“የደራሲው መብት በሕግ የተጠበቀ ነው፡፡ ደራሲውን በቅድሚያ በፅሁፍ ሳያስፈቅዱ፤መጽሀፉን በከፊልም ሆን በሙሉ ማባዛት፤መተርጎምና ማሰራጨት፤ እንዲሁም በኤሌክትሮኒክ፤ በመካኒካል፤በፎቶ ኮፒ፤ በድምፅ በመቅረፅ፤ በመሳሰሉትና በሌላም መንገድ መገልበጥ ወይም ማስተላለፍ በሕግ ያስቀጣል፡፡”

        ለዚህ ፅሁፍ መነሻ የሆነኝ ከላይ በትዕምርተ ጥቅስ ውስጥ ያስቀመጥኩት በአቶ አስራት አብርሃም፣ፍኖተ ቃኤል፣ በሚለው መጽሀፉ በመጀመሪያዎቹ ገፆች ላይ የተፃፈው የባለቤትነትን መብት የሚያስጠብቅ ጠንከር ያለ የማስጠንቀቂያ መልእክት ነው፡፡ የእኔ አትኩሮት መልእክቱ በራሱ ችግር አለው የሚል እምነት ኖሮኝ ሳይሆን ጸሐፊው የዚህን ያህል ስለ ባለቤትነት ግንዛቤ እያለው ለምን “መምህሬ እና ጓደኛዬ” የሚለው የዶ/ር ዳኛቸው አሰፋን የአእምሮ ሥራ (ማለትም በተለያዩ መጽሄቶች፣ጋዜጦች---የጻፉቸውንና በተለያዩ ጊዜያት በቃለ ምልልስ የሰጣቸውን ሃሳቦች) ከእሱ ፈቃድ ወጪ “የዳኛቸው ሀሳቦች” በሚል ርእስ በአቶ ሙሀመድ ሀሰን የታተመውን መጽሐፍ----እንዴት በዋነኛነት የአከፋፋይነቱን ሚና ሊረከብ ቻለ? በመጀመሪያ ይህ የአስራት አብርሃም የባለቤትነት ማስጠንቀቂያ መልእክት እና እየተፈጸመ ያለው ተግባር በእጅጉ እንደሚፋለስና እንደሚቃረን በግልፅ የሚታይ እውነታ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ ከዚህም እውነታ በመነሳት በዚህ ጽሑፍ ለማተኮር የፈለግሁት የዶ/ር ዳኛቸው “ተማሪ እና ወዳጅ ነኝ” የሚለው አስራት አብርሃምን አስነዋሪ ተግባር ከሞራል ተጠያቂነት አንጻር መፈተሽ ነው፡፡ ለዚህም በቀዳሚነት የሞራል እሳቤና ተግባሮት ከፍልስፍና አንፃር ምን እንደሚመስል በጥቅሉ ካስቀመጥኩ በኋላ በቀጣይም  ይህ ሰው እያደረገ ያለውን ኢ-ሞራላዊ ተግባር በሦስት ዋና ዋና ነጥቦች በቅደም ተከተላቸው መሠረት አቀርባቸዋለሁ፡፡

የሞራል እሳቤ እና ተግባሮት ከፍልስፍና አንፃር
በጥንታዊው ግሪክ የነበሩት ታላላቅ ፈላስፎች( ሶቅራጥስ፤ፕሌቶን እና አሪስቶትል) ህይወታቸውን በሙሉ ከሶፊስቶች ጋር ሲሟገቱ እንደኖሩ በተለያዩ ድርሳናቸው በተደጋጋሚ ይገልጻሉ፡፡ የዚህም ዋነኛ ምክንያታቸው ደግም የሶፊስቶች አስተምህሮት የነገሮችን እውነተኛ ምንነት ከመፈለግ ይልቅ የግለሰቦች የመናገር ችሎታና አፈቀላጤነት ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ሲሆን ይህም አንድ ግለሰብ ከነገሩ ተጨባጭ እውነታ ውጪ የንግግር ክህሎትን በመጠቀም ሌሎችን በመርታት በሚገኝ ጊዜያዊ እውቀት ላይ የሚያተኩሩ በመሆናቸው ነበር፡፡ በዚህም ዕይታቸው መሠረት ለማንኛውም ዓይነት እሳቤ ኑባሬያዊ የሆነ እውቀት የለም የሚል እምነት ያላቸው ሲሆን ለእነርሱ እውቀት እንደየግለሰቦች ትንታኔ እና ዕይታ የሚለያይ እንደሆነ ይገልጸሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሶፊስቶች እውቀትን በራሱ እንደ ግብ የሚመለከቱ ሳይሆን ዋነኛ የገቢ ማግኛ ምንጫቸው በማድረግ፣ ከእውነታው ይልቅ ወደ ንግድ የሚያተኩሩ በመሆናቸውም ጭምር ነበር፡፡
ከላይ ከጠቀስኩት ባህርያቸው አንፃር የሞራል አስተምህሮታቸውም ግለሰባዊነት ላይ የሚያተኩር ሲሆን እንደ እነርሱ እምነት አንድ ሰው ሞራሊቲ፣ ጥሩ ወይም መጥፎ ድርጊት ሊፈፅም የሚችለው በስተመጨረሻ ሊያስገኝለት የሚችለውን ትርፍ እና ኪሳራ በማሰብ እንደሆነ ያምናሉ፡፡ በዚህም የእውቀት ዕይታቸው የተነሳ ከላይ በጠቀስኳቸው ታላላቅ ፈላስፎች ክፉኛ ትችት ይደርስባቸው ነበር፡፡ የዚህም ምክንያት ደግም ለእነዚህ ፈላስፎች የሞራልቲ እሳቤዎችም ሆኑ ጥያቄዎች በባህርያቸው ማኅበረሰባዊ ይዘት ያላቸው በመሆናቸው ተግባሮታቸው እንደ ግለሰቦች ፍላጎትና ምኞት የሚከናወን እንዳልሆነ በአፅንኦት ይገልፃሉ፡፡ ይኽም በመሆኑ ማንኛቸውም ዓይነት የሞራል ተግባሮቶች የሚከናወኑት እኛ የሰው ልጆች ምክንያታዊነትን በመጠቀም ሁላችንም የምንስማማባቸው ሕግ እና ደንቦችን መሠረት በማድረግ እንደሆነም ጭምር ያስረዳሉ፡፡
ፕሌቶ “ዘ ሪፐብሊክ” በሚለው ድርሳኑ ስለ ሞራል ምንነት በአስተማሪው ሶቅራጥስ እና በሶፊስቶች መካከል የነበረውን ምይይጥ (ዲያሎግ) በሰፊው የሚያቀርብ ሲሆን በመጨረሻም ሶቅራጥስ የሶፊስቶቹን የሞራል ዕይታ ለማረቅ ችሏል፡፡ ለሶቅራጥስ የሞራል ተግባሮቶች የሚከናወኑት በሚገኘው ትርፍ ወይም በሚታጣው ኪሳራ ሳይሆን እኛ የሰው ልጆች ምክንያታዊነትን በመጠቀም የምንፈፅማቸው ድርጊቶች እንደሆኑ ያስረዳል፡፡ ስለዚህም ማንኛውም ሰው ኑባሬያዊ የሆነ የሞራል እውቀት ያለው በመሆኑ፣ ይህንንም በአግባቡ በመተግባር ሰላማዊ ህይወትን እንድንመራና ግቦቻችንን ወይም ዓላማዎቻችንን እንድናከናውን ያስችለናል፡፡ ይኽም ሲባል ማንኛውም ሀገረ-መንግሥት፤ማኅበረሰብ የሚተዳደርባቸውን ሕግም ሆነ ደንብ ሲያርቅ የሞራል እውቀትን መሠረት በማድረግ ሲሆን በዚህም ግለሰቦች የማንንም መብት ሳይነኩ በማኅበረሰቡ ውስጥ እንዴት እና በምን መልኩ መኖርና ሥራቸውን ማከናውን እንዳለባቸው የሚገልፀ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም እነዚህ የሞራል ሕጎች በሃይማኖት አስተምህሮት ሥር የተካተቱ ሲሆን ለዚህም በዋነኝነት አስተዋጽኦ ያደረገው በመካከለኛው ዘመን የነበረው የሀገረ-መንግሥት እና የሃይማኖት የአስተዳደር ትስስር እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ይኽም ሃይማኖታዊ የሞራል አስተምሮት ከዓለማዊ ሕግ በተጨማሪ ግለሰቦች እራሳቸውን ከማንኛቸዉም ክፋት እንዲቆጠብ በማድረግ አሁን እስካለንበት ዘመን ድረስ አስተዋጽኦው ከፍተኛ እንደሆነ የሚታወቅ ነው፡፡ እኔም ከእነዚህ የሞራል እሳቤዎችና ተግባሮቶች በመነሳት፣አቶ አስራት አብርሃም  በዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ ላይ እያከናወነ ያለው ኢ-ሞራላዊ የሆኑ ድርጊቶቹን ሦስት ዋቢ የሆኑ ነጥቦችን በማንሳት  በቀጣይነት እንደሚከተለው አቅርቤዋለሁ፡፡  

ከሞራል ተጠያቂነት የማያመልጥባቸው ምክንያቶች

በቀዳሚነት የምንመለከተው በዓለማችን ከሚኖሩ ነገሮች ሁሉ ከሞራል ተጠያቂነት ነፃ ሊሆኑ የሚችሉት ህጻናት፤እንስሳት እና ግዑዝ ነገሮች ሲሆኑ ይኽውም ከላይ ባለው ክፍል እንዳስረዳሁት የሞራል ሕጎች የሚተገበሩት ምክንያታዊነት ላይ ተመሥርተው በመሆናቸውና እነዚህ ሦስቱ የጠቀስኳቸውም ይኽንን ሟሟላት የማይችሉ በመሆናቸው ነው፡፡ ስለዚህም ማንኛውም  ክፉ እና በጎውን መለየት የሚችል ሰው፣ በዚህ መሥፈርት መሠረት ከሞራል ተጠያቂነት ሊያመልጥ አይችልም፡፡ ይኽንን ስል ግን በህክምና የተረጋገጠ የአእምሮ ህሙማንን ከሞራል ተጠያቂነት አንፃር የማይካተቱ መሆናቸውን መገንዘብ ይኖርብናል፡፡ ከእዚህ በመነሳት የአስራትን የሞራል ተጠያቂነት ስንመዝነው፣ ክፉውን እና በጎዎቹን ከሚለዩት ወገን ውስጥ የሚካተት በመሆኑ እንዲሁም እኔ እና ዶ/ር ዳኛቸውን ባገኘን ጊዜ ሁሉ “እስር ቤት መታሰሩን” እንጂ አማኑኤል ሆስፒታል ገብቶ እንደነበር ነግሮን ስለማያውቅ፣በዚህ ምዘና መሠረት በምንም መልኩ ከሞራል ተጠያቂነት ማምለጥ አይችልም፡፡
በሁለተኛ ደረጃ የምንመለከተው ደግሞ አንድ ግለሰብ ከእውቀት ማነስ የሞራል ግድፈት ሊፈፅም ይችላል፡፡ ሆኖም ይኽንን  ስህተቱን በተለያየ መንገድ በሚያገኘው የሞራል አስተምህሮቶች ሊያርም ይችላል፡፡ ነገር ግን የአስራት አብርሃምን ምግባር ስንመለከተው የእራሱ መጽሐፍ በማንኛውም መልኩ ከእርሱ ፈቃድ ውጪ ማሳተም፤ማሰራጨት፤ማባዛት እንደማይቻል በአፅንኦት ያሳስባል፡፡ ይኽም የሚያሳየው አስራት ስለ ግለሰብ  የባለቤትነት መብት ጠንቅቆ እንደሚያውቅ ሲሆን በዶ/ር ዳኛቸው ላይ እየፈጸመ ያለው መጥፎ ድርጊት ባለማወቅ የሠራው ስህተት እንዳልሆነ በግልፅ ያሳያል፡፡ ከዚህም በመነሳት ይኸው ግለሰብ በራሱ ላይ እንዳይፈፀምበት የሚፈልገውን ነገር ለምን በሌሎች ላይ ማለትም በዶ/ር ዳኛቸው ላይ ሊፈፅም ቻለ? የሚል ጥያቄ በአእምሯችን ሊያጭርብን ይችላል፡፡
ለዚህ የእኔ ምላሽ ሊሆን የሚችለው፣በዚህ ጽሑፍ በመጀመሪያው ክፍል በሶፊስቶቹ እና በፈላስፋዎቹ የነበረውን የሞራል የዕይታ ልዩነት በአግባቡ ሊያስረዳን እንደሚችል አምናለሁ፡፡ ሶፊስቶቹ ማንኛውንም ዓይነት የሞራል ተግባራት የሚያከናውኑት ከሚያገኙት ጥቅም አንፃር ብቻ ሲሆን በዚህም የተነሳ በሚኖሩበት ማኅበረሰብ ዘንድ ያስወግዛቸው እንደነበር ይታወቃል፡፡ ይኽ የአስራትም ድርጊት የሚያሳየን ልክ እንደ ሶፊስቶቹ የእራሱ ለሆኑት ንብረቶቹ ብቻ የሞራል ሕጎችን የሚጠቀምባቸው ሲሆን በተቃራኒው ደግም እነዚህን ሕጎች በመጣስ፣ የዶ/ር ዳኛቸውን የእምሮአዊ ንብረቶችን ካለእርሱ ፈቃድ እንደወጡ እያወቀ፣ የግል ጥቅሙን ብቻ በማየት፣በዋነኛነት እያሻሻጠ ያለ በመሆኑ ነው፡፡ ነገር ግን ሞራሊቲ የእራስን ደህንንት ማስጠበቂያ ብቻ ሳይሆን የሌሎችንም ደህንነት በተግባር ማክበር መቻል እንደሆነ አስራት መረዳት ይኖርበታል፡፡   
በሦስተኛ  ደረጃ አቶ አስራት አብርሃምን የሞራል ተጠያቂ ሊያደርገው የሚችለው፤”መምህሬ አና ጓደኛዬ” የሚለውን የዶ/ር ዳኛቸውን ጽሑፎች ካለእርሱ ፈቃድ እንደወጡና እርሱም ተባባሪ እንዳይሆን እየነገረው፣”እኔ እኮ ነጋዴ ነኝ” የሚል ምላሽ መስጠቱና  በመቀጠልም ዶ/ር ዳኛቸው ወደ ሕግ ከሚሄድ ይልቅ ከሚገኘው የመጽሐፉ ሽያጭ ገቢ  የተወሰነ ብር በድርድር ቢወስድ ይሻለዋል የሚል አቋም መያዙም ጭምር ነው፡፡ እነዚህ የአስራት መልሶች እጅጉኑ የሚያሳፍሩና ሶፊስታዊነቱን እንደቀጠለ የሚያሳዩ ናቸው፡፡ሶፊስቶቹ እዉቀትን በራሱ እንደ ግብ ከማየት ይልቅ በሚያገኙት አጋጣሚ ሁሉ እየቸበቸቡ ለመክበር የሚፈልጉ ከመሆናቸው የተነሳ ብዙም ለእውነት ቦታ አይሰጡም፡፡
ከአስራት መልሶች መረዳት የምንችለው፣ ልክ እንደ ሶፊስቶቹ የራሱን ፍላጎት ለማስፈፀም ሲል እውነታውን ወደ ጎን በመተው፣ ዶ/ር ዳኛቸውን በጥቅም ለመደለል መሞከሩ በእጅጉ አሳፋሪ አና ኢ-ሞራላው ድርጊት እንደሆነ ማረጋገጫ ነው፡፡ ዶ/ር ዳኛቸው ገንዘብ ለማግኘት ብሎ የሚጽፍ እንዳልሆነ ማንኛችንም ጠንቅቀን የምናውቀው እውነታ ነው፡፡ ዶ/ር ዳኛቸው የሚፅፋቸውም ሆነ በሚዲያ የሚያደርጋቸው ቃለ-ምልልሶች አብዛኛውን ጊዜ ማኅበረሰቡ ይማርባቸዋል ብሎ የሚያምንባቸውን እንደሆነ ማንም የሚያውቀው ሀቅ ነው፡፡ አስራት ግን አንዴ “ዶ/ር ዳኛቸውን ጠንቅቄ አውቀዋለሁ”፣ በሌላ ጊዜ ደግም “አላውቀውም” በማለት ከእራሱ ጋር እንኳን መግባባት አልቻለም፤ ምክንያቱም ዶ/ር ዳኛቸው እሱ እንደሚፈልገው ሶፊስት መሆን ባለመቻሉ ነው፡፡
 አሁንም ቢሆን አስራት ሊገነዘበው ያልቻለው ጉዳይ አለ፡፡ ዶ/ር ዳኛቸው ወደ ሕግ የሄደበት  ዋነኛው ምክንያት ገንዘብ ለማግኘት አይደለም፡፡ ፍትሕን ኢ-ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ማስተናገድ አግባብ እንዳልሆነ ስለሚያምን ነው፡፡ ዶ/ር ዳኛቸው እኔንም ሆነ ጓደኞቼን በፍልስፍና ትምህርት ክፍል ሲያስተምረን፣የሞራል ኃላፊነትን በአግባቡ መወጣት እንዳለብን በአፅንኦት ይነግረን ነበር፡፡ አሁንም እያደረገ ያለው ነገር የሚያሳየው ለፍትሕና ለሞራል ሕግጋት ምን ያኽል ታማኝ እንደሆነ ነው፡፡  ጽሑፌን የማጠናቅቀው፣አቶ አስራት አብርሃም ባለፈው ሳምንት ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋን በተመለከተ በአዲስ አድማስ ጋዜጣና እና በቁም ነገር መፅሄት ላይ ከጻፈው ውስጥ እየፈፀመ ያለውን የሞራል ግድፈት ለመሸፈን ከሞከረባቸው ምክንያቶች አንደኛው ላይ በማተኮር ነው፡፡እራሱን ብቸኛ በማስመሰል፣ዶ/ር ዳኛቸው ከጀርባው ሌሎች ሰዎችን በመያዝ እያጠቃኝ ነው ማለቱ አሁንም ሶፊስትነቱን እያጠናከረ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ አስራት  የሠራውን ስህተት ለመሸፈን ሲል ሌሎች ከነገሩ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸውን አሉባልታዎች መንዛቱ፣እኔም ሆንኩ ሌሎች በእርሱ ላይ ትዝብትና ጥርጣሬ እንዲያድርብን ነው ያደረገው፡፡ምክንያቱም አስራት የሚነዛው አሉባልታና እውነታው የተገላቢጦሽ በመሆኑ ነው፡፡ “ጅራፍ እራሱ ገርፎ እራሱ ይጮሀል” እንደሚባለው ሁሉ፣ እርሱም መጀመሪያ መጽሐፉን ሲያከፋፍል፣ዶ/ር ዳኛቸውን ምንም አያመጣም ሲል እንዳልነበር፣ አሁን ደግሞ ሌላ የማይመስል አሉባልታዊ ምክንያት ማቅረቡ በእጅጉ ያሳዝናል፡፡ ለነገሩማ ዶ/ር ዳኛቸው እርሱ እንደሚያወራው፣ ከጀርባው ሌሎች ሰዎች ቢኖሩት፣ መሀመድ ሀሰንም ሆነ እርሱ ይህቺን ተግባር እንደማይፈጽሙ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ስለ ዶ/ር ዳኛቸው ማንነት እኔ ብቻ ሳልሆን አንባቢው ሕዝብም ጭምር የሚያውቁት ስለሆነ፣ እራስን ከተጠያቂነት አድናለሁ ብሎ ሌላ ትዝብት ላይ መውደቅ ጥሩ አይደለም፡፡ ፡
በአጠቃላይ ይህን ጽሑፍ ለመጻፍ ያነሳሳኝ አንድም ከላይ እንዳስቀመጥኩት፣የአስራት የመጽሐፍ የባለቤትነት መልእክት ግርምት ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ዶ/ር ዳኛቸው እኔንም፣ሌሎችንም በፍልስፍና ትምህርት ክፍል ዉስጥ ከመጀመሪያ ዲግሪ እስከ ማስትሬት ዲግሪ በእውቀት ኮትኩቶ ያሳደገን መምህራችንን በመሆኑ ያልተገባ ነገር ሲደረግበት ከጎኑ መሆናችንን ለማሳየትም ጭምር ነው፡፡ አቶ አስራት፤ዶ/ር ዳኛቸውን ጓደኛዬ ማለቱን ይተወውና ቢያንስ በመምህርነቱ ከግብረገብነት አንፃር እንኳን ሊያከብረው ይገባል የሚል እምነት አለኝ፡፡
በመጨረሻም ለማንሳት የምወደው፣እኔን በሚመለከት አቶ መሀመድ ሀሰን በተለያዩ ሚዲያዎች ከመጽሐፉ መውጣት ጋር አያይዞ ሲጠቅሰኝ የሰነበተውን በተመለከተ ነው፡፡  አቶ መሀመድ እንደሚለው፤ዶ/ር ዳኛቸው መጽሐፉ በወጣበት ቀን ከደስታው የተነሳ አምቦ ዩኒቨርስቲ ለሚያስተምረው ወዳጁ በመደወል፣”ይሄ ጉደኛ ልጅ ጉድ የሆነ መጽሐፍ አወጣ; ብሎ ነግሮታል፡፡ እውነትም ይሄ ሰው ጉደኛ ነው ባይ ነኝ፤ምክንያቱም ዶ/ር ዳኛቸው በወቅቱ ከደሴ ወደ አዲስ አበባ እየመጣ ስለነበር፣ ስለ መጽሐፉ መውጣት እንኳን እኔ ነኝ ደውዬ  የነገርኩት፡፡ በእርግጥ ከእኔ በኋላ ሌሎች ሰዎችም ደውለው ነግረውታል፡፡
 እኔ ለአቶ መሀመድ ውሸት በወቅቱ መልስ ያልሰጠሁበት ምክንያት የጀርመኑ ፈላስፋ ኒቼ፣ ስለ ውሸት የተናገረውን ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው፡፡ ለዚህ ፈላስፋ ውሸት ማለት በሬ ወለደ ወይም እንደ መሀመድ ሀሰን ያልተባለ ማውራት አይደለም፡፡ ለኒቼ ውሸት ማለት ያሉበትን ነባራዊ ሁኔታ እያዩ እንዳላዩ ማለፍ ነው፡፡ መሀመድ ሀሰን እንደተናገራቸው ያሉ ውሸቶች በማንኛውም ጊዜ ሊጠሩ ወይም ሊረጋገጡ የሚችሉ በመሆናቸው እኔም ብዙ ትኩረት አልሰጠዋቸውም ነበር፡፡

የአሜሪካ መንግስት፣ ለሃይል ማመንጫ ተቋም ብድር ከሰጠ አይቀር፣ የሕዳሴ ግድብ ግንባታን ለማጠናቀቅ የሚረዳ ብድር መስጠት ይችል ነበር። ወይም እቅድ የተዘጋጀላቸው አዳዲስ የግድብ ግንባታዎችን፣ ማገዝ ይችላል - ብድር በመስጠት። ኧረ፣ ከዚህም የተሻለ ዘዴ አለ! መንግስት በቢዝነስ ውስጥ ከገባ አይቀር፣ የግል ኩባንያዎች የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ግድብ እንዲገነቡ፣ የተወሰነ ብድር በመስጠት ሊያግዛቸው ይችላል። ተግቶ ለሚሰራ፣ የግድብ ግንባታ፣ ያዋጣል! በአነስተኛ ወጪ፣ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ሃይል ለማመንጨት ያስችላል። ትርፋማ መሆን ማለት ከዚህ የተለየ ትርጉም የለውም።

      “የ40 ቢሊዮን ብር ኪሳራ”፣... ለዚያውም ኢትዮጵያን በመሰለ እጅግ ድሃ አገር፣ እንዴት ሊሆን ይችላል? ... እውነት፣ ሊሆን ይችላል? ጥያቄ መሆኑ ነው። ቁርጡን ማወቅ ለሚፈልግ ሰው ካለ፣ የጥያቄው መልስ፣ “አዎ ሊሆን ይችላል” የሚል አይደለም። “አዎ፣ በእውን፣ እየሆነ ነው!” ... ይሄ ነው፣ ትክክለኛው መልስ።
“ይሄማ እብደት ነው!” ብትሉ አይገርምም - “this is insane, this is crazy” ሲሉ እንምንሰማቸው ፈረንጆች። እንዲህ የምትሉት ከምር ከሆነ፣ የሚያከራክር ነገር የለኝም። መድሃኒቱን መፈለግ አይከብድም። ግን...
“ይሄማ እብደት ነው፤ ስለዚህ ሊሆን አይችልም” ለማለት ከሆነ ግን፤ ራሳችንን ወደ ምርመራ ጣቢያ ከመሄዳችን በፊት፤ ለአፍታ እውነተኛዎቹን መረጃዎች ለመቃኘት እንሞክር።
 በባራክ ኦባማ ፕሮጀክት...፣ በተግባር እየተሰራበት ባለው በዚሁ ፕሮክት፣ ኢትዮጵያዊያን የ40 ቢሊዮን ብር ኪሳራ (... በየመሃሉ የሚያጋጥሙ ተጨማሪ ችግሮችን ሳናሰላ፣... በትንሹ የ40 ቢሊዮን ብር ኪሳራ) እንደሚደርስባቸው የሚያሳዩ መረጃዎችን እንመልከት።
በሚስጥር የተገኙ ልዩ መረጃዎች አይደሉም። አገር ምድሩ የሰማቸው መረጃዎች ናቸው። “Power Africa የተሰኘው የፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ፕሮጀክት” ሲባል አልሰማችሁም? ይህም ብቻ አይደለም። ለሁለት አመታት አድናቆት ሲጎርፍለት የነበረ ፕሮጀክት ነው። አድናቆቱና ውዳሴው፣ ከእንግዲህ ሊቀጥል አይችልም እንጂ። ለምን? በሁለት አቅጣጫ፣ “የአፍሪካ ኪሳራ” እና “የኢትዮጵያ ድርሻ” በሚል ከፋፍለን እንየው።
የአፍሪካ ኪሳራ - 300 ቢሊዮን ብር!
“10ሺ ሜጋዋት የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ተቋማትን ለመገንባት ይረዳል” ተብሎ በጀመረው የኦባማ ፕሮጀክት፣ እስካሁን የተለያዩ የፋይናንስ ምንጮች ወደ 27 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ኢንቨስት ለማድረግ ቃል ገብተዋል - ከዚህ ውስጥ 7 ቢሊዮን ዶላር ከአሜሪካ መንግስት የሚገኝ ብድር ነው። (ይህን መረጃ፣ ፕሮጀክቱን በበላይነት ከሚቆጣጠረው ዩኤስአይዲ ዌብሳይት ማግኘት ትችላላችሁ)።
እንግዲህ አስቡት። “10ሺ ሜጋዋት” ማለት ... ከሁለት የሕዳሴ ግድብ ያንሳል። ግን ሁለት የሕዳሴ ግድብ ለመስራት 10 ቢሊዮን ዶለር ቢፈጅ ነው። በኦባማ ፕሮጀክት ግን፣ ከ30 ቢሊዮን ዶላር በላይ ይፈጃል - እስካሁን የተገኘው 27 ቢሊዮን ዶላር ቢሆንም። የገንዘብ ብክነቱ ምን ያህል መረን እንደለቀቀ ለማየት አይከብድም። እንዲህ የሚሆነው አለምክንያት አይደለም።
እስከዛሬ ባለው ቴክኖሎጂ፣ አፍሪካ ውስጥ በዝቅተኛ ወጪ ከፍተኛ የኤክትሪክ ሃይል ለማመኝጨት፣ ሁነኛው ዘዴ የውሃ ግድብ (ሃይድሮ ኤሌክትሪክ) ነው። በኦባማ ፕሮጀክት ግን፣ የውሃ ግድብ ተቀባይነት የለውም። የአካባቢ ጥበቃ ቡድኖች በጭራሽ የግድብ ግንባታን ማየት አይፈልጉምና - እናም የኦባማን ፕሮጀክት እያዳነቁ ያወዱሱታል። (ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ፣ “የአካባቢ ጥበቃ ቡድኖች፣ የድህነት ጠበቃ” ናቸው በማለት የሰየሟቸው ወደው አይደለም)።
የሆነ ሆኖ፣... በአነስተኛ ወጪ (በ10 ቢሊዮን ዶላር፣ ወይም እጅግ እግጅ በዛ ቢባል በ15 ቢሊዮን ዶላር) ግድቦችን በመገንባት ኤሌክትሪክ ማመንጨት እየተቻለ፣... በተቃራኒው፣ ከእጥፍ በላይ በሆነ ወጪ የነፋስ ተርባይኖችን ለመትከልና የእንፋሎት ሃይል ማመንጫ ጉድጓዶችን ለመቆፈር፣ ከ30 ቢሊዮን ዶላር በላይ ሃብት ለማፍሰስ ያስገድዳል - የኦባማ ፕሮጀክት።
ልዩነቱ ከ15 ቢሊዮን ዶላር ይበልጣል፤... ይሄ ሁሉ ሃብት፣ በከንቱ የሚባክን ንፁህ ኪሳራ ነው። በሌላ አነጋገር፣ የኦባማ ፕሮጀክት በአፍሪካዊያን ላይ ከ15 ቢሊዮን ያላነሰ ኪሳራ ያደርሳል - ከ300 ቢሊዮን ብር በላይ ኪሳራ!።

የኢትዮጵያ የኪሳራ ድርሻ።
ኦባማ በአፍሪካ ላይ ከሚያደርሱት ኪሳራ ውስጥ፣ የኢትዮጵያ ድርሻ ምን ያህል ይሆናል? ለመነሻ ያህል፣ 40 ቢሊዮን ብር ኪሳራ!
የኦባማ ፕሮጀክት አማካኝነት፣ በአሜሪካ መንግስት የብድር ድጋፍ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚተከለው የመጀመሪያው ተቋም፣ ኩርቤቴ የተሰኘው የእንፋሎት ሃይል (ጂኦተርማል) ፕሮጀክት ነው።
የአሜሪካ መንግስት፣ ለሃይል ማመንጫ ተቋም ብድር ከሰጠ አይቀር፣ የሕዳሴ ግድብ ግንባታን ለማጠናቀቅ የሚረዳ ብድር መስጠት ይችል ነበር። ወይም እቅድ የተዘጋጀላቸው አዳዲስ የግድብ ግንባታዎችን፣ ማገዝ ይችላል - ብድር በመስጠት። ኧረ፣ ከዚህም የተሻለ ዘዴ አለ! መንግስት በቢዝነስ ውስጥ ከገባ አይቀር፣ የግል ኩባንያዎች የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ግድብ እንዲገነቡ፣ የተወሰነ ብድር በመስጠት ሊያግዛቸው ይችላል። ተግቶ ለሚሰራ፣ የግድብ ግንባታ፣ ያዋጣል! በአነስተኛ ወጪ፣ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ሃይል ለማመንጨት ያስችላል። ትርፋማ መሆን ማለት ከዚህ የተለየ ትርጉም የለውም። በአነስተኛ ወጪ፣ ከፍተኛ ምርት (ከፍተኛ አገልግሎት) በጥራት ማመንጨት ነው ትርፋማነት። የግድብ ግንባታ ትርፋማ በመሆኑም፣ የግል ኩባንያዎች በብቃት ሊሰሩት ይችላሉ - ትርፋማ ለመሆን ሲሉ። “ትርፋማ እስከሆነ ድረስ፣ የመንግስት ጣልቃገብነትና ድጋፍ ለምን ያስፈልጋል?” ብሎ መጠየቅ ይቻላል። አዎ፤ አያስፈልግም።
ነገር ግን፣ አብዛኞቹ መንግስታት፣ የቢዝነስ ስራ ውስጥ ጣልቃ ከመግባት መቆጠብ አይፈልጉም። የመቆጣጠር ሱስ ተጠናውቷቸዋል። ይሄ አልበቃ ሲል ደግሞ፣ “እደጉማለሁ፤ ድጋፍ እሰጣለሁ፤ በብድር አበረታታለሁ” በማለት ይገቡበታል። ለምሳሌ፣ የባራክ ኦባማ የብድር ድጋፍ!።
እዚህ ላይ የሚነሳው ጥያቄ፤ ጣልቃ ገብተው ብድር ከሰጡ አይቀር፤ ምናለ ለ“ትርፋማ” ግንባታዎች ብድር ቢሰጡ? አክሳሪ ግንባታዎችን እየፈለጉ ማበደር ለምን አስፈለገ? በአነስተኛ ወጪ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ሃይል የሚያመነጩ ግንባታዎችን እንደመደገፍ፤ በከፍተኛ ወጪ አነስተኛ የኤልክትሪክ ሃይል የሚያመነጩ ፕሮጀክቶችን መፈልፈል... ምን ይባላል?
በኦባማ የብድር ድጋፍ የሚገነባው የኩርቤቴ የእንፋሎት ሃይል ፕሮጀክት፣ 4 ቢሊዮን ዶላር ይፈጃል (ከ80 ቢሊዮን ብር በላይ መሆኑ ነው)። እንዲህ አይነት ፕሮጀክት፣ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ለመሳሰሉ ድሃ አገራት... ምን ቢባል ይሻላል? “it is insane, it is crazy”... ቢባል አይበዛበትም።
የእንፋሎት ሃይል ፕሮጀክት፣ በብዙ ጣጣዎች አሉበት።

አንደኛ፡ አያስተማምንም!
ከሁሉም የሃይል ማመንጫ ዘዴዎች ጋር ሲነፃፀር፣ በአስተማማኝነቱ እጅግ ዝቅተኛ ነው። በአፍሪካ ከተተገበሩት የሃይል ማመንጫ ዘዴዎች መካከል፣ አስተማማኙ ዘዴ የትኛው ነው ቢባል፤ የግድብ ግንባታ ነው። ላለፉት ሰባ ዓመታት የነበረው የየአመቱ የዝናብ መጠን፣ ከዓመት ዓመት በጥቂቱ ከፍና ዝቅ ቢልም (ለእርሻ ችግር የሚፈጥር ቢሆንም)፣ በአማካይ ሲታይ ግን ይህ ነው የሚባል ለውጥ አልታየበትም። እናም፣ በግድቦች አቅም ላይ ያን ያህልም ተፅእኖ አያሳድርም። በቃ... የሕዳሴ ግድብ፣ ያለጥርጥር ውሃ እንደሚያጠራቅምና ኤሌክትሪክ እንደሚያመነጭ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል።
በኩርቤቱ የሚቆፈሩ በመቶ የሚቆጠሩ የእንፋሎት ማመንጫ ጉድጓዶችን ደግሞ ተመልከቱ። እያንዳንዱ ጉድጓድ፣ ለኤሌክትሪክ ማመንጫነት የሚጠቅም መሆን አለመሆኑ የሚረጋገጠው፣ ተቆፍሮ ካለቀ በኋላ ነው። ከዚያ በፊት እርግጠኛ ለመሆን የሚያስችል ቴክኖሎጂ ገና አልተፈጠረም።
በእርግጥ፣ አካባቢው፣ በእንፋሎት ምንጭነት የማገልገል እድል እንዳለው በደፈናው ማወቅ ይቻላል። ነገር ግን፣ ‘እዚህች ቦታ’ ወይም ‘እዚያች ቦታ’ የሚቆፈረው ጉድጓድ፣ በብቃት የእንፋሎት ሃይል የሚመነጭ መሆን አለመሆኑ የሚረጋገጠው፣ ከተቆፈረ በኋላ ነው።
 እንግዲህ አስቡት። በኩርቤቴ ፕሮጀክት፣ ለቁፋሮ ብቻ እስከ 1 ቢሊዮን ዶላር ማፍሰስ ሊያስፈልግ ይችላል - ከ20 ቢሊዮን ብር በላይ መሆኑ ነው። ምን ያህሉ ጉድጓዶች ውጤታማ እንደሚሆኑ ግን አይታወቅም። የኪሳራ አደጋው ምን ያህል ከፍተኛ እንደሆነ አያችሁ? ግን ይህንን ኪሳራ ከቁጥር አላስገባሁትም። ለጊዜው እንተወውና፣ ወደ ሌላው ችግር  እንዝለል።

2ኛ፡ ለብልሽት የተጋለጠ፤ ለጥገና ሃብት የሚባክንበት
የጉድጓድ ቁፋሮው፣ መቶ በመቶ ውጤታማ የመሆን እድል ቢኖረው እንኳ፣ በአጠቃላይ 4 ቢሊዮን ዶላር ወጥቶበት ፕሮጀክቱ ቢጠናቀቅ እንኳ፣ ...ከዚያ በኋላ፣ እንደ ግድብ ግንባታ፣ በእፎይታ መተንፈስና በእርጋታ ሃይል ሲያመነጭ እናያለን ማለት አይደለም።
በተፈጥሮው፣ ለብልሽት እጅጉን የሚጋለጥ፣ ለጥገና ደግሞ እጅጉን የሚስቸግር ፕሮጀክት ነው - የእንፋሎት ሃይል ፕሮጀክት። በሌላ አነጋገር፣ ከግንባታ በኋላም፣ በየጊዜው ከፍተኛ የገንዘብ ወጪ ያስፈልገዋል።
ነገር ግን፣ በዚህ ሳቢያ የሚመጡ ኪሳራዎችን ከቁጥር አላስገባሁትም። በአገራችን እንደተለመደው “አርቆ ማሰብን” ለጊዜው ትተን፣ የዛሬውን የግንባታውን ወጪ ብቻ እንመልከት።

3ኛ፡ የግንባታ ኪሳራ ብቻ!
የኩርቤቴ ፕሮጀክት፣ በጉድጓድ ቁፋሮ ላይ ምንም ኪሳራ ሳያጋጥመው፣ ተገንብቶ ከተጠናቀቀ በኋላም በአንዳች ተዓምር አንዳችም ብልሽት ሳይደርስበት ቢሰራ፣ ምን ያህል የኤልክትሪክ ሃይል ያመነጫል? ከተሳካለት፣ በዓመት “7ሺ ጊጋዋት አወር” ማመንጨት ይችል ይሆናል። በሚቀጥለው አመት ይጠናቀቃል የሚባለው የጊቤ3 ግድብም እንዲሁ፣ ከዚህ ጋር የሚቀራረብ የኤሌክትሪክ ሃይል ያመነጫል። ማለትም...
ከኩርቤቴ እና ከጊቤ3 ፕሮጀክቶች የሚመነጨው የሃይል መጠን ተመሳሳይ ነው። የግንባታ ወጪያቸውን ደግሞ ተመልከቱ። የጊቤ3 የግንባታ ወጪ ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በታች ነው። የኩርቤቴ ደግሞ 4 ቢሊዮን ዶላር! በሌላ አነጋገር...
ከ4 ቢሊዮን ዶላሩ ውስጥ ግማሹ ብቻ በመውሰድ፣ ከሁለት ቢሊዮን ዶላር ባነሰ ወጪ ግድብ ገንብቶ ተመሳሳይ የሃይል መጠን ማመንጨት ይቻላል - ሌላኛው 2 ቢሊዮን ዶላር በከንቱ የሚባክን ኪሳራ ነው - ከ40 ቢሊዮን ብር በላይ ኪሳራ - በባራክ ኦባማ ፕሮጀክት ሳቢያ ኢትዮጵያዊያን ላይ የሚደርስ ኪሳራ!
(ኪሳራውን ማን ይሸፍናል? ኪሳራውን ለመሸፈን እዳው ማን ላይ ይቆለላል?... እነዚህ ጥያቄዎች ላይ በሰፊው መነጋገር ይቻላል። በብዙ ጉራንጉር አለው። ፍንትው ብሎ የሚታይና ወዲህ ወዲያ የማያስብል እውነተኛው መረጃ ላይ የዛሬ ትኩረታችን - በግዙፉ ኪሳራ ላይ!)
ታዲያ፣ “ኪሳራው 40 ቢሊዮን ብር ነው” ተብሎ ሲፃፍ፣... “አነሰ ቢባል” የሚል ማስተካከያ ያስፈልገዋል። ኪሳራው፣ ከዚህም በላይ እንደሚሆን አትጠራጠሩ።
 በኩርቤቴ ከሚቆፈሩት በመቶ የሚቆጠሩ ጉድጓዶች መካከል አንዳንዶቹ ውጤታማ ሳይሆኑ እንደሚቀሩ ሲታሰብ፣ ከዚያም ፕሮጀክቱ ከተጠናቀቀ በኋላ በየጊዜው ብልሽቶች እንደሚደርሱበትና ለጥገና ከፍተኛ ወጪ እንደሚያስፈልገው ሲታሰብ... ኪሳራው፣ የትና የት እንደሚደርስ ገና አልተሰላም።
ሰዎች፣ የ40 ቢሊዮን ብር ኪሳራው፣ ለመነሻ ያህል ነው።

 አንዳንዴ ፈረንጆችን ከእኛ የሚለያቸው ስለ ሰማይ ቤትም ለመቀለድ መቻላቸው ነው፡፡ የሚከተለው ተረት አንድ ምሣሌ ነው፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ጠበቃ ይሞትና ወደ ሰማይ ቤት ይሄዳል፡፡ በገነት በራፍ ላይ ቅዱስ ጴጥሮስ ያገኘዋል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ የሁሉም ሰው ኃጢያት መዝገብ በእጁ ነውና የጠበቃውን ስም ፈልጎ ያገኘዋል፡፡ ከዚያ የሰራውን ኃጢያት ዝርዝር ያያል፡-
1ኛ. አንድን ከአየር መበከል ጋር ተያይዞ የተከሰሰን ሰው በመከላከል ጥብቅና ቆሟል
2ኛ. ደህና ገንዘብ ይከፈልሃል ስለተባለ ብቻ በግልፅ በነብስ ግድያ የተከሰሰን ነብሰ ገዳይ በመከላከል ጥብቅና ቆሟል፡፡
3ኛ. አብዛኛዎቹን የጥብቅና ደምበኞቹን ከልኩ - በላይ አስከፍሏል፡፡
4ኛ. አንዲትን የዋህ ሴት ለሌሎች ወንጀለኞች ጥፋት ማምለጫ ሰበብ እንድትሆን በመፈለግ፤ እንዲፈረድባት አድርጓል፡፡
ጠበቃው ይህን ክስ በመቃወም ተሟገተ፡፡ ክሶቹን በሙሉ ተቀበለና አንድ መሟገቻ ግን ይዞ ቀረበ፡-
“አንድ የምፅዋት ስጦታ ለነዳያን በህይወቴ አንዴ ሰጥቻለሁ” አለ፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ መዝገቡን አየና፤
“አዎን አዎን ስምህ አለ፡፡ ለአንድ ጎዳና ተዳዳሪ አሥር ሳንቲም ሰጥተሃል! ለአንድ ሊስትሮ ደግሞ አንድ ሳንቲም ሰጥተሃል! ትክክል ነኝ?” ጠበቃው ግራ የተጋባ መልክ እየታየበት፤ “አዎን!” አለ፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ አጠገቡ ወዳለው መልዐክ አየ፡፡
“ይሄን ልጅ አሥራ አንድ ሳንቲሙን ስጠውና ወደ ገሀነም አስገባው!” አለው፡፡
*       *     *
በሰው ላይ ግፍ ማስፈረድ፣ አላግባብ ገንዘብ መዝረፍ፣ የአብዬን እከክ ወደ እምዬ ልክክ ማድረግ፣ የማታ ማታ ማስጠየቁ አይቀሬ ነው፡፡
በርካታ ሌብነት፣ በርካት ግፍ፣ በርካታ የማጭበርበር ተግባር ፈፅመን ስናበቃ፣ ቅንጣቷ ደግነቴ ትመዝገብልኝ ማለት ግብዝነት እንጂ ብልጠት አይሆንም፡፡ ዕድሜያችንን ሙሉ የሰራነው ተንኮል እየታወቀ፣ አንድ ቀን የመፀወትኩትስ? ብሎ መከራከር ዐይናውጣነት ከመሆን በቀር ከፍርድ አያድንም! ዐረቦች “ሌባው በሰረቀው ሳይሆን ሳይሰርቅ በተወውም ይታወቃል” ይላሉ፡፡
የሀገራችን ፖለቲከኞች ነገር ለተፎካካሪ የሚመችና የተጋለጠ ነው፡፡ “ብቅል አስጥታ ነበር፤ እሽ ብትል እንዴት ጥሩ ነበር” ተብሎ ሁሌም የሚታለፍ ፌዝ መሳይ ነው፡፡
የሀገራችን ኢኮኖሚም ጥቂቶች ከዝሆን ጥርስ (Ivory - Power) ላይ ሆነው የሚነጩበት፣ ብዙሃኑ ትቢያ ላይ የሚተኙበት ዓይነት እየሆነ ነው፡፡ ቱርኮች “አንዱ በይ አንዱ የበይ ተመልካች የሆነ ዕለት የዓለም መጨረሻ መጣ ማት ነው” ይላሉ፡፡ እንደዚያም ቢባል አይገርምም፡፡
የመሰረተ - ልማት ሂደቱ ደግ ነው ቢባልም፤ በዙሪያው ያለው ሙስና ቀለም በተቀባ ቆርቆሮ እንደሚሸፈን ቆሻሻ ቦታ ሊሆን አልቻለም፡፡ የሚያስደንቀው ሌቦቹ ቀና ብለው የሚሄዱበት፣ ተመዝባሪዎቹ የሚያቀረቅሩበት ሁኔታ መሆኑ ነው፡፡
የካፒታሊዝምን ነገረ - ሥራ ሳንመረምር ተቀብለን አንድምታዎቹ በፖለቲካችንም፣ በኢኮኖሚያችንም፣ በማህበራዊ ኑሯችንም ሲንፀባረቁ መማረራችን አስገራሚ ነው፡፡ ዲሞክራሲ ልሙጥ በሆነ ህብረተሰብ ውስጥ ፋይዳው ከሲታ ነው፡፡ የሚወዳደር፣ የሚፎካከር፣ የሚከራከር፣ የሚታገል፣ የሚደራደር ህብረተሰብን ግድ ይላል፡፡ “ሞኝ ሸንጎ ተሰብስ አገኘሽ፣ ቁርስ የሌለው ቡና አፈላሽ” አይነት ከሆነ ጉዞው ዘገምተኛ ይሆናል፡፡ ቢያንስ “ምቀኛ አታሳጣኝ” የሚለውን አገርኛ ባህላዊ አነጋገር ማስተዋል ይጠቅማል፡፡
ኃያላን መንግሥታት ዐይን ቢጥሉብን ፍፅምና ያለን ሊመስለን አይገባም፡፡ ሁሉም የየራሱ ገበታ እንዳለው አንርሳ፡፡ ዞሮ ዞሮ ራስን ችሎ እንደመገኘት የመሰለ ነገር የለም! “ተሸፋፍነው ቢተኙ፣ ገልጦ እሚያይ አምላክ አለ” የሚለውን ተረት አንርሳ፡፡ የኢኮኖሚ ችግርን መባባስ መደበቅ አይቻልም፡፡
ምድረ - በዳውን እየማተርን የበረሀ - ገነት (oasis) አየን ብንል ራስን ከማታለል በቀር ሌላም መላ የለው፡፡ ያለን አለን፣ የሌለን የለንም፡፡ የማንኖረውን ኑሮ እየኖርን ነው ብለን ብንኩራራና ብንቦተልክ ኑሯችን አጋልጦ እርቃናችንን ያሳየናል!
ሥራችን የሆነውን ኃላፊነት ሳንወጣ ከሁሉም በላይ ደግሞ፤ ሌላው ላይ መላከክ ሀገራችን በየጊዜው የሚያጋጥማት የፖለቲካ ጨዋታ ነው፡፡ ሁሉ ወቃሽ ሁሉ ከሳሽ ሆነና የየራሱን ግዴታ የሚያይበት ዐይን ጠፋ፡፡ “ሁሉም ፈረስ ላይ ከወጣ፣ ማን መንገድ ይምራ?” እንደሚለው የወላይትኛ ተረት ነው፡፡ የጠያቂው ብዛት የተጠያቂውን ደብዛ ያጠፋዋል! ይህ መፈተሽ ያለበት የፖለቲካ ችግራችን ነው፡፡
“ድመት አይጥ እንዲይዝ ተብሎ ችቦ አይበራለትም” የሚለው የጉራጌ ተረት ሁሉም በየራሱ ሥራ መፈተሽና መጠየቅ እንደሚገባው ነው የሚያሳየን፡፡ ይህንን ልብ እንል ዘንድ ልብ ይስጠን!

Published in ርዕሰ አንቀፅ

 ተቃዋሚዎች ኦባማ በአፍሪካ ህብረት በሚያደርጉት ንግግር ላይ እንዲገኙ ተጋብዘዋል
            በኢትዮጵያ ይፈፀማሉ የተባሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በቸልታ እንዳያልፉ ተጠይቀዋል
                           
   ፕሬዚዳንት ኦባማ በኬንያና በኢትዮጵያ በሚያደርጉት ጉብኝት፣ በዲሞክራሲና በሰብአዊ መብቶች አያያዝ ላይ መሻሻል እንዲፈጠር ግፊት ሊያደርጉ እንደሚችሉ የጠቆሙ ሲሆን በኬንያ ተቃዋሚዎችን እንደሚያነጋግሩ ይጠበቃል፡፡
የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ማክሰኞ እለት ፕሬዚዳንቱ በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ  በሚያደርጉት ንግግር ላይ እንዲገኙ የተጋበዙ ሲሆን በስብሰባው ላይ የአፍሪካ አገራት ተወካዮችና የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ይሳተፋሉ፡፡
የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ)፣ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) እና የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ) የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ኢትዮጵያን ሲጐበኙ እኛንም ያነጋግሩን የሚል ደብዳቤ በአዲስ አበባ ለሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ማስገባታቸው የሚታወቅ ሲሆን እስካሁን ፕሬዚዳንቱ ፓርቲዎችን በተናጠል የማነጋገር ዕቅድ እንዳልያዙ የኤምባሲ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
የኢዴፓ የሥራ አስፈፃሚ አባልና የጥናትና ምርምር ኃላፊ አቶ ዋሲሁን ተስፋዬ ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት፤ ሦስቱ ፓርቲዎች ለኤምባሲው ያስገቡት ደብዳቤ ፕሬዚዳንቱ ፅ/ቤት (ዋይት ሃውስ) መድረሱን ያረጋገጡ ሲሆን ምናልባት ሊያነጋግሩን ከፈቀዱ በሚል በሃገሪቱ በምርጫ ስርአት እንዲሁም በዲሞክራሲና የህግ የበላይነት ዙሪያ ከፕሬዚዳንት ኦባማ ጋር ለመወያየት ከፍተኛ ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ ፓርቲዎቹ ዕድሉ ከተገኘ ለባራክ ኦባማ በእጅ የሚሰጥ ደብዳቤም በጋራ እያዘጋጁ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ለፕሬዚዳንቱ የሚቀርበው ደብዳቤ በሃገሪቱ ስላለው የምርጫ ስርአት፣ የሰብአዊ መብቶች አያያዝ፣ የፕሬስ ነፃነት እንዲሁም የዲሞክራሲና የህግ የበላይነትን የሚመለከቱ ጉዳዮችን በስፋት የሚያብራራ እንደሚሆን ተገልጿል፡፡  
ፕሬዚዳንቱ ጉብኝታቸውን አስመልክቶ በትናንትናው እለት ለቢቢሲ በሰጡት ቃለ ምልልስ፤ ዋነኛ የጉብኝታቸው አላማ በኢኮኖሚያዊ ትብብር፣ እንዲሁም በፀጥታና ሽብርተኝነትን በመከላከል ዙሪያ ውይይት ለማድረግ መሆኑን አበክረው ተናግረዋል፡፡
ኦባማ በኬንያ በሚኖራቸው ቆይታ በንግድ ፈጠራ  ጉባኤ ላይ እንደሚሳተፉ ጠቁመው ወጣት የንግድ ስራ ፈጣሪዎችን እንደሚያበረታቱና በሙስናና በግልፅ አሰራር ዙሪያ መንግስት ስለሚከተለው አካሄድ ውይይት እንደሚያደርጉ ገልፀዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ወደ ስልጣን ሲመጡ “አሜሪካ የምትፈልገው ጠንካራ የዲሞክራሲ ተቋማት እንጂ ጠንካራ ግለሰቦችን አይደለም” ሲሉ መናገራቸውን በመጥቀስ በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በፓርላማው አንድም ተቃዋሚ በሌለበት እንዲሁም የኬንያው ፕሬዚዳንት በወንጀል ተከሰው ምርመራ እየተደረገባቸው ባለበት ሁኔታና ጠንካራ መንግስታዊ ተቋማት ሳይኖሩ ጉብኝት የማድረጋቸውን አግባብነት በተመለከተ ከቢቢሲው ጋዜጠኛ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ የተባለውን ያህል ባይሆንም ችግሮች እንዳሉ ጠቁመው ጉብኝቱ በሃገራቱ ውስጥ የሰብአዊ መብት አያያዝ እንዲሻሻልና የሲቪክ ማህበረሰብ ተሳትፎ እንዳይገደብ ግፊት የምንፈጥርበት አጋጣሚ ይኖረዋል ብለዋል፡፡
ከዚህ ቀደም የሊበራል ርዕዮተ ዓለም ተከታይ ያልሆነችውን በርማን መጎብኘታቸውን የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ፤ ከጉብኝታቸው በኋላ የሃገሪቱ ዲሞክራሲና የሰብአዊ መብት አያያዝ እንደተሻሻለ ገልፀው፣ በሁለቱ የምስራቅ አፍሪካ ሃገራት የሚያደርጉት ጉብኝትም ተመሳሳይ ተፅዕኖ ሊፈጥር እንደሚችል አስረድተዋል፡፡
በኬንያ በሚያደርጉት የ3 ቀናት ጉብኝት ከግብረሰዶማውያን መብት ተቆርቋሪነታቸው ጋር በተያያዘ ተቃውሞ ሊገጥማቸው እንደሚችል ከቢቢሲ ጋዜጠኛ የተጠየቁት ፕሬዚዳንቱ፤ “እኔ በፆታ እኩልነት አምናለሁ፤ እንዲከበርም እታገላለሁ፤ በአፍሪካ ያለውን ነገር አውቃለሁ፣ ከዚህ ቀደም በሴኔጋል ባደረኩት ጉብኝት እንዲህ ያለው ስጋት አጋጥሞ ነበር፤ በጋዜጣዊ መግለጫዬ ላይ ግን ስለጉዳዩ በቀጥታ አላነሳሁም፤ አሁንም የሚሆነው ተመሳሳይ ነው” ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል ፕሬዚዳንት ኦባማ፤ በኢትዮጵያና በኬንያ በሚያደርጉት ጉብኝት በዲሞክራሲና የሰብአዊ መብት ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገው ከየሃገራቱ መንግስታት ጋር እንዲወያዩ የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችና ግለሰቦች በደብዳቤ እንደጠየቁ ታውቋል፡፡
በመጪው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ይወዳደራሉ ተብለው የሚጠበቁት ሴናተር ማርኮ ሩቤዩ፤ ፕሬዚዳንቱ ኢትዮጵያን በሚጐበኙበት ወቅት በሰብአዊ መብት አያያዝ ጉዳይ ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ በፃፉት ደብዳቤ አሳስበዋል፡፡
“ምንም እንኳ አሜሪካ እና ኢትዮጵያ አሸባሪነትን ለመዋጋት በጋራ ቢቆሙም ኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶችን ስትጥስ አሜሪካ አይቶ እንዳላየ ማለፍ የለባትም” ያሉት ሴናተሩ፤ በኢትዮጵያ ያለው የፕሬስ ነፃነት ጉዳይም ትኩረት እንዲደረግበት በደብዳቤያቸው ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ ጉብኝቱን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ፤ የኦባማና የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ውይይት በዋናነት በሰላም ማስከበርና በኢኮኖሚ ትብብር ላይ ያተኩራል ብሏል፡፡
ከጉብኝቱ ቀደም ብሎ ዋሽንግተን ፖስት እና ዘ ጋርዲያን የተባሉት ታዋቂ ጋዜጦች፤ ኦባማ የፕሬስ ነፃነት ያልተከበረባትና ዲሞክራሲያዊ ተቋማት ያልተጠናከሩባትን ኢትዮጵያን መጎብኘታቸው፣ ዓለም የዲሞክራሲ ፅንሰ ሃሳብን በተንሸዋረረ መልኩ እንዲገነዘብ የሚያደርግ ነው ሲሉ ተቃውሟቸውን መግለፃቸው አይዘነጋም፡፡
ፕሬዚዳንቱ በሁለቱ ሃገራት በሚያደርጉት ጉብኝት ከአጃቢ ልኡካኖች በተጨማሪ 20 የአሜሪካ ከፍተኛ የህግ ባለሙያዎችም አብረዋቸው እንደሚጓዙ ታውቋል፡፡
ባራክ ኦባማ በስልጣን ዘመናቸው ከአፍሪካ አገራት ጋና፣ ግብፅ፣ ታንዛኒያ፣ ሴኔጋልና ደቡብ አፍሪካን የጎበኙ ሲሆን የአሁኑ የኬንያና የኢትዮጵያ ጉብኝታቸው የፕሬዚዳንትነት ዘመናቸው የመጨረሻ የአፍሪካ ጉብኝት ሊሆን እንደሚችል የፖለቲካ ተንታኞች ጠቁመዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ኦባማ በነገው ዕለት ማታ የኬንያ ጉብኝታቸውን አጠናቀው አዲስ አበባ እንደሚገቡ የሚጠበቅ ሲሆን ሰኞ እለት በብሄራዊ ቤተመንግሥት አቀባበል ይደረግላቸዋል፡፡ በዚያው እለት ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያምና ከፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ጋር በደቡብ ሱዳንና በአካባቢያዊ የደህንነት ጉዳዮች ላይ ይወያያሉ ተብሏል፡፡ በእለቱም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያምና ፕሬዚዳንት ኦባማ ለጋዜጠኞች መግለጫ ይሰጣሉ፡፡
በማክሰኞ ቀን ውሏቸው ከሲቪል ማህበረሰቡ ከተውጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት የሚያደርጉ ሲሆን በመቀጠልም ከአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ዲላማኒ ዙማና ከህብረቱ አባል ሀገራት መሪዎች ጋር በምግብ ዋስትና እና ቀጣይነት ያለው ልማት ለማረጋገጥ በሚደረጉ ኢኮኖሚያዊ ጥረቶች ዙሪያ ይወያያሉ ተብሏል፡፡

Published in ዜና

ጊዜው 1998 ዓ.ም፡፡ ወቅቱ እንደ አሁኑ ክረምት ነው፡፡ ድሬዳዋ በደረሰባት ድንገተኛ የጐርፍ አደጋ ከ260 በላይ ነዋሪዎቿ ለህልፈት የተዳረጉበት ክፉ ጊዜ ነበር፡፡ ሐምሌ 29 እኩለ ሌሊት ላይ ከከተማዋ ደጋማ አጐራባች አካባቢዎች ተጠራቅሞ የመጣው ጐርፍ ያስከተለው አደጋ ከሞቱት በተጨማሪ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የከተማዋ ነዋሪዎችን ከመኖሪያ ቤታቸው አፈናቅሏቸዋል፡፡
የከተማዋ አስተዳደር በጐርፍ አደጋው ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጐች ለመታደግ አቅም አጠረው። በአደጋው ቤት ንብረታቸውን ያጡ በርካቶች በየትምህርት ቤቶቹ እንዲጠለሉ ቢደረግም ሁኔታው ከአቅም በላይ ሆነ፡፡
ይሄኔ ነው ለጋሽ ድርጅቶች የእርዳታ እጃቸውን እንዲዘረጉ ጥሪ የቀረበው። ለጥሪው አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት ቀዳሚነቱን የያዘው የአሜሪካ ባህር ኃይል፤ ጅቡቲ ከሚገኘው ካምፑ እያንዳንዳቸው 28 ሰዎችን የሚይዙ 60 ድንኳኖችን በመጫን ድሬዳዋ ከተማ ደረሰ፡፡ ይህ እርዳታ በወቅቱ እጅግ ከፍተኛ ግምት የተሰጠውና የብዙዎችን ህይወት የታደገ ነበር፡፡ ድንኳኖቹ በአደጋው ምክንያት ቤት ንብረታቸውን ላጡት ነዋሪዎች፣ አስተዳደሩ ቤት ሰርቶ እስከሚሰጣቸው ድረስ ለመጠለያነት አገልግለዋል፡፡
ይህንን የባህር ኃይሉን በጐ ተግባር ለመጐብኘት የአሁኑ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት፣ የዚያን ጊዜው የኢሊኖይሱ ሴናተር ባራክ ኦባማ ድሬዳዋ የገቡት አደጋው ከተከሰተ ከሁለት ሳምንታት በኋላ ነበር። በወቅቱ ለኦባማ በአስተርጓሚነት ይሰራ የነበረው ወጣት ሄኖክ ወንድሙ፤ “ኦባማ ቀለል ያለና ተጫዋች ነበር፤ በድሬዳዋ ከተማ በተከሰተው አደጋም እጅግ ማዘኑን አስታውሳለሁ ብሏል፡፡ ያኔ ሄኖክ የሁለተኛ ዓመት የህግ ተማሪ ሲሆን ኦባማም የህግ ምሩቅ መሆኑን ነግሮኝ ነበር ይላል፡፡
ኦባማ ወደ አገሩ ከተመለሰ በኋላ ከሄኖክ ጋር የተነሱትን ፎቶግራፍ በኢሜይል እንደላከለት የሚናገረው ሄኖክ፤ ፎቶግራፉ በወቅቱ ብዙ ስሜት እንዳልሰጠው ያስታውሳል፡፡ ፎቶውን ለረዥም ጊዜ ረስቶት እንደቆየ ጠቁሞ ኦባማ ፕሬዚዳንት ሆነው ሲመረጡ ፎቶው በቅርብ ጓደኛው አማካኝነት ለአደባባይ መብቃቱን ገልጿል፡፡
በአሁኑ ወቅት በግል የንግድ ሥራ የሚተዳደረው ሄኖክ፤ ከኦባማ ጋር አብሮ የተነሳውን ፎቶ በሞባይል ስልኩ ላይ ስክሪንሴቨር ያደረገው ሲሆን ብዙዎች ግን እንደሚጠራጠሩትና በፎቶሾፕ የተሰራ ነው እንደሚሉት ይናገራል፡፡ ሆኖም ከአገሪቱ ታላላቅ ባለስልጣናት አስቀድሞ ከመጀመሪያው የአሜሪካ ጥቁር ፕሬዚዳንት ጋር ፎቶ ለመነሳት የቻለ ብቸኛ ኢትዮጵያዊ መሆኑን በኩራት ይገልፃል፡፡
ሴናተሩ ኦባማ ድሬን በጐበኙበት ወቅት ለፕሬዚዳንትነት እንደሚወዳደሩ ይወራ ነበር የሚለው ሌላው የድሬ ነዋሪ ካሊድ ኢስማኤል፤ በአሜሪካ ባህር ኃይል የተደረገውን እርዳታ እንዲመለከቱ ተጋብዘው ከነበሩት የአሜሪካ ወታደራዊ ባለስልጣናት ይልቅ ለኦባማ ጠንከር ያለ ጥበቃ ይደረግላቸው እንደነበርም ያስታውሳል፡፡
ከዘጠኝ ዓመታት በፊት ሴናተር ኦባማ ወደ ድሬዳዋ የመጡት በጅቡቲ በኩል ሲሆን በወቅቱም ጅቡቲ የሚገኘውን የአፍሪካ ቀንድ ፀረ ሽብር ጥምር ግብረ ኃይል እንቅስቃሴን በመጐብኘት ላይ ነበሩ። ድሬዳዋ ሲገቡ የተደረገላቸው ጥበቃ እምብዛም የተጠናከረ አልነበረም፡፡ በሶስት አጃቢዎችና በጥቂት መኪኖች የኢትዮጵያን ምድር ለመጀመሪያ ጊዜ የረገጡት ሴናተር ኦባማ፤ አሁን ግን ኢትዮጵያን የሚጐበኙት በከፍተኛ ወታደራዊ አጀብ ነው። ፕሬዚዳንቱ በኬንያና በኢትዮጵያ ለሚያደርጉት ጉብኝት እስከ 2 ቢሊዮን ብር የሚገመት ገንዘብ ወጪ እንደሚደረግ የሚገመት ሲሆን አብዛኛው ወጪም ለጥበቃና ደህንነታቸው የሚውል ነው ተብሏል፡፡ ለኦባማ የሚደረገው ጥበቃ በልዩ ትእዛዝ በተሰሩና ጥይት በማይበሳቸው መኪኖች፣ በተጠናከረ የአየር ላይ ጥበቃ፣ በሃምሳ ስድስት ልዩ ተሽከርካሪዎችና ከ250 በላይ በሚሆኑ የደህንነት ሠራተኞች የተደራጀ ነው፡፡

Published in ዜና

* መንግሥት የመሬት አቅርቦት በመጨመር ዋጋውን አረጋጋለሁ ብሏል
              * ከሊዝና ሌሎች ገቢዎች ከ1.6 ቢ. ብር በላይ ተሰብስቧል
                          
        የአዲስ አበባ ከተማ የመሬት ሊዝ ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየናረ መምጣቱን የሚናገሩ አንዳንድ የመዲናዋ ነዋሪዎች፤ ሁኔታው መፍትሄ ካልተበጀለት ከጥቂት ባለፀጐች በቀር መሬት ማግኘት የማይታለም ይሆናል ሲሉ ስጋታቸውን ገልፀዋል፡፡ መንግሥት በበኩሉ፤ የመሬት አቅርቦቱን በመጨመር የሊዝ ዋጋን አረጋጋለሁ ብሏል፡፡
የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ፤ የሊዝ ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ መምጣቱን አምኖ፣ ችግሩን ለመፍታት በዘንድሮ በጀት ዓመት የመሬት አቅርቦቱን ከ44 ሄከታር ወደ 60 ሄክታር እንደሚያሳድግ አስታውቋል፡፡
ባለፈው ህዳር ወር በተካሄደው 11ኛው ዙር የሊዝ ጨረታ፣ መርካቶ አካባቢ ለቀረበው 449 ካ.ሜ ቦታ፣ ዝዋይ ኢንተርናሽናል ግሩፕ የተባለ ተጫራች 305 ሺ ብር በማቅረብ በአዲስ የዋጋ ክብረወሰን ጨረታውን ሲያሸንፍ፣ ሁለተኛው ተጫራች ደግሞ 268 ሺ ብር ማቅረቡ ይታወሳል፡፡ ጉዳዩም በፓርላማ የመወያያ አጀንዳ እስከመሆን ደርሶ ነበር፡፡
ሆኖም ባለፈው ሳምንት በተከፈተው 15ኛው ዙር የሊዝ ጨረታ፣ አሸናፊው ድርጅት መሬቱን በወቅቱ ሳይረከብ በመቅረቱ፣ ለጨረታ ማስረከቢያ ያስያዘው 118ሺ 805 ብር ለመንግስት ገቢ ተደርጐ መሬቱ በድጋሚ ለጨረታ ቀርቧል፡፡
አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች፤ የሊዝ ዋጋ ከመጠን በላይ እንዲያሻቅብ ያደረገው የሊዝ መሬት አቅርቦት አናሳ በመሆኑ ነው ይላሉ፡፡ መንግሥት ለጉዳዩ እልባት ካላበጀለት የዋጋ መናሩ እየቀጠለ ሄዶ መሬት የጥቂት ባለሃብቶች እንዳይሆን እንሰጋለን ብለዋል - አስተያየት ሰጪዎቹ፡፡
የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች የስራ ሂደት መሪ አቶ ማርቆስ አለማየሁ ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በሊዝ ለማቅረብ የታቀደው መሬት 44 ሄክታር ቢሆንም የቀረበው ግን 58 ሄክታር ነው ብለዋል፡፡ በአዲሱ የበጀት ዓመትም የሊዝ መሬት አቅርቦት ወደ 60 ሄክታር እንደሚያድግ ሃላፊው ገልፀዋል፡፡
በሌላ በኩል መንግስት በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ከሊዝ ጨረታ አሸናፊዎች ከ549.3 ሚሊዮን ብር በላይ ለማግኘት አቅዶ፣ ከ639 ሚሊዮን ብር በላይ በማስገባት የእቅዱን 116 በመቶ እንዳከናወነ አስታውቋል፡፡ ከእቅድ በላይ የተገኘው ስኬት የዋጋ ንረቱ ውጤት አይደለም ወይ? ተብለው የተጠየቁት አቶ ማርቆስ ሲመልሱ፤ መንግስት የመሬት ዋጋ እንዲንር ፍላጐት እንደሌለው ገልፀው፤ ይልቁንም በመሬቱ ላይ በሚሰራው ኢንቨስትመንትና በሚፈሰው መዋዕለ ንዋይ በሚገኘው ልማት ተጠቃሚ እንዲሆን በመፈለጉ፣ የሊዝ መሬት የመነሻ ዋጋ በማስፋፊያ ከ191 እስከ 355 ብር፤ በሽግግር ዞን ከ555 እስከ 1035 ብር እንዲሁም በማእከላዊ ንግድ ቀጠና አካባቢዎች ከ894 እስከ 1686 ብር እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
ቢሮው በበጀት ዓመቱ ከመሬት ሊዝና ከልዩ ልዩ ገቢዎች በአጠቃላይ ከ1.6 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን አስታውቋል፡፡

Published in ዜና

  አሁን ከ21ሺ በላይ አልጋ ያላቸው ከ600 በላይ ሆቴሎች አሉ
                   የአዲስ አበባ እና የኦሮሚያ የሆቴሎች ኮከብ ምደባ ተጠናቋል
                                  
       ኢትዮጵያ 3ኛውን ገንዘብ ለልማት ኮንፈረንስ በማስተናገዷ ለሚዲያ ከፍላ ከምታገኘው እጅግ የላቀ የገጽታ ግንባታ ማከናወኗን የባህልና ቱሪዝም ሚ/ር አስታወቀ፡፡ ሆቴሎች ለኢኮኖሚ ዕድገት ከፍተኛ ሚና አላቸው ብሏል - ሚ/ር መስሪያቤቱ፡፡  
አገሪቷ በአንድ ጊዜ ከ7 ሺህ በላይ እንግዶች ተቀብላ ያለአንዳች የመስተንግዶ ችግር መሸኘቷ እጅግ የሚደነቅ ነው ያሉት በባህልና ቱሪዝም ሚ/ር የህዝብና የዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ አባተ፣ እንግዶቹ በተደረገላቸው መስተንግዶ ተደስተው በአገሪቷ ዕድገት ተገርመውና ተመልሰው ለመጎብኘት ቃል ገብተው የሄዱት ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃ ባሟሉ ሆቴሎች በመስተናገዳቸው ነው ብለዋል፡፡
ሆቴሎች በአንድ አገር የኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ የሚጫወቱት ሚና እጅግ የላቀ እንደሆነ የጠቀሱት አቶ ገዛኸኝ ሆቴል ማለት እንግዶች ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ከአንድ ቀን በላይ ለአጭርና ለረዥም ጊዜ ሲንቀሳቀሱ ምግብ፣ መጠጥና መኝታ አገልግሎት እየሠጠ የሚያቆይ ተቋም ነው ብለዋል፡፡
እንግዶቻችንን ለማስተናገድ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያሟሉ 8,000 አልጋዎች ያላቸው 138 ሆቴሎች መዘጋጀታቸውን፣ ድንገት አልጋ ቢያንስ በማለት ቢሾፍቱ ሄደው መጠባበቂያ መያዛቸውን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ፤ ከፍተኛ የደህንነት ጥንቃቄ የሚደረግላቸው ቪአይፒ የአገር መሪዎችና ም/ትል ፕሬዚዳንቶች፣ ጠቅላይ ሚኒስትሮች፣ የተባቡት መንግሥታት (ተመድ) መሪዎች፣ የተለያዩ የኤጀንሲ ኃላፊዎች፣ የቢዝነስ ኩባንያ ባለቤቶች …. አንዳች ነገር ሳይጓደል በብቃት ማስተናገድ፣ ኢትዮጵያ እያደገች ነው የሚለውን በተጨባጭና በተግባር የመሰከረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
እኛ የምናየው ሆቴሎች፣ ሬስቶንቶች … ምን ያህል ገቢ አገኙ የሚለውን ሳይሆን አጠቃላይ ገጽታውን ነው፡፡ አንድ ሰው በአገራችን ውሎ ሲያድር በቀን 234 ዶላር ወጪ ያደርጋል ተብሎ ይገመታል፡፡ ለእንግዶቹ መኝታ ተይዟል፣ ሬስቶራንቶች ምግብ አቅርበዋል፣ ሻይ፣ ቡና ማኪያቶ፣ ቢራ፣ ዊስኪ፣ … ተጠጥቷል፡፡ የምሽት ቤቶች ተጎብኝተዋል፤ አየር መንገዶች፣ ባንኮች… አገልግሎት ሰጥተዋል፡፡ የተጓጓዙባቸው መኪኖች ቤንዚን ቀድተዋል፣ የስጦታ ዕቃዎች ተገዝተዋል፡፡ ከተማ ተጎብኝቷል፣ በአጠቃላይ ከአምራች ገበሬው እስከ የበሰለ ምግብ አቅራቢው በእያንዳንዱ ዘርፍ የሥራ ዕድል ተፈጥሯል፡፡ ይህ ሁሉ የገንዘብ እንቅስቃሴ ነው በኢኮኖሚ ውስጥ ትልቅ ሚና የሚጫወተው፡፡
ለዚህ ሁሉ የሆቴሎች መኖር እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡ ሆቴሎች በአንድ ጊዜ ብዙ ህዝብ የማስተናገድ ልምድ አግኝተዋል፡፡ እኛም አገሪቷ ያላትን አቅም አውቀንበታል፡፡ ምክንያቱም እነዚህን ሁሉ እንግዶች የሚያስተናግድ ሆቴል ባይኖር ስብሰባው እዚህ ባልተካሄደ፣ እንግዶችም ባልመጡ ነበር፣ … በማለት አስረድተዋል፡፡
ከ24 ዓመት በፊት በመላ አገሪቷ 51 ሆቴሎች ብቻ እንደ ነበሩ ያስታወሱት አቶ ገዛኸኝ፤ በአራቱም የአገሪቷ ማዕዘኖች ግዮን ሆቴሎች፣ በቀለ ሞላ፣ ኢትዮጵያ፣ ዋቢ ሸበሌ፣ ራስ ሆቴል፣ ሐራምቤ፣ ዲ አፍሪክ፣ ጣይቱ፣ መርካቶ አካባቢ ደግሞ አስፋው ተክሌ፣ የምስራች፣ ምዕራብ፣ አስፋ ወሰን … ብቻ ነበሩ፡፡ በአሁኑ ወቅት በመላ አገሪቱ ከ21 ሺህ በላይ መኝታ ያላቸው 621 ሆቴሎች አሉ፡፡ ይህም በአዲስ አበባና በክልሎች እየተሠሩ ያሉትን እንደማይጨምር ተናግረዋል፡፡
በዚህ ሳምንት መጨረሻ የአረብ - አፍሪካ የፓርላማና የቢዝነስ ፎረም ይደረጋል፡፡ በሚቀጥለው ሳምንት እነ ኦባማ የሚሳተፉበት የመሪዎች ጉባኤ ይካሄዳል፡፡
 ቀጥሎም እስከ 10ሺህ የሚደርሱ ዲያስፖራዎች ይመጣሉ፡፡ የኮንፈረንስ ቱሪዝምን በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በክልል ከተሞችም ለማዘጋጀት ታቅዷል፡፡ ባህርዳር ተፈትናለች፡፡ ሀዋሳና ሌሎችም ከተሞች ዓለም አቀፍ ስብሰባ የማካሄድ አቅም እንዳላቸው በመረጋገጡ በእነዚህም ከተሞች ጉባኤዎች ይካሄዳሉ ሲሉ ገልፀዋል፡፡ የአዲስ አበባ ሆቴሎች የኮከብ ደረጃ በዚህ ወር ይገለጻል ቢባልም እስካሁንም ምንም የለም፡፡ ለምን ተብለው የተጠየቁት አቶ ገዛኸኝ፤ “ምደባውን በብቸኝነት የሚያካሂዱት ከዓለም ቱሪስት ድርጅት የመጡ ባለሙያዎች ናቸው፡፡ እስካሁን ድረስ በ1ኛው ዙር የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ሆቴሎች የኮከብ ደረጃ ምደባ አልቋል፡፡ አሁን መዳቢዎቹ ለእረፍት ወደ አገራቸው ሄደዋል፡፡ ለ2ኛ ዙር ሲመጡ እስካሁን የሰሩትን ተረክበን ለሚዲያም ሆነ ለየሆቴሎቹ እናስታውቃለን፡፡ ያኔ “የተሰጠኝ ደረጃ አይመጥነኝም፣ አልቀበልም” የሚል ሆቴል ካለ ቅሬታ ማቅረቢያ ደንብና ሥነ - ሥርዓት ስላለ እንደገና ይታይለታል በማለት አቶ ገዛኸኝ አስረድተዋል፡፡

Published in ዜና

በደራሲና ጋዜጠኛ አንተነህ ይግዛው የተጻፈው “ባቡሩ ሲመጣ...” የተሰኘ የአጫጭር ልቦለዶች ስብስብ መጽሐፍ፣ የፊታችን አርብ ከ11፡30 ሰዓት ጀምሮ በኢትዮጵያ ሆቴል በሚከናወን ኪነጥበባዊ ዝግጅት ተመርቆ በገበያ ላይ ይውላል፡፡
የደራሲው ሁለተኛ ስራ የሆነው “ባቡሩ ሲመጣ...”  በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያጠነጥኑ 14 አጫጭር ልቦለዶችን በ210 ገጾች አካትቶ የያዘ ሲሆን፣ የመሸጫ ዋጋውም ለአገር ውስጥ 60 ብር፣ ለውጭ አገራት ደግሞ 16 ዶላር እንደሆነ ደራሲና ጋዜጠኛ አንተነህ በተለይ ለአዲስ አድማስ ገልጿል፡፡
ጋዜጠኛና ደራሲ አንተነህ ይግዛው፣ የመጀመሪያ ስራው የሆነውን “መልስ አዳኝ” የተሰኘ የአጫጭር ልቦለዶች ስብስብ መጽሃፍ በ2003 ዓ.ም ለንባብ ያበቃ ሲሆን፤ በቅርቡም የወጎች ስብስብ መጽሃፍ ለህትመት እንደሚያበቃና በአንድ ታዋቂ ኢትዮጵያዊ የቢዝነስ ሰው የህይወት ታሪክ ዙሪያ የሚያጠነጥን መጽሐፍ እያዘጋጀ እንደሚገኝም ገልጿል፡፡
አንተነህ ይግዛው፣ ከሁለት አመታት በፊት በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በኩል ለአንድ አመት ከአራት ወራት የተላለፈውን “ስውር መንገደኞች” የተሰኘ ተወዳጅ ሳምንታዊ የሬዲዮ ድራማ በደራሲነትና በተዋናይነት ለአድማጭ ማቅረቡም ይታወሳል፡፡

የአቶ ካሣዬ ተክለአረጋይ ቤተሰቦች የተለያየ ቅፅ ኢንሳይክሎፒዲያ፣ የወንጀለኛ መቅጫ፣ የተጠቃለሉ ሕጐች፣ የሕግ መጽሔቶችና ጠቅላላ ዕውቀትን ጨምሮ 60 ያህል መፃሕፍትን ለዕውቀትና ትጋት አሰፋ ጎሳዬ የሕዝብ ቤተ-መፃሕፍት ሰሞኑን አበረከቱ፡፡
የሕግ ባለሙያ የነበሩት አቶ ካሣዬ ተክለአረጋይ በሕይወት ሳሉ ሲጠቀሙባቸው የነበሩ መፃሕፍትን ለቤተመፃሕፍቱ ያበረከቱት ልጃቸው አቶ ሰለሞን ካሣዬ ናቸው፡፡ የአቶ ሰለሞን ካሣዬ ባለቤት ወ/ሮ ምህረት ጌታቸው በወቅቱ እንደተናገሩት፤ “መጻህፍቱን እንድንሰጣቸው  የጠየቁ ግለሰቦች የነበሩ ቢሆንም መፃሕፍቱ የበለጠ ከአንባቢያን ጋር ሊገናኙ የሚችሉት በቤተ-መፃሕፍት ውስጥ ቢቀመጡ ነው በሚል እምነት አበርክተንላችኋል” ብለዋል፡፡

 በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ የሰሉ ሥነ ፅሁፋዊ ሂሶችን በማቅረብ የሚታወቀው ደራሲና ሃያሲ ዓለማየሁ ገላጋይ የጻፈው “ወሪሳ - የውድቀት ፈለጎች” የተሰኘ የረዥም ልብ ወለድ መፅሃፍ ሰሞኑን ለንባብ በቃ፡፡
አዲሱ ልብወለድ ለደራሲው 9ኛ መፅሃፉ ሲሆን በ49 ብር እየተሸጠ መሆኑ ታውቋል፡፡
ዓለማየሁ ከዚህ ቀደም “አጥቢያ”፣ “ቅበላ” እና “የብርሃን ፈለጎች” የተሰኙ ግሩም የረዥም ልብወለድ ስራዎችን ያሳተመ ሲሆን “ኩርቢት” የሚል የአጭር ልቦለድ መድበልም ለአንባቢያን አድርሷል፡፡ በደራሲ ስብሃት ገብረእግዚአብሄር ህይወትና ክህሎት ዙሪያ ያሰናዳው መፅሃፉም የሥነፅሁፍ  ምሁራንን ያነጋገረና ያሟገተ መሆኑ ይታወሳል፡፡ ደራሲው፤ “ፍትህ”፣ “አዲስ ታይምስ” እና“ፋክት” በተሰኙ የህትመት ውጤቶች ላይ ያቀርባቸው በነበሩ ማራኪና ኮርኳሪ መጣጥፎቹ የብዙዎችን ቀልብ ለመሳብ ችሏል፡፡

Page 4 of 17