Saturday, 24 August 2013 11:31

እዚያው ሁን ግዴለም!

Written by  ነ.መ
Rate this item
(5 votes)

ሰሌ…
አገርህ ያችው ናት፤
ዛሬም ልባም የላት፡፡
የድሀ አገር ህዝቦች፣ ህልማቸው አንድ ነው
ራዕይ ይሉታል፣ ቅዠቱን ደራርተው፡፡
አምኜ ፃፍኩልህ፣ ግጥም የነብስህ ነው፡፡
እዚያው ሁን ግዴለም፤ እዚያው አጣጥመው፡፡
ሰሌ………..
“አንድ ዓመት አለፈ
አንድ ዓመት አረፈ”
አልንህ ተሰብስበን፤
ባንድ ሻማ ጉልበት፣ እኛ አንድ ዓመት ኖረን፡፡

አንድ ዓመት፣ ብዙ ቀን፣ ይመስለኝ ነበረ
አንድ ዓመት ሩቅ ቀን፤ ይመስለኝ ነበረ
ግን አሁን ሳሰላው
ተቀጭቶ ከቀረ፣ በዚያ ዓመት አንድ ሰው
ለካ አንድ ዓመት ማለት፣ አንድ ዕምቅ አፍታ ነው፡፡
ሰሌ…
እንዳላለቀ ፊልም
እንዳልጨረሱት ህልም
እንዳልቋጩት ፍቅር
ትዝ ትለኛለህ፡፡
እና ዛሬም አለህ፡፡
አልፏል እልህና
የማለፍን ትርጉም ታስጠፋብኛለህ፡፡
አይበቃኝም ቃሉ፣ ትዝታ እንዳልልህ
ምንም ነህ ሁሉም ነህ
ዛሬም ትስቃለህ …
ዛሬም ታሾፋለህ…
ዛሬም ብቻህን ነህ…
ግን እኛ ውስጥ አለህ!!
እንዴት ነው ትዝታ፣ አንተን እሚገልጽህ?
ሰው ትንግርቱ አያልቅም
ምኑ እንደሚማርክ ፣ ምክኑ አይታወቅም፤
ኪኑ አይገለጥም፡፡
አለው ብርቱ ውበት፣ አለው ብርቱ ህመም
ክፉም ክፉ አደለም፣ ደግሞ ደግ አደለም
እንደዚያ ነህ አንተም፡፡
ሰሌ …
አንዳንዴ አገር ማለት፣ ዕንቆቅልሽ አደል?
ጨካኝ - ተጨካኙ፣ አንድ ላይ ይኖራል፡፡
ያው እንደምታውቀው፣ መብራቱም ይጠፋል
ያው እንደምታውቀው፤ ባምቧውም ይደርቃል
ያው አምና እንዳየኸው፤ ስልኩም መስመር የለው፡፡
ንገር ጐንህ ካለ የሚመለከተው - አገር የመራ ሰው፡፡
ከነሙስናችን …
ከነብዥታችን…
ከነብሶታችን…
የሞትነውን ያህል፣ ኖረናል እያልን፤
እዚያው ቁጭ ብለናል፣ ያው እንዳስቀመጥከን፡፡
ሰሌ….
ዝም ብለህ ተኛ እዚያው፣ ለዓለም ለዘለዓለም
ያየኸው ነው ያለው፣ ካምናው ሌላ የለም፡፡
ንብረት ተዟዙሯል፣ ሰው አልተሻሻለም፤
በዕድሜ ማርጀት እንጂ፣ ልምላሜ የለም፤
ቀኑ ተገፋ እንጂ፣ ኑሮ አልተለወጠም
ውሃው ሊገድብ ነው፣ ኑሮ አልተገደበም፡፡
ሰሌ…
የእኛ ችግኝማ፣ ምኔም ሰው ነውና
በጐራ ወይ በጐጥ፣ ስለማንፈርጀው
ያንተ መታሰቢያ፣ ልባችን ብቻ ነው
ልብ ያነባ እንደሆን፣ የዕንባ ወንዙን እየው!
ዛሬም አብረኸን ነህ፣ እዚያው ሁን ጉድ የለም፡፡
ቀኑን ገፋን እንጂ ኑሮ አልተለወጠም
የነገን እንጃልን፣ ተስፋ ግን አይሞትም!!
ነሐሴ 15 2005 ዓ.ም
(ለሰለሞን ጐሣዬ ሙት ዓመት፣ ለቤተሰቡና ለካዛንቺስ ወዳጆቹ)
(የሰለሞን ጐሣዬን ሙት ዓመት ለማክበር፤ የጧፍ ማብራትና
የነብስ ይማር ሥነስርዓት አከባበር ላይ ለተገኛችሁ የካዛንቺስ አካባቢ ወዳጆቹ ልባዊ ምሥጋና ይድረሳችሁ!)

Read 2222 times