Saturday, 05 January 2013 11:03

“አቦ! እኛ ጋ ችግር የለም፤ ጣጣ የምታበዙት የመሃል አገር ሰዎች ናችሁ”

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ /ከድሬዳዋ/
Rate this item
(1 Vote)

ገና እና መውሊድ በድሬዳዋና ሐረር
የበረሃዋ ገነት በሚል መጠሪያ የምትታወቀው የድሬዳዋ ከተማ ሰሞኑን በበዓላት ግርግር ተሟሙቃለች፡፡ ከአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በተሰባሰቡ ምዕምናን የቁልቢ በዓልን በቅርቡ ያከበረችው ድሬዳዋ፤ አሁን ደግሞ የገና እና የመውሊድ በዓላትን ለማክበር ሽርጉዱን ተያይዛዋለች። አካባቢውን ከሌሎች አካባቢዎች ለየት የሚያደርገው ሁለቱንም በዓላት በእኩል ደረጃ ለማክበር የሚዘጋጁ ነዋሪዎች ያሉበት መሆኑ ነው፡፡ የድሬዳዋው ታይዋን ገበያ በገና ዛፎችና መብራቶች ገበያ ሞቋል፡፡ እየተዘዋወርኩ ገበያውን ስቃኝ በገና ዛፍ ገበያ ላይ የነበረች አንዲት ሴት ትኩረቴን ሳበችውና ተጠጋኋት፡፡ የለበሰችው ድርያና ኢጃቧ ወጣቷ የእስልምና እምነት ተከታይ እንደምትሆን ግምት አሳደረብኝና ጠየቅኋት፡፡

ላቀረብኩላት ሠላምታ የሰጠችኝ ምላሽ ሞቅ ያለና ደስ የሚል ነበር። ሃናን እባላለሁ አለችኝና የግምቴን ትክክለኛነት አረጋገጠችልኝ፡፡ በገና ዛፍ ገበያ ላይ እሷን ማየቴ እንዳስገረመኝ ስነግራት፣ በእኔ መገረም እሷ መልሳ ተገረመች፡፡ የገና ዛፉ ለክርስትያን ጓደኛዋ ስጦታ የተገዛ መሆኑንና በእነሱ አካባቢ ይህ የተለመደና ሁሉም ሰው የሚያደርገው መሆኑን አጫወተችኝ። ሃናን በክርስቲያን በዓላት ላይ ሁሌም እንደምትገኝ በተለይ በተለይ ግን ለደመራ፣ ለገና እና ለጥምቀት በዓላት ልዩ ስሜት እንዳላት ነገረችኝ፡፡ ይህ ሁኔታ በእሷ ብቻ ሣይሆን በአብዛኛው የድሬዳዋና ሃረር ከተሞች ነዋሪዎች ዘንድ የተለመደ ጉዳይ መሆኑንም ጠቆመችኝ፡፡ ሃናንን ተሰናብቼ በደመቀው የታይዋን ገበያ መሀል ወጣሁ። ደቻቱ፣ ነምበርዋን፣ ኮኔል፣ ከዚራ፣ ለገሃሬ፣ ፈረስ መጋላ፣ ካራማራ … ሰፈሮቹን አካለልኳቸው፡፡ ድሬዎች ለሚጠየቁት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠትና ለመተባበር ዝግጁ ናቸው፡፡ አንድም ሰው ጥያቄዎቼን በጥርጣሬ የተመለከተና ምላሽ ለመስጠት ያንገራገረ አልነበረም። “አቦ ችግር የለም! እኛ ጋ ሁሉም አንድ ነው፡፡ ገናን በፊት እናከብራለን፤ ቀጥለን መውሊድን” የብዙዎች ምላሽ ነው፡፡ “ወላሂ” እያለ የሚምለውን ክርስትያን፣ “በእግዚብሔር” እያለ የሚማፀነውን ሙስሊም ማግኘት በድሬ አስገራሚ ጉዳይ አይደለም፡፡ ይህ ደግሞ የዛሬ ወይም የትናንት ሣይሆን የአመታት ብሎም የዘመናት እውነታ ነው። እስላም ክርስቲያኑ ተዋዶ፣ ተጋብቶና ተዋልዶ የሚያድርባት፤ ሁሉም እንደየእምነቱ ተከባብሮና ተቻችሎ የሚኖርባት ምድር ናት ድሬ፡፡ ይህ የድሬ መንፈስ ሐረሮች ላይስ እንዴት ይሆን ብዬ ከድሬዳዋ በሃያ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደምትገኘው ሐረር ከተማ ሄድኩ፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ መስጊዶችና በርካታ ቤተክርስቲያኖች መሣ ለመሣ የሚታዩባት የሐረር ከተማ እንደወትሮዋ ሁሉ በፍቅር ተቀበለችኝ። የሐረር ከተማ ተወላጇና ጋዜጠኛ ጓደኛዬ ከተማዋን ከዳር ዳር እየተዟዟርኩ እንዳይና ነዋሪዎቿን እንደልቤ እንዳናግር ረድታኛለች፡፡ በከተማዋ መሀል የሚገኘው ኪም ካፌና ሬስቶራንት የመጀመሪያው ማረፊያዬ ሆነ፡፡ የሲም ሞባይል ባለቤት የሆነው አቶ መሀመድ አህመድ በካፌው ውስጥ ያገኘሁት ተስተናጋጅ ነበር። መሀመድ በክርስቲያን ት/ቤት ውስጥ ተማሪ የሆኑት ልጆቹ የገናን በዓል በትምህርት ቤታቸው ውስጥ ከጓደኞቻቸው ጋር አክብረው፣ ልጆቹን ከት/ቤት ወደ ቤት አድርሶ መምጣቱ እንደሆነ አጫወተኝ። እሱም ከልጅነቱ ጀምሮ ገና፣ ጥምቀት፣ ፋሲካና ደመራን ከክርስቲያን ጓደኞቹ ጋር ሲያከብር መኖሩንና በዚያው መጠን ኢዱን፣ አረፋውንና መውሊዱን ከሙስሊም ጓደኞቹ ጋር አብሮ ማክበሩን ጭምር ነገረኝ፡፡ “እዚህ አካባቢ እስላሙንና ክርስቲያኑን ነጣጥለሽ ማሰብ አትችይም፡፡ በዓላችን እርስ በርሱ የተወራረሰና የተዋሃደ ነው፡፡ የሃይማኖት ልዩነት እኛ ጋ ቦታ የለውም፤ አብሮነቱ ውስጣችን ተዋህዶ ያለ ነው፡፡ የእስላም ምግብ የክርስቲያን ምግብ ብሎ ነገር እኛ ጋ የለም፡፡ እንደዚህ አይነት ልዩነት የሚፈጥሩትን እንደውም እንጠየፋቸዋለን። ጐን ለጐን በተሰሩት የእምነት ቦታዎቻችን እንደየእምነታችን ፀሎታችንን እናደርሳለን፡፡ አንዱ አንዱን ወገን ረበሽከን ጮህክብን ተባብሎ አያውቅም፡፡ አንዳንዴ የፀሎት ሰዓታችን በአንድ አይነት ቀንና ሰዓት ሊገጥም ይችላል። አንዲትም ቀን ግን ችግር ገጥሞን አያውቅም፡፡ ሌሎች አካባቢዎች በሁለቱ እምነት ተከታዮች መሀል ችግር ተፈጠረ ሲባል ስንሰማ በጣም ነው የሚገርመን፡፡ እነዚህ የኑሮ ሲስተሙ ያልገባቸው፣ እምነታቸውን ጠንቅቀው የማያውቁ ሰዎች ናቸው፡፡ የገናን በዓል ከክርስቲያን ጓደኞቼ ጋር በጋራ ለማክበር ተዘጋጅቻለሁ፡፡ እነሱም መውሊድን አብረውኝ ያከብራሉ፡፡ ይህ ዛሬም ያለ ወደፊትም የሚቀጥል ጥንታዊ በዓላችን ነው፡፡” 
በላይ ገ/ህይወት የሐረር ከተማ ነዋሪና የኪም ካፌና ሬስቶራንት ሥራ አስኪያጅ ሲሆን የክርስትና እምነት ተከታይ ነው፡፡ ከሙስሊም ጓደኞቹ ጋር የሁለቱንም በዓላት በጋራና በመተሣሰብ እንደሚያከብሩ ይናገራል። እኛ ጋ አድልዎና መገለል ብሎ ነገር የለም፡፡ ክርስቲያኑ ቤት የጐደለውን ከሙስሊሙ ቤት ሙስሊሙ ቤት የጠፋውን ከክርስቲያኑ ቤት እያሟላን ነው አብረን የኖርነው፡፡ እኔ እምነቴ ክርስትና ቢሆንም ከጓደኛዬ ጋር ቁርአን ቀርቻለሁ፡፡ ገናም ሆነ መውሊድ ለእኔ አንድ ናቸው፡፡ ሁለቱም ጋ አለሁበት፡፡
ይህንን እውነት ሌላው የሃረር ከተማ ነዋሪው መሀመድ ኑር አረጋግጦልኛል፡፡ ሐረር እንኳን ከሰው ከጅብ ጋር ተቻችሎ የሚኖር ነው፡፡ ይህ ባህል ዛሬና ትናንት የመጣ አይደለም፤ የጥንት ነው፡፡ ጀጐል ግድግዳ ለግድግዳ ተቀጣጥሎ በተሰራ ቤት ውስጥ ሙስሊሙና ክርስቲያኑ አብሮ ይኖራል፡፡ እኛ ጋ ልዩነት የለም፡፡ ገናም መውሊድም የሁላችንም በዓላት ናቸው፡፡ የሚኒባስ ሾፌሩ ሱራፌል ሐረር ከተማ ተወልዶ ድሬዳዋ ያደገ የ32 ዓመት ወጣት ነው። ከተሳፋሪም ሆነ ከረዳቱ ጋር እያወራ ወላሂ እያለ ይምላል፡፡ አንገቱ ላይ ያሰረው ጥቁር ክር /ማህተም/ የክርስትና እምነት ተከታይነቱን ቢናገርም እየደጋገመ የሚጠራቸው “ስቶፋሩላህ” እና “ወላሂ” የሚሉት ቃላቶች ሙስሊምነቱን ጠቋሚ በመሆናቸው ግራ ገባኝ፡፡ ግራ መጋባቴን ገልጬ እምነቱን ጠየቅሁት። “ክርስቲያን ነኝ፣ ግን ሙስሊምም ነኝ”፡፡ “እንዴ … እንዴት ይሆናል?” የበለጠ ግራ ገባኝ፡፡ “እንግዳ ነሽ?” መልሶ ጠየቀኝ፡፡ “አዎ ከአዲስ አበባ ነው የመጣሁት” “ለዚህ ነዋ የገረመሽ አቦ! እኛ ጋ ችግር የለም፡፡ ጣጣ የምታበዙት እናንተ የመሀል አገር ሰዎች ናችሁ፡፡ ሁሉም የእግዚአብሔር ፍጡር ነው፡፡ ገና እና መውሊድ ሁለቱም ለእኔ አንድ ናቸው፡፡ አቦ እንዲህ አይነት ጥያቄ ራሱ ይሸክከኛል፡፡ /አልወድም አይመቸኝም ማለቱ ነው/ እኛ አካባቢ እስላሙ ከኛ ጋር ፍልሰታን ሲፆም ልታገኚው ትችያለሽ፤ እኛም ረመዳንን ብዙ ጊዜ ፆመናል ምንድነው ችግሩ?” የሁሉም ምላሽ አንድ ነው፡፡ በከተማዋ በሚገኙት የመድሃኒያለም፣ ጊዮርጊስ፣ ገብርኤል፣ ስላሴ፣ ኪዳነ ምህረት፣ ሚካኤልና ተክለሃይማኖት ቤተክርስቲያናት በራፍ ላይ በርከት ያሉ የእስልምና እምነት ተከታዮች አረፍ ብለው አይቻለሁ፡፡ በቀላድ አምባ፣ ሜንሻ ሰፈር፣ ፈዲስ መንገድ፣ ሸንጐር፣ ጨፌ ሰፈር፣ ሸዋበርና ጀጐል እየተባሉ በሚጠሩ ሰፈሮች ስዘዋወር ባየኋቸው በርካታ መስጊዶችም እንዲሁ ክርስቲያን የከተማዋ ነዋሪዎች በየበራፉ አረፍ ብለው ሲያወጉ አይቼ ተገርሜአለሁ፡፡ ሥራዬን አጠናቅቄ ከሃረር ስወጣ “መልካም የገና በዓል ይሁንልሽ” እያሉ የተሰናበቱኝ በርካታ የእስልምና እምነት ተከታዮች ነበሩ፡፡

Read 3572 times Last modified on Saturday, 05 January 2013 11:30