Saturday, 02 August 2014 12:08

አለማየሁ ቢራቢሮዎች በ”የብርሐን ፈለጎች”

Written by  ተፈሪ መኮንን
Rate this item
(3 votes)

ያመሸ እንግዳ
‹‹የብርሃን ፈለጎች››ን ካነበብኩት ቆየሁ፡፡ ግን ቻርልስ ቻፕሊን ‹‹ብቻዬን ከበብኳቸው›› እንዳለ፣ ኑሮ ብቻዋን ክብብ አድርጋ ብታዋክበኝ፤ደግሞም ጸጋዬ ገ/መድህን ‹‹የማይበስል ወጬት ጥጄ›› እንዳለ፤ የማይበስል ኑሮ ጥጄ፤ ያን እፍፍ… ስል፤ ይህን ሳከስል፤ አላደርስ ቢለኝ፤‹‹የብርሃን ፈለጎች››ን እንዳነበብኩ የተሰማኝን ስሜት በአፍላው የመግለፅ ዕድል አጥቼ ቆየሁ፡፡ አሁንም፤ ወጬቱ ባይበስል፤ እሣቱም ባይከስል፤ ጭሱም ገለል ባይል፤ ‹‹በዋልድማም ይዘፈናል›› ብዬ፤ ያመሸ እንግዳ ሆኜ መጥቻለሁ፡፡ ቢመሽም ለመምጣት የወሰንኩት ምክንያት ስላለኝ ነው፡፡
የ‹‹የብርሃን ፈለጎች›› ደራሲ አለማየሁ ገላጋይ፤ ዘመነኛዬ ከሆኑ ደራስያን መካከል አንዱ በመሆኑ፤ እኔም የዘመኔን የድርሰት ቀለም የመመርመር ብርቱ ፍላጎት ስላለኝ፤ ‹‹የብርሃን ፈለጎች›› ወደፊት የአዲስ ትውልድ መልክ ተደርጎ የመጠቀስ ዕድል እንዳለው ስለማስብ በዚህ ድርሰት ላይ በአደባባይ አስተያየት ሳልሰጥ መቅረት አልፈለግሁም፡፡ ፎር ዘ ሪከርድ፡፡
አሁን ጨክኜ አስተያየት ለመስጠት ስነሳ፤መለስ ብዬ፤ ከዚህ ቀደም በጋዜጣና በመፅሔት የወጡ አስተያየቶችን የማንበብ ፍላጎት ነበረኝ፡፡ ሆኖም፤ መፅሐፉን እንደገና ማየት በጀመርኩ ጊዜ የተፈጠሩብኝን እንደሳሙና አረፋ ዕድሜ የሌላቸው አንዳንድ ስሜት እና ሐሳቦች ሳይጠፉ ለማጥመድ በማሰብ ያነሳሁት ብዕር እንደ ውሃ እያሳሳቀ ወሰደኝና የኔው መጣጥፍ መልክ ያዘ፡፡
አለማየሁ ገላጋይ፤ ከአብራከ-ምናቡ አንቅቶ፤ ከህይወት ልምዱ ቀምሮ ፤ ሦስት ረጅም ልቦለዶችን አስነብቦናል፡፡ አለማየሁ፤ በ‹‹አጥቢያ›› ቀድሶ፤ በ‹‹ቅበላ›› ቀጽሎ፤ በ‹‹ብርሃን ፈለጎች›› አለዝቧል፡፡ ወትሮም፤ ‹‹ልማ በሥሉስ፣ ጥፋ በሥሉስ›› ይባላልና፤ በሦስተኛው ክሂሎቱን እንዳጸና አይቻለሁ፡፡ አሁን፤ ከፃፈው ይልቅ፤ እርግጠኛ ሆነን የሚፅፈውን መናፈቅ እንችላለን፡፡
አደረጃጀት
ያው እንደወትሮው አስተያየቴን ከምን ልጀምር በሚለው ጥያቄ ብዙ ከባዘንኩ በኋላ፤ በመጨረሻ፤የድርሰቱን አደረጃጀት በመቃኘት አጠቃላዩን ስዕል በማየት ለመጀመር ወሰንኩ፡፡
‹‹የግንፍሌ ማለዶች›› የሚለው የክፍል-አንድ ትረካ ርዕስ፤ የደራሲው ትኩረት ግንፍሌ (መንደሯ) ይመስላል፡፡ ሆኖም፤ ደራሲው የሚተርክልን የግንፍሌን የማለዳ ዘመን ታሪክ ሳይሆን፤ግንፍሌ በተባለች መንደር የሚኖሩ ታዳጊ ህፃናትን (‹‹ማለዶችን››) ህይወት ነው፡፡ የክፍል - ሁለት ትረካ፤ግንፍሌን ትቶ ሄዶ ‹‹የሞጆን ቀትሮች›› ያወጋናል። በክፍል - አንድ፤ ‹‹የግንፍሌ ማለዶች››ብሎ፤ በክፍል - ሁለት፤ ‹‹የሞጆ ቀትሮች›› ሲል፤ ለውጡ የመቼት (የቦታ) ብቻ አይደለም፡፡ ትኩረቱም ከ‹‹ማለዳ›› ወደ ‹‹ቀትር›› ተለውጧል፡፡ ‹‹…ማለዶች›› በልጅነት ዘመን፤‹‹…ቀትሮች›› በጉርምስና ዘመን ያተኮሩ ናቸው፡፡
ታሪኩ ወደ ሞጆ ሲሄድ፤መቼቱ እና በ‹‹ክፍል - አንድ›› የምናውቃቸው ገፀ-ባህርያት በሙሉ (ከዋናው ባለታሪክ በስተቀር) ተሽረው ሌሎች ገፀ-ባህርያት ተመልምለው ይመጣሉ፡፡ ነገር ግን፤ በዚህ ‹‹ሥር-ነቀል›› ሹምሽር መሐል አንድ ፀንቶ የቆመ ነገር እናገኛለን - ትኩረት፡፡  
ታሪኩ፤ዋናውን ገፀ - ባህርይ ተከትሎ ሞጆ ሲገባ፤ ‹‹ክፍል - አንድ››ን ‹‹የግፍንሌ ማለዶች›› ያሰኘችው የትረካ ፀሐይ፤ በዕድሜ ሰማይ ተጉዛ ከቀትር ግቢ ገብታ ነበር። ስለዚህ፤ የ‹‹ክፍል-ሁለት›› ትረካ ‹‹የሞጆ ቀትሮች›› የሚል ሆኗል፡፡ ትረካው እንደ ሱፍ አበባ የተከተለው የሰውን የዕድሜ ዘመን ዑደት ነው፡፡ ስለዚህ፤ መቼቱ እና ብዙዎቹ ገፀ-ባህርያት ሲቀየሩ፤የትረካው ትኩረት ከዕድሜ ዑደት አልተነሳም፡፡ በሁለቱ ክፍሎች (ግንፍሌ እና ሞጆ) መካከል ስውር ዝምድና የፈጠረውም ጉዳይ ይኸ ነው፡፡ ከዚህ ሌላ፤ ደራሲው በሁለቱ ክፍሎች መካከል ያለውን ዝምድና ለማጠናከር የተጠቀመበት አንድ የትረካ ብልሃት መኖሩን አይቻለሁ፡፡ ይህን ብልሃት ‹‹መታታት›› በሚል ንዑስ ርዕስ ሥር የምመለከተው ቢሆንም፤ ሊፈጥር የሞከረው ዝምድና ‹‹ድህረ ታሪክ›› የሚል የትረካ ምዕራፍ እንዲቀር ማድረግ አለመቻሉ ግልፅ ነው፡፡
‹‹የብርሃን ፈለጎች››ን ሁለት ክፍሎች ራሳቸውን አስችለን ስናያቸው፤የሳቢያ እና ውጤት ሰንሰለትን አጥብቀው ሠርተው የሚጓዙ መሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ሁለቱን ክፍሎች አጋጥመን ስንመለከት፤ ከሳቢያ እና ውጤት ዝምድና ይልቅ የ‹‹ትኩረት›› ዝምድና ጎልቶ ይታያል፡፡
ትረካ
ታሪኩ፤ በእኔ ባይ ተራኪ (አንደኛ መደብ) የሚተረክ ነው፡፡ ትረካው፤ እንደ ታሪክ ባለሙያዎች (Historians) ወግ፤ ‹‹ታሪከ - ዘመን››ን የተከተለ ነው፡፡ የታሪክ አጥኚዎች፤ ‹‹ዘመነ መሳፍንት››፣ ‹‹ቅድመ -አብዮት››፣ ‹‹ድህረ - አብዮት›› እያሉ  ‹‹ታሪከ - ዘመን››(Period) ላይ እንደሚያተኩሩ፤ ‹‹የብርሃን ፈለጎች›› ትረካም፤ የአንድን ገፀ- ባህርይ የህፃንነት (ማለዳ) እና የጉርምስና (ቀትር) የህይወት ውጣ ወረድ፤ ከቤተሰቦቹ፣ ከጓደኞቹ፣ ከጎረቤቶቹ ወይም ከመምህሮቹ ጋር ያለውን ግንኙነት የሚተርክ ድርሰት ነው፡፡ የአንድ ሰው ‹‹ታሪከ - ዘመን››፤ ከዕድሜ ዑደት አንፃር ሲቃኝ፤ የልጅነት፣ የጉርምስና፣ የጉልምስና እና የእርጅና ዘመን ተብሎ ሊከፈል ይችላል። እናም፤ ‹‹የብርሃን ፈለጎች›› ትረካ፤ የአንድ ገፀ-ባህርይን (ባህርያትን) ‹‹ታሪከ - ዘመን›› መሠረት አድርጎ ሲተርክ የአንድ ትውልድ (ዘመን)ወኪል የመሆን የሁለንተናዊነት ማዕረግ አላብሶ ነው፡፡
የትረካው መሠረታዊ ክፍል ዕውቂያ (Exposition) ነው፡፡ ደራሲው አለማየሁ ገላጋይ በ‹‹የብርሃን ፈለጎች››አድጎ የታየኝ በዕውቂያ አመሠራረት ጥበቡ ነው። ዕውቂያ ከባድ የትረካ ክፍል ነው፡፡ ዕውቂያ፤ ትናንትናን ጠቅሶ፣ ዛሬን ተንተርሶ፣ ነገን የሚያማትር ትረካ መሆን አለበት፡፡ ነገሮችን በሦስት የጊዜ አውታር የማውተርተር ወይም የማያያዝ ብቃትን የሚጠይቅ ሥራ ነው፡፡ አሁን (ዛሬ) ሥራ ፈትቶ፣ ስለትናንት ወይም ስለነገ የሚዘበዝብ እንዳይሆን አድርጎ፤ አንዱን ከሌላው አመዛዝኖ መተረክን ይጠይቃል፡፡ እንዲያ ካልሆነ፤ ትረካው ይሰናከላል። ይቀየዳል፡፡ ይወዘፋል፡፡ አለማየሁ በዕውቂያው አመሠራረቱ፤ እንደ ግጥም ቁጥብ ሆኖ፤ ማለፊያ እና ትብ በሆነ ዝርው ገለፃ፤ ወሸኔ ትረካ የመፍጠር ብቃቱን አሳይቷል፡፡ አስረጅ የሚሻ፤የሦስት ገፅ ዕድሜ ያለውን የመጀመሪያ ምዕራፍ ማንበብ ነው፡፡
አለማየሁ፤ በአሁን ጉዳይ ላይ ትኩረት አድርጎ፤ ለአሁኑ ድርጊት መደላድል የሚሆን የትናት ነገር እያነሳ ስለመጪው ሁኔታ እየጠቆመ የመተረክ ድንቅ ችሎታውን አሳይቶናል፡፡
የልቦለዱ ዋና ገፀ-ባህርይ መክብብ በጋንጩር ተፈንክቶ፤ ተራኪው እንዳለ ‹‹በእጅ ቃሬዛ›› እንደተንጋለለ ወደ ቤቱ ሲሄድ፤ ስለ ሠፈሩ፣ ስለራሱ፣ ስለጓደኞቹ፣ ስለጎረቤቶቹ ወዘተርፈ ይነግረናል፡፡ ‹‹ከእጅ ቃሬዛ›› ላይ እንደተንጋለለ፤ በዙሪያው የሚከሰቱ ሁነቶችን (የአሁን ድርጊቶች) መነሻ እያደረገ፤ ትናትን እና ነገን እየሰገሰገ ይተርካል፡፡ የአሁን ድርጊትን መነሻ እያደረገ፤ ቁጥብነቱን እንደጠበቀ ስለትናንት ይነግረናል፡፡ በ‹‹ተውኔታዊ›› የትረካ ዘዬ ለገለፃው ደርዝ ይጨምርለታል፡፡     
አለማየሁ ትረካውን ሲጀምር፤ ‹‹ተፈነከትኩ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ደሜ ፈሰሰ›› ይላል፡፡ የልቦለዱ ዓቢይ ገፀ ባህርይ የሆነው እኔ ባዩ ተራኪ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደ ተፈነከተ ገልፆ፤ ‹‹የበኩር ፍንክቴ ልበለው?›› እያለ ይጠይቃል፡፡ ደም ከሰው አካል ሲፈስ ‹‹እንደ እሣት ጅረት ያረፈበትን ቆዳ እየለበለበና እያኮማተረ የሚወርድ ፈሳሽ ስቃይ ይመስለኝ ነበር፡፡ ግን እንደዚያ አይደለም›› (ገፅ፣ 6) የሚለው ተራኪ፤ ደም ከጭንቅላት ሲፈስ ‹‹አናት ላይ ከተከለበሰ ሙቅ ውሃ የተለየ ስሜት›› እንደሌለው ያጫውተናል፡፡ ተራኪው ከጉዳቱ ይልቅ ልምዱን ሲናገር ማየታችን የልጅነት ባህርይ በመሆኑ፤ ደራሲው የተራኪ ገፀ -ባህርይውን ጠባይ ሳይለቅ መተረኩን ያረጋግጣል፡፡
እኔ ባዩ ተራኪ፤ ልጅ በመሆኑ፤ ዕውቂያው የሚካሄደው በእርሱ ዓይን መሆን አለበት፡፡ እናም ገለፃው ከህፃን ባህርይ ጋር ሳይጣላ መከናወን ይኖርበታል፡፡ አለማየሁ፤ ይህን ውስንነት ተቋቁሞ፤ በሦስት ገፅ ገለፃ የታሪኩን ውል ያስይዘናል፡፡
ተራኪው ፍንክቱን መነሻ አድርጎ ከሚገልፀው ነገር በተጨማሪ የልጅ ምልከታውን፤ ‹‹የመንደሩ ሐኪም ገበያ ይዘንላቸው እንዳልሄድን ሁሉ እየተነጫነጩ አንድ መርፌ ወጉኝ›› (ገፅ፣ 8) በሚለው ቃል እናስተውላለን። እንዲሁም የሚኖርበትን ዓለም በመፈተሽ ላይ ያለ ልጅ መሆኑን፤ ‹‹የኛ ሰፈር ወንዶች ይጋርዱ ቂጦን ሲያዩ የሚያነሆልላቸው አንዳች ሚስጥር እንዳለ ይሰማኛል›› (ገፅ፣ 6) ከሚል ገለፃው እንረዳለን፡፡
በሌላ በኩል፤ ባለ ታሪኩ ገፀ ባህርይ ‹‹ለመፈንከት ፍርሃቴ ዘላለማዊ ፈውስ ሰጥቶኛል›› ሲለን፤ በህፃን መንፈስ የተነገረ የልምድ ርሃብ መሆኑን እያሰብን፤ በንባቡ እየገፋን ስንሄድ፤የህፃኑ ተራኪ አስተያየት የማህበራዊ ምህዳሩ ጉልህ ባህርይ መገለጫ መሆኑን እንመለከታለን፡፡
ደራሲው፤ ከዚህች አንዲት ሁነት ተነስቶ፣ ዋና ገፀ-ባህርይውን ከቤተሰቡ፣ ከጓደኞቹ፣ ከመንደሩ ነዋሪ፣ ከልጅነት ዘመን ዓለሙ ግንፍሌ መልክዓ ምድር ጋር ለዛ ባለው ቋንቋ እና ዘዬ አስተዋውቆ የታሪኩን ፈር ያስይዘናል፡፡
ከአንዴም ሁለት-ሦስቴ የተፈነከቱ ጓደኞቹ፤ በእሱ መፈንከት በጣም መርበትበታቸው እየገረመው፤ እያንዳንዳቸው ስንት ጊዜ እንደተፈነከቱ፤ቆጥሮ ይነግረናል። ‹‹የመፈንከት ቆሌያቸው ስላልተገፈፈ ወይም የሞትኩ ያህል ስለቆጠሩኝ እንደ አስክሬን ተሸከሙኝ›› የሚላቸው ጓደኞቹ ‹‹በሚጢጢ እጆች ከሰሩለት ርብራብ ቃሬዛ›› (ገፅ፣ 7) ላይ ዘና ብሎ እንደተንጋለለ የሚያስበው፤ ‹‹የጉም ችፍርጉን እየጣሰ ሲሸሽ ይታየኛል›› የሚለውን ፈንካቹን ጋንጩርን ነበር፡፡ እንዲሁም፤ ፈንካቹ ጋንጩር ‹‹ግንፍሌ ላይ ሠፈር›› እንደሚኖርና ጎረቤት መሆናቸውን ጠቅሶ፤ ‹‹ለስሙ ላይ ሠፈር ይባላል እንጂ ያሉት ቤቶች ሁለት ናቸው›› (የእነሱ እና የእነጋንጩር ቤቶች) እያለ ሠፈሩን ያስተዋውቀናል፡፡ ተራኪው ዋና ገፀ-ባህርይ፤ በ‹‹ቃሬዛው ተንፈላሶ›› በዙሪያው የሚመላሱ ድምፆችን እያደነ፤ ብዙ ጉዳዮችን ይነግረናል፡፡ አስተያየትም ይሰጣል፡፡
‹‹…አበስኩ ገበርኩ! ደሙ ማለቁ አይደለም እንዴ?›› ሲባል ይሰማል፤ ‹‹…የጋሙዳ እናት እንደሆኑ አውቄያለሁ። ታች ሰፈር ደርሰናል ማለት ነው፡፡ ሜዳውን ካቋረጥን፤ እቤት[ደረሰን ማለት ነው፡፡]›› (ገፅ፣ 7) አፍታ ቆይቶ ደግሞ ‹‹የይጋርዱ ቂጦ ድምፅ እያስገመገመ ከበበኝ (ዝከ) ይላል፡፡ ይቺን አሳብቦ፤ ይጋርዱ ቂጦ የተባሉ ገፀ- ባህርይ መሠረታዊ መገለጫ ሆኖ የሚዘልቅ ጉዳይ እጅግ ተቆጥቦ ገልፆልን ያልፋል፡፡
ስለይጋርዱ ቂጦ በተወሰኑ መስመሮች የሚሰጠን ዕውቂያ፤ ስለዋናው ባለታሪክ አባት እና እናት ግንኙነት ሁኔታ ትልቅ ቁምነገር አስጨብጦን የሚያልፍ ነው፡፡ ተራኪው ይጋርዱ ቂጦ፤ ‹‹አይ ያቺ እናቱ አሁን ስታየው … አሉ በሚያስተጋባ ቀጭን ድምጻቸው›› (ገፅ፣ 8) ካለ በኋላ፤ ‹‹የእናቴ ነገር ሲነሳ የሞት መቀስቀሻ ወስፌ ሆነብኝ፡፡ ሸለበታዬ ጠፋ›› (ዝከ) ብሎ ከእናቱ ጋር ስላለው ግንኙነት ወይም ስለእናቱ ባህርይ ውል ያስይዘናል፡፡ ‹‹የእናቴ ለወይን ጠጅ የቀረበ ፊት ብዙ ቋንቋ አለው›› የሚለው ገለፃ ለእናቱ ባህርይ መሠረታዊ መገለጫ የሚሆን ትልቅ ቁምነገር ይጠቁምና፤የይጋርዱ ቂጦን ድምፅ ሰበብ አድርጎ አንድ ገጠመኝ ያነሳል፡፡
‹‹የእኚህ ሴት ‹ነገር› ምን ያህላል? የጤና ብለሽ?›› ሲሉ አባቱ አስተያየት መስጠታቸውን ጠቅሶ፤ በዚህ የተነሳ ለኩርፊያ የዳረጋቸው ጭቅጭቅ መነሳቱን ያስታውሳል። በዚህም፤ የእናት እና የአባቱን ግጭት መሠረታዊ መነሻ ይነግረናል፡፡
ተራኪው መክብብ ከተፈነከተበት ሥፍራ ተነስቶ፤ እቤት እስኪደርስ ብዙ የታሪክ ውል እያስጨበጠን ይሄዳል፡፡ ‹‹የቤተክርስትያን ደጃፍ እንደሚሳለም አስክሬን የኛን ቤት አሳይተው መለሱኝ›› (ዝከ) በማለት ሚስማር ፋብሪካ መዳረሻ ካሉ አንድ የመንደር ሐኪም እንደወሰዱት በመግለፅ፤ የክፍል አንድ -ምዕራፍ፤ አንድን ትረካ ይደመድማል፡፡
ደራሲው፤ ሦስት ገፅ (ከ6 - 8) በምትሆን አጭር የትረካ ምዕራፍ፤ ከእጅ ቃሬዛ ላይ ተጋድሞ በሚሄድ አንድ እኔ ባይ ተራኪ፤ ከዚያ ወዲያ ተጨማሪ ገለፃ አያስፈልግም በሚያሰኝ መጠን እና አኳኋን ስለመንደሩ፣ ስለአካባቢው፣ ስለዋና ዋና ባለታሪኮች መሠረታዊ ባህርይ እንድናውቅ አድርጎናል፡፡ በአጫጭር ዐረፍተ ነገር፣ በጥልቅ እይታ እና በለዛ የታሪኩን ውል አስጨብጦናል፡፡ የህፃን አተያይ መሆኑ ሳይጠፋ የግንፍሌን ዓለም አሳይቶናል፡፡
እንዲሁም፤ በዚህ የሦስት ገፅ ትረካ የተነሳ፤ በፍካሬ ብዙ ትርጉም የሚይዝ አንድ ጉዳይ አለ፡፡ ተራኪው፤ የእነጋንጩር ቤት በኮሸለለ ቅጠል የታጠረ መሆኑን ያነሳል፡፡ ‹‹የኮሸለለ ቅጠል አጥር››የሚለው ሐረግ፤ በታሪኩ ውስጥ የብዙ ነገሮች ማጠንጠኛ ሊደረግ የሚችል ተምሣሌታዊ ማዕረግ ያለው የትረካ ነጥብ ነው፡፡
ደግሞም የግንፍሌ ነዋሪዎች ዋና መገለጫ ሆኖ ስለሚገኝ ጉዳይ ስለባህላዊ ህክምና ጠቆም ያደርገናል፡፡ ‹‹ቆም አድርጋችሁ፤ ደቃቅ አፈር ነስንሱበት እንጂ ደሙን እንዲያቆምለት›› (ገፅ፣ 7) ሲባል ያሳየናል፡፡ መቼም ድንቅ ነው፡፡
ከትንሽ ድፍረት ጋር በእነዚህ ሦስት ገፆች በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ ያልተጠቀሰ አንዳች ነገር ወደፊት አይገኝም እላለሁ፡፡ በጥቅሉ፤ የክፍል- አንድ ትረካ፤ በዚህ ዓይነት ቁጥብነትና ጥልቀት፣ ለዛና ወዝ የተገሩ ሁነቶችን የምናነብበት ክፍል ነው፡፡ በአንፃሩ፤ ክፍል ሁለት፤ በዚህ መጠን የተዋጣ መሆኑን ለመመስከር አመነታለሁ፡፡ ይህ ትረካ፤ የተገለፀባቸው የአለማየሁ ዐረፍተ ነገሮች አጫጭር ናቸው፡፡ የቋንቋ አጠቃቀሙ ግልጽ ነው፡፡  የቃላት ምርጫውም ውብ ነው፡፡ እንግዲህ ደራሲው በዚህ ትረካ ሊያሳየን የፈለገው ህይወት ምን እንደሚመስል ወደ ማየት እንለፍ፡፡
ግንፍሌ
የ‹‹የብርሃን ፈለጎች›› ተራኪ ‹‹ግንፍሌ›› ከተባለች መንደር ህይወት ጋር ያስተዋውቀናል፡፡ ግንፍሌ ላይ ሠፈር እና ታች ሠፈር የሚባሉ ክፍለ-መንደሮች አሏት፡፡ ግንፍሌ ትንግርት የምትሆን መንደር ነች፡፡ ግንፍሌ፤ በዳግማዊ ምኒልክ ት/ቤት እና በዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል መካከል የምትገኝ መንደር ነች፡፡ ታዲያ ተራኪው ስለግንፍሌ ሲያስብ ግር የሚለው፤ መሐል አዲስ አበባ የምትገኘው ገጠራማይቱ መንደር ግንፍሌ፤ ዘመናዊ ተቋማት ከአጠገቧ እያሉ በረከታቸው እንደራቃት መኖርዋ ነው። የዘመናዊ ከተማ እምብርት ስትሆን፤ ገጠራማ መንደር መሆን መቻሏ፤ ዘመናዊ የማህበራዊ ተቋማትን ታቅፋ፤ ባህላዊ ተቋማትን የሙጥኝ ብላ የያዘች መንደር መሆኗ ድንቅ ነገር ነው፡፡
‹‹እኛ እንግዲህ የእነዚህ ገጠር ናፋቂ ሠፋሪዎች ልጆች ነንና ገጠሬነት በግድ ተጭኖብን አድገናል፡፡ …. ወላጆቻችን ከተሜነትን ይፀየፋሉ›› ሲል ተራኪው የሚገልፃቸው ግንፍሌዎች፤ ለጉድጓድ፣ ለምንጭ እና ለወንዝ ውሃ ያላቸው ፍቅር፤ የቧንቧ ውሃን የሚንቁ እና ‹‹የመኪና ወፍጮ በረከት የለውም›› እያሉ፤ እህል በድንጋይ ወፍጮ የሚፈጩ፣ የሚሰልቁ፣ የሚሸከሽኩ መሆናቸውን ይነግረናል (ገፅ፣ 42)፡፡
አውጥ፣ የዋንዛ ፍሬና ኮሽም እየለቀሙ፣ ሾላ እያረገፉ፣ በእምቧይ እየተወራወሩ፣ በሰንሰል እየተጋረፉ፣ ግንፍሌ ወይም ቀበና ወንዝ ወርደው ገላቸውን እየታጠቡ፣ ከብት እየጠበቁ አዛባ እየዛቁ ያደጉት እኒያ የግንፍሌ ‹‹ቢራቢሮች››፤ ቀበጥ ሲያደርጋቸው፣ ዘመናዊነትን የሚጠየፉ ወላጆቻቸውን፤ ቦላሌ ግዙልን ይላሉ። ይህ የቀበጥ ጥያቄ፤ እንደማሽላ እያረሩ እንዲስቁ የሚያደርጋቸው የግንፍሌ ወላጆች፤ ‹‹አየሽልኝ የዚህን ልጅ ጉድ›› ይላሉ፡፡ የግንፍሌ ‹‹ቢራቢሮች››፤ አዲስ አበቤዎች ስለሆኑ፤ ነካ ያደረጋቸው ቀን፤ በከተማ ሲደረግ ያዩት ሲያምራቸው፤ ‹‹ለስላሳ አጠጡን›› ይላሉ። የግንፍሌ ወላጆች ጣሪያው እስኪነቀል ይስቃሉ፡፡ ‹‹አሃሃሃሃ…. የኔ ዘበናይ አረንቻታ አማረህ? አንተ አረንቻታ ጠጥተህ ጠላውን በአንኮላ ማን ሊግፍልህ ነው?›› ብለው፤ መገረምን በቀላቀለ ቁጣ ልጆቻቸውን ይገስፃሉ፡፡ ግንፍሌ ይህን ትመስላለች፡፡ ከብት መጠበቅ ወይም አዛባ መዛቅ እምቢ የሚሉ ልጆችዋን፤ በርበሬ ታጥናለች፡፡ በሣማ ትገርፋለች፡፡
ታዲያ ከዚህ መሰሉ የግንፍሌ ነዋሪዎች ህይወት ያፈነገጠ አንድ አባት በድርሰቱ እናገኛለን፡፡ ልጁን ‹‹ለስላሳ ልጋብዝህ?›› ብሎ የሚጠይቀው ይህ ‹‹አፈንጋጭ›› አባት የግንፍሌን ወግ ያፈርሳል፡፡ ሆኖም ባህሉን የሚዳፈረው፤ በዓይኗ ብቻ የምታሽቆጠቁጠው ባለቤቱ፤ እግሯ ከቤት ወጣ ባለጊዜ ነው፡፡ ‹‹እናቴ ሞጆ ስትሄድ አባቴ የትኛውን ዓይነት መጠጣት ትፈልጋለህ? ይለኛል፡፡ አይ! ቢንጎ ብርቱካን የሴቶች ነው፡፡ ካናዳ ድራይ ይሻልሃል፡፡ አየሩ ልብህ ላይ ሲቆም ወንድነት ይሰማሃል፡፡ ‹ቧ› ስታደርገው እንደ አንበሳ ያገሳህ ይመስልሃል›› (ገፅ፣ 43) ይለኛል የሚለው እኔ ባዩ ተራኪ፤ የአባቱ ባህርይ ከመንደሩ ባህል እንደማይገጥም ሲነግረን፤ ‹‹እዚህ መካከል የከተሜነት ንቃት ያለው አባቴ ብቻ ነው፡፡ ሳንባ፣ ትዊስት፣ ቡጊቡጊ፣ … ይደንሳል፡፡ ያፏጫል፣ ፀጉሩን ኤልቪስ ፕርስሊ ይቆረጣል፣ ጊታር ይጫወታል፡፡ ከሁሉም በላይ እኔን ለስላሳ ያጠጣል›› (ዝ.ከ) ይለናል፡፡
ሆኖም ግንፍሌ፤ ከዚህ በላይ የሚሄድ ልዩነትን የምትፈቅድ አትመስልም፡፡
የግንፍሌ ‹‹ቢራቢሮዎች››፤ አባቶቻቸው በታላቅ ቅናት እና ፅናት በከተማ ባህር ውስጥ የፈጠሩትን የገጠር ደሴት አኗኗር እንዲወርሱ ይገደዳሉ፡፡ የአባቶቻቸው ልጆች የሆኑት የግንፍሌ ‹‹ቢራቢሮዎች›› እንደ አባቶቻቸው እነሱም ይደባደባሉ፣ ይፈነካከታሉ፡፡ ዋናው ባለታሪክ መክብብ፤ ‹‹…እኛ ግንፍሌዎች  እንድናድግ የተፈቀደልን፤ መንግስት ሰላሙን እንደሚጠብቅለት ማህበረሰብ ልጅ አይደለም፡፡ እንደ ጥንቱ አኗኗር የጎሳ ወረራ እንደሚያሰጋቸው ሕዝቦች ሁሉ፤ ወላጆቻችን ጠላትነትን ፣ ጥንካሬን፣ ጭካኔን፣ ንቁነትን፣ ስጋትን፣ ….እርስ በእርስ እንድንሞክረው ያበረታቱን ነበር፡፡ ሌላው ቀርቶ፣ ጨዋታችን እና መደሰቻችን እንኳን ሰላማዊ አልነበሩም›› (ገፅ፣ 56) ይላል፡፡ ይህን የጨለማ ፈለግ ተከትለው፤ ከወላጆቻቸው የወረሷቸውን እና እነሱም የፈጠሯቸውን የተንኮል ጨዋታዎች ሲጫወቱ ያድጋሉ፡፡
ግንፍሌ፤ ግብግብ እና ኡኡታ የማይለያት መንደር ነች፡፡ ድርሰቱ ከግንፍሌ ጋር የሚያስተዋውቀን፤ እኔ ባዩ ተራኪ እንደ ገድል የሚያወራውን የግንፍሌ ህፃናት ድብድብ እየነገረን ነው፡፡ የግንፍሌ ህይወት (ገመና) መጋረጃው የሚገለጠው፤ ጋንጩር መክብብን ፈንክቶት ደም ከግንባሩ ሲጎርፍ ነው፡፡ በግንፍሌ፤ መብት የጉልበት ስጦታ ነው፡፡
የጋንጩር አባት ጋሼ ድንቁ፤ ‹‹የሠፈሩ ‹ጉልቤ› ናቸው›› የሚለን ተራኪው ገፀ ባህርይ መክብብ፤ ጋሼ ድንቁ ‹‹እንደ ኮርማ በሰውነታቸው የሚመኩ ባላገር›› እንደሆኑና ብዙ ጊዜ ሲደባደቡ እንዳጋጠመው ጠቅሶ›› (ገፅ፣ 11)፤ ገጠመኙን ይተርካል፡፡ ፀብ ፍለጋ የሰው ቤት የሚዞሩት የጋንጩር አባት፤ በባህላዊ የትግል ስልት የሚችላቸው እንደሌለ፤ ልጃቸውም ጋንጩር፤ አዘውትሮ የድንጋይ ውርወራ ልምምድ ሲያደርግ የሚታይ፤ በቀኝ እና በግራ እጅ የድንጋይ ውርወራ ጥበብ ተክኖ አባቱ ሲጠቁ የሚያግዝ፤ በዚህም ተግባሩ የመንደሪቱን ነዋሪ ሁሉ ያስመረረ ታዳጊ መሆኑን ያወጋናል፡፡
የእኔ ባዩ ተራኪ የመክብብ አባትም እንዲሁ ተደባዳቢ ናቸው፡፡ ልዩነታቸው፤ የመክብብ አባት የከተሜ የድብድብ ስልት ያላቸው ‹‹አራዳ›› መሆናቸው ብቻ ነው፡፡ የመክብብ አባት፤ ልጃቸውን የድብድብ ጥበብ የሚያስተምሩ ሰው ናቸው፡፡ ‹‹አባቴ ፀብን በቅልጥፍና እና በዘዴ በማከናወን ያምናል›› (ገፅ፣ 12) የሚለው ተራኪው፤ ብልጫ ባስገኘላቸውና ተለዋዋጭ በሆነው የድብድብ ስልታቸው፤ የጋንጩርን አባት እንዳስገበሩ፤ ሚስታቸው ‹‹ጃስ›› ካለቻቸው ለፀብ የማይመለሱ ሰው መሆናቸውን የሚነግረን ተራኪው፤ ‹‹እንደ ውሻ ድንበራቸውን በሽንታቸው ያሰምራሉ›› (ገፅ፣12) ሲል የሚገልፃቸውን የጋንጩርን አባት ጋሼ ድንቁን፤ የካራቴ ጥበብ በሚመስል ስልት አጥቅተው ባሸነፏቸው ጊዜ ድፍን ግንፍሌ ጉድ እንዳለ፤ ‹‹ለካ ዳንሰሪ ብቻ አይደለምና…. ›› (13) እንደተባለ››፤ ሚስታቸው ወ/ሮ ለምለም በልጃቸው መገረዝ አሳብበው ዶሮ እንዳረዱላቸው ያጫውተናል፡፡ ግንፍሌ ይህች ናት፡፡
የግንፍሌ ቢራቢሮ
የፈለገ- ግንፍሌን እና የፈለገ - ቀበናን ውሃ እየጠጣች ያደገች አንዲት ህይወት፤ ወደ ስምጥ ሸለቆ ወረደች። የሞጆን አቧራ እየቃመች አደገች፡፡ ተመልሳ ሸገር መጣች። መጥታም ተፈወሰች፡፡ በ‹‹የብርሐን ፈለጎች›› የዚህችን ህይወት ውጣ ውረድ ያስነብበናል፡፡
መክብብ የላይ ሠፈር እና የታች ሠፈር መለያያ ነጥብ ላይ ያለውን የውሃ ጉድጓድ አልፎ፤ ሜዳውን አቋርጦ፤ ታች ሰፈርን ተሻግሮ፤ ከወደ ስርጡ ወርዶ፤ ከፈለገ-ግንፍሌ ጨረቻ ሲደርስ፤ ከሳማው የተነሳች አንዲት ቢራቢሮ ይመለከታል፡፡ በህሊናው ያውጠነጥን ከነበረው ነገር ያናጠበችውን ሽልምልም ቢራቢሮ ይከተላል። ‹‹አንዲት ሽልምልም ቢራቢሮ በዓይኔ ሥር አለፈች ተከተልኳት›› (ገፅ፣ 60) ይላል፡፡
‹‹አመጣጧ ከወደ ሳማው አካባቢ ስለነበር፤ ምናልባትም ቢራቢሮዋ በመጀመሪያዋ በረራዋ ላይ ትሆን ይሆናል ብዬ አሰብኩ፡፡ እነዚህ ሳማ ላይ ቅፍፍፍፍ እያሉ የሚጎተቱትን አባ ጨጓሬዎች በመሸሽ ላይ ትሆን ይሆናል›› የሚለው መክብብ፤ እንደ ህፃን ዓለሙን ለመረዳት ሲሞክር እናየዋለን፡፡ እኒያ አባጨጓሬ ብሎ ያስባቸው የነበሩ ነፍሳት፤ አባቱ እስኪነግሩት ድረስ ቢራቢሮ ለመሆን የሚችሉ አይመስለውም ነበር፡፡ እንዲህ ይላል፤ ‹‹እንደውም አባጨጓሬዎቹ ቢራቢሮዎቹን ለመብላት የሚሳቡ አድፋጮች እየመሰሉኝ እጨፈጭፋቸው ነበር፡፡ ግን አይደለም፤ እነዚያ ቀፋፊዎች ልጅነታቸው በደረታቸው እንዲሳቡና እንዲኮሰኩሱ ያስገደዳቸው ነበሩ፡፡ ነገ ክንፍ አውጥተው ለዳንስ በቀረበ አባባይ ውበታቸው፤ በበረራ ከግንፍሌ ተነስተው ዓለምን ያዳርሳሉ፡፡ ለብዙ ብቸኞች የመኖር ምክንያትም ይሆናሉ። ለዓለም ክፋትና ክርፋት ማለዘቢያነት ያገለግላሉ፡፡ ይቺ ዓለምና ሕዝቦቿ ያለ ቢራቢሮዎችና መሰሎቻቸው ምንድን ናቸው? ክፋትና ክርፋት አይደሉም?›› (ገፅ፣60)፡፡
በግንፍሌ ጨረቻ ካለ አንድ ሳማ ላይ ይርመሰመሱ የነበሩትና መክብብ በስህተት ‹‹አባጨጓሬ›› አድርጎ ያሰባቸው ነፍሳት፤ ሳማ በሆነው የግንፍሌ ማህበራዊ ምህዳር ላይ የሚርመሰመሱት የእነ መክብብ፣ ጋሙዳ፣ ሙቄ፣ ቀጮ፣ ሴንጢ፣ አሰፋ ጢሪሪ፣ ጋንጩር ተምሳሌት ናቸው፡፡ ነገ ክንፍ አውጥተው … ከግንፍሌ ተነስተው ዓለምን የሚያዳርሱትን፤ ለብዙ ብቸኞች የመኖር ምክንያት የሚሆኑትን፤ ለዓለም ክፋትና ክርፋት ማለዘቢያ ሆነው የሚያገለግሉትን እነዚህ የፈለገ - ግንፍሌ ዳርቻ ቡቃያዎች፤ እንደ መክብብ የተሳሳቱት ወላጆች እንደ አባጨጓሬ እየተመለከቷቸው ‹‹ይጨፈጭፏቸዋል፡፡›› የህይወትን ዜማ እየተከተሉ፤ በሐዘን፣ በደስታ፣ በብሶት፣ በክፋት ወዘተ ዜማ የሚደንሱት የግንፍሌ ቢራቢሮዎች አበባ ሳይሆን ሳማ እየቀሰሙ አድገው ሲበተኑ እናያለን፡፡
ከእነዚህ የግንፍሌ ቢራቢሮዎች አንዷ ሳማ ከሆነ ማህበራዊ ምህዳር ተነስታ፤ በህይወት ወጀብ እና አውሎ ተገፍታ ሞጆ ትወርዳለች፡፡ ይህች ቢራቢሮ የብርሃን ፈለግን ለመከተል ስትሞክር፤ ኑሮ የእሣት ራት እያደረጋት ስትቃጠል፤ መሬት ወድቃ ስትዳክር እናያታለን። ከግንፍሌ ተነስታ ‹ዓለምን› ታዳርሳለች፡፡ የተለያዩ ማህበራዊ ምህዳሮችን እየተሻገረች ትበራለች፡፡ ለብዙ ብቸኞች የመኖር ምክንያት ትሆናለች፡፡ ለዓለም ክፋትና ክርፋት ማለዘቢያ ስትሆን ትታያለች፡፡ እውነትም፤‹‹ይህች ዓለምና ህዝቧ፤ ያለ ቢራቢሮዎች ምንድን ናቸው?›› (60) ብለን እንድንጠይቅ ያደርጉናል፡፡
ብርሃንን ፍለጋ የምትባክን አንዲት የግንፍሌ ቢራቢሮ፤ ሞጆ ወርዳ የጉርምስናን በር ስትሻገር እሣት ራት መሆን ትጀምራለች፡፡ ለሁለት የሞጆ ብቸኞች የመኖር ምክንያት ስትሆን ትታያለች፡፡ መምህርት ሙና እነ አክስት የሞጆ ወርቅ ዙሪያቸውን ለከበባቸው ክፋትና ከርፋት ማለዘቢያ ሊያደርጓት ሲሞክሩ እንመለከታለን። የእምነት ዕዳ ያጎበጣት ይህች መምህርት፤ የመጀመሪያ በረራ ስታደርግ ያገኘቻትን መክብብ የተባለች ‹‹ቢራቢሮ›› ውርውር ስትል ለአደጋ እንዳትጋለጥ የቻለችውን አደረገች፡፡ ጉርምስና እና ሥነ-ልቦናዊ ቀውስ ማገዶ ሆነው የፈጠሩት እሣት እራት አድርጎ እንዳያስቀራት፤ በመለኮታዊ ትዕግስት  ትንከባከባታለች፡፡ የመኖር ምክንያት ታደርጋታለች፡፡ መምህርት ሙና፤ አንድ የትግል ጓዷጥሎባት የሄደውን ከባድ ዕዳ በመክብብ ለመክፈል አሣሯን ትበላለች፡፡
የግንፍሌዋ ቢራቢሮ በበኩሏ፤የገዛ ህይወትዋ በሞጆ ታዳጊዎች ተመስሎ እየታያት፤ በሚንቀለቀል የኑሮ እና የጉርምስና እሣት የሚለበለቡ መሰሎችዋን ለማዳን ስትታገል እናያለን፡፡ እነዛ ገና ‹‹ክንፍ ያላወጡ›› ታዳጊ አባጨጓሬዎች፤ ወይም በተራኪው አገላለፅ፤ ‹‹እነዛ ቀፋፊዎች፤ ልጅነታቸው በደረታቸው እንዲሳቡና እንዲኮሰኩሱ ያስገደዳቸው›› በሚል ሊጠቀሱ የሚችሉ የሞጆ ታዳጊዎችን ለመታደግ ትሞክራለች፡፡
ከኑሮ በርሃ የተነሳው አውሎ ነፋስ፤ ከግንፍሌ ጨረቻ አንስቶ ሞጆ ከተማ‹‹ልዑል መውደቂያ›› ከተባለ መንደር የጣላት ያች የላይ ሠፈር ቢራቢሮ፤ መሰሎችዋ በህይወት ሳማ ላይ ቅፍፍፍ እያሉ በደረታቸው ሲሳቡ አይታ፤ ‹‹ዕድል ለእኔ ባታደላ ኖሮ፤ እኔም የእነሱ ዕጣ ይደርሰኝ ነበር›› በሚል ርኅራኄ፤ ከአክስቷ የአበባ መደብ ‹‹ዱቄት›› እየቆነጠረች ትበትናለች፡፡
ታዲያ የግንፍሌዋ ቢራቢሮ፤ ከመስኳ የሚቀሰም አበባ ባይቸግራትም፤ ውስጧን እንደ ሞጆው አሸዋማ ‹‹አፈር ያልበሰለ የበቆሎ እንኩሮ፣ የሚግለበለብ ጢስ እና የጋለ ብረት ምጣድ›› (ገፅ፣ 88) እንዲመስል ያደረገ ችግር እየነሸራት መጨነቋ አልቀረም፡፡ ‹‹የብርሃን ፈለጎች›› የግንፍሌ እና የሞጆ ቢራቢሮዎች ታሪክ የሚነበብበት ልብወለድ ነው፡፡
መታታት
ቀደም ሲል አለማየሁ፤ በ‹‹ብርሃን ፈለጎች›› የተጠቀመበት አንድ ልዩ የትረካ ስልት ያልኩትን ጉዳይ በማንሳት አጠቃልላለሁ፡፡ ይህ ልዩ የትረካ ስልት ደራሲው፤ በትረካው የሚያነሳቸውን ጉዳዮች በንፅፅር እንዲታዩ የማድረግ ስልትን እንዲቀዳጅ አድርጎታል፡፡
‹‹የብርሃን ፈለጎች›› ስዕል ሳይሆን ልብወለድ በመሆኑ፤ የህይወት መግለጫ ጥበቡ ቃል ነው፡፡ በልቦለዱ የሚገልጸውም የግንፍሌና የሞጆ ነዋሪዎች ህይወት ነው። ታዲያ በገለፃ ስልቱ ያስተዋልኩትን ይህን ስልት፤ ‹‹ግለ - ጥቁምታ›› (self - allusion) በሚል መጥቀስ ይቻል እንደሆነ አላውቅም፡፡ የሆነ ድንጋጌ የሚፈልግ ነገር ሆኖብኛል፡፡ ግን በነገሩ ብዙ አስቤበት ከጥሩ ውሳኔ መድረሱ ቢያቅተኝ ወይም የምለው ነገር ባጣ ‹‹መታታት›› አልኩት፡፡
አማርኛ ‹‹የተታታ›› ሲል የተጠላለፈ ማለቱ ነው። ይህን ቃል በዚህ መጣጥፍ ስጠቀምበት ያልተደነባ የሆነብኝን ነገር፤ ለመደንባት እና ስያሜ ለመፍጠር እንጂ፤ ደንቡ እና ስያሜው ከዚህ መጣጥፍ ውጪ ሙያ እንደማይኖረው አውቃለሁ፡፡ በልክ የተሰፋ ደንብ እና ስያሜ ነው - ለ‹‹የብርሃን ፈለጎች›› ቅኝት እንዲያገለግል የታሰበ፡፡
‹‹መታታት›› ውስጥ መደጋገም አለ፡፡ እናም ‹‹መታታት›› ያልኩት ‹‹የብርሃን ፈለጎች›› ዘዬ፤ በመደጋገም ትከሻ የሚቆም ሆኖ፤ድግግሞሹ በጥበብ ነው፡፡ ‹‹መታታት›› በዚህ የአለማየሁ ገላጋይ ድርሰት ውስጥ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ተንሰራፍቶ የሚታይ ዘዬ ነው።
ዘዬው ደራሲው አቅዶ እና አልሞ የተጠቀመበት እንጂ ወፍ ዘራሽ ወይም የአጋጣሚ ክስተት  እንዳልሆነ ምስክሩ፤ ራሱ ድርሰቱ ነው፡፡
የመታታት ስልቱን ፋይዳ በደንብ አደላድዬ የያዝኩት ባይመስለኝም፤ ሁለት ዋና ተክሮችን የተኮሰለት ይመስለኛል፡፡ በአንድ በኩል፤ የድርጊት አንድነት ችግርን ጨርሶ ባያስወግደውም፤ በሁለት ክፍሎች የተደራጀውን ትረካ፤ በስውር ስፌት ለማያያዝ ያገዘው ይመስለኛል፡፡ በሌላ በኩል፤ ለዛ ከመስጠት በተጨማሪ የገፀ ባህርያቱን ጠባይ፣ ግብር፣ መልክ ወዘተ እንደ ሰዓሊ ብሩሽ መላልሶ እየጣለ እና ኪነት እየሰራ ለማድመቅ አስችሎታል። የድርሰቱ እና የደራሲው አንድ መለያ ዘዬ (ስታይል) በመሆን ሊጠቀስ የሚችል ጉዳይ ሆኖም ታይቶኛል፡
ደራሲው ‹‹መታታት›› ባልኩት ስልት እንዴት እንደሚጠቀም ጥቂት ገፀ-ባህርያትን በምሣሌ በማንሳት እንመለከታለን፡፡ የጋንጩር እህት የሆነችውን ማናሉን ሲገልፃት፤‹‹ቀይ፣ የተዘረጠጠ አፍንጫ እና ቁርንድድ ፀጉር›› (ገፅ፣ 11) ያላት መሆኗን ይነግረናል፡፡ ከዚህ ሌላ የማናሉ መሠረታዊ መገለጫ የሆነው ያማረ ድምጧ ነው። ይህን ይዞ ይታታዋል፡፡ ነገሩን አስፋፍቼ ለመተንተን አልችልም፡፡ ሆኖም፤ ጉዳዩን ለማሳየት ያህል ጥቂት ምሣሌዎችን አቀርባለሁ፡፡
ደራሲው ድምፅዋን ከሽሮ፣ ከቢራቢሮ፣ ከሸካራው ቁርንድድ ፀጉሯ ጋር ይታታዋል፡፡ እናም፤ ‹‹ማናሉ የፀጉርሽን ሸካራ በዚህ አለስልሺው ተብላ ድምፅ ተሰጥታለች›› (ገፅ፣ 59) ይላል፡፡
እንዲሁም፤ ‹‹ከማናሉ ድምፅ ተሸርፋ ለዕይታ የበቃች ሽልምልም ቢራቢሮ በዓይኔ ሥር አለፈች›› (ገጽ፣ 60)፡፡ ደግሞም ‹‹…ከወጡ ከእንጀራው፤ የማናሉ ድምፅ ጣዕም ሆኖ መጣ ያስብላል። የማናሉ ድምፅ ቅድም ቢራቢሮ አሁን ሽሮ … በኋላ ምን ሆኖ ይመጣ ይሆን››(ገፅ፣ 63) የሚለው ተራኪው፤ ‹‹በእነ ጋንጩር ጓሮ ብቅ ስል የጠበቅኩት ጊታር አልነበረም። በዚያ ፋንታ እንደተቃኘው ጊታር ስልቱ የማያደናቅፍ የሽሮ ወጥ ዜማ ለአፍንጫዬ ደረሰው›› (ገፅ፣ 62) እያለ ድምፅን ይታታል፡፡
ቀደም ሲል እንደገለፅኩት፤ የደራሲው ትኩረት ‹‹ታሪከ ዘመን›› (Period) በመሆኑ፤ የዋናውን ባለታሪክ ጉዞ ተከትሎ ሞጆ ሲሄድ እና እኛም ከመክብብ በስተቀር ከሌሎች አዳዲስ ባለታሪኮች ጋር ስንተዋወቅ፤ ድርሰቱን አንድነት የሚያሳጣ ችግር ሊፈጠር ይችላል፡፡
የደራሲው ምርጫ የዕድሜ ዘመን ምዕራፎችን መግለጥ በመሆኑ፤ የድርጊት አንድነት ጉዳይ ሳያሳስበው ታሪኩን ከደጋ አንስቶ ወደ ቆላ ይዞ ወረደ፡ ታሪኩ ሞጆ መውረዱ ለድርሰቱ ዜማ ሰጥቶታል፡ ለእኛ ተደራስያንም አዲስ የቆላ ትዕይንት ፈጥሮ አናፍሶናል፡፡ አለማየሁ ከዚህ ቀደም በፃፋቸው ድርሰቶቹ ከአዲስ አበባ ወጥቶ አያውቅም፡፡ ስለዚህ፤ እርሱም ወደ ሞጆ ወረድ ብሎ መናፈስ የፈለገ ይመስለኛል፡፡
እርግጥ ታሪኩ፤ በአንድ ጭብጥ ዙሪያ ወይም የአንድ ድርጊት ትልም ተከትሎ የሄደ አይደለም፡፡ በአንድ ሰው የህይወት ዘመን እንጂ በአንድ ድርጊት ላይ የተመሠረተ አይደለም፡፡ ሆኖም፤ አንዱን በሌላኛው ዓይን ለማየት፤ በሁለቱ መካከል ተመሳሳይነት ለመፍጠር በሚያደርገው ጥረት ነው፡፡ ሞጆ እና ግንፍሌ፤ እንዲሁም በሁለት የ‹‹ዘመን ግቢ›› የሚገኙ ሁነቶች  አንድነት ያገኙት በመታታት መላ ነው፡፡
አለማየሁ፤ አንድ ገፀ ባህርይ በመከተል፤ አንድን የዘመን ስፍር (ልጅነት) በመውሰድ፤ ከአንድ የባህርይ ምንጭ በተቀዳ የአንድ ገፀ- ባህርይ የተለያዩ ድርጊቶች የተደራጀ ታሪክ ውስጥ አንድነት ለመስጠት የሞከረው በመታታት የትረካ ዘዴው ነው፡፡

Read 2123 times