ይሄ ዘፈን በረጅም ዘመን ሂደት ውስጥ አልፎ ለአዲሱ ትውልድ ሲደርስ ግርምት የሚያጭር ሆኗል፡፡ ምክንያቱም የዶሮ ዋጋ ከአንድ ብር በታች እንደነበር ዘፈኑ ይጠቁማላ! በዚህ ላይ ዶሮ አንድ ብር ማውጣቷ እንደ ተአምር መቆጠሩ በራሱ ተአምር ነው፡፡ የዛሬውን የዶሮ ገበያ በቅጡ ያውቀዋልና የዚያ ትውልድ አቀንቃኝ አሁን መጥቶ ቢያይ ምን ይሰማው ይሆን? ሲል ይገምታል፡፡ ከአሥር ብር ያልበለጠ የነበረ የዶሮ ገበያ አምና በአሥር እጥፍ ተመንጥቆ መቶ ብር ገብቶ ነበር፡፡ የዘንድሮ ዘመን መለወጫ የዶሮ ገበያ እንዴት ሆኖ ይሆን?
የዋጋ ምጥቀት እንደተረት ሲያወሩት የማይታመን መሆኑ አብቅቷል፡፡ አያት የልጅ ልጆቹን ኮልኩሎ የሚተርተው የእሳት ዳር ወግ አይደለም፡፡ አንድ የስምንት አመት ልጅ በእድሜው ያየውን የዋጋ ለውጥ ቢያወራ በራሱ እንደመናፍስት ገድል ብዙ ተአምራት የተካተተበት ይሆናል፡፡ ያንኑ የስምንት ዓመት ልጅ አስቡት፡፡ ከሁለትና ከሦስት ዓመት በፊት ኬክ በስንት ብር ይበላ ነበር? ከ2 ብር እስከ 2 ብር ከሃምሳ፡፡ አሁን እነዛ ኬኮች በቁመና ተሸማቅቀው ስንት ብር ገቡ? ከስምንት ብር እስከ አስር ብር፡፡ በእነዚህ አጭር አመታት የታየው የዋጋ ንረት በአራትና አምስት እጥፍ አሻቅቧል ማለት ነው፡፡ ቀደም ሲል በነበረው የተረጋጋ ህይወት በዚህ መጠን ዋጋ የሚያሻቅበው ከትውልዶች መተካካት በኋላ ነበር፡፡ የዋጋ ለውጡን ከአዛውንቶች በስተቀር አነፃሮ የሚደርስበት የአዲስ ትውልድ አባል አይኖርም ነበር፡፡ ጥቂትም አሮጌው ሲያወራ አዲሱ ምራቁን ቢውጥ ነው፡፡ ከረር ካለም ቢወቅስ ነው፤ እንደዚህ...
ያኔማ ያኔ ምን ያርጉ
ያፍ ተረት እያስመሰለ፣ ጊዜ ቢያርቀው በህጉ
ሌላ ነው የድሮ ወጉ፣ ልዩ ነው ሞትና ሠርጉ፣
ነገር ከርሞ የዘጋ፣ ትውልድን የሚዘነጋ
ሌላ ነው የድሮ ወጉ
በድንጋይ ዳቦ ነበረ፣ በያኔ ዘመን በደጉ
መኖርን አንጠፍጥፈዋት፣ አራግፈው እነሱ ኖሯት
በጮማ እያላመጡ፣ በማር ጠጃቸው አጠቧት
እንገር ወተቷ ጠቡና ከቅቤአቸው ጋር ፉት አሏት
መኖርን እነርሱ ኖሯት፣
ሳቋንም ጨርሰው ስቀው፣ ሙጥጥ አርገዋት ቦረቁ
ትራፊያቸውን ቆጣጥረው፣ ዘጉብንና ጠለቁ
ምናለ ታዲያ ምናለ!...
በጠፍ በረሃ ማሳ ላይ፣ እኛኑ ዘርተው ሲያበቁ
ምናለ በኛ ባይስቁ፣ ምናለ ባይሳለቁ፡፡
...
(ግጥሙ የመስፍን አሸብር መሆኑን በመጥቀስ እንለፍ)
ሊታመን በማይቻል ፈጣን የኑሮ ውድነት ውስጥ ሆነን ነው አዲሱን ዓመት የምንቀበለው፡፡ ዋጋው ሁሉ እንደ ሮኬት ለመመንጠቅ የተበጀ ይመስላል፡፡ ከትናንቱ ዋጋ ጋር የዛሬው ምጥቀት ሲነፃፀር ሰውነት በሥጋት ይጨርሳል፡፡ ከትናንት ወዲያ ስንት የነበረው ሸቀጥ ትናንት ስንት ገባ? ዛሬስ? ነገስ? ዋጋ እንደ እድሜ እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ እንደማይሄድ ተደምድሟል፡፡ ምን ይሄ ብቻ? እንደ ተፈጥሮ ሂደት ሁሉ የሰው ልጅ በዋጋ ንረቱ ሂደት ውስጥ ጣልቃ መግባት የማይችል አድርጐ ማሰብ ተጀምሯል፡፡
በአመት በአል ምድር ስነተርካችሁ ዝም ትላላችሁ? ለዚያውም እንደ ውሃ ወቃጭ ትርፋችን ሁሉ ..እምቦጭ!.. በሆነበት ዘመን? በወሬ እንኳን ዘና እንበል እንጂ፡፡ እኔ የምላችሁ ከዚህ ከዋጋ ንረት ጋር ተያይዞ አንድ ትእዛዝ ተላልፏል አሉ፡፡ የዋጋ ተመን እንዳይመስላችሁ፡፡ የከሸፈ-ጥይት ይተኮሳል? ይልቅዬ ነገሩ ሌላ ነው፡፡ ከ1997 ዓ.ም በፊት የነበሩት ዋጋዎች ካለመታመናቸው የተነሳ የፎክሎር ዲፓርትመንት የትውፊት ኮርስ ማስተማሪያ አድርጓቸዋል አሉ፡፡ ከተካተቱት ውስጥ...
..ክትፎ በሐምሳ ሳንቲም ተበላ፣ በግ በአንድ ብር ከ50 ሣንቲም ታርዶ ቆዳው በሁለት ብር ተሸጠ፣ ቀይ ወጥ በ25 ሣንቲም ተወደደ ተብሎ ድንፋታ ተደመጠ፣ የበሬ ሽንጥ በአንድ ብር ተገዛ፣ እንቁላል በአንድ ብር ሃያ ተሸጦ ሁለት ተመረቀ፣ ኩንታል ጤፍ በአስር ብር ተዋውሎ ሲፈጭ ማኛው ውስጠ ጥቁር ሆኖ አነታረከ፣ የቤት ሠራተኛ በወር ሃምሣ ሣንቲም ተከፈለ... ይህም ሆኖ ሕዝቡ ..ኑሮ በጣዕር.. የሚል ብሒል ያዘወትሩ ነበር፡፡..
ከዚህ ጋር ተያይዞ አንዳንድ የጥንት ዘፈኖችም የትውፊቱ አካል ተደርገው ተማሪዎች እያዳመጧቸው ለፈተና እንዲዘጋጅ ተደርጓል አሉ፡፡ ከመሰል ዘፈኖች መካከል የአለማየሁ እሸቴ ይገኝበታል፡፡
የአስር ሳንቲም ቆሎ ክርሽም አደርግና
የአስር ሳንቲም ጠላ ጭልጥ አደርግና
ተመስገን እላለሁ ኑሮ ይባልና፡፡
አይወራ የለ! አንዳንዶቹ ወሬዎች ደግሞ ጥቂት ግራ ያጋባሉ፡፡ እነዚሁ ከ1997 ዓ.ም በፊት የነበረው የዋጋ ለውጥ እጅግ አዝጋሚ ከመሆኑ የተነሳ የዝግመተ ለውጥ (Evolution) ሊቆች እንዲያጠኑትና ቻርት እንዲያዘጋጁ ታዘዙ አሉ፡፡ ኧረ እንደሚወራው ከሆነ የየዘመኑን ዋጋ ስም ሰይመውለታል አሉ፡፡ ዋጋ እሬክተስ፣ ዋጋሚንዲተስ፣ ዋጋዎሎፒቲከስ...
ከ1997 ዓ.ም ወዲህ ያሉ የሸቀጣ ሸቀጥ ዋጋዎችን እንኳን ለማጥናት ለማየትም በማዳገታቸው ..የከተማ ሽምቅ ውጊያ.. ተብለዋል አሉ፡፡ ብቻ እንደሚወራው ከሆነ የመከላከያ ኢንጂነሪንግ ዋጋዎቹ የመጠቁበትን ስልት ለሮኬት ሳይንስ፣ ስለምጠቀምበት እንዳጠናቸው ይፈቀድልኝ ብሏል አሉ፡፡ እንግዲህ አሉ ነው፡፡
የዘንድሮ የዋጋ ተመን እንኳን ለሸማቹ ለነጋዴውም አዳግቷል አሉ፡፡ ቀን የፃፉትን የዋጋ ዝርዝር ሌሊት ሲሰርዙና ሲደልዙ ማደር እራሱ ሌላ ሥራ ሆኖባቸዋል ነው የሚባለው፡፡ ለዚህ ችግር አንድ ዘዴ የዘየዱት የምግብ ቤት ባለቤት የአጂፕ ነዳጅ መቅጃ ማሽን በርካሽ ገዝተዋል አሉ፡፡ ..የአንድ ሊትር ዋጋ.. የሚለው ላይ ..የምግብ ዋጋ.. ብለው በመለጠፍ ሌሊት እጀታውን ጨብጠው ያድራሉ አሉ፡፡ ጠዋት ቁጥሩ ያረፈበት ዋጋ የዕለቱ ምግብ መሸጫ ይሆናል አሉ፡፡ እንግዲህ አሉ ነው፡፡ አሉ ደግሞ ብዙ ቦታ ያደርሳል፡፡ ይሄን አሉ ትተን ..አላሉን.. እናውራ እስኪ፡፡
የህብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት የንግድና ቱሪዝም ሚኒስቴር ለ1969 ዓ.ም አዲስ ዓመት የዕቃዎች ዋጋ ዝርዝር አውጥቶ ነበር፡፡ የመሸጫ ዋጋው የጅምላና የችርቻሮውን አንድ ላይ የያዘ ነው፡፡ ለዚህ ዘመን ሸማች ለትንግርት የሚታዩ ዋጋዎች ተደርድረዋል፡፡ የስንዴ ዱቄት (አንደኛ ደረጃ) የችርቻሮ መሸጫ ዋጋው 0.60 ሣንቲም ነው፡፡ እንዳያደናግር በአሐዝ ልፃፍላችሁ፡፡ ስድሳ ሳንቲም ብቻ፡፡ የዱቄቱ ሁለተኛ ደረጃ በዋጋ ዝቅ የሚለው 5 ሣንቲም ብቻ ነው፡፡ በዚያ ዘመን ደረጃውን ከፍ አድርጐ ለሚያስብ ሰው የታሸገ ዱቄት ቀርቦለታል፡፡ ሆሚኒስ ስንዴ ዱቄት ፋሪስ ሱፔርየር (የታሸገ) ይላል፡፡ ስሙ ነው ከባድ፡፡ ዋጋው 0.60 ሣንቲም ነው፡፡ ይሄም አይመጥነኝም ካለ ቼሬአሊያ ዱቄት አለልዎት፡፡ የታሸገ፣ የመጨረሻው ባለ ሦስት ኮከብ፣ ደረጃ ያለው ነው፡፡ ዋጋውን እችላለሁ ካሉ 0.70 ሣንቲም ነው፡፡ እንግዲህ በዱቄት ከዚህ በላይ መቀናጣት የለም፡፡
ዘመናዊነት ለሚሰማው ቤተሰብ ፓስታና ማካሮኒ ቀርቧል፡፡ የፓስታውን ዋጋ እንመልከት፡፡ በፆምም ሆነ በሌላ እንቁላል የሌለው S¬ የመረጡ ከሆነ ግማሽ ኪሎ ፓስታ 0.55 ሣንቲም ነው፡፡ ምናባቱ፣ ለማን ብዬ ነው ሆዴን የምበድለው? ሊሉ ይችላሉ፡፡ እንቁላል ያለው ቀርቦሎታል፡፡ የዋጋውን ልዩነት ግን ልብ እያሉ፡፡ 0.60 ሣንቲም ነው፡፡ አንድ ኪሎ ስኳር 0.75 ሣንቲም፣ የልብስ ሣሙና (100 ግራም) 0.15 ሣንቲም፣ ሮል የሳሙና ዱቄት (50 ግሪም) 0.30 ሣንቲም... መሆናቸውን ብቻ ነግረን እንለፍ፡፡
ሰው መቼም በልቶ ጠጥቶ አያበቃም፡፡ መልበስና መጫማት ይፈልጋል፡፡ የልብሱ ይቆየንና የጫማውን ዋጋ እንይ፡፡ ፕሊምሶል ሸራጫማ 3 ብር ከ40 ሣንቲም ነው፡፡ ይሄ ሸራ ጫማ ዋጋው የናረው ሰማያዊ በነጭ (ተፈላጊ) ቀም ስላለው ነው፡፡ ይሄንኑ ጫማ ቡና ጥቁር ቀለም ከመረጡ በ 2 ብር ከ45 ሣንቲም ያገኙታል፡፡ ያንኑ ሸራ ጫማ የክረምት ቦት ከፈለጉ ደግሞ 5 ብር ከአምስት ሳንቲም ነው፡፡ ታዲያ ይሄ ዋጋ እንደ ትውፊት ተቆጥሮ መማሪያ ቢሆን ይነሰው? በሉ መልካም አዲስ አመት - እቴ!!