Saturday, 15 December 2018 15:57

የጅማው “የአረጋውያንና ሕፃናት መርጃ”

Written by  መንግስቱ አበበ
Rate this item
(4 votes)


     “--እንዲህ ዓይነት ርህራሄና ጥንካሬ ያላት ሴት አይቼ አላውቅም፡፡ በምትሠራው ሥራ በጣም ተገርሜአለሁ፡፡ ስለ እሷ አንድ ነገር መናገር እፈልጋለሁ፡፡ እኛ ሐኪሞች ተረኛ ስንሆን ሆስፒታል እናድራለን፡፡ እሷ ግን ሁልጊዜ ላልወለደቻቸውና ከየጐዳናው ላነሳቻቸው ሕፃናት ሆስፒታል ማደር፤ ቅንነት፣ርህራሄና ፍቅር አይገልፀውም፡፡--”



    ለሰው ልጅ ሃዘኔታና ርህራሄ ያደረባቸው ገና በጧቱ፣ የ1ኛ ደረጃ ት/ቤት ተማሪ እያሉ ነበር፡፡ የ3ኛ ክፍል ተማሪ እያሉ፣ አንድ ቀን ከጓደኞቻቸው ጋር ወደ ት/ቤት ሲሄዱ አንድ ጨቅላ ሕፃን ቆሻሻ ላይ ተጥሎ፣ ዙሪያውን ውሾች ከበውት፣ ጆፌ አሞራ ደግሞ እላዩ ላይ ቆሞ፣ ዓይኑን ሊጠነቁል ሲል፤ “እኔስ ይህንን አላይም፤ እንዴት ሰው በልጁ ይጨክናል” በማለት ዓይናቸውን ጨፍነው መሸሻቸውን ያስታውሳሉ- የ47 ዓመቷ ወ/ሮ ዘመናይ አስፋው፡፡
ከተጣሉበት ቆሻሻ ላይ አንስተው ከሚያሳድጓቸው ሕፃናት አንዱ የሆነውና ድክድክ የሚለው ዮሐንስ፤ ሰብሳቢውና አሳዳጊ እናቱ ከውጭ ወደ ቤት ሲመለሱ፣ እንዲያነሱትና እንዲያቅፉት ሁለት እጆቹን ዘርግቶ፣ ሞግዚቶቹ ያደረሱበትን “በደል” እየተነጫነጨ፣ በኮልታፋ አፉ ነገራቸው፡፡ ወ/ሮ ዘመናይ አንስተው ሲያቅፉት፣በደስታ ተሞልቶ ይፈነድቅ ጀመር፡፡
በጅማ ከተማ በጐዳናና ቆሻሻ ቦታ የሚጣሉ ሕፃናት ቁጥር፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ፣ በውስጣቸው የነበረውን የበጐ አድራጐት ፍላጐት ለማሳካት፣ ባለፈው ዓመት ኅዳር 2010 ዓ.ም “ሰው ለሰው የአረጋውያንና የሕፃናት መርጃ ድርጅት” ማቋቋማቸውን ወ/ሮ ዘመናይ ይናገራሉ፡፡
ወደ በጐ አድራጐት ሥራ ከመግባታቸው በፊት፣ በሚዛን ተፈሪ ትዳር ይዘው፣ በመምህርትነት ነበር የሚያገለግሉት፡፡ ባላቸው በሞት ሲለይዋቸው፣ አባታቸው ካላቸው ቦታ ላይ “ነይ እዚህ ኑሪ” ብለው፣ ቆርሰው ሰጧቸው፡፡ ወ/ሮ ዘመናይም ወደ ጅማ ከተማ ተመልሰው፣ ከወላጆቻቸው ባገኙት ቦታ ላይ ጎጆ ቀልሰው መኖር ጀመሩ፡፡ ለመተዳደሪያቸው፣ በጅማ ከተማ አንድ መዋለ ሕፃናት ከፈቱ፡፡ ከጅማ ከተማ ወጣ ብላ በምትገኘው ቢሊዳ የተባለች ስፍራ፣ ከመዋለ ሕፃናት እስከ 6ኛ ክፍል የሚያስተምር ት/ቤት አላቸው። ሌላው መተዳደሪያቸው፣ ከአዲስ አበባ የተማሪዎች ዩኒፎርም እያስመጡ መሸጥ ነው፡፡ በበዓላት ጊዜ ደግሞ ጐመንና ሽንኩርት ይፈጫሉ፤ ዶሮ ይበልታሉ፤ ይሸጣሉ፡፡
የበጎ አድራጎት ድርጅቱን ሲያቋቁሙ፣ ወ/ሮ ዘመናይ ከርኅራሄና ከፍላጐት በስተቀር የገንዘብ አቅም አልነበራቸውም፡፡ አሁንም አንዳንድ የተቀደሰ ተግባራቸውን የሚያደንቁ ሰዎች በሙያቸው ከሚያደርጉላቸው እገዛ እንዲሁም  ጥቂት ሰዎች ከሚሰጧቸው የሞራል ድጋፍና መጠነኛ ዕርዳታ በስተቀር ምንም የላቸውም፡፡
በተወለዱበትና ባደጉበት የወላጆቻቸው ግቢ፤ አባታቸው በሰጧቸው ቦታ ላይ ለበጎ አድራጎት ድርጅቱ፤ በ800ሺ ብር ወጪ ለሴቶችና ለወንዶች አረጋውያን እንዲሁም ለሕፃናት ማሳደጊያ አንድ አንድ መጠለያ መሥራታቸውን ገልፀዋል፡፡ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ቀደም ሲል ተማሪዎች ይጠቀሙባቸው የነበሩ 20 አልጋዎችና ፍራሾች ሲለግሳቸው፣ የጅማ ሪፌራል ሆስፒታል 5 የሕፃናት አልጋ እንዲሁም የጅማ ግብርና ኮሌጅ፤ መቶ የ45 ቀናት ጫጩቶች፣ ዕንቁላል መጣል እስኪጀምሩ ድረስ ምግባቸውን ችለው ሊሰጣቸው ቃል እንደገበና ቤቱን ሠርተው እየጠበቁ መሆኑን ወ/ሮ ዘመናይ ተናግረዋል፡፡ የጅማ ከተማ ማዘጋጃ ቤትም፤ ቦታ ፈልገው እንዲሰጧቸው፣ ለ3 ቀበሌዎች ደብዳቤ መጻፉን ጠቁመዋል፡፡
 ዕቅዳቸው በዓመት 8 ሕፃናትና 20 አረጋውያን መቀበል ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት ተጥለው የተገኙና ከሆስፒታል የተሰጣቸው 6 የጨቅላ ሕፃናት፣ 6 አሳዳጊ የሌላቸው ከጐዳና ላይ የተሰበሰቡ ከፍ ከፍ ያሉ ልጆች፣ እንዲሁም 6 ሴትና 12 ወንድ አረጋውያን በመጠለያው እንደሚገኙ ገልጸው፤ ተደራራቢ አልጋ ላይ መውጣት የማይችሉና መሬት ላይ እንዲነጠፍላቸው የሚፈልጉ 10 አረጋውያንም ወረፋ እየተጣጠበቁ መሆኑንን መሥራቿ ተናግረዋል፡፡  
ወ/ሮ ዘመናይ በቅርቡ አንድ ህጻን እንዴት እንደተቀበሉ ሲናገሩ፤ -“አንድ ቀን ከሴቶችና ሕፃናት ተደውሎ በተለምዶ አጂፕ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ፣ አንድ ሕፃን ተጥሏልና ድረሽ ተባልኩ፤ ስደርስ አንዲት ሴት ሕፃኑን ታቅፋ ተቀምጣለች፡፡ ቆሻሻ ውስጥ ተጥሎ ነው የተገኘው አሉኝ፡፡ ሕፃኑን አየሁትና፤ ሌላ ቦታ እየሄድኩ ስለሆነ ወደ ድርጅቱ ወስዳችሁ ቆዩኝ፣ ብዬ ወደ ጉዳዬ አመራሁ፡፡
“የተጣለ ሕፃን ስናገኝ፣ ከአንድ ሰዓት በኋላ ገላውን እናጥባለን፡፡ ሕፃኑን ለማጠብ የተጠቀለለበትን ጨርቅ ስንፈታው፣ ጀርባው ላይ እባጭ የመሰለ ፍሳሽ የሚያወጣ ቀዳዳ የመሰለ የተከፈተ ነገር አየሁ፡፡ እንዲህ ያለ ነገር እስካሁን ገጥሞኝ ስለማያውቅ በጣም ደነገጥኩና ሕፃኑን ሕክምና ወደሚያገኝበት ሆስፒታል ይዤው ሄድኩ፡፡ ሐኪሞቹ ተሯሩጠው አዩትና፣ የማያውቁት ነገር ስለሆነባቸው፣ ወደ አዲስ አበባ ውሰጂው አሉኝ፡፡
“ከሆስፒታሉ ጋር ስለምንሠራ፤ ይህን ሕፃን አዲስ አበባ ውሰጂው ተብያለሁ፤ እንዴት ነው ማድረግ ያለብኝ? ሊሻለው ይችላል? ወይስ ዝም ብዬ ነው የምለፋው? በማለት የሕፃናት ሜዲካል ክፍል ኃላፊ የሆኑትን ዶ/ር መልካሙን ጠየቅሁ፡፡ እሳቸውም “ይቆይ” በማለት አረጋጉኝና፣ እዚያው እንዲተኛ ተደረገ፡፡ እስከዚያን ጊዜ ድረስ ምንም ምርመራ አልተደረገለትም ነበር፡፡ “ምርመራ ይደረግለት” ብለው ስላዘዙ፣ የተለያየ የደም ምርመራ ተደረገለት። እዚያው ጅማ ሆስፒታል ውስጥ ለ4 ቀናት ቢቆይም ተባባሰበት እንጂ ምንም አልተሻለውም፡፡ “በሰው ለሰው የአረጋውያንና የሕፃናት መርጃ” ውስጥ በበጐ ፈቃደኝነት የሕክምና ድጋፍ የሚያደርጉትንና የጅማ ሆስፒታል፣ የጤና መኮንን የሆኑትን አቶ ሲሳይ ደጀኔን፤“ለምንድነው የማይሻለው?” ስል ጠየቅሁ፡፡ ሐኪሞቹ ተነጋግረው ስለነበር እንደማይድን አውቀዋል። “ወደ ቤት ውሰጂው” አሉኝ፡፡ ከሺህ ውልደቶች መካከል እንዲህ ያለ የተፈጥሮ ችግር እንደሚከሰት አቶ ሲሳይ ነገሩኝ፡፡ ይኼው እቤት ከገባ 6 ቀን ቢሆነውም ምንም አልተሻለውም፤ እየተሰቃየ ነው፡፡ ጭንቅላቱ አልረጋም፤ ሲነካ እንደበሰለ ፓፓዬ ስርጉድ ስርጉድ ይላል--” በማለት ሕፃኑ ስላለበት ሁኔታ አስረድተዋል፡፡
ሌላው ችግር ያለበት የዓመት ከሦስት ወር ሕፃን ነው፡፡ “እናቱ ጅማ ሆስፒታል ሙቀት ክፍል አስተኝታው፣ ጥላው ጠፋች፡፡ ሆስፒታሉ ውስጥ ለ11 ወራት ቆይቷል፡፡ የተኛበት ክፍል ሞቃት ስለሆነ እዚያ እንደተኛ በረሮ ፊቱን ይበላዋል፡፡ ሌሎች ሕፃናት ለመውሰድ ነበር የሄድኩት፡፡ ደህና የሆኑትንና ችግር የሌለባቸውን ሕፃናት ሌሎች ሰዎች በጉዲፈቻ ሊወስዷቸው ይችላሉ፡፡ መረዳት ያለበት እንዲህ ያለው ነው ብዬ  ሌሎቹን ትቼ፣ እሱን ይዤ መጣሁ፡፡
“የዚህ ሕፃን ችግር ኅብለሰረሰር (ስፓይናል ኮርድ) አካባቢ ነው፡፡ ሐኪሞች፣ ሕፃኑን ምናልባት የካቲት 12 ሆስፒታል ሊረዱት ይችሉ ይሆናልና እዚያ ውሰጂው። ካልሆነ ሕክምናው በውጭ ሀገር ነው መካሄድ የሚችለው፡፡ በሕፃንነቱ ሕክምና ካላገኘ እንዲህ ሆኖ እንደሚቀር አንድ ሐኪም ነግሮኛል፡፡ በዚህ ዕድሜው (ዓመት ከ3 ወር) በእግሩ መሄድ ይገባው ነበር - አይሄድም፤ አይናገርም፣ አይቀመጥም፡፡ አሁን እኛ ፊዚዮቴራፒ እያሠራነው ትንሽ ለመቀመጥ እየሞከረ ነው፡፡ በየካቲት ሆስፒታል የሕክምና ዕድል እስኪያገኝ እየጠበቅን ነው፡፡ ሐኪሞቹ፤ ተጠያይቀን እንነግርሻለን ብለውኝ ነበር፡፡ እስካሁን ድረስ ግን የነገሩኝ ነገር የለም” በማለት ሕፃኑ ያለበትን ሁኔታ ገልፀዋል፡፡
የጅማ ዩኒቨርሲቲ የዛሬ ሳምንት የሕክምና ዶክተሮችና ሌሎች ያሠለጠናቸውን ተማሪዎች አስመርቆ ነበር፡፡ ዶ/ር አብዱል ቃድር መሐመድ አወል በዕለቱ ከተመረቁት 331 ሐኪሞች መካከል አንዱ ነው። አንድ ቀን ወ/ሮ ዘመናይ ጨቅላ ሕፃን ለማሳከም እንደመጡና ቀና ሲል “ሰው ለሰው የአረጋውያንና የሕፃናት መርጃ ድርጅት” የሚል ቲ-ሸርት መልበሳቸውን ማየቱን ያስታውሳል፡፡ “እንዲህ የሚባል ድርጅት አለ እንዴ?” በማለት ጠየቃቸው፡፡ “አዎን አለ” አሉት፡፡ “የት?” የሐኪሙ ጥያቄ ነበር፡፡ “እዚሁ ጅማ ውስጥ” አሉት ወ/ሮ ዘመናይ፡፡ “ሊያሳዩኝ ይችላሉ?” አላቸው፡፡ “በዚያኑ ቀን ድርጅቱን ሄጄ አየሁት” ይላል ዶ/ር አብዱል ቃድር፡፡
“እንዲህ ዓይነት ርህራሄና ጥንካሬ ያላት ሴት አይቼ አላውቅም፡፡ በምትሠራው ሥራ በጣም ተገርሜአለሁ። ስለ እሷ አንድ ነገር መናገር እፈልጋለሁ፡፡ እኛ ሐኪሞች ተረኛ ስንሆን ሆስፒታል እናድራለን፡፡ እሷ ግን ሁልጊዜ ላልወለደቻቸውና ከየጐዳናው ላነሳቻቸው ሕፃናት ሆስፒታል ማደር፤ ቅንነት፣ርህራሄና ፍቅር አይገልፀውም፡፡ የእሷ ድርጊት ከዚህ ሁሉ በላይ ነው። ገና ብዙ  ታሳየናለች--” ሲል ለወ/ሮ ዘመናይ ያለውን አድናቆት ገልጧል፡፡
ዶ/ር አብዱል ቃድር በምረቃው ዕለት፣ ወ/ሮ ዘመናይ ለአቋቋሙት የአረጋውያንና የሕፃናት መርጃ ድርጅት፣ በግሉ 100ሺህ ብር ድጋፍ አድርጓል፡፡ ዕርዳታውን ለመቄዶንያ አረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን ድርጅት ለመስጠት ነበር ያሰበው፡፡ የጅማውን “ሰው ለሰው የአረጋውያንና ሕፃናት መርጃ” ድርጅትን ሲያይ ሐሳቡን ቀየረ፡፡ “ድርጅቱ ምንም የሌለውና በመቋቋም ላይ ያለ ቢሆንም እየፈፀመ ያለው ተግባር ግን ትልቅ ነው፡፡ መበረታታትና መደገፍ አለበት፡፡ በሙስሊም እምነት ከምታገኘው አንድ አስረኛ በማውጣት ሰደቃ (ተዝካር) አድርገህ ድሆችን ታበላለህ፡፡ እኔም ለዚሁ ተግባር ያጠራቀምኩትን ገንዘብ ነው፣ ለ”ሰው ለሰው የአረጋውያንና ሕፃናት መርጃ ድርጅት” የሰጠሁት” ብሏል፡፡
ወ/ሮ ዘመናይ፣ በጅማ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ምርቃት ላይ እንድትገኝ ከመጋበዟ በስተቀር ድጋፍ አገኛለሁ የሚል አንዳችም ግምት እንዳልነበራት ተናግራለች፡፡ “ወደ ከመድረክ ስጠራ ደነገጥሁ፡፡ የተደረገልኝ ድጋፍ ደግሞ ለእኔ ብዙ ነው፤ 100ሺህ ብር ነበር፡፡ ማመን አልቻልኩም፤ ተገረምኩ፡፡ ወጣቱ ዶ/ር አብዱል ቃድር እንዲህ በማድረጉ እጅግ አድርጌ አከብረዋለሁ፡፡ ያደረገልኝን ስጦታ እግዚአብሔር ይክፈለው” በማለት አመስግነዋል፡፡
አሁን ድርጅቱን ካቋቋሙበት ቦታ ጐን ያለውን ስፍራ በ400ሺህ ብር ለመግዛት ተዋውለው፣ 200ሺህ ብሩን ተበድረው ከፍለው፣ 200ሺህ ብር ይቀርባቸዋል። “ከዶ/ር አብዱል ቃድር ያገኘሁትን 100ሺህ ብር ስከፍል 100ሺህ ብር ይቀርብኛል፡፡ እንዴት እንደማገኝ አላውቅም፡፡ በተስፋ እጠብቃለሁ፡፡ መቶውን ሺህ ብር አግኝቼ ቦታውን ብረከብም ለአረጋውያን፣ ለሕፃናትና ለአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ሕንፃ ግንባታ፣ የኢትዮጵያውያን ወገኖቼን ዕርዳታ ከመጠበቅ በስተቀር ምንም የለኝም” በማለት ወገኖቻቸው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሂሳብ ቁጥር 1000251272321 በስልክ ቁጥር፡- 0917801906 ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው ተማጽነዋል፡፡

Read 3006 times