Saturday, 20 July 2013 11:26

የኢትዮጵያ ቡድን ለሞስኮና የዓለም ሻምፒዮና የውጤት ታሪክ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(10 votes)

ለ14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከ3 ሳምንት በኋላ በሞስኮ ሲካሄድ በኢትዮጵያ እና ኬንያ መካከል በረጅም ርቀት የአትሌቲክስ ውድድሮች ጠንካራ ፉክክር እንደሚታይ ተጠበቀ፡፡ ባለፈው ሰሞን ሁለቱም አገራት በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናውን የሚሳተፉባቸውን አትሌቶች ዝርዝር ሲገልፁ፤ ኢትዮጵያ በቡድኗ ከፍተኛ ልምድ ያላቸውንና ወጣት አትሌቶችን ስታዘጋጅ፤ በኬንያ በኩል በርካታ አዳዳዲስ አትሌቶች መያዛቸው ታውቋል፡፡የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በ14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በሚያሳትፈው ቡድን አትሌቶችን የመረጠው ወቅታዊ ብቃትና ለውድድር የሚያበቃ ሚኒማ የሚያሟሉትን በመለየት መሆኑን አመልክቷል፡፡ 42 አትሌቶች ይፋ በሆኑበት ዝርዝር ኢትዮጵያ በዓለም ሻምፒዮናው ከ800 ሜትር እስከ ማራቶን ባሉት የአትሌቲክስ ውድድሮች መሳተፏ ተረጋግጧል፡፡ ለ14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በተዘጋጀው የኢትዮጵያ ቡድን ከፍተኛ ልምድ ያላቸው አትሌቶች የያዘው ጥሩነሽ ዲባባ፤ መሰረት ደፋር፤ ቀነኒሳ በቀለ፤ ገለቴ ቡርቃ እና መሰለች መልጀካሙን ያካተተ ስብስብ በመኖሩ ነው፡፡

ጥሩነሽ ዲባባ በዓለም ሻምፒዮናው የተሳትፎ ታሪኳ 2 ወርቅ በ5ሺ እንዲሁም ሁለት ወርቅ በ10ሺ ሜትር ያገኘች ሲሆን መሰረት ደፋር ደግሞ በ5ሺ ሜትር 1 ወርቅ፣ 1 ብረና ሁለት የነሐስ ሜዳልያዎች ተጎናፅፋለች፡፡ በ10ሺ ሜትር ተጠባባቂ ሆኖ የተያዘው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በበኩሉ በ10ሺ አራት የወርቅ እንዲሁም በ5ሺ 1 የወርቅ እና 1 የነሐስ ሜዳልያዎችን ሰብስቧል፡፡ በኢትዮጵያ ቡድን በረጅም ርቀት የተያዙ አትሌቶች በውድድር ዘመኑ የተመዘገቡ ፈጣን ሰዓቶችን ከ1 እስከ 5 ያለውን ደረጃ የያዙ መሆናቸው በርቀቶቹ ሊኖር የሚችለውን የሜዳልያ ተስፋ ያጠናከረ ነው፡፡ በተለይ በ5ሺ ሜትር የኔው አላምረውና ሃጎስ ገብረህይወት እንዲሁም በ10ሺ ሜትር ኢብራሂም ጄይላንና ኢማና መርጋ ለሜዳልያ ተፎካካሪነት የሚጠበቁ ወጣት አትሌቶች ናቸው፡፡ በሌላ በኩል የቡድኑ ጥንካሬ በማራቶን ቡድኑ የሚታይ ሲሆን ብዙዎቹ ማራቶኒስቶቸ ዘንድሮ በትልልቅ የማራቶን ውድድሮች ያሸነፉ መሆናቸው በሞስኮ የሜዳልያ እድል ሊኖር እንደሚችል ግምት ያሳድራል፡፡
በ800፤በ1500 በ3000 ሜትር መሰናክል
ሶስቱ የርቀት አይነቶች የኢትዮጵያን ተሳትፎ ከማጠናከር እና ተፎካካሪነቷን ከማጎልበት አንፃር የሚታዩ ይሆናሉ፡፡ ከ800 ሜትር እስከ 3000 ሜትር መሰናክል ባሉ የአትሌቲክስ ርቀቶች የሚኒማ መስፈርቱን ያሟሉ ጥቂት በመሆናቸው ያለውን ኮታ ለማሟላት ፌዴሬሽኑ ከማናጀሮች ጋር በመነጋገር እስከ ሐምሌ አጋማሽ ሚኒማ የሚያስመዘግቡበት እድል መኖሩን በፌደሬሽኑ በኩል ተገልጿል፡፡ ኢትዮጵያ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ1500 ሜትር የሜዳልያ ስኬት የላትም፡፡ በሴቶች 1500 ሜትር ሜዳልያ ተወስዶ የማያውቅ ሲሆን በወንዶች ብቸኛ የሜዳልያ ድል የተገኘው ደግሞ በ2009 እኤአ ላይ ደረሰ መኮንን በወሰደው የብር ሜዳልያ ነው፡፡ በ3ሺ መሰናክልም በሁለቱም ፆታዎች የሜዳልያ ውጤት ተመዝግቦ አያውቅም፡፡
በ14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ1500 ሜትር ሴቶች በዳይመንድ ሊግ ውድድሮች ጥሩ ብቃት በማሳየት ላይ የምትገኘው ገንዘቤ ዲባባ ብቻ ተይዛለች፡፡ በ1500 ሜትር ወንዶች ደግሞ መኮንን ገብረመድህን፣ አማን ወጤ፣ አብዮት አብነት እና በተጠባባቂነት ዘነበ ዓለማየሁ ተመርጠዋል፡፡ በ800 ሜትር ሴቶች ከዓመት በፊት የለንደን ኦሎምፒክ ባለቀ ሰዓት በደረሰባት ጉዳት ያመለጣት ፋንቱ ሜጌሶ አሁን በጥሩ ሁኔታ በማገገም ለዓለም ሻምፒዮናው ትደርሳላች ተብሎ ሲጠበቅ፤ በዳይመንድ ሊግ ውድድሮች ውጤታማ የሆነውና የኬንያው ሩዲሻ አለመኖር ብቸኛ የሜዳልያ ግምት የሚያገኘው አትሌት መሐሙድ እንዲሁም አዲሱ ወጣት አትሌት አማን እና አማን ወጤ በ800 ሜትር ወንዶች የተያዙ ናቸው፡፡ በ3ሺ ሜትር መሰናክል በለንድን ኦሎምፒክ በመሳተፍ ጥሩ ልምድ ያገኙ አትሌቶች በኢትዮጵያ ቡድን ሲያዙ በሴቶች ሶፊያ አሰፋ፣ ሕይወት አያሌው፣ እቴነሽ ዲኖና በተጠባባቂነት ብርቱካን ፈንቴ ተመርጠዋል፡፡ በወንዶች 3ሺ ሜትር መሰናክል ደግሞሮባ ጋሪና ሐብታሙ ጃለታ ተይዘዋል፡፡
በ5ሺ ሜትር
ሞስኮ ላይ ኢትዮጵያ ቢበዛ 6 ቢያንስ 3 የሜዳልያ ድል ከምትጠብቅባቸው ውድድሮች አንዱ በ5ሺ ሜትር ነው፡፡ በእርግጥ በ5ሺ ሜትር ሴቶች ፍፁም የበላይነት የነበራት ኢትዮጵያ የወርቅ እና የብር ሜዳልያዎች ሳታገኝ ሁለት የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች አልፈዋል፡፡ በወንዶች 5ሺ ሜትርም ቢሆን የወርቅ ሜዳልያውን ለማግኘት ለኢትዮጵያ አትሌቶች ፈተና ሆኖ ቆይቷል፡፡ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ5ሺ ሜትር ሴቶች ኢትዮጵያ በነበራት የተሳትፎ ታሪክ 3 የወርቅ ፤ 1 የብርና 5 የነሐስ ሜዳልያዎችን ሰብስባለች፡፡ በ1999 እና በ2001 እኤአ ላይ በተደረጉት ሁለት ተከታታይ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች አየለች ወርቁ ሁለት የነሐስ ሜዳልያዎችን በማግኘት ፈርቀዳጅ ነበረች፡፡ ከዚያም በ2003 እኤአ ጥሩነሽ ዲባባ የወርቅ፤ በ2005 እኤአ ጥሩነሽ ዲባባ የወርቅ፣ መሰረት ደፋር የብር እንዲሁም እጅጋየሁ ዲባባ የነሐስ፤ በ2007 እኤአ መሰረት ደፋር የወርቅ፤ በ2009 እና በ2011 እኤአ መሰረት ደፋር ሁለት የነሐስ ሜዳልያዎችን በርቀቱ አግኝተዋል፡፡ በሌላ በኩል በ5ሺ ሜትር ወንዶች በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ለኢትዮጵያ የመጀመርያው የሜዳልያ ውጤት የተመዘገበው በ1991 እኤአ ላይ በፊጣ ባይሳ በተገኘው የብር ሜዳልያ ነው፡፡

ከዚያ በኋላ በ1993 እኤአ ላይ ሃይሌ ገብረስላሴ የብርና ፊጣ ባይሳ የነሐስ፤ በ2001 እኤአ ላይ ሚሊዮን ወልዴ የብር፤በ2003 እኤአ ላይ ቀነኒሳ በቀለ የነሐስ፤ በ2005 እኤአ ላይ ስለሺ ስህን የብር፤ በ2009 እኤአ ላይ ቀነኒሳ በቀለ የወርቅ እንዲሁም በ2011 እኤአ ላይ ደጀን ገብረመስቀል የነሐስ ሜዳልያዎችን ወስደዋል፡፡ በአጠቃላይ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ5ሺ ሜትር ወንዶች በኢትዮጵያ አትሌቶች የተመዘገበው ውጤት ከሴቶቹ ያነሰ ሲሆን 1 የወርቅ፤ ሁለት የብርና ሁለት የነሐስ ሜዳልያዎች ናቸው፡፡
በ14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ5ሺ ሜትር በሁለቱም ፆታዎች የተያዙት አትሌቶች የውድድር ዘመኑን ፈጣን ሰዓቶችን በማስመዝገብ ከ1 እስከ 3 ያለውን ደረጃ የያዙ ናቸው፡፡ በሴቶች 5ሺ ሜትር ጥሩነሽ ዲባባ፣ አልማዝ አያና፣ መሠረት ደፋር በዋና ቴዳዳሪነት ሲመረጡ በተጠባባቂነት ገለቴ ቡርቃ ተይዛለች፡፡ በወንዶች ደግሞ የኔው አላምረው፣ ሐጐስ ገብረሕይወት፣ ሙክታር ከድር እንዲሁም በተጠባባቂነት ይገረም ደመላሽ ተመራጭ ሆነዋል፡፡ 
በ10ሺ ሜትር
በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የኢትዮጵያ የበላይነት ካልተነቀነቀባቸው የውድድር ርቀቶች ዋንኛው 10ሺ ሜትር ነው፡፡ ከ1983 እኤአ ጀምሮ በተካሄዱ 13 የዓለም ሻምፒዮናዎች ኢትዮጵያ 9 የወርቅ ሜዳልያ በወንዶች እንዲሁም 5 የወርቅ ሜዳልያ በሴቶች በማግኘት ተሳክቶላታል፡፡ በዓለም ሻምፒዮና ላይ በ10ሺ ሜትር ወንዶች የመጀመርያው የሜዳልያ ድል የተመዘገበው በ1993 እኤአ በኃይሌ ገብረስላሴ በተገኘው የወርቅ ሜዳልያ ነበር፡፡ ከዚያም በኋላ በ1995፣ በ1997 እና በ1999 እኤአ ላይ ሶስት የወርቅ ሜዳልያዎችን አከታትሎ የተጎናፀፈውም ራሱ ኃይሌ ገብረስላሴ ነበር፡፡ በ1999 እኤአ ላይ አሰፋ መዝገቡ ተጨማሪ የብር ሜዳልያ ወስዷል፡፡ በ2001 እኤአ ላይ አሰፋ መዝገቡ የብርና ኃይሌ ገብረስላሴ የነሐስ፤ በ2003 እኤአ ቀነኒሳ በቀለ የወርቅ፣ ኃይሌ ገብረስላሴ የብርና ስለሺ ስህን የነሐስ፤ በ2005 እኤአ ላይ ቀነኒሳ በቀለ የወርቅ እና ስለሺ ስህን የብር፤ በ2009 እኤአ ቀነኒሳ የወርቅ እንዲሁም በ2011 እኤአ ላይ ኢብራሂም ጄይላን የወርቅ እና ኢማና መርጋ የነሐስ ሜዳልያዎችን በመሰብሰብ የኢትዮጵያን የበላይነት ለረጅም ጊዜ አስጠብቀዋል፡፡ በአጠቃላይ ኢትዮጵያ በዓለም ሻምፒዮና የተሳትፎ ታሪኳ በ10 ሺ ሜትር ወንዶች 9 የወርቅ፣ 4 የብርና 4 የነሐስ ሜዳልያዎችን ሰብስባለች ማለት ነው፡፡

በሌላ በኩል በ10ሺ ሜትር ሴቶች በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የኢትዮጵያ የመጀመርያው የሜዳልያ ድል የተመዘገበው በ1995 እኤአ ደራርቱ ቱሉ በተጎናፀፈችው የብር ሜዳልያ ነበር፡፡ በ1999 እኤአ ላይ ጌጤ ዋሚ የወርቅ፤ በ2001 እኤአ ደራርቱ ቱሉ የወርቅ፣ ብርሃኔ አደሬ የብር እና ጌጤ ዋሚ የነሐስ፤ በ2003 እኤአ ብርሃኔ አደሬ የወርቅ እና ወርቅነሽ ኪዳኔ የብር፤ በ2005 እኤአ ጥሩነሽ ዲባባ የወርቅ፣ ብርሃኔ አደሬ የብር እና እጅጋየሁ ዲባባ የነሐስ፤ በ2007እኤአ ጥሩነሽ ዲባባ የወርቅ፤ በ2009እኤአ መሰለች መልካሙ የብርና ዉዴ አያሌው የነሐስ ሜዳልያዎች አግኝተዋል፡፡ በአጠቃላይ ኢትዮጵያ በዓለም ሻምፒዮና የተሳትፎ ታሪኳ በ10 ሺ ሜትር ከ2 አመት በፊት ምንም አይነት የሜዳልያ ውጤት ባይኖራትም ከዚያ በፊት በተካሄዱ የዓለም ሻምፒዮናዎች 5 የወርቅ፣ 5 የብርና 3 የነሐስ ሜዳልያዎችን አግኝታለች፡፡
በ14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ10ሺ ሜትር ሴቶች መሠረት ደፋር፣ ጥሩነሽ ዲባባ፣ በላይነሽ ኦልጅራ በዋና ተወዳዳሪነት ሲመረጡ አባብል የሻነው የተባለች አዲስ አትሌት ተጠባባቂ ነች፡፡ በወንዶች የ10ሺ ሜትር ቡድን ደግሞ ከ2 ዓመት በፊት በዴጉ የዓለም ሻምፒዮና ለኢትዮጵያ ብቸኛውን የወርቅ ሜዳሊያ ያስመዘገበውና በቀጥታ ተሳታፊ የሚሆነውን ኢብራሂም ጃይላን ጨምሮ ደጀን ገብረመስቀል፣ አበራ ኩማና ኢማና መርጋ በዋናነት ሲመረጡ በተጠባባቂነት የተያዘው ቀነኒሳ በቀለ ነው፡፡
በማራቶን
ኢትዮጵያ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የተሳትፎ ታሪኳ በማራቶን ውድድር በሁለቱም ፆታዎች ከ1 በላይ የወርቅ ሜዳልያ አግኝታ አታውቅም፡፡ በወንዶች ማራቶን ኢትዮጵያ የመጀመርያ የሜዳልያ ድሏን በመጀመርያው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ1983 እኤአ ላይ ያገኘችው ከበደ ባልቻ ባስመዘገበው የብር ሜዳልያ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ በ2001 እኤአ ላይ ገዛሐኝ አበራ ብቸኛውን የወርቅ ሜዳልያ ድል አስመዘገበ፡፡ በ2009 እኤአ በፀጋዬ ከበደ እንዲሁም በ2011 እኤአ በፈይሳ ሌሊሳ ሁለት የነሐስ ሜዳልያ ተገኝቷል፡፡በሴቶች ማራቶን ኢትዮጵያ በዓለም ሻምፒዮናው ያስመዘገበችው ብቸኛው የሜዳልያ ድል በ2009 እኤአ ላይ አሰለፈች መርጊያ ያስመዘገበችው የነሐስ ሜዳልያ ብቻ ነው፡፡
በ14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በወንዶች ማራቶን ፀጋዬ ከበደ፣ ሌሊሳ ዲሳሳ፣ ፈይሳ ሌሊሳ፣ ታደሰ ቶላ፣ ጥላሁን ረጋሳ ዋና ተወዳዳሪዎች ሲሆኑ በተጠባባቂነት የተያዘው የማነ ፀጋዬ ነው፡፡ በሴቶች ደግሞ የለንደን ኦሊምፒክ አሸናፊዋ ቲኪ ገላና፣ አበሩ ከበደ፣ ፈይሴ ታደሰ፣ መሠረት ኃይሉ፣ መሰለች መልካሙ ሲመረጡ መሪማ መሐመድ ተጠባባቂ ነች፡፡ ተካተዋል፡፡ 
ምርቃት
ከ1983 እኤአ ጀምሮ በተካሄዱ 13 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች 92 አገራት የሜዳልያ ስኬት ያገኙ ሲሆን ከአንድ ለሶስት ለሚወጡ ስፖርተኞች 1756 ሜዳልያዎች ተሸልመዋል፡፡ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የምንግዜም የሜዳልያ ስብስብ ደረጃ አንደኛ የሆነችው 275 (132 ወርቅ፤ 74 ብር እና 69 ነሐስ)ሜዳልያዎች በማስመዝገብ ነው፡፡ ራሽያ በ151 (46 ወርቅ፤ 56 ብር እና 49 ነሐስ) ሜዳልያዎች በመሰብሰብ ሁለተኛ ደረጃ ስትይዝ ጎረቤት አገር ኬንያ በ100 (38 ወርቅ፤ 33 ብር እና 29 ነሐስ) ሜዳልያዎች ሶስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ ኢትዮጵያ ባለፉት 13 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች በሙሉ በመሳተፍ በ54 (19 ወርቅ፤ 16 ብር እና 19 ነሐስ) ሜዳልያዎች በማስመዝገብ በ7ኛ ደረጃ ተቀምጣለች፡፡
በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ታሪክ የኢትዮጵያን ትልቅ ውጤት ያስመዘገበው አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ ሲሆን 7 ሜዳልያዎችን (4 የወርቅ፤ ሁለት የብር እና 1 የነሐስ) በመሰብሰብ ነው፡፡ ይህ የኃይሌ ወጤት በከፍተኛ የሜዳልያ ስብስብ ከዓለም 4ኛ ከኢትዮጵያ አንደኛ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ ቀነነኒሳ በቀለ በ6 ሜዳልያዎች (5 የወርቅ እና 1 የነሐስ) በማስመዝገብ ከዓለም 6ኛ ከኢትዮጵያ 2ኛ ነው፡፡
በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በኢትዮጵያውያን ተይዘው የሚገኙ ሶስት የዓለም ሻምፒዮና ሪከርዶች አሉ፡፡ የመጀመርያው በ2003 እኤአ ላይ በ9ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ በ10ሺ ሜትር ብርሃኔ አደሬ የወርቅ ሜዳልያ ስታገኝ በ30 ደቂቃ ከ04.15 ሴኮንዶች ያስመዘገበችው ነው፡፡ ሁለተኛው በ2005 እኤአ በ10ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ5ሺ ሜትር ጥሩነሽ ዲባባ አሸንፋ የወርቅ ሜዳልያ ስትወስድ በ14 ደቂቃ ከ38.59 ሰኮንዶች በሆነ ጊዜ ያስመዘገበችው ነው፡፡ 3ኛው ደግሞ በ2011 እኤአ በ12ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ10ሺ ሜትር ቀነኒሳ በቀለ የወርቅ ሜዳልያ ሲጎናፀፍ 26 ደቂቃ ከ46.31 ሰኮንዶች በሆነ ጊዜ ያስመዘገበው ነው፡
ኢትዮጵያ ከ1983 እኤአ ጀምሮ በተካሄዱት 13 የዓለም ሻምፒዮናዎች በነበራት የተሳትፎ ታሪክ ሜዳልያ ሳታገኝ የቀረችው ውድድሩ 2ኛው የዓለም አትሌቲስ ሻምፒዮና በ1987 እኤአ በተካሄደበት ወቅት ብቻ ነበር፡፡

በ1983 እኤአ ላይ በ1ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ሄልሲንኪ ፊንላንድ ላይ በ1 የብር ሜዳልያ ከዓለም 15ኛ፤ በ1991 እኤአ በ3ኛው ስቱትጋርት ጀርመን ላይ በ1 የብር ሜዳልያ ከዓለም 21ኛ፤ በ1993 እኤአ በ4ኛው በ1 የወርቅ፣ በ1 የብርና በ1 የነሐስ ሜዳልያ ከዓለም 12ኛ፤ በ1995 እኤአ በ5ኛው ጉተንበርግ ስዊድን ላይ በ1 የወርቅ እና በ1 የብር ሜዳልያ ከዓለም 16ኛ፤ በ1997 እኤአ በ6ኛው አቴንስ ግሪክ ላይ በ1 የወርቅ ሜዳልያ ከዓለም 22ኛ፤ በ1999 እኤአ በ7ኛው ሲቪያ ስፔን ላይ በ2 የወርቅና 3 የነሐስ ሜዳልያ ከዓለም 9ኛ፤ በ2001 እኤአ በ8ኛው ኤድመንትን ካናዳ ላይ በ2 የወርቅ፣ 3 የብርና 3 የነሐስ ሜዳልያ ከዓለም 7ኛ፤ በ2003 እኤአ በ9ኛው ሴንትዴኒስ ፈረንሳይ ላይ በ3 የወርቅ፣ 2 የብርና 2 የነሐስ ሜዳልያ ከዓለም 4ኛ፤ በ2005 እኤአ በ10ኛው ሄልሲንኪ ፊንላንድ ላይ በ3 የወርቅ፣ 4የብርና 2 የነሐስ ሜዳልያ ከዓለም 3ኛ፤ በ2007 እኤአ በ11ኛው ኦሳካ ጃፓን ላይ በ3 የወርቅና 1 የነሐስ ሜዳልያ ከዓለም 4ኛ፤ በ2009 እኤአ በ12ኛው በርሊን ጀርመን ላይ በ2 የወርቅ፣ 2 የብርና 4 የነሐስ ሜዳልያ ከዓለም 7ኛ እንዲሁም በ2001 እኤአ በ13ኛው ዴጉ ደቡብ ኮርያ ላይ በ1 የወርቅና 4 የነሐስ ሜዳልያ ከዓለም 9ኛ ደረጃ ያገኘችበትን ውጤት አስመዝግባለች፡፡

Read 6133 times