Saturday, 28 September 2013 13:44

ተራ ዜጋ መሆን አሰኘኝ!

Written by  ቱዋ (ጋርጋንቱዋ)
Rate this item
(1 Vote)

እስር ቤቱን እኔ አልፈጠርኩትም፡፡ ለእስር ቤቱ የንጽህና አያያዝ ምንም ማበርከት የምፈልገው ነገር የለም፡፡ ሌሎቹ የሚደርጉትን አደርጋለሁ፡፡ ሌሎቹ የማያደርጉትን አላደርግም። ሲሰሩ እሰራለሁ፣ ሲፈሩ እፈራለሁ፣ ሲገድሉ እገድላለሁ…ሲዘርፉ እዘርፋለሁ፡፡ ንሰሐ ሲገቡ እገባለሁ፡፡


ተራ ዜጋ መሆን አሰኘኝ፡፡ ተራ፤ ማንንም የማልጐዳ ማንንም የማልጠቅም፡፡ በቀዮች መሀል የምቀላ፣ በጠይሞች መሀል የምጠይም፤ በጥቁሮች መሀል ጠቁሬ የምመሳሰል፡፡ ማስመሰል ሳያስፈልገኝ የምመሳሰል ተራ ዜጋ መሆን አማረኝ፡፡
አማርኛ የምናገር ተራ ዜጋ በአማሮች ሀገር። የአማሮች ሀገር ወደ ትግሬዎች አሊያም ወደ ኦሮሞዎች ስትቀየር እኔም መስዬ የምቀያየር፡፡ ጥርሰ ፍንጭት ወይንም ግንባረ ቦቃ ሆኜ ድሮ የሆንኩትን፣ ድሮ የከረምኩበትን ማንነት ለአሁኑ ለሆንኩበት የማላሳብቅ፡፡ ሌሎቹንም ሆነ እራሴን የማላሳቅቅ፡፡
ሀገር ሰላም ሲሆን ሰላምን የምመስል፣ ጦርነት ሲመጣ የምዘምት፡፡ ከአሸናፊዎች ጋር እምጨፍር፣ ከተሸናፊዎች ጋር አንገቴን የማቀረቅር ተራ ዜጋ ልሁን፡፡ ንጉስ ሲመጣ በንጉሱ የምምል፣ በደርግ ዘመን የመንግስቱን ፎቶ በጭቃ ቤት ግርግዳዬ ላይ የምለጥፍ…በልማታዊው መንግስት ዘመን ልማትን የማፋፍም…ለሁሉም ወቅት የምሆን ዘመናዊ ተራ ዜጋ ልሁን፡፡ ዘመኔ የሚያራምደኝ፡፡ የሚያራምደኝን የማራምድ፡፡ “የምራመደው ወደ የት ነው?” ብዬ ከመጠየቅ የተሰወርኩ ልሁን፡፡ የተሰወርኩለት ይሰውረኝ!
ስሜ ብሔሬን፣ ብሔረሰቡ በሌለበት የማይመሰክር፤ ፀጥ ያለ ስም ለራሴ የማወጣ፤ ሰፈር ስቀይር የሚቀየር ነፃ አመለካከት ያለኝ አድርባይ ያድርገኝ፡፡ በስብሰባ መሀል የሰውን አትኩሮ የማይስብ አስተያየት ከተገደድኩ ብቻ የምሰነዝር… ሌሎች ቢሰነዝሩብኝ እንኳን የማልከላከል፤ ነገር ግን፤ ሰው በተሰበሰበበት ስፍራ ተሰብስቤ ከመገኘት የማልቦዝን ልሁን፡ የምሰበሰበው፤ ለመመሳሰል እንጂ ለመካፈል እንዳይሆን የምጠነቀቅ…የማንም የሃሳብ መራቀቅ እንዳይገባኝ…የማንም አጉል ሀገር ወዳድነት እንዳያገባኝ ሆኜ የተሰራሁ…የእስር ዘመኔን ብቻ በዚህ ሲኦል ውስጥ አጠናቅቄ መሞት የምፈልግ ተራ ዜጋ መሆን አሰኘኝ፡፡ አማረኝ ተራነት፡፡ በተራው ላይ መጀመሪያም መጨረሻም ያልተሰለፍኩ፣ መሪም ተከታይም ያልሆንኩ ስም የለሽ መሆን ናፈቀኝ፡፡
ልታይ ልታይ ባዮቹንስ ማን አያቸው? ልታይ ልታይ ሲሉ ያያቸው መከራ ብቻ ነው፤ በእኔ ዕይታ። ግን፤ “የኔ እይታ” ብሎ ነገር የለም፤ በተራነት ጽንሰ ሃሳብ ውስጥ፡፡ የኔ ሃሳብ የሚያዋጣ ነው፡፡ የሚያዋጣው መደበቅ ነው፡፡ በእስር እያለሁ፤ የእስር ቤቱ ዘበኛ ሆንኩ ወይንም እስረኛን አሰልፎ ነጂ ምንም ትርጉም የለውም፡፡ ራስን ከመሸወድ ውጭ። በሞት ነፃ ለምትለቀቅበት እስር ቤት በህይወት ላይ የምታደርገው ነገር ምን ይጠቅማል? ተራ ሆኖ መደበቁ ይሻላል፡፡
እስር ቤቱን እኔ አልፈጠርኩትም፡፡ ለእስር ቤቱ የንጽህና አያያዝ ምንም ማበርከት የምፈልገው ነገር የለም፡፡ ሌሎቹ የሚደርጉትን አደርጋለሁ፡፡ ሌሎቹ የማያደርጉትን አላደርግም፡፡ ሲሰሩ እሰራለሁ፣ ሲፈሩ እፈራለሁ፣ ሲገድሉ እገድላለሁ…ሲዘርፉ እዘርፋለሁ፡፡ ንሰሐ ሲገቡ እገባለሁ፡፡ እኔ ተራ ዜጋ ነኝ፡፡ ምንም ልዩ ነገር ከእኔ አትጠብቁ፡፡
“ከሰይጣን እና ከእግዚአብሔር ማንን ታምናለህ?” አትበሉኝ፤ “በቀላሉ ከህዝቡ ጋር እሚያመሳስለኝን” እላችኋለሁ፡፡ ሰይጣን እና እግዜርን ደባልቆ በሚጠቀም ህዝብ መሀል ለነብሳቸው የቆሙትን አበሳ እንዴት እንዴት አድርጐ እንደገነጣጠላቸው ተመልክቻለሁ። እኔ መገነጣጠልም መነጣጠልም አልፈልግም። ከስምንት ቢሊዮን የፉርጐ ቅጥልጥሎች መሀል አንዱ ነኝ። የተለየ ቀለም ፉርጐዬን ቀብቼ ለኢላማ ራሴን አላጋልጥም፡፡ ሌሎቹ የሚያደርጉትን እያደረግሁ፣ ያደረግሁት እንዳይታወቅ በሚያደርግ ድርጊት ውስጥ መደበቅ እፈልጋለሁ፡፡ አስር ልጆች እወልዳለሁ፡፡ ስም እና ታሪክ ከሌላት ሴት፡፡ ስም እና ታሪክ አላት በተባለላት ሀገር ላይ ለአለም የህዝብ ቁጥር መጨመር እንደሁሉም ሰው የተቻለኝን አስተዋጽኦ አደርጋሁ። “የአለም ህዝብ ቁጥር ጨመረ፤ በመጨመሩ ላይ አስተዋጽኦ አታድርግ” ብለው የሚያስተምሩኝን የስነ ተዋልዶ ወሬኞችንም ምክር እጠቀማለሁ፡፡ ከሚስቴ ውጭ በኮንዶም እጠቀማለሁ፡፡ ከሚስቴ ጋር በኮንዶሚኒየም እኖራለሁ፡፡ የእኔ ብቻ የሆነ የተለየ ጥፋት የለም፡፡ ጥፋቱ የሁላችንም ነው፡፡ እኔ እነሱን ነኝ፡፡ ተራ ዜጋ፡፡ ተርታውን የማያዛንፍ፡፡ ከ “ከንዳ እስከ አሳርፍ” ሁሉም ወደ ተኮሱበት አቅጣጫ፣ ለሁሉም በተሰጠው ጠመንጃ ተኩሻለሁ፡፡ ብዙ ጊዜ ተመትቻለሁ፡፡ ማን እንደመታኝ አላውቅም፡፡ ማንን መትቼ እንደገደልኩም አይወቁብኝ፡፡
እናት (ሀገሬን) እና አባቴን የማከብረው በዙሪያዬ ያሉ እስካከበሩ ድረስ ነው፡፡ ሲተዉ እተዋለሁ፡፡ ሲጀምሩ እጀምራለሁ፡፡ ስሜን ከአባቴ እስከ አያቴ ድረስ ብዙሀኑን የሚመስለውን ለራሴ እሰይማለሁ። መንግስት ይቅርና ፈጣሪ ራሱ ከአካል (የፉርጐ) ሰንሰለቶች ውስጥ እኔን መለየት እንዲያቅተው። በስጋ ሳይሆን በነፍስ ከሌሎች ጋር አንድ መሆን አምሮኛል፡፡ እነሱ ከሚሞቱ እኔ ብሞት ይሻለኛል። ከእስር ቅጣቴ ለመገላገል ሳይሆን…እነሱ ከሞቱ እኔ ማንን እመስላለሁ? በማን ውስጥ እደበቃለሁ? ራሴን መከተል ይከብደኛል፡፡ ራሴ (ጭንቅላቴ) ለመሆኑ የቱ ጋ ነው ያለው? እንዲኖር የምፈልገው እነሱ (ብዙሃኖቹ) ትከሻ ላይ ነው፡፡ እኔ ተራ ዜጋ ነኝ። ምንም የማውቀው ጉዳይ የለም፡፡ እውቀትም ጉዳዬም አይደለም፡፡ በጥርጊያ መንገድ እንጂ ባልተረገጠ ጐዳና መጓዝ ያስፈራኛል፡፡ ባልተረገጠ ጐዳና ተጉዤ ምን እንደሚገጥመኝ እንዴት አቃለሁ? የሰው ልጅ ገጥሞት የማያቅ አሁን ካለሁበት እስር ቤት የበለጠ ስቃይ እና መከራ የያዘ ሌላ እስር ቤት ቢገጥመኝስ?...ደግሞም የበለጠ ስቃይ ያለው እስር ቤት አለ፡፡ ስሙንም ሰምቸዋለሁ፡፡
“ነፃነት” ይባላል፡፡ ከተራነት ያፈነገጠ ሰው… ብቻውን በራሱ ውስጥ የሚታጐርበት እስር ቤት ነው፡፡ ከሁሉም የሚሰቀጥጠኝ ግን፤ ባልተረገጠ ጐዳና ስጓዝ… ማንንም የማይመስለውን፣ የማይፈራውን፣ ፈጣሪን የሚወደውን፣ ልባሙን እኔን ማግኘቴ አይቀርም ብዬ ነው፡፡ ባልተረገጠ ጐዳና መጓዝ የምፈራው ለዚህ ነው፡፡ ራሴን ላለማግኘት ነው የምሸሸው፡፡ አሁን ካለሁበት ራስን ማጣት ከሚቻልበት እስር ቤት የጠነከረ ነው ያኛው፡፡ ደካማውን አድክሞ፣ ጠንካራውን አጠንክሮ ይገድላል፡፡ ለመድከም - ለመድከም ምን እዛ ድረስ ወሰደኝ?...እዚሁ ተራዎቹ መሀል ድካሜን ጥንካሬ አድርጌ መቆየት ስችል!
“ነፃነትን” እና “እኔነትን” አልችላቸውም፡፡ የምችለውን አውቀዋለሁ፡፡ የምችለው የምፈልገውን ነው፡፡ የምችለውን ያህል ነው የምፈልገው፡፡
የምፈልገውን ነው ከላይ ያሰብኩት፡፡ ያሰብኩት ተራ ዜጋ መሆን ነው፡፡

Read 2549 times