Administrator

Administrator

   በጋሻው መርሻ የተዘጋጀው በዕውቁ የቀዶ ጥገና ሃኪምና ፖለቲከኛ ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ህይወት ላይ የሚያጠነጥነው “አንፀባራቂው ኮከብ፣ ፕ/ር አስራት ወልደየስ” የተሰኘ መፅሀፍ ሰሞኑን ለንባብ በቃ፡፡ ፀሐፊው ለመፅሀፉ የሚውሉ ግብአቶችን ለማሰባሰብ ሶስት ዓመት፣ መረጃዎቹን አጠናቅሮ ወደፅሁፍ ለመቀየር አንድ ዓመት ከሁለት ወራት እንደፈጀበት ለአዲስ አድማስ ገልጿል፡፡ ፕ/ሩ ከልጅነት ህይወታቸው ጀምሮ ስለትምህርታቸው፣ ስራቸው፣ በእስር ላይ በነበሩበት ጊዜ ስላደረጓቸው… ክርክሮች እስከ ዕድሜያቸው ፍፃሜ ድረስ ያለውን ህይወት በመፅሀፉ ለመዳሰስ ሞክሯል፡፡ ፀሐፊው ስለፕሮፌሰሩ ሙሉ ምስል ለማግኘት  ወዳጆቻቸውን፣ የስራ ባልደረቦችን ቤተሰባቸውን ያነጋገረ ሲሆን በተለያዩ ጊዜያት  የሰጧቸውን ቃለ ምልልሶች፤ የውጭና የአገር ውስጥ ሚዲያዎች ስለእሳቸው ያወጧቸውን ዘገባዎች መጠቀሙን ጠቁሟል፡፡ በ260 ገፆች የተቀነበበው መፅሀፉ፤ በ81 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡

     በየዓመቱ የሚካሄደውና ዘንድሮ ለአራተኛ ጊዜ “New Trends in Art Education in Ethiopia” በሚል ርዕስ የተዘጋጀው የኪነ ጥበብ ጉባኤ ባለፈው ረቡዕና ሀሙስ ተካሄደ፡፡ ጉባኤው በዋናነት በኪነ ጥበቡ ላይ የሚታዩ ችግሮችን፣ የፖሊሲ ክፍተቶችንና መሰል ጉዳዮችን በጥናት አስደግፎ መፍትሄ ማፈላለግ ላይ እንደሚያተኩር የጉባኤው አዘጋጅ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴአትር ጥበባት ት/ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ እሸቱ ተናግረዋል፡፡ ለጉባኤው ጥናቶች እንዲቀርቡ ት/ ቤቱ ከሁለት ወራት በፊት ባደረገው ጥሪ በርካታ ጥናቶች መግባታቸውን ሃላፊው ጠቁመው ከነዚህ ውስጥ ውሃ የሚያነሱና ጥልቀት ያላቸው 15 ያህል ጥናቶች ተመርጠው መቅረባቸውን ተናግረዋል፡፡ ከጥናቶቹ መካከል በረዳት ፕሮፌሰር በቀለ መኮንን የቀረበው “የሥነ ጥበብ ሁለንተናዊ ጉዞ
ከየወቅቱ ጥያቄዎች አንፃር”፣ በዓለም ፀሐይ ለማ የቀረበው “የከፍተኛ ትምህርት ተቋም የጥበብ ትምህርቶች ማስተማሪያ ዘዴ (ፔዳ ጎጂ) በቴአትር ትምህርቶች ላይ ያለው ሚና” እና በምስጋናው ዓለሙ የቀረበው “በኢትዮጵያ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ቴአትር የማስተማር ፈተናዎች” የሚሉት ይገኙበታል፡፡ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ፣ ተ/ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሰሰ አርቲስት ፍቃዱ ከበደ ወግና ፅሁፍ በማቅረብ ተሳትፈዋል፡፡፡ በአምስት ኪሎ ቴአትር ጥበባት ት/ቤት አዳራሽ በተካሄደው በዚህ ጉባኤ ላይ በኪነ-ጥበቡ ላይ ያሉትን ፈተናዎች ለመቅረፍና የትምህርት ፖሊሲው ለዘርፉ ሊሰጠው በሚገባው ትኩረት ላይ ውይይቶች እንደተካሄዱም ታውቋል፡፡

    በዶ/ር ሱባህ ኤ የሱፍ በእንግሊዝኛ የተሰናዳው “Sharing Costss Nothing” ሰሞኑን ለገበያ የዋለ ሲሆን በተለያዩ የጤና ጉዳዮች ላይ እንደሚያጠነጥን ታውቋል፡፡ መፅሀፉ በዋናነት ህብረተሰቡ በተደጋጋሚ  የሚያያቸው ነገር ግን ትኩረት ሰጥቶ ወደ ህክምና የማይመጣባቸው እንደ ስቅታ፣ ነስር፣ የመንገድ ጉዞ ህመም፣ የከፍታ በሽታ (Mountain Sikness)፣ ሀንግ ኦቨር፣ እና በጎጂ የጤና ልማዶች ላይ አተኩሮ የተዘጋጀ ነው፡፡ መፅሀፉ ለአገር ውስጥ በ45 ብር ፣ ለውጭ አገራት በ10 ዶላር ለገበያ ቀርቧል፡፡

    የገጣሚ መብራቱ መሀመድ “ሽሽት” የተሰኘ የግጥም መድበል ዛሬ ከ9፡30 ጀምሮ በሀገር ፍቅር ቴአትር ይመረቃል፡፡ በመፅሀፉ ውስጥ የተካተቱት ግጥሞች በዋናነነት ሰው ከሀገሩ፣ ከህሊናው፣ ከፖለቲካ፣ ከዓለም፣ ከፍቅር፣ ከእውነት፣ ከጥበብና ከፈጣሪው ይሸሻል ወይ?
ቢሸሽስ የት ይደርሳል፣ ማንስ ነው መጠጊያው? በሚሉት ጉዳዮች ላይ ያጠነጥናሉ ተብሏል። በምርቃት ሥነ ስርዓቱ ላይ ወጣትና አንጋፋ ገጣሚያን ስራዎቻቸውን የሚያቀርቡ ሲሆን ከመፅሀፉ የተመረጡ ግጥሞች ለታዳሚው ይቀርባሉ ተብሏል፡፡ በ83 ገፆች የተቀነበበው መፅሀፉ፤ በ30 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡

የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ብሔራዊ ማህበርና መስከረም ፕሮሞሽን በመተባበር ያዘጋጁት “አገር አቀፍ ተጓዥ የንግድ ትርኢትና ባዛር” ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ተከፈተ፡፡ “አካል ጉዳተኞችን ማሳተፍ የህዳሴው አካል ነው” በሚል መርህ የመጀመሪያውን የንግድ ትርኢትና ባዛር ሜክሲኮ አደባባይ የከፈተው ማህበሩ፤ በተለያዩ የክልል ከተሞች ለ1 ዓመት እንደሚቀጥል አስታውቋል፡፡
ከተቋቋመ 23 ዓመታትን ያስቆጠረውና በአገር አቀፍ ደረጃ 16ሺህ አባላት ያሉት ማህበሩ፤ የአካል ጉዳተኞችን መብት ለማስከበርና በሁሉም ዘርፍ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሶ፤ አካል ጉዳተኞች አካል ጉዳተኝነታቸው ሳይገድባቸው የሚያመርቷቸውን ምርቶች ከገዢ ጋር ለማገናኘትና ለማበረታታት ባዛሩ መዘጋጀቱን የማህበሩ ሃላፊዎች ባለፈው ረቡዕ በመክፈቻ ስነ-ስርዓቱ ላይ ተናግረዋል፡፡
በንግድ ትርኢትና ባዛሩ ላይ አካል ጉዳተኖች ያመረቷቸው ቆዳና የቆዳ ውጤቶች፣ የእጅ ስራዎች፣ ቦርሳዎች፣ ቀበቶዎች፣ የሶፋ ጨርቆች፣ የህትመትና የማስታወቂያ ስራዎችና ሌሎችም እቃዎች ለእይታና ለሽያጭ እንደሚቀርቡ ተገልጿል፡፡

በምግብ ማብሰል ሙያ አለማቀፍ እውቅናን ያተረፈው ትውልደ ኢትዮጵያዊው ሼፍ ማርከስ ሳሙኤልሰን፤“ፌስቱፌስ አፍሪካ; የተባለው የፓን-አፍሪካን ሚዲያ ተቋም ለሚያዘጋጀው አመታዊው የ“ፌስ ሊስት” ሽልማት በ“ግሎባል አምባሳደር አዋርድ” ዘርፍ ለሽልማት መመረጡን ተቋሙ ባወጣው መግለጫ አስታወቀ፡፡
ተቋሙ በተሰማሩበት የሙያ መስክ የላቀ ተግባር ለፈጸሙ፣ ለወጣቱ ትውልድ አዲስ መንገድን ለከፈቱና የፓን-አፍሪካኒዝምን በጎ ገጽታ  በተመለከተ በሚደረጉ ውይይቶች ተጽዕኖ ለፈጠሩ ጀግኖች በየአመቱ የሚሰጠው የ“ፌስ ሊስት” ሽልማት ዘንድሮም ለ5ኛ ጊዜ በመጪው ሃምሌ ወር መጀመሪያ ላይ ኒውዮርክ ሲቲ ውስጥ በሚካሄድ ስነስርዓት ለሼፍ ማርከስ ሳሙኤልሰንና ለሌሎች አራት ታዋቂ ግለሰቦች ይበረከታል ተብሏል፡፡
በኢትዮጵያ ተወልዶ በስዊድን ያደገውና በአሁኑ ሰዓት ነዋሪነቱ በኒውዮርክ ሲቲ የሆነው ሼፍ ሳሙኤልሰን፤በሙያው አለማቀፍ ዝናን እንዳተረፈ የገለጸው ተቋሙ፣ሬድ ሮስተር የተባለ የራሱን ሬስቶራንት ከፍቶ ትርፋማ ቢዝነስ እያከናወነ እንደሚገኝና በኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ለሁለት ጊዚያት ያህል የ3 ኮከብ ደረጃ የተሰጠው በእድሜው ትንሹ ሼፍ መሆኑን ጠቁሟል፡፡
በዋይት ሃውስ ለኦባማ በኣለ ሲመት በተዘጋጀ የክብር የእራት ስነስርዓት ላይ በተጋባዥነት ምግብ በማብሰል የሚታወቀው ሼፍ ሳሙኤልሰን፣ ለጥቁር አፍሪካውያን የስኬት ተምሳሌት መሆኑንና በሙያው የተለያዩ ታላላቅ ሽልማቶችን ማግኘቱንም መግለጫው አስታውቋል፡፡
ለ2016 የ“ፌስ ሊስት” ሽልማት የተመረጡት ሌሎቹ ዝነኞች፣ የግራሚ ተሸላሚው ድምጻዊ ዋይክሌፍ ዣን፣ ዋይቴከር ግሩፕ የተባለው ኩባንያ ፕሬዚዳንት ሮዛ ዋይቴከር፣ የታዋቂው ኢሰንስ መጽሄት ዋና አዘጋጅ የሆነቺው ቫኔሳ ዲ ሊካ እና የኩራሞ ካፒታል ኩባንያ መስራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዋሌ አዲኦሱን መሆናቸውንም ተቋሙ አስታውቋል፡፡


   የኡጋንዳው ፕሬዚዳንት ዮሪ ሙሴቬኒ በመፈንቅለ መንግስት ስልጣኔን ለመቀማት ሲያሴሩ ደርሼባቸዋለሁ ያሏቸውን 30 ያህል የአገሪቱ ከፍተኛ የጦር መሪዎችና ባለስልጣናት ማሳሰራቸውን ተከትሎ በአገሪቱ ውጥረት መንገሱ ተዘገበ፡፡
ከአገሪቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር በመተባበር በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት ለመጣል አሲረዋል የተባሉት የጦር መሪዎችና ባለስልጣናቱ፣ ባለፈው ሳምንት መታሰራቸውን ያስታወሰው አሶሼትድ ፕሬስ፤ ይህን ተከትሎም ድርጊቱን የተቃወሙ ታጣቂዎች በመንግስት ፖሊሶች ላይ ተኩስ መክፈታቸውንና ውጥረት መንገሱን ገልጧል፡፡
የአገሪቱ ፖሊስ ከመፈንቅለ መንግስት ሴራው ጋር ንክኪ አላቸው ያላቸውን በርካታ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትንና ደጋፊዎችን ማሰር መቀጠሉን የጠቀሰው ዘገባው፤ 12 ያህል የተቃዋሚ ፓርቲ ደጋፊ ታጣቂዎች፣ ኡጋንዳ ፒዩፕልስ ኮንግረስ የተባለው ፓርቲ አባል የሆኑትንና በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉትን ዳን ኦላ ኦዲያ የተባሉ ግለሰብ ለማስለቀቅ፣ባለፈው እሁድ በፖሊስ ላይ ተኩስ በመክፈት ብጥብጥ መፍጠራቸውን ጠቁሟል፡፡  
ባለፈው የካቲት ወር በተካሄደው የአገሪቱ ምርጫ የሙሴቬኒ ተፎካካሪ ሆነው የቀረቡትና የምርጫውን ውጤት በመቃወም ብጥብጥ አስነስተዋል በሚል ወደ ወህኒ የተወረወሩት ፎረም ፎር ቼንጅ የተባለው ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ዶ/ር ኪዛ ቢሲጂ፤ባለፈው ረቡዕ በአገር ክህደት ተከሰው በናካዋ ከተማ ፍርድ ቤት በቀረቡበት ወቅት፣ በአካባቢው ከፍተኛ ውጥረት ነግሶ እንደነበር ዘገባው አመልክቷል፡፡
መፈንቅለ መንግስቱን የጠነሰሱት ኪዛ ቢሲጄ የተባሉ የአንድ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር እንደሆኑ መነገሩን የጠቆመው ዘገባው፣ ግለሰቡ በአገር ክህደት ከተከሰሱት ቢሲጂ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት እንዳላቸው ገልጾ፣ ቢሲጂ በመንፈንቅለ መንግስቱ ሴራ እጃቸው ሊኖርበት እንደሚችል መጠርጠሩን አስታውቋል፡፡
ቪኦኤ በበኩሉ፤ የአገሪቱ መንግስት ባለስልጣናቱን በመፈንቅለ መንግስት ሴራ ጠርጥሮ ማሰሩ በቀጣይም ከፍተኛ ብጥብጥ ሊፈጥርና አገሪቱን ወደ ከፋ ቀውስ ሊከታት እንደሚችል እየተነገረ እንደሚገኝ ዘግቧል፡፡

  ታዋቂው ማይክሮሶፍት ኩባንያ፣ሊንክዲን የተባለውን ዝነኛ የማህበራዊ ድረገጽ በ26.2 ቢሊዮን ዶላር ለመግዛት ስምምነት ላይ መድረሱን እንዳስታወቀ ሮይተርስ ዘገበ፡፡
ኩባንያው በታሪኩ ከፍተኛውን ግዢ የሚፈጽምበት ነው በተባለው በዚህ ስምምነት ወደ ማህበራዊ ድረገጽ አለም በይፋ ይቀላቀላል ያለው ዘገባው፤ ማይክሮሶስፍት ሊንክዲንን መግዛቱ ከፌስቡክና ከጎግል ጋር ለሚያደርገው የቴክኖሎጂ ፉክክር ትልቅ አቅም ይፈጥርለታል መባሉንም ገልጧል፡፡
በቢዝነስ ላይ በተሰማሩ ተጠቃሚዎች ዘንድ የሚዘወተረው ሊንክዲን የማህበራዊ ድረገጽ፤ከ400 ሚሊዮን በላይ ተጠቃሚዎች እንዳሉት የጠቆመው ዘገባው፣ ማይክሮሶፍት ግዢውን እስከ መጪው ጥር ወር ድረስ አጠናቅቆ ሊንከዲንን በእጁ ያስገባል ተብሎ እንደሚጠበቅም አስታውቋል፡፡
የሊንክዲን ተጠቃሚዎች ቁጥር ባለፉት አመታት በአማካይ በ19 በመቶ እድገት በማሳየት፣ 433 ሚሊዮን ያህል መድረሱን የጠቆመው ሮይተርስ፤ በትርፋማነቱም እንደማይታማና በማይክሮሶፍት ባለቤትነት ስር መተዳደሩ የበለጠ ውጤታማ ያደርገዋል ተብሎ እንደሚታመን አስረድቷል፡፡
ማይክሮሶፍት ከአምስት አመታት በፊት ስካይፒን በ8.5 ቢሊዮን ዶላር፣ የኖኪያ የሞባይል ቀፎ አምራችነትንም በ7.2 ቢሊዮን ዶላር መግዛቱን ያስታወሰው ዘገባው፤ሁለቱ ግዢዎች በታሪኩ ከፍተኛ ወጪ ያወጣባቸው ተብለው ተመዝግበው እንደነበርም ገልጧል፡፡

- እስካሁን 6 ክብረ ወሰኖችን አስመዝግቧል
- ከወራት በፊት የአመቱ ምርጥ አትሌት ተብሏል

በአሜሪካ የ3ኛ ክፍል ተማሪ የሆነውና የ8 አመት ዕድሜ ያለው ትውልደ ኢትዮጵያዊው ታዳጊ ታም ጋቬናስ፤ ባለፈው ሳምንት በኒውዮርክ በተካሄደው የኬንዝ ዶላን መታሰቢያ የ5 ሺህ ሜትር የሩጫ ውድድር አዲስ የአለም ክብረወሰን ማስመዝገቡን ያሁ ኒውስ ዘግቧል፡፡
ታዳጊው የ5ሺህ ሜትር ሩጫውን በ18 ደቂቃ በማጠናቀቅ፣በዚህ ዕድሜ ርቀቱን ፈጥኖ የጨረሰ የዓለማችን ባለተስፋ ታዳጊ አትሌት ተብሏል ያለው ዘገባው፤ታዳጊው ከሶስት አመታት በፊትም በዚያው በአሜሪካ በተካሄደ የ5 አመት ዕድሜ ያላቸው ታዳጊዎች የሩጫ ውድድር ላይ በ800 ሜትርና በ1ሺህ 500 ሜትር አዲስ የዓለም ክብረወሰን ማስመዝገቡን አስታውሶ፣ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በርካታ ሽልማቶችን ማግኘቱንና መነጋገሪያ መሆኑን አስታውቋል፡፡  
ባለፈው አመት በ800 ሜትር፣ በ1ሺህ 500 ሜትርና በ400 ሜትር ውድድሮች አዳዲስ ብሄራዊ ክብረ ወሰኖችን ያስመዘገበው ታዳጊው፤ከወራት በፊትም በአሜሪካ በተካሄደው ዩኤስኤቲኤፍ አመታዊ የታዳጊ አትሌቶች ሽልማት፣የአመቱ ምርጥ አትሌት ተብሎ መሸለሙም ታውቋል፡፡  
ታም ጋቬናስ በኢትዮጵያ እንደተወለደና ዕድሜው ሶስት አመት ሳይሞላው፣ ሜሪ ሊዛ ጋቬናስ በተባለቺው አሜሪካዊት አማካይነት በጉዲፈቻ ወደ አሜሪካ መወሰዱን ያስታወሰው ያሁ ኒውስ፣ አሳዳጊው የተፈጥሮ ክህሎቱን በማጤን ለስኬት እንዲታትር ታበረታታው እንደነበር ጠቁሟል፡፡

     በባንግላዴሽ ባለፈው ሳምንት የታጠቁ ሃይሎች በፈጸሙት ተከታታይነት ያለው ጥቃት፣ በበርካታ ዜጎች ላይ አሰቃቂ ግድያዎች መፈጸማቸውን ተከትሎ የጽንፈኛ ቡድኖችን እንቅስቃሴ ለመግታት የተጠናከረ እርምጃ መውሰድ የጀመረው የአገሪቱ መንግስት፤ ከ11 ሺህ በላይ ተጠርጣሪዎችን ማሰሩን ሲኤንኤን ዘገበ፡፡
የአገሪቱ መንግስት ሰሞኑን በርካታ ዜጎችን በመግደል ከፍተኛ ጥፋት ካደረሱ ጽንፈኛ ቡድኖች ጋር ግንኙነት አላቸው ያላቸውን 150 ታጣቂዎችና በአገሪቱ በተከሰቱ ብጥብጦች በተለያዩ ወንጀሎች ተሳትፈዋል በሚል የጠረጠራቸውን ከ11 ሺህ በላይ ግለሰቦች ማሰሩን ዘገባው ገልጧል፡፡
የአገሪቱ ፖሊስ አብዛኞቹ በቁጥጥር ስር የዋሉ ግለሰቦች ጃማቱል ሙጅሃዲን የተባለው አክራሪ ቡድን አባላትና ለጥፋት ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ናቸው ቢልም፣ ባንግላዴሽ ናሽናሊስት ፓርቲ የተባለው የአገሪቱ ተቃዋሚ ፓርቲ ግን፣ የመንግስት እስር በአባላቶቼ ላይ ያነጣጠረ ነው፤ 2 ሺህ 100 አባላቶቼና ደጋፊዎቼ ታስረውብኛል ማለቱ ተዘግቧል፡፡
በባንግላዴሽ ባለፈው አንድ አመት ብቻ 35 ያህል ተመሳሳይ የሽብር ጥቃቶችና ግድያዎች መፈጸማቸውን ያስታወሰው ዘገባው፤ በአገሪቱ በህቡዕ የሚንቀሳቀስ አንድ አክራሪ ጽንፈኛ ቡድንም ከእነዚህ ጥቃቶች መካከል ሃያ ሶስቱን ለመፈጸሙ ሃላፊነት መውሰዱን ገልጧል፡፡