Saturday, 14 December 2013 11:54

የወርቅ ኳሱ ለሮናልዶ ይገባል?!

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(3 votes)

    በፊፋ እና በፍራንስ ፉትቦል ትብብር ዘንድሮ ለሶስተኛ በሚዘጋጀው የዓመቱ ኮከብ እግር ኳስ ተጨዋቾች፤ አሰልጣኞች እና ምርጥ ቡድን ምርጫ ላይ በየዘርፉ ለመጨረሻው ፉክክር የቀረቡት እጩዎች በየዘርፉ ከሰሞኑ ታውቀዋል፡፡ በድምፅ አሰጣጡ ሂደት የፊፋ አባል አገራት የሆኑ 209 ፌደሬሽኖች በብሄራዊ ቡድኖቻቸው ዋና አሰልጣኞች እና በአምበሎች፤ እንዲሁም ታዋቂ ዓለም አቀፍ የስፖርት ሚዲያዎች ተሳትፈውበታል፡፡ ዓመታዊው የዓለም እግር ኳስ ክዋክብት የሽልማት ስነስርዓት ከ1 ወር በኋላ በዙሪክ የሚካሄድ ነው። በከፍተኛ ደረጃ እያከራከረ በሚገኘው የዓለም ኮከብ ተጨዋች ምርጫ ለመፎካከር የመጨረሻ እጩ ሆነው የቀረቡት ሶስት ተጨዋቾች አርጀንቲናዊው ሊዮኔል ሜሲ፤ ፖርቱጋላዊው ክርስትያኖ ሮናልዶ እና ፈረንሳዊው ፍራንክ ሪበሪ ናቸው፡፡ በዓለም ኮከብ አሰልጣኝ ምርጫ በመጨረሻ ተፎካካሪነት የቀረቡት ደግሞ የማንችስተር ዩናይትድ ክለብ አሰልጣኝ የነበሩት ስኮትላንዳዊው ሰር አሌክስ ፈርጉሰን፤ ባለፈው ዓመት ከባየር ሙኒክ ጋር የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን አንስተው የተሰናበቱት ጀርመናዊው ጁፕ ሃይንከስ እና የቦርስያ ዶርትመንዱ አሰልጣኝ ጀርመናዊው የርገን ክሎፕ ናቸው፡፡

በዓመቱ ምርጥ ጎል ምርጫ ለፑሽካሽ አዋርድ በመፎካከር ደግሞ ዝላታን ኢብራሞቪች፤ ኔማንጃ ማቲች እና ፓብሎ ኔይማር ተመርጠዋል፡፡ ለ2013 የዓለም ምርጥ ቡድን የሚበቁ 11 ተጨዋቾን ለመምረጥ የዓለም አቀፉ የፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጨዋቾች ማህበር አባላት የሆኑ 55ሺ ተጨዋቾች በሚሰጡት ድምፅ መሰረት የመጨረሻ እጩዎች ሆነው የቀረቡም ተለይተዋል፡፡ ለምርጥ 11 ቡድኑ የቀረቡ የመጨረሻ እጩዎች 5 ግብጠባቂዎች፤20 ተከላካዮች 15 አጥቂዎችና 15 አማካዮች ናቸው፡፡ ሊዮኔል ሜሲ ላለፉት 4 ዓመታት የወርቅ ኳሱን አከታትሎ በማሸነፍ በመጨረሻ እጩነት የቀረበ ሲሆን ዘንድሮ ካሸነፈ ለአምስተኛ ጊዜ የሚሸለምበት ይሆናል፡፡ ክርስትያኖ ሮናልዶ በበኩሉ የወርቅ ኳስ ሽልማቱን በ2008 እኤአ ላይ ብቻ ተሸልሞበታል፡፡ ክርስትያኖ ሮናልዶ የዘንድሮውን የወርቅ ኳስ ሽልማት እንደሚያሸንፍ ግምት እያገኘም ነው፡፡ ሰሞኑን ታዋቂው የስፖርትመፅሄት ዎርልድሶከር ሮናልዶን የዓመቱ የዘንድሮ ኮከብ አድርጎ ከመረጠው በኋላ የወርቅ ኳሱንም እንደሚወሰድ ያመለክታል ተብሏል፡፡ ባለፉት ዓመታት በዎርልድ ሶከር መፅሄት ኮከብ ሆነው ከተመረጡት 14 ተጨዋቾች የወርቅ ኳስ ተሸላሚ ለመሆን መብቃታቸው ለዚህ ምክንያት ሆኖ ነው፡፡

ክርስትያኖ ሮናልዶ ባለው ጎል የማስቆጠር ወቅታዊ ብቃት፤ ፖርቱጋልን በመጨረሻ የጥሎ ማለፍ ማጣርያ ጨዋታ በሰራው ሃትሪክ ወደ ዓለም ዋንጫ በማሳለፉ የመመረጥ እድሉ ሰፊ እንደሆነ እየተገለፀ ነው፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት በተካሄዱት ሁለት የወርቅ ኳስ ሽልማቶች ሮናልዶ በድምፅ ብዛት ሜሲ እየበለጠው በሁለተኛ ደረጃ አጠናቅቋል፡፡ ዘንድሮ ሊያሸንፍ እንደሚችል ግምት ቢኖርም ከፊፋ ባለስልጣናት የገባው አተካታ ተፅእኖ ሊፈጥርበት ይችላል፡፡ የፊፋ ፕሬዝዳንት ሴፕ ብላተር በኦክስፎርድ ተማሪዎች ፊት እሱን በተመለከተ በሰጡት አስተያየትና ባህርይውን ለመግለፅ በይፋ ባሳዩት ድራማ ተቀይሞ በሽልማት ስነስርዓቱ ላይገኝ ይችላል በሚል የተወራ ቢሆንም ከሰሞኑ ክለቡ ሪያልማድሪድ ስለመገኘቱ ማረጋገጫ እንደሰጠ ተዘግቧል፡፡ ብላተር በሜዳ ላይ ወታደራዊ አዛዥ ይመስለኛል ፤ ግዜውን ለፀጉር ሰሪ የሚያባክን ነው፤ ብለው ሮናልዶን እንዳሾፉበት አይዘነጋም፡፡ ሊዮኔል ሜሲ በአጥቂ መስመር ለባርሴሎና እና ለአርጀንቲና ባለፈው የውድድር ዘመን አንስቶ ያሳየው ምርጥ ብቃት ቢደነቅም ከቅርብ ወራት ወዲህ በጉዳት ከጎል አልቢነት መራቁ በምርጫው ተፅእኖ ሊፈጥርበት ይችላል፡፡

የፈረንሳዩ ምርጥ የአማካይ መስመር ተጨዋች ፍራንክ ሪበሪ ከሮናልዶ እና ከሜሲ ጋር ለወርቅ ኳስ ሽልማት ለመፎካከር በእጩነት የገባው ለመጀመርያ ጊዜ ነው፡፡ ባለፈው የውድድር ዘመን ባየር ሙኒክ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ፤ የጀርመን ቦንደስሊጋ እና ኤፍኤ ካፕ ሶስት የዋንጫ ድሎችን ያጣጣመው ሪበሪ ፈረንሳይን ለ20ኛው የብራዚል ዓለም ዋንጫ እንድታልፍ ጉልህ ሚና በመጫወቱም አድናቆት አትርፏል፡፡በ2013 ሮናልዶ ለሪያል ማድሪድ ለፖርቱጋል ጎሎች ሲያስመዝግብ ሜሲ ለባርሴሎና እና ለአርጀንቲና 45 እንዲሁም ሪበሪ ለባየር ሙኒክ እና ለፈረንሳይ 21 ጎሎች በማግባት በርቀት ይከተሉታል። የ26 ዓመቱ ሊዮኔል ሜሲ በትራንስፈርማርኬት የዝውውር ገበያ 120 ሚሊዮን ዩሮ የዋጋ ተመን ሲኖረው የ28 ዓመቱ ክርስትያኖ ሮናልዶ የተተመነው በ100 ሚሊዮን ዩሮ ነው፡፡ የ30 ዓመቱ ፍራንክ ሪበሪ ደግሞ 42 ሚሊዮን ዩሮ እንደሚያወጣ ተገምቷል፡፡

Read 7838 times