ነገ፡-
ያራራቁንን መቶ ኪሎ ሜትሮች በፈጣኖቹ የመኪናው ጎማዎች ሽክርክሪት ስር እየጠቀለልኩ ወዳንቺ እከንፋለሁ፡፡ ናፍቆት ያሳበጠው ገላዬን ተሸክሜ እነዚያን የፎቅ ደረጃዎች መንታ መንታ እየተሻገርኩ በየእርምጃዬ ልክ ወዳንቺ እቀርባለሁ…….
የግንባሬን ላብ በክንዴ እየከላሁ፣ ያቀፍኩትን ስጦታ ለማበርከት እያመቻቸሁ፣ በኔና ባንቺ መካከል ያለውን ኮሪደር ጣጥሼ አልፋለሁ፡፡ የልቤን ፈጣን ምት ከቁብም ሳልቆጥር፣ ስለዛለ ገላዬ ላፍታም ሳላስብ፣ የውብ ገላሽን ማማርና የብቻ የጠረን ጣዕምሽን እያሰብኩ ድካሜን በናፍቆቴ አጣፋዋለሁ …….
እጣዬን የሚመስለኝን ቀዩን በርሽን በጉጉትና በጉጉት ደጋግሜ አንኳኳለሁ ……..
በሩን ቶሎ አትከፍቺም ……
በዚህም፣ ልቤ በጉጉት ልትፈርጥ፣ ቀልቤ በርሃብሽ ጠኔ ሊደባይ ምንም አይቀረውም፡፡ በናፍቆትሽና በሰቀቀንሽ ሲኦል ውስጥ ለድፍን ሁለት ደርዘን ሰከንዶች ተነክሬ ከተሰቃየሁ በኋላ በሩን ትከፍቻለሽ ……… !
ከዚያስ?
ከዚያ ……
“ውይ በናቲ ሞት! አንተው ነህ እንዴ?!” ትይኛለሽ - በልጅሽ እየማልሽ፣ ክንፉን ተሰብሮ እንዳልተሰበረ ለማሳየት ባየር ላይ እንደሚንደፋደፍ አሞራ ሆነሽ ……
ያኔ …….. አይሻለሁ! …….
ታላቁ ቅላትሽ ከፍም እያምታታ፣ ከፀሃይ እያጥበረበረ ይንቦገቦጋል ….. ታላላቅ ጡቶችሽ በለበስሺው ፒጃማ ውስጥ ሆነው ፋፍተው ይታያሉ ….. ጠብደሎቹ ጭኖችሽ በተራመድሽ ቁጥር ዳሌሽን እያውረገረጉ ውስጤን በሙቀት ያጥለቀልቁታል …… የሽንጥሽ ቅጥነትና ክበ’ት ምራቄን አድርቆ ጥምሽን ያረካልኝ ይመስል መቀነትሽን መሆን ያስመኘኛል ….. በዚህ መሃል አሎሎ አይኖችሽ የምስኪኖቹን አይኖቼን አከርካሪ በፍጥነት ሰባብረው የዕይታ አፅናፌን ከሽፋሽፍትሽ ዳርቻ በማንሳት በበርሽ ስር ምንጣፍ ላይ ይፈጠፍጡታል …..
ዕይታዬን እዚያው አርመጥምጬ ስረጋጋ፣ የአይኖቼን ብርሃን የእግሮችሽ ጣቶች ላይ አሳርፋለሁ ….. አቀላላቸው ….. አረዛዘማቸው ….. አደራደራቸው …… አወቃቀራቸው …… ሁሉ ነገራቸው ውብ፣ ውቦች ……
“አ ……… አዎ ….. ደህና ዋልሽ ፀደይ! እ…. አብርሃም ነው እንዳደርስልሽ የላከኝ” እየተርበተበትኩ የያዝኩትን ያደራ ዕቃ አስረክባለሁ ……
“ውይ አብርሽዬ … የኔ ጌታ! እሱ ግን ደህና ነው? ወይኔ ሲያም…ር! ውይ የኔ ቆንጆ፣ ባለፈው ስላወራሁለት እኮ ነው ዛሬ የላከልኝ! ምስኪን አብርሽ! ቆይ አሁኑኑ እደውልለታለሁ ……. አንተ አትገባም ታድያ?” ትይኛለሽ ….
“አይ ….. እቸኩላለሁ፤ ደህና ዋይ” ብዬሽ ለስንብት አይኖቼን ወዳይኖችሽ እልካለሁ ….
አይኖችሽ እኔን አያዩም፤ ይልቅ ከአለቃዬና ከባልሽ የተላከልሽን ስጦታ በፍቅርና በናፍቆት ሰክረው ያደንቃሉ …… የቀኝ እጅሽ ውብ ጣቶች የስጦታውን ጀርባ ይደባብሳሉ ……. ውብ ጡቶችሽ የስጦታውን ደረት ከደረቶቻቸው ጋር ለጥፈው ለስጦታውና በስጦታው ይጨመቃሉ …… የግራ እጅሽ ጣቶችም እንደቀኞቹ ሁሉ የስጦታውን ቀሪ ጀርባ ለማቀፍ ሲሉ የያዙትን የበር መዝጊያ ይለቁታል …… ያ ደም መሳይ በራችሁም “ጥዝዝዝዝዝ …..” እያለ ሄዶ በበሩ መቃን ላይ በሚጠብቀው ሽንቁር ስር ምላሱን ይወትፋል ……
በሩ ይጋርድሻል፡፡
ያኔ ……
እኔ ……
በቀስታ የፎቁን ደረጃዎች መውረድ እጀምራለሁ።
Saturday, 07 February 2015 13:38
ወደ ነገ የፍቅር ወግ
Written by አሸናፊ መለሠ (ashusheger@gmail.com)
Published in
ጥበብ