Monday, 23 December 2013 09:52

በ«ቻን» ኢትዮጵያን ምን ይጠብቃታል?

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

በደቡብ አፍሪካ በሚስተናገደው 3ኛው የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮንሺፕ (CHAN) የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዝግጅቱን ከሳምንት በኋላ እንደሚጀምር ታወቀ፡፡  በቻን ውድድር ለመጀመርያ ጊዜ የሚቀርበው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከምድብ ማጣርያው ማለፍ እንደሚችል ግምት ቢያገኝም በቂ ዝግጅት ሳይኖረውና ለአቋም መፈተሻ የሚሆን የወዳጅነት ጨዋታ  አለማድረጉ ተሳትፎውን ሊያከብድበት ይችላል፡፡ ዋልያዎቹ በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያውያንን ድጋፍ በቻን ውድድር  በማግኘት ትኩረት ይስባሉ፡፡ በአገር ውስጥ ክለቦች በሚገኙ ተጨዋቾች ስብስብ በሚዋቀረው ብሄራዊ ቡድኑ ላይ ወሳኝ ሚና ሊኖራቸው ከሚችሉ ተጨዋቾች መካከል  በሴካፋ የታዩ አዳዲስ ዋልያዎች ይጠቀሳሉ፡፡
በ3ኛው የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮንሺፕ በምድብ 3 ኢትዮጵያ ፤ ከጋና፤ ከሊቢያ እና ከኮንጎ ብራዛቪል ጋር መደልደሏ ይታወቃል፡፡ የመጀመርያ ጨዋታዋን ከሊቢያ ጋር፤ ሁለተኛ ግጥሚያዋን ከኮንጎ ብራዛቪል ጋር እንዲሁም የመጨረሻ ግጥሚያዋን ከጋና ጋር ታደርጋለች፡፡ ሁሉንም ጨዋታዎች የምታደርግበት ፍሪስቴት ስታድዬም 40911 ተመልካች የሚያስተናግድና በብሎምፎንቴን ከተማ የሚገኝ ነው፡፡ ፍሪስቴት ስታድዬም በ1996 እኤአ ላይ 7 የአፍሪካ ዋንጫ  ጨዋታዎችን፤ በ2009 እኤአ አራት የኮንፌደሬሽን ካፕ ካፕ ጨዋታዎችን እንዲሁም በ2010 እኤአ 6 የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎችን ያስተናገደ  ነው፡፡
ኮንጎ ብራዛቪል እና ኢትዮጵያ በቻን ውድድር የመጀመርያ  ጊዜ ተሳታፊ ናቸው፡፡ ጋና ለሶስተኛ ጊዜ ከመሳተፏም በላይ በ2009 እኤአ ለዋንጫ ተጫውታ ሁለተኛ ደረጃ ስታገኝ በ2011 እኤአ ደግሞ ከምድብ ማጣርያው ተሰናብታለች፡፡ ሊቢያ ደግሞ ለሁለተኛ ጊዜ  በቻን የምትሳተፍ ይሆናል፡፡  
ኢትዮጵያ የምድብ ማጣርያውን አልፋ ወደ ሩብ ፍፃሜ ከገባች በጥሎ ማለፍ ልትገናኝ የምትችለው በምድብ 4  ከሚገኙት ከኮንጎ ዲ ሪፖብሊክ፣ ጋቦን፣ ብሩንዲ ወይም ሞውሪታንያ ጋር ነው፡፡ ኢትዮጵያ በምድብ 3 አንደኛ ከሆነች በምድብ 4 ሁለተኛ ሆና ከጨረሰው ጋር በኬፕታውን ከተማ በሚገኘው የኬፕታውን ስታድዬም ወይም ደግሞ በምድብ 3 ሁለተኛ ከሆነች ከምድብ 4  አንደኛ ጋር በፖልክዋኔ ከተማ  በሚገኘው ፒተር ሞካባ ስታድዬም  በጥሎ ማለፉ ትገናኛለች፡፡ ከኢትዮጵያ ጋር በአንድ ምድብ ለሚገኘው የጋና ቡድን 28 ተጨዋቾች ከአገሪቱ ስኬታማ ክለቦች ተመርጠውበት ባለፈው ማክሰኞ ዝግጅቱን በአክራ ጀምሯል፡፡ ይህ የጋና  ቡድን  በነገው እለት ለአቋም መፈተሻ እንዲሆነው በአክራ የማሊን ብሄራዊ ቡድን ያስተናግዳል፡፡ ከዚህ ጨዋታው በኋላ የመጨረሻ ዝግጅቱን ለማድረግ በሚቀጥለው ሰኞ  ወደ ናሚቢያ እንደሚያቀና ሲታወቅ ከውድድሩ መጀመር በፊት ከናሚቢያም ጋር የወዳጅነት ጨዋታ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት በሱዳን በተደረገው 2ኛው የቻን ውድድር የጋና ቡድን ከምድብ ማጣርያው የተሰናበተበትን ደካማ ውጤት ዘንድሮ እስከ ዋንጫው በመገስገስ ለማሻሻል ታስቧል፡፡ የጋና ቡድን በምድቡ የተሻለ ግምት በመስጠት የሚጠባበቀው የኢትዮጵያ ቡድንን እንደሆነ እየተገለፀ ሲሆን የምድብ ድልድሉ በወጣበት ወቅት በስፍራው የነበሩት የሊቢያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ከምድብ 3 የምናልፈው እኛ እና ዋልያዎቹ ነን ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
በሌላ በኩል በቻን ውድድር የናይጄርያ ቢ ቡድንን ይዞ እንደሚቀርብ ያስታወቀው ስቴፈን ኬሺ ዋንጫውን ማሸነፍ አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል ተናግሯል፡፡ በምድብ 1 ከአዘጋጇ ደቡብ አፍሪካ፤ ማሊ፤ እና ሞዛምቢክ ጋር የተመደበው የናይጄርያ  ቡድን ለቻን ያደረገው ዝግጅት በቂ እንዳልሆነ የተናገረው ስቴፈን ኬሺ ለአቋም መፈተሻ የሚሆነው ግጥሚያ አለማድረጉ በብቃት ላይ ተፅእኖ መፍጠሩ አይቀርም ብሏል፡፡ የናይጄርያ ቢ ቡድን በቀን ሁለቴ ልምምድ እየሰራ የቻን ውድድርን ይጠባበቃል፡፡ የቻን ውድድር ለዋናው ብሄራዊ ቡድን በብቃት ተተኪ የሚሆኑ ተጨዋቾችን ለማግኘት ያስችላል ያሉት ደግሞ የደቡብ አፍሪካ ብሄራዊ ቡድንን በዋና አሰልጣኝነት ይዘው የሚቀርቡት ጎርደን ሌጀሰንድ ናቸው፡፡ ደቡብ አፍሪካ የቻን ውድድርን በማዘጋጀቷ ብሄራዊ ቡድኑ በውድድሩ እስከመጨረሻው ምእራፍ ሊጓዝ የሚችልበትን ድጋፍ ያስገኝለታል ያሉት ጎርደን ሌጀሰንድ ዋንጫውን የማሸነፍ ፍላጎት አለኝ ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የኡጋንዳ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ የሆነው ሰርዴዮቪች ሚሉቲን ለቻን ውድድር ቡድኑን በወጣትነት እና ልምድ ባላቸው ተጨዋቾች በመገንባት እንደሚቀርብ ተናግሯል፡፡ ዘ ክሬንስ የተባለው የኡጋንዳ ብሄራዊ ቡድን በቻን ውድድር በተከታታይ ለሁለተኛ ጊዜ የሚሳተፍ ሲሆን ያሉበት ምድብ ጠንካራ ቢሆንም ወደ ጥሎ ማለፍ ምዕራፍ ለመግባት ከፍተኛ ትግል እናደርጋለን ብለዋል፡፡ በ3ኛው የአፍሪካ አገሮች የእግር ኳስ ሻምፒዮንሺፕ ላይ ያሉት አራት ምድቦች ድልድል ማን የበላይ እንደሚሆን ለመገመት የሚያስቸግር ነው የሚለው ሚቾ ኡጋንዳን እስከ ሩብ ፍፃሜ ለማድረስ እቅድ እንዳለው አመልክቷል፡፡ ኡጋንዳ በምድብ 2 ከዚምባቡዌ ፤ ከቡርኪናፋሶ እና ከሞሮኮ  ጋር መመደቧ የሚታወስ ሲሆን የውድድሩ ቀላል ድልድል በተባለው ምድብ 4 ዲሞክራቲክ ሪፖብሊክ ኮንጎ፤ ጋቦን፤ ብሩንዲና ሞውሪታንያ ተገናኝተዋል፡፡

Read 2722 times