Saturday, 26 March 2016 11:21

ከሉሲዎቹ ዋና አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው ጋር

Written by 
Rate this item
(0 votes)

       ዋና አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድኑ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ጥሩ እድል እንዳለው ያምንበታል፡፡ ዛሬ በአዲስ አበባ ስታድዬም የመልስ ጨዋታ ያደርጋሉ፡፡ ከሁለት ሳምንት በፊት በአልጀርስ ተደርጎ በነበረው ጨዋታ ሉሲዎቹ በአልጄርያ አቻቸው 1ለ0 መሸነፋቸው ይታወሳል፡፡ ዛሬ ጥሎ በማለፍ ወደመጨረሻው የማጣርያ ምእራፍ ለመሸጋገር 2ለ0 እና ከዚያም በላይ ማሸነፍ አለባቸው፡፡
     አልጄርያ በሴቶች እግር ኳስ ጥሩ ደረጃ ላይ እንደሆነች ለስፖርት አድማስ የተናገረው ዋና አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው፤ በሰሜን አፍሪካዊቷ አገር የሴቶች እግር ኳስ በተናጠል  ፌደሬሽን፤ ሊግ አስተዳደር፤ ስታድዬሞች መከናወኑ በረጅም ግዜ በተዘረጉ እቅዶች የሚካሄድ መሆኑን ልንማርበት ይገባል ሲል ያሰምርበታል፡፡ በአልጄርያ እግር ኳስ በሀ 17 እና በሀ 20 የሴቶች እግር ኳስ መንቀሳቀሱን እንደተምሳሌት በመውሰድም በኢትዮጵያ ልንሰራበት ይገባል ብሎም አስተያየት ይሰጣል፡፡
ሉሲዎቹ ዛሬ የሚገጥሙት የአልጄርያ ብሄራዊ ቡድን 12 ፕሮፌሽናል ተጨዋቾች እንዳሉበት የሚገልፀው ዋና አሰልጣኝ ብርሃኑ፤  በመጀመርያው ጨዋታ 1ለ0 መሸነፋቸው የሉሲዎችን ጥንካሬ እንደሚያሳይ አስገንዝቦ፤  በመልሱ ጨዋታ በሜዳችን፤ በአየራችን እና በደጋፊያችን ፊት ውጤቱን ለመቀልበስ ነው ተስፋ የምናደርገው በሁላችንም ትግልና ጥንካሬ ነው ሲል ይናገራል፡፡ የመልሱን ጨዋታ በከፍተኛ ጥንቃቄ  የምናደርገው ይሆናል ያለው ዋና አሰልጣኙ፤ ጥሩ ዝግጅት ማድረጋቸውን፤ በሜዳቸው ብዙ ዋጋ ሊያከፍል የሚችል ግብ እንዳይቆጠር መስራታቸውን  ለስፖርት አድማስ አብራርቷል፡፡
የሉሲዎቹ አባላት በስነምግባራቸው ጥሩ ደረጃ ላይ መሆናቸውን የሚገልፀው ዋና አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው፤  እንደ ሎዛ አበራ አይነት ወጣትና ምርጥ የአጥቂ መስመር ተጨዋች፤ በአፍሪካ ዋንጫ ልምድ ያላቻቸው አጥቂዋ ረሂማ ዘርጋው፤  ግብ ጠባቂዋ ዳግማዊትና አምበሏ ብርቱካን ገብረክርስቶስ ቡድኑን በመምራት ባላቸው ከፍተኛ ሚና ደስተኛ ነው፡፡ በአጠቃላይ ቡድኑ በታዳጊ፤ በወጣት እና በአንጋፋ ተጨዋቾች ስብስብ የተገነባ መሆኑ ጠንካራ እንደሚያደርገውም ለስፖርት አድማስ በሰጠው ቃለምልልስ ዋና አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው ተናግሯል፡፡ ለወደፊቱ ብሄራዊ ቡድኑ ለተጨዋቾቹ በቂ ጥቅም ሆነው የሚታዩ ማበረታቻዎችን፤ ለዝግጅት የሚያግዙ በቂ የወዳጅነት ጨዋታዎችን በማዘጋጀት ፌደሬሽኑ የቡድኑን ጥንካሬ ለማጎልበት መንቀሳቀስ አለበትም ሲል መልዕክቱን ያስተላልፋል፡፡ ስፖርት አድማስ ከሉሲዎቹ ዋና አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው ጋር ያደረገው ልዩ ቃለምልልስ ከዚህ በታች የቀረበው ነው፡፡
በስፖርት ላይ የሚያተኩር ልዩ እና ፈርቀዳጅ መፅሃፍ አሳትመሃል ቃለምልልሱን በሱ ስንጀምርስ
አዎ፤ ልክ ነህ፡፡ በስፖርት ብቻ ሳይሆን በህይወት ታሪኬ ላይ የሚያተኩር መፅሃፍ ነው፡፡ “ከስደት መልስ እስከ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝነት” በሚል ርእስ የተዘጋጀ ነው፡፡ ብዙ ወጣቶች በስደት ህይወት እንደሚባክኑ የሚታይ ቢሆንም በመፅሃፌ ከስደት ህይወት ተመልሶ ስኬት ማግኘት እንደሚቻል ለማስረዳት ሞክርያለሁ፡፡ በተጨማሪም መፅሃፉ በግል ህይወቴ ብቻ ሳይሆን ከስፖርቱ ጋር በተያያዘ እግር ኳስን በተጫዋችነት ከዚያም በአሰልጣኝነት እንዴት እንዳሳለፍኩ፤ ወደስልጠና ሙያ ለመግባት በምን አይነት ስነምግባር በርካታ ውጣውረዶችን እንዳለፍኩ የሚያወሳ ነው፡፡
የስፖርት መፅሃፍ አዘጋጅቶ ለገበያ ማቅረብ የተለመደ አይደለም፤ አንተን ምን አነሳስቶህ ነው?
መፅሃፉን ሳሰትም ዋናው ዓላማዬ የህይወት ተመክሮዬና በስፖርቱ ያሳለፍኩትን ጥረትና ልምድ ለህዝብ እንዲደርስ በማሰብ ነው፡፡ በመጀመርያው እትም የመፅሃፉ ብዛት ያን ያህል አርኪ አልነበረም፡፡ 1500 ኮፒ ብቻ ነበር ያሳተምኩት። ወዲያው ለገበያ እንደቀረበ ወርም ሳይሞላ ነበር ያለቀው፡፡ አሁን በቅርብ ጊዜ ሁለተኛ እትም ለማሳተም እየተንቀሳቀስኩ ነው። እንደእቅዴ ከሆነ ሁለተኛውን እትም በ4ሺ እና በ5ሺ ኮፒ ለማሳተም ነው፡፡
መፅሃፉን በምን ዓላማ ነው አሳተምከው፤  ታላላቅ አትሌቶችና የእግር ኳስ ባለታሪኮች በዚህ ረገድ ብዙም ሲንቀሳቀሱ አይታይም፤ ማንስ ነው መፅሃፍ የማዘጋጀት ሃላፊነት ያለበት ጋዜጠኞች ወይንስ ባለታሪኮቹ ስፖርተኞች?
እኔ እንደሚመስለኝ  ባለቤቱ ራሱ እንደመሆኑ ሃላፊነቱ የስፖርተኛው ነው፡፡ ያለፍክባቸውን የስፖርት ተመክሮዎች፤ የሰራሃቸውን ታሪኮች አስተማሪነት እንዳላቸው ካመንክበት በራስህ ጥረት ልታደርገው የሚገባ ስለሆነ ነው፡፡ ግን በስራ ዘመንህ ታሪኮችን በአግባቡ መሰነድ፤ በማስታወሻ እየከተብክ ማኖር እና ከተለያዩ አቅጣጫዎች በማገናዘብ አዘጋጅተህ ተግባራዊ ልታደርገው የምትችል ነው፡፡ እኔ መፅሃፉን ያሳተምኩት ልጄን ከወለድኩ በኋላ ስለሆነ ከዚያ እንደሁለተኛ ልጄ ነው የቆጠርኩት፡፡ መፅሃፍ ታሪክን የሚያስቀምጥ ነው፡፡ የሚመጣ ትውልድ ሊማርበት የሚችል ነው፡፡ ከታሪክህ ብዙ ስፖርተኛ አንብቦ ሊማር የሚችለው ብዙ ቁምነገር መኖሩን መገንዘብ አለብህ፡፡ በእኛ አገር ስፖርተኞች የተለመደው ጡረታ ከተወጣ በኋላ መፃፍ ነው፡፡ ነገር ግን እኔ እንደማስበው በስራ ዘመንህ፤ በህይወት ላይ ጉልበት እና ሞራል እያለህ በምታልፍባቸው የስራ ውጣውረዶች እና ጎዳናዎች ያሉህን ተመክሮዎች እየተገነዘብክ በየጊዜው መፃፉ አስፈላጊም ተገቢም ነው፡፡
እንግዲህ አንተ ባለህ የስራ ልምድ አብዛኛውን ድርሻ የሚወስደው በሴቶች እግር ኳስ ላይ ያለህ ተመክሮ ነው፡፡ ‹‹ከስደት መልስ እስከ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝነት” በሚለው መፅሃፍህ በሴቶች እግር ኳስ ዙርያ ምን ምን ተወስቷል፡፡
በሴቶች እግር ኳስ አሰልጣኝነት መስራት ከጀመርኩ እንግዲህ 17 ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በ17 ዓመት ውስጥ  የሴቶች እግር ኳስ ሲጀመር ማለትም ገና ሲፀነስ ነበርኩ፤ ከዚያም እርግዝናው ላይ ምጡ ላይም አለሁበት፡፡ ከዚያም ተወልዶ ዳዴ ብሎ ማደግ ሲጀምርም እየሰራሁበት ነው፡፡
የሴቶችን እግር  ኳስ ከጅምሩ እዚህ አገር ውስጥ ብዙም ተቀባይነት ስላልነበረው ከመጀመርያው ይህን ተቀባይነት ለማግኘት ብዙ ጥረት ማድረግ ነበረብን፤ ይገርምሃል ያኔ ከ17 ዓመታት በፊት ሜዳ ለወንድ ተጨዋቾች ሲለቀቅ ለሴት ኳስ ተጨዋቾች የሚለቅ ሁሉ አልነበረም፡፡ በሌላ በኩል የፋይናንስ እጥረት ነበር፡፡ ያኔ በገንዘብ በኩል ያለብንን ችግር ለመቅረፍ ይገርምሃል ሆያ ሆዬ፤ አበባየሁሽ እየጨፍርን ገቢ ለማግኘት እንጥር ነበር፤ ይህ እንግዲህ ከ14 ዓመታት በፊት ነው፡፡ ከሆያ ሆዬ እና ከአበባየሁሽ ጭፈራ በኋላም እኛ አሰልጣኞቹ እና ወጣቶቹ ሴት እግር ኳስተጨዋቾች የራሳችንን እጣ እንደበግ እና ሌሎች ሽልማቶች ያሉበትን ሎተሪ አዘጋጅተን እና ተዟዙሮ በመሸጥ ገንዘብ ለማግኘት ሁሉ ሰርተናል፡፡ እነዚህን ገቢ የማሰባሰብ ተግባራት በመጀመርያ ጃንሜዳ አካባቢ ጀምረነው ከዚያም፤ ወደ ፒያሳ መርካቶ ኮተቤ እየሄድን የምንሰራቸው ነበሩ፡፡ ወደ ተለያዩ ክልሎችም እየተንቀሳቀስን ገንዘብ ሰብስበናል፡፡ በእነዚህ እንቅስቃሴዎች የምናገኘውን ገንዘብ የምንሰበስበው ከልምምድ በኋላ ነበር፡፡ ድንችና ፓስታ ቀቅለን ተጨዋቾቻችንን እየመገብን ሁሉም ከየተሰማራበት አቅጣጫ የሰበሰበውን እንረከባለን፡፡ አምበሎች አማካኝነት የተሰበሰበው ገንዘብ ኳስ እና፤ ማሊያ የተለያዩ ትጥቆች ይገዙበታል፡፡ በአዲስ አበባ ከፍተኛ ዲቪዚዮን እና አንደኛ ዲቪዚዮን ውድድሮች ከፍለን በመመዝገብ ተሳትፎ ማድረግ እየቻልን መጣን። በእነዚህ ውድድሮች ለመሳተፍእስከ 1000 ብር መክፈል ነበረብን። ከ14 ዓመታት በፊት ይህ ብዙ ገንዘብ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው አንገቱ ላይ የወርቅ ሃብል አጥልቋል፡፡ ሰው ወርቁን ሲያይ ሊደንቀው ይችላል፡፡ ግን መጀመርያ ወርቁ የመጣበትን ወርቁ የተፈተነበትን፤ ወርቁ እንዴት ተቃጥሎ እንደመጣ የሚያቀው ወርቁ ራሱ ነው፡፡ ግን ከፈተና የወጣ  ሁል ጊዜ ማማር ይችላል። እኛ በሴቶችእግር ኳስያሳለፍነው ተመክሮ እንደዚህ የሚገለፅ ነው፡፡ የመጽሐፌም ይህን የመሰሉ ታሪኮች ተነስተዋል፡፡
በፌደሬሽኑ በኩል ያን ግዜ የምታደርጉትን እንቅስቃሴ የሚደግፍ አሰራር አልነበረም እንዴ
እንግዲህ ዓለም አቀፉ  የእግር ኳስ ማህበር በሴቶችእግር ኳስ ላይ ማተኮር የጀመረው ከ25 ዓመታት በፊት እንደሆነ ታውቃለህ፤ እናም እኛ በሴቶች እግር ኳስ መንቀሳቀስ ስንጀምር ከፊፋ የሚላክ ገንዘብ ቢኖርም በፌደሬሽኑ በኩል የነበረው ትኩረት ደካማ ስለነበር የሚመጣው የበጀት ድጋፍ ለወንዶቹ ውድድሮች ነበር የሚሰራጨው፡፡ እንደምታውቀው ፊፋ ለአባል ፌደሬሽኖች ከሚያበረክታቸው የገንዘብ ድጋፎ ለሴቶችና ወጣቶች የእግር ኳስ እንቅስቃሴ እስከ 250ሺ ዶላር በየውድድር ዘመኑ ይሰጣል፡፡ ይህ በጀት ወደ ውድድሮች ነው የሚሄደው በአንድ ታዳጊ አገር አቅሙ ባለመኖሩ የሚያስደነግጥ አይደለም፤ እኛ ስንጀምረው  በሴቶች እግር ኳስ አሰልጣኝነት የምንሰራ ባለሙያዎች ጥቂት ነበርን፡፡ ጋሽ ይተፋ፤ ያሬድ ቶሌራ፤ ደረጀ ነጋ፤ ፍቃዱ ማሙዬ እና እኔ በማሰልጠን እንሰራ በነበርነበት ጊዜ በጃንሜዳ አካባቢ የተወሰነ ነበር እንቅስቃሴያችን፡፡ ደረጃ ብቻ ነበር የካ አካባቢ ይሰራ ነበር። እኔ ማሰልጠኑን ስጀምር በወንዶችእግር ኳስ ነበር ለምሳሌ እነ አሉላ ግርማን የመሳሰሉ ተጨዋቾች ባፈሩ ፕሮጀክቶች እሰራ ነበር፡፡ ከግዜ በኋላ ግን በሴቶችእግር ኳስ ብዙ የሚሰራ ባለመኖሩ ወደዚያ መስክ ለመዞር በመወሰን የገባሁበት ነው፡፡ ብዙ ሙያተኞች በዚህ ውሳኒያችን ተገርመው ይንቁንም ነበር። በጃንሜዳ  የአዲስ አበባ ከፍተኛ ዲቪዝዮን በሚባል መደበኛ ውድድር ቡድኖቻችንን ይዘን እንሳተፍ ነበር፡፡
ብዙ ዓመታትን በጃሜዳ የዲቪዚዮን ውድድሮች ካሳለፍን በኋላ የክልል ሻምፒዮናዎች መካሄድ ጀመሩ፤ ከዚያም ፕሪሚዬር ሊግ መጣ፡፡ የሚገርምህ በከፍተኛ ዲቪዝዮን ይጫወቱ የነበሩ ልጆች ኳስ ብዙም ገቢ ስለማይፈጥርላቸው ወደ አረብ አገራት መሰደድን ሁሉ የሚመርጡበት ሁኔታ ነበር፡፡ ፕሪሚዬር ሊግ ሲጀመር ግን  የሴቶች እግር ኳስ ከስደት የተሻለ ህይወት እና ገቢ የሚገኝበትን እድል ስለሚፈጥር ሁኔታው ሊቀየር ችሏል፡፡
እንግዲህ ባለፉት 14 ዓመታት የሴቶችእግር ኳስ ያለፉባቸውን ውጣውረዶች በመጠኑ ዳስሰሃቸዋል፡፡ አሁን ያለበትን ደረጃ የምትገልፀው እንዴት ነው
 አሁን የሴቶች እግር ኳስን  ህብረተሰቡ ተቀብሎታል፤ ቤተሰብምም ተቀብሎት የሚደግፈው ሆኗል፤ ከወንዶች የእግር ኳስ እንቅስቃሴ እኩልም ትኩረት እየተሰጠው ነው፡፡ አሁን ለምሳሌ በክፍለ ከተማ ደረጃ እንኳ የወንዶችም የሴቶችም ቡድኖች እየተመሰረቱ ናቸው፡፡ እግር ኳሱን እያሻሸለው ያለ አቅጣጫ ነው፡፡ ክለቦችም ከመቼውም ጊዜ በላቀ ሁኔታ ትኩረት ሰጥተው እየሰሩበት ናቸው፡፡ ድሮ ቡና ጊዮርጊስ ብለን ስለቡድኖቹ የምንሰማው በወንዶች ብቻ ነበር፣ አሁን ደግሞ በሴቶችም የሚታይ መደበኛ ተግባር እየሆነ ነው፡፡ በፕሪሚዬር ሊግ ደረጃ ክለቦች የየራሳቸውን ቡድኖች በማቋቋም መወዳደራቸው የሚያደስት ቢሆንም ግን አንዳንድ ክፍተቶች አሉ በታዳጊዎች ደረጃ እየተሰራ….
ይቅርታ ብርሃኑ የብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ እንደመሆንህ ያሉትን ክፍተቶች በግልፅ ልትናገራቸው ያስፈልጋል..
ልክ ነህ፡፡ ለሴቶች እግር ኳስ መለወጥ እና ማደግ ከፍተኛ መስዕዋትነት ከፍዬ የደረስኩበት ደረጃላይ የወደፊቱን ተስፋ የሚያደበዝዝ እና እድገቱን የሚያንቀራፍፍ ሁኔታ ከታዘብኩ እተቻለሁ፡፡ ክለቦች በፕሪሚዬር ሊግ ደረጃ የሴቶች ቡድኖችን መስርተው መወዳደር ሲጀምሩ ለተጨዋቾቻቸው የወንድ ትጥቆችን በማቅረብ፤ አነስተኛ በጀት በመመደብ ነበር፡፡ አሁን ግን ሁሉም ክለቦች በሴት ቡድኖቻቸው ምስረታ የእኔነት ስሜት በማዳበር መንቀሳቀሳቸው ትልቅለውጥ ይመስለኛል። ይህ ብቻውን ግን በቂ አይደለም፡፡ አሁን አንዳንድ ክለቦች የመሰረቷቸውን ቡድኖች ያለበቂ ምክንያት እያፈረሱ ናቸው፡፡ ለሴቶች እግር ኳስ ክብር የማይሰጡ ክለቦች አሉ፡፡ ለወንዶች  ከፍተኛ በጀት እየመደቡ የሚንቀሳቀሱ አንዳንድ ክለቦች የሴት ቡድኖቻቸውን እንደዘበት የሚያፈርሱት አካሄድ በፍፁም ልክ አይደለም፡፡ ሴቶች እኮ በየትኛውም መስክ ዋንኛ አካላት ናቸው። ምናልባት በየክለቡ ሴት አመራሮችም ይኖራሉ እና ታድያ የተመሰረተ ክለብን ማፈራረስ እና መበታተን ለምንድነው፡፡ ቡድኖቻቸውን ካፈረሱ ክለቦች መካከል  ወላይታ ዲቻና መድን ይጠቀሳሉ፡፡ በወላይታ ዲቻ በኩል ክልሉ፤ በመድን በኩል የክለቡ አስተዳደር ይህ ተግባር ለምን ዝም እንዳሉት አይገባኝም፡፡ በሌላ በኩል እንደወልዲያ ከነማ አይነት ክለቦች የሴቶች ቡድን እንዲመሰርቱ ፌደሬሽኑ ለምን አያስገድድም፡፡ የተመሰረቱ ቡድኖችን ማፍረስ፤ ከእነጭራሹ በሴቶች እግር ኳስ ያለመስራት ሁኔታዎች መጥፎ አዝማሚያዎች ይመስሉኛል፡፡ በትጋት በሚሰሩ ክለቦች ላይ የሚዛመቱ ችግሮች ስለሚሆኑም ስጋት አለኝ፡፡ የግንዛቤ እግር በአመራሮች ላይ ይታያል፡፡ ጠንካራ የሴቶች እግር ኳስ እንቅስቃሴን በሚያሳዩ እንደ ንግድ ባንክ፤ ደደቢት እና ዳሸን፤ ቡናና ጊዮርጊስ ያሉ ክለቦች ያለው ችግር ደግሞ በወንዶቹ የሚሰጡትን ትኩረት ያህል አለመስራታቸው ነው፡፡ በተለይ በታዳጊ ደረጃ ወርደው የሚሰሩ ክለቦች አለመኖራቸውነው የሚያሳስበኝ፡፡ በታዳጊ ደረጃመስራት ለነገው መሰረት መጣል ነው፡፡
በአጠቃላይ ክለቦች በሴቶች እግር ኳስ ታዳጊ ቡድኖችንም አቋቁመው ለመስራት መትጋት ይኖርባቸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በፕሪሚዬር ሊጉ ተወዳዳሪ በሆኑ ክለቦች ለሴት ተጨዋቾች ተመጣጣኝ ደሞዝ የሚከፈልበት አሰራር መፈጠር ይኖርበታል፡፡ በእርግጥ በታዳጊዎች ላይ መስራት ብቻን መፍትሄ ላይሆን ይችላል፡፡ ከፕሪሚዬር ሊጉ ባሻገር የታዳጊ ውድድሮች ያፈልጋሉ፤ በስልጠና የሚሰሩ ብቁ ባለሙያዎችም ሊኖሩ ግድ ይላል፡፡ ለምሳሌ ባለሙያዎችንም ማብቃት የፌደሬሽኑ ስራ መሆን አለበት፤ ለምሳሌ እግር ኳስን ያቆሙ የቀድሞ ሴት ተጨዋቾች በየቤታቸው ተቀምጠዋል እነሱን ወደ ስልጠናው መስክ ለማስገባት የሚያስችሉ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች መፈጠር አለባቸው፡፡ ከዚያቀጥሎ ክለቦች ብቁ ባለሙያዎችን ይዘው የታዳጊ ቡድኖችን መስርተው መንቀሳቀስ ሲጀምሩ ውድድሮችን ለመፍጠር እና ለማካሄድ ብዙ የሚቸግር አይሆንም፡፡
በግሌ እምነት በሴቶችእግር ኳስ  በሁሉም ክለቦች ያሉት እንቅስቃሴዎች የሚያበረታቱ ቢሆንም በደደቢት እና በንግድ ባንክ ክለቦች እንዲሁም በዳሸን ያሉ ተግባራት እንደ ተምሳሌት ሊጠቀሱ የሚችል ነው፡፡ በእነዚህ ክለቦች ለሴት ተጨዋቾች ከወንዶቹ እኩል በቂ ትኩረት እየተሰጠ ነው፡፡ ተመጣጣኝ የደሞዝ ክፍያም እየተገበሩ ናቸው፡፡ በትጥቅ አቅርቦት፤ በአስተዳደር ትኩረት፤ በደሞዝ መሻሻሎች መኖርአለባቸው። እነዚህን አሰራሮች ሌሎች አንጋፋ ክለቦችም መከተል አለባቸው፡፡

Read 2511 times