አባ ኬና ይባላል፡፡ አባ ኬና የገዳ ስርአቱንም ሆነ ሃይማኖታዊ ስርአቱን ልቅም አድርጐ የሚያውቅ ሊቅ ነው፡፡
በዚህ የኢሬቻ በአል አያንቱዎች ተሣትፎ ያደርጋሉ፡፡ ከእነሡ ጋርስ ያላችሁ ግንኙነት ምንድን ነው?
እንዲህ አያንቱ የሚባለው በሃይማኖታዊው ስርአት ውስጥ ያለ ነው፡፡ ነገር ግን እኛ የምንቀበለው አንድ አያንቱ ሠዎችን ይሄን አደርግላችኋለሁ ብሎ ገንዘብ የማይቀበልና አስቀድሞ የተጠቀሡትን ልማዳዊ ክዋኔዎች የማይከውን ከሆነ ብቻ ነው። ከነዚህ ሁሉ የፀዳ ከሆነ ትክክለኛ አያንቱ ነው ብለን እንቀበላለን፡፡ ከመርሆው የወጣ እንደሆነ ግን አንቀበለውም፡፡

=============
“የኢሬቻ በአል
ባህላዊነቱ ያመዝናል” - አቶ ጫላ ሶሪ
የባህልና ቱሪዝም ቢሮው ስለ ኢሬቻ የሚሠጠው ትንታኔ ምንድን ነው?
ኢሬቻ ማለት የኦሮሞ ህዝብ የዋቄፈና ስርአት ነው፡፡ ዋቄፈና ማለት ሃይማኖታዊ ማለት ነው። ትልቁ ነገር የዋቄፈና በአል ነው ብንልም በባህል የተሞላ ነው፡፡
እንደ ሌላው ንፁህ ሃይማኖታዊ በአል ነው ማለት አይቻልም፡፡ በአብዛኛው ባህሉ ነው ጐልቶ የሚንፀባረቀው፡፡ “ኢሬቻ” የምትለዋ ቃል የምትወክለው ሣር ወይም አበባ ነው፡፡ ያንን የያዘ ሠው ኢሬቻ የሚሄድ ሠው ነው፡፡ ዋቄፈና ማለት ደግሞ ለአንድ አምላክ ብዙ ሆኖ ምስጋና ማቅረብ ማለት ነው፡፡
የኦሮሞ ህዝብ በአንድነት ተሠብስቦ በፈጣሪው ምስጋና የሚያቀርብበት ነው፡ ይህ ሃይማኖታዊ ቢያሠኘው ይችል ይሆናል፡፡
እድምተኞቹ “መሬሆ” የሚለውን የምስጋና መዝሙር በአንድነት እያሠሙ ለአምላካቸው ምስጋና ያቀርቡበታል፡፡ ባህላዊ የምንለው ደግሞ ህዝቡ የፈለገውን የባህል ጭፈራ እየጨፈረ ነው የሚመጣው ወንዱም ሴቱም በልዩ አለባበስ ተውቦ በአሉ ወደሚከበርበት ስፍራ ይሄዳል፡፡ እንደ ኢሬቻ ባህልን በጉልህ የሚያሣይ በአል የለም፡፡ ለዚህ ነው ባህሉ ስለሚያመዝን ሃይማኖታዊነቱ ይሸፈናል፡፡ በኦሮሞ ባህሎች በእጅጉ የተሞላ ነው፡፡
የዋቄፈና ሃይማኖት ተከታዮች የእምነቱን መሠረታዊ መርሆች በጠበቀ መልኩ እየተከበረ አይደለም የሚል ቅሬታ ያነሣሉ?
አንዳንድ ፈሩን የለቀቁ ሠዎች የሚያደርጉት ድርጊት አለ፡፡
እኛም፣ የኦሮሞ ህዝብም፣ አባ ገዳዎችም የሚቃወሙት ድርጊቶች አሉ፡፡ የኦሮሞ ዋቄፈና በአንድ አምላክ ብቻ ነው የሚያምነው፡፡ እግዚአብሔር ተአምር የሠራበት ቦታ ብለው ነው እዚያ የሚሄዱት እንጂ ወንዝ ለማምለክ አይደለም፡፡
የኦሮሞ ህዝብ ሰይጣን አለ ብሎ አያምንም፡፡ ሰው ሲያብድ በአንድ ጣሳ ውሃ የሚለቅ ሰይጣን እንደት ባህር ውስጥ ይተኛል ብሎ ነው የሚጠይቀው ስለዚህ ኦሮሞ በዛፍ እና በወንዝ አያምንም፡፡
እዚያ ቦታ ግን መሰብሰቦያና ፈጣሪን የሚያገኝበት ቦታ ነው፡፡ ነገር ግን አንዳንዶች በስለት ስም ውሃ ውስጥ ሽቶ መወርወራቸው የመሳሰለው ለባህሉም በእምነቱም ተቀባይነት የሌለው ድርጊት ነው፡፡
በዘንድሮ በአካልም ይህን መሰሉን ድርጊት ለማስቀረት በአባገዳዎ በስፋት ትምህርት ይሰጣል፡፡
በሚዲያዎች ላይ እሬቻ ባህላዊ ነው እንጂ ሃይማኖታዊ አይደለም ብላችሁ መግለፃችሁን የሚስኪኑም አሉ?በዚህ ላይ የእርሶ ምላሽ ምንድን ነው?
አንድ ማንም ያልገነዘበው ነገር አለ፡፡ ባህልና ሃይማኖት የጤፍ ቅዳች ነው፡፡ ሊለያይ የማይቻል ነው፡፡ በማንኛውም ሃይማኖት ውስጥ ባህል ይንፀባረቃል፡፡ በጋብቻ ውስጥ እንኳ ሁለቱም ይንፀባረቃሉ፡፡
የቀለበት ቃልኪዳን ማህበር ከእምነት ጋር ይገናኛው፣ ጭፈራዎቹና ፌሽታዎች ደግሞ ባህል ናቸው ባህል ማለት የማንነት መግለጫ ነው፡፡ ሃይማኖት፣ ታሪክ ቋንቋ ባህል ውስጥ የሚጠቀለሉ ናቸው እንሊ ባህልና ሃይማኖትን ለያይቶ መመልከት ትክክል አይደለም፡፡ በእሬቻ ላይ ደግሞ የበለጠ የሚንፀባረቀው ባህላዊነቱ ነው የኦሮሞ ትልቁ ፀሎት የሚባለው ምረቃ ነው። ምረቃውን ደግሞ ሙስሊምም ክርስቲያንም ይመርቃል፡፡ ስለዚህ እሪቻ ሁሉንም ሃይማኖት የሚያሳትፍ ባህል ነው፡፡
እሬቻ በዓል የሚውልበት ቀን በምንድነው የሚታወቀው?
በእርግጥ አሁን የእሬቻ አቆጣጠር ከመስቀል ደመራ ጋር ይገናኛል፡፡ ድሮ ሌሎች ሃይማኖቶች ማይገቡ ቀኑ ከነሃሴ ጀምሮ ይከበር ነበር ነገር ግን አሁን ከመስቀል ደመረ ማግስት ባለው እሁድ ቀን ነው የሚሆነው፡፡
በመስቀል ደመራ ነው ቀኑ የሚታወቀው ወቅቱ የአበባና የልምላሜ ወቅት ትልቅ ተስፋ የሚታይበት ስለሆነ ለዚህ በቅተናል ተብሎ ነው የሚታሰበው፡፡

Read 13333 times