Saturday, 10 November 2012 16:45

ሀሳብ፣ወይንስ ሀሳብ፣ወይንስ ሃሳብ

Written by  ሌሊሣ ግርማ
Rate this item
(0 votes)

ጥያቄው ኦባማ አሸነፈ ወይንም ተሸነፈ ሳይሆን…ኦባማ ራሱ ሰው ነው ወይንስ ሃሳብ ነው?...የሚል ነው (ሆነብኝ)፡፡ ከአንድ የሃሳብ ወዳጅ ጋር ቁጭ ብለን ስናወራ ፈጠጥ ያለ ሃሳብ አመጣብኝ፡፡ ሃሳብም እንደ አይን ወይንም እንደ ችግር ይፈጥጣል፡፡ “አሁን እግዚአብሔር እንደ ሌላው ነገር በሚጨበጥ በሚለካ የእውነታ ደረጃ አለ…ወይንስ የለም?” አለኝ፡፡ ሃሳብ ሲፈጥ በሃሳብ መልሶ ማፍጠጥ ወይንም አይንን መስበር ነው መፍትሔው፡፡ ማፍጠጥ ይሻላል ብዬ ተፋጠጥኩት፡፡ እግዚአብሔር አለ ወይንስ የለም?... የሚለው ጥያቄ ፋሽኑ ያለፈበት እንደሆነ ፋሽን ያለፈባቸው የምዕራብ ፈላስፎች እንኳን ያውቁታል፡፡ “እግዚአብሔር” የሚል ስም ሰይሞ፤ መልሶ ደግሞ “የለም” ማለት ራስን በራስ እንደመፃረር ስለሚቆጠር፤ ጥያቄው ዋጋ አይኖረውም፡፡ የተሰየመ ስም ሁሉ የሚወጣው… ላለ ነገር ነው፡፡ ለሌለ ነገርማ ስያሜም አይበጅም፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር አለ፡፡ 

የወዳጄ ጥያቄ ግን:- መኖር እና አለመኖሩ በመለኪያ ይረጋገጣል?... ወይንስ አይረጋገጥም፤ ነው፡፡ መለኪያችን አምስቱ የስሜት ህዋሳቶቻችን ብቻ ቢሆኑ ኖሮ…የምናየው፣ የምንቀምሰው፣ የምንነካው፣ የምናደምጠው እና የምናሸተው ብቻ ይኖራል፤ ከዚህ ውጭ ያለው ከመኖር ይሰረዛል፡፡ አይናችን ብቻውን አያይም፡፡ ከአንጐል ጋር መተባበር አለበት፡፡ አንጐል የስሜት ህዋሳቶቻችንን (የስሜት ዳታ) ተቀብሎ ወደ ሃሳብ ይቀይረዋል፡፡ ሃሳቡ በመግለጫ አማካይነት ተመልሶ ወደ ውጫዊው እውነታ ይፈስሳል፡፡ እንግዲህ፤ በአጭሩ ያለው ነገር ሃሳብ ነው፡፡ የሰው ልጅ የስሜት ህዋሳቱን (ዳታ) ወደ ሃሳብ ካልቀየረ መረዳት አይችልም፡፡ እግዚአብሔር ብቻ ሳይሆን ሰውም ራሱ ሃሳብ ነው፡፡ ስለዚህ፤ ይህ ያፈጠጠብኝ የወዳጄ ሃሳብ ቀለል ብሎ ሲቀመጥ:- “ሃሳብ በተጨባጭ በሚለካ በሚቆጠር ደረጃ አለ ወይንስ የለም?” የሚል ነው፡፡ “ለምን እንደዚህ ትለኛለህ?” ብሎ ግልፍ አለው ወዳጄን፡፡ “በሬ ሃሳብ አይደለም ስለዚህ በሬ አለ ወይንም የለም? ብለህ ልትጠይቀኝ አትችልም”በሬው አለ፡፡ ግን በሬው ጥብስ፣ ቅቅል ወይንም ክትፎ ሆኖ እንድመገበው ያስቻለው ሃሳብ ነው፡፡ ከእለታት አንድ ቀን በሬውን ለመብላት አንዱ የጥንት ሰው አሰበ፡፡ በሃሳቡ አማካኝነት በሬውን ከራሱ የምግብ ፍላጐት ጋር ማቆራኘት ባይችል በሬው አይኖርም ነበር፡፡ ወይንም የበሬ ትርጉም ከዝሆን አይለይም ነበር፡፡ (እሱ በውጭ ግልፍ ሲለው እኔ በውስጥ መልስ መስጠት መብቴ ነው) ወደ እግዚአብሔር እውነታ ስንመጣ የምንመለከተው ሰውን ነው፡፡ በብዙ ባህሎች የተለያየ እምነቶች አሉት ሰው፡፡ እምነቱን በእምነት ደረጃ ብቻ ሳይሆን ወደ ህይወት አገልግሎት ገብቶ ሲኖርበት ይታያል፡፡ እግዚአብሔር እንደራሱ/ለራሱ ሳይሆን በሰው ልጅ ሃሳብ እና በሰው ልጅ ባህል ውስጥ አለ፡፡ የለም ማለት አይቻልም፡፡ ሀሳቡ/እምነቱ ሃይማኖት ሆኖት ከባህሉ/ሃሪሶቱ ጋር ተቆራኝቶ በተጨባጭ እየኖረበት ያለ ሃሳብን የለም የሚል ሰው…ራሱ ለራሱ የሌለ ነው፡፡ …ድርሰት ወይንም የፈጠራ ጥበብ ተጨባጩን እውነታ ከሚመስለው ይበልጥ ሃሳብን ይመስላል፡፡ ከሰው ገለፃ ስለወጣ፡፡ የአክሱም ሀውልት ከሌላው የመልክአ ምድር የአለት ገጽታዎች የሚለየው… በውስጡ በያዘው ሃሳብ ብቻ ነው፡፡ ሀውልቱን በሃሳብ ቅርጽ ለመጥረብ ሰው አስፈልጓል፡፡ በሰው እጅ የሚቀረጽ ተፈጥሮ የሰውን እንጂ የተፈጥሮን ሃሳብ አያንፀባርቅም (ሰው የተፈጥሮ አካል መሆኑን እንዳላወቅን ችላ እንበለው! አይን ሌንስ ብቻ ሆኖ ብርሃን ወደ ሰውኛ ትርጉም ባይቀየር…ሰው ከመስታወት የተለየ ባልሆነ ነበር፡፡ እግዚአብሔር አለ ወይ? ብሎ መጠየቅ ሰው ራሱ አለ ወይ ብሎ እንደመጠየቅ ነው፡፡ ሰው (ዴካርት) ራሱን በራሱ… በህልውና መኖሩን ለማረጋገጥ ሞክሮ የደረሰው “I think therefore I am” የሚል ድምዳሜ ላይ ነበር፡፡ “በህይወት መኖሬን ያረጋገጥኩት ስለማስብ ነው” እንደማለት፡፡ ስለማሰብ እንደማውቅ ማወቄን እንጂ… ህልውናዬን ማረጋገጥማ አልችልም፤ ይላል ሳርተር፡፡ ህልውናዬን ለማወቅ፤ በሌላ ማወቁን የሚያውቅ (Conscious) ህልውና መረጋገጥ አለበት ባይ ነው፡፡ “I am seen therefore I am” ግን በዚህም ተባለ በዚያ …ጉዳዩ ያለው ሃሳብ ላይ ነው፡፡ የእኔን ህልውና ሌላው የሚያውቅልኝ በሃሳቡ አማካኝነት ነው፡፡ ሃሳብን በሂሳብ ብንተነትነው እንኳን ውጤቱ ያው ሃሳብ ነው፡፡ሃሳብ በህልውና የመገኘታችን ሚስጥር ከሆነ፤ ሃሳቦች በሙሉ ህልውና ወይንም ከህልውና ጋር ቁርኝት አላቸው፡፡ ሃሳብ ባህልን ይፈጥራል፣ ሃሳብ አብዮት ያስነሳል፣ ሃሳብ የአባይ ግድብን ይገድባል፣ ሃሳብ ፈጠራን ይፈጥራል፡፡ ሃሳብ ውብ ወይንም አስቀያሚ መሆኑ… ስለመኖሩ ወይንም አለመኖሩ አይነግረንም፡፡ ሰይጣንም ሆነ እግዚአብሔር በስም የተወከሉ እለት መኖር ጀምረዋል፡፡ በሃሳብ የምናውቀውን በህልውና ላይ ማጣት አንችልም፡፡ ታሪክ በአጭሩ፤ የሃሳብ ታሪክ ነው፡፡ ምክንያቱም፤ ታሪክ ስለ ሰው ልጅ ስለሆነ፡፡ ስለሰው ልጅ ታሪክ ሲነሳ፤ በየትኛውም ዘመን፤ ታሪኩን የሚያስኬደው ሃሳብ ሲወለድ ሲያድግ እንደዚሁም መስራት ሲያቆም መታዘብ ይቻላል፡፡ የእውቀት እምነት “ሄሊኒዝምን” ከፈጠረ፣ የመለኮት እምነት “ሂብራይዝምን” ፈጥሯል፡፡ ሁለቱም ግን የሃሳብ ውጤት ናቸው፡፡ ግን እዚህ ላይ መጠንቀቅ አለብኝ፡፡ ሃሳብ ሞቶ ተግባር መስራቱን ሊጥል ይችላል፡፡…ከንፈራቸውን ሰንጥቀው ሰፋፊ ሸክላ በመክተት ባህላዊ የውበት መገለጫቸው የሆኑ ብሔረሰቦች፤ በመጀመሪያ ለከንፈራቸው መሰንጠቅ ምክንያቱ በባርነት ለሚሸጧቸው ሰዎች መልካቸውን አጥፍተው ለመታየት ነበር፤ የሚል ጥናት የነገረኝ ሰው አለ፡፡ ሃሳቡ ለተፈጠረለት ተግባር ውሎ እስከመጨረሻው ላይዘልቅ ይችላል፡፡ በሃሳብ ላይ ሃሳብ ሲታከልበት እና ሲደበላለቅ ታሪክም እውነተኛ ገጽታውን ያጣል፡፡ ስሜትን ከሃሳብ መነጠልም ሌላው አበሳ ነው፡፡ መነጣጠል የማይቻልን ነገር ለመነጠል መጣሩ አበሳው፡፡ አበሳው የሳይንስ እና እምነትን ያህል ርቀት የፈጠረ መስሎት ሊፈራገጥ ይችላል፡፡  ኦባማ በንግግሩ የሚያቀርበው ሃሳብን ነው፡፡ በተረፈ ሰውየው ያለ ሃሳቡ ምን እንደሆነ ማወቅ አይቻልም፡፡ ሃሳብ ህልውና አለው፡፡ ጥበብም ፈጠራ ብቻ ሳይሆን የሰውን ሃሳብ የያዘ ፈጠራ በመሆኑ፤ ህልውና አለው፡፡ እንግዲህ በተለያየ ገለፃ አማካኝነት በጥበብ ውስጥ የቀረቡ ሃሳቦች በሂደት ሃሳቦቻችን እና ህልውናዎቻችን ሆነው ቁጭ ይላሉ፡፡  በፊልም ላይ የሚተውኑ ገፀ ባህሪዎች ሃሳብን ተመስለው ነው ለተመልካች የሚቀርቡት፡፡ የሃሳቡ ምንጭ የተውኔቱ ፀሐፊ ሊሆን ይችላል፡፡ ተውኔት ፀሐፊውስ  ሃሳቡ የመጣለት አንድ ሃሳብን ከማስታወቂያ ሰሌዳ ላይ ተመልክቶ ቢሆንስ?…ሁሉም ነገር በአጠቃላይ ሃሳብ አለመሆኑን እንዴት ማወቅ እንችላለን? ሲንቀሳቀስ የምናየው መኪና የተንቀሳቀስ የመሰለን በሀሳባችን የእውቀት መንገድ እንጂ መኪናው ስለተንቀሳቀሰ እንዳልሆነ እንዴት ማረጋገጥ እንችላለን? “ከሚንቀሳቀሰው መኪና ጋር ተመልካቹን ማሰር ነዋ!” ብትሉኝ ትክክል ናችሁ፡፡ መሬት ላይ እያንፏቀቀ፣ እየጐተተ ሲወስደው በሃሳቡ ሳይሆን በተጨባጭ እንደሆነ ያውቃታል…ያኔ! ግን መንፏቀቁንም ያወቀው ያው በስሜት/ሃሳቡ ሲሆንስ?…የሚጐትተውን መኪናም የሰራው ከሃሳቡ አመንጭቶ ነው፡፡ እኮ የመኪናውን ፍጥነት በሌላ ውጫዊ መሳሪያ ቢለካም…መለኪያው መሳሪያም ከሀሳቡ የተፈጠረ ነው፡፡ …ሰው ውስጥ የሚገባውም የሚወጣውም ሃሳብ ነው፡፡…እና ለዚህ ቁጡ፣ እግዜርን በመለኪያ መሳሪያ የሚፈልግ ወዳጄ… ከላይ ያስቀመጥኩትን እንደመልስ በአፌ ሳይሆን በሃሳቤ አሰብኩኝ፡፡ ያሰብኩትን በጽሑፍ አሰፈርኩኝ፡፡ ጽሑፌም የሚነበበው… በሃሳብ ስለሆነ የምታነብቡ ሃሳብ ጭናችሁ ኑ!...ወይንም ሃሳብ ሆናችሁ፡፡

Read 3312 times