አዲስ አድማስ ጋዜጣ ለአስራ አምስት አመታት ጨለማና ብርሃን እየሰነጠቀ ለመነበብ መብቃቱ የዋዛ እድሜ አይደለም። ልደታችንን ስናከብር ዳቦ በመቁረስና ወደፊት በመገስገስ ብቻ መቀንበብ አይመጥነንም፤ በፈጠራ ድርሰት ሶስት ምርጦችን መሸለምና ማበረታት ለጥበባዊ ተስፋም አስተዋፅዖ ነው። በግጥምና አጭር ልቦለድ የተሳተፉትን ሁሉ እናመሰግናለን። በሥነፅሁፍ እንቅስቃሴ የሆነ ደራሲ-ገጣሚ የተለመደውን ድንበር በመሻገር ብርቅ ጽሑፍ ለማጣጣም ይፈቅድልናል ብለን ብንጓጓ እንኳን፥ በውድድሩ ለመሳተፍ በማቅማማቱ ሳቢያ ተነጥቀናል --አይኖርም አትኖርም ብለን አንደመድምም። በአንፃሩ ግን ሲነበቡ የማይሰለቹ፥ ህይወትን አዛዙረን ምስጢሩን ለመቅሰም ያነቃቁን በግጥምም በአጭር ልቦለድም ሶስት ብዕሮች አሸናፊ ሆነዋል። ስድሳ ግጥሞች እና አርባ አራት አጫጭር ልቦለዶች ከምናባችንና ጥሞናችን ፈክተውም ተስለምልመውም ሶስቱ አጐንቁለው ፀደቁ።
የአጭር ልቦለድ ውጤት
አንደኛ የትዕግስት ተፈራ “ፀሐይ” ፤ ከደረት ፈልቃ ሣቅ መስላ የከበደች ጩኸት እያስታመመ በእናቱ ሞት ውስጡ የተመዘመዘ ግለሰብ፥ ጋቢ ደርቦ ለቀናት ባለመቆዘሙ ማኅበረሰቡ ተንሾካሾከበት። ደራሲዋ ድርጊትንና ሥነልቦናዊ ውስጠትን በመበርበር የእናትና የተፈጥሮ ፀሐይን ቅኔያዊነት በመገንዘብ ሳታንዛዛ፥ የጐርፍን ተምሣሌት እስከ ምትሀታዊ እውነታ -magic realism- ተሻገረችበት፤ ትረካዋ ይመስጣል።
አለመደማመጥ ሰውን ከእብደት ጠርዝ ሊያንፏቅቀው መቻሉ ያሳስበናል፤ የሌላው መታወክ ቀርቶ፥ የእጆቹ መንቀጥቀጥ እንኳን በቂ ምልክት ነው፤ የግለሰብን ሥነልቦናዊ መድፍረስ ለማጤን።
ሁለተኛ የፍፁም ገ/እግዚአብሔር “የዱበርቲዋ ጀበና”፤ በጉጉት የሚነበብ ብቻ ሳይሆን በቀበልኛ ቋንቋ የወረዛም ልቦለድ ነው። “ፍርሀት ሆድ ውስጥ ገብቶ፥ እንደ ቅቤ መግፍያ ቅል መናጡ” ያልገታው ገፀባህሪ፥ ደም እንዳይቃባ ለመካስ ጥማድ በሬውን የሸጠ ግለሰብ ይከታተላል። ለአድባር ቡና አፍልተው፥ ለሴት ዛራቸው የሚስጉት ዱበርታዊ ትረካውን ያበለፅጉታል። የኑሮ አጋጣሚ ሲያደናቅፍ ለፈጣሪ ከማደር በላቀ ለተውሳከ-እምነት መሸነፍ ከጀበና ዋልታ ዙሪያ ተጠንጥኖ መንደሩ ይታመሳል።
ሶስተኛ የሀውኒ ደበበ “በሩን ክፈቱልኝ”፤ የመንፈስ መታወክና ስጋት ከልቦናዋ ሰርገው ለመተንፈስ የሚከፈት በር ፍለጋ አንዲት ወጣት ታቃስታለች። በሶስት ጐረምሶች በአስራ ስድስት አመቷ የተደፈረች ልጃገረድ ለአመታት ተንገላታለች። ለትልሙ -plot- ቆምታ የስሜት ይሁን የቁሳቁስ ርዕስ እየተሾመ (እንባ፥ ዛሬ፥ ሙሽራ ቀሚስ ...) ሣይበተን የሚሰበሰብ ልቦለድ እንደ ግለታሪክ ወይም የእለት መዝገብ ይነበባል። ከመደፈር የባሰ ሰቆቃው እውስጣችን ዘቅጦ የሚታመሰው ዕዳ መሆኑን በማጤን ደራሲዋ እስከ መንፋሳዊ ጓዳ ዘልቃበታለች።
የግጥም ውጤት
አንደኛ የየማነ ብርሃኑ “አልቀርም መንኩሼ”፤ ዝምታን አላምጣ ተናጋሪውን ያገለለች እንስት ትሁን ተምሣሌት ያማሰለችው ህላዌ አልሰከነም። ቋንቋና ዘይቤው ጥልቀት ለግሰውት እስከ መንፈስ ዳርቻ ለመዝለቅ ስንኞች አልሰነፉም። ወንጌላዊ ቃና ለምድር ፍላጐት ፈረጠበት።
ሁለተኛ የደመረ ብርሃኑ “ሞልተዋል ብላቴና”፤ ሰሌዳ ዕውቀት የሚፈካበት የተወጠረ ዝርግነት ሳይሆን፥ በማድያት ተላልጦ መማርና መብሰል ይፋቁበታል። በሚነዝር ቋንቋ እየኮሰኮሰን፥ላልጠና አእምሮ ገጣሚው ተብሰክስኳል። የግል ቁዘማ ሳይሆን ለትውልድ መታመመ እንጂ።
ሶስተኛ የመዝገበቃል አየለ “ግፍ አይሆንም?”፤ ፈጣሪ ተወርዋሪ ኮከብን አፈፍ አድርጐ ከጅራቱ የብርሃን ዝሃ መዞ የውብ ሴት ሽፋል ከኳለበት በኋላ ከመንደራችን ብታጐጠጉጥ እንዴት በዝሙት እንከሰስ? ለሴት ሰውር ስፌታዊ ውበት አለመቅበዝበዝ እንዴት ይቻላል በማለት ገጣሚው ዘይቤና ምስል እያፈራረቀ ፈጣሪን ይሞግታል።
Published in
ጥበብ