Saturday, 04 February 2012 12:55

“ራስ ምታት”ን እንዳነበብኩት

Written by  መልካሙ ተክሌ
Rate this item
(0 votes)

ዘወትር በመስታወት መልክዎን ሊመለከቱ ይችላሉ፡፡ አላዘወትርም ካሉም በጣም አልፎ አልፎ መመልከት አይቀሬ ነው፡፡ ከእለታት በአንዱ ቀን ግን የሚያዩት መልክ የሌላ ሰው ሆኖ ቢያገኙት ምን ያደርጉ ይሆን?

ለረዥም ጊዜ የተለየዎትን አለያም በሞት ያጡትን ሰው የሚመስል “ቁርጥ ራሱን” የሚባል አይነት ሰው ገጥምዎትም ይሆናል፡፡ የሚቻል ከሆነ በአደጋ ወይም በህመም የተጐዳ ፊትዎን ወይም ሌላ የአካልዎን ክፍል መቀየር የግድ የሚሆንበትም ጊዜ ሊያጋጥም ይችላል፡፡ የአጥንት ወይም የኩላሊት ቀዶ ሕክምና የመደረጉን ያህል እጅግ ውስብስቡ የአእምሮ ቀዶ ሕክምናም ይፈለጋል፡፡ እነዚሀ ሁሉ ይቻላሉ፤ እድሜ ለሳይንስ - ይለናል ባለፉት ጥቂት ወራት ለንባብ የበቃው የአስመሮም ወልደጊዮርጊስ የሳይንስ ልቦለድ መፅሐፍ፡፡

“የራስ ምታት” የተሰኘው ይሄ መፅሐፍ ሊደረጉ በሚችሉ፣ ወደፊት በሚመጡ የሳይንስ ምርምር ውጤቶች ላይ ብቻ ሳይሆን ሊያስከትሉ የሚችሉት ውጤት ላይ ተንተርሶ የተፃፈ ነው፡፡ኢትዮጵያ ተጠቃሽ የሆኑ የሳይንስ ልቦለድ የፃፉ ፀሐፍት ባይኖሯትም በዓለም አቀፍ ደረጃ ግን በርካታ ፀሐፍት አንቱ የተሰኙበትን የሳይንስ ልቦለድ መፃህፍትን አበርክተዋል፡፡ ከነዚህም አንዱ ፈረንሳዊው ደራሲ ዩል ቨርን ነው፡፡ ዩል ቨርን ‘Round The World In Eighty Days’ እና ‘Round The Moon’ የሚሉ ታዋቂ የሳይንስ ልቦለድ መፃህፍት አበርክቷል፡፡ የልቦለድ ሥራ እንደሆነ ቢታወቅም ታዲያ ኤልዛቤጥ ኮችሬን የተባለች ጋዜጠኛ ማድረግ የሚቻል ነው በማለት ተነሳች፡፡ የልቦለዱ ገፀባህርይ ከፈጀበት ቀን አምስት ቀን በማሻሻል አለምን ዞሬ እገባለሁ ያለችው ጋዜጠኛ፤ በ72 ቀን ከ6 ሰዓት ከብዙ መከራዎችን መቋቋም በኋላ ጉዞዋን ፈፅማለች፡፡ ዩሪ ጋጋሪ ወደ ጠፈር ከመምጠቁ በፊት፣ እነ አርምስትሮንግም የጨረቃን ምድር ከመርገጣቸው በፊት ሳይንስ ልቦለዶች ብዙ ተንብየው ነበር፡፡ በሕክምናው ዘርፍ ስለሚደረጉ ምርምሮችም በርካታ መፃህፍት ለአንባቢዎች ቀርበዋል፡፡ በዚህ ዘርፍ ተጠቃሽ ከሆኑት ውስጥ የኤች ጂ ዋልስ “Invisible Man” ተጠቃሽ ነው፡፡ የአስመሮም ወልደጊዮርጊስ “ራስ ምታት”ም በሕክምናው ዘርፍ ዓለም ምን ላይ ልትደርስ እንደምትችል የተነበየ መፅሐፈ ነው፡፡ ከትንቢቶቹ አንዳንዶቹ እየተፈፀሙ ያሉ ናቸው፡፡ ነገር ግን ሳይንስ ልቦለድ እንደ ሰርግ ቤት በግኝቶቹ የማስፈንጠዙን ያህል ግኝቶቹ በሚያስከትሉት ያልተፈለገ ውጤትም  የለቅሶ ቤትን ያህል አንገት ያስደፋሉ፡፡

አሜሪካ ለከፍተኛ ትምህርት የሄደው ዳዊት እዚያው እያለ በደረሰበት የመኪና አደጋ አእምሮው ሲቀር መላ አካሉ እንዳይጠገን ሆኖ ይጐዳል፡፡ ሆኖም የመሞቱ መርዶ ለቤተሰቦቹ ይመጣላቸዋል፡፡ እድሜ ለሕክምና ሳይንስ አካሉ ቢቀበርም እሱ ግን አልሞተም፡፡ መፅሐፉ ይዞ ከተነሳው የሕክምና ሳይንስ፤ የሰው ህይወትን መታደግ ዋነኛ ጭብጡ ቢሆንም ሰው ሞተ የሚባለው መቼ እንደሆነ ይጠይቃል፡፡ በተለምዶ ሰው ሞተ የሚባለው ነፍስና ሥጋው ሲለያዩ ነው፡፡ በነፍስና ሥጋ መኖር ለማያምን ሰው ሞትን ለማስረዳት መተንፈስ አቆመ፣ የደም ዝውውሩ ተቋረጠ ሊል ይችላል፡፡ ሆኖም መተንፈስ ካቆመ በኋላ ህይወት የሚዘራም ያጋጥማል፡፡

የዳዊት ከዚህ በጣም የተለየ ነው፡፡ እንደ ኢኮኖሚው ሁሉ በሕክምናውም የላቀችው አሜሪካ፤ ዘመኑ ያፈራውን ቴክኖሎጂ ተጠቅማ ዳዊትን እንደገና ነፍስ ዘርታበታለች፡፡ ነፍስ ዘርታበታለች፡፡ ዳዊትነቱን ግን ቢያንስ መጀመርያ ላይ እንኳን ሌሎች ራሱን በመስታወት ያየው ዳዊት አልተቀበለውም ነበር፡፡

“ባጋጠመው ችግር ምክንያት ቢሰማውም እንኳ ከመሞት ይልቅ ስለሚወዱት ቤተሰቦቹ ቢኖር ይሻላልና መኖርን ተስፋ አደረገ፡፡ ይበልጥ የመኖር ተስፋውን ያሳመረችለት ደግሞ ዶ/ር ባርባራ ነች፡፡ እንደምንም እየተንተባተበ በአደጋው ጊዜ አብሮት የነበረውን የጓደኛውን አብዱልን ሁኔታ ባርባራን ጠየቃት፡፡ ነገር ገን አስደንጋጭ መርዶ ሰማ፡፡ ያላየው ጉድ የመጣው ከመኝታ ክፍሉ ጋር ተለጥፎ ወደተሰራው ሽንት ቤትና ባኞ ቤት በቀስታ ነገሮችን እየተደገፈ እንደገባ ነው፡፡ በስተቀኝ ወደሚኘው የፊት መመልከቻ መስታውት ዘወር ሲል አስፈሪውን ምስል ፊት ለፊት ድንገት በማየቱ ሃይለኛ ድንጋጤ ተሰማው፡፡ እንደልብ በማያዘው አካል የህልም ሩጫ በሚመስል ሩጫ እንደምንም በጭንቅ ፊቱን አዙሮ በሮቦት አካሄድ ወደ አልጋው ሄዶ ደወሉን ደጋግሞ አጮኸው” (ገፅ 45)

ለምን እንደደነገጠ ለማወቅ መፅሐፉን ከመጀመርያ እስከ መጨረሻ ማንበብ ያስፈልጋል፡፡ የድንጋጤው መነሾ ሰዎችን ለስደት፣ የስለላ ድርጅቶችን ለፍጥጫ፣ የሕክምና ተመራማሪዎችን ለተጨማሪ ራስምታት ዳርጓል፡፡ ለውሳኔ የሚያስቸግር አማራጭም የቀረበበት ነው፡፡

መፅሐፉ በሦስተኛ መደብ ተራኪ ጀምሮ በዚያው ተራኪ ቢያልቅም አብዛኛውን ክፍል የሸፈነው የተራኪው ታሪክ አካል ያልሆነ ሁሉ አወቅ ተራኪ (omniscient narrator) ነው፡፡ ሁሉ አወቅ ተራኪ ከመሆኑ አንፃር በመግቢያው አንድ ገፅ ከሁለት መስመር ምልልስ እና በመጨረሻ ገፅ ያለው አምስት መስመር ምልልስ አያስፈልግም ነበር፡፡ ማንኛውም አንባቢ ካለ ሁለቱ ክፍሎች መፅሐፉን ቢያነብ ከአጠቃላይ ጭብጡ የሚያመልጠው ነገር የለም፡፡ ክፍሎቹን ጨምሮ ቢያነብም የሚያገኘው ነገር የለም፡፡ “ራስ ምታት” ደካማ ግጭት ስላለው ታሪክ አይራመድም ለማለት አያስደፍርም፡፡ ሆኖም አፍን ሞልቶ ዘውጉ የልብ ሰቀላ ሳይንስ ልቦለድ ነው ለማለትም አይቻልም፡፡ ይህንን ከመፅሐፉ ማረጋገጥ ይችላል፡፡

እስከ ገፅ 139 ያነበበ ሰው፣ ዳንኤልና ባርባራ ሶደሬ ለምን እንደሚሄዱ አያጣውም፡፡ ሶደሬ ደርሰው ምን ይገጥማቸው ይሆን ከማለት ይልቅ በመዝናኛ ቦታው ብዙ ሰዎች ስለመኖራቸው፣ ስንት ሰአት እዚያ ደረሱ፣ ደብረዘይት ከአዲስ አበባ አርባ አምስት ኪሎ ሜትር ስለመራቋ ወዘተ ነው የሚነገረው፡፡ በልቦለድ አፃፃፍ አንድ ቦታ ወይም እቃ ወይም ጊዜ ሲወሳ ከአጠቃላይ ታሪኩ ጋር የሚገናኝ ምን ተደረገበት፣ ለምን መጣ የሚለውን መመለስ ካልቻለ ነው የሚሆነው፡፡ በቀጥታ እንደሚተላለፍ የሬዲዮና ቴሌቪዥን ዝግጅት “አሁን ልብሱን አወለቀ… ሰውነቱን ተለቃለቀ… ዘሎ ወደ መዋኛው ገባ…” መሆን አይኖርበትም፡፡ ከዚያ ይልቅ “ልብሱን አውልቆ ወደ መዋኛው ሊገባ ሲል እግሩ አልታዘዝ አለው…” ቢባል አንባቢ ከዚያስ እያለ በመጠየቅ ቀጣዩን የታሪክ ክፍል ያነባል፡፡

የአስመሮም ወልደጊዮርጊስ “ራስ ምታት” መፅሐፍ የህክምና ሳይንስ ሲመጥቅ የሰው ልጅ የጤና ችግሮች ይቃለላሉ፣ ግን መራቀቁ መሳቀቅ እና ራስ ምታት ያስከትላል በሚል ድምዳሜ የተፃፈ ነው፡፡ የመፅሐፉ ገፀ-ፅሁፍ (layout) ጥቅጥቅ ያለ ስለሆነ ለንባብ አይጋብዝም፡፡ ይህንን ተቋቁሞ ማንበብ የጀመረ ራሱን በውስጡ ካሉት ገፀ ባህርያት ጋር እያዛመደ እስከ መጨረሻው ይዘልቃል፡፡  ልቦለድ ከእለት ተእለት የቋንቋ አጠቃቀም የተለዩ ውብ ቃላትን በዒላማ ተኳሽነት የሚያሰማሩበት ነው፡፡ ውበቱ ሲጨምር ኢላማውን የመምታት አቅም ይጠነክራል፡፡ በዚህ መፅሐፍ የቋንቋ ኪናዊ ውበት እንደውም በዘገባ አፃፃፍ ላይ የሚዘወተሩ ቃላት የበረከቱበት ይመስላል፡፡

ለምሳሌ “እኔ ተማሪዎች እንደሚጠሉኝ አረጋግጫለሁ” (ገፅ 74) ይላል፡፡ ስለዚህ መፅሐፍ ድክመትና ጥንካሬዎች የሚነሱ ሌሎች ነጥቦች ቢኖሩም ዓላማዬ መፅሐፉን መተቸት ሳይሆን  ያላነበባችሁ እንድታነቡት በመሆኑ በዚህ ዳሰሳዬን ልቋጭ፡፡ 289 ገፅ ያለው “ራስ ምታት” በ43 ብር ለገበያ የቀረበ መጽሐፍ ነው፡፡

 

 

Read 3177 times Last modified on Saturday, 04 February 2012 12:59