Saturday, 28 September 2013 11:29

እግር ኳስ ፌደሬሽኑ ባለፉት 4 ዓመታት

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(4 votes)

በሚቀጥሉት ሳምንታት የኢትዮጵያ እግር ኳስ በወሳኝ ምዕራፎች ውስጥ ያልፋል። ከሳምንት በኋላ ፌዴሬሽኑን ለቀጣዮቹ አራት ዓመታት የሚመሩ አዲስ የስራ አስፈፃሚ አመራሮችን ለመምረጥ በሸራተን አዲስ የሚካሄድ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ ይኖራል፡፡ ጥቅምት አራት ላይ ደግሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከናይጄሪያ አቻው ጋር በአዲስ አበባ ስታዲየም በወሳኝ የዓለም ዋንጫ ጥሎ ማለፍ የመጀመርያ ግጥሚያውን ይፋለማል፡፡ ጠቅላላ ጉባዔው ብሄራዊ ቡድኑ በወሳኝ ምዕራፍ ባለበት ዋዜማ ሰሞን ላይ መካሄዱ ግድ የሆነው ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) ቀነ ገደቡን በማሳወቁ ነው፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ጠቅላላ ጉባኤ ከመስከረም 28 እና 30 በሸራተን አዲስ ሲካሄድ በዋነኛ አጀንዳው አዲስ አመራሮችን ይመርጣል፡፡ በመደበኛው ጠቅላላ ጉባዔ በመሳተፍ በሚካሄደው ምርጫ በፌዴሬሽኑ የአመራርነት ድርሻ ለመጠቀም ሁሉም ክልሎችና የከተማ መስተዳድሮች የሚደግፏቸውን ዕጩ ተወዳዳሪዎች እስከ ሳምንቱ አጋማሽ ሲያሳውቁ ቆይተዋል፡፡ ሁሉም ክልሎችና ሁለቱ የከተማ አስተዳደር ፌዴሬሽኖች በቀጣይ አራት ዓመት ፌዴሬሽኑን ለሚመራው አካል ሁለት ሁለት ሰዎችን እጩ አድርገው ማቅረብ ይችላሉ፡፡

ከሁለት ወራት በፊት በግዮን ሆቴል በተደረገው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ ወቅት የፌዴሬሽኑ አመራር ከኃላፊነቱ ሙሉ ለሙሉ እንዲነሳ ጉባኤተኛው ይዞት የነበረውን አቋም መሠረት ያደረገ ምርጫ እንዲካሄድ ይፈለጋል፡፡ የፕሬዚዳንትነቱን ኃላፊነት ለመውሰድ በመንቀሳቀስ ላይ ናቸው ከተባሉት ቀደም ሲል በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የነበሩ ግለሰቦች ይገኙበታል፡፡ በፕሬዝዳንትነት ሥልጣን ላይ የሚገኙት አቶ ሳሕሉ ገብረወልድ ቀደም ሲል የወከላቸውን የደቡብ ክልል ጫና በማሳደር ድጋፍ ለማግኘት ቢሞክሩም እንደተቸገሩ ይገለፃል፡፡ የኢትዮጵያን እግር ኳስ ፌዴሬሽን ላለፉት አራት ዓመታት በተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንትነት ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ ተካ አስፋው አማራን እንደሚወክሉ፣ ኦሮሚያ ደግሞ በአሁኑ ወቅት የፓርላማ አባል የሆኑትን አቶ ደምሴ ሽቶን ለፕሬዚዳንትነት እንዳቀረበ ተነግሯል። ከሐረሪ ክልል አምባሳደር ቶፊቅ አብዱላሒ ውክልና ማግኘታቸውን ካረጋገጡ መሰንበታቸው ሲገለፅ፤ በፌዴሬሽኑ ስራ አስፈፃሚነት ሲሰሩ የቆዩት አቶ አሊሚራህ መሐመድ የአፋር ክልል በመወከል እንደሚቀጥሉ ተነግሯል፡፡

ከአዲስ አበባ መስተዳደር አቶ ዮሴፍ ተስፋዬ በእጩ ተወዳዳሪነት እንደተወከሉም ተወስቷል፡፡ ጋምቤላና ቤንሻንጉል የእጩ ተወዳዳሪዎች ማሳወቂያ ጊዜ ከማብቃቱ በፊት የወከሏቸውን እንደገለፁም ታውቋል፡፡ ከዶር አሸብር ወደ አቶ ሳህሉ ከ6 ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን በዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ ፕሬዝዳንትነት ይመራ ነበረ፡፡ በዶክተር አሸብር የስራ ዘመን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተሳትፎ በክፍለ አህጉር ደረጃ ተወስኖ በሴካፋ ዞን ሁለት የሻምፒዮናነት ድሎችን በአገር ውስጥ እና ከአገር ውጭ ማስመዝገቡ ትልቁ ውጤት ነበር፡፡ ብሄራዊ ቡድኑ በፊፋ የእግር ኳስ ደረጃ በታሪክ ከፍተኛውን የ86ኛ ደረጃን ያስመዘገበበት ጊዜም እንደነበር ይታወሳል፡፡ የፊፋው ፕሬዝዳንት ሴፕ ብላተር በኢትዮጵያ ያደረጉት ጉብኝት የዶር አሸብር ወልደጊዮርጊስ አመራር አበይት ምዕራፍ አድርጎ መጥቀስ ይቻላል፡፡ የጎል ፕሮጀክት እንቅስቃሴዎችን ለማጠናከር በፌደሬሽኑ በኩል የተመቻቹ ጅምር ሁኔታዎችም ይነሳሉ፡፡ በአጠቃላይ ግን በዶክተር አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ የሚመራው የእግር ኳስ ፌደሬሽን በአገር ውስጥ ውድድሮች ያን ያህል አበረታች ውጤቶች ባለማስመዝገቡ በተያያዘ በውዝግብ መናጡ አልቀረም፡፡ በሚሊኒዬሙ ዋዜማ ላይ የፕሪሚዬር ሊግ ተሳታፊ የነበሩ ክለቦች በእግር ኳስ ፌደሬሽኑ አስተዳደር ምሬት እና ተቃውሞ አበዙ፡፡

በተደራጀ ሁኔታ ሲንቀሳቀሱ ቆይተውም በመጨረሻ የክለቦች ህብረት የተሰኘ ቡድን በመመስረት ፕሬዝዳንቱን ከስልጣን ለማውረድ ዘመቻ አደረጉ፡፡ ብዙም ሳይቆይ የክለቦች ህብረት የተባለው ቡድንና ሌሎች የእግር ኳሱ ባለድርሻ አካላት አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ በመጥራት ተሰበሰቡ፡፡ የፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት የነበሩት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስን ከስልጣን እንዲወርዱም ውሳኔ አሳለፉ ፡፡ ዶር አሸብር ግን ውሳኔ በመቃወም ከስልጣን አልወርድም አሉ፡፡ መደበኛ ስራቸውን ለማከናወን በአዲስ አበባ ስታድዬም ወደ የሚገኘው ቢሯቸው ለመግባት ሞክረው ሳይሳካላቸው ቀረ፡፡ በዚህም ሳቢያ በእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ላይ የተፈጠረው ውዝግብና ቀውስ በከፍተኛ ደረጃ ተባባሰ፡፡ በዚህ ጊዜ ጉዳዩን በቅርብ ይከታተል የነበረው ፊፋ የፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት ዶክተር አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ የስልጣን ዘመናቸው ሳይጠናቀቅ በጠቅላላ ጉባኤ ከሃላፊነት መውረዳቸውን ተቃወመ፡፡ በእግር ኳስ ፌደሬሽኑ የውስጥ አስተዳደር እና ችግር መንግስት ጣልቃ ገብቷል በሚል ምክንያትም ኢትዮጵያ በፊፋ የነበራትን አባልነት በጊዜያዊነት ማገዱን ገልፆ የቅጣት ውሳኔ አሳለፈ፡፡ በዚሁ የእገዳ ቅጣት ሳቢያ በ2010 እኤአ ላይ በአፍሪካ ምድር በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ በደቡብ አፍሪካ አዘጋጅነት ለተስተናገደው 19ኛው የዓለም ዋንጫ ማጣርያ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከሞሮኮ አቻው ጋር የሚያደርገው የደርሶ መልስ ግጥሚያ ተሰረዘ፡፡

የአገር ውስጥ ውድድሮችና ዋናው የፕሪሚዬር ሊግ ውድድርም ውዝግቡ ከተጀመረ አንስቶ ለሁለተኛ የውድድር ዘመን መቋረጡ ግድ ሆነ፡፡ ፌደሬሽኑ ቅጣት ውስጥ በነበረባቸው ሁለት የውድድር ዘመናት ኢትዮጵያ በሴካፋ፤ በካፍ እና፤ በፊፋ የብሄራዊ ቡድንና የክለብ ውድድሮች ሳትሳተፍ ቀረች፡፡ ፊፋ በኢትዮጵያ አባልነት ላይ የጣለው የእግድ ውሳኔ ከተላለፈ ከአመት ከመንፈቅ በኋላ በፌደሬሽኑ ዙርያ የተፈጠረው ውዝግብ ረገብ ማለት ጀመረ፡፡ የፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት የነበሩት ዶር አሸብር ወልደጊዮርጊስ በጠቅላላ ጉባኤ ፊት የያዙትን ሃላፊነት በፈቃዳቸው እንደለቀቁ በማሳወቃቸው ነበር፡፡ በዚያው ጠቅላላ ጉባዔ ከፊፋ የተወከሉ ሶስት ታዛቢዎች ተገኝተዋል፡፡ ምርጫ ተካሂዶ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን አዲስ ፕሬዝዳንት እና የስራ አስፈፃሚ ቡድን ተመረጠ፡፡ ከዚሁ የስልጣን ሽግግር በኋላም ፊፋ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የተካሄደው የአዲስ አመራሮች ምርጫ የሚያረካ መሆኑን በመግለፅ እውቅና ሰጥቶ በኢትዮጵያ ላይ ጥሎት የነበረውን የአባልነት እግድ ውሳኔ አነሳ፡፡ ከዶር አሸብር ወልደጊዮርጊስ በኋላ የእግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት በመሆን በሃላፊነት የተሾሙት አቶ ሳህሉ ገብረወልድ ሲሆኑ፤ ስራቸውን የጀመሩት ዓላማቸው በኢትዮጵያ የእግር ኳስ አስተዳደር የተንሰራፋውን የውዝግብ ሁኔታ ለማጥፋት እና የእግር ኳሱን ትንሳኤ እውን ለማድረግ ያላቸውን ፍላጎት በመግለፅ ነበር፡፡

አቶ ሳህሉ ገብረወልድ ወደ ኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንትነት ሲመጡ በኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ በተጫዋችነት ያሳለፉና እስከ 10ሺ ተማሪዎች በሚያስተናግደው የኮተቤ ኮሌጅ ዲን ሆነው የሰሩ መሆናቸው ይታወቅ ነበረ፡፡ በሃላፊነቱ መስራት ከጀመሩ በኋላ በካፍ እና ፊፋ ጠቅላላ ጉባኤ አባልነት፤ በካፍ የኢንተር ክለብ ውድድር አባልነት እንዲሁም በዓለም አቀፍ የጨዋታ ኮሚሽነርነት ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡ በዋልያዎቹና ሉሲዎች ታሪክ የተፈጠረው መነቃቃት በአቶ ሳህሉ ገብረወልድ የሚመራው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የስልጣን ዘመኑ በሚያበቃበት የመጨረሻዎቹ ሳምንታት ሲደርሱ ሁለቱ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድኖች በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያስመዘገቡት ውጤት በእግር ኳሱ ላይ ከፍተኛ መነቃቃት ፈጥሯል፡፡ የዋልያዎቹ የሉሲዎቹ ትውልድ ታሪክ ሰሪ የሆኑት በአቶ ሳህሉ የፌደሬሽን አስተዳደር ወቅት ነው፡፡ ከመንፈቅ በፊት ዋልያዎቹ የተባለው ብሄራዊ ቡድኑ ከ31 ዓመታት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ በማለፍ በ29ኛው አፍሪካ ዋንጫ ለመሳተፍ የበቃ ነበር፡፡ ዋልያዎቹ በሚቀጥለው ዓመት ደግሞ በደቡብ አፍሪካ በሚስተናገደው የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮንሺፕ ተሳታፊ ናቸው፡፡ 2005 ዓ.ም በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ትልቁ ስኬት እንዲመዘገብ ያደረጉት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾች በነበረው የፌዴሬሽን አመራር ሲደገፉ የቆዩ ነበሩ፡፡

ዋልያዎቹ ባለፉት አራት ዓመታት የአገሪቱን የእግር ኳስ ደረጃ ከማሻሻላቸውም በላይ ወደ 6 የተለያዩ አገራት ወደ የሚገኙ ክለቦች በመሰማራት ለመስራት የሚችሉበትን እድል ፈጥረው በዝውውር ገበያው ተፈላጊነታቸውን እያሳዩ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በወንዶች ለዓለም ዋንጫ ለማለፍ 180 ደቂቃዎች ቀርተውታል፡፡ በሴቶች ብሄራዊ ቡድንም ድንቅ ውጤቶች ታይተዋል፡፡ ሉሲዎችበ2013 እኤአ በኢኳቶርያል ጊኒ 8ኛው የአፍሪካ ዋንጫ መሳተፍ የቻሉ ሲሆን ከዚያ በፊት ለለንደን ኦሎምፒክ ለማለፍ ከመጨረሻው ምእራፍ የደረሱ ነበሩ፡፡ በዋልያዎቹና ሉሲዎች ታሪክ የተፈጠረውን መነቃቃት የተለያዩ የማበረታቻ ሽልማቶችን በመስጠት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን፤ በፌዴራል የስፖርት ኮሚሽንና በባለሃብቶች የተፈፀሙ ተግባራትም በስኬታማነት ሊነሱ የሚችሉ ይሆናሉ፡፡ ከዋናው የወንዶች ብሄራዊ ቡድን ጋር በተያያዘ በስፖንሰርሺፕ እና በገቢ ማሰባሰብ እንቅስቃሴዎች ተደርገው እስከ 90 ሚሊዮን ብር ሊሰበሰብ መቻሉም ሌላ ትልቅ ውጤት ሆኖ የሚገለፅ ነው፡፡ በ2013 የአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ እና ኮንፌደሬሽን ካፕ ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ደደቢት የነበራቸው ተሳትፎ በአገሪቱ እግር ኳስ የተፈጠረውን መነቃቃትን ያስቀጠለ መሆኑ ሌላው የነበረው ፌደሬሽን ስኬታማ ሂደት ነው፡፡ ከ5 ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በተለያዩ ኢንተርናሽናል ግጥሚየዎች የሚለብሰው ማልያ አንድ ወጥ መልክና ቀለም አልነበረውም፡፡ በተጠቀሰው ጊዜ ብሔራዊ ቡድኑ ከ5 በላይ የተለያዩ ቀለሞችና ገፅታዎች ያሉአቸው ማልያዎችን ሲለብስ ታይቷል፡፡ በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ግን ብዙ ለውጦች ተፈጥረዋል፡፡ የተለያዩ የአፍሪካ መገናኛ ብዙሐናት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን “ጥቁር አናብስት” Black lions ብለው እየጠሩት ቢቆይም በነበረው የፌደሬሽን አስተዳደር አሁን በብዛት የሚታወቀው የብሔራዊ ቡድኑ ቅጽል ስም ዋልያዎቹ መውጣቱ ሌላው ስኬት ነው፡፡

ዋልያ ደግሞ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኝ ብርቅዬ የዱር እንስሳ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ታድያ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በዚህ ቅጽል ስያሜ መወከሉ ብቻ ይሆን የራሱ አርማ መያዙ ቁልፍ እርምጃ ሆኖ ይታያል፡፡ ታሪካዊ ቀውስ በዝርክርክ አሰራር ሳቢያ በ2014 እኤአ ብራዚል ለምታስተናግደው 20ኛው የዓለም ዋንጫ ለማለፍ በአፍሪካ አህጉር ባለፈው አንድ ዓመት ሲካሄድ የቆየው የምድብ ማጣርያ ላይ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ግስጋሴ ከመቼውም የላቀ ውጤት የተመዘገበበት ነበር። የነበረው የፌደሬሽን አስተዳደር ትልቁ ጠባሳ ያጋጠመውም በዚሁ አህጉራዊ ትንቅንቅ ውስጥ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በምድብ ማጣርያው 4ኛ ዙር ጨዋታ ከሜዳው ውጭ ቦትስዋናን 2ለ1 ባሸነፈበት ጨዋታ ላይ ሁለት ቢጫ ካርድ ያየው ምንያህል ተሾመ ተሰልፎ በመገኘቱ ከፍተኛው ጥፋት ነበር፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን በዚሁ ታሪካዊ ጥፋት በፊፋ የውድድርና ስነስርዓት ኮሚቴ ክስ ቀረበበት፡፡ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ በፈፀመው ንዝህላልነት ስህተቱ ማጋጠሙን በመግለፅ ጥፋተኛነቱን በማመኑ አገሪቱ ለቅጣት መዳረጓ አልቀረም፡፡ በዚሁ ተገቢ ያልሆነ ተጨዋች የማሰለፍ ጥፋት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ሶስት ነጥብ እንዲቀነስበት እና 150ሺ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲከፍል ተወስኖበታል። ኢትዮጵያ በእግር ኳስ ስፖርት ከፍተኛ እድገትና መሻሻል እንዳታስመዘግብ በቀዳሚነት እንቅፋት ከሆኑባት ነገሮች የፌደሬሽን አስተዳደር መሆኑ በዚህ ታሪክ የማይረሳው ጥፋት ተረጋግጧል፡፡ በእግር ኳስ ፌደሬሽን ዝርክርክ አሰራር ሳቢያ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በገጠመው የነጥብ መቀነስ እና አስተዳደራዊ ቀውስ ጋር በተያያዘ ወዲያውኑ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ ተደርጓል፡፡

ከወር በፊት ይህ የፌደሬሽኑ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ ሊመክር የተጠራበት ዋና ጉዳይ ብሄራዊ ቡድኑ በገጠመው ወቅታዊ ጉዳይና የወደፊት አቅጣጫ ላይ በስራ አስፈፃሚው የሚቀርበውን የውሳኔ ሃሳብ አዳምጦ ውሳኔ ላይ ለመድረስ ነበር፡፡ በዚህም መሰረት የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ ለብሄራዊ ቡድኑ ነጥብ መቀነስ ተጠያቂ ናቸው ባላቸው ሃላፊዎች ላይ አስፈላጊውን ምርመራ አድርጎ የጥፋተኝነት ውሳኔ አሳልፏል፡፡ በወቅቱ ፕሬዝዳንቱ አቶ ሳህሉ ገብረወልድ ለጉባኤው የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ በጥቅሉ ተጠያቂ እንደሆነ ገልፀው ነበር፡፡ አንዳንድ የጉባኤው አባላትም ከብሄራዊ ቡድኑ ነጥብ መቀነስ ጋር በተያያዘ ተጠያቂ መሆን የሚገባቸው ሁለቱ ሃላፊዎች ብቻ ሳይሆኑ ፌደሬሽኑን በጋራ የሚያንቀሳቅሱት የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት በሙሉ በመሆናቸው ከሃላፊነታቸው መልቀቅ አለባቸው በሚል በወቅቱ ተሟግተዋል፡፡ ይሁንና የእግር ኳስ ፌደሬሽን ሙሉ አመራር የስልጣን ጊዜውን ሳይጨርስ ከሃላፊነት እንዲለቅ ማስገደድ የፌዴሬሽኑ መተዳደርያ ህገ ደንብ አይፈቅድም ነበር፡፡ የጠቅላላ ጉባኤው አባላት ስራ አስፈፃሚውን ከሃላፊነት በማንሳት ፌደሬሽኑ ከፊፋ ጋር አላስፈላጊ ውዝግብ ውስጥ መገባት የለበትም በማለት አመራሩ ብሄራዊ ቡድኑ ያለበትን ቀጣይ ጨዋታ በድል እንዲያጠናቅቅ በጋራ እየሰራ እንዲቆይና ከምድብ ማጣርያ ጨዋታው መፈፀም በኋላ በሚጠራው ጉባኤ ላይ የስራ አስፈፃሚው እጣ ፈንታ እንዲወሰንና ስራ አስፈፃሚው እስከ መስከረሙ ጉባኤ እንዲቆይ ከስምምነት ላይ ተደርሷል። በዚሁ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤው ላይ ፌደሬሽኑ የፅህፈት ቤት ሃላፊ የሆኑትን አቶ አሸናፊ እጅጉን ከሃላፊነት እንደተነሱ ይታወሳል፡፡ በሌላ በኩል ግን የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የቡድን መሪ የሆኑት አቶ ብርሃኑ ከበደ ያቀረቡትን የስንብት ጥያቄ ስራ አስፈፃሚው አሳውቆ ጉባኤው ግን ሳይቀበለው ቀርቷል፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ከገጠመው ከዚሁ ታሪካዊ ቀውስ በኋላ ፕሬዝዳንቱ አቶ ሳህሉ ገብረወልድም በሃላፊነት የመቆየት ፍላጎት እንደሌላቸው ሲያስታውቁ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ተካ አስፋውም ተመሳሳይ አቋማቸውን ገልፀው ነበር፡፡ ኦኑራ እና ሴንትፌንት በአቶ ሳህሉ ፕሬዝዳንትነት ዘመን በእግር ኳስ ፌደሬሽኑ አስተዳደር ለብሄራዊ ቡድን በተቀጠሩ የውጭ አሰልጣኞች አቀጣጠር እና ስንብት አወዛጋቢ ሁኔታዎች እንደተፈጠሩ ይታወቃል፡፡ በመጀመርያ የተቀጠሩት የውጭ አሰልጣኝ ናይጄራዊ የዘር ግንድ ያላቸው እና በትውልድ ስኮትላንዳዊ የሆኑት ኢፌም ኦኑራ ነበሩ፡፡

በፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት የግል ጥረት ድንገት የተገኙ እና የተቀጠሩ አሰልጣኝ ነበሩ። በእንግሊዝ ከፍተኛ የክለብ ውድድሮች በተጨዋችነት፤ በአሰልጣኝነት እና በስፖርት ተንታኝነት ከፍተኛ ልምድ አላቸው፡፡ ኢፌም ኦኑራ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝነት መስራት ከጀመሩ በኋላ ግን መንገዱ ጨርቅ አልሆነላቸውም፡፡ በወቅቱ የኢትዮጵያ እግር ኳስ በክለቦች የውድድር ሂደት ደካማነት፤ በተጨዋቾች የፕሮፌሽናሊዝም ደረጃ መውረድ፤ በፌደሬሽኑ አስተዳደር በቂ ትኩረት ባለማግኘት እና በሌሎች ተያያዥ ችግሮች መውተበተበቸው ምቹ አልሆነላቸውም፡፡ ለውጥ ይገኛል በሚል አስተሳሰብ የኢትዮጵያን እግር ኳስ አንዳንድ ገመናዎች ለውጭ ሚዲያዎች መፃፍ ጀመሩና በፌደሬሽኑ አመራሮች ጥርስ ውስጥ ገቡ። ጋቦንና ኢኳቶርያል ጊኒ ላዘጋጁት 28ኛው አፍሪካ ዋንጫ በሚደረግ የማጣርያ ጨዋታ በናይጄርያ አቡጃ ላይ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን 4ለ0 ከተሸነፈ በኋላ የኦኑራ እና የፌደሬሽኑ ቅራኔ ተጧጧፈ፡፡ ኦኑራ በወቅቱ የብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ከነበሩ ረዳታቸው ጋር ተጣልተው እንደውም ድብደባ አደረሱ ተባለ፡፡ አብረዋቸው በፉትቦል ዲያሬክተርነት የተሾሙ ሌላው ኢትዮጵያዊ ኢንስትራክተር ከሃላፊነት እንዲነሱ መደረጉን ተከትሎም የኦኑራ ቆይታ አጠያያቂ እየሆነ መጣ። በሴካፋ ውድድር ላይም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በኦኑራ አሰልጣኝነት ተሳትፎ ደካማ ውጤት አስመዘገበ፡፡

በአጠቃላይ በኦኑራ አሰልጣኝነት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን 11 ጨዋታዎች ሲያደርግ በ4 ብቻ ድል ሲቀናው በአንድ አቻ ወጥቶ በ6 ጨዋታ የተሸነፈበት ደካማ ውጤት ነበር ያስመዘገበው፡፡ በመጨረሻም ፌደሬሽኑ አሰልጣኝ ኢፌም ኦኑራን ከ9 ወራት የሃላፊነት ቆይታቸው በኋላ ለማሰናበት ወሰነ፡፡ ለስንብቱም ከውጤት መዳከም ባሻገር ኢፌም ኦኑራ የአገርን ሉዓላዊነት በሚጥስ ተግባር ጥፋት መፈፀማቸው እና በተለያዩ የዲስፕሊን ግድፈቶች ተጠያቂ መሆናቸው ምክንያት መሆኑን ፌደሬሽኑ አስታወቀ፡፡ ከስንብታቸው በኋላ ኦኑራ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሮፌሽናል አሰራር እና አደረጃጀት እንደሌለው፤ በአገሪቱ ያለው የክለቦች ውድድር በወረደ ደረጃ እንደሚገኝ፤ ኳስ ተጨዋቾች በአካል ብቃት ፣ በአመጋገብ፣ በጤና አጠባበቅ እና ከስር መሰረቱ ስልጠና ባለማግኘታቸው ሃላፊነታቸውን አስቸጋሪ እንዳደረገባቸው ከመግለፃቸውም በላይ የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ለአንድ የብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ እስከ 4 ዓመታት የሚዘልቅ የስራ ዘመን በትግስት ሰጥቶ ሊያሰራ አለመቻሉን ተችተው ነበር፡፡ ከኦኑራ በኋላ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድኑን ዋና አሰልጣኝነት ተረክበው እንዲሰሩ ሃላፊነት የተሰጣቸው በጋዜጠኛ ጥቆማ የተገኙት ቤልጅማዊው ቶም ሴንት ፌንት ነበሩ፡፡ በዛምቢያ እና በናሚቢያ ቡድኖች አሰልጣኝነት የሰሩበት ልምድ ነበራቸው፡፡ ቶም ሴንትፌንት ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ጋር በመስማማት ስራ ሲጀምሩ በተወሰኑ ጨዋታዎች ብቃታቸው ተመዝኖ ቋሚ ቅጥር እንዲፈፀምላቸው በማሰብ ነበር፡፡ በቶም ሴንትፌንት አሰልጣኝነት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ሶስት የአፍሪካ ዋንጫ የማጣርያ ግጥሚያዎችን አደረገ፡፡ አስከፊ ውጤታቸው እዚህ አዲስ አበባ ላይ ብሄራዊ ቡድኑ በጊኒ 4ለ1 የተረታበት ሆነ፡፡ በሌላ ጨዋታ በአዲስ አበባ ስታድዬም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከናይጄርያ አቻው ጋር 2ለ2 መለያያቱ ደግሞ በጠንካራ ውጤቱ የሚጠቀስ ነበር፡፡

ይሄ የአቻ ውጤት ኢትዮጵያን ለምንም ባያበቃም ናይጄርያ ግን ጋቦንና ኢኳቶርያል ጊኒ ላዘጋጁት 28ኛው አፍሪካ ዋንጫ እንዳታልፍ ምክንያት የሆነ ነበር፡፡ ቤልጅማዊው ቶም ሴንትፌንት ከዚህ በኋላ የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ቋሚ ቅጥር እንዲፈፀምላቸው በመጠየቅ ለእረፍት ወደ አገራቸው ሄዱ፡፡ ይህንኑ ተከትሎ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ቶም ሴንት ፌንት በሌሉበት በብሄራዊ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝነት መቀጠል እንደማይችሉ በማስታወቅ በወቅቱ ረዳታቸው የነበሩትን አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው የብሄራዊ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ አድርጎ ሾመ፡፡ ቶም ሴንት ፌንት በወቅቱ በሰጡት አስተያየት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የገባውን ቃል የማያከብር አስተዳደር ነው በማለት መኮነናቸውም አይዘነጋም፡፡ የፊፋ ጎል፤ በጀት እና ስልጠና በአቶ ሳህሉ ፕሬዝዳንትነት ዘመን እግር ኳስ ፌደሬሽን ከዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌደሬሽን ማህበር ፊፋ ጋር ተስማምቶ መስራት ከጀመረ በኋላ ለስፖርቱ እድገት እንዲሰራ የሚያግዙ በርካታ የገንዘብ እና የስልጠና በርካታ ድጋፎችን ሲያገኝ ቆይቷል፡፡ የገንዘብ ድጋፎቹ የፊፋ አባል የሆኑ ፌደሬሽኖች ተጠቃሚ በሚሆኑባቸው የጎል ፕሮጀክቶች፤ ዓመታዊ የበጀት አስተዋጽኦ እና በፊፋ የገንዘብ ድጋፍ ፕሮግራም በኩል የሚገኙ ናቸው፡፡ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችም በፊፋ በኩል የሚገኙት የፌደሬሽኑን አስተዳደር ዘላቂ በሆኑ የእድገት እንቅስቃሴዎች ለማነሳሳት እና ለማሳደግ በተሰነቀ አላማ ነው፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ከፊፋ ያገኛቸው የገንዘብ ድጋፎች እና የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች በተመለከተ ከፊፋ ኦፊሴላዊ ድረገፅ በኢትዮጵያ ልዩ ገፅ የሰፈሩት መረጃዎች ከዚህ እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡

የጎል ፕሮጀክቶች ግባቸውን መትተዋል? በፊፋ ኦፊሴላዊ ድረገፅ ላይ በጎል ፕሮጀክት እና በፊፋ የገንዘብ ድጋፍ ፕሮግራም አማካኝነት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ላይ እድገት እና ለውጥ ለመፍጠር በሚል ባለፉት አራት አመታት የተሰሩ ተግባራት በዝርዝር ተቀምጠዋል፡፡ በጎል ፕሮጀክት አማካኝነት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ከፊፋ ያገኘው የመጀመርያ ድጋፍ በ2009 እኤአ ህዳር ወር ላይ በጎል ፕሮጀክት ቁጥር 1 ስም የተሰጠው 400 ሺ ዶላር እንዲሁም በፊፋ የገንዘብ ድጋፍ ፕሮግራም ስር የተመደበለት 399,081 ዶላር ነበር፡፡ በድምሩ 799,081 ዶላር ማለት ነው። ይህ ገንዘብ በአምቦ በሚገኘው የእግር ኳስ ማሰልጠኛ ፕሮጀክት ስፖርቱን ከስር መሰረቱ ለማሳደግ እና የታዳጊዎችን ችሎታ ለማዳበር ያግዛል በሚል ዓላማ በማሰልጠኛው የሚገኙ ሁለት የመጫወቻ ሜዳዎችን በአርቴፊሻልና የተፈጥሮ ንጣፍ ለመስራት ወጭ ሆኗል፡፡ በኮንትራክተርነት ለሰሩት ሃይለገብሬል ኮንሰልታት 64,00 ዶላር እንዲሁም ግሪንላንድ ቢቪ ለተባለ ኩባንያ 664,785 ዶላር ተከፍሎበታል፡፡ ቀጣዮቹ የጎል ፕሮጀክት የገንዘብ ድጋፎች በቁጥር ሁለት በ2010 እኤአ ላይ እንዲሁም በቁጥር ሶስት በ2012 እኤአ ላይ የተሰጡ ናቸው፡፡ በዋናነት የፌደሬሽኑን ዋና መስርያ ቤት ለማስገንባት በተያዘ እቅድ በድምሩ 980ሺ ዶላር በጀት የተገኘባቸው፡፡ የእግር ኳስ ፌደሬሽኑን ዋና መስርያ ቤት ለማስገንባት ዓላማዎች ተብለው በተዘረዘሩ ነጥቦች የዋና ፅህፈት ቤቱ መገንባት ባለድርሻ አካላትን በአንድ ጣርያ ለማሰባሰብ፤ የፌደሬሽኑን ስራ እና ሰራተኞቹን ብቃት ለማሳደግ፤ የፌደሬሽኑን ገፅታ እና ደረጃ ለማጠናከር እንዲሁም በተለያያዩ የገቢ ማስገኛ ፕሮጀክቶች የሚሰራበትን ሁኔታ ለማመቻቸት እንደሆነ በፊፋ ኦፊሴላዊ ድረገፅ ተገልጿል፡፡ በዚህም መሰረት በ2010 እኤአ ላይ በፊፋ የጎል ፕሮጀክት ቁጥር ሁለት 480ሺ ዶላር ተበርክቷል፡፡

ፌደሬሽኑ በስራ ተቋራጭነት 302,613 ዶላር ክፍያ ወስዶበታል፡፡ በ2012 እኤአ ላይ ደግሞ በጎል ፕሮጀክት ቁጥር 3 አሁንም የፌደሬሽኑ ዋና መስርያ ቤት ለማስገንባት በተባለ እንቅስቃሴ 500ሺ ዶላር ከፊፋ ተገኝቷል፡፡ በአቶ ሳህሉ ፕሬዝዳንትነት ዘመን እግር ኳስ ፌደሬሽን ዋና መስርያ ቤት ማስገንባት አልሆነም፡፡ የፊፋ ዓመታዊ በጀቶች የት ገቡ? ፊፋ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ለሚያደርጋቸው ለተለያዩ የእድገት እና የአቅም ግንባታ እንቅስቃሴዎች ማካሄጃ የሚሆን የበጀት ድጋፍ በየዓመቱ ከ2009 እኤአ ጀምሮ ያለማቋረጥ ሲሰጥ መቆየቱን በኦፊሴላዊ ድረገፁ በኢትዮጵያ ገፅ በዝርዝር ያሰፈራቸው መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በዚህ መሰረት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ባለፉት አምስት አመታት ከፊፋ ያገኘው የበጀት ድጋፍ በድምሩ 2.1 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ በእነዚህ የፊፋ ድጋፎች የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የተገበራቸው የእድገት እንቅስቃሴዎች አፈፃፀም በስፋት ግምገማ ባይደረግባቸውም ከፊፋ የተገኙ ዓመታዊ በጀቶች በየዓመቱ በዝርዝር ሲቀመጡ በ2009 እኤአ 250ሺ ዶላር፤ በ2010 እኤአ 250ሺ ዶላር፤ በ2011 እኤአ 550ሺ ዶላር ተጨማሪ የቦጀት ቦነስ 300 ሺ ዶላር፤ በ2012 እኤአ 250ሺ ዶላር እንዲሁም በ2013 እኤአ 250ሺ ዶላር የተገኘባቸው ናቸው፡፡ ፊፋ ለእግር ኳስ ፌደሬሽኑ በየዓመቱ የሚያደርጋቸው የበጀት ድጋፎች በምን አይነት የስራ እቅዶች እና የእድገት እንቅስቃሴዎች ተከፋፍለው እንደሚሰራባቸው በድረገፁ በ2013 በጀት የቀረበውን ዝርዝር በናሙናነት መመልከት ይቻላል፡፡ በዚህም መሰረት በፊፋ የዘንድሮ የ250ሺ ዶላር በጀት ስብጥር መሰረት ለወጣት እግር ኳስ 22,500፤ ለወንዶች እግር ኳስ 7,480 ፤ለሴቶች 39,500፤ ለቴክኒክ ዴቨሎፕመንት 44,700፤ ለዳኝነት 12,050፤ ለህክምና 6,050፤ ለአስተዳደራዊ እቅዶች 78,000፤ ለውድድር ማዘጋጃ 5,900፤ ለማርኬቲንግ እና ኮሚኒኬሽን ስራዎች 7,820 ፤ ለመሰረተልማት እንቅስቃሴ 2,000 እንዲሁም ለተለያዩ ስራዎች 20,000 ዶላር መመደቡ ታውቋል፡፡ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች አሻሽለዋል? ፊፋ በስሩ ለሚገኙት የአባል አገራት በየጊዜው ትምህርታዊ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን በማዘጋጀት እና በመስጠትም ልዩ ድጋፍ እንደሚያደርግ ይታወቃል፡፡

በዚህ መሰረትም በአቶ ሳህሉ ገብረወልድ የሚመራው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን በስልጣን ላይ በቆየባቸው ባለፉት 4 አመታት ከ30 በላይ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን በተለያዩ ዘርፎች ከፊፋ ሲያገኝ ቆይቷል፡፡ ስልጠናዎቹ ከክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽኖች፤ ከፕሪሚየር ሊግ ክለቦች እና ከፌዴሬሽኑ ጽ/ቤት ለተውጣጡ አመራሮች የሚሰጡ ናቸው፡፡ በፊፋ ኦፊሴላዊ ድረገፅ እነዚህን መሰል እንቅስቃሴዎች በተመለከተ በቀረበው ዝርዝር ማብራርያ ፌደሬሽኑ ከ2009 እኤአ ጀምሮ በፊፋ በኩል ማግኘት ከቻላቸው 15 ትምህርታዊ ስልጠናዎች መካከል 3 በአስተዳደራዊ አሰራሮች፤ በክለብ ማኔጅመንት፤ 2 በአሰልጣኞች፤ 2 በሴቶች እግር ኳስ፤ 4 በዳኝነት፤ 2 በታዳጊ ማሰልጠኛ ፕሮጀክቶች እንዲሁም አንድ በፉትሳል እግር ኳስ ዙርያ ያተኮሩ ነበሩ፡፡ በሌላ በኩል በፌደሬሽኑ የፅህፈት ቤት ባለሙያ አመላመልና እና የአመራር ብቃት ማሳደግ ዙርያ 2 ፤ በፋይናሽናል ማኔጅመንት አሰራር እና አተገባበር 6 እንዲሁም በፌደሬሽኑ አደረጃጀት፤ ቴክኒካዊ ተግባራት እና አጠቃላይ የትግበራ ስራዎች 3 እንዲሁም በማህበረሰባዊ እንቅስቃሴዎች እና ትብብሮች አሰራር፤ በኮምኒኬሽን በማርኬቲንግ እና በገቢ ማስገኛ አሰራሮች ሁለት የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን ፊፋ ማከናወኑን ገልጿል፡፡

Read 4362 times