ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ በግጥሞቹ አንባቢን መመሰጥና መዉሰድ ችሏል። ፍካት ናፋቂዎች እና እዉነት ማለት የኔ ልጅ በተሰኙ ሁለት የግጥሞች ስብስብ ኮስታራ ጭብጦች በዉብ ቋንቋና ዜማ ተቀርፀዉ ያዉካሉ፤ ያወያያሉ። በዚህ ብዕሩ ለግጥም እጁን የሰጠ አልያም አልቀነበብ ያለ ጉዳይ በአጭር ልቦለድ ለማበልፀግ፥ ለመግራት መወሰኑ ለሚናፍቀን ተደራሲያን ስጋትም ጥርጣሬም ነዉ። አንደ ብርቅ ባለቅኔ ግጥሞቹን ችላ ብሎ በትረካ እየቀዘፈ ሳይመለስ በዚያዉ ይቀር ይሆን ? ወሳኙ ጥያቄ ግን አጭር ልቦለዶቹ የግጥሞቹን ጥልቀትና ጥበባዊ ዉበት ይመጥናሉ ወይ ? አንድ ብርቱ የልቦለድ ደራሲ በ“ያልተከፈለ ስለት” ምናባችንን ሲያንኳኳ አድምጠነዋል ወይስ እንደነገሩ ነዉ ? ዶ. በድሉ በመቀኘትም በመተረክም ሰምሮለታል። እርካታም ተስፋም ነዉ፤ በሁለቱም ዘዉጐች ምናልባትም በአብይ ልቦለድ [novel] ገና የሚያስነብበን የኑሮ ምስጢር ይኖራል።
ጊዜና ሰዉን የታከኩ ክስተቶች ጐምዝዘዉ ጣፍጠዉም የተደራሲን ልቦና እና የዕለት በዕለት ኮሽታዉን ለማፍጠንም ለመገደብም ይበቁ ይሆናል። ስምንት አጭር ልቦለዶች ናቸዉ፤ መቼታቸዉና ጭብጣቸዉ እጅጉን ይለያያሉ፤ በአንድ ጉዳይ ወይም አዉድ መታጠር መድንዘዝ አይመቸዉም፤ ከአንድ የዉሃ ጉድጓድ ብቻ አይቀዳም። ዛሬ፥ ትናንት በደርግ ዘመንና በመሳፍንት አገዛዝ ወቅት ለኑሮ መብሰክሰክ፥ በስልጣን የመቆየት አባዜ፥ ለቤተክርስትያንና ለአድባር የማደር ትንቅንቅ፥ ለመንፈስ የመገጣጠብ ክፋት ... ተጠላልፎበታል። ወሲብና ፍቅር የጣዕም ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ለባል ጓደኛ በስምምነት መዉለድ ሥነልቦናዊና ኅላዌ ቀዉሱ ያደናቅፋል። ረዘም የሚለዉ - በስድሳ ገፅ የተፍታታዉ ልቦለድ “ዉድቅትን በዉድቅት” ግለ ታሪክ ቢሆንም በአፃፃፍና ትረካ ጥበቡ ከሌሎቹ አይተናነስም።
በአማርኛ ልቦለድ ታሪክ በግልጥ ደራሲዉ የኖርኩትን ህይወት ነዉ የፃፍኩት ማለቱ ፈር-ቀዳጅ ነዉ። የእዉነተኛ ታሪክና የልቦለድ ድርሰት ወሰን የት ላይ ነዉ ? ... አንዳንዱ የተኖረ ህይወት የልቦለድ ድርሰትን ያህል እዉነትነት ያንሰዋል። አንዳንዱ ልቦለድ ድርሰት ደግሞ ከተኖረ ህይወት የበለጠ እዉነት ሆኖ ይገኛል። ህይወትና ድርሰት ሁነታቸው የተጣቀሰ፥ ድንበራቸዉ የተጣረሰ ነዉ። [ገፅ 121 ] ግለ ታሪክ ይባል እንጂ፥ ዶ.ዮናስ አድማሱና ዶ.ፈቃደ አዘዘ አድማጭና አሳብ ቀስቃሽ ሆነዉ በትረካዉ መካከል እየተናገሩ እና የዉድቅት እንቅልፍ ሳያሸልባቸዉ፣ ለእሳት ዳር የአባቶች ተረት ከልጅነት ስንቅ መጓጓትን እየተዋሱ ቢደምቅም፣ ጥሬ ታሪክ አይደለም። እንደፈሰሰ ሳይከረከም የሚያወጉት አይደለም። ዋናዉን ዶ.በድሉ የኖረዉን ከሞት ወደ እዉቀት የሽሽት ጉዞ ሌጣዉን ሳይሆን በሁለት ምሁራን እንቅስቃሴና መጠበብ ተርብም ታጅቦ፥ በመካከሉ በሽፍታዉ አዛዉንት ታሪክ፥ ወኔና ጭካኔ የተወጠረም ነዉ።
የአካባቢ ገለጣ፥ በጥንቃቄ መተረኩ እና የቋንቋዉ መሳጭነት በግለ ታሪክ ጥበት አያስቀነብበዉም። የደረሰን ታሪክ በአፃፃፍ ጥበብ ወደ ፈጠራ ድርሰት እንደ ማበልፀግ ነዉ። ሰዉ ከሞት አፋፍ ለመመለስ ሲዳክርና ለትምህርቱ ሲያድር -የወጣት በድሉ ታሪክ- በአንፃሩ ቀላል እንደነበር የምናጤነዉ፥ የአዛዉንቱን ሽፍታ ወደ ሞት የምንደርደር ተደጋጋሚ ሩጫና መብሰክሰክ ሲያስደምመን ነዉ። የተኖረም ይሁን፥ ምናብ የጫረዉ ታሪክ፥ የአጻጻፍ ክህሎቱ ነዉ ወደ ልቦለድ ጥበብ የቀላቀለዉ። “መስዋእት ፍለጋ” ወደ መሳፍንት ዘመን ያፈገፈገ ታሪክ ይምሰል እንጂ፥ ሁሉንም ዘመን የሚወክል ተምሣሌት ነዉ። ተደጋጋሚ የእንቅልፍ ቅዠት እዉነታን ተክቶ፥ ግለሰብ በፍርሃት ተሸብቦ፥ ሰዎች ውስጠታቸዉ ሲላላጥ ራስን እንደ መታዘብ ነዉ። ለስብስቡ ርዕስ የተመረጠዉ “ያልተከፈለ ስለት” ፖለቲካዊ ይዘት እንዴት ጥበባዊ ብስለት ሊወርስ እንደሚችል እና በዶ.በድሉ ክህሎት ደረቅ ጉዳይ ሲለሰልስ፥ ሲገራ እንደመምበታለን። ምርጫዉን ማን አሸነፈ ሳይሆን ሰዉ በፈቃዱ የጠየቅኩህን ከፈፀምክልኝ እምከፍልህ አለኝ ብሎ ለፈጣሪዉ ለታቦት ... ሲሳልና ቃል ሲገባ ድባቡና ገመናዉን ታክኮ መተረኩ ድንቅ ነዉ።
የሰፈር ሰዎች የግንቦት ልደታን ሲያከብሩ፣ እየተበላና እየተጠጣ ሊጨፈር ብቻ ሳይሆን ከታደሙት ጥቂቶቹ “ነፍሳቸዉ በየግል ተብሰልስሎታቸዉ ይናጣል”፤ ይህም ነዉ ልቦለዱን ከፍ ያደረገዉ። ልብስ ሰፊዉና አሮጌ ዕቃ እየጠጋገነ የሚኖረዉ ጓደኛሞች ናቸዉ። “የወዳጅነታቸዉ ጥልቀት ... ሁለቱም የግንፍሌን ነዋሪ ጓዳ ጐድጓዳ ፥ ገመናዉን ማወቃቸዉ ነዉ።” ለህሊና ወይስ ለጥቅም ወይስ ስለት ለመክፈል የምትቅበዘበዝ ነፍስ መሸሸጊያ ትነፈጋለች። ቅኔያዊ ርዕስ የታከለበት አጭር ልቦለድ “የህይወት ቅዳጆች”፣ ደራሲዉን የረጅም ጊዜ የአተራረክ ክህሎት የተካነ ያስመስለዋል። ተራኪዉ ሥራዉን ትቶ ለሁለተኛ ድግሪ እጅ አጥሮት እየተማረ ነዉ። ከተከራየዉ ቤት የሰፈሩን ሰዉ በመላላክ የምታገለግል ወይኗ አለች። “ገና አስር አመት ሳይሞላት እናቷንና አሮጊት አሳዳጊዋን የገፋች፥ በያለችበት የምታድር የመንደሩ ተላላኪ” “እሱ በዝርግ ሰሀን እያረመደ፥ እሷ በእጇ ጨምድዳ በጥርሷ እየቦጨቀች” ምሳቸዉን እንጀራ በሚጥሚጣ ተካፈሉ።
ወይኗ ከሰል እያቀጣጠለችለት ሳለ ስኳር የተገዛበትን ወረቀት ሲገላልጥ “በጥቁር እስክሪብቶ ጥቅጥቅ ተደርጐ ተጽፎበታል” ትረካዉን አንዲት ልጃገረድ ትረከበዋለች። “ንጽህናዬን አላስደፍር ብዬ ስሮጥ፥ የሚያባርረኝ የአያ ንግሩ ልጅ ጉግሳ፥ ሳር ጥልፎት ወደቀ። ሲወድቅ ጉቶ በደረቱ ተሰንቅሮ ኖሮ አፍታም ሳይቆይ ሞተ።” በዚህ ምክንያት ወደ አክስቷ ቤት ብትሸሽም አሁንም በሌላ ወንድ ላለመደፈር ባደረገችዉ ሙከራ አክስቷም የዋህነቷም ለእንግልት ይበቃሉ፤ ሴት መሆን፥ እጦት ታክሎበት ያስጠቃል። ዶ.በድሉ “የህይወት ቅዳጆች” ሲል ሰዉ በተለይም ህፃንና ወጣት ሴት ትልታይ፥ ቁራጭ፥ እራፊ ... አክላ ከኑሮ ለመላተም እጅጉን ሊከብዳት እንደሚችል፥ የንብረት የረባ ዘመድ አለኝታ መነፈግ የአዋቂንም ጉዞ እንዲሚያዳልጥ የተቀኘበት ነዉ።
ሶስት ታሪኮች በአንድ አጭር ልቦለድ የተወሳሰቡበት ነዉ። ይበልጥ ግን አንጀት የምትበላዉ ገና በአስር አመቷ መጠለያ አጥታ፣ ሜዳ ላይ እጣ ፈንታዋን የባዶ ድስት ህይወት ለመዉረስ የምትዳክረዉ ወይኒቱ ናት። ይህን የሚታዘበዉ ሥራዉን ትቶ ለድኅረ ምረቃ ትምህርት መስዋዕት እየከፈለ -እየተራበ- የሚያቃስተዉ ተራኪዉ ነዉ። ከሰፈሩ የእንጀራ ጋጋሪዋን ልጅ፥ ብሎም መቅዘፍያዋን የተቀማች ህፃን ፥ ሌላዉንም እያጤነ አያበቃም። ሳይጠብቀዉ፥ ከሩቅ ይሁን ከቅርብ መንደር ከስኳር ጋር አብሮ የተጠቀለለ የአንዲት ልጃገረድ የድንግልና ታሪክ አስተዉሎቱን ያደፈርስበታል። ቀና ብሎ ነገን በጉጉት ሳይሆን በስጋት የመጠበቅ አባዜ ይመዘምዛል። በዕዉቀቱ ሥዩም በአንድ እምቅ ግጥሙ የተቀኘዉን ያስታዉሰናል። “ያንን ገለባ ልብ ከደጅ የወደቀዉ/ አድራሻህ ወዴት ነዉ ? ብለህ አትጠይቀዉ/ የነገዉ ነፋስ ነዉ መንገዱን የሚያውቀው” ተራኪዉ ብቻ ነዉ እያቃሰተ የነገዉን ህይወት አቅጣጫ ለማግኘት አቅም የሰበሰበዉ። ህፃኗ አትተርፍም፤ ወጣቷም ዉስጧ የመሸገ የሚርበተበት ዉበት ስንቅ ከሚሆናት ወጥመድ ሆናት።
ልቦለዱ እንደ ዘመናዊ አጣጣፍ ታሪኩ ሳያበቃ -open end- ከምናብ ለምናክልበት ስፍራ ያስተርፋል። ከስምንት ትረካዎቹ በተሰለቸ ጉዳይ የተጣደዉና ውይይቱ ደራሲዉ የቀረፀዉ -fabricated- የመሰለዉ በ “ከቀብር መልስ” ነዉ። የዶ. በድሉን ክህሎት አይወክልም። “ሰዉ የተሰበሰበበት ቦታ ይጨንቀኛል፤ ... ይሉኝታ ከአግዳሚዉ ጋር ሰፍቶ ይዞኝ እንጂ መሄድ ከፈለኩ ቆየሁ” ድንኳን ዉስጥ የተጨናነቀዉ እድርተኛ ለልዩ አጭር ልቦለድ ሊበቃ አቅም እያለዉ ዋናዉ ገፀባህርይ ከአንድ ምሽት ቤት ሲገባ፣ ልቦለዱ መዝመም ይጀምራል፤ ይሰለቻል። የመጀመሪያዉ ልቦለድ “አዝማሪዉ፥ ከተሜዉ ...” ትረካዉ በአዝማሪ ስንኞች እየታደሰ፥ በአደባባይ “ሰዉ” መስለዉ ህሊናቸዉ ለነቀዙ ግለሰቦች ትዝብት ነዉ። ግጥምና ትረካ እየተፈራረቁ ጥርጣሬ፥ ቅናት፥ ሙስና ... እንደ ዘገባ ሳይሆን እንድ የኑሮ ቅኔ ይጠራራሉ። ሆኖም በአንደኛ መደብ ስለሚተረክ ገፀባህርዩ ባልተገኘበት የዴንማርኩን ፈረንጅ ገመና እንዴት አወቀ ? ከጐጆዉ ክዳን የሚነሳዉን ጭስ እያስተዋለ በስጋትና በተስፋ መንፈሱ ስለጣመነ ገበሬ አጠገቡ ሳይገኝ እንዴት ተረከ ? አንደኛ መደብ የአንፃር ምርጫ ስለማይፈቅደዉ ወደ ሁልን አዋቂ መሻገር ይቻል ነበር። ይህ ግን ለተአማኒነት ካልሆነ በልቦለዱ ለመመሰጥ አያግድም።
“ያልተከፈለ ስለት” ከታተመ ገና ጥቂት ወራት አልቆጠረም፤ በተደራሲያን እጅ ሲመላለስና ሲነበብ ለዳግም ሂሳዊ ንባብ መቀስቀሱ አይቀርም። ሰባት ልቦለዶች ባይሰለቹም በተለይ ለኔ ለጥልቅና ዝርዝር ሂስ የሚያጓጉኝ ሁለት ናቸዉ። “እናታቸዉ የሞተች እለት” እና “የረከሰ መብአ” አይዘነጉም። ዶ. በድሉ ከነአዳም ረታ፥ ዓለማየሁ ገላጋይ፥ በዕዉቀቱ ሥዩም እና እንዳለጌታ ክልል በመቀላቀል የራሱን የጥበብ ድንበር እያበጀ ይገኛል። አማረ ማሞና ዘርይሁን አስፋዉ ያስተማሩንን የአጭር ልቦለድ አፃፃፍ ብልሀት ቸል ብሎ ዘመናዊ ይትበሃል በመከተሉ ረቀቅ እያለ ነዉ። ይህን ሀሌታ ንባብ፣ ወጣት ገጣሚ በአካል ንጉሤ “ፍላሎት” በሚል ርዕስ ካሳተመዉ ስብስቡ “ብርሃን ከላይ” በመጥቀስ መቋጨት ይቻል ይሆን? ብርሃን እንደ ዝሃ ህላዌን እንደ ማግ አድርቼና አቅልሜ ሸምኜ ሸምኜ ያን የብርሃን ሸማ፥ ደርቤ ብለብሰዉ ጨለማ ወረሰዉ። (ለካንስ) ብርሃን መሆን እንጂ፥ ብርሃንን መደረብ አይጠቅመዉም ለሰዉ።
ዶ. በድሉ ሰዉና ክስተትን ብርሃን በመሆንና ብርሃን በመደረብ ቅንፍ ሳይቀነብብ ከጨላማ ፥ ከግራጫ ግለሰብን እያደባ ትናንት በመቀኘቱ፥ዛሬ በመተረኩ ለኛም በጅቶናል። የሚመጥን የፈጠራ ድርሰት ባነበብኩ ወቅት ዝነኛዉ Milan Kundera ስለ ልቦለድ የተናገረው ትዝ ይለኛል። “All great works (precisely because they are great) contain something unachieved” የልሂቃን ትልቅ የጥበብ ዉጤት የሚመስጠን፥ የሚያነቃቃን በሰመረላቸዉ ፈጠራ ብቻ ሳይሆን፥ ሞክረዉ አልሰበሰብ ባለዉም ምናባቸዉ ጭምር እንጂ እንደማለት።