Saturday, 24 October 2015 09:14

የዓለም ጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ውጤቶች በሚሊኒየም አዳራሽ ደምቀው ሰነበቱ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

     በርካታ የስፌት መኪኖች በሰልፍ ተደርድረዋል፡ አንዱ እጅግ ዘመናዊ መሳሪያ ሰፊ ቦታ ይዞ እየተሽከረከረ እንዴት ደረጃ በደረጃ እንደሚሰራ ያሳያል፡፡ ገሚሱ አርማ፣ መለያና የንግድ ምልክት ይጠልፋል፡፡ የልብስ ታጎች የሚሰሩም ሞልተዋል፡ ብዙ ኢንዱስትሪዎች የተለያየ ቀለም ያላቸው ድውሮች አቅርበዋል፡፡ የሚያመርቷቸውን የሸሚዝ ኮሌታዎች ብቻ ዓይነት በዓይነት የደረደሩም ብዙ ናቸው፡፡ ከውስጥና ከላይ የሚለበሱ ከጥበብ የተሰሩ የህፃናት፣ የሴቶችና አዋቂ ልብሶች፣ የተለያየ ዓይነትና መጠን ያላቸው የህፃናትና የአዋቂ ካልሲዎች፣ ፒጃማዎች፣ የበጋና የክረምት ልብሶች፣ ሙሉ ልብሶች፣ ኮቶች፣ ጂንሶች፣ … የደረደሩ ሞልተዋል፡፡ የተለያየ ዓይነትና ዲዛይን ያላቸው የሴት ቆዳ ቦርሳዎች፣ የወንድና የሴት ጫማዎች፣ ከጥጥ የተሰሩ ሻርፖች፣ በቀለም የደመቁ የአፍሪካውያን ልብሶችና ጨርቆች፣ ጌጣ ጌጦች፣ የተለያዩ የማሳጅና የስፓ ፎጣዎች፣ ምንጣፎች፣ መጋረጃዎች… ትናንት በተጠናቀቀውና በሚሊኒየም አዳራሽ በተካሄደው
“ኦሪጅን አፍሪካ - 2015 ኤግዚቢሽን” ከቀረቡ በርካታ የጥጥ ምርቶች ውስጥ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ካለፈው ረቡዕ እስከ ትናንት በቆየው ኦሪጅን አፍሪካ ኤግዚቢሽን፤ የአፍሪካ ታዋቂ የጥጥ፣ የጨርቃጨርቅ፣ የልብስ፣ የቤት ማስዋቢያ ጨርቆችና የቴክኖሎጂ ኢንዱስትሪዎች ምርቶቻቸውን ለዕይታ ያቀረቡ ሲሆን ከ180 በላይ ዓለም አቀፍ አምራቾችና ኤክስፖርተሮች ምርቶቻቸውን በኤግዚቢሽኑ አቅርበው አስተዋውቀዋል፡፡
ኤግዚቢሽኑን ያዘጋጁት ኦሪጅን አፍሪካ፤ ከኢትዮጵያ ጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩትና ከኢትዮጵያ ጨርቃጨርቅ አልባሳት አምራቾች ማኅበር ጋር በመተባበር ሲሆን አላማውም የአፍሪካን የጥጥ ምርት በማቅረብ ዓለም አቀፍ ኤክስፖርተሮች ጥራቱን አይተው እንዲገዙ፣ የገበያ ትስስር እንዲፈጥሩ፣ አፍሪካውያኑ ዓለም አቀፍ አምራቾች ይዘዋቸው የመጡትን ዘመናዊ መሳሪያዎች በማየት፣ ዓለም በዘርፉየደረሰበትን ደረጃ መገንዘብ ያስችላቸዋል፡፡ በኦሪጅን አፍሪካ 2015 ኤግዚቢሽን የተሳተፉት አገሮች ከአፍሪካ ኢትዮጵያን ጨምሮ 12፣ ከኤስያ 7 እንዲሁም ከአውሮፓ 7 ሲሆኑ ከአፍሪካ ኬንያ፣ ታንዛኒያ፣ ዩጋንዳ፣ ሩዋንዳ፣ ዛምቢያ፣ ማዳጋስካር፣ ሱዳን፣ ሌሴቶ፣ ግብፅና ደቡብ አፍሪካ፣ ከኤስያ፣ ጃፓን፣ ቻይና፣ ሕንድ፣ ሲንጋፖር፣ ስሪላንካ፣ ታይላንድ፣ የተባበሩት ዐረብ ኢመሬትስ፣ እንዲሁም ከአውሮፓ እስራኤል፣ ቱርክ፣ እንግሊዝ፣ ጀርመን፣ ኢጣሊያ፣ ስዊዘርላንድና አሜሪካ ተሳትፈዋል፡፡ ዓለም አቀፍ አምራቾችና ኤክስፖርተሮቹ በኤግዚቢሽኑ የተሳተፉት ምርቶቻቸውንና መሳሪያዎቻቸውን በማሳየት አብራቸው የሚሰራ ሸሪክ ወይም ወኪል ፍለጋ ነው፡፡ አፍሪካውያኑ ደግም የምርቶቻቸውን ጥራት በማሳየት የሚገዛ ወይም በስምምነት ተቀብሎ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያከፋፍል ደንበኛ ለማግኘት ነው፡፡ ከኤግዚቢሽኑ ጎን
ለጎን ሴሚናሮችም ተካሂዷል፡፡ በመጀመሪያው ዕለት “ኤክስፓንዲንግ ፋውንዴሽን ፎር ኮተን ፕሮዳክሽን ኢን አፍሪካ” በሚል ርዕስ በአክሱም አዳራሽ ፅሑፍ ቀርቦ ውይይት ተካሂዶበታል፡፡ በላሊበላ አዳራሽ ደግሞ “ኦፖርቹኒቲስ ኤንድ ቻሌንጅስ ቱ አጉዋ ኤክስቴንሽን - ዘ ኔክስት ቴን ይርስ በሚል ርዕስ ጽሑፍ ቀርቧል፡፡ ሐሙስ ዕለት ጧት “ኢመርጂንግ ማርኬት ኢንቨስትመንት ኦፖርቹኒቲስ ኢን አፍሪካ፤ ሪኳየርመንትስ ኦፍ ኢሮፕያን ካምፓኒስ ሶርሲንግ ፍሮም አፍሪክ ማኑፋክቸረርስ”፣ … በሚልና በሌሎች በርካታ ርዕሶች ላይ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበዋል፡፡

Read 1915 times