Monday, 16 September 2013 08:23

በ“መልክዐ ስብሃት” ላይ የተካሄደው ውይይት

Written by  ወልደመድህን ብርሃነመስቀል
Rate this item
(3 votes)

“ስብሐት የጫማውን ገበር አራግፈን እንድንፈትሸው ዕድል ሰጥቶናል”
“አንድ ፀሐፊ የራሱን ጽሑፍ እንዲያሔስ ሲጠራ እኔ የመጀመሪያው ሰው ሳልሆን አልቀርም። በ‘መልክዐ ስብሐት’ መጽሐፍ ውስጥ እኔ ያቀረብኩት ጽሑፍ ብዙ እያነጋገረ ስለሆነ ለዛሬው መድረክ እንድጋበዝ ምክንያት ሆኗል፡፡ ጽሑፉን ሳዘጋጀው አምኜበትና ተጠያቂነቱን ወስጄ ነው፡፡ በፃፍኩት ጽሑፍ ላይ አልወያይም ልል አልችልም። አስተማሪው ወላጅ አምጣ እንዳለው ልጅ አባት፤ ችግሩ ምንድነው? እስቲ ሄጄ እውነቱን ሐሰቱን ልለይ ብዬ ነው የመጣሁት፡፡
“ጽሑፌ ለስብሐት የተለየ አክብሮት ያላቸው ሰዎችን ስሜት እንደጎዳ ሰምቻለሁ፡፡ ይህንን ለማዘለብና ልዩነት ካላቸው ሰዎች እማራለሁ ብዬ ብመጣም ሌሎቹ ለመምጣት ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ሰማሁ፡፡ ተሳስቼ ከሆነ ልታረምና ልማር ነበር የመጣሁት፡፡ ተቀራርበን መወያየትን መልመድ አለብን፡፡ በግላዲያተር ፊልሞች እንደምናየው ግቡ መጠፋፋት የሆነ አካሄድ ማንንም አይጠቅምም፡፡ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን እንደቀረበው አሽሙር፣ ስድብ፣ ስላቅና መበሻሸቁ ለውጥ አያመጣም፡፡ ሀሳብን በሀሳብ መሞገት መልመድ ይኖርብናል፡፡
“ከእኛ ውጭ የሆነን የማንንም ሀሳብ አንቀበልም የሚል አመለካከት በቡድን ከማሰብ የሚፈጠር ነው፡፡ የተለየ ሀሳብ ያቀረበ አድርባይ፣ የሕብረተሰቡ ችግር የማይገባው፣ ኦፖርቹኒስት … እየተባለ እንዲገለል ይደረጋል፡፡ የእንዲህ ዓይነቱ አካሄድ መጨረሻው ተያይዞ መውደቅ ነው፡፡ በገጠር ያደጋችሁ ሰዎች እንደምታውቁት የበጎችን ሥነ ልቦና የሚገልጽ “መናጆ” የሚባል ነገር አለ፡፡ አንድ በግ ለመሸጥ ያሰበ ገበሬ አምስቱን አብሮ እየነዳ ወደ ገበያ ይወስዳቸዋል፡፡ የምትሸጠው በግ በአገር የመጣ ነው ብላ ትሄዳለች፡፡ አራቱ ተሽጠው አንዷ ተመለሽ ብትባል እሽ አትልም፤ በአገር የመጣ ነው ብላ ተከትላ መሄዱን ትመርጣለች፡፡ በቡድን ማሰብ እንዲህ ዓይነት አደጋ አለው፡፡”
እሁድ ጳጉሜ 3 ቀን 2005 ዓ.ም ሚዩዚክ ሜይዴይ ኢትዮጵያ ባዘጋጀው መድረክ የተጋበዙት አርክቴክት ሚካኤል ሽፈራው ናቸው ይህንን ንግግር በመግቢያቸው ያቀረቡት፡፡ በብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመፃሕፍት ኤጀንሲ አዳራሽ የመፃሕፍት ውይይት መድረኩ ሲካሄድ፣ ለዕለቱ የተመረጠው “መልክአ ስብሐት” በሚል ርዕስ በደራሲና ሐያሲ አለማየሁ ገላጋይ አርታዒነት የታተመው መጽሐፍ ነበር፡፡
ስብሐት ገብረእግዚአብሔርን ከሌላ ማዕዘን ማየት ለምን አስፈለገ? በሚል ወደ ዋና ርዕሰ ጉዳያቸው የገቡት አርክቴክት ሚካኤል፤ ሽፈራው አነጋጋሪ የሆነው ጽሑፋቸው የመጽሐፉ አካል ሊሆን እንዴት እንደቻለ አመለከቱ፡፡ ሁለቱ ተቀጣጥረው የተገናኙበት ጉዳይ ሌላ ነበር፡፡ አርክቴክቱ ስለ ስብሐት ገብረእግዚአብሔር ያላቸው አመለካከት የተለየ መሆኑን ያስተዋለው አርታዒው፤ ሀሳቡን እንዲጽፉት ጠየቃቸው፡፡ ይህ ከሆነ ከስምንት ወር በኋላ አነጋጋሪው ጽሑፍ የመጽሐፉ አካል ሆነ፡፡
“የስብሐትን መልካም ሰውነት፣ ጎበዝ ፀሐፊነት በ“መልክአ ስብሐት” መጽሐፍ 26 ፀሐፍት መስክረውለታል፡፡ ከእነዚህ በተለየ ብቸኛ ሆኖ በቀረበው ጽሑፌ ስብሐትን ሳይሆን አመለካከቱን ሊተች ነው የሚሞከረው፡፡ ከስብሐት አጠገብ ከነበሩ ወጣቶች አንዱ ነበርኩ፡፡ እርግጥ ነው ስብሐት ንግግር ያውቃል፣ አንደበቱም ለስላሳ ነው። ከስብሐት ጋር መከራከር ግን አይቻልም፡፡ ሁሉም ነገር መልካምና ጥሩ ነው ይላል፡፡ ይህ አመለካከትና አቋሙ ደግሞ ብዙ ወጣቶችን ለጉዳት ዳርጓል” ያሉት አርክቴክት ሚካኤል ሽፈራው፤ ሌሎች ማሳያዎችን አቅርበዋል፡፡
“ስብሐት በአመለካከቱ፣ በባሕልና ሥነ ምግባር ተጋፊነቱ አብዮተኛ ተደርጎ መወሰዱ ትክክል አይደለም፡፡ አብዮተኛ ግብ አለው፡፡ አብዮተኛ ወዳስቀመጠው ግብ ሲጓዝ ከባህል፣ ከልማድ፣ ከክልከላ … ጋር ይጋጫል፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ዝም ብሎ ይፍረስ የሚሉ “አናርኪስቶችም” አሉ፡፡ እነዚህ ደግሞ አብዮት ሲረጋጋ አይወዱም፡፡ ስብሐት ገብረእግዚአብሔር አብዮተኛም አናርኪስትም አይደለም፡፡ በራሱ መንገድ ነው የሚኖረው፡፡ ሁሉም ነገር ትክክል ነው ይላል፡፡ ከሱ ጋር መጋጨት አይቻልም፡፡ መሰደብ ያማረው በስብሐት መሰደብ አይችልም፡፡”
ስብሐት ገብረእግዚአብሔር አመለካከቱንና የሕይወት መርሁን የቀዳባቸው ናቸው በሚል የተለያዩ ፈላስፎችን አቋም በስፋት ለማቅረብ የሞከሩት አርኪቴክት ሚካኤል ሽፈራው፤ የ“ስብሐትን ከሌላ ማዕዘን” ጽሑፍ ተጠያቂነት ምላሽ ለመስጠት ጥረዋል፡፡
የሰው ልጅ የሚኖረው ለደስታ ነው፤ ሕይወት ትርጉም የላትም፤ ሥነ ምግባር አይገዛንም፤ ጥበብን ለጥበብነቱ … የሚሉትን አመለካከቶች ይከተል የነበረ የሚመስለው ስብሐት፤ ማንንም የማስተማር ኃላፊነት የለብኝም የሚል አቋም ነበረው” ብለዋል፡፡ የፃፈልንም ሕይወቱን ነው፤ ልዩ የሚባለው “አምስት ስድስት ሰባት”ም የትግራይ ገበሬ ታሪክ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ከተከተሉት ወጣቶች አንዳንዶቹ የስብሐት አቋምና አመለካከትን ‘አብርሆት’ ነው የሚሉ ቢኖሩም፤ ለእኔ ግን ጨለማ ነበር ያሉት አርኪቴክቱ፤ “ሳይማር ልጆቹን ለማስተማር፣ ልብስና ምግብ እንዳያጥረን ይተጋ የነበረው አባቴን መከተል ትቼ ስብሐትን ተከታይ መሆኔ ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ጥሎኛል፡፡ ከዚህ ዓለም ለመውጣት ብዙ ኃይል ጠይቆኛል፡፡ ከሰባተኛው ሲኦል እንደመውጣት ነበር” ብለዋል፡፡
“ምስጢራዊ ባለቅኔ” በሚለው መጽሐፌ ከስብሐት በላይ የተቸሁት ፀጋዬ ገ/መድህንን ነው ያሉት አርክቴክት ሚካኤል ሽፈራው፤ ታላላቅ ሰዎቻችንን መጠየቅና መሞገት መቻል አለብን፤ ነገር ግን ይህ ዓይነቱን ሒስ ያዳበርን አይመስልም ካሉ በኋላ፤ ለ “ስብሐትን ከሌላ ማዕዘን” ጽሑፋቸው፤ አንተ ማነህ? በራስህ ሄደህ ጠፍተህ ስብሐት ምን ያድርግህ? ሰውየውንና ሥራውን ለምን ታደበላልቃለህ? … የሚሉ የማይጠቅሙ ትችቶች በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን መቅረቡን አመልክተዋል፡፡
በ“መልክአ ስብሐት” መጽሐፍ ስብሐትን በሌላ ማዕዘን ለማሳየት የሞከረው የእኔ ጽሑፍ ብቻ ሳይሆን የካርቱን ስዕል ሰዓሊያን በሰላ አገላለጽ ስለ ስብሐት ገ/እግዚአብሔር የልባቸውን ተናግረዋል ያሉት ንግግር አቅራቢ፤ ስብሐት በጭቃ ትንንሽ ሰዎችን እየሰራ ሲለቃቸው፣ በተነፋ ፊኛ አየር ላይ ተንጠልጥሎ የሚታየው የስብሐት ምስል ጠንካራ መልዕክት አስተላላፊ ትችት መሆኑ ሲያመለክቱም “ሰዓሊ በቀለ መኮንን ጆሯችን እንጂ ዓይናችን አልሰለጠኑም እንደሚለው ልብ አላልነውም። ስዕሎቹ ግን ከባድና አነጋጋሪ ናቸው” ካሉ በኋላ ከተሰብሳቢዎች የተለያዩ አስተያየትና ጥያቄዎች ቀረቡ፡፡
የስብሐት አስተሳሰብና አመለካከት ገና ያልተደረሰበትና ወደፊትም አነጋጋሪ ሆኖ መቀጠሉ አይቀርም፡፡ ሚዩዚክ ሜይዴይ ኢትዮጵያ የሚጋብዙኝ ከሆነ በስብሐትና በበአሉ ግርማ ዙሪያ ለ19 ዓመታት ያህል የሰራሁት ጥናት ስላለ አቀርብላችኋለሁ፡፡
ስብሐት በአፃፃፉ፣ በአኗኗሩ፣ በአነጋገሩ የተለየ ነበር፡፡ እሱን ማምለክ ደረጃ መደረሱ ተገቢ ነው ወይ? ሀይማኖስት ነበረው?
26ቱን ፀሐፍት የሚወክል አንድም ሰው ሳይኖር አንተ ብቻ መገኘትህ ያሳዝናል፡፡ በጽሑፋቸው ያደነቁትን በአደባባይ ወጥተው ካልመሰከሩ የስብሐት አድናቂነታቸው ምኑ ላይ ነው? የስብሐት አድናቂዎች የሚከተሉትን አቋም መሞገት ተገቢ ይመስለኛል፡፡ አንድ ሕብረተሰብ ባሕል፣ ወግ፣ ሥርዓት ባይኖረውና ሁሉም አመንዝራ፣ ጠጪ፣ ማጋጭ … ቢሆን ሕብረተሰብ ይቀጥላል ወይ? ይህ አካሄድ ሕዝብን አያጠፋም? ብዙ ያነበበ ሰው ይህንን መረዳት እንዴት ያቅተዋል? ሌላው የሒስ ባህላችን አልዳበረም በሚለው አቋምህ አልስማማም፡፡ ዘመናዊ ትምህርት ስንቀበል አላሰብንበትም እንጂ በቅኔ ትምህርት ቤት አሁንም ድረስ የሚሰራበትና ከ1500 ዓመታት በላይ ያስቆጠረ በሒስ የሚመራ ዕውቀት በአገራችን አለ፡፡
“እንደ ጥላ የገዘፉ፤ አጠገባቸው ሰው የማያስደርሱ” ብለህ ነው ንግግርህን የጀመርከው፤ አንተ የጠፋኸው ደክመው ያሳደጉህ አባትህን ትተህ ስብሐትን ለመከተል የሄድክ ዕለት ነው፡፡ ከስብሐት አመለካከት ማፈንገጥ ችያለሁ እያልክም እሱኑ ነው የምትመስለው፡፡ ከ26ቱ ፀሐፍት ብቸኛው እኔ ነኝ እያልከን ነው ያለኸው፡፡ በስብሐት ፂም ላይ ከተንጠለጠሉት ሰዎች አንዱ ነህ፡፡
የመጽሐፉ አርታዒ አለማየሁ ገላጋይ 26ቱን ፀሐፍት ወክሎ አንድ ነገር ማለት ያለበት ይመስለኛል፡፡ ሌላው፤ መልክአ መልኮች የሚፃፉት ለማነው? መልክአ ማርያም፣ መልክአ ኢየሱስ … ለቅዱሳን ነበር የሚፃፉት፡፡ የመጽሐፉ ርዕስ የተሰጠው ስብሐትንም ከቅዱሳን ጋር እንድናስበው ተፈልጎ ነው ወይ? በአሁኑ ወቅት መስመር የሳቱ፣ በምዕራባዊ አስተሳሰብ የተጠመቁ፣ ግራ የተጋቡ … ሰዎችን እናያለን፡፡ ውሉ የጠፋብን የቱ ጋ ነው? ኢትዮጵያ ሀሳቢዎቿንና አላሚዎቿን ያጣችው መቼ ነው?
“ዲሞክራሲ የመንግሥት አጀንዳ ብቻ አይደለም፡፡ ሁላችንም በየቤታችን፣ በሥራ ቦታና በተለያዩ መድረኮች ተከባብረን ለመኖርና ለመሥራት በመነጋገር የምንተማመንበት ነው ያሉት አርኪቴክት ሚካኤል ሽፈራው፤ “የእግዚአብሔርን ማንነት እየመረመርን ሰዎችን ግን ትልቅ ናቸው፣ ውስጣቸው ጥልቅ ነገር አለ በሚል እንደ ጣኦት መመልከታችን ተገቢ አይደለም” ብለዋል፡፡
“ክርክር፣ ሙግትና ውይይታችን የሚያስገኘው የተሻለ ሦስተኛ ሀሳብ ካለ አምነን መቀበልን መልመድ አለብን፡ እነ ፕሌቶን በጽሑፋቸው ስናውቃቸው የአክሱማዊያን ዘመን ፈላስፎቻችንን አናውቃቸውም፡፡ ክፍተት መተው እንዲህ ዓይነት ጉዳት ያስከትላል፡፡ ትህትና የሌላቸው ትላልቅ ሰዎች ሌላውን ዝቅ አድርገው ይመለከታሉ፡፡ እንደነዚህ ዓይነት ታላላቆቻችንን መሞገት መልመድ አለብን፡፡
“ስብሐትን አትንኩት” የሚሉ ሰዎችን ሀሳብ አከብራለሁ፡፡ ለምን መነካት እንደሌለበት ግን ሊያስረዱን ይገባል፡፡ “እነ እከሌ ቤት ቢሆን ማን ያስገባህ ነበር?” የሚሉኝ ይኖራሉ፡፡ እውነት ነው ስብሐት እንድናውቀው፣ በሱ ዙሪያ እንድንነጋገር በሩን ከፍቶልናል፡፡ ስብሐት ባለው ዝነኛነት እሱን በመቃወም መፃፃፍም ሆነ መድረክ ላይ መውጣት ያስፈራል፡፡ ለተጠያቂነት ዝግጁ የሆንኩት በጎውን ወስደን የማይጠቅመውን እናርም በማለት ነው፡፡ ዛሬ ቤተሰብ እየመራሁ ነው፡፡ እኔን አርአያው አድርጎ የሚከተለኝ ልጅ አለኝ፡፡ እዚህ ደረጃ መድረስ ቀላል ነገር አልነበረም፡፡ መጠየቅና መጠየቅ ስጀምር ነው መሠረት መያዝ የቻልኩት” በማለት ሲያጠቃልሉ ደራሲና ሐያሲ አለማየሁ ገላጋይ ማጠቃለያ ሀሳብ አቀረበ፡፡
“መጽሐፉን ለማሳተም ያሰብኩት ስብሐት በሕይወት እያለ ነበር፡፡ ስብሐት አንብቦት አስተያየት ሰጥቶበት ነበር፡፡ የቀድሞውን ትውልድ መንካት ከባድ ነው፡፡ ግን መለመድ አለበት፡፡ “መልክአ ስብሐት” የትውልዱ መልክ ነው፡፡ እኔ ከስብሐት ጋር ተዋውቄ በራሴ መንገድ መሄድ ችያለሁ፡፡ ስብሐት የሁሉንም ሰው አመለካከትና አካሄድ ያከብራል፡፡ የጫማውን ገበር አራግፈን እንድንፈትሸውም ዕድል ሰጥቶናል፡፡”

Read 2178 times