Saturday, 02 July 2016 13:20

የናይጀሪያው መሪ ልዩ ጠባቂ ከቦኮ ሃራም ጋር ይገናኛል በሚል ታሰረ

Written by 
Rate this item
(4 votes)

የአየር ሃይል አዛዡና ሌሎች ባለስልጣናትም በ74 ሚ. ዶላር ሙስና ተከስሰዋል

   የናይጀሪያው ፕሬዚዳንት ሙሃመድ ቡሃሪ ልዩ ጠባቂ የሆነው ሃሰን አሚኑ የተባለ የአገሪቱ የደህንነት አባልና ሌሎች ለፕሬዚዳንቱ ቅርበት ያላቸው የደህንነትና የጦር ሃይል አባላት አገሪቱን በሽብር ከሚያምሰው ጽንፈኛው ቡድን ቦኮ ሃራም ጋር ንክኪ አላቸው በሚል ተጠርጥረው ባለፈው ረቡዕ አቡጃ ውስጥ በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸው ተዘገበ፡፡
የአገሪቱ መንግስት የደህንነት ልዩ ግብረ ሃይል ለፕሬዚዳንቱ ቅርበት ያላቸውን ግለሰቦች የጀርባ ማንነትና ድብቅ አጀንዳ በመመርመር ላይ እንደሚገኝ የዘገበው ናሽናል አኮርድ ኒውስ ድረገጽ፤ይሄው የፕሬዚዳንቱ ጠባቂና የደህንነት አባላትም ከአሸባሪው ቡድን ጋር የድብቅ ግንኙነት እንዳላቸው በመረጋገጡ መታሰራቸውን ገልጧል፡፡ግለሰቡና ግብረ አበሮቹ ከቦኮ ሃራም ጋር ግንኙነት እንዳላቸው መረጋገጡንና በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተከትሎ፣ ሽብርተኞች በፕሬዚዳንቱ ጠባቂዎችና ለቤተመንግስቱ ቅርበት ባላቸው ግለሰቦችና ሰራተኞች አማካይነት ጥቃት እንዳይፈጽሙ ለመከላከል የተጠናከረ ክትትል እየተደረገ መሆኑም ተነግሯል፡፡ የፕሬዚዳንቱ ጠባቂና የደህንነት አባላቱ ከቦኮ ሃራም ጋር ግንኙነት እንዳላቸው መረጋገጡ፣ አሸባሪ ቡድኑ ከሽምቅ ውጊያ ባለፈ ምን ያህል እስከ ቤተ መንግስቱ የሚደርስ የጥቃት ሰንሰለት እንደዘረጋ ያመላክታል ተብሏል፡፡በተያያዘ ዜናም፣ የቀድሞው የናይጀሪያ አየር ሃይል አዛዥና ሌሎች ሁለት የጦር ሃይል ባለስልጣናት በሚሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር  የህዝብ ገንዘብ ለግል ጥቅማቸው አውለዋል በሚል ተከስሰው ፍርድ ቤት መቅረባቸውን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል፡፡ የቀድሞው የአገሪቱ የአየር ሃይል ላይ አዛዥ ማርሻል ጃኮብ ቦላ አዲጉን እና ሌሎች በቁጥጥር ስር የዋሉት ባለስልጣናት በድምሩ 74 ሚሊዮን ዶላር የህዝብ ገንዘብ መዝብረዋል በሚል ነው የተከሰሱት፡፡

Read 1662 times