Saturday, 07 September 2013 11:27

ድምፃዊ ሐመልማል አልበም አሳተመች የሞሃ ፔፕሲ ለአልበሙ ከግማሽ ሚ. ብር በላይ አውጥቷል

Written by 
Rate this item
(5 votes)

በ40 ዎቹ መጨረሻ ዕድሜዋ ላይ የምትገኘው አንጋፋዋ ድምፃዊ ሐመልማል አባተ፤ ሰሞኑን ዘጠነኛ አልበሟን ለጆሮ አብቅታለች፡፡ በአዲሱ አልበሟ ምን አዲስ ነገር ይዛ መጣች? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ሰላም ገረመው ከሐመልማል አባተ ጋር ተከታዩን ቃለምልልስ አድርጋለች፡፡

ብዙ ጊዜ አልበም የምታወጪው የበአላት ሰሞን ነው፡፡ ይሄ በአጋጣሚ ነው ወይስ ሆን ብለሽ?
አጋጣሚ ነው፡፡ ከዚህ በፊት “አውደ አመት” የሚል ካሴት ለአዲስ አመት አውጥቼ ነበር፡፡ ከዛ በኋላ ሠው ሁልጊዜ ለአዲስ አመት ካሴት የማወጣ ይመስለዋል፡፡ እንደ አጋጣሚ ሆኖ የአሁኑም አልበሜ ሄዶ ሄዶ አዲስ አመት ጋ ደረሠ፡፡ በዚህ ደሞ ደስተኛ ነኝ፡፡
ከኮፒ ራይት ጥሰት ጋር በተገናኘ በቀዳሚነት “ካሴት አላወጣም” ያልሽው አንቺ ነሽ፡፡ ውሳኔሽ አልጐዳሽም?
እርግጥ አንድ ነገር ስትፈልጊ አንድ ነገር ታጫለሽ፡፡ በፊት የሚሠራው ከቨር ነበር፤ ከቨር ይሠራና ይላካል፡፡ በዚህ ጊዜ ሁሉም ሰው አንድ አይነት ጥራት ያለው ስራ አያገኝም፡፡ ምክንያቱም ሁሉም በራሱ ቴፕ ነበር የሚቀዳው፡፡ አንዳንዴ ክፍለ ሀገር ሔጄ የተቀዳውን ድምፄን ስሠማው፣ የህፃን ልጅ ድምፅ የሚመስልበት ጊዜ አለ፡፡ አንዳንድ ቦታ ደግሞ የወንድ ድምፅ ይመስላል፡፡ ያኔ ነው ውሳኔ ላይ የደረስኩት። “ከቨር የሚባል ነገር አይታተምም፤ ካሴቱ በፋብሪካ ነው የሚታተመው” ብዬ ወሠንኩ። ምክንያቱም ሠው የሚከፍለው ገንዘብ እኩል ነው፤ ግን የተለያየ ጥራት ነው የሚያገኘው። አሁን ካሴቱን እራሱ በፋብሪካ አሳትሜ ሁሉም ሠው አንድ አይነት ጥራት ያለው ሥራ እንዲያገኝ እየጣርኩ ነው። ለእኔ ምናልባት ሊጐዳኝ ይችላል፡፡ ቢሆንም ይሔንን ማድረግ የግድ ነው፡፡ በኮፒ ራይት ጥሰት ዙሪያ መንግስት መፍትሔ እንዲሰጠን ብዙ ጊዜ ጠይቀናል፡፡ ለረጅም ጊዜ ጠብቀናል፡፡ ህጉ ተፈፃሚ መሆን ነበረበት፡፡ ነገር ግን የኮፒራይት ጥሰት ፈጽመው የምናሳስራቸው ሠዎች ቶሎ ይፈታሉ፡፡ ይሄ ተገቢ አይደለም፡፡ አሁን ትንሽ ለውጥ እየታየ ነው፡፡ የሚመለከተው ወገን ለጉዳዩ ትኩረት ቢሠጠው እኮ አርቲስቱ ብቻ ሳይሆን ሁሉም ተጠቃሚ ነው፡፡ እኛ ሀብታም ስንሆን መንግስትም ሀብታም ይሆናል፡፡ እና አሁንም ተስፋ አንቆርጥም፡፡
የአሁን ዘመን ድምፃውያን በቴክኖሎጂ ይታገዛሉ። ይሄ ነገር ጥቅሙ ነው ጉዳቱ የሚያመዝነው?
ቴክኖሎጂ ጥቅም እንዳለው ሁሉ ጉዳትም አለው፡፡ የድሮ አሠራር አድካሚ ቢሆንም ደስ ይላል፡፡ ሁሉም ሙዚቀኛ እኩል አጥንቶ፣ እኩል ሠርቶ ቀጥታ ነበር የሚቀዳው፡፡ አንድ ዘፈን ሰርተን ሰርተን ሊያልቅ ሲል ከተሳሳትን፣ እንደገና ሀ ብለን ነበር የምንጀምረው፡፡ ግን ቀጥታ እየሠሙ መቀዳት በጣም ደስ የሚል ነገር አለው። አሁን ደግሞ ቴክኖሎጂው በጣም አግዞናል፡፡ ብሳሳት እዛችው የተሳሳትኩበት ቦታ ብቻ ነው የምንቀዳው። ግን ኦሪጅናሉን የድምፅ ቅላፄ እየወሠደው ነው። እርግጥ እንደ ድምፃዊው ችሎታ ይለያያል፡፡ ለምሳሌ ቴክኖሎጂ እንዳለ ሆኖ በጥንቃቄና በጥራት መስራት ይቻላል፡፡ ይሄ ግን በባለሙያው ብቃት ይወሰናል፡፡ አንዳንዴ የሚዘገንን ነገር እሠማለሁ፡፡ አንዴ ሰምተሽው ሆ ብሎ የሚጠፋ ነገር ይሆናል፡፡ እናም ቴክኖሎጂ ጥቅምም ጉዳትም አለው፡፡
በኮምፒውተር ታግዘው አልበም የሚያወጡ አርቲስቶች በተለይ መድረክ ላይ ያንኑ ድምጽ ለማውጣት ሲቸገሩ ይታያል…
ልክ ነው፤ ድምፅ ላይ በጣም ችግር ያመጣል። ለዚህ ነው በተፈጥሮ ድምፅ መቀዳት ያለብን። አንድ ዘፋኝ ያልሆነ ሠው የድምፅ ልምምድ በማድረግ ዘፋኝ መሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን በእነዚህ የኮምፒውተር ሲስተሞች ታግዞ ከሰራ እንደምናየው ነው፤ መድረክ ላይ ያስቸግራል፡፡
አልበም በማውጣት ረገድ ከአሁኑኑ ከድሮው አሰራር የትኛው ቀና ነው? ለአርቲስቱ ማለቴ ነው…
የመጀመሪያ ካሴቴ የወጣ ጊዜ እኮ እንደ አሜሪካ ሰለብሪቲ ነበር የምንሠራው፡፡ ሁሉም ነገር በአሳታሚው በኩል ነው የሚያልቅልሽ። አሁን ግን በኮፒራይት ጥሰት የተነሳ ነጋዴው ከስራው ወጥቷል፡፡ ያሉትም ቢሆኑም በጣም እየከበዳቸው ነው፡፡ ብዙ ብር ካወጡ በኋላ ስራው ኮፒ ስለሚሆን አይደፍሩትም፡፡ አሁን ትንሽ ለውጥ አለ፡፡ በ2006 ደግሞ የተሻለ ለውጥ ይመጣል ብዬ አስባለሁ፡፡ እስከዛው ግን በግላችን እየሞከርን ነው። አልበም ሲሰራ ብዙ ወጪዎች አሉ፡፡ አልበሙን ካስደመጥን በኋላ ከኮንሠርት እናገኛለን በሚል ነው የምንሰራው፡፡
እስቲ ስለአዲሱ አልበምሽ ንገሪኝ…ወጪውን፣ አሳታሚውንና ስለ ስራዎችሽ ይዘት…
አልበሜ መጠሪያው “ያደላል” የሚል ነው። ስያሜው ብዙ ትርጉም አለው፡፡ አርቲስቱን ቤቱ ቁጭ ብሎ የሚዘርፈውን የሚመለከት ሊሆን ይችላል፡፡ ሰሙ ደግሞ እግዚአብሔር በአምሳሉ ሲፈጥረን ለሠው አድልቷል የሚል ነው፡፡ ወርቁን እንደተፈለገ መተርጐም ይቻላል። በዚህ አልበም ሳይካተቱ የቀሩ ብዙ ትላልቅ ስራዎች አሉ፡፡ ሁሉም ነገር ሊወጣ ስለማይችል ያልተሠሩት ከተሠሩት በላይ አሉ። ለአዲሱ አልበሜ ብዙ ወጪ ነው ያወጣሁት፡፡ በዚህ አጋጣሚ መግለጽ የምፈልገው ካሴቱ ላይ ከተለመደው ውጭ ብዙ ስራዎች መካተታቸውን ነው፡፡ ሌላ ጊዜ የተለመደው ሲዲ ላይ ነበር፡፡ አሁን ግን ካሴቱን “C80” አድርጌ 16 ዘፈኖች ተካተውበታል፡፡ ሲዲው ላይ 14 ዘፈኖች አሉ፡፡ አሁን በአሜሪካ ካሴት ፋሽን ሆኗል፡፡ የእኛ አገር ሲዲ ጥራቱ ብዙም አይደለም፡፡ ስለዚህ ካሴቱን ተመራጭ አድርጌያለሁ፡፡ ሙዚቃውን ሙሉ በሙሉ ያቀናበረው አበጋዝ ነው፡፡ በግጥምና በዜማ አዳዲስ ደራሲዎችን አሳትፌያለሁ:- ምስክር አወል፣ ማስረሻ ተፈራ፣ የእኔው አካሉ፣ ፀጋዬ ስሜ (ጥሩ ጉራጊኛ ሠጥቶኛል) የሸዋ ኦሮሞ ባህላዊ ዘፈንም ሠርቼአለሁ። እስከዛሬ የሀረር ኦሮሞን ባህላዊ ዜማዎች ነበር የምሰራው፡፡ አሳታሚዋ እኔ ነኝ፡፡ ለዚህ ስራ ከ500ሺ ብር በላይ ወጪ አድርጌአለሁ። አከፋፋዩ ደግሞ ትልቅ ስም ያለው ሮማርዮ ሪከርድስ ነው። በጣም ቆንጆ ስራ ነው። አንድን ስራ እኔ ካላመንኩበት አላወጣውም፡፡ ያለዚያ እኮ በየአመቱ ካሴት አወጣ ነበር፡፡
ጳጉሜ 5 ለአዲስ ዓመት ዋዜማ በሚሊኒየም አዳራሽ ትዘፍኛለሽ፡፡ ዝግጅት ምን ይመስላል?
የምንችለውን ያህል እያደረግን ነው። ከአዳዲሶቹ ዘፈኖችም የተወሰኑትን እጫወታለሁ። በአዲስ አመት ያልተደሠተ ሰው አመቱን ሙሉ አይደሠትም ይባላል፡፡
በ2005 ዓ.ም በአገር ደረጃ ምን ለውጥ አስተውለሻል?
ሁሌም መጥፎ ጐን ብቻ ማውራት ጥሩ አይደለም፤ በጐ ጐንም መወራት አለበት። ለምሳሌ ከአሠራር ለውጥ ብንነሳ፣ የውልና ማስረጃ ቢሮ ትልቅ አርአያ ነው፡፡ ልክ እንደ ውጪ አገር ቁጥር እየሰጠ ነው የሚያስተናግደው፡፡ ያለ ወረፋው የሚገባ የለም፡፡ በዚህ ረገድ አቶ ይርጋን በጣም ማመስገን ነው የምፈልገው፡፡ ምክንያቱም ሌላ ቦታ እኛ ቁጭ ብለን ስንጠብቅ፣ ነጮች በቅድምያ ሲስተናገዱ ነው የምናየው። ቅር ያለኝ የቦሌ መንገድ ነው፡፡ እርግጥ ነው የቦሌ መንገድ በጣም አምሮበታል ፤ ነገር ግን ባለ ህንፃዎቹ ፓርኪንግ አለመስራታቸው እንዳለ ሆነ የፓርኪንግ ችግር ተፈጥሯል፡፡ እዚያ አካባቢ መኪና አቁሞ እቃ መግዛት አልተቻለም። ድሮ ቦሌ የሚታወቀው ካፌዎቹ በረንዳ ላይ ሠዎች ቁጭ ብለው ሲዝናኑ ነበር፡፡ አሁን ከሠኞ እስከ አርብ ጭር ብሎ ነው የሚውለው፡፡ ሌላው የመንገዶቹ አሠራሮችና የመብራት ሁኔታ አካል ጉዳተኛን ያማከለ አይደለም፡፡ እነሱም ዜጐች ናቸው፡፡ ይሄን ጉዳይ በተመለከተ ሁለት ቀን በግሌ መንገድ ትራንስፖርት ሄጄ ነበር፡፡ ግን የማናግረው ሰው ማግኘት አልቻልኩም፤ ስብሠባ ናቸው በሚል ምክንያት፡፡ በኪነጥበብ ዘርፍ ግን ምንም ለውጥ የለም፤ አርቲስቱ እየደከመ ነው ያለው፡፡ እኔ ውጪ ሀገር ሠርቼ የመጣሁትን ነው እየበላሁ ያለሁት እንጂ፤ ኪነ ጥበብ ቀዝቅዟል፡፡
በትርፍ ጊዜሽ ምን ትሰርያለሽ?
የቤት ስራ ያስደስተኛል፤ አበስላለሁ። አትክልቶችን እንከባከባለሁ፡፡ የሁለት ልጆች እናት ነኝ፡፡ ትልቋ ልጄ ማክዳ ትባላለች። በዚህ አመት ከአሜሪካ፣ ፖኖን ዩኒቨርስቲ ትመረቃለች፡፡ አሜሪካን አገር ጐበዝ ተማሪዎችን ለማበረታታት የምርቃት ሰርተፍኬታቸውን ፕሬዚዳንቱ ናቸው የሚሰጡት - በኋይት ሀውስ፡፡ የእኔም ልጅ ከክሊንተን፣ ከቡሽ እና ከኦባማ እጅ ወስዳለች። ይሔ ደስ ይላል፡፡ አሁን በአንትሮፖሎጂ ትመረቃለች፡፡ ከዚያ ወደ አገሯ መጥታ የመስራት ፍላጐት አላት፡፡
ሀመልማል ትዳር ትፈራለች እንዴ?
ምን ያስፈራል? እግዚአብሔር ላለለት ሠው በጣም ይመከራል፡፡ ከመጣ ደግሞ ሠርግ መደገስ ይቻላል፡፡ ልጆቼም አንዳንዴ ያሾፉብኛል፤ “እኛ ሚዜ እንሆናለን፤ አንቺ ደግሺ፤ ግን ባል የለም” ይሉኛል፡፡ አሁንም ከመጣ እሰየው ነው፡፡
ምን ዓይነት ሙዚቃዎችን ማድመጥ ትወጃለሽ?
ማናቸውንም የትዝታ ዘፈኖች አደምጣለሁ። ከበፊቶቹ ሙሉቀን ለእኔ ልዩ ነው፤ ከወጣት የጐሳዬን ዘፈኖች እወዳለሁ፡፡ ሁሉም ግን የራሱ የሆነ ጣዕም አለው፡፡
በ2005 ዓ.ም ያስደሰቱሽንና ያስከፉሽን ጉዳዮች ጥቀሺልኝ…
የጥበብ አጋራችን የነበረውን ድምፃዊ እዮብን ማጣታችን አሳዝኖኛል፡፡ የእዮብን መልካምነት ለማወቅ የቀብር ስነስርዓቱን መመልከት በቂ ነው፡፡ እንደ አንጋፋዎቹ ነው በበርካታ ህዝብ የተሸኘው፡፡ ሌላው በመብራት ሃይል ችግር ቤቴ ተቃጥሎ ነበር። ምንም እንኳን ራሱ መብራት ኃይል ቢሠራውም። እንደዚህ አይነት ስህተት እንዳይከሠት መብራት ሀይል ጥንቃቄ ማድረግ አለበት፡፡ ካሴቴ አልቆ ለ2006 አዲስ ዓመት መድረሱ ደግሞ በዓመቱ ካስደሰቱኝ ነገሮች ዋነኛው ነው፡፡
ሞሃ ለስላሳ እንዴት 500ሺህ ብር ስፖንሰር አደረገሽ?
ይሄ ገና ያልተሰራና ያልተጣራ ነገር ነው፤ ስለዚህ በዚህ ጉዳይ ላይ ምንም መናገር አልፈልግም፡፡
ቀጣይ ዕቅድሽ ምንድነው?
በሙዚቃው መገስገስ ነው የምፈልገው፤ከራሴ ስራ አልፌ የሌሎችን ፕሮዲዩስ ማድረግ እፈልጋለሁ። አመል ፕሮዳክሽን የተባለ ድርጅት አቋቁሜያለሁ፤ በዛ በኩል የሌሎችን ስራዎች ለማሳተም እቅድ አለኝ።
ለዋዜማ ኮንሰርት ምን ያህል ተከፈለሽ?
ይሄ የግል ጉዳይ ነው፤ መናገር ይከብዳል፤ ምክንያቱም እኔ እንደሌሎች ያልተከፈለኝን ተከፈለኝ ብዬ አጋንኜ ማውራት አልፈልግም፡፡ ከአዘጋጆቹም ጋር ጉዳዩ በግል እንዲያዝ ተነጋግረናል፡፡ ስለዚህ መናገሩ አስፈላጊ አይደለም፡፡

Read 5011 times Last modified on Friday, 13 September 2013 13:13