በሽብርተኝነት የተሰየመው “ግንቦት 7” ድርጅት አባል በመሆን በተለያዩ የሽብር ድርጊቶች ተሳታፊ ነበሩ ተብለው የተከሰሱት የአንድነት፣ የአረና እና የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችና ሌሎች ተከሳሾች “በማረሚያ ቤት ህገወጥ ፍተሻ ተደርጎ ገንዘብና ንብረት ተወስዶብናል” ሲሉ በቃል ያቀረቡት አቤቱታና ክርክር በመቅረፀ ድምፅ ባለመቀረፁ እንደገና አቤቱታቸውን በፅሁፍ እንዲያቀርቡ ፍ/ቤቱ ከትናንት በስቲያ ትዕዛዝ ሰጠ፡፡
10 ሰዎች በሚገኙበት መዝገብ ስር የተካተቱት የአንድነት ፓርቲ ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሃብታሙ አያሌውና የፓርቲው የድርጅት ጉዳይ ም/ኃላፊ አቶ ዳንኤል ሺበሺ፣ የሰማያዊ ፓርቲ ብሄራዊ ም/ቤት ም/ሰብሳቢ አቶ የሽዋስ አሰፋና የአረና ፓርቲ አመራር አባል አቶ አብርሃ ደስታን ጨምሮ ሌሎች ተከሳሾች በጠበቆቻቸው በኩል በማረሚያ ቤት የደረሰባቸውን በደል በቃል ሲያስረዱ ያልተቀረፁበትን ምክንያት የፍ/ቤቱ የችሎት አገልግሎት ክፍል እንዲያስረዳ ፍ/ቤቱ ተጨማሪ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
ተከሳሾች ታህሳስ 15 ቀን 2007 ዓ.ም በጠበቃቸው አማካኝነት በማረሚያ ቤቱ ሌሊት በተደረገ ፍተሻ ገንዘብን ጨምሮ የማስታወሻ ደብተሮቻቸው እንዲሁም በቀጣይ ለሚደረገው ክርክር ያዘጋጁት መከራከሪያ ነጥቦች ከማስታወሻቸው ጋር እንደተወሰደባቸው፤ ያመለከቱ ሲሆን ፍ/ቤቱ ማረሚያ ቤቱ ምላሽ እንዲሰጥበት የዘጠኝ ቀናት ቀጠሮ ሰጥቶ እንደነበር ይታወሳል፡፡
ከዘጠኝ ቀን በኋላ ታህሳስ 24 ቀን 2007 ዓ.ም ማረሚያ ቤቱ አቤቱታው ተገልብጦ እንዳልተሰጠውና ምላሽ ማቅረብ እንዳልቻለ አመልክቶ፣ ፍ/ቤቱ በድጋሚ ተገልብጦ እንዲሰጠው ትዕዛዝ አስተላልፎ፣ ጉዳዩን ለመመልከት ከትናንት በስቲያ ቀጥሮ የነበረ ሲሆን በእለቱ የቀረበው የተከሳሾች አቤቱታ እንዳልተቀረፀ ፍ/ቤቱ አረጋግጧል፡፡ ማረሚያ ቤቱም የአቤቱታው ግልባጭ እንዳልደረሰው ተመልክቷል፡፡
የተከሳሽ ጠበቆች በበኩላቸው፤ ፍ/ቤቱ፤ ያልተቀረፀበትን ምክንያት አጣርቶ በሚመለከተው አካል ላይ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቀው አቤቱታው ከቀረበ ጊዜ ጀምሮ ባሉት ጊዜያት ሁሉ በደንበኞቻቸው ላይ የሚደርሰው የመብት ጥሰት እንዳልቆመ ተናግረዋል፡፡
የጠበቆችን አቤቱታ ያዳመጠው ፍ/ቤቱ ያልተቀረፀበትን ምክንያት እንደሚያጣራና የራሱን እርምጃ እንደሚወስድ ጠቅሶ ጠበቆች አቤቱታቸውን በፅሁፉ ያቅርቡ ሲል ለቀጣዩ ሃሙስ ጥር 14 ቀን 2007 ዓ.ም ቀጥሯል፡፡ በቀጠሮው እለት ተከሳሾች መቅረብ እንደማይጠበቅባቸውና ጠበቆች ብቻ በችሎት ተገኝተው አቤቱታውን ማቅረብ እንደሚችሉ ፍ/ቤቱ ጠቁሟል፡፡
በአንደኛ ተከሳሽ ዘላለም ወ/አገኘሁ መዝገብ ስር አራቱን የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጨምሮ 10 ተጠርጣሪዎች በኢትዮጵያ መንግስት ሽብርተኛ ተብሎ የተሰየመው ግንቦት 7 አባል በመሆን አላማውን በሽብር ለማሳካት ተንቀሳቅሰዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸው፣ በእስር ላይ ሆነው ጉዳያቸውን እየተከታተሉ መሆኑ ይታወሳል፡፡

Published in ዜና

          ዘንድሮ በሎስ አንጀለስ በሚካሄደው የፓን አፍሪካ ፊልም ፌስቲቫል የቴዎድሮስ ተሾመ “ሶስት ማዕዘን” ፊልም በፌስቲቫሉ አጋማሽ ላይ ለእይታ እንደሚቀርብ ተገለፀ፡፡ በየዓመቱ በሚካሄደው በዚህ ፌስቲቫል ላይ በውድድሩ ለመካፈልና የ “ኦፊሻል ሰሌክሽን” ማዕረግ ለማግኘት ከ6-10 ሺህ ፊልሞች ከመላው ዓለም እንደሚመዘገቡና 200 እንደሚመረጡ የገለፀው አርቲስት ቴዎድሮስ ተሾመ፤ ከእነዚህ ፊልሞች መካከል ሶስቱ በክብር ተመርጠው በመክፈቻው፣ በፌስቲቫሉ መሃልና በመዝጊያው ስነ ስርዓት ላይ እንደሚታዩ ጠቁሞ በተለይ በፌስቲቫሉ መሃል (ሴንተር ፒስ) ላይ የመታየት እድል ማግኘት እጅግ ከፍተኛ ማዕረግ እንደሆነ ለአዲስ አድማስ ተናግሯል፡፡ የዘንድሮው የፓን አፍሪካን ፊልም ፌስቲቫል ከጥር 28 እስከ የካቲት 9 2007 ዓ.ም በሎስ አንጀለስ የሚካሄድ ሲሆን ከተመረጡት 200 ፊልሞች በአምስት ዘርፍ ለተዘጋጀው ሽልማት ከየዘርፉ አምስት አምስት ፊልሞች እንደሚመረጡ፣ ነገር ግን በመክፈአቻው፣ በፌስቲቫሉ መሃልና በመዝጊያው ስነ-ስርዓት ላይ ለመታየት የተመረጡ ፊልሞች በአምስቱም ዘርፍ ውስጥ ለመመረጥ ከፍተኛ እድል እንዳላቸው የገለፀው አርቲስት ቴዎድሮስ፤ “ሶስት ማዕዘን” ፊልም ለዚህ መብቃቱ ለአገር እና ለወገን ኩራት እንደሆነ ገልጿል፡፡ በፌስቲቫሉ ከአምስቱም ዘርፍ ተመርጠው ለሚያሸንፉ ፊልሞች አምስት ትልልቅ ሽልማቶች የተዘጋጁ ሲሆን “ሶስት ማዕዘን” ፊልም በአምስቱ ዘርፎች ውስጥ በዳኞች የመመረጥ እድል ካጋጠመው ሊሸለም እንደሚችል ተስፋ ተጥሏል ብሏል - ቴዎድሮስ፡፡ በፌስቲቫሉ ላይ በአፍሪካውያንና በአፍሪካ አሜሪካውያን የፊልም ባለሙያዎች የተሰሩ የተመረጡ ፊልሞች ለዕይታ የሚበቁ ሲሆን፣ የፓናል ውይይቶችና የተለያዩ ስነጥበባዊ ዝግጅቶችም ይከናወናሉ፡፡

•    ለ3ኛ ጊዜ ጠቅላላ ጉባኤ ማካሄድ አንችልም ብለዋል

ጠቅላላ ጉባኤ በማካሄድ በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ የውስጥ ችግራቸውን ፈተው እንዲቀርቡ የመጨረሻ እድል የተሰጣቸው መኢአድና አንድነት፤ ለሶስተኛ ጊዜ ጠቅላላ ጉባኤ እንደማያካሂዱና የምርጫ ቦርድን ውሳኔ እንደሚጠብቁ ተናገሩ፡፡
የመላው ኢትዮጵያውያን አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ቢሮን የያዙት የፓርቲው ፕሬዚዳንት አቶ ማሙሸት አማረ፤ ፓርቲያቸው ባለፈው እሁድ የምርጫ ቦርድን ፍላጐት ለማሟላት ሲል በድጋሚ ጠቅላላ ጉባኤውን ማካሄዱን ጠቁመው፣ ቦርዱ ለሶስተኛ ጊዜ ጠቅላላ ጉባኤ እንድናካሂድ መጠየቁ አግባብ አይደለም ብለዋል፡፡
ምርጫ ቦርድ ከፓርቲው የቀረቡለትን ሰነዶች መርምሮ ትክክለኛውን ውሳኔ መስጠት ይችላል ያሉት አቶ ማሙሸት፤ ይህ ካልሆነ ግን ቦርዱ መኢአድን ከምርጫ የማስወጣት ተልእኮ እንዳለው ልንገምት እንችላለን ብለዋል፡፡
ፓርቲያቸው በእሁዱ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የቦርዱ ተወካዮች እንዲገኙለት ጥሪ ማስተላለፉን የጠቆሙት አቶ ማሙሸት፤ ቦርዱ ግን ተወካዮቹን ልኮ ለሁለተኛ ጊዜ የተካሄደውን ጠቅላላ ጉባኤ በራሱ ምክንያት ሳይታዘብ ቀርቷል ብለዋል፡፡ “በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለን ለ3ኛ ጊዜ ጠቅላላ ጉባኤ መጥራት የማይታሰብ ነው፤ ከዚህ በኋላ የቦርዱን የመጨረሻ ውሳኔ ነው የምንጠብቀው” ብለዋል፤ አቶ ማሙሸት፡፡
በቦርዱና በፓርቲው መካከል በተፈጠረው አለመግባባት ሳቢያ መኢአድ እጩዎቹን ማስመዝገብና ደጋፊዎቹ የምርጫ ካርድ እንዲወስዱ መቀስቀስ አለመቻሉን፣ ይሄም በፓርቲው አጠቃላይ የምርጫ እንቅስቃሴ ላይ ተፅእኖ ማሳረፉን አቶ ማሙሸት ጨምረው ገልፀዋል፡፡
የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ፅ/ቤትን ይዘው የሚገኙትና ኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው በገዛ ፈቃዳቸው ከስልጣን መልቀቃቸውን ተከትሎ በፓርቲው ብሄራዊ ም/ቤት በተመረጡት በአቶ በላይ ፈቃዱ ካቢኔ ተቀዳሚ ም/ፕሬዚዳንት የሆኑት አቶ ግርማ ሰይፉ በበኩላቸው፤ ፓርቲያቸው ባለፈው እሁድ ምርጫ ቦርድ በፈለገው መልኩ ጠቅላላ ጉባኤውን ለሁለተኛ ጊዜ ማካሄዱን ጠቅሰው፣ ለሦስተኛ ጊዜ ጠቅላላ ጉባኤ እንደማይጠሩ ተናግረዋል፡፡
ፓርቲው ትናንት በሰጠው መግለጫ፤ ምርጫ ቦርድ፣ አንድነት የአመራር ምርጫውን ያደረገው የፓርቲውን ደንብና የምርጫ አዋጆችን መሰረት አድርጎ መሆኑን ከቀረበለት ሰነድ መርምሮ የሚሰጠውን ውሳኔ እንደሚጠብቅ አስታውቋል፡፡ “እነ አቶ ትዕግስቱ አወሉ አንድነትን የመወከል ህጋዊ መብት ስለሌላቸው ከነሱ ጋር ለድርድር መቀመጥ የማይታሰብ ነው” ብለዋል - አቶ ግርማ፡፡
ባለፈው እሁድ በዲአፍሪክ ሆቴል ጠቅላላ ጉባኤ በማካሄድ በፕሬዚዳንትነት የተመረጡት አቶ ትዕግስቱ አወሉ በበኩላቸው፤ ምርጫ ቦርድ በሰጠው የሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ከእነ አቶ በላይ ቡድን ጋር ተነጋግሮ ጠቅላላ ጉባኤ በድጋሚ የሚጠራበት ሁኔታ እንዲመቻች ለድርድር ለመቀመጥ ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ “በኛ በኩል በችግሮቹ ላይ ተወያይቶ ፓርቲውን ለማዳን ዝግጁ ነን” ያሉት አቶ ትዕግስቱ፤ የእነ አቶ በላይ ቡድን የሚስማማ ከሆነ ጠቅላላ ጉባኤ በጋራ ተካሂዶ አዲስ ፕሬዚዳንት ይመረጣል ብለዋል፡፡
ምርጫ ቦርድ እስከ ጥር 4 ቀን 2007 ዓ.ም ያስቀመጠው ቀነ ገደብ መጠናቀቁን ተከትሎ በሰጠው መግለጫ፤ በመኢአድም ሆነ በአንድነት በኩል አልተፈቱም ያላቸውን ችግሮች ዘርዝሮ በማስረዳት፣ ችግራቸውን ፈተው እንዲቀርቡ ለሶስተኛ ጊዜ ዕድል መስጠቱን ያስታወቀ ሲሆን በሚቀጥለው ሳምንት የተሰጠው ቀነ ገደብ ያበቃል፡፡

Published in ዜና

በመቶ ከሚቆጠሩ አገራት ከአስር ሺ በላይ ተሳታፊዎችን በማስተናገድ በአዲስ አበባ ከተካሄዱ አለማቀፍ ጉባኤዎች መካከል አንዱ ይሆናል የተባለው 3ኛው “ፋይናንስ ለልማት” የተሰኘ ዓለም አቀፍ ኮንፍረንስ በሰኔ ወር ለማካሄድ የኢትዮጵያ ባለስልጣናትና የፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ዋና አማካሪዎች እየተዘጋጁ ነው፡፡
የተለያዩ ሀገራት መሪዎችና ሚኒስትሮች፤ እንዲሁም የቢዝነስ ሰዎችን ጨምሮ 10 ሺ ተሳታፊዎች በኮንፈረንሱ ይገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የተናገሩት የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም፤ ኮንፍረንሱ የእዳ ቅነሳና ስረዛ ላይ የሚያተኩር ይሆናል ብለዋል፡፡ ከፍተኛ እዳ የተከማቸባቸው የአፍሪካና የሌሎች ድሃ አገሮች መንግስታት ባለፉት አስር አመታት የእዳ ስረዛ እንደተረገላቸው የሚታወስ ሲሆን፤ ከቅርብ አመታት ወዲህ እንደገና እዳ ውስጥ እየገቡ መምጣታቸው ይታወቃል፡፡ በእዳ ብዛት ሌሎች የአፍሪካ መንግስታት በርካታ ቢሆኑም፤ በኢትዮጵያ መንግስት ስር የሚገኙ ድርጅቶች በብድር የተከማቸባቸው እዳ በጥቂት አመታት ውስጥ ከእጥፍ በላይ ጨምሯል፡፡
ከ14 ቢሊዮን ዶላር በላይ (ወደ 300 ቢሊዮን ብር ገደማ) የውጭ እዳ፣ እንዲሁም የዚያን ያህል 300 ቢሊዮን ብር የአገር ውስጥ የባንክ እዳ እንዳለባቸው ከመንግስት ተቋማት የተገኙ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
በሰኔ ወር የሚካሄደው አለማቀፍ ጉባኤ ለድሃ አገራት የእዳ ቅነሳና ስረዛ በሚደረግበት ሁኔታ ላይ የሚወያይ ቢሆን፤ ከዚሁ ጐን ለጐን የድሃ አገር መንግስታት ራሳቸውን የሚችሉበት ጉዳይም ይነሳል ተብሏል፡፡ ጉባኤው የአገር ውስጥና ፋይናንስ መፍጠሪያ ዘዴዎችን በማስፋፋት ላይ ትኩረትን ያደርጋል ብለዋል፡፡ የሀገር ውስጥ አለማቀፍ ፋይናንስን እንዴት ማንቀሳቀስ ይቻላል በሚለው ጥያቄ ላይም  ይመከራል ተብሏል፡፡  
ሚኒስትሩ ሐሙስ ጥር 7 ቀን ከአሜሪካ ከመጡ የፕሬዚዳንት ኦባማ ከፍተኛ አማካሪዎች ጋር የተወያዩ ሲሆን፤ የሰኔው ጉባኤ ውጤታማ እንዲሆን ድጋፋቸውን ለመስጠት መምጣታቸውን ከኦባማ ዋና አማካሪዎች መካከል ከፍተኛ ተሰሚነት ያላቸው ጆን ፓዴስታ ተናግረዋል፡፡
 ዶ/ር ቴዎድሮስ አዳኖም በበኩላቸው፤ የኦባማ ዋና አማካሪዎች እዚህ መምጣታቸው ለጉዳዩ ምን ያህል ትኩረት እንደሰጡት የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡ በገንዘብ ሚኒስትሩ ሶፍያ አህመድ የሚመራ የበላይ ኮሚቴ የጉባኤውን ዝግጅት እያከናወነ ሲሆን፤ የመጀመሪያው አለማቀፍ የፋይናንስ ለልማት በ2002 ዓ.ም በሞንትሪያል ሁለተኛው አለማቀፍ “ፋይናንስ ለልማት” ደግሞ በ2008 ዓ.ም በዶሀ መካሄዱን ሚኒስትሩ ገልፀዋል፡፡

Published in ዜና

የደም ባንክ በመያዣነት ወስዶ ለዓመታት ያስቀመጣቸውን ከ40ሺህ በላይ መታወቂያዎች፣ መንጃ ፍቃድና ፓስፖርት ለባለቤቶቹ ሊመልስ ነው፡፡
በቀድሞ የደም ባንኩ አሰራር ለደም ፈላጊዎች ደም ሲሰጥ ተጠቃሚዎቹ በምትኩ ለባንኩ ደም ማቅረብ የሚጠበቅባቸው ሲሆን ባንኩ ምትክ ደም ማቅረብ ያልቻሉ ሰዎችን መታወቂያ፣ መንጃ ፍቃድና ፓስፖርት በመያዣነት ወስዶ ያስቀምጥ ነበር፡፡
የደም ባንኩ ከተለያዩ በጐ አድራጊ ግለሰቦች ደም የማግኘት አሰራሩን እያሰፋ በመምጣቱ ካለፈው ዓመት ታህሳስ ወር ጀምሮ አዲስ መመሪያና አሠራር በማውጣት የደም ልገሳ ሂደቱ በፍቃደኝነት ላይ ብቻ የተመሰረተ እንዲሆን አድርጓል፡፡ ይሄንን ተከትሎም ደም በፈቃደኝነት የሚለግሱ ዜጐች ቁጥር እየጨመረ የመጣ ሲሆን ቀደም ሲል በመያዣነት አስቀምጦአቸው የነበሩትን 40 ሺ የሚደርሱ የመንጃ ፍቃድ፣ ፓስፖርትና የመታወቂያ ካርዶች ለደንበኞቹ ለመመለስ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን የደም ባንኩ የኮሙኒኬሽን ኦፊሰር አቶ ክበበው ዘነበ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡   

Published in ዜና
Wednesday, 14 January 2015 09:15

ትመጣለች ብዬ

ትመጣለች ብዬ ሳይ ማዶ ሳይ ማዶ
የልጅነት ዓይኔ ሟሟ እንደበረዶ፡፡
ትመጣለች ብዬ እየጠበቅሁ ነው፡፡ የሷ መምጣት ግን ከኢየሱስ መምጣትም በላይ ዘገየ፡፡ እሷን የማይበት ቀን እንደ ምፅአት ቀን ራቀኝ፡፡ ስትሄድ ቃል ገብታልኝ ነው፡፡ ፈፅሞ ላትረሳኝ ምላ፡፡ እንደምትወስደኝ ተገዝታ፡፡ ቢያንስ ቶሎ መጥታ እንደምንገናኝ ቃል ገብታልኝ ነው፡፡ ዲቪ ደረሳትና የሚፈለግባትን አጠናቃ ወደ አሜሪካ አቀናች፡፡ መልካም የሚባል ጊዜ አብረን አሳልፈናል፤ እንደ ከርቤ አፍንጫ የሚያውድ፣ እንደ ናና ከረሜላ ለአፍ የሚጣፍጥ፣ እንደ ቤትሆቨን የሙዚቃ ቅንብር ጆሮ የሚያሰምጥ፤ እንደ አደይ አበባ ለዓይን የሚማርክ፤ እንደ መልካም መዝሙር ልብ የሚያስመልክ … ጊዜ!... የእስራኤል ገናንነትን እንደሚመኝ፣ የኢየሩሳሌምን ማክተም እንደሚፈልግና “ብረሳሽ ቀኜ ይርሳኝ!” እንደሚለው አይሁድ፣ እኔም ስምዋን እየጠራሁ እንደዛው እምላለሁ፡፡ ያጋጣሚ ነገር ሆኖ ስምዋ ኢየሩሳሌም ነው፡፡ እና ዘወትር እንዲህ እላለሁ፡፡ “ኢየሩሳሌም ሆይ፤ ብከዳሽ ቀኜ ትክዳኝ!” በሄደች በስድስተኛ ወርዋ ደብዳቤ ፃፈችልኝ፡፡ እንዲህ የሚል፡- “እዮብዬ እንዴት ነህልኝ? እኔ ካንተ ሀሳብና ናፍቆት በስተቀር በጣም ደህና ነኝ፡፡

ስራ ጀምሬያለሁ፡፡ ይሄ ሀገር እንደ ኢትዮጵያ አይደለም፡፡ ዶላር ውድ ነው፡፡ ዶላር የምታገኘው ላብህን አንጠባትበህ ነው፡፡ ቢሆንም ለክፉ የሚሰጥ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ  ለመስራት ብትፈልግ እንኳ የምትሰራው ስራ አታገኝም፡፡ ወይም ገቢህ ትንሽ ይሆናል፡፡ እዚህ ግን ሰርቶ መኖር ይቻላል፡፡  ስራ መምረጥ እኛ ስደተኛ ኢትዮጵያውያንን የሚመጥን አይደለም፡፡ ለዚያ ማዕረግ ለመብቃት ብዙ ይቀረናል፡፡ ስለዚህ ያገኘነውን ስራ ነው የምንሰራው፡፡ የመብራት፣ የውሃ የምን የምን ቢል ስለሚመጣብህ እንደ ኢትዮጵያ ተኝተህ ማደር አትችልም፡፡እንደምንም ተፍ ተፍ ማለት አለብህ፡፡ ያለበለዚያ መኖር አይቻልም፡፡ ዛሬ ላይ ሆኜ ሳስበው የኛ የኢትዮጵያውያን ኑሮ አብዝቶ ይገርመኛል፡፡ በኢትዮጵያ እንደ ሌላው ላይ እንደ አነባበሮ ተነባብሮ ነው የሚኖረው፡፡ እዚህ አስራ ስምንት ዓመት ከሞላህ ራስህን መቻል ግዴታ ነው፡፡ ከወላጆችህ ቤት ወጥተህ ወደ ራስህ ቤት፤ ከጥገኝነት ተላቀህ ወደ ወንደላጤነት መቀየርህ የሚጠበቅና የሚከወን እውነት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ዕድሜያቸው እስከ ሰላሳና አርባ ደርሶ ከቤተሰብ ጋር የሚኖሩ አሉ፡፡ እዚህ ይሄ አይታሰብም፡፡ (የሚታሰብ አይደለም)፡፡ በተረፈ አሜሪካ ለትጉሃን የአፖርቹኒቲ - የዕድል አገር ናት፡፡ ከለፋህ ከደከምክ፤ ከጠራክ ከጋርክ ስኬታማ ልትሆን ትችላለህ፡፡
እዚህ ከመጣሁ በኋላ በጣም የከበደኝ ነገር ቢኖር ያንተ ናፍቆት ነው፡፡ በጣም ትናፍቀኛለች፡፡
በጣም ትናፍቀኛለህ፡፡ እጅግ በጣም ትናፍቀኛለህ፡፡ አብረን ያሳለፍነውን ጊዜ ሁሌም ስዘክረው እኖራለሁ፡፡
ያደረግናቸው ነገሮች አንድ በአንድ ትዝ ሲሉኝ ደስታ ውስጤ እንደ ችቦ ይለኮሳል፡፡ የትውስታ ማህደሬ የተሞላው ባንተ ነው፡፡ ቤተሰቦቼን ሳስብ አንተን አስባለሁ፡፡ አዲስ አበባን ሳስብ አንተን አስባለሁ፡፡
ኢትዮጵያን ሳስብ አንተን አስባለሁ፡፡ በሰላም እንድትቆይልኝ የሰርክ ፀሎቴ ነው፡፡ ተመቻችቶልኝ እስክወስድህ ድረስ ስናፍቅ እኖራለሁ፡፡ ያንተው ኢየሩስወይም አንተ እንደምትጠራኝ ያንተው ጄሪ!
እወድሃለሁ!
ቻዎ!”
እኔም መልሼ ፃፍኩላት፡፡ የኔ ደብዳቤ ይህን ይመስል ነበር፡፡ “ጄሪዬ እንዴት ነሽልኝ?!.... እኔ እግዚአብሔር ይመስገን በጣም ደህና ነኝ፡፡ አንቺ ከሄድሽ ወዲህ ጭር ብሎብኛል፡፡ ታምኚኛለሽ? … አዲስ አበባ ጭር አለችብኝ፡፡ ለካ ያንቺ መኖር ነበር ሙቀት የሚሰጣት፡፡ ለካ አንቺ ነበርሽ ጨለማዋን የምትገፊ፣ ዕለቱን በብርሃን የምታደምቂ ፀሐይዋ!
አንቺ ከሄድሽ ወዲህ … በኔ በኩል … ሁሉ ጨለማ ነው፡፡ የደስታ ጣዕም እንደትነት እንኳን ተስቶኛል፡፡  ከደስታ ጋር ተረሳስተናል፡፡ ከሳቅ ጋር ተፋተናል፡፡ ሳቅ ከልቤ ፈልቆ ጥርሴ ላይ የሚታየው ያሳለፍነውን ጊዜ ሳስብ ነው፡፡
አቅፌሽ     ወክ ሳደርግ!
አቅፌሽ ስተኛ!
አቅፌሽ ስውል!
አቅፌሽ ሳድር!
ፀሀዬ ነበርሽ ሙቀት የምትሰጪኝ! ጨረቃዬ ነበርሽ የምሽትን ድንግግዝ ጨለማ ገፈሽ ምሽቴን የምታደምቂ! አንቺ ከተለየሽኝ በኋላ ብዙ ነበር ጎድሎብኛል፡፡ ጉድለቱ ስትመጪ ይሞላል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ በተረፈ እንደዚያው እንደ ድሮው ነኝ፤ ኪሎ ወይም ቁመት አልጨመርኩም፡፡ ልቤም ባንቺ ንግስትነት እምነቱ እንደፀና ነው፡፡ ሁሌ እንዲህ እዘምራለሁ፡፡
አንቺ እዛ ማዶ እኔ እዚህ ማዶ
አንገናኝም ወይ ተራራው ተንዶ
እወድሻለሁ!
ቻዎ!
በሄደች በአስር ወርዋ ደግሞ እንዲህ የሚል ደብዳቤ ፃፈችልኝ፡፡ “ውዴ እንዴት ነህልኝ?! … ኑሮ እንዴት ይዞኻል?! እኛ ጋ ኑሮ አድካሚም አስደሳችም ነው፡፡ ኑሮአችን የላብም፣ የላቭም ድቅል (ዲቃላ) እውነት ነው፡፡ ስራ ላይ የምታፈሰው ላብ አለ፡፡ በህይወት ድንገት የሚያጋጥምህ ላቭም አለ፡፡ እንደ አበበ ቢቂላ የዞረበት መልስ አንሰጥም፡፡ ታሪኩን ሰምተሃል?! አበበ ቢቂላ በሮም ውድድር ላይ ብቻውን ወደ ስቴዲየሙ ገባ፡፡ ውድድሩንም አንደኛ በመሆን አሸነፈ፡፡ በጉብዝናው የተደነቀች አንዲት ነጭ ሴት ወደ አቤ ቀረብ ብላ እንዲህ አለች፤
“አይ ላቭ ዩ!”
አበበ መልስ ለመስጠት አላመነታም፡፡ “የላቡን ነገርማ ተይው” አላት ይባላል፡፡ ለማንኛውም እኔ ደህና ነኝ፡፡ በቅርቡ ትምህርት ለመጀመርም እያሰብኩ ነው፡፡ አሜሪካ ከጉልበት ስራ መገላገያ ብቸኛው መንገድ መማር ነው፡፡ ተምሬ የተሻለ ስራ የመስራት ራዕይ አለኝ፡፡ አሁነ ባለው ሁኔታ እየሰራሁ መማር የምችል ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ በቅርቡ ትምህርቴን መጀመሬ አይቀርም፡፡ ለዛሬ በዚህ ይብቃኝ፡፡
እወድሃለሁ!
ቻዎ!
እኔም እንዲህ የሚል መልስ ፃፍኩላት፡፡ “ጄሪዬ ነፍሴ … እንዴት ነሽልኝ?! … እኔ በጣም ደህና ነኝ፡፡ ፃፍሽልኝን ደብዳቤ አነበብኩ፡፡ ሀሳብሽ ጥሩ ነው፡፡ መማርን የመሰለ ነገር የለም፡፡ እንዳልሽው ጠንከር ብለሽ በፅናት መማር አለብሽ፡፡ ትምህርት የዕውቀት መሰላል ነው፡፡ እዛ መሰላል ላይ የሚወጡት የታደሉት ናቸው፡
የተማረ ሰው ከመሰላሉ ጫፍ ላይ ሆኖ ቁልቁል ያያል፡፡ የሰው ልጅ አጥቶ የሚቸገረው ቁልቁል

ማየትን ነው፡፡
ሁሉም የሚያየው ሽቅብ ነው፤ ወደ ላይ! …
ወደ ላይ በማየት ግን የሚመጣ ለውጥ የለም፡፡ ለረጅም ጊዜ ለማጎንበስና አጎንብሶ ለመቆፈር የደፈሩት ናቸው ቀና ብለው መሄድ የሚችሉት፡፡ የቆሸሹ እጆች ባለቤት መሆን በስኬት አሳንሰር ላይ ለመሳፈር ወሳኝ ነው፡፡
እና አንቺም በትጋትሽ     ቀጥይ! … በርቺ….ጄሪዬ ብታውቂው ደስ የሚለኝ፣ ብደብቅሽ መደበቁ አግባብ የማይመስለኝ አንድ እውነት አለ፡፡ እሱም ከምንም ከምንም በላይ አንቺን ለማየትና ለማግኘት መጓጓቴ ነው፡፡ በጣም ናፍቀሽኛል፡፡ ሁሌም በህልሜ አይሻለሁ፡፡ ከአጠገቤ ብትሆኚ፣ ከጎኔ ብትቆሚ እደሰታለሁ፡፡ እውነታውን እያወቅሁ እውነታውን ለመካድ ይዳዳኛል አንዳንዴ!
መሀላችን አትላንቲክ ውቅያኖስ ተዘርግቷል፡፡ ስለዚህ መገናኘታችን በዋዛ የሚሆን አይደለም፡፡ አንቺን ወደኔ ለማምጣት፤ ወይም እኔን ወዳንቺ ለመውሰድ እግዜር ቢተባበረን ምን አለ? እላለሁ ብዙ ጊዜ፡፡
ለማንናውም አብዝቼ እንደምወድሽ አትርሺ!
ቻዎ!
… ጄሪ ከዚያ ደብዳቤ በኋላ ሌላ ደብዳቤ አልፃፈችልኝም፡፡ ለምን እንደሆነ ሊገባኝ አልቻለም፡፡ ስራ በዝቶባት ይሆን? ወይስ ትምህርት አጨናንቋት?! እርግጡን እንኳን እኔ አዋቂ የሚባሉት ጠንቋይ እንኳን አያውቁም፡፡ አሜሪካ ከሄደች ዓመታት አለፏት፡፡ ደብዳቤ ከፃፈችልኝም አራተኛ ወርዋ ሆነ፡፡ ምን ነካት? ስል አሰብኩ፡፡
ጊዜው በረዘመ ቁጥር ደህንነትዋ ሁሉ ያሳስበኝ ጀመረ፡፡ አንዱ ጥቁር  ወንበዴ ሽጉግጥ ተኩሶባት አቁስሏት ወይም ገድሏት ይሆን? ስል ተጨነቅኩ፡፡ ጠብቄ ጠብቄ ሌላ ደብዳቤ አልመጣ ሲል እኔ ፃፍኩላት፡፡ እንነዲህ ብዬ፡- “ ጄሪዬ፤ በጤና አለሽን?
… በጤናሽ ከሆንሽ ለእኔ ይሄ ብቻ በቂዬ ነው፡፡ ደብዳቤሽ መጥፋቱ (መቆሙ) ግን ብዙ ነገር አሳስቦኝ… በጤናሽ አይሆንም ብዬ ገመትኩ፡፡ የታመምሽ ወይም የሞትሽ መሰለኝ፡፡ ይሄ ጥርጣሬዬ ብቻ ሆኖ እንዲቀር ፈጣሪዬን ለመንኩት፡፡ ግን ምን ሆነሽ ነው?!... ይሄ ደብዳቤ ከደረሰሽ፤ እንደደረሰሽ በአስቸኳይ መልስ ጻፊልኝ፡፡
የሚያርፍብሽ ዝንብ ራሱ እሽሽ እንዲባል አልፈልግም፡፡ እንድትጎጂ፤ እንድትታመሚ ወይም እንድትሞቺ አልፈልግም፡፡ እነዚህን ሁሉ ለጠላቶችሽ እመኛለሁ፡፡ አንቺ የኔ ቀዘባ ግን ሙሉ ጤንነትና ሰላም እንዲኖርሽ እመኛለሁ፡፡ (እወድሻለሁ) …
ለማንኛውም እንደምወድሽ ለሰከንድ እንኳን እንዳትረሺ!
ያንቺው አፍቃሪ ነኝ … ከአዲስ አበባ!”
የኔና የኢየሩስ ፍቅር የተለየ ነበር፡፡ ብዙዎች በመገረም ያወሩታል፡፡ ጥቂቶች ግራ በመጋባት ያሙታል፡፡
የሚቀናብን ነበርን፡፡ ጥምረታችን እንደ እውነት የሰመረ፤ ተግባቦታችን እንደ ከዋክብት ያማረ፣ ፍቅራችን እንደ ጅማት የከረረ ነበር፡፡ ምና ያደርጋል በመጨረሻ ስደት መሀላችን ሰርጎ ገባ፡፡ ፍቅራችንን መገላለፅና ፍቅራችንን መኖር የምንችለው በደብዳቤ ልውውጥ ብቻ ሆነ፡፡ በያን ደብዳቤ ከፃፍኩላትም በኋላ ኢየሩስ መልስ ሳትፅፍልኝ ቀረች፡፡ ከብዙ ወራት በኋላ ግን አንድ ኢንቨሎፕ እጄ ገባ፡፡ ከፍቼ አነበብኩት፡፡ ፀሀፊዋእየሩሳሌሜ ናት፡፡ ደብዳቤ አፃፃፍዋና ቃላት አጠቃቀምዋ ከወትሮው ለየት አለብኝ፡፡     የፃፈችው እንዲህ ለማለት ነበር፤
“ኢዮብ እንዴት ነህ?” (ይህን አረፍተ ነገር ሳነብ ተራው ነገር እንደትልቅ ነገር ሆዴን አሳመመኝ፡፡ “ዬ” ጠፍታለች፡፡ እና ተከፋሁ፤ የ“ዬ” ከኢዮብ ቀጥሎ አለመግባት አንዳች ነገር ነገረኝ፡፡ ነገሩን በሆዴ ይዤ ንባቤን ቀጠልኩ፡፡)“…. እኔ ደህና ነኝ፡፡ ያልፃፍኩልህ ስላልተመቸኝ ነው፡፡
እንደውም ቀደም አድርጌ ላሳውቅህ ይገባ የነበረ ነገር ሳልነግርህ ዘገየ፡፡ በነገራችን ላይ ይህ ደብዳቤ የመጨረሻዬ ነው፡፡ አንተም ባለፈው የፃፍከውን ደብዳቤ የመጨረሻህ አድርገው፡፡ ኢዮብ ህይወት አጋጣሚ ናት፡፡ ድንገት በገጠመህ ነገር ተወስነህ ትኖራለህ፡፡ ስለዚህ እኔም አንድ አጋጣሚ ገጥሞኛል፡፡ አንድ የምቀራረበው ሰው ነበረ፡፡ ተግባባን፡፡ እና ቸኩሎ ካልተጋባን (ወይም  ካላገባሁሽ) አለኝ፡፡ ጓደኛ
እንዳለኝ ላስረዳው ሞከርኩ፡፡ ሊረዳኝ ግን አልቻለም፡፡ ስለወደደኝ ብቻ ሊያገባኝ ፈለገ፡፡ አንተ በፍቅርህ ፀንተህ በመታመን እንደምትጠብቀኝ እርግጠኛ ስላልነበርኩ፣ እንጋባ ስልህ የምትሰጠኝ መልስም ቀዝቀዛ ስለነበር እሺ አልኩት፡፡ እና ተጋባን፡፡ ከተጋባን አሁን እነሆ ስድስተኛ ወራችን! … አንድ ነገር እመክርሃለሁ፡፡ በተስፋ እየጠበከኝ ከነበረ በሆነው ነገር አትፀፀት፡፡ ኢዮብ እኔ የምመክርህ ቶሎ ብለህ የራስህን ህይወት መኖር እንድትጀምር ነው፡፡ ቢጤህን ፈልገህ አግባ፡፡ ስለኔ ግን ፈፅሞ እንዳታስብ፤ ይህ በመካከላችን እየተካሄደ ያለው የደብዳቤ ልውውጥ የመጨረሻ መሆን አለበት፡፡ ምክንያቱም ለትዳሬ ጥሩ አይደለም፡፡ በተረፈ መልካሙ ሁሉ እንዲገጥምህ እመኛለሁ፡፡
ቻዎ!
ገረመኝ፡፡ ደነቀኝ፡፡
(ተደመምኩ፡፡)…
ፍቅርና ተረት አንድ ሆኑ ማለት ነው?!
ተረት ሲሰሙት ደስ ይላል፡፡
ፍቅርም ሲኖሩት ደስ ይላል፡፡
ተረት ከረሱት ይረሳል፤ ፍቅርም ከተዉት ይተዋል ማለት ነው?!
ነው ወይስ መራራቅ ለመለያየት ምክንያት ይሆናል?! …
ይሆናል እንግዲህ፤ ይሆን ይሆናል፡፡
ጄሪ ትክደኛለች ብዬ አስቤ አላውቅም፡፡ አንዳች ነገር ልቤን እንደ ድመት ሲቧጭረው ይሰማኛል፡፡
ነፍሴ የእሾህ አክሊል ደፍታለች፡፡ የሀዘን ማቅ ለብሳለች፡፡ የማይላክ ደብዳቤ ለጄሪ መፃፍ ጀመርኩ፡፡ ‹ደብዳቤዬን የምጀምረው አለማመኑን በመግለፅ ነው፡፡ የማላምነው በእግዜር አይደለም፡፡
የማላምነው ወይም ያላመንኩት ያነበብኩትን ነገር ነው፡፡
እውነቱን ልናገርና  ከዓይኔ ይሆን ብዬ ተጠራጥሬያለሁ፡፡
የደብዳቤው ማዕከላዊ መልዕክት ግን ግልፅ ነበር፡፡ ቁም ነገሩ ካንቺ ከፍቅረኛዬ ጋር መለያየቴን የሚያረዳ ነው፡፡ ማመን አቃተኝ፡፡ ጄሪ ፍቅራችን ይህን ያህል በቀላሉ የሚፈርስ፤ ማገሩ በማይረባ ልጥ የታሰረ ነገር ነበር ማለት ነው?! ገርሞኝ ነው፡፡ ወደ አሜሪካ በሄድሽ በሁለተኛ ዓመትሽ ሌላ ሰው ማግባትሽን ነገርሽኝ! … ከዛ በፊት በፍቅር ያሳለፍናቸው ሶስት ዓመታት ሚዛን ሊደፉ አልቻሉም ማለት ነው?!ቢገርመኝ ነው ይህን መጠየቄ፡፡ ለማንኛውም አንቺ የራስሽን ህይወት መኖር ጀምረሻል፡፡ እኔም የራሴን ህይወት መጀመር እንዳለብኝ አምናለሁ፡፡ ትመጫለሽ ብዬ ለብዙ ጊዜ በጉጉትና በናፍቆት ጠብቄ ነበር፡፡ መምጣትሽ ግን ቀላል አልሆነም፡፡ መጥተሽ ወይም ወስደሽኝ አብረን እንኖራለን የሚል ምኞት ነበረኝ፡፡ አልሆነም፡፡ ምኞቴ ለፀሐይ
እንደተሰጣ ገብስ አደባባይ ላይ ተበተነ፡፡ ከኔ መለየትሽ እውነት መሆኑን ሳረጋግጥ ፍቅርሽ ከልቤ
ይወጣ እንደሁ ብዬ ምንም እንዳልተፈጠረ ሁሉ፤ ላንቺ ያለኝ ስሜት ከቁብ እንደማይገባ ሁሉ፤

እንዲህ ስል በስነ ቃል ተሳደብኩ፡-
“ድዳም የድዳም ልጅ መሰረተ ድዳም
 ብትመጪ አልጠቀም ብትሄጂ አልጎዳም!”

Published in ልብ-ወለድ

በባህር ዳርና በአዲስ አበባ ከ15 ዓመታት በላይ በምሽት ክበቦች ሰርቷል፡፡ “ስያሜ አጣሁላት” በሚለው የመጀመሪያ አልበሙ ከህዝብ ጋር የተዋወቀው ድምፃዊ ማዲንጎ አፈወርቅ፤ ሦስተኛ አልበሙን (ስወድላት) ሰሞኑን ለቋል፡፡ በአዲሱ ስራውም ስለ ሃገር፣ ስለ ፍቅር፣ ስለ ታማኝነት፣ ስለ ጎንደር፣ ስለ ወሎና ምንጃር ብዙ አቀንቅኗል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ ከድምፃዊ ማዲንጐ ጋር በአዲሱ አልበሙና በሙያው ዙሪያ ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርጋለች፡፡
የመጀመሪያ ስራህ “ስያሜ አጣሁላት” የሚል ነበር፡፡ በሁለተኛው “አይደረግም” ብለህ መጣህ፡፡ አሁን ደግሞ “ስወድላት” እያልክ ነው…
የመጀመሪያው አልበሜ የልጅነት ስራዬ ነው፡፡ ያኔ ጠቆር ያልኩ ነበርኩኝ፤ እንዳሁኑ አልገፈፍኩም ነበር፡፡ አሁን እንደ እባብ ቆዳ ቀይሬያለሁ፡፡ የሆነ ሆኖ “ስያሜ አጣሁላት” በልጅነት እድሜ ከህዝብ ያገናኘኝ ስራ ነው፡፡ ወቅቱ የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ነበር፡፡ ታዲያ “ስያሜ  አጣሁላት” እና “አማን ነው ወይ ጎራው” የተሰኙት ሁለት ዘፈኖች በተለየ መልኩ ተወደውልኝ ነበር፡፡ ሁለተኛው ስራዬ የትዝታ ዘፈን ያለበት “አይደረግም” በሚል ስያሜ የወጣው ነው፡፡ አሁን “ስወድላት”ን ይዤ ወደ አድማጭ ቀርቤያለሁ፡፡
በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅት “ስያሜ አጣሁላት” እና “አማን ነው ወይ ጎራው” የተወደዱበት ምክንያት ምንድን ነው? ከጦርነቱ ጋር የተገናኘ ሃሳብ ይዘዋል እንዴ?
በተለይ “ስያሜ አጣሁላት” ከኤርትራ ጠብ አጫሪነት ጋር ሳይያያዝ አይቀርም፡፡ እኔ በወቅቱ እንደነገርኩሽ ልጅ ስለነበርኩ ጉዳዩ አይገባኝም ነበር፡፡ ግጥሙን የፃፈው አንጋፋው የሙዚቃ ግጥም ደራሲ ይልማ ገ/አብ ነበር፡፡ ይልምሽ ደግሞ ወቅታዊ ፈጠራዎችን በመስራት አይታማም፡፡ አሁን ነው የሚገባኝ፡፡ እኔ ከሴት ልጅ ፍቅር ጋር ብቻ ነበር አገናኝቼ የዘፈንኩት፡፡ በነገራችን ላይ አሁንም ቢሆን ግጥሙ ከወቅቱ ጦርነት ጋር እንዲሄድ ሆን ተብሎ ይሰራ አይሰራ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ግምቴን ነው የነገርኩሽ፡፡
ሁለተኛው አልበምህ “አይደረግም” የሶስት አራት ድምፃዊያንን ትዝታ አፈራርቀህ የሰራህበት ሲሆን የትዝታው ዘፈን ድምፅህ የተፈተነበትና ወደ አድማጭ በደንብ የቀረብክበት እንደሆነ ይነገራል፡፡ እውነት ነው?
በጣም ትክክል ነው፡፡ እኔም ባለውለታዬ የምለው ዘፈን ትዝታው ነው፡፡ የእኔ የመዝፈን ብቃት ምን ያህል እንደሆነ ለህዝብ ግልፅ ያደረገ ስራ በመሆኑ በሚባለው ነገር መቶ በመቶ እስማማለሁ፡፡
“አይደረግም” ከወጣ ረዘም ያለ ዓመት ሆኖታል… ባልሳሳት ሰባት ዓመት አካባቢ… ለምን እንደዚህ ቆየህ?
ተቃርበሻል! ስምንት ዓመት አልፏል አልበም ሳልሰራ፡፡ በመሃል ግን የተሳኩና የተወደዱ ነጠላ ዜማዎችን ሰርቻለሁ፡፡ ለምሳሌ “የበላይ ዘለቀ”፣ “አንበሳው አገሳ”፣ ለ“አባይ ወይስ ቬጋስ” ፊልም የሰራሁት ማጀቢያ ሙዚቃ “አባይ ወይስ ቬጋስ” ህዝቡ ስምንት ዓመት አልበም አለመስራቴን እንዳያስታውስ አድርገውታል፡፡ ከህዝብ ጆሮ አልጠፋሁም ነበር ማለት ነው፡፡ በዚያ ላይ ኮንሰርቶች እሰራለሁ፤ የሰርግ ስራዎችንም እንደዚሁ፡፡ ይህን ስታይው ስምንት ዓመት ሙሉ የጠፋሁ አይመስልም፡፡ ከዚህ በኋላ ግን እንደዚህ አልጠፋም፤ በየሁለት አመቱ አልበም ይኖረኛል፡፡
አዲሱ አልበምህ በግጥማና ዜማ የነማን አስተዋፅኦ አለበት? ምን ያህል ጊዜስ ወሰደ?
በመጀመሪያ ደረጃ የአልበሙን ስራ ኃላፊነት ሙሉ በሙሉ የወሰድኩት እኔ ነኝ፡፡
ምን ማለት ነው?   
ይሄ ማለት ግጥምና ዜማ የመምረጡን ስራ ያለምንም ጣልቃ ገብነት የተወጣሁት እኔው ነኝ፡፡ ከልጅነቴ ጀምሮ ሙዚቃ ውስጥ እንደመሆኔ፣ ግጥምና ዜማን በማስተዋል በኩል ጥሩ ተሰጥኦ አለኝ ብዬ አምናለሁ፡፡ የአልበሙን ግጥምና ዜማ የመረጥኩት ራሴ ነኝ፡፡ ነገር ግን ግጥምና ዜማ እንዲሰሩ ትልልቅ የሚባሉና የካበተ ልምድ ያላቸውን ሰዎች አሳትፌአለሁ፡፡ ይልማ ገ/አብ፣ ጸጋዬ ደቦጭ፣ አበበ ብርሃኔ፣ አማኑኤል ይልማ፣ ታመነ መኮንን፣ አህመድ ተሾመ (ዲንቢ)፣ መኮንን ለማ (ዶክተሬ) እና መሰል ታዋቂዎች ተሳትፈዋል፡፡ ላለፉት ስምንት ዓመታት የተለያዩ ግጥምና ዜማዎችን ስሰበስብና ስመርጥ ነው የቆየሁት፡፡ 30 ዘፈኖች መረጥኩና ስቱዲዮ ተቀረፅኩ፤ ከ30ው ግን 14ቱን ነው የመረጥኩት፡፡ 14ቱም ዘፈኖች አንዱ ከአንዱ እንዳይበልጥና በጥሩ ሁኔታ እንዲደመጥ ከፍተኛ ጥንቃቄና ጥረት አድርጌያለሁ፡፡ እነዚህ ዘፈኖች የቀደመውን (የወርቃማውን ዘመን) የሙዚቃ ደረጃ እንዲይዙ ነው የፈለግሁት፡፡
የወርቃማው ዘመን ድምፃዊያን የሚባሉት እነማን ናቸው? የአሁኑ አልበህም ያስቀመጥከውን ደረጃ አሳክቷል ብለህ ታስባለህ?
ኤፍሬም ታምሩ፣ ንዋይ ደበበ፣ ፀጋዬ እሸቱ፣ አረጋኸኝ ወራሽ ያሉበት ዘመን  ለእኔ ወርቃማውና የምወደው ዘመን ነው፡፡ እኔም ያን ዘመን ሊያስታውሱ የሚችሉ በሳል ዘፈኖችን ከአሁኑ ትውልድም እንዳይርቁ አድርጌ ሰርቻለሁ፡፡ አልበሙ ሰሞኑን ነው የወጣው፤ በእነዚህ ጥቂት ቀናት ውስጥ የደረሰኝ የአድማጮች አስተያየትና ምላሽ ያለምኩትን ግብ እንደመታሁ አመላካች ነው ብዬ አምኜያለሁ፡፡
በአንድ ወቅት አልበም ማሳተም ተቀዛቅዞ ነበር፡፡ አሁን አሁን ዘፋኞች ደፈር እያላችሁ የመጣችሁ ትመስላላችሁ?
ልክ ነው፤ የአልበም ስራ የተኛበት ጊዜ ነበር፡፡ ይሄ የቅጂ መብት ጉዳይ ዘፋኙንም አሳታሚውንም ተስፋ አስቆርጦት ነበር፡፡ አሁን እነ ሸዋንዳኝ፣ እነ ሚካኤል በላይነህ፣ እነ ታምራት ደስታ፣ እነ አብነትና ሌሎችም ደፍረው አልበም በማውጣታቸው ሌሎቻችንን አበረታተውናል፡፡ አሁን ሰውም ኦሪጂናል አልበም የመግዛት ፍላጎቱ እየጨመረ መምጣቱን ያወቅሁት፣ የእኔ አልበም በወጣ በሶስተኛው ቀን እንኳን በጥሩ ሁኔታ በመሸጥ ላይ መሆኑን ስመለከት ነው፡፡
አልበሙን ሰርቶ ለማጠናቀቅ በትክክል ምን ያህል ጊዜ ፈጀብህ?
ግጥምና ዜማ መምረጥ የጀመርኩት ከስምንት ዓመት በፊት ነው፡፡ ነገር ግን ወደ ስቱዲዮ መግባትና ስራውን በደንብ መስራት የጀመርኩት ከአምስት ዓመት በፊት ነው፡፡ ያልገባሁበት ያልወጣሁበት ስቱዲዮ የለም፡፡
ለምንድነው በየስቱዲዮው እየገባህ የወጣኸው?
ያሉትን ግጥምና ዜማዎች ይዤ ስራውን እጀምራለሁ፤ ነገር ግን መርካት አልቻልኩም፡፡ አንድ ስራ ይዤ እገባና አያስደስተኝም ትቼ እወጣለሁ፡፡ ይህን ሳደርግ በራሴ የገንዘብ ኪሳራ ነው፤ ዛሬ አንድ ዘፈን ለመስራት ከ20 ሺህ ብር በላይ ይጠይቃል፡፡ ቅንብር 10 ሺህ ብር፣ ግጥምና ዜማ በቀላሉ 10 ሺህ ብር ወጪ ይጠይቃሉ፡፡ ሌሎች ጥቃቅን ወጪዎችን ሳይጨምር ማለት ነው፡፡ ከኤሌክትራ ሙዚቃ ቤት ጋር የዛሬ ስድስት ዓመት ነው የተፈራረምኩት፡፡ ስንፈራረም ግን በራሴ ስራውን አጠናቅቄ ማስተሩን ላስረክበው ተስማምተን ነው፡፡ ይሄ ማለት ዜማ፣ ግጥም ቅንብር… እያንዳንዱ ወጪና ልፋት በእኔ ላይ ነበር፡፡ ታዲያ ከስድስት አመት በፊት የነበረው ዋጋና የአሁኑ ልዩነቱ ሰማይና ምድር ነው፡፡ በዚያ ላይ ስቱዲዮ ገብቼ ጀምሬ የተውኳቸው አሉ፡፡ ያ ኪሳራ በራሴ ነው፡፡ ቀደም ብዬ እንደነገርኩሽ 30 ዘፈን ሰርቼ፣ 14ቱን ብቻ ነው የመረጥኩት፡፡ 16ቱ ቀሩ ማለት ነው፡፡
ታዲያ ምን ያህል ወጪ ወጣበት አዲሱ አልበምህ?
ያለማጋነን ከ500 ሺህ ብር በላይ አውጥቻለሁ፤ ሆኖም ለህዝብ ጆሮ የሚመጥን ስራ እንደሰራሁ ይሰማኛል፡፡ ራሴን በጣም አስደስቶኛልና፡፡
ከአንተና ከእህትህ ትዕግስት አፈወርቅ ሌላም ታናናሽ ድምፃዊ እህትና ወንድሞች አሉህ ይባላል፡፡ እንደነ አምስቱ እርጎዬዎችና እንደነ ጃክሰን ፋሚሊ “የአፈወርቅ ቤተሰቦች” ለመባል እየተቃረባችሁ ነው ወይስ?
እኛ እንኳን የአፈወርቅ ቤተሰቦች ለመባል አልበቃንም፤ ምክንያቱም በሙዚቃው ነጥረን የወጣነው እኔና ትዕግስት ብቻ ነን፡፡ አንድ ወንድሜ ፍላጎት ስላለው በመሞከር ሂደት ላይ ነው፡፡ ካናዳ ነው የሚኖረው፡፡ ጂጂ የምትባለው የታናሼ ታናሽ በጣም የሚገርምና የሚመስጥ ድምፅ አላት፤ ነገር ግን ዘማሪ መሆን ነው የምትፈልገው፡፡ አሁን እንግሊዝ ነው የምትኖረው፤ ስለዚህ የአፈወርቅ ቤተሰቦች ለመባል አልደረሰንም፡፡ እኔና  ትዕግስት ግን ወደፊት አስተዳደጋችንን፣ ባህላችንን የሚያሳይ አንድ ዘፈን የመስራት ሃሳብ አለን፡፡
ብዙ አድናቂዎች እንዳሉህ ይታወቃል፡፡ አንተስ የማን አድናቂ ነህ?
ኢትዮጵያ የቅዱስ ያሬድ አገር ናት፡፡ በቤተክርስቲያን ስትቀርቢ ዜማ ማህሌትና የመሳሰሉት ያስደምሙኛል፡፡ ወደ ዘፈኑ ስትመጪ አገራችን ብዙ አንጋፋና ተሰጥኦ ያላቸው ድምፃዊያንን አፍርታለች፤ ከእነ ጥላሁን ገሰሰ ጀምሮ፡፡ እኔ ሞዴል ብዬ የያዝኩትና ወደ ሙዚቃው እንድገባ የተሳብኩት በኤፍሬም ታምሩ ነው፤ በጣም ነው የምወደው፡፡ ሙሉቀን መለሰን፣ ቴዎድሮስ ታደሰን፣ እነ ጸጋዬ፣ አረጋኸኝ… እንዲሁም ቀደም ሲል ወርቃማው ዘመን ላይ የነበሩ ብዬ የገለፅኩልሽን በሙሉ አደንቃለሁ፡፡ ቀደም ካሉት ፍሬው ኃይሉ የቤተ-ክህነት አይነት ድምፅ ስላለው እወደዋለሁ፡፡ ከወጣቶች ጎሳዬ፣ ብዙአየሁ፣ አብነት፣ ቴዲ አፍሮን አደንቃለሁ፡፡
ግጥምና ዜማ ድርሰት ላይ እንዴት ነህ?
ባለፈው አልበም ላይ “አፋር” የተሰኘውን ዜማ ሰርቻለሁ፡፡ “ማን እንደኔ ንገሪኛ”፣ “አባይ ወይስ ቬጋስ” እና “አንበሳው አገሳ” የኔ ዜማዎች ናቸው፤ ዜማ ላይ ምንም አልልም፡፡ ግጥም ግን ሰርቼ አላውቅም፡፡ በአሁኑ አልበሜ ላይ በዜማም አልተሳተፍኩም፤ ሁሉንም በሌሎች ባለሙያዎች ነው ያሰራሁት፡፡
በአዲሱ አልበምህ እስካሁን ከመጡት አስተያየቶች በጣም ያስደመመህ አለ?
ያው ብዙ አስተያየቶች ይመጣሉ፡፡ በአብዛኛው አድናቆትና ማበረታታት ናቸው፡፡ አንድ ሰው ግን ደውሎ “ለገና ለበግ መግዣ ያስቀመጥኩትን ብር የአንተን ሲዲ እየገዛሁ ለወዳጅ ዘመድ አድዬበታለሁ፤ በጉን አንተ ግዛልኝ” ብሎኛል፡፡ በጣም ገርሞኛል፡፡ አንዳንዴ ሰው ሲወድሽ እንዲህ ሁሉ ያደርጋል፡፡ ሌላው ችሎታህን በአሁኑ አልበም ላይ በአግባቡ ተጠቅመሃል የሚል አበረታች አስተያየት ነው፡፡
ታዲያ ምን አሰብክ… በጉን ትገዛለታለህ?
 እገዛለታለሁ፡፡ ይሄ ሰው እኮ ሲዲውን ሲገዛ ገንዘቤ በተዘዋዋሪ እኔው ኪስ ገብቷል፡፡ ስለዚህ ደስ እያለኝ እገዛለታለሁ፡፡
በመጨረሻስ….
በመጨረሻ እንግዲህ ይሄ አልበም እንዲህ አምሮ እንዲወጣ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላደረጉት የግጥምና ዜማ ደራሲዎች አመሰግናለሁ፡፡ የተለያዩ ጉዳዮችን በማስጨረስ ድካሜን ሲያቀልልኝ የነበረው የአቻሬ ጫማ ባለቤት (አቻሬ) ሳላመሰግነው አላልፍም፡፡ አቀናባሪ ሙሉጌታ አባተና ኤልያስ መልካ፣ እህቴ ትዕግስት አፈወርቅን፣ ማርታ ዘለቀን፣ አህመድ ተሾመንና ሌሎችም በመዘንጋት ስማቸውን ያላነሳሁትን ሁሉ በጣም አመሰግናለሁ፡፡ የሙዚቃው ኢንዱስትሪ በደከመበት በአሁኑ ወቅት ከጎኔ ሆኖ የክብር ስፖንሰር የሆነኝን ዳሽን ቢራንና የኤሌክትራ ሙዚቃ ቤት ባለቤትን አቶ ተሾመ ፀጋዬን እንዲሁም በአስተያየት እየኮተኮተ ያሳደገኝን የኢትዮጵያን ህዝብ በጣም አመሰግናለሁ፡፡ እግዚአብሔር ለሁሉም ብድሩን ይክፈልልኝ እላለሁ፡፡ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች እንኳን የገናን በዓል በሰላም አሳለፋችሁ፤ መጪው የጥምቀት በዓል የምትደሰቱበት ይሁን እላለሁ፤ አመሰግናለሁ፡፡

Published in ጥበብ

ባለፈው ረቡዕ የኢየሱሥ ክርስቶስ ልደት (ገና) በኢትዮጵያውያን ክርሥቲያን ምዕመናንና  በመላው ኢትዮጵያውያን ዘንድ ተከብሮ አልፎአል፡፡
ገና፡- የጌታ ልደት ነው፤ የጌታ ኢየሡሥ ክርሥቶሥ ልደት፡፡ የገና ራሥ ደግሞ ለክርሥትና ሃይማኖት መከሠትና እውን መሆን ምክንያት የሆነው በክርሥትና የመለኮት ሊቃውንት የቤተ ክርሥቲያን ራሥ የሚሠኘው ኢየሡሥ ክርሥቶሥ ነው፡፡ ኢየሱሥ ክርሥቶስ፡- አዳኝ ጌታ ብርሀን የንጋት ኮከብ…መሆኑን በእምነትም በእውቀትም መናገር ይቻላል፡፡ እርሡ ራሡ መፅሐፍ ቅዱስ ላይ፡- እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ…ይላል፡፡ በሌላ ሥፍራ ደግሞ፡- እኔ መንገድ እውነትና ህይወት ነኝ…ብሎ ራሡን ይገልፃል፡፡
ከአንድ መቶ ዘጠና ሥምንት ዓመታት በፊት በእኛ በ1809 በጥንታዊቱ ፋርሥ ወይ ፐርሺያ በአሁኒቱ ኢራን ሺራዝ ከተማ አቅራቢያ የተወለደውን በኋላ ላይ ለእግዚአብሄር መልዕክተኝነት የእግዚአብሔር ክብር በእርሡ ላይ የሚመጣውን ሁሴን ዓሊ ሚርዛ (ን)፤ ሙሥጠፋ የሚባል ባህታዊ እመንገድ ላይ አግኝቶት፡…አንተ የእውነት ብርሀን ነህ፤ አንተ የመመሪያ ፀሀይ ነህ፤ ራሥህን ለሌሎች ግለፅ…ነው ያለው፡፡
በዚህ በዛሬው ዘመን በዓለማችን ላይ ካሉ ሃይማኖቶች ሁሉ ብዙ ተከታዮች ያሉት ክርሥትና ነው፡፡ የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ብቻ እንኳን ከአንድ ቢሊዮን በላይ ክርሥቲያን ምዕመናን እንዳሏት ከሚያረጋግጡት ጥናታዊ መረጃዎች፡- Man Kind’s Search For God (የሠው ልጅ እግዚአብሔርን ለማግኘት ያደረገው ፍለጋ) በሚል ርዕስ በእንግሊዝኛ እና በሌሎች ሰላሳ ሶስት ቋንቋዎች የተፃፈው መፅሀፍ አንዱ ነው፡፡ የክርሥትና ሃይማኖት በተከታይ ምዕመናን ብዛት እዚህ አሀዝ ላይ ለመድረሥ ሁለት ሺህ ዓመታት ተጉዙአል፡፡ ይሄ ገለፃ:- ኢየሡሥ ክርስቶስ የተወለደው ከሁለት ሺህ ዓመታት በፊት መሆኑን ያሣያል፡፡ ኢየሡሥ ክርሥቶስ ሲሰቀል በምድር ላይ መቶ ክርስቲያኖች እንኳን አልነበሩም፡፡ ደቀ መዛሙርቱና ጥቁት ሴቶች ብቻ ናቸው አብረውት የነበሩት፡፡ አሁን ከአንድ ቢሊዮን በላይ ተከታይ ምዕመናን አሉት፡፡
መሰረታዊ የሆኑ የክርስትና ሃይማኖት አውደ ዓመቶች ሁሉ የኢየሱስ ክርስቶስን ህይወት ህያው ክንዋኔዎች መነሻና መድረሻ (መሰረት) ያደረጉ ናቸው፡፡ ገና፡- ልደቱ ነው፤ ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተልሄም በከብቶች በረት ውስጥ የተወለደበት እለት፡፡ ስቅለት፡- ስቅለቱ ነው፤ ኢየሱስ ክርስቶስ በጎለጎታ ጌተሰማኒ ቀራንዮ መስቀል ላይ የተሰቀለበት ዕለት፡፡ ጥምቀት፡- ጥምቀቱ ነው፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ዕድሜው ሰላሳ ዓመት በሆነ ጊዜ በዮርዳኖስ ወንዝ በመጥምቁ ዮሐንስ አጥማቂነት የተጠመቀመበት፡፡ ፋሲካ፡- ትንሳኤው ነው፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ከተሰቀለ ከተቀበረና ሶስት ቀናት በመቃብር ውስጥ ካደረ በኋላ ሞትን ድል አድርጎ የተነሳበት ዕለት፡፡ መሥቀል፡- ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት እውነተኛው መስቀል ያለበት ስፍራ የት እንደሆነ ፍንጭ የተገኘበት ወይም ምልክት የታየበት ዕለት ነው፡፡ ይኸውም እንዲህ ነው፡- ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል ከሶስት መቶ ዓመታት በላይ ቆሻሻ ሲከመርበት ከኖረ በኋላ ንግስት እሌኒ መስቀሉን ከተቀበረበት የቆሻሻ ክምር ውስጥ ለማውጣት በችቦ ብርሃን ታግዛ በትክክል፤ መስቀሉ ያለበትን ስፍራ ለማወቅ ፍለጋዋን ጀመረች፡፡ መስከረም አስራ ሰባት ቀን የችቦው ጭስ ሽቅብ ወደ ሰማይ ወጣ፤ ከዚያም ቁልቁል ወደ ምድር ከተመለሰ በኋላ ሰገደ፡፡ ንግስቲቱ ጭሱ የሰገደበትን ስፍራ ማስቆፈር ጀምራ አንድ መቶ ሰባ ሁለት ቀናት ከፈጀ ቁፋሮ በኋላ መጋቢት አስር ቀን መስቀሉ ተገኘ፡፡
ከክርስቶስ ልደት በፊት ታህሳስ ሃያ ዘጠኝ ቀን የተወለዱ አዱኒስን ወይንም አዱንያስን የመሳሰሉ ሌሎች ኃያላት መኖራቸውን ዳቪንቺ ኮድ የተሰኘው መፅሀፍ በገፆቹ አስፍሮአል፡፡ እንዲሁም ከክርስቶስ ልደት በኋላ ከዘጠኝ መቶ ዓመታት በፊት የኖረውና ከአንድ ድንጋይ ከአስራ አንድ ያላነሱ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ያነፀው ኢትዮጵያዊው ቅዱስ ንጉሥ ጠቢብ ላሊበላ የተወለደው በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የልደትቀን ነው፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ፡- ፍፁም ሰው፤ ፍፁም አምላክ ነው … ይላል ክርስቲያናዊ የመለኮት እውቀት፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ በኖረባቸው ዓመታት መለኮታዊ ክብሩን፤ አምላካዊ ባህሪውን የሚገልፁ በርካታ ተግባራት አከናውኖአል፡፡ አጋንንትን ማውጣት የሞተውን ማስነሳት ፈውስ ተአምራት … እነዚህና የመሳሰሉት የመለኮታዊ ክብሩ ሰብዕና ገላጮች ናቸው፡፡ በጎነት ፍቅር፣ እውነት፣ ርህራሄ፣ ደግነት፣ ቅንነት፤ ግልፅነት፣ ቀጥተኝነት፣ ቅድስና፣ ንፅህና … እነዚህና የመሳሰሉት ደግሞ የአምላካዊ ባህሪው ነፀብራቆች ናቸው፡፡ ክርስቲያኖች እግዚአብሄር ሰውን በአምሳሉ ፈጠረው … ሲሉ፤ ከባህሪው አጋራው ማለታቸው ነው፡፡ ኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ ሁለት ቁጥር ሰባት ላይ፡- እግዚአብሔር አምላክ ሰውን ከጭቃ አፈር አበጀው፤ በአፍንጫውም የህይወትን እስትንፋስ እፍ አለበት፤ ሰውም ህያው ነፍስ ያለው ሆነ … ይላል፡፡ ከእግዚአብሔር የወጣው ወደ ሰው ገባ ማለት ነው፡፡ እርሱም የእግዚአብሔር ባህሪ ነው፡- ህያውነት፣ እውነት፣ እውቀት፣ በጎነት፣ ደግነት፣ ርህራሄ፣ አዛኝነት እና የመሳሰሉት፡፡ ትንቢተ ኤርሚያስ ምዕራፍ አንድ ቁጥር አምስት ላይ፡- በሆድ ሳልሰራህ አውቄሃለሁ፤ በማህፀን ሳለህ ቀድሼሃለሁ፤ በህዝብ ላይ ነቢይ አድርጌ ሾሜሃለሁ … ሲል፡- በዚህ ማህፀን ውስጥ ከመፀነስህ በፊት በእኔ ውስጥ ህያው ሆነህ ነበርክ ማለቱ ነው፡፡
*          *          *
ዘኬዎስ ቁመቱ በጣም አጭር የሆነ ቀራፂ ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስን ለማየት ፈልጎ ቁመቱ አጭር ከመሆኑ የተነሳ መሲሁን የሚከተሉት ብዙ ህዝቦች እንዳይጋርዱት ኢየሱስን ለማየት ይቻለው ዘንድ ዛፍ ላይ ወጣ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በዚያ ሲያልፍ፡- ዘኬዎስ ብሎ ጠራው፡፡ ና ከዚያ ዛፍ ላይ ውረድ፤ እኔ ዛሬ በአንተ ቤት ምሳ እበላለሁ … አለው፡፡ ዘኬዎስ እንደዚያን ቀን ተደስቶ አያውቅም፡፡ እርሱ የፈለገው፡- ኢየሱስን ለማየት ነው፤ ኢየሱስ ግን ዛሬ ከአንተ ጋራ እሆናለሁ … አለው፡፡ ዘኬዎስ እንደ ህንቦቃቅላ ህፃን እየፈነደቀ፡- ዛሬ ለዚህ ቤት መዳን ሆኖለታል … አለ፤ የተበደርኩት እንኳ ቢኖር አራት እጥፍ አድርጌ እከፍላለሁ ….፡፡ የዘኬዎስ መሻት፡- ኢየሱስን ማየት ሆኖ ሳለ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ምሳውን ከዘኬዎስ ጋር በዘኬዎስ ቤት ለመብላት ፈቀደ፡፡ ዘኬዎስን አከበረ፡፡ እናም ወደ ዘኬዎስ ቤት ገባ፡፡ የዘኬዎስን የልብ መሻት አይቶ እርሱ ደግሞ ይበልጡን አብዝቶ አከበረው፡፡ በዚህም ለዘኬዎስና ለቤቱ መዳን ሆነለት፡፡
በዚህን ጊዜ አንዲት ሴት ተንደርድራ ወደ ዘኬዎስ ቤት ገባችና በብልቃጥ የተሞላውን አልባጦሮስ ሽቶ ብልቃጡን ሰብራ ኢየሱስ ክርስቶስ እግር ላይ አፈሰሰችው፡፡ መጫሚያውን ደስ የሚልሽቶ ቀባችው፡፡ እግሮቹ ላይ ተደፍታ እንደ ጥቁር ወርቅ በሚንተገተግ ውብ ፀጉሯ እግሮቹን አበሰች …፡፡ የዚህችን ሴት ሁለንተናዊ አድራጎት የተቃወመውን አንድ ሰው፤ ኢየሱስ፡- ተው! … አለው፡፡ አንተ ለእግሬ ውኃ አልሰጠኸኝም፤ እርሷ ግን እግሮቼን በሚያውድ ሽቶ አበሰች…
ብዙ ሺህ አጋንንት ሰፍረውበት በመቃብር ቤት ውስጥ ጠላት ዲያቢሎስ እያጎሳቆለው የሚኖር ሰው አለ፡፡ ልክ ኢየሱስን እንዳየው በላዩ ላይ የሰፈሩት ሺህ አጋንንት መታወክ እና መንጫጫት ጀመሩ፡፡ ወደ ገደል እንዳትከተን ሲሉ … ኢየሱስን ለመኑት፡፡ ከኢየሱስ ክርስቶስ ሁለንተና እና ከዓይኖቹ ውስጥ የሚወጣው ኃይል ወደ ሰውዬው በገባ ጊዜ፤ ከሰውዬው ውስጥ አጋንንት መውጣትጀመሩ፡፡ ሂዱ ከዚህ ሰው ውጡና ወደነዚያ አሳሞች ግቡ … ብሎ ኢየሱስ ክርስቶስ በኃይል ገሰፃቸው፡፡ አጋንንቱ ሰውዬውን በለቀቁት ጊዜ ፊቱ በደስታ ነደደ፤ ተፍለቅልቆ በራ ….፡፡ የዓሳማው መንጋ በአጋንንቱ ታመሰ፡፡
አንድ፤ ልጅ የታመመበት መቶ አለቃ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ መጣና፡- ልጄ ታሞአል፤ አንተ ብቻ ቃልህን ልቀቅ፤ ልጄ ይድናል! … አለው፡፡ ኢየሱስም፡- በሰላም ወደ ቤትህ ሂድ፤ ልጅህን ድኖ ታገኘዋለህ፤ እምነትህ አድኖሀል … ሲል መለሰለት፡፡ የመቶ አለቃው ቤቱ ሲደርስ ልጁ ከደዌው ተፈውሶ እንደ እንቦሳ ጥጃ ሲፈነጭ አገኘው፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ ከስፍራ ስፍራ በብዙ አጀብ ሲንቀሳቀስ አንዲት አስራ ስምንት ዓመት ሙሉ ባለማቋረጥ ደም ሲፈስሳት የኖረች ሴት በአጀቡ መሃከል ተጋፍታ ጨርቁን ነካች፡፡ ሲፈስሳት የኖረው ደም ወዲያውኑ ቀጥ አለ፡፡ መፍሰሱን አቆመ፡፡ የአሥራ ስምንት ዓመት ደዌ በቅፅበት ተመታ፡፡ ቀጥ፡፡ በዚህን ጊዜ ኢየሱስ ማነው የነካኝ … አለ፡፡ ማንም አልነካህም … አሉት፡፡ ኃይል ከእኔ ወጥቷል … የነካኝ ሰው አለ፤ አላቸው፡፡
ኢየሡሥ ክርሥቶስ በቤተመቅደስ በማስተማር ላይ እያለ፤ አይሁድ፡- ጋለሞታ ናት…ያሏትን ሴት ትልልቅ ጓል ይዘው ሢያሣድዷት ሴትዮይቱ እየሸሸች ወደ ቤተመቅደሡ ገባች፡፡ ጓል ይዘው የሚያሣድዷትም ሠዎች ተከትለዋት ገቡ፡፡ ኢየሡሥ ክርስቶስ የሆነውን ሁኔታ ሁሉ አጢኖ ጐንበሥ ብሎ ምድር ላይ ፃፈና ሴትዮይቱን ወደ ተከተሉት ጓል የያዙ አሣዳጆች እያየ፣ ከናንተ መሃከል ንፁህ የሆነው ሠው በዚህች ሴት ላይ የመጀመሪያውን ጓል ይወርውር…አላቸው፡፡
በዚህን ጊዜ አሣዳጆቹ ከኋለኞች እስከ ፊተኞች ፊታቸውን አዙረው መሠሥ ብለው ከቤተመቅደሱ እየወጡ ሄዱ፡፡ ሴትዮይቱ ብቻዋን ቆማለች፡፡ ኢየሡሥ፡- አንቺ ሴት እምነትሽ አድኖሻል፤ ደግመሽ እንዳታጠፊ፤ በሰላም ወደ ቤትሽ ሂጂ…ብሎ አሠናበታት፡፡
እነዚህ እስከዚህ የቀረቡት መወሣቶች የሚገልፁት ከኢየሡሥ ክርስቶስ መለኮታዊ ክብሮችና አምላካዊ ባህሪያት መገለጫ የሠብዕና ክፍሎች ጥቂት ሠበዞች የመምዘዝ ያህል ነው፡፡
*        *       *
ለአገሬ ለኢትዮጵያ ክርስቲያን ምዕመናን፤ ለመላው ኢትዮጵያውያን እና ለመላው ዓለም ክርስቲያኖች ያለኝን የሚደነቅ ፍቅር በተጌጠ ክብር ለመግለፅ፤ እንኳን ለዘንድሮው የገና በዓል በሠላም አደረሰን ለማለት፡፡ ለብርሃን ክብር፤ ለኢየሡሥ ክብር፤ ለክርሥትና ክብር፤ ለአምላክ ክብር፤ ለኢትዮጵያ ክብር፣  ለህዝቦች ክብር፤ ይህ ተፃፈ፡፡ እነሆ፡- የገና ራሥ፡፡
ሠላምዎ ይብዛ! በፍቅር!
Soli Deo! Gloria!  
 

Published in ጥበብ

ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከተጠናቀቀ በኋላ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጦርነቱን መግለጽ የሚችል የሥነ-ግጥም ውድድር ተካሂዶ ነበር፡፡ አያሌ ገጣምያንም በቋንቋ ውበት የተራቀቁበትን አያሌ ቅኔያት ዘረፉ፡፡ ብዙ ሺ ታዳሚያን በተሰበሰቡበትም ዳኞች ተሰይመው… ግጥሞችን መፈተሽ ያዙ፡፡ ገጣሚ “ያሸንፍልኛል” ያለውን ግጥም እየያዘ መድረኩን ነገሰበት፡፡ ሶስት አሸናፊዎች እኩል በመውጣታቸው እነሱን መለየት ግድ ሆነ፡፡ ስለዚህ ተጨማሪ ግጥሞች እንዲያቀርቡ ተደረገ፡፡ ቅፅበታዊ በነበረው የመለያ ውድድር አንዱ ባለቅኔ አሸነፈ፡፡ ግን እንዴት?
አንደኛው ተወዳዳሪ ያቀረበው ግጥም ከሌሎቹ የተለየ ነበር፡፡ ማይክራፎኑን ይዞ የመድረኩ መሀል ላይ ዝም ብሎ ቆመ፤ ትንፋሹ እንኳን አይሰማም፡፡ ይኼኔ ታዳሚው መበሳጨት ጀመረ … “ምን እንደ ጅብራ ይገትረዋል… ግጥሙን አያነብም?!” አለ፡፡ እሱ ግን አሁንም ዝም እንዳለ ነው … ጉርምርምታዎች ሲበዙ … ከዳር እስከ ዳር የከባድ መሳሪያና መብረቅ ቅልቅል የሚመስል ድምጽ በማይክራፎኑ ለቀቀበት … “ዷ! ዷ! ዷ!” የታዳሚዎቹ ቀልብ ተገፈፈ … ደነገጡ፡፡ ለጆሮ ታምቡር የከበደ ጩኸት ነበር፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ ከመጀመሪያው ባነሰ ሰዓትና ድምፅ ሁነቱን ደገመው፡፡ ከዚያም ለሶስተኛ ጊዜ ባነሰ ድምፅ ደገመውና መድረኩን ለቀቀ፡፡ አሸናፊ ሆኖም ሽልማቱን ታቀፈ፡፡
አንድ ገጣሚ ከሌላው የሚለየው በፈጠራ ክህሎቱ፣ በሐሳብ ልቀቱ፣ በቋንቋ እርቀቱና አርቅቆቱ ነው፡፡ ገጣሚ በላይ በቀለ ወያ “እየሄዱ መጠበቅ” በተሰኘው የግጥም መድበሉ መግቢያ ላይ የግጥምን ምንነት በተመለከተ ምርጫዎች ይሰጠናል፡፡ ሁሉም ምርጫዎች ግን “ግጥም በቃ ግጥም ነው!” የሚል አንደምታ ያላቸው ናቸው… ይህ የእሱ አተያይ ነው፡፡
የአይናችንን ሥርዓተ እርግብግቢት … የልባችንን ሥርዓተ ምት… ብናስተውል፣ ረቂቅና ቅንብሩም ከጥበብ በላይ የሆነ ኃይል ያለው ነው፡፡ ጥበብ ከመጋረጃ ጀርባ ያለን የተደበቀን ምሥጢር ፈልፍሎ የሚያወጣ… የተሰወረን አዚም ማርከሻ የሚቆፍር .. የጠፋን መንገድ የሚጠቁም … ሁሌም የሚኖር ሕያው ጉልበት ነው፡፡ ጎበዙ ገጣሚ ቴዎድሮስ ፀጋዬ፤ በ“ነፍሰጡር ስንኞች” የግጥም መድበሉ  “ባለፀጋው” በሚል የከተባት ግጥም እንዲህ ታትታለች …
ባለጸጋው
ትንሽ ሰጥቶ
ብዙ አትራፊ
ነጋዴ እኮ ነው ገጣሚ፣
ለሚጭረው ጥቂት ስንኝ
ቢሊዮን አይነት ፍቺ የሚሰጥ ስላለው እልፍ ተርጓሚ፡፡
ለአንዲት ግጥም አንባቢያን እልፍ ትርጓሜ ሊሰጧት እንደሚችሉ ሲነግረን ነው፡፡ ባለቅኔና ጸሐፌ ተውኔት ጋሼ መንግስቱ ለማ ደግሞ፤ “ሸጋ ግጥም ጥሩንባ አያሻውም፤ ባይሆን ትሬንታ-ኳትሮ እንጅ!” ብለው ኳኳቴ በበዛበት ቦታም ጥሩ ግጥም ጆሮ ጎትቶ ስሙኝ እንደሚል አስረግጠዋል፡፡
ወደ ድግሳችን ስናመራ፣ በግጥም መድበሉ ላይ የማቀርበው የግል ምልከታዬን እንደሆነ ከወዲሁ  ለመግለፅ እሻለሁ፡፡ “እየሄዱ መጠበቅ” ከሚለው  ርዕስ እንጀምር፡፡ “እየሄዱ መጠበቅ” ማንን? ለምን? የት ድረስ? ምን ያህል ጊዜ? ገደቡስ? እኒህን ጥያቄዎች ይዤ የሽፋኑን ምስል ስመለከት በግራ በኩል ተጠቅልሎ የተኛ ድርብ ቀለም ያለው እባብ የሚመስል የጫማ ገመድ፣ መሃል ላይ ደግሞ እግሩን አንቧትሮ እርምጃ የሚቆጥብ ሰው የመሰለ የተጠላለፈ የጫማ ገመድ አስተዋልኩ፡፡ ሆኖም “እየሄዱ መጠበቅ”ን የሚያህል ሀሳብ በዚህ ምስል ተገልጧል አልልም፡፡ ለወደፊቱ ስዕሉ ቢቀየር የሚል ሃሳብ አለኝ፡፡
46 ግጥሞች የያዘችው “እየሄዱ መጠበቅ”፤ በ65 ገጾች ትጠናቀቃለች፡፡ “ማነው?” ባዩ የመጀመሪያው ግጥም ሲሆን “ማነው ደግሞ ዛሬ ጀምበር ከጠለቀች ከደጃፌ ቆሞ በሬን የሚመታ/ትሆን እንደሆነ፣ የፀባዎት ጌታ” በማለት ይጀምራል፡፡ የበሩ መንኳኳት “ርቦኝ ቤትህ መጥቼ አላበላኸኝም… ጠምቶኝ ቤትህ መጥቼ አላጠጣኸኝም” ከሚለው የእምነት ሃሳብ ጋር የተቆራኘ ይመስለኛል፡፡
“ደግሞስ እስኪ አስበው፤ ሎሌ ሆነው ሳሉ፣
ምን ይሉት ድፍረት ነው፤ በሻገተ እንጀራ ጌታን መቀበሉ፣” …
ሁለተኛዋ ግጥም ከማጠሯ መጐጠሯ…ዓይነት ናት… “የኋላው ባይኖርም … ” ትሰኛለች፡፡ በፈጣሪ ቁጣ የምትጠፋን ሀገር
እየዞሩ ማየት ጥፋት እንደነበር
 ሲነገር የሰማ ቤተሰቡን ይዞ
እንደሎጥ ያለ ሰው ከጥፋት ይድናል የኋላውን ሳያይ
ወደፊት ተጉዞ (ገፅ 10…)
ለማምለጥ ወደፊት መራመድን ጮሃ የምትጣራ ውድ ግጥም ናት!!
ሶስተኛዋ መንቶ ግጥም “እሱ እየሻከረ…” ትላለች፡፡ ይህ ደግሞ ሞረድ ወትሮስ ለስላሳ ነበርን? ብዬ እንድጠይቅ አስገድዶኛል … ባይሆን ሌሎችን ለመሳል ሲል አካሉ እየተሸራረፈ እየለሰለሰ ሊሄድ ይችላል፡፡ የተወጠረበት ሃሳብ ቢስተካከል (በእኔ እይታ) ብዙ ግጥም ነች!
“የአንዱ ሰው ህይወት ሞረድን ይመስላል
እሱ እየሻከረ ሌላውን ይስላል … ትላለች፡፡
“ተረትና ምሳሌ” (ገጽ 17) የምትለዋ ግጥም ምርጥ ናት፡፡ እንዲህ ያለግጥም ሺህ ቢገጠም ማንስ ይጠላና!
ሞኝና ወረቀት
የያዘውን አይለቅ ለሚባለው ተረት
ምሳሌው እኔ ነኝ
አንቺን ብቻ ይዤ የያዘኝን ሁሉ የማልመለከት፡፡
ቀጣዩዋ ግጥም የመጽሐፉ የጀርባ ሽፋን ላይ የሰፈረች ስትሆን ብቻዋን መጽሐፍ የመሆን አቅም ያላት ናት፡፡ “ፍጥነትና ነጻነት” ትላለች፡፡
አልጋ ባልጋ ሆኖ የጥንቸሎች ፍጥነት፤
ፍጥነት ከተባለ፣
በዔሊዎች ጫንቃ፤ ራሱን ያልቻለ፤
ግዙፍ ድንጋይ አለ…
(ስርዐተ ነጥብ ከራሴ) ራሱን መቻል ያቃተው ድንጋይ ምንድነው? ኤሊን ተጭኖ ምን አምጪ እያላት ይሆን? እነጥንቸል፤ እንደ ኤሊ ድንጋይ ቢጫናቸው ምን ይገጥማቸው ነበር? በሳል … ፍልስፍናው ተፈልፍሎ የማያልቅ ግጥም  ነው፡፡ የዘመን ፍዳ ትከሻውን ያጎበጠው ሰውን ምስል ይከስታል፡፡
“የወረኞች ወሬ” የምትለዋ ግጥም ጭራሽ ባትካተት ጥሩ ነበር … እንደነ “አበሻ ቀጠሮ”ን፣ “እንቅልፍና ንጉሥ”ን መከተብ የቻለ ብዕር፤ “የወረኞች ወሬ”ን መፃፉ “የባለቅኔ ብዕር ዥንጉርጉር” ያሰኛል፡፡ “እንቅልፍና ንጉስ” የሚለውን ግጥሙን እንየው፡-
የደቀ መዛምርቱ መሪ በታንኳ ላይ ሳለ
ክርስቶስ ላፍታ ተኝቶ
አልቀው ነበር ባይቀሰቅሱት
ሞገድ
ማዕበል ተነስቶ
ለካስ ላፍታ ያህል ንጉስ ካንቀላፋው
ቀስቃሽ ሰው ከሌለ ህዝብ ነው ‘ሚጠፋው፡፡
የመጨረሻው ገጽ ላይ ያለችዋ “የሐበሻ ቀጠሮ” የተሰኘች ግጥምም ጥልቅና ድንቅ ናት፡፡
ከዚህ ውጭ ያለውን እንግዲህ እናንተው ተወጡት፤ በግጥሞቹ ተብሰልሰሉበት፡፡
(አዘጋጁ፡- ከዚህ በላይ የቀረበው የግጥም መፅሃፍ ቅኝት፣ በማህበራዊ ድረገፅ ላይ በወጣ ውድድር በአንደኝነት አሸንፎ የተሸለመ መሆኑን ጠቅሰው አዘጋጆቹ የላኩልን ነው፡፡ ፅሁፉ በዝግጅት ክፍሉ የአርትኦት ስራ ተደርጎለት የወጣ ነው)

Published in ጥበብ

(በእውቀቱ ስዩም)

በሰላላው መንገድ
የትየለሌ እግር፣ እንደ ሊጥ ባቦካው
ጸአዳ ጣትሽን ፣ጉድፍ እንዳይነካው
ማጡን እየዘለልሽ
ዳጥ ዳጡን እያለፍሽ
ጤዛ የወረረው ዛፍ እየተደገፍሽ
ትንሽ ስትመጭ
ብዙ ስታዘግሚ
ሁለቴ ተራምደሽ፣ አስሬ ስትቆሚ...
ለተደናገረው ፣መንገድ ስትጠቁሚ
የተላከ ሕጻን ፣አስቁመሽ ስትስሚ…

እኔ ስናፍቅሽ
እኔ ስጠብቅሽ
እንደ ጉድ ተውቤ
ላማልልሽ ጥሬ
በጆንትራ ዘይቤ
ጠጉሬን አበጥሬ
ጅማት እያጠበቅሁ፣ጅማት እያላላሁ
የገዛ ከንፈሬን ፣ቀርጥፌ እየበላሁ፡፡
ስጠብቅሽ በጣም
ምስልሽ ነው እንጂ አካልሽ አልመጣም፡፡

ባይኖቼ ስፈልግ
መስኮት እከፍትና
ሌላ ነው የሚያልፈው ፣በሰፊው ጎዳና
ያው ገጣባ አህያ፣ያቻት ድኩም በቅሎ
በግ እየጎተተ፣አለፈ ቆለኛ
ቅርጫት ያጎበጣት ፣ሚስቱን አስከትሎ
ያውና ድሀ አደግ ፣መንገድ ዳር የተኛ
የተጎነጎነ፣የሣር አምባር መስሎ፡፡
ባይኖቼ ሳማትር ፣መስኮት እከፍትና
ሌላ ነው የሚያልፈው፣ በሰፊው ጎዳና፡፡

ሁሉም ተለውጦ
ያ ገጣባ አህያ፣ ጸጉር አቆጥቁጦ
ያች ድኩም በቅሎ ፣ሰጋር ፈረስ ቀድማ
ቆለኛው ሰውየ፣ ሙክት በጉን ሽጦ
ለሚስቱ ነጭ ሻሽ ፣ለሱ ሸራ ጫማ
በትርፉ ሸምቶ
ሁሉም ከሄደበት ፣ቀንቶት ተመልሶ
ሁሉም ከድቀቱ፣ በወግ ተፈውሶ
እኔ ብቻ ቀረሁ፡፡
መንገድሽ ረዝሞ፣ ባሳብ እያሳጠርሁ፡፡
አንቺን እየናፈቅሁ
አንቺን እየጠበቅሁ
ጅማት እያላላሁ፣ ጅማት እያጠበቅሁ፡፡

Published in የግጥም ጥግ
Page 12 of 18