Saturday, 21 September 2013 11:13

“የተዘነጋ ቅርስ” ኤግዚቢሽን በአሊያንስ ኢትዮ ፍራንሴስ

Written by  ወልደመድህን ብርሃነመስቀል
Rate this item
(3 votes)

በ1995 ዓ.ም ለአዲስ አበባ ዘጠነኛ ሆኖ ሊፀድቅ የተዘጋጀው የከተማ ፕላን ይፋ ከመሆኑ በፊት የከተማው ነዋሪ እንዲወያይበትና ሃሳቡን እንዲሰጥ የሚችልበት መድረክና ኤግዚቢሽን ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ መስቀል አደባባይ በሚገኘው አዲስ አበባ ሙዚየም ለወራት በቆየው ኤግዚቢሽንና የውይይት መድረክ ላይ ትኩረት ስበው ከነበሩት ርእሰ ጉዳዮች መካከል በመሃል ፒያሳ ሊገነባ ስለታቀደው ባለ 40 ፎቅ ሕንፃ ይሰጥ የነበረው ማብራሪያ አንዱ ነበር፡፡ “አባወራ የሌለበት የሴት ቤትና ባዶ መሬት ተመልካቹ ብዙ ነው” እንደሚባለው የፒያሳው ቦታ ለ40 ፎቅ መስሪያ ከመታሰቡ በፊት የብዙ ታሪካዊ ነገሮች ሥፍራ ነበር፡፡ ከጣሊያን ወረራ በፊት ከፊል የአራዳ ገበያ መደብሮች ቦታው ላይ ነበሩ፡፡ በኋላ ላይ የሩስያ ባህል ማዕከል የመጀመሪያው ቤት፣ የእንዳልካቸው መኮንን ቤተ መፃህፍት፤ ኪንግ ጆርጅ ቡና ቤት… የመሳሰሉ ታሪካዊ ቅርሶች ነበሩበት። ቤቶቹ ከፈረሱ በኋላ በስፖርት ማዘውተሪያ ቦታነት ለብዙ ዓመታት አገልግሏል፡፡ በደርግ ዘመን የመስቀል ደመራ በዓል ሥነ ስርዓት ማከናወኛም ሆኖ ነበር፡፡

ኢሕአዴግ ስልጣን ከያዘ በኋላ ሜዳው በኳስ መጫወቻነት ለተወሰኑ አመታት አገልግሏል፡፡ በመጨረሻ ለአልሚ ባለሀብት ተሰጠ…. በውይይት መድረኩ በፒያሳው መሬት ላይ ባለ 40 ፎቅ ሕንፃ መሥራቱ በአይነቱ የመጀመሪያ ስለሚሆንና ለአዲስ አበባም የእድገት ምልክት ነው የሚል አስተያየት የሰጡ ቢኖሩም በተቃራኒው ሜዳው ላይ ያን ያህል ርዝመት ያለው ሕንፃ መሰራት የለበትም ብለው የሚቃወሙም ነበሩ። የተቃዋሚዎቹ ምክንያት ሊገነባ የታሰበው ሕንፃ በአካባቢው ያሉ ነበር ሕንፃዎችን ውበትና ታሪካዊነት ያደበዝዛል የሚል ነው፡፡ ቦታው ላይ የጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን፤ የአፄ ምኒልክ ሐውልት፤ በአቡነ ጴጥሮስ ላይ ጣሊያኖች የሞት ፍርድ የሰጡበት ቤትና የጳጳሱ ሐውልት፣ የኢየሩሳሌም መታሰቢያ ሕንፃ፤ አሮጌና አዲሱ የማዘጋጃ ቤት ሕንፃዎች፤ በአርመን፣ በግሪክ፣ በሕንድና በጣሊያኖች የተሰሩ የመኖሪያና የንግድ ቤቶች ይገኛሉ፡፡

ነባሮቹ ህንፃዎችና ሃውልቶች አንዳቸው ሌላኛቸውን ሳይጫኑ፣ ለአካባቢው ውበት ፈጥረዋል፡፡ ባለ 40 ፎቅ ሕንፃ በአቅራቢያቸው ቢገነባ ውበታቸው ድራሹ ይጠፋል፡፡ ታሪካዊነታቸው እንዲደበዝዝ ምክንያት ይሆናል በሚል ነበር የግንባታው ሃሳብ ተቃዋሚዎች አስተያየታቸውን የሰጡት፡፡ በደርግ ዘመን የተገነባው የ”አራዳ ሕንፃ” በአካባቢው ላይ የፈጠረውን ጫና እንደማሳያ ያቀረቡ ሰዎችም ነበሩ፡፡ ይህንን ታሪካዊ ክስተት እንዳስታውስ ምክንያት የሆነኝ ከሰሞኑ በአሊያንስ ኢትዮ ፍራንስ የቀረበው የፎቶግራፍ ኤግዚቢሽን ነው፡፡ “የተዘነጋ ቅርስ” በሚል ርእስ የአፍሪካ መዲና (አዲስ አበባ) የመጀመሪያዎቹ 50 አመታት ኪነ ሕንፃ ፎቶ አውደ ርዕይ አዘጋጅተው ያቀረቡት አርክቴክት ፋሲል ጊዮርጊስና ህላዊ ዮሴፍ ናቸው፡፡ ጳጉሜ 4 ቀን የተከፈተው አውደ ርዕይ እስከ መስከረም 16 ቀን 2006 ዓ.ም ድረስ ለሕዝብ ክፍት ሆኖ ይቆያል፡፡ በተለያዩ ተቋማት ባለሙያዎችና ግለሰቦች ትብብር ለእይታ የበቃው ኤግዚቢሽን፤ ታሪካዊና መረጃ ሰጪ ፎቶግራፎችን አቅርቧል - ከግርጌ ማስታወሻ ጋር፡፡ ወደ ኤግዚቢሽኑ አዳራሽ መግቢያ በር ላይ የተመልካቹን ቀልብ የሚስብ ፎቶግራፍ ይታያል፡፡

የአውደ ርእዩ አካል ያልሆነው ይህ ምስልና መግለጫው ስለ 1911 ዓ.ም ነው መረጃ የሚሰጡት፡፡ በዚያን ዘመን ፈረንሳዊያን በዚያው ግቢ ውስጥ ኢትዮጵያውያን ሕፃናትን ሰብስበው ሲያስተምሩ ያሳያል፡፡ በአውደ ርእዩ ስብስቦችም የዚህኑ ታሪክ እውነታ የሚያረጋግጥ ተጨማሪ ፎቶግራፍ ቀርቧል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ እ.ኤ.አ ከ1886 እስከ 1936 ባሉት 50 አመታት ከተገነቡ ቤቶች 36 ያህሉ የት እንደሚገኙ፣ መቼ እንደተሰሩ፣ በማንና በምን ማቴሪያል እንደተገነቡ፣ እንዴት ሊሰሩ እንደቻሉ ጭምር በፅሁፍና በፎቶግራፍ የሚያስቃኘው አውደ ርእይ ካቀረባቸው መሐል በቤተ መንግሥትና በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ግቢ የሚገኙ አዳራሾች፤ የጣይቱ ሆቴልና የንግሥት ዘውዲቱ እንግዳ ማረፊያ አይነት ልዩ ስራዎች፤ የሙሴ ሚናስና የአልፍሬድ ኢግል አይነት ኢንጂነሮች መኖሪያ፤ የነጋዴና ባለስልጣን ቤቶች፤ የእንግሊዞች መፅሐፍ ቅዱስ ማህበር መገኛ የነበረ ሕንፃ፤ እንደ ሰይጣን ቤት ልዩ ስያሜ የተሰጣቸው ግንባታዎች… ከፊሎቹ ናቸው፡፡ አንድ ሕንፃ ወይም መንደርን በ50 አመታት ልዩነት በተነሱ ሁለት ፎቶግራፎች አማካኝነት ከሚያሳዩ ፎቶግራፎች አንዱ የማህተመ ጋንዲ ጐዳና ነው፡፡ ጐዳናውና የመንደሩ ቤቶች እ.ኤ.አ በ1960 እና በ2013 በተነሱት ፎቶዎች፤ የተጠበቀውና የጠፋውን ያመለክታሉ፡፡ አካባቢው እንዲህ ቢሆንስ በሚል በቀረበው ፕሮፖዛል ማሳያ ምስል ደግሞ የጠፋውና የተበላሸው ታድሶ፣ የጐደለው ሞልቶ ይታያል፡፡

የሙሴ ሚናስ መኖሪያ ቤትም በተመሳሳይ መልኩ በ50 አመታት ውስጥ የሚታይበትን ለውጥ የሚያስቃኙ ፎቶግራፎች ቀርበውለታል፡፡ ከእሪ በከንቱ ወንዝ በላይ ወደ ፒያሳ በሚያደርሰው ጐዳና የሚገኘው የዚህ ቤት ባለቤት አርመናዊ መሆናቸውን፣ በሙያቸውም መሐንዲስ እንደነበሩ እና መኖሪያ ቤታቸውም ለአዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያው ባለ 4 ፎቅ ሕንፃ እንደሆነ ከአውደ ርእዩ መረጃው መረዳት ይቻላል፡፡ በዚህ ታሪካዊ ቤት 25 አባወራ ቤተሰቦች እየኖሩበት እንደሆነም መረጃው ሲያመለክት፤ እንዲህ ቢሆንስ በሚል የቀረበው ፕሮፖዛል አመልካች ምስልም የታሰበለትን ሆኖ ባየነው የሚያስብል ነው፡፡ ሰኞ መስከረም 6 ቀን 2006 ዓ.ም ምሽት በአውደ ርዕዩ ላይ የውይይት መድረክም ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ በአሊያንስ ኢትዮ ፍራንሴስ ግቢ በተሰናዳው መድረክ ላይ የጥናት ፅሁፍ ያቀረቡት አርክቴክት ፋሲል ጊዮርጊስ “በአዲስ አበባ ከተማ ከልማት ሥራ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ የሆነ ለውጥ ያለ መሆኑ የሚታይ ቢሆንም ለሥራው እውቅና የሰጠን አይመስልም” በሚል የመግቢያ ንግግር ጀምረው ስለ “የተዘነጋው ቅርስ” ሰፋ ያለ ማብራሪያ አቅርበዋል፡፡

አዲስ አበባ በነዋሪዎቿ ፈቃድና ተነሳሽነት ያለ ምንም የከተማ ፕላንና መመሪያ መገንባት መጀመሯን ያመለከቱት አርክቴክቱ፤ ይህ ደግሞ እስካሁንም አልቀረፍ ላለው ችግር መሰረት መሆኑን ገለፁ፡፡ የአድዋ ጦርነት ድል ኢትዮጵያ አለም አቀፍ ትኩረት እንድታገኝ ምክንያት በመሆኑ፤ አዲስ አበባ የበርካታ አገራት ዲፕሎማቶች መገኛ እንድትሆን አስተዋፅኦ ማድረጉንና የከተማዋ ታሪካዊ የግንባታ ሥራዎች የውጭዎቹ አሻራ እንዲያርፍበት አድርጓልም ብለዋል፡፡የ1928ቱ የጣሊያን ወረራ በኢትዮጵያ ላይ ካስከተለው ጉዳት ባሻገር፣ በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ካስገኘው ጥቅሞች መካከል ፕላንን መሰረት ያደረጉ የግንባታ ሥራዎች መሰራታቸውና መታቀዳቸው ተጠቃሽ እንደሆነም ተነግሯል፡፡ ከዚያ በኋላ የከተማ መሪ እቅድን የተከተሉና ያልተከተሉ የግንባታ ሥራዎች መሰራታቸውን፤ አዲስ አበባም ከእለት ወደ ዕለት እየሰፋችና እያደገች መምጣቷን አብራርተው፤ የታሪካዊ ቤቶች ጉዳይ አደጋ ላይ ስለመሆኑን በተለያዩ ማሳያዎች አስደግፈው ገልፀዋል፡፡ የመንግሥትና የሕብረተሰቡ የለውጥ ፍላጐት ለቅርሶች ትኩረት እንዳይሰጥ አንዱ ምክንያት እንደሆነም ተነግሯል፡፡ በፊት በጉለሌና ቦሌን በመሳሰሉት የከተማዋ ዳርቻዎች በቀላሉ ይገኝ የነበረው መሬት አሁን የቦታ ፈላጊዎች ቁጥር መበራከት ቅርሶችን ለአደጋ ያጋለጠ የመሬት ሽሚያ መፍጠሩም ሌላው ምክንያት ነው ተብሏል፡፡

አዲስ አበባ ከተማ ታሪካዊ ቤቶችን መጠበቅ አለመቻል ብቻ ሳይሆን ለተለያዩ ግልጋሎት ሊውሉ የሚችሉ ክፍት ቦታዎችም እያጣች መምጣቷ ከዚሁ ጋር በተገናኘ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ በመንግሥትም በሕብረተሰቡም ዘንድ ታሪካዊ ቤቶችን መጠበቅ ስለሚያስገኘው ጠቀሜታ ግንዛቤው ያለ አይመስልም ያሉት አርክቴክት ፋሲል ጊዮርጊስ፤ ለውጡ ሊመጣ የሚችለውና ችግሩም የሚቀረፈው፤ ሕብረተሰቡን ግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት በተከታታይ በመስጠትና ለቅርሶችም ሕጋዊ ከለላና ጥበቃ በማዘጋጀት ነው ብለዋል፡፡ በተለይ በህብረተሰቡ ዘንድ ያለው ግንዛቤ በጣም አነስተኛ ነው ያሉት ጥናታዊ ፅሁፍ አቅራቢው፤ የሚኖሩባቸውን ታሪካዊ ቤቶች የአጥር እንጨት እየመዘዙ ለማገዶ የሚጠቀሙ አሉ፤ ታሪካዊ ቤቶቹ ይታደስ ሲባል ሞቼ እገኛለሁ፤ ሙዚየም ሊሆን ነው ልቀቁ ሲባሉ አሻፈረኝ የሚሉ… ነዋሪዎች ጥቂት እንዳልሆኑ ገልፀዋል፡፡ከቅርስና ታሪካዊ ስራዎች ጋር በተያያዘ የሐረር፣ የአክሱም፣ የጐንደር… ምሳሌዎችን እያቀረቡ ማብራራታቸውን የቀጠሉት አርክቴክቱ፤ ለቱሪስቶች ደረጃውን የጠበቀ ሆቴልና ማረፊያ ለመሥራት እየጓጓን ቱሪስቶችን ለሚስበው ታሪካዊ ቅርስ ትኩረት አለመስጠት ያነጋግራል በማለት ገለፃቸውን ቋጭተዋል፡፡

Read 1504 times