Saturday, 24 August 2013 11:28

ሰላሳ ምናምነኛው ጋጋታ

Written by  አሸናፊ አሰፋ
Rate this item
(1 Vote)

      በቅርቡ “መልክአ ስብሃት፤ ስብሃት ገብረእግዚአብሔር በሰላሳ ፀሐፊያን፤ ገጣሚያን እና ሰዐሊያን እይታ” የምትል መፅሀፍ በአለማየሁ ገላጋይ አርታኢነት ታትማለች፤ አርታኢው በመጽሐፉ ጀርባ ላይ እንዲህ ብሎ ጽፏል፡- “ሠላሳ ያህል ፀሐፊያን፣ ገጣሚያንና ሰዐሊያን ስለስብሀት ገብረእግዚአብሔር ያላቸውን የተለያየ አመለካከት በአንድ ላይ አጣምረው በዚህ መድበል አቅርበዋል፡፡ ሥራው ለሥነ-ፅሑፋዊም ሆነ ለማህበራዊ ሂስ በአዲስነትና በበር ከፋችነት የሚጠቀስ ለመሆኑ አያጠራጥርም፡፡”
መልካም፡፡
ተስማምተናል፡፡
ይህ አዲስ እና የመጀመሪያው “መልክአ…” ስለሆነ (መልክአ ፀጋዬ፣ መልክአ በዐሉ፣ መልክአ አዳም ይኖራል ተብለናል) እንዴት መፃፍ እንዳለበት፣ ቅርጹ እና ይዘቱ ምን መሆን እንዳለበት የታወቀ ነገር ያለ አይመስለንም፡፡ ለምሳሌ፣ የአስፋው ዳምጤ ፅሁፍ ለምን መጀመሪያ፣ የፀደይ ወንድሙ ፅሁፍ ለምን መጨረሻ ላይ እንደቀረበ ምንም የተባለ ነገር የለም፡፡ ለካርቱኖቹ ማውጫ የላቸውም፤ ካርቱኖቹ የገቡበት ገጽ ላይ ለምን እንደገቡ አናውቅም፡፡ ለረዥም ዘመን የስብሃት መለያ የነበረውና የእግረመንገድ አምድ ጽሁፎቹን የሚያጅበው የማህሌት ወርቁ ካርቱን ለምን እንዳልተካተተም ገርሞናል፡፡ የወደድናት ካርቱን፣ ገጽ 263 ላይ ስብሃት ከሚወረወሩበት ጦሮች አንዷን ሲጋልብ የምታሳየው ናት፤ ድንቅ ብለናል፡፡
ከይዘት አንፃር አራት ህፀጾችን እንጠቅሳለን፡፡
የሌሊሳ ስህተት
የከበደ ስህተት
የአዳም ስህተት
የአውግቸው ስህተት
የሌሊሳ ስህተት
ሌሊሳ ግርማ “ስብሃት እና ሄሚንግዌይ አንድ ናቸው” በሚለው ፅሁፉ እንዲህ እያለ ያመሳስላቸዋል “ስብሃት የተወለደው አድዋ ነው፤ ሄሚንግዌይ ደግሞ ኦክፓርክ (ኤሊኖይ)፡፡ ሄሚንግዌይ በ 1899 እ.ኤ.አ. ነው የተወለደው፣ ስብሃት ደግሞ በአበሻ አቆጣጠር 1929 … ሁለቱም በተወለዱበት ዓመት ላይ ሁለት ዘጠኝ ቁጥሮች አሉባቸው፡፡ ስለዚህ አንድ ናቸው፡፡…” ተው እንጂ! እሺ 1899 እና 1929 በሁለት ዘጠኞች ይመሳሰሉ፡፡ አድዋ እና ኦክፓርክ (ኤሊኖይ) በምን ይመስላሉ? “አ ፊደል እና የአ ፊደል ዝርያ ስላላቸው ነዋ!” ሳይለን አይቀርም ብራቮ ልጅ፤ አሪፍ አዛምድ ነው ባክህ! “አይ ሌሊሳ ሲቀልድ ነው” ልንባል ይችል ይሆናል፡፡ እሱም እንዲያ አስመስሏል፡፡ እንዲያውም፡- “ይቅርታ! አሁን ወደ ቁምነገሩ ልምጣ…” በማለት በቀጥታ ወደ “ቁም ነገሩ” የሚመጣው እንዲህ እያለ ነው፡- “የሁለቱም ደራሲዎች ህይወት አልፏል፤… የሁለቱም ፊት በነጭ ፂም የተሸፈነ ነው…” ይሄ ነው ቁምነገሩ፡፡ ምን እየተባልን ነው? የሞቱና ፊታቸው በነጭ ፂም የተሸፈነ ደራሲዎች ሁሉ ይመሳሰላሉ? ኤድያ! አቦ ተዉና! “ስብሃትና ሄሚንግዌይ አንድ ናቸው” የሚል፤ “ እስኪ፣ እስኪ፣ እንዴት፣ እንዴት …” የሚል ጉጉት የሚፈጥር ርዕስ ይዞ ተነስቶ፣ በዘጠኝ ቁጥር፣ በሞት እና በፂም አንድ ናቸው ብሎ ነገር ምን ይሉት ማመሳሰል ነው?! መድበሉ ውስጥ ከተካተቱት ጽሁፎች አጭሩ የሌሊሳ ነው፡- እንኳንም አጠረ፡፡ ቢረዝም ሌላ ረዥም ስህተት ይጽፍ ነበር፡፡ ከላይ ያሉትን እንደምሳሌ ጠቀስን እንጂ ሌሎችም ማመሳሰያዎቹም ስህተት ናቸው፡፡ ሄሚንግዌይ ለቦክሰኛ አገዘ፣ ስብሃት ለዘፋኝ (ዘሪቱ) አገዘ፤ ስለዚህ አንድ ናቸው” ብሎ ማመሳሰል ምን ይሉት ነው?
የከበደ ስህተት
“ህያው ስብሃት” የሚል ርዕስ ያለው የከበደ ደበሌ ሮቢ ፅሁፍ እንዲህ ሲል ነው የሚጀምረው፡- “The Seventh Seal (ሰባተኛው ማህተም) የዝነኛው ስዊዲናዊ ደራሲ(?) ኢንግማን በርግማን መፅሀፍ (??) ርዕስ ነው፡፡” ውዲ አለን “ሁሉን አስተውለን ስንዳኝ፣ ኢንግማን በርግማን የሲኒማ ካሜራ ከተፈለሰፈ ወዲህ ከተፈጠሩ የፊልም ባለሙያዎች ታላቁ ነው፡፡” ያለለት የፊልም ፀሀፊ፣ ፕሮዲዩሰር እና ዳይሬክተር ነው - ኢንግማን በርግማን፡፡ ከበደ ሊጠቁም እንደሞከረው የልብ ወለድ ፀሀፊ አይደለም፤ The Seventh Sealም መፅሀፍ አይደለም፤ ፊልም ነው፡፡ ወይስ ከበደ ደበሌ ሮቢ መጽሐፍ ያያል፤ ፊልም ያነባል ሊባል ነው?
የአዳም ስህተት
“የዛሬ ድርጊት ትናንትናና ነገ በትውስታ የሚያያዙበት ነው፡፡” ብሎ የሚጀምረው አዳም ረታ፤ “የስብሃት ተረቶች ትዝታ” በሚል ርዕስ የቀረበ ነው፡፡ ፅሁፍ ስብሃትን “የማያፍር አስታዋሽ ነበር” ብሎ አሞግሶታል፡፡ የአዳም ፅሁፍ ከሌሎች ይለያል፡፡ ፍልስፍናዊ ነው፡፡ “ያለፉት በእርግጥ አልፈዋል” በሚል ጀምሮ፣ “ያለፉት በእርግጥ አልፈዋል?” ብሎ የሚያበቃ አሪፍ ፅሑፍ ነው፡፡ (ልዩነቱን ልብ ይሏል፡፡) ይህ ሰውም ግን የማትታለፍ ስህተት ፅፏል፡- “ከብዙ አስደሳች(?) አጫጭር ታሪኮቹ ሞፖሳ በ “ዘ ጊፍት ኦፍ ዘ ሜጃይ ትዝ ቢለን ከስርዓት አልወጣንም፡፡” ይላል አዳም፡፡ The Gift of the Magi የ ኦ ሄነሪ አጭር ልብ ወለድ ናት፡፡ ለምሳሌ፡- “ከብዙ አስደሳች አጫጭር ታሪኮቹ ከሰማይ የወረደ ፍርፍር ደራሲ ስብሃት ገብረእግዚሀብሄር ትዝ ቢለን ከስርዓት አልወጣንም፤ ወይም ከብዙ አሳዛኝ አጫጭር ታሪኮቹ የአምስት ስድስት ሰባት ደራሲ አዳም ረታ ትዝ ቢለን ከስርዓት አልወጣንም፡፡” የሚል አይነት ስህተት ብንሰራ አዳም የሚደብረው ይመስለናል፡፡ ይደብራል፡፡
የአውግቸው ስህተት
የአውግቸው ተረፈን ስህተት ምን ብለን እንደምንጠራው አላወቅንም፡፡ አውግቸው ለምን እንደፃፈው፣ አርታኢው ለምን ነቅሶ እንዳላስቀረው አልገባንም፡፡ ያለቦታው የገባ በጣም የሚያስጠላ የቂም አስተያየት ነው፡፡ አንብበነው ቀፈፈን፡፡ አውግቸውን ከጽሁፍ ስራዎቹ በተጨማሪ በጣም ያወቅነውና የወደድነው፣ ስንዱ አበበ በተናገረችው ነገር ነው፡፡ የሆነ ቃለ መጠይቅ ላይ ስለ አውግቸው ስታወራ፡- “እብደት ውስጥ እያለ ሌሎች ያንን እንዲያውቁ ስለእብደት መጽሀፍ ከመጻፍ የላቀ ደግነት የለም፡፡” ብላ ነበር፡፡
አውግቸው ስለባሴ ሀብቴ የፃፈውን እንዲህ እንደወረደ እንጠቅሳለን፡- “ያኔ እኔ የመንፈስ ጭንቀት አደረብኝና የኩራዝ መስሪያ ቤትን በገዛ ፈቃዴ ለቅቄ ወጣሁ፡፡ በየጠቅላይ ግዛቶቹም እዞር ጀመር፡፡ ደሴ፣ አሰብ፣ ድሬዳዋ፣ አርሲ፣ አዋሳ፣ ሻሸመኔ፣ ዲላ፣ መተከል፣ ደብረማርቆስ… አካልዬ ከተመለስኩ በኋላ ያጐቴ ልጅ አማኑኤል ሆስፒታል ወስዶ አስገባኝ፡፡ ከዚያ በደንብ ሳልታከም ጠፍቼ ወጣሁ፡፡ ያኔ ወደ አሮጌ መጽሐፍ ተራ እሄድ ነበር፡፡ ባሴ ሀብቴም “ውሽንፍር” እና ቃል የተባሉትን የትርጉም ስራዎች የመጽሐፍ ተራ ነጋዴዎች አሳትመውለት ከ “ውሽንፍር” አስር ሺህ ብር፣ ከ“ቃል” ሶስት ሺህ ብር አግኝቶ ስለነበር ከመጽሐፍ ተራ አይለይም ነበር፡፡
ያኔ የመጽሐፍ ተራ ሰዎች የኔን መታመም እና ጩቤ እየያዝኩ መዞር አይተው፣ ጩቤውን አስጥለው ወደ አማኑኤል ሆስፒታል ሊወስዱኝ ከእኔ ጋር ሲታገሉ “ተዉት፣ ልቀቁት ይሂድ፡፡ እሱ ሰሞኑን ሟች ነው” ብሎ ተናገራቸው፡፡ የመጽሐፍ ተራ ሰዎች ግን የሱን ቃል ሳይሰሙ እኔን ወደ አማኑኤል ሆስፒታል ወስደው አሳከሙ፡፡ እኔ ይኸው እስካሁን አለሁ፡፡ እሱ ግን ዘላለም ኗሪ መስሎ የነበረው ከኔ ቀድሞ ሞተ፡፡ ባሴ ማለት ከእኔ ጋር በአንድ ቤት ውስጥ ለስድስት ዓመታት አብሮኝ የኖረ ነው፡፡ ከአቶ ስብሃት ጋርም ያስተዋወቅሁት እኔ ነበርኩ፡፡”
ለህይወት እና ለሰው ምርጥ ፍቅር ስለነበረው ሰው (ስለ ስብሃት) የሚጽፍ ሰው፣ ከሞተ ከ 10 ዓመት በላይ ስለሆነው ባሴ ሃብቴ እንዲህ ያለቦታው የሻገተ ቂም ሲጽፍ፣ አስቀያሚ ስህተት ነው ከማለት ሌላ ምን እንላለን? (በነገራችን ላይ ነፍሱን ይማረውና ደምሴ ጽጌ እራሱ ባሴ ሃብቴ በሞተበት ዓመት አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ እንዲህ አይነት ቀፋፊ ጽሁፍ ጽፎ ነበር፡፡)
የአውግቸው ተረፈ ርዕስ “እኔና አቶ ስብሃት” ነው የሚለው፡፡
እኛ፣ አንዳንዶቹን ፅሑፎች ስናያቸው ፀሐፊዎቹ ስብሃትን ከራሳቸው አንፃር ያዩበትና ያሳዩበት ሳይሆን እራሳቸውን ከስብሃት አንጻር ለማየትና ለማሳየት የታተሩበት ነው፤ ባፈጠጠ ሁኔታ፡፡ ምን ያህል ያፈጠጠና ያገጠጠ መሆኑን የፀሐፊዎቹን ፅሑፍ እየጠቀስን እናሳያችኋለን፡፡ (ዋናውን ቁም ነገር በሚቀጥለው ሳምንት)

Read 2077 times