Saturday, 17 October 2015 09:21

የሴቶች ጤና ...

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ/ዮዲት ባይሳ ኢሶግ
Rate this item
(3 votes)

 በአለማችን ላይ ቁጥራቸው በርካታ የሆኑ ሴቶች ለተለያዩ የስነተዋልዶ ጤና ችግሮች ይጋለጣሉ፡፡ ያልተፈለገ እርግዝና፣ውርጃ፣ወሲባዊ ጥቃት እንዲሁም ሌሎች ከእርግዝና እና ከወሊድ ጋር በተያያዘ ለሚከሰት የጤና ችግር ይጋለጣሉ፡፡  UNFP ባወጣው መረጃ መሰረት ከሰሀራ በታች ባሉ ሀገራት ብቻ በየአመቱ ቁጥራቸው ወደ 183.000 የሚሆኑ ሴቶች ከእርግዝና እና ከወሊድ ጋር በተያያዙ የጤና ችግሮች ህይወታቸውን ያጣሉ፡፡ እንደሚታወቀው  በሰውልጅ እራስን የመተካት ሂደት ውስጥ የሴቶች ሚና እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ አንድ ፅንስ ተረግዞ እስከሚወለድበት ግዜ ድረስ በእናቲቱ ማሕፀን ውስጥ ነው የሚቆየው ፡፡የፅንሱ ደህንነትም  እናቲቱ በምታደርገው ክትትል ወይም የእለት ተእለት እንቅስቃሴ ላይ ይወሰናል፡፡ ለዚህም ነው ሴቶች ህይወት ሰጪ ወይም ተሸካሚ ናቸው የሚባለው፡፡ ስለዚህ ሴቶች ይህን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ጤንነታቸውን መጠበቅ ወይም እራሳቸውን መንከባከብ ይኖርባቸዋል፡፡ ለዚህ እትም ሴቶች ጤናቸውን ረገድ የታዩ አበረታች ነገሮችንና ጤናቸውን መጠበቅ የሚችሉባቸውን 10/ መንገዶች እናስነብባችሁ..ለን፡፡  
    ***
ወይዘሮ ትሁን አለም ፣ ወ/ሮ ሐረጊቱ እንደሻው እና ወ/ሮ እመቤት በጎንደር ከተለያየ አቅጣጫ ወደጎንደር ሆስፒታል እና ፌስቱላ ሐኪም ቤት መጥተው ያነጋገርናቸው እናቶች ናቸው፡፡ ሁሉም ወደሆስፒታሎቹ የመጡት በማህጸን መውጣት ሕመም ምክንያት ነው፡፡ በጎንደር ሆስፒታል ያገኘናት ወ/ሮ እመቤት ባለቤትዋ ካለፈ ከስድስት አመት በላይ ሆኖታል፡፡ ለእሱም 6/ ልጆች ወልዳለች፡፡ በአሁኑ ወቅትም ሌላ ትዳር እንድትመሰርት ጥያቄ ቀርቦላት አግብታለች፡፡ ነገር ግን ከአዲሱ ባለቤትዋ የቀረበላት ጥያቄ አለ፡፡ ‹‹...እኔም ልጅ አለኝ... አንቺም ልጅ አለሽ... ነገር ግን ሁለታችን በጋራ ልጅ እንዲኖረን አንድ ልጅ ብንወልድስ ?››  የሚል ነው፡፡ እስዋ ግን ...አ...አ...ይ ... ቆይ እስቲ መጀመሪያ ጤናዬን ልከታተል በማለት በጎንደር ራቅ ካለው አካባቢ ወደ ጎንደር ሆስፒታል መጥታለች፡፡ ስትመረመርም የማህጸን መውጣት ህመም እንዳለባት እና ከእርግዝናው በፊት መታከም እንደሚገባት ተነግሮአታል፡፡ እንደሐኪምዋ ዶ/ር ኤፍሬም እማኝነት ሴትየዋ ምንም እንኩዋን በገጠር የምትኖር ቢሆንም ቅድመ እርግዝና ጤናዋን ለመታየት መምጣትዋ እጅግ የሚያስመሰግናት ሲሆን በሌሎችም ሊለመድ ይገባዋል ብለዋል፡፡ ወ/ሮ ትሁን አለም ከወረታ ዙሪያ አዲስዘመን ነው ወደሕክምናው የመጡት፡፡ እሳቸውም እንደሚሉት ከማህጸናቸው መጥፎ ሽታ ሲሰማቸውና በጤንነታቸውም በተለይም ጎንበስ ቀና ብሎ ስራ መስራት እንዲሁም ወዲያ ወዲህ ማለት ሲያስቸግራቸው በቤተሰቦቻቸው እገዛ በሬአቸውን ሸጠው ወደሆስፒታል የመጡ ናቸው፡፡ እኚህም እናት ከገንዘብ ይልቅ ጤና ይበልጣል ብለው መምጣታቸው የሚያስመሰግናቸው መሆኑን የህክምና ባለሙያዎቹ መስክረዋል፡፡
ወ/ሮ ሐረጊቱ እንደሻው እንደዚሁ በጎንደር ፌስቱላ ሆስፒታል በማህጸን መውጣት ችግር ምክንያት ከሆስፒታል ተኝታ ያገኘናት እናት ናት፡፡ በተለይም እንደወ/ሮ ሐረጊቱ ምስክርነት በገጠር ብዙዎች በዚህ ሕመም ከቤታቸው ሁነው በመሰቃየት ላይ የሚገኙ በመሆኑ እስዋ ሕክምናዋን ጨርሳ እንደተመለሰች ሕክምናው የሚሰጥ በመሆኑ ወደሆስፒታል እንዲሄዱ የምትመክር እና ለጤና ኤክስ..ንሽን ሰራተኞችም እንደምትጠቁም ለራስዋ ቃል ገብታለች፡፡
በጎንደር ፊስቱላ ሆስፒታል ያገኘናቸው ዶ/ር ኪሮስ ተረፈ እንደሚመሰክሩት በገጠራማው የኢትዮጵያ አካባቢ ሴቶች በማህጸን መውጣት ሕመም እንደሚሰቃዩና ብዙዎችም ወደ ሕክምናው እንደማይቀርቡ ነው፡፡ ዶ/ር ኪሮስ በጎንደር ፊስቱላ ሆስፒታል በአንድ አመት ገደማ ወደ ስድስት መቶ የሚደርሱ እናቶች ሕክምናውን እንዳገኙና ገና ወደፊትም በርካት ስራ መስራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡  
ሴቶች ጤናቸውን መጠበቅ የሚችሉባቸው 10 መንገዶች፡-
1. እንቅልፍ፡-
በአሜሪካን ሀገር በሚገኝ አንድ ሆስፒታል የኢንተርናል ሜድስን ሀላፊ የሆኑት ዶክተር     ዶኒ ኤግ እንደሚሉት ከሆነ በቂ እንቅልፍ አለማግኘት ጤናማ ላልሆነ የሰውነት ክብደት፣ ለልብ በሽታ እንዲሁም ትኩረት ማጣት፣ አእምሮ ንቃት መቀነስ  ወይም የማስታወስ ችሎታ መቀነስ ለማሳሰሉት ችግሮች ሊዳርግ ይችላል፡፡ ስለዚህም ይላሉ     ዶክተር ዶኒ አንዲት ሴት በቀን ውስጥ ቢያንስ ለ8/ስምንት ሰአታት ያህል እንቅልፍ     ማግኘት ይኖርባታል፡፡
2. የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ፡-
የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ጤናማ እና ንቁ እንድንሆን ከሚያደርጉ ነገሮች መካከል አንዱ ነው፡፡ በየቀኑ ለ30/ ወይም ቢያንስ ለ10/ ደቂቃዎች ያህል የሚደረግ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንደ ካንሰር፣ የልብ በሽታ እና የአጥንት መሳሳት ለመሳሰሉት     የጤና     ችግሮች የሚኖረንን ተጋላጭነት በእጅጉ እንደሚቀንስ  የፅንስ እና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት የሆኑት ፍራንሲስ ስሚዝ ይናገራሉ፡፡ በተጨማሪም መጠነኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ የወር አበባ በሚቆምበት (ሜኖፖዝ) በስኳር ህመም     እንዲሁም በሌሎች የጤና እክሎች ወቅት የሚስተዋሉ ምልክቶች በእጅጉ እንዲቀንስ ያደርጋል፡፡
3. የጥርስን ጤንነት መጠበቅ፡-
ቁጥራቸው ከ25-40% የሚጠጉ ሴቶች ከወሊድ፣ከልብ ወይም ከካንሰር በሽታ ጋር በተያያዘ ለሚከሰት የጥርስ ህመም እንደሚጋለጡ ዶክተር ዶኒ ይገልፃሉ፡፡ ስለዚህም ይህ ከመሆኑ አስቀድሞ በየእለቱ የጥርስን ንፅህና መከታተል እና ጤንነቱን መጠበቅ ያስፈልጋል፡፡
4. ቅድመ-ምርመራ፡-
አንዲት ሴት የማህፀን እና ፅንስ እንዲሁም ሌሎች አጠቃላይ ምርመራዎችን በየግዜው     ማድረግ ይኖርባታል፡፡  ዶክተር ፍራንሲስ ስሚዝ ሴቶች በየአመቱ ሊያደርጓቸው ከሚገቡ ቅድመ-ምርመራዎች መካከል ፓፕስሜር..አመታዊ የማህፀን ምርመራ.. እና የጡት ምርመራ ዋነኞቹ ሊሆኑ እንደሚገባ እና በተጨማሪም ደግሞ ሌሎች አጠቃላይ ምርመራዎችም መዘንጋት እንደሌለባቸው እንዲሁም ቅድመ-ምርመራው ቢያንስ በ     አመት ወይም በየ2 አመቱ መደረግ እንዳለበት አፅንኦት ሰጥተው ይናገራሉ፡፡ እንደ የስ..ር ህመም፣ የልብ በሽታ እና ካንሰር የመሳሰሉትን በተመለከተም ተገቢውን ጥንቃቄ     እና ክትትል ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
5. ቁርስን በአግባቡ መመገብ፡-
በመኝታ ወቅት ሰውነት እረዥም ሰአታትን ያለ ምግብ ያሳልፋል ስለዚህም ጠዋት ከእንቅልፋችን ስንነሳ በቂ ምግብ ማግኘት ይኖርብናል፡፡ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ቁርስን በአግባቡ አለመመገብ በነገሮች ላይ ትክክለኛውን ውሳኔ መስጠት፣ የመማር እንዲሁም ነገሮችን የማስታወስ ችሎታችን ላይ ከፍተኛ ተፅኖ ያደርጋል፡፡ ስለዚህም ይላሉ ዶክተር ዶኒ አንዲት ሴት ከፍተኛ የፋይበር ይዘት ያላቸውን ምግቦች፣    ፍራፍሬዎችን እንዲሁም ወተት እና የወተት ተዋፅኦ ምግቦችን በቁርስ ገበታዋ ላይ አመጣጥና ማካተት ይኖርባታል፡፡
6. እጅን መታጠብ፡-
    በጀርም ወይም በባክ..ሪያ አማካኝነት የሚመጡ በሽታዎችን ለመከላከል እጅን በሳሙና እና በውሀ በሚገባ መታጠብ ያስፈልጋል፡፡
    (እንደሚታወቀው ምግብ የማብሰሉ እና ልጆችን የመንከባከቡ ሀላፊነት በአብዛኛው ለሴቶች የተተወ ነው ፡፡ስለዚህ ይህንን በማድረግ የእራስዋን ብቻ ሳይሆን የቤተሰቦችዋንም ጤንነት ትጠብቃለች ማለት ነው፡፡)
7. ካልሲየም፡-
የካልሲየም ይዘት ያላቸውን ምግቦች መመገብ ወይም በመድሀኒት መልክ መውሰድ የአጥንትን ጥንካሬ በመጠበቅ የአጥንትን መሳሳት ችግርን መከላከል ይቻላል፡፡
8. አመጣጥኖ መመገብ ፡-
ይህ እንግዲህ የሚመገቡትን ምግብ በአይነትም ሆነ በይዘት ማመጣጠንን ይመለከታል፡፡     በየእለቱ የሚመገቡትን ምግብ ቢቻል ሁሉንም አለበለዚያ ደግሞ የተወሰኑትን የምግብ አይነቶች ቢያካትት ይመረጣል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሁለግዜም በልክ ወይም በመጠኑ     መመገብ ያስፈልጋል፡፡ ..ይህንን ተግባራዊ የምታደርግ ሴት ጤናማ የሆነ የሰውነት አቋም እንዲኖራት ማድረግ እና እንደ የደም ግፊት፣ የስኳር ህመም እና የልብ በሽታ የመሳሰሉት የጤና እክሎች መከላከል ትችላለች፡፡.. ይላሉ ዶክተር ዶኒ፡፡
9. ሲጋራ አለማጨስ፡-
ሲጋራ ከማጨስ ጋር ተያይዞ በሚከሰት የካንሰር ህመም እንዲሁም የልብ በሽታ ሳቢያ     በየአመቱ ቁጥራቸው 140,000/ የሚሆኑ ሴቶች ህይወታቸውን እንደሚያጡ ዶክተር     ፍራንሲስ ስሚዝ ይገልፃሉ፡፡ ከዚህም ሌላ ሲጋራ ማጨስ መሀንነት፣ ውርጃ እንዲሁም ሌሎች የስነተዋልዶ ጤና ችግሮችን ሊያስከትል ይችላል፡፡ ስለዚህ ሲጋራ የማጨስ ልምድ ያላቸው ሴቶች ማጨሳቸውን እንዲያቆሙ ይመከራል፡፡
10.  እራስን ነፃ ማድረግ ፡-
በመጨረሻም ዶክተር ስሚዝ እራስን ከጭንቀት ነፃ ለማድረግ የሚረዱ ተግባራትን በማከናወን ንቁ አእምሮ እንዲኖረን ማድረግ እንዲሁም ጤናማ ህይወትን መምራት እንደሚቻል ይገልፃሉ፡፡ስለዚህ አንዲት ሴት እነዚህ ቀደም ሲል የጠቀስናቸውን ነጥቦች በእለት ተእለት እንቅስቃሴዋ  ላይ ተግባራዊ በማድረግ ጤንነቷን መጠበቅ ብሎም እራሷን መንከባከብ ትችላለች፡፡ምንጭ ዌብ ሜድ

Read 5520 times