ኢህአዴግ - አንድነት - ወህኒ ቤት
* ከ20 በላይ ሠላማዊ ሠልፍ ብመራም አንዲት ጠጠር አልተወረወረችም
* ኢህአዴጎች ለልጅ ልጆቻቸው የማይቆጭ ነገር ትተው ቢያልፉ መልካም ነው
* ከፖለቲካ ጋር የተዋወቅሁትና የተጠመቅሁት በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ነው
የአንድነት ፓርቲ አመራር የነበረው ወጣቱ ፖለቲከኛ ሃብታሙ አያሌው፤በሽብር ወንጀል ተጠርጥሮ አንድ አመት ከ8 ወር ያህል በእስር ላይ የቆየ ሲሆን ባለፈው ማክሰኞ በዳኛ ትዕዛዝ ከማረሚያ ቤት ሊለቀቅ ችሏል፡፡ ከፖለቲካ ጋር የተዋወቅሁት በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ነው የሚለው ሃብታሙ፤የመጀመሪያ ፓርቲውም ኢህአዴግ መሆኑን ይናገራል፡፡ ከኢህአዴግ ጋር በምን ተቀያየመ? ተቃዋሚዎች እንዴት ተቀበሉት? ለእስር የዳረገው ምንድን ነው በአንድነት እጣፈንታ ምን ተሰማው? ወጣቱ ፖለቲከኛ ሃብታሙ አያሌው፤ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ከእስር በተፈታ ማግስት በፖለቲካ ህይወቱ፣እምነቱና ፈተናዎቹ ዙሪያ አውግተዋል፡፡
ከአንድነት ፓርቲ ብንጀምርስ? እንዴት ነበር ፓርቲውን የተቀላቀልከው?
በኢትዮጵያ ውስጥ በወቅቱ ከነበሩ ፓርቲዎች የተሻለ ነው ብዬ ነበር የተቀላቀልኩት፡፡ በወቅቱ በሠላማዊ ትግሉ ላይ የተሻለ ነገር ማምጣት ይችላል የሚል እምነት ነበረኝ፡፡ አንደኛ የሊበራል አስተሳሰብ ይዞ ወደ ግራ ሆነ ወደ ቀኝ ጠርዙ ሳይሄድ መካከለኛውን የያዘ ነበር፡፡ ይሄ አስተሳሰብ ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚጠየቁ የፖለቲካ መብቶችን፣ የቡድን ጥያቄዎችን ይመልሣል፡፡ ማዕከሉን ሊብራሊዝም አድርጓል፡፡ መካከለኛ ፓርቲ ሆኖ መሄዱ ለምርጫዬ አንዱ መሠረት ነበር፡፡ ሌላው በኢትዮጵያ ሉአላዊነትና አንድነት ላይ ያለው አቋም ጥሩ ነበር፡፡ በተጨማሪም በፓርቲው ውስጥ ተስፋ የሚጣልባቸው ወጣት አመራሮች ነበሩ፡፡ ከነሱ ሥር በመሆን በኢትዮጵያ ውስጥ ዘመናዊ የሆነ የዲሞክራሲ ሥርዓት ለመገንባት እድል ይኖራል፡፡ ስለዚህ ከነዚህ ሰዎች ጋር መታገል አለብኝ ብዬ፣ ጥያቄው ሲቀርብልኝ ቀጥታ በብሔራዊ ም/ቤት ደረጃ ነበር አባል የሆንኩት፡፡
ከዚያ በፊት ግን በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ርዕዮተ ዓለም የሚመራው ኢህአዴግ አባል ነበርክ፡፡ ከአብዮታዊ ዲሞክራሲ ወደ ሊበራል ያደረግኸው ሽግግር አላስቸገረህም?
የኢህአዴግን አብዮታዊ ዲሞክራሲ ከማወቄ በፊት የፖለቲካ እውቀቱም እምብዛም አልነበረኝም፡፡ ከፖለቲካ ጋር የተዋወቅሁበት ጊዜ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በ1997 በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የለውጥ እንቅስቃሴ ከሚከተሉና ከሚፈልጉ ወጣቶች አንዱ ነበርኩ፡፡ በእርግጥ ከ3 ዓመታት በላይ በውጭ ሀገር በትምህርትም በስራም ቆይቼ የተመለስኩት በ1997 አጋማሽ ላይ ነበር፡፡ ስመጣ የለውጡን እንቅስቃሴ በሚገባ ተከታትያለሁ፡፡ በወቅቱ የበኩሌን አስተዋጽኦ ለማድረግም ጥረት አድርጌያለሁ፡፡ ከምርጫው በኋላ ቅንጅት ላይ የተፈጠረው ሁኔታ ወደ ሌላ ምዕራፍ አሸጋገረኝ፡፡ እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የራሴን ስራ እየሠራሁ ኑሮዬን ቀጠልኩኝ፡፡
በ1999 ዓ.ም መጨረሻ ላይ የአዲስ አበባ ወጣቶች ፎረም ሲመሠረት፣ በወቅቱ የሚያውቁኝ አመራሮች ጥሪ አድርገውልኝ፣ ምስረታው ላይ እንድገኝ አደረጉኝ፡፡ የፎረሙ ምስረታ በጣም ሳቢ ነበር፡፡ በኋላ የሚከተለው አካሄድ የተሳሳተ መሆኑን አውቀን፣ መታገል እስከጀመርንበት ድረስ መነሻው ላይ ባይቀለበስ ጥሩ ነበር፡፡ ከመንግስት ጋር መቀራረብ፣ መመካከር፣ በሀገር ጉዳይ ላይ ወጣቱ ተሣታፊ እንዲሆን ማድረግ ነበር ዓላማው፡፡
የመንግስት አመራሮች ተጠያቂ መሆን በሚገባቸው መጠን ተጠያቂ እንዲሆኑ የሚከታተል፣ የሚቆጣጠር የህብረተሰቡ በተለይም የወጣቱ ተወካይ እንዲሆን ነበር የታሰበው፡፡ ጥቅሙንም ተሣትፎውንም ማስከበር የሚችል፣ ከማንኛውም የፖለቲካ ወገንተኝነት የፀዳ በሚል ነበር የተመሠረተው፡፡
እየቆየን ስንሄድ በፎረሙ አመራር ላይ ለነበርን ወጣቶች የፓርቲ አባልነት ጥያቄ እየቀረበልን መጣ፡፡ ፖለቲካን ለመካን ደግሞ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ምንድን ነው እየተባለ እንድንሰለጥን ተደረግን፡፡ ያኔ የኢህአዴግን ፖሊሲዎች በዝርዝር ለማንበብ ሞከርኩኝ፡፡ ከእኔ ውስጣዊ አቋም ጋር ይሄዳል አይሄድም የሚለውን ስገመግም ቆየሁ፡፡
የሶሻሊዝሙ ጐራ ምንድን ነው? የሊበራሊዝሙስ? አብዮታዊ ዲሞክራሲ ከእነዚህ ጋር ያለውን አንድነትና ልዩነት ሠፊ ጊዜ ወስጄ አጠናሁ፡፡ በ2001 ዓ.ም ኢህአዴግ ከፍተኛ አመራሮችን አላጌ ወስዶ ባሰለጠነ ጊዜ ተሣታፊ በመሆን በአጠቃላይ በድርጅቱ አስተሳሰብ ላይ በቂ ግንዛቤ ያዝኩኝ፡፡
በኢህአዴግ ውስጥ የነበረህ ተሳትፎ ምን ያህል ነበር?
በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ላይ ሠፊ ክርክሮች ሲደረጉ በንቃት ከሚሳተፉት አንዱ ነበርኩ፡፡ በኢህአዴግ ቤት ውስጥ የማይነኩ የሚባሉ እንደ የመሬት ፖሊሲው፣ በቋንቋ ላይ የተመሠረተው ፌደራሊዝም --- የመሳሰሉ ጉዳዮችን አንስቼ እከራከራቸው ነበር፡፡ በተለይ የቋንቋ ፌደራሊዝም እነ ራሺያን ከመበታተን እንዳላዳናቸው በመረዳቴ፣የኢህአዴግ ፌደራሊዝም እንደማይጠቅመን ፊት ለፊት እነግራቸው ነበር፡፡ ሌላው “ዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት” የሚባል ነገር አለ፤ ግለሰቦችን ፈላጭ ቆራጭ የሚያደርግ ነው፡፡ አንድ መሪ የተናገረውን ከመቀበል ውጪ ሌላ ሃሳብ ማራመድ የማይቻልበት አካሄድ ነው፡፡ በኢህአዴግ ቤት ውስጥ አማራጭ ሃሳብ ማቅረብ እንደማይፈቀድና ከነውር እንደሚቆጠር ተረዳሁኝ፡፡ እነዚህንና መሠል ጉዳዮችን በየትኛውም መድረክ ላይ በድፍረት እቃወማቸው ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በነበሩበት ስብሰባ ላይም በግልጽ “ተሳስተሃል” ብዬ አውቃለሁ፡፡ አቶ መለስ “ይሄን አስተያየት እንቀበለዋለን” ያሉበት ጊዜ አለ፡፡ “ለምን እንዲህ ያለ ጥያቄ ይጠይቀኛል” ብለው የተቃወሙበት ጊዜም አለ፡፡
በኢህአዴግ ውስጥ ምን ያህል ቆየህ?
ከ2001 እስከ 2002 አጋማሽ ድረስ በኢህአዴግ ውስጥ ቆይቻለሁ፡፡ በወቅቱ ፖሊሲውን በዝርዝር ለመረዳት ችያለሁ፡፡ እነዚህን በሂደት የተረዳኋቸውንና ያላመንኩባቸውን ጉዳዮች ይዤ ዲሞክራሲያዊ ትግል ማድረግ ነበረብኝ፡፡ ኢህአዴግ ጭፍንና አምባገነናዊ አካሄድ ነው የሚከተለው፡፡ በኢህአዴግም ሆነ በተቃዋሚዎች ጐራ የተሠለፉ ጫፍ የረገጡ የ60ዎቹ ፖለቲካ አራማጆች አሉ፡፡ ይሄን ጭፍንነት ይዘው ትግሉን እየጐተቱ ያሉ ሰዎች ስፍራውን ለአዲሱ ትውልድ እንዲለቁ መሠራት አለበት የሚል ጽኑ እምነት ነበረኝ፡፡
አንድነት ውስጥ ዘመናዊ የሚባሉ፤ ለዚህች ሀገር የሚጠቅሙ ወጣቶች ወደፊት እንዲመጡ ከገባሁበት ጊዜ ጀምሮ ታግያለሁ፡፡ አማራጮች እንዲፈልቁ፣ ፓርቲው ከህዝብ ጋር የበለጠ እንዲተዋወቅ ጥረት አደርግ ነበር፡፡ ለኔ ትልቅ ስልጣን ከተባለ ከተቃዋሚ ፓርቲ ይልቅ ኢህአዴግ ቤት ውስጥ የነበረኝ ነው፡፡ ኢህአዴግ ውስጥ ባለስልጣን ሆነህ የፈለከውን በኩርኩም እየመታህ ትሄዳለህ፡፡ አንድነት ጋ ባለስልጣን ስትሆን ግን እንደዚህ እስር ቤት ነው የምትወረወረው፡፡ ይሄን ጠንቅቄ አውቅ ነበር፡፡
እኔ ውስጣቸው አባል ሆኜ ብዙ ነገር ለማስተካከል፣ በሃሳብ ለመሞገት ጥረት አድርጌያለሁ፡፡ ፈጽሞ ሃሳብ የሚስተናገድበት ሁኔታ ኢህአዴግ ቤት ውስጥ የለም፡፡ የምችለውን ሁሉ ከጣርኩ በኋላ በተአምር የሚቀየር ነገር ባለመኖሩና በሮች በሙሉ በመዘጋታቸው ከፓርቲው ወጥቼ የጥሞና ጊዜ ወሰድኩ፡፡ ከዚያ ደግሞ የባለራዕይ ወጣቶች ማህበርን መሠረትን፡፡ በወቅቱ የኢትዮጵያዊነት ስሜት እየተሸረሸረ መሆኑ ያሳስበኝ ስለነበር ማህበሩ በዚህ ረገድ አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ነበር የመሠረትነው፡፡ የፌደራሊዝም ስርአት ለኢትዮጵያ እንደሚያስፈልጋት አምናለሁ፤ ነገር ግን አሁን ቋንቋን፣ ዘርን --- መሠረት ያደረገው ስርአት ሃገሪቱ ወደማትወጣው ችግር ውስጥ የምትገባበት እንዳይሆን እፈልጋለሁ፡፡ በኢህአዴግ አካሄድ ሀገሪቱ አደጋ ላይ ትወድቃለች የሚል እምነት ነበረኝ፡፡ ደግሞም የያዝኩት እምነት ትክክል እንደነበር አሁን እያየነው ያለው ውጤት ምስክር ነው፡፡ የልዩነቱ ድንበር መድመቅ አልነበረበትም፡፡
በ1983 ኢህአዴግ ሲገባ ይዞት የመጣው አስተሳሰብ ጊዜው በሚጠይቀው ልክ የነበረ ነው፡፡ በወቅቱ በብሔር ጥያቄ ነፍጥ ያነገቡ ከ18 ድርጅቶች በላይ ነበሩ፡፡ እነዚህን “አንዲት ኢትዮጵያ” ቢሏቸው ኖሮ አስቸጋሪ ነበር፡፡ እንደገና ጦርነቱ ይቀጥላል፡፡ ነገር ግን በየጊዜው የማህበረሰቡን እድገትና ስነልቦናዊ አንድነት እየተመለከተ፤ የነበሩትን ስጋቶችና አለመተማመኖችን እየሰበረ፣ ብሔራዊ አስተሳሰብን መገንባት ነበረበት፡፡ ቆይተው ተቃውሞው ሲበረታ ነው “የሰንደቅ አላማ ቀን” የመሳሰሉትን የጀመሩት፡፡ ኢህአዴጐች፤ “ልዩነታችን አንድነታችን፣ አንድነታችን ውበታችን” የሚሉት ነገር አላቸው፤ ግን ከልዩነታችን አንድነታችን ይበልጣል ብለን ብንይዘው፣ ሰው ውስጥ የአንድነት ሃሳብን ማሳደግ ይቻላል፡፡ በባለራዕይ ወጣቶች ማህበር ውስጥ በዚህ መልኩ ብዙ ጥረት አደረግን፤ግን ኢህአዴግ አንድ የተሰባሰበ አካል ሲያይ ይፈራል፡፡ እናም ማህበሩን እንዳይንቀሳቀስ አደረገው፣ እኛም ስንታሰር ስንፈታ ቆየንና --- በመጨረሻም ማህበሩ ተዳክሞ ተበተነ፡፡ ከዚያ በኋላ የያዝኩት አላማና አስተሳሰብ ለሀገሬ ይጠቅማል፤ ግን እንዴት ልታገል ብዬ ሳስብ አንድነት ፓርቲን አማራጭ አድርጌ መታገል ጀመርኩ፡፡ በዚህች ሀገር ከጦርነት በመለስ ያለው ትግል መኖር አለበት፡፡ አንዱ ሌላውን በሃይል የሚጥልበት አካሄድ መቆም አለበት፡፡ በሃይል የሚመጣ አካል፣ በሃይል ብቻ ነው የሚወድቀው፡፡ “ሰይፍ የሚያነሳ በሠይፍ ይሞታል” ነው የሚለው መጽሐፍ ቅዱስም፡፡ ስለዚህ ሰይፍ ማንሳት ሳያስፈልግ፣ በሠላማዊ ትግል መንግስት መቀየር አለበት የሚል ጽኑ እምነት አለኝ፡፡
የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር ከሆንክ በኋላስ ችግሮች ቀነሱልህ?
በተቃውሞው ጐራና በኢህአዴግ መካከል ያለው ልዩነት በራሱ ለወጣቱ እጅግ በጣም ፈተና ነው፡፡ በሁለቱም ውስጥ ጫፍና ጫፍ የረገጡ ሃይሎች አሉ፡፡ ያንን መስበር እጅግ ከባድ ነው፡፡ እነዚህን አመራሮች የሠለጠነ አስተሳሰብ ባላቸው ሰዎች መቀየር አንዱ አማራጭ ነው፡፡ እኔ ኢህአዴግ ውስጥ ሃሳብ እንደልብ ማንሸራሸር አይቻልም ብዬ ወደዚኛው ስመጣ፣ “ወያኔ” በደንብ አሠልጥኖ ልኮብናል” የሚል አቋም ይዘው አላሠራም ያሉበት ሁኔታ ነበር፡፡ ይሄን ሁሉ ታግለን ፓርቲው እየተጠናከረና ለስርአቱ አደጋ እየሆነ ሲመጣ፣ኢህአዴግ “እነዚህን ከጀርባ ሆኖ የሚገፋ አለ” ብሎ ከፍተኛ ስጋት ውስጥ ገባ፡፡
እኔ ወደ ተቃውሞ ጐራ ከገባሁ በኋላ ከ20 በላይ ሠላማዊ ሠልፍ መርቻለሁ፡፡ አንዲት ጠጠር አልተወረወረችም፡፡ በሆስፒታሎች አካባቢ ስናልፍ በፍፁም ጨዋነትና ፀጥታ ነበር፡፡ ግን በመጨረሻ አሸባሪ ነው የተባልነው፡፡ በተቃውሞው ጐራ ደግሞ “ወያኔ ነው የላከብን” እየተባልኩ በመሃል ላይ በሁለት እሣት እየተጠበስኩ ነው ትግል ሳደርግ የነበረው፡፡ ሌላው በተቃውሞ ጐራ ያለው ችግር አንዳንዱ ዝም ብሎ የጡረታ ጊዜውን የሚያሣልፍበት ነው የሚመስለው፡፡ ምንም ለውጥ አያመጣም ግን ዝም ብሎ እየተቃወመ መኖርን የመረጠ ነው፡፡ ይሄ መለወጥ አለበት፤ አካሄዱ ትክክል አይደለም፡፡ ዘመናዊ ዲሞክራሲያዊ ስርአት እንገንባ ባልን ነው መከራ የምናየው፡፡ እኔም ሆንኩ አብረውኝ የታሠሩ ጓዶቼ ይሄ ነው አመለካከታችን፤ ግን ያልተገባ ዋጋ እንድንከፍል ነው እየተደረግን ያለነው፡፡ ነገ ይህቺን ሀገር ሁሉም ትቷት ይሄዳል፤ ግን ለልጅ ልጆቻቸው የማይቆጭ ነገር ትተው ቢያልፉ መልካም ነው፡፡
ወደ እስር የተወሰድክበት ሁኔታ እንዴት ነበር?
እኔና ጓደኞቼ የተያዝነው ለምርጫ 2007 ዝግጅት በሚደረግበት ወቅት ላይ ነው፡፡ ምንም ጥርጥር የለውም፤ ኢህአዴግ እኛን ደጅ ትቶ ምርጫ ማካሄድ አልፈለገም፡፡ ወደፊትም የሚፈልግ አይመስለኝም፡፡ በወቅቱ ኢህአዴግን በሃሳብ ማሸነፍ እንደሚቻል እኛ በተግባር ማሳየት እንችል እንደነበር ምንም ጥርጥር የለኝም፡፡ ሃሳብ በማንፀባረቅ ብቻ ኢህአዴግን እንበልጠዋለን፡፡ ስለዚህ ከአነሣሣችን ከኢህአዴግ በተሻለ የህዝቡን ቀልብ እንደምንገዛ፣ ሌላ አማራጭ ይዘን እንደምንቀርብ ጥርጥር አልነበረኝም፡፡
በምን አይነት ሁኔታ ነበር በቁጥጥር ስር የዋልከው?
እኔ በወቅቱ ባንክ ቤት ነበርኩኝ፡፡ የፓርቲያችንን ፕሬዚዳንት ጨምሮ 6 አመራሮች ወደ አሜሪካን ሀገር ሄደን፣ በስድስት ስቴቶች ላይ ከዳያስፖራው ጋር ለመወያየት መድረክ ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ ለዚህም የመጨረሻውን የቪዛ ክፍያ ጨርሼ፣ የሁሉንም አመራሮች ፎርም አንድ ላይ ይዤ ለአሜሪካን ኤምባሲ 4 ሰአት ላይ ለማቅረብ ልሄድ ባልኩበት ቅጽበት ነው ከእነ ፓስፖርቱ መጥተው የያዙኝ፡፡ አያያዛቸው በጣም የሚገርም ነበር፡፡ አንድ ተራ ሰው የሚይዙ አይመስሉም፡፡ ኦሣማ ቢላደን ያለ ነበር የሚመስለው፡፡ በወቅቱ የተሰማኝ፤ “ወይኔ ታሰርኩ በቃ” የሚል አይደለም፡፡ እኛ በገዛ ሀገራችን መታሰር ችግር የለውም፤ ስንቱ እየተሰደደ የበረሃ ሲሳይ ሆኖ የለም እንዴ፡፡ ልጄ 1 አመት ከ4 ወሯ ነበር፤ ከሷና ከባለቤቴ ነጥለው ወሰዱኝ፡፡ ቤቴን ፈተሹ፤ ምንም የተገኘ ነገር አልነበረም፡፡ ማዕከላዊ ለ4 ወር ቆየሁ፡፡ እኔ ፊት ለፊት የግንባር ስጋ ሆኜ የምታገል ሰው ነኝ፡፡ ከጀርባ ሆኖ የሚታገል ሰው እኮ አደባባይ አይወጣም፡፡ ሲይዙኝ እንፈጥረዋለን ብለን ያሰብነው የመድብለ ፓርቲ ስርአት ወደ ኋላ መመለሱ አሳዝኖኝ ነበር፡፡ የማታ ማታም ያው እንደሚታወቀው ፓርቲያችን እንዲፈርስ ተደረገ፡፡
በምርጫ ቦርድ ውሣኔ የአንድነት ፓርቲ አመራር ሲለወጥ ምን ተሰማህ?
እኔ በመሠረቱ ከድርጅት (ፓርቲ) ጋር የተለየ ፍቅር የለኝም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የመጠፋፋትና የጥላቻ ፖለቲካ እንዲቆም፣ በተቻለ መጠን ለሌላው አለም ምሣሌ የሚሆን ዲሞክራሲያዊ ስርአት እንዲገነባ ነው ፍላጎቴ፡፡ ይሄን ማምጣት የሚችል ድርጅት ለመገንባት ነበር ስንጥር የነበረው፡፡ ግን አንድነት በዚህ ሁኔታ እንዲበተን ሲደረግ የፖለቲካ ስርአቱ አንዳች መደምደሚያ እየተሠራለት መሆኑ ገባኝ፡፡ አንድነት ስለተበተነና እኔ ስለታሠርኩ የኢትዮጵያ መድብለ ፓርቲ ስርአት ግንባታ አበቃለት ማለት አይደለም፡፡ በሠላማዊ ትግሉና በህዝብ ላይ ተስፋ እንደመቁረጥ አድርጌ ስለምወስደው፣ የበለጠ መስራትና ዋጋ እየከፈልን መቀጠል አለብን የሚል እምነት አለኝ፡፡
ኢህአዴግ እግር ያወጣውን ፓርቲ እግሩን ሲቆርጥ የተቃዋሚ አመራሩ ደግሞ በቀላሉ የሚወድቅ የተልፈሰፈሰ መሆኑ፤ ቁርጠኛ የሆነ ታጋይና አመራር አለመፈጠር የመሳሰሉት ክፍተቶች ነበሩ፡፡ ኢህአዴግ ኩርኩም በሰደደ ቁጥር የምንፈርስ ሆነን ነው የተገኘነው፡፡ የኢህአዴግን ኩርኩም መቋቋም የሚችል ድርጅት ለመገንባት ባለመቻላችን በራሳችን በጣም አዝኛለሁ፡፡ እውነት አብሬያቸው ስታገል የነበረው ከነማን ጋር ነው? የሚለውን ሳስብ ነበር፡፡
የማረሚያ ቤት ቆይታህን በምን ነበር የምታሳልፈው?
መፃህፍት አነብ ነበር፡፡ አብዛኛውን ጊዜዬን ያሳለፍኩት በማንበብ ነው፡፡ ወዳጆቼ የማረሚያ ቤቱን ሳንሱር ያለፉ መፃህፍትን ያስገቡልኝ ነበር፡፡ መፃህፍቶች በአስገራሚ ሁኔታ ሳንሱር ይደረጋሉ፤በማረሚያ ቤቱ፡፡ በሀገሪቷ ታትመው የተሠራጩ መፃህፍት ሁሉ ማረሚያ ቤት ለመግባት ለምን እንደሚከለከሉ አይገባኝም፡፡
ከዚያ ውጪ እንግዲህ ቴሌቪዥን ያለ አማራጭ እንከታተላለን፡፡ የመልካም አስተዳደር ጉዳይ ተነስቶ ጠ/ሚኒስትሩ ጭምር እንዲያ ሲናገሩ የተስፋ ጭላንጭ ታይቶኝ ነበር፤ነገር ግን ወዲያው በማረሚያ ቤቱ የሚፈፀመው ተግባር እንኳን እየተጠናከረ ሄደ፡፡ መጽሐፍቶች ላይ የሚደረገው ክልከላም ተጠናከረ፡፡ ሽብርተኛ ተብለን እንደተከሰስነው ሁሉ፣ልክ እንደ አሸባሪ ከሰው እንድንገለል ተደረግን፡፡ ይሄ ይገርመኛል፡፡ እዚያ ያለው አካል ለለውጥ ዝግጁ እንዳልሆነ ነው የተረዳሁት፡፡ ከማንበብ ውጪ የሚተርፈኝን ጊዜ እዚያ ለሚገኙ ታራሚዎች የህግ ድጋፍ አገልግሎት በነፃ እሰጥ ነበር፡፡ የክስ ማቆሚያ ንግግራቸውን ማዘጋጀት፣ መሪና መስቀለኛ ጥያቄያቸውን ማደራጀት የመሳሰሉ የህግ አገልግሎት በነፃ እሰጥ ነበር፡፡
በማረሚያ ቤት ቆይታህ የሀገሪቱን የፖለቲካ ሁኔታ በEBC ስትከታተል እንደነበር ነግረኸኛል፡፡ ምን ታዘብክ ታዲያ?
አንዱ እንግዲህ የወቅቱ የኢህአዴግ አጀንዳ የሆነው የመልካም አስተዳደር ጉዳይ ነው፡፡ በመልካም አስተዳደር ውስጥ ችግሩን የፈጠረው ሰው ችግሩን አይፈታም፡፡ እኔ እንደዚህ አይነት እምነት አለኝ፡፡ ኢህአዴግ የመልካም አስተዳደር ችግር ፈጥሯል፡፡ መልካም አስተዳደር ግን ማምጣት አልቻለም፡፡ ችግሩን ራሱ መፍታት ይችላል ወይ ስንል? ኢህአዴግ ራሱን መፈተሽ አለበት፡፡ ሙስና አለ ከተባለ ሙሰኞች አይደሉም ችግሩን የሚፈቱት፡፡ ስለዚህ መጀመሪያ ማድረግ ያለበት የችግሩን ፈጣሪዎች ለይቶ ማውጣት ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ነው ስለ መልካም አስተዳደር ማውራት ያለበት፡፡ ጠ/ሚኒስትሩም ተስፋ ቆርጠው፤ “ከዚህ ስትወጡ ወደ የኔት ዎርኮቻችሁ ነው የምትሄዱት” ብለ
ዋል፡፡ እንግዲህ ሁሉንም ወደፊት የምናየው ይሆናል፡፡
ከአሁን በኋላ ምን አሰብክ? በፖለቲከኝነቱ ትቀጥላለህ … ?
እውነቱን ለመናገር ገና አላወቅሁም፡፡ አሁን ምንም ማለት አልችልም፡፡ ዝም ብዬ ተራ የፖለቲካ ታጋይ ሆኜ ነው የምቀጥለው? ወይስ የሚለውን አልወሰንኩም፡፡ ገና ብዙ ማየትና ማገናዘብ አለብኝ፡፡
በመጨረሻ…ምን ትላለህ ?
እናንተ ከእስር መልስ ሃሳቤን ሰው እንዲሠማው ስላደረጋችሁ አመሰግናለሁ፡፡
እየታሠርን ሁሌም ስንፈታ ስራችን መደሰት ቢሆንም ጓደኞቼ አብረውኝ ባለመውጣታቸው ደስታዬ ሙሉ እንዳይሆን አድርጐታል፡፡ ከዚያ በተረፈ ግን ባለቤቴ ቤተልሄም አዛናውና ልጄ ኤማንዳ ሃብታሙ፣ እህቴ ገነት አያሌውና ወንድሞቿ ከባድ ዋጋ ከፍለዋል፡፡
ጠበቃ ተማም አባቡልጉና አመሃ መኮንን ላደረጉልኝ ድጋፍና ትብብር በሙሉ አመሰግናለሁ፡፡ ከእግዚአብሔር ቀጥሎ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ፣ በሀገርም በውጪም ላሉት ምስጋናዬ ይድረስ፡፡
Published in
ነፃ አስተያየት