Saturday, 17 August 2013 12:12

“ሰውን ማሳቅ ከባድ ነው፤ ኑሮው ተጭኖታል”

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(7 votes)

ኮሜዲያንና ድምፃዊ ታሪኩ ሠማኒያ ሸሌ
ታሪኩ ሰማኒያ ሸሌ፤ ሀዋሳ ውስጥ ተወልዶ ያደገ ድምፃዊ፣ ኮሜዲያንና ተዋናይ ነው፡፡ “ጫት ያመረቅናል” በሚለው ነጠላ ዜማው የሚታወቅ ሲሆን መድረክ ላይ በሚያቀርባቸው ቀልዶቹ በተለይ በሀዋሳ ከፍተኛ እውቅናን አትርፏል፡፡ ወጣቱ በቅርቡ ሻና ፊልም ፕሮዳክሽን ፕሮዱዩስ ያደረገውን “ሀ በሉ” የተሠኘ የኮሜዲ ዘውግ ያለው ፊልም ከጓደኛው ቢኒያም ዳና ጋር የፃፈ ሲሆን የኦሊሴን ባህሪ ወክሎ በመሪ ተዋናይነት ተውኗል፡፡“ሸሌ” በተሰኘው የአያቱ ስም ምክንያት ስለገጠሙት ችግሮች፣ በአርቲስትነት ህይወቱና በወደፊት ህልሞቼ ጉዳዮች ዙሪያ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ በሀዋሳ አግኝታ አነጋግራዋለች፡፡

 እንተዋወቅ?

ስሜ ታሪኩ ሰማንያ ሸሌ ይባላል፡፡ ተወልጄ ያደግሁት እዚሁ ሃዋሳ ውስጥ ነው፡፡
ሸሌ የአያትህ ስም ነው? ትርጉሙ ምን ማለት ይሆን?
ረጅም ሳቅ… አንቺ ለምን የአያቴ ስም ላይ ትኩረት እንዳደረግሽ ገብቶኛል፡፡ ሸሌ የሚለው ቃል በህብረተሰቡ ምን ያህል ከባድና ምን ማለት እንደሆነ ስለምታውቂ ነው፡፡ ለማንኛውም ሸሌ የአገር ስም ነው አርባ ምንጭ አካባቢ የምትገኝ ትንሽ ከተማ ናት፡፡ እናም የአያቴ እናት እርጉዝ ሆነው በዚያ አካባቢ ሲያልፉ ድንገት ምጥ ይዟቸው አያቴ እዛች ከተማ ውስጥ በመወለዳቸው ነው ሸሌ የሚል ስያሜ ያገኙት፡፡
በአሁኑ ሰዓት ኮሜዲያን፣ ዘፋኝና ተዋናይ ከመሆንህ ባሻገር “ሀ በሉ” የተሰኘ ፊልም ከጓደኛህ ቢኒያም ዳና ጋር ጽፈህ ለእይታ አብቅተሃል፡፡ እስቲ ስለ ኪነ ጥበብ ህይወትህ ትንሽ አጫውተኝ?
የኪነ - ጥበብ ህይወቴ የሚጀምረው ከቤተ - ክህነት ነው፡፡ በሀዋሳ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ - ክርስቲያን ውስጥ ዘማሪ ነበርኩኝ፡፡ በቤታችን ውስጥ ለሀይማኖት ከሚሰጠው ከፍተኛ ግምት የተነሳ ቴፕ ለሬዲዮ ካልሆነ ሙዚቃ እንኳን ማዳመጥ አይፈቀድም ነበር፡፡ እኔ ግን የሙዚቃ ፍላጐት ስለነበረኝ ቤተሰቤን ፈርቼ ሌላ ሰፈር እየሄድኩ እዘፍን ነበር፡፡
ያኔ በልጅነትህ ስትዘፍን ቅጽል ስም እንደነበረህ ሰምቻለሁ፡፡ ንገረኝ እስቲ?
ልክ ነሽ ቅጽል ስሜ “ሻላ ባንድ” ይባል ነበር፡፡ ስታዲየም ውስጥ ገብቼ ብቻዬን ስዘፍን ነው ይህን ስም ያወጡልኝ፡፡ በስታዲየሙ የጨዋታው ግማሽ 45 ላይ እረፍት ሲሆን “ሻላ ባንድ እረፍት ላይ ነው” ብለው ቁም ሸንኮራ ይሰጡኛል፡፡ እኔም እስከቻልኩ ሸንኮራዬን ከበላሁ በኋላ ወደ ስራዬ እገባለሁ፡፡
መቼም አንድ ቁም ሸንኮራ ከበላህማ አጥር አፈረስክ እንጂ በላህ አይባልም አይደለ?
(በጣም እየሳቀ) ያው በይው… አጥር አፈረስክ ነው ያልሽኝ… ልክ ነሽ አጥር ማለት ነው፡፡
መቼ ነው ኮሜዲያን መሆን እንደምትችል ያወቅኸው?
በ1991 ዓ.ም መከላከያ ያወጣውን ማስታወቂያ በሬዲዮ ሰምቼ ሄድኩኝ፡፡ ግን እድሜዬ በወቅቱ ትንሽ ስለነበር ማደግና ማሻሻል እንዳለብኝ ተነግሮኝ ተመለስኩና እዚሁ ሃዋሳ ውስጥ በአማተር ክበባት ውስጥ መሳተፍ ጀመርኩኝ፡፡ ያኔ ግን ኮሜዲያን እና ዘፋኝ እንደምሆን እርግጠኛ ነበርኩ፡፡ እንደነገርኩሽ ከሰፈሬ ርቄ ሌላ ሰፈር እየሄድኩኝ እዘፍን ነበር፡፡ በፀረ -ኤድስ ክበባትም ውስጥ እንዲሁ ተሳትፎ ነበረኝ፡፡ በዚህ በዚህ አሁን ላለሁበት እደርሳለሁ የሚል እምነት ነበረኝ፡፡
በትክክል መድረክ ላይ መዝፈን የጀመርከውስ መቼ ነው?
ከቢጂአይ ድራፍት ባንድ ጋር ስራ ጀመርኩኝ፡፡ በዘፈንና መድረክ በመምራት የቢጂአይን ምርቶች አስተዋውቅም ነበር፤ እዚሁ ሃዋሳ ውስጥ፡፡ እግረ መንገዴንም ቀልዶችን አቀርብ ነበር ኮሜዲያንነትን ሳስብ ሞዴሌ ተስፋዬ ካሳ ነው፡፡ በጣም በጣም ነው የማደንቀው እንደሱ ያለ ኮሜዲያን ድጋሚ የማይ አይመስለኝም እና ከቢጂአይ ጋር ነው መድረክ ላይ መቆም የጀመርኩት፡፡
እንደሚታወቀው ተስፋዬ ካሳ ኮሜዲያን ብቻ ሳይሆን ድምፃዊም ነበር፡፡ ከዚህ ተነስተህ ነው ሁለቱንም አጣምረህ የቀጠልከው?
በትክክል! ተስፋዬን ከማድነቄ የተነሳ የእርሱን ስራዎች በጣም እከታተልና አዳምጥ ነበር፡፡ የእሱን ስራዎች ስከታተል ዘፋኝ እንደነበርም አወቅሁኝ፤ ያን ጊዜ ሁለት ቦታ ይከፈል የነበረው ልቤ ተረጋጋ፡፡ ወደ ሙዚቃው ጓዜን ጠቅልዬ ልግባ ወይስ ወደ ኮሜዲያንነቱ እያልኩ ልቤ መንታ መንገድ ላይ ነበር፤ ሁለቱንም ጐን ለጐን ማስኬድ እንደሚቻል ከተስፋዬ ነው የተማርኩት፡፡ አሁን ከሙዚቃና ከኮሜዲያንነት በተጨማሪ ተዋናይና የፊልም ደራሲ እስከመሆን ደርሻለሁ፡፡ ለሙያሽ ፍቅር ካለሽ የሚያቅት ነገር የለም፡
እንደሚመስለኝ መጀመሪያ የታወቅኸው “ጃ ያስተሰርያል” የተሰኘውን የቴዎድሮስ ካሳሁንን ዘፈን “ጫት ያመረቅናል” በሚል ከዘፈንክ በኋላ ነው…
አዎ ትክክል ነው፡፡ የዚህ ዘፈን ለአደባባይ መብቃት በራሱ ትንግርት ነው፡፡
እንዴት?
እየሁልሽ… ጫት ያመረቅናል የተሰራው በሀዋሳ ዩዝ ካምፓስ የወጣቶች ማዕከል ውስጥ ነው፡፡ በዚህ ማዕከል ውስጥ የተለያዩ የኪነ ጥበብ ስራዎች ይሰራሉ፡፡ ሰርከስ እና ከሰርከስ ጋር በተያያዘ ኦፔራ ሾው ይካሄዳል፡፡ እና አንዴ “ጐልደን ኤግ” የሚል ኦፔራ ሾው ተዘጋጅቶ ይህ ሾው በአንድ ሱሰኛ የሆነ ገፀ - ባህሪ ላይ ያጠነጥን ነበረ፡፡ ሾው ላይ ያለ ንግግር (“ማይም”) እያደረጉ ይሰሩ ስለነበር በሱስ ዙሪያ የማጀቢያ ሙዚቃ እንድሰራ ተጠየቅሁኝ፡፡ እኔ እንግዲህ በሙዚቃው በኩል ቴዲ ተጽእኖ ፈጣሪ ነው ብዬ የማስብና የማደንቀው በመሆኔ ዘፈኖቹን በማስመሰል እጫወት ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ሰው ሊቀበለውና ተጽእኖ ሊፈጥር በሚችል መልኩ “ጃ ያስተሰርያል”ን “ጫት ያመረቅናል” በሚል፡፡ በወቅቱ የሰራሁት ለዚያ ሾው ብቻ እንጂ ለገበያ አልነበረም፡፡
ግን እኮ በየሞባይሉ ሁሉ ተለቆ ሲደመጥ ነበር፡፡ እንዴት ለገበያ አልነበረም ትላለህ?
እኔ ያኔ ለተዘጋጀው ሾው ተጠቅመን እንዲጠፋ ነበር የፈለግሁት፡፡ አሁን አሜሪካ የሚገኝ ተስፋዬ የተባለ ጓደኛዬ,፣ (የአይኪዶ ስፖርት ኤክስፐርት ነበር) አሬንጅመንቱን የሰራልኝ፡፡ ይሄ ነገር ከተወደደ ለምን አትለቀውም አለኝ፡፡ እኔ ግን ቴዲ አፍሮን በጣም አከብረው ስለነበር መጠየቅ አለብኝ በሌላ ድምፅና ቅንብር እሰራዋለሁ የሚል አቋም ያዝኩኝ፡፡ በዚህ አቋም ላይ እንዳለሁ አማሮ ኬሌ ለስራ ሄጄ አንድ የአሮኬሌ ሰው አገኘኝ፡፡ እኔ የኮሬ ዘፈን ስዘፍን መጣና እያደነቀኝ እያለ ስልኩ ጠራ፡፡ መጥሪያው ደግሞ “ጫት ያመረቅናል” የሚል ነው፡፡ በጣም ደነገጥኩኝ፡፡
ከዚያስ? ከቴዲ አፍሮ በኩል ችግር አልገጠመህም?
በጣም ደግንጬ ከየት እንዳገኘው ስጠይቀው,፣ “አገር ምድሩ ሰምቶ የጨረሰውን እንዴት የት አገኘኸው ትለኛለህ?” አለኝ፡፡ እኔ ይህ ሙዚቃ ያለበት ኮምፒዩተር በፓስዎርድ እንደተቆለፈ ነበር የማውቀው፡፡ ሰውየውም ሀዋሳ አንድ ሞባይል ቤት ነው ያስጫንኩት አለኝ፡፡ ለካስ እዚህ ሀዋሳ አንድ ጆኒ ሞባይል የሚባል ሞባይል ሴንተር ያለው ጓደኛዬ ነው የለቀቀው፡፡ ያስፈመሰኝ መስሎት አሳነሰኝ (ያሳወቀኝ መስሎት ለማለት ነው) ከዚህ በኋላ አንዴ አምልጧል ከቴዲ በኩል ለሚመጣብኝ ጥያቄ መልስ የሚሆነኝን ነገር ማዘጋጀት ጀመርኩ፡፡ ሌላ አማራጭ የለኝም፡፡ ከዚያም ቴዲ ደወለ፤ ሁለት ቴዲ የሚባሉ ጓደኞች ነበሩኝ፡፡ እነሱ እንዳልሆኑ ብዬ በደንብ ጠየቅኩኝ “ቴዲ አፍሮ ነኝ” አለኝ፡፡ ደነገጥኩኝ፡፡ ስልኬን ከአርቲስቶች እንዳገኘ ነገረኝ፡፡ ተቀያየምን፡፡ ከዚያ አዲስ አበባ ሄጄ በወቅቱ “ዘማይንድ” የተባለ መፅሄት ላይ በሰጠሁት ቃል ይቅርታ ጠየቅኩት፡፡ በዚህ ተቋጨ፡፡
እንደሰማሁት ሙዚቃው ጫትን የሚያወድስ ሳይሆን የሚያወግዝ ነው፡፡ ቅመህ ታውቃለህ?
በፊት አልፎ አልፍ እሞክር ነበር፡፡ በነገርሽ ላይ የጫትን አስከፊነት፣ ከምርቃና በኋላ የሚፈጥረውን ነገር ለመግለፅ የግድ መቃም የለብሽም፡፡ የጫት ሱሰኛ ያልጠበበውን ጫማ ጠበበኝ ብሎ ይሸጣል፣ የሚቅምበት ካጣ የቤተሰቡን ንብረት ይሸጣል፡፡ አልፎ ተርፎም እስከ ስርቆት ይሄዳል፡፡ ይህ አይነት ጉዳት አለው ብሎ መልዕክት የሚያስተላልፍ ነው “ጫት ያመረቅናል” ብዬ የዘፈንኩት፡፡
በቅርቡ አንተና ቤሾ የተባለ ወጣት (“ጉዱ ማሌ” በተሰኘ ዘፈኑ ይታወቃል፡፡) በይሳቃል ኢንተርኔይመንት ተጋብዛችሁ ሸራተን ጋዝ ላይት ውስጥ ስራችሁን አቅርባችኋል፡፡ የታዳሚው አቀባበል ምን ይመስል ነበር?
ሸራተን ውስጥ ሰው እንደዚያ በጣም ሲስቅ ሳይ በጣም ነው የገረመኝ፡፡ በጣም ጥሩ ምላሽ ነው ያገኘነው፡፡ “በርቱ አሪፍ ነው” ያሉን አሉ፡፡ በዚህ አጋጣሚ ለስራው የጋበዙንን እናመሠግናለን፡፡
ሰውን ማሳቅ ከባድ ነው፤ ከፍተኛ የፈጠራ ችሎታና ጥረትን ይጠይቃል፡፡ አንተ በዚህ በኩል ምን ያህል እየተጋህ ነው?
አንድ ትልቅ ነገር አንስተሻል፡፡ በአሁኑ ወቅት ሰውን ማሳቅ ከባድ ነው፡፡ ሰው ኑሮው ተጭኖታል፤ ከተስፋ ይልቅ በትዝታ መኖር የጀመረበት ወቅት ነው፡፡ “ቁርጥ በኛ ጊዜ ቀረ” “ጤፍ በኛ ጊዜ ቀረ” የሚል ሰው በርክቷል፡፡ እንዲህ ያለ ጫና ያለበትን ሰው ለማሳቅ አንቺ ማማጥ አለብሽ፡፡ እኔ ሰው ሳቅ እንደሚፈልግ ሸራተን ስራዬን ባቀረብኩበት ወቅት ተመልክቻለሁ፡፡ በሳይንሱም ሳቅ ለብዙ ነገሮች ጠቃሚ ነው፤ ይህን ለማሳካት በጣም እየተጋሁ ነው፡፡ በሀዋሳ ብቻ ነበር የምታወቀው አሁን ከጓደኞቼ ጋር ወደ አዲስ አበባም እየመጣሁ መስራት ጀምሬያለሁ፡፡ ሁሌም መትጋትና መፍጠር ወሳኝ እንደሆነ ስለማምን፣ በአሁኑ ሰዓት በየቀኑ ሶስትና አራት ፈጠራዎችን እሠራለሁ “ታሪኩ ምን አዲስ ነገር አለ” ሲሉኝ፤ ደረቴን ነፍቼ መናገር እችላለሁ፡፡
ሸራተን ላይ ስራህን ስታቀርብ ስምህን በእንግሊዝኛ ተርጉመህ ሰውን አስቀኸው እንደነበር ሰምቻለሁ፡፡ እስኪ ለአንባብያን ተርጉሞላቸው…
የዛን ቀን እንዲህ አይነት ስም በአለም የለም፣ በጊነስ ላይ መመዝገብ አለበት ብለው አስተያየት የሰጡ ነበሩ፡፡ ስሜ ታሪኩ ሰማኒያ ሸሌ ነው፤ በእንግሊዝኛ ደግሞ “ሒስትሪ ኤይቲ ባር ሌዲ” ይባላል ስላቸው፣ ህዝቡ መሳቁን ማቋረጥ አልቻለም ነበር፡፡ እንደገና በአራድኛ ስሙን እንጥራው አሉ፡፡ “ታሪኩ ጋብቻ ባርሌዲ” ይሁን ተባለ፡፡ ያው ጋብቻ ሰማንያ ስለሚባል ለማንኛውም በእለቱ ስሜ አወዛጋቢና የስም “ኦሾ” ሆኖ ነበር ያመሸው፡፡
ከአያትህ ስም ጋር በተያያዘ የገጠሙህ ፈተናዎች እንዳሉ ሰምቻለሁ፡፡ እውነት ነው?
የሚገርምሽ ፋይናንስ ሀላፊ ተሳደብክ ተብዬ ከመንግስት መስሪያ ቤት ተገፍትሬ ወጥቻለሁ፡፡ የአያቴን ስም በመናገሬ ነው ተገፍትሬ የወጣሁት፡፡ የአያቴን ስም ስትጠይቀኝ ኮስተር ብዬ “ሸሌ” አልኳት፡፡ “እንዴት ሸሌ ትለኛለህ” ብላ ጮኸች፤ ተገፍትሬ ወጣሁ፡፡ ከዚያም በስንት መከራ ነው መታወቂያ አሳይቼ ያመኑኝ፡፡
ከአባትህ ሞት ጋር በተያያዘ ስማቸው ሲነሳ ብዙ ነገር መባሉን ከጓደኞችህ ሰምቻለሁ፡፡ እስኪ አጫውተኝ?
በነገርሽ ላይ አባቴ አቶ ሰማኒያ ሸሌ ከ1986 ወዲህ እስከሞተበት ጊዜ ድረስ ጭስ አልባው ኢንዱስትሪ በሚባለው በሽመና ስራ ላይ ብዙ እውቅና ነበረው፡፡ የሽመና ኢንዱስትሪ አስፋፍቶ ከ30 በላይ ሰራተኞች ያስተዳድር ነበር፤ ብዙ ሰው ያውቀዋል፡፡ በአጋጣሚ በወጣበት ይርጋለም ላይ በመኪና አደጋ ይሞትና አስክሬኑ መምጣቱ ሲሰማ፣ ሀዋሳ ላይ የህዝቡ ጩኸት ከዳር እስከዳር ቀውጢ ሆነ፡፡ የአማረ ሆቴል ባለቤት “አንተ አቡሽ ምንድነው ጩኸቱ?” ብለው አንዱን ልጅ ሲጠይቁት “ሰማኒያ ሸሌ በመኪና አደጋ ሞተ” ይላቸዋል፡፡ “ከአንድ መኪና ይሄ ሁሉ ሴት በአንዴ? ከካቻማሊ የበለጠ ከ60 ሰው በላይ የሚጭን መኪና አለ እንዴ? እንዴት በአንድ ጊዜ ሰማኒያ ሴቶች ይሞታሉ” ብለው እንደነበር በለቅሶው ሰሞን ሰምቻለሁ፡፡ አንዱ ደግሞ ሰማኒያ ሸሌ ሞተ ሲባል “የሀዋሳ ወንድ ጦሙን አደረ በለኛ” ብሎ ቀልዷል አሉ፡፡ ብቻ በአያቴ ስም ብዙ አስገራሚና አስቸጋሪ አጋጣሚዎችን አልፌያለሁ፡፡
“ሀ በሉ” የተሰኘውን ፊልም ከጓደኛህ ቢኒያም ዳና ጋር ፅፋችሁና መሪ ተዋናይ ሆናችሁ ሠርታችኋል፡፡ ሙዚቃ በውስጣችሁ ስላለ ነው ታሪኩን ከአይዶል ውድድር ጋር ያያያዛችሁት?
ታሪኩን እውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሠረተ ብንለውም ሊያዋጣ ይችላል፡፡ ማንኛውም አይዶል ተወዳዳሪ ብትመለከቺ፣ በዚህ ሂደት ያለፈ ይመስለኛል፡፡ እናም የውድድሩ ሂደት እኛ ፊት ለፊት እንደምንመለከተው አይደለም፡፡ ከጀርባው ስንመለከተው ብዙ ታሪክ አለው፡፡ አይዶል ሊወዳደሩ መጥተው በርካታ ውጣ ውረዶችን ያለፉ፣ “የመጣሁበት አካባቢ ምን ይለኛል” በሚል ሳይመለሱ በዚያው የቀን ስራ፣ የሆቴል አስተናጋጅ እየሆኑ የቀሩ ሞልተዋል፡፡ ወንዱም ዘበኛ የሆነበት አጋጣሚ ይኖራል፡፡ “ሀ በሉ” ፊልም ላይም የኤጌናና የኦሊሴ ታሪክ ይህን ነው የሚያሳየን፡፡ የሰራነው በአካባቢው የቋንቋ ዘይቤ ነው፤ የተሰራውም የተመረቀውም እዚሁ ሀዋሳ ውስጥ ነው፡፡ እነዚህ ገፀ ባህሪያት አገራቸው ላይ ያየሽው ስኬት ላይ የደረሱት ከስንት ልፋትና መማቀቅ በኋላ ነው፡፡ እና ሙዚቃ ውስጥ ስለሆንን ይህንን እናውቀዋለን፤ ለዚህ ነው የፃፍነው፡፡
ከቢኒያም ጋር ለመስራት እንዴት አሰብክ?
መጀመሪያ ፊልም አልነበረም፡፡ አጫጭር ስታንዳፕ ኮሜዲዎች ነበሩ፡፡ 16 ያህል ቀልዶችን ዳይሬክተሩ ዘታሪያን ጋር ይዤ ሄድኩኝ፡፡ ዘታሪያን የፊልሙ ዳይሬክተር ነው፤ በኋላ ቢኒ ሀሳቡን እንዲያካፍለን አደረግን፡፡ እያንዳንዱን ቀልድ ፊልም ሊያደርግ የሚችል ነፍስ ዘታሪያን ዘራበት፡፡ ከ16ቱ ቀልዶች ታሪክ ሊሆኑ የሚችሉትን መረጥን፡፡ ከነዚህም ውስጥ “አይዶል” የሚለው ቀልድ አንዱ ሆነ፡፡ ሌላው “ስጋ በል ስኩል” የሚለውም ቀልድ ልኳንዳ ቤቱ ላይ ያለውን ክፍል ሸፈነልን፡፡
በዚህ መልኩ ፊልሙ በፕሮፋዩሠርና ተዋናይ ሻሸሞ ዱካሌ በሻና ፊልም ፕሮዳክሽን አማካኝነት ለዚህ በቃ፡፡ በሲዳማ ባህል አዳራሽም ተመረቀ፡፡
በሙዚቃውም ሆነ በፊልሙ ወደፊት ምን አስበሀል?
በነገራችን ላይ ሁለተኛ ፊልሜን ጨርሻለሁ፡፡ “የአይን አባት” የተሰኘ ፊልም ፅፌ ጨርሻለሁ፡፡ ይህ ፊልም ከሙዚቃ ህይወቴም ጋር ይገናኛል፡፡ የ “ሀ በሉ” ፊልም ዳይሬክተር ዘታሪያን ፊልሙን ገምግሞታል፡፡ የተሻለ የታሪክ አወቃቀርና ይዘት እንዳለውም ነግሮኛል፡፡ ወደፊት የምናየው ይሆናል፡
ብዙ ሰው የሙዚቃም ይሁን የፊልም ስራ ተሰጥኦ አለኝ ብሎ ሲያስብ ቀጥታ የሚመጣው ወደ አዲስ አበባ ነው፡፡ እናንተ እዚሁ የተወለዳችሁበት ቦታ ስትሰሩ ገንዘብ ታወጣላችሁና ባያዋጣንስ ብላችሁ አልፈራችሁም?
ይህን ጥያቄ ሸራተንም በተጋበዝኩበት ጊዜ ተጠይቄ ነበር፤ የሚገርመው መስመር የሚጀምረው ከነጥብ ነው አይደለ? እኔ ከነጥብ ጀምሬ ሸራተን ውስጥ በርካቶችን ማሳቅ ችያለሁ፡፡ ፍፁም የራሴ ፈጠራ የሆኑ ፈጠራዎችን ይዤ ማለቴ ነው፡፡ ሸራተን ለመጋበዝ የበቃሁት ግን እዚሁ ሀዋሳ ጀምሬ በሠራሁት ስራ ነው፡፡ ይሳቃል ኢንተርቴይንመንት እኔን፣ ቢኒያምንና ቤሾን ጋብዞን ባገኘሁት አጋጣሚ፣ የእኔና የቢኒን ቁርኝት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታ እንደሆንን አድርጌ አስተዋውቄያለሁ፡፡ ምን ለማለት ፈልጌ ነው… የትውልድ አካባቢያችን ላይ ጀምረን ነው ወደ ዋና ከተማው እየተጋበዝን ያለነው፡፡ እዚህ ሀዋሳም ምቹ የኪነ-ጥበብ እድሎች እየተፈጠሩ ስለሆነ ብዙ መስራት እንችላለን፡፡ አሁን ለምሳሌ ሻና ፊልም ፕሮዳክሽን ተከፈተ፤ ብዙ እድሎችን እያመቻቸልን ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ ሻሸሞ ዱካሌን አመሰግነዋለሁ፡፡ ከዚህ ባለፈ አዲስ አበባም መጥተን ለመስራት የሚያግደን የለም፡፡ በጣም የምወደውና የማደንቀው ገጣሚና ደራሲ በእውቀቱ ስዩም በጋዝ ላይት የሰጠኝ አስተያየት ወደፊት በርካታ እድሎች ከፊት ለፊቴ እንዳለ የሚያመላክት ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ የትም ሆነሽ ጥሩ ከሰራሽ ስራሽ ራሱ ወደ ዋና ከተማው ይስብሻል፡፡ ይሄ ነው፡፡
በክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ውስጥ ትሰራ ነበር ልበል?
ትክክል ነው የባህል አምባሳደር፣ የመድረክ መሪ እና የግጥምና ዜማ ኤክስፐርት ሆኜ እሰራ ነበር፡፡ አሁን ግን በግሌ የኮሜዲውንም የሙዚቃውንም የፊልሙንም ስራ ለመስራት በገዛ ፈቃዴ ስራዬን ለቅቄ በግሌ እየተንቀሳቀስኩኝ እገኛለሁ፡፡
በመጨረሻ የምትለው ካለ…
የአይን አባት የተሠኘው ፊልሜን ከሠራሁ በኋላ አዲስ አበባ የመግባት ሀሳብ አለኝ፡፡ አንድም የመንግስት ስራዬን የለቀቅኩት በዚህ ምክንያት ነው፡፡ አዲስ አበባ ከመግባቴ በፊት “ምን ይዤ ልግባ” በሚለው መሰረት የቤት ስራዬ ላይ እየሰራሁ ነው፡፡ አዲስ አበባ ብዙ ሙዚቀኞች፣ ብዙ ኮሚዲያኖች፣ ብዙ የፊልም ፀሀፍት እና ተዋንያን ያሉባት ከተማ ናት፡፡ እኔም ተፎካካሪ ሆኜ መግባት አለብኝ እነዛን ስራዎቼን ከወዲሁ እየሰራሁ ነው እልሻለሁ፡፡ በዚህ ሁሉ ስራዬ አብረውኝ የሚሠሩትን አመሠግናለሁ፡፡

 

Read 6613 times