Saturday, 28 December 2013 10:13

ማራቶን ልዕልቷ በቀነኒሳ ዒላማ ገባች

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

አትሌት ቀነኒሣ በቀለ ከ2 ሳምንት በኋላ በስኮትላንድ ኤደንብራ አገር አቋራጭ በታሪክ ለ6ኛ ጊዜ እንደሚሳተፍ ታወቀ፡፡ በጭቃማና አስቸጋሪ መሮጫው በሚለየው ኤደንብራ አገር አቋራጭ በ4 ኪሎ ሜትር ውድድር ከ2006 እ.ኤአ ጀምሮ ሲሳተፍ በዚሁ ለ3 ዓመታት አከታትሎ ያሸነፈው አትሌቱ በ2010 እ.ኤ.አ 2ኛ እንዲሁም ባለፈው ዓመት 11ኛ ደረጃ ነበረው፡፡ የዘንድሮው ተሳትፎ ወደ አሸናፊነቱ ለመመለስ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ በዓለም አገር አቋራጭ ውድድሮች በከፍተኛ ውጤት የሚመራው ቀነኒሣ፤ በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና በአጭር 4ኪሎ ሜትርና በ12 ኪሎ ሜትር ረዥም ርቀት ውድድሮች11 የወርቅ ሜዳልያዎች መሰብሰቡ ይታወቃል፡፡ በሌላ በኩል በ2014 የለንደን ማራቶን አዘጋጆች የዓለም ሪከርድ ባለቤት የሆነውን ኬንያዊውን ዊልሰን ኪፕሳንግ፣ እንግሊዛዊውን ሞ ፋራህና ቀነኒሣን የማገናኘት ዕቅድ አላቸው ፡፡ ከሞ ፋራህ ይልቅ የማራቶን ክብረወሰንን ለመስበር እድሉ ለቀነኒሳ በቀለ እንደሆነም ይገለፃል፡፡ የማራቶን ሪከርድ በዊልሰን ኪፕሳንግ 2 ሰዓት ከ03 ደቂቃ ከ23 ሰኮንዶች በሆነ ጊዜ የተያዘ ነው፡፡ ቀነኒሣ ወደ ማራቶን ፊቱን እንዳዞረ ዋናው ፍላጎቱ በ2016 እኤአ ላይ በሪዮዲጄኔሮ በሚደረገው 31ኛው ኦሎምፒያድ በ34 ዓመቱ በመሳተፍ የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳልያ ማግኘት እንደሆነ በመግለፅ ነበር፡፡ በ2014 ወደ ማራቶን ሙሉ ለሙሉ ለመግባት እቅድ እንዳለው መናገሩም የሚታወስ ነው፡፡ ቀነኒሣ በቀለ ባለፉት 3 የውድድር ዘመናት ከነበረበት ጉዳት በተያያዘ ከውድድር እንደተገለለ ሲነገር ቆይቷል፡፡ አሁን የዓለማችን የምንጊዜም ምርጥ የረጅም ርቀት ሯጭ ተብሎ የሚደነቀው ቀነኒሣ በቀለ የመጀመርያው ማራቶኑን የት ሊሮጥ ነው? እንዴት እየተዘጋጀ ነው ?ለተሳትፎ ስንት ይከፈለዋል? ምርጥ ሰዓት ያስመዘግባል ወይ? ሪከርድስ ሊሰብር ይችላል? በሚሉና ሌሎች ጥያቄዎች በአትሌቲክሱ ዓለም እያነጋገረ ነው፡፡ የ31 ዓመቱ አትሌት ቀነኒሣ‹‹ ማራቶንን ከሮጥኩ ለማሸነፍ ነው፡፡ በመጥፎ ውጤት ልጀምር አልፈልግም፡፡ ብሎ ለአይኤኤኤፍ የተናገረ ሲሆን ‹‹ የመጀመርያው ማራቶኔን የት እንደምሮጥ አላውቀውም፡፡ በሩጫ ዘመኔ ያስመዘገብኳቸው ትልልቅ ታሪኮችን በሚመጥን ደረጃ መሮጥ ግን እፈልጋለሁ፡፡ እንዳለኝ ውጤታማነት በቂ የተሳትፎ ክፍያ የሚያቀርብልኝን እየጠበቅኩ ነው፡፡ ሁሉ እስኪሳካ ጉዳዩን ምስጥር ማድረግም ተገቢ ነው፡፡ ምርጫዬ ትልቅ ክብር እና ታሪክ ያለው፤ ምርጥ አትሌቶችን የሚያሳትፍ የማራቶን ውድድር ነው፡፡ በማይረባ የማራቶን ውድድር እና ጥሩ ገቢ በማይገኝበት ሁኔታ አጥንቴን አልሰነጥቅም›› በሚል ማብራራያም ሰጥቷል፡፡ ‹‹ፈጣን ሰዓት ለማስመዝገብ ስለምፈልግ በከፍተኛ ትኩረት ጠንካራ ዝግጅት እያደረግኩ ነኝ፡፡ 2፡03፤ 2፡05፤ 2፡06 እገባለሁ ብዬ ለመናገር አልችልም፡፡ ዋናው በቂ እና የተሟላ ዝግጅት ማድረግ ነው፡፡ ልምምዱ ፈታኝ ነው፡፡ ሁሉን ተቋቁሞ በስነልቦና ጠንካራ ሆኖ ራሴን በማነሳሳት ጥሩ ውጤት ለማምጣት ፍላጎት አለኝ፡፡›› ብሏል፡፡‹‹አንዳንድ ሯጮች ማራቶን ከ30 ኪሎሜትሮች በኋላ ፈታኝ ይሆናል ይላሉ፤ ሌሎች ደግሞ ከ35፤ ከ38 እና ከ40 ኪሎሜትሮች በኋላ ማራቶንን መሮጥ እንደሚከብድ ይገልፃሉ፡፡ የማራቶን ልምድ በእያንዳንዱ አትሌት ብቃት ላይ የተመሰረተ መሆኑንም ገልፆታል፡፡ ቀነኒሣ የማራቶን ልምምዱን ካለፈው ሁለት ወር ወዲህ እየሰራ ነው፡፡ ከባህር ጠለል በታች 2700 ሜትር ከፍታ ባላቸው ሱልልታ እና ሰንዳፋ፡፡ ለማራቶን መዘጋጀት ሲጀምር ከነበረው መደበኛ ልምምድ ባሻገር በሳምንት ፕሮግራሙ ላይ 3 ሰዓት ተጨማሪ አድርጓል፡፡ በአጠቃላይ በሳምንት 130 ኪሎሜትሮችን እየሮጠ ነው፡፡ ከተግባር ልምምዱ ባሻገር በማራቶን ውድድር የአሁን ዘመን አትሌቶች ያላቸውን ልምድ እና ውጤት የተለያዩ የመረጃ ምንጮች እና ድረገፆችን እየተከታተለ ያጠናልም፡፡ ማናጀሩ የሆኑት ሆላንዳዊው ጆስ ሄርማንስ የመጀመርያ ማራቶኑን የት ሊሮጥ እንደሚችል፤ ስንት ሊከፈለው እንደሚገባ እና ከየትኞቹ አትሌቶች ጋር ሊፎካከር እንደሚችል በማጥናት መላው የዓለም አትሌቲክስ ስፖርት አፍቃሪዎች ሁኔታውን በጉጉት እንዲጠባበቅ በሚያደርግ ዘመቻ ላይ ናቸው፡፡ ከታላላቅ የማራቶን ውድድሮች ለቀነኒሣ በቀለ የመጀመርያ ማራቶን ተሳትፎ ሰፊ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ የሚገኘው የለንደን ማራቶን ነው፡፡ የለንደን ማራቶን አዘጋጆች ለአትሌት ቀነኒሣ በቀለ ተሳትፎ ብቻ እሰከ 1 ሚሊዮን ፓውንድ የመክፈል ፍላጎት እንዳላቸው ከተወራ ሰነባብቷል፡፡ ከ3 ወራት በፊት በቡፓ ግሬት ኖርዝ ራን አትሌት ቀነኒሳ በቀለ የመጀመርያ ግማሽ ማራቶኑን ሲያሸንፍ በመጨረሻዎቹ ሜትሮች ሞ ፋራህን ቀድሞ በመግባት ነበር፡፡ ውድድሩ ካለቀ በኋላ ሞ ፋራህ ለንደን እንገናኝ ብሎታል፡፡ የለንደን ማራቶን አዘጋጆች ሞ ፋራህ ከቀነኒሳ ጋር የመጀመርያ ማራቶኑን እንዲወዳደር እያግባቡ ናቸው ፡፡ ቀነኒሳ የመጀመርያ ማራቶኑን የት ሊሮጥ እንደሚችል በይፋ አልተናገረም፡፡ የኒውዮርክ ፤የሮተርዳምና የበርሊን ማራቶን አዘጋጆችም የቀነኒሣን ተሳትፎ ይፈልጋሉ፡፡ ራነርስ ዎርልድ በአትሌት ቀነኒሣ በቀለ የመጀመርያው ማራቶን ተሳትፎ ዙርያ በሰራው ትንተና ርቀቱን በ2 ሰዓት ከ01 ደቂቃ 05 ሰኮንዶች በማጠናቀቅ ሪከርድ ሊያስመዘግብ እንደሚችል ወይም 2 ሰዓት ከ06 ደቂቃ ከ10 ሰኮንዶች በሆነ ጊዜ በማስመዝገብ መልካም አጀማመር ሊኖረው እንደሚችል ገምቷል፡፡

Read 2056 times