Saturday, 22 March 2014 12:48

ወጣቶች የነገሱበት “አዲስ የጥበባት ትርኢት”

Written by  ይትባረክ ዋለልኝ Yetebarek@yahoo.com
Rate this item
(2 votes)

       አንድ ቀን ሁለት ኢትዮጵያዊያን ጓደኛሞች እንደወትሮው ሻይ ቡና እያሉ ይጨዋወታሉ። በጨዋታቸው መሃል አንደኛው አንድ ሐሳብ ያመጣል፡፡ “ለምንድን ነው እኛ ሀገር ብዙ ሰዓሊያን የሚሣተፉበትና በርካታ የስዕል ስራዎች የሚቀርቡበት ፕሮግራም የማይዘጋጀው?” ሃሳቡን በጥሞና ያደመጠው የጥበብ አፍቃሪ፤ ከዚያች ሰዓት ጀምሮ የወዳጁን ትልቅ ሃሳብ እውን ለማድረግ ቆርጦ ተነሣ፡፡ የዚህ ሃሳብ አመንጪም “ይህን ታላቅ ሐገራዊ ስራ ከግብ ለማድረስ እኔም ሆንኩ የምመራው ድርጅት ካጠገብህ ሆነን እንደግፍሃለን” ሲሉ ቃል ገቡለት፡፡ እናም “Addis Art Fair” (አዲስ የጥበባት ትርኢት) ተወለደ፡፡
የዚህ ሃሳብ አመንጪ የደርባን ሲሚንቶ ፋብሪካ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሃይሌ አሰግዴ ሲሆኑ  ሃሳቡን ወደ ተግባር የለወጡት ደግሞ አርቲስት አበበ ባልቻ፤ ከዶ/ር ኤልሣቤጥ ወ/ጊዮርጊስ፣ ከረዳት ፕሮፌሰር በቀለ መኮንን እና ከአለ የስነጥበባት ት/ቤት ጋር በመሆን ነው፡፡
ባለፈው ቅዳሜ መጋቢት 6 ቀን 2006 ዓ.ም በሚሌኒየም አዳራሽ በታላቅ ድምቀት የተከፈተው “Addis Art fair” (አዲስ የጥበባት ትርኢት) በይዘቱም ሆነ በአቀራረቡ ለየት ያለ ነበር። የስነጥበብ ዓውደ ርዕዩ የተከፈተው በተለያዩ የኪነጥበብ ዝግጅቶች ታጅቦ ነው፡፡ ከ15ሺህ ሰው በላይ በሚይዘው የሚሌኒየም አዳራሽ፤ በመክፈቻው ዕለት የቀረበው የሲንፎኒ ሙዚቃ ልዩ ስሜት የሚፈጥር ነበር፡፡ እምብዛም በሐገራችን ያልተለመደው የሲንፎኒ ሙዚቃ፤ በዚህ ግዙፍ አዳራሽ ውስጥ ጥራቱን በጠበቀ የድምጽ ስርዓት ሲንቆረቆር የብዙዎቻችንን ቀልብ ማርኳል፡፡ በተለይ ከሲንፎኒ ኦርኬስትራው ጀርባ ባለው ግዙፍ ስክሪን በርካታ ህፃናት ካሚዮን ላይ የሚፈልጉትን የስዕል ስራ ሲሰሩ የሚያሣየው ፊልም፣ ከሲንፎኒ ሙዚቃው ጋር ልዩ የጥበብ ህብር ፈጥሯል፡፡
100 የስነጥበብ ባለሙያዎች በተሣተፉበት በዚህ አውደርዕይ፤ ከ600 መቶ በላይ የስዕል፣ ቅርፃቅርፅ እና የዲዛይን ስራዎች ለዕይታ በቅተዋል፡፡ በ“አዲስ የጥበባት ትርኢት” ላይ የተሳተፉት የስነጥበብ ባለሙያዎች በሙሉ ወጣቶች ናቸው፡፡ አብዛኛዎቹ ከዚህ ቀደም ስራዎቻቸውን ለተመልካች የማሣየት እድል ያላገኙ ሲሆኑ የተለያዩ ጋለሪዎችም ተሣታፊ ነበሩ፡ በዚህ ዝግጅት ላይ ከቀረቡት ስራዎች መካከል በቅርቡ ህይወታቸው ያለፈው የሰዓሊ ኤርሚያስ ማዘንጊያ እና የሰዓሊ ማቲያስ ሉሉ ውብ የጥበብ ስራዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ የስነጥበብ ትርኢቱ በተለይ ለወጣት የስነጥበብ ባለሙያዎች ትልቅ እድል የፈጠረ እንደ ነበር ብዙዎች መስክረዋል - ወጣት ሰዓሊያንን ጨምሮ፡፡ ስራዎቻቸው በጥበቡ አፍቃሪያን ከመጎብኘታቸውም ባሻገር የጥበብ ፍሬያቸውን በመሸጥ የኢኮኖሚ አቅማቸውን እንዲያሣድጉና ለተሻለ የጥበብ ስራ እንዲተጉ መልካም አጋጣሚ ፈጥሮላቸዋል፡፡
በአገራችን ህብረተሰቡና የስነ-ጥበብ ስራው በእጅጉ የተራራቁ እንደነበር የሚታወቅ ነው፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን አዲስ አበባ በሚገኙ ጋለሪዎችና ሙዚየሞች እንዲሁም ሆቴሎች ውስጥ በሚዘጋጁ የስዕል አውደርዕዮች ላይ የተስፋ ብርሃን መፈንጠቅ ጀምሯል፡፡ በሚሌኒየም አዳራሽ በተዘጋጀው የጥበባት ትርኢት ላይ የተመልካች ጐርፍ ተመልክቼአለሁ፡፡ ለአራት ቀናት ክፍት ሆኖ የዘለቀውን የጥበባት ዓውደርዕይ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ጐብኝተውታል፡፡ በተለይ እኔ በሄድኩባቸው ሁለት ቀናት፣ በርካቶች በቡድን በመሆን እንዲሁም ቤተሰቦች ልጆቻቸውን እየያዙ የስነጥበብ ስራዎቹን ሲመለከቱ ታዝቤያለሁ፡፡ ተመልካች ስራዎቹን ተመልክቶ ከመሄድ በዘለለ ከሰዓሊያኑ ጋር የመወያየት ዕድል ማግኘቱንም አስተውያለሁ። በብዙ አውደርዕዮች የስነ-ጥበብ ስራዎችን ሲገዙ የሚታዩት የውጭ አገር ዜጎች ነበሩ፡፡ በሚሌኒየሙ “አዲስ አርት ፌር” ግን ብዙ ኢትዮጵያዊያን የጥበብ ሥራዎችን እንደገዙ ለማወቅችያለሁ፡፡ በእርግጥ የስነ-ጥበብ ስራዎቹ ዋጋ እንደሌላው ጊዜ የተሰቀሉ አልነበሩም፡፡ ከፍተኛው ዋጋ 8 ሺህ ብር ነበር፡፡ እንደ እኔ አተያይ የጥበብ ስራዎች ዋጋ ዝቅ መደረጉ፣ ኢትዮጵያዊያን በስነጥበብ ገበያ ውስጥ እንዲገቡ በር ከመክፈቱም ባሻገር ከጥበብ ሥራዎች ጋር የበለጠ ቅርርብና ትውውቅ እንዲፈጥሩም ዕድል ሰጥቷቸዋል፡፡
በቅርቡ ለንባብ የበቃው “African Business” መጽሔት፤ “Fortunes to be made from African Creativity” በሚል ርዕስ ባወጣው ጽሑፍ፤ በርካታ የባህልና ጥበብ መፍለቂያ የሆነችው አፍሪካ ከመስኩ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንዳላገኘች ያትታል። መጽሔቱ እንደሚለው፤ የፈጠራ ኢንዱስትሪ ለዓለም ኢኮኖሚ 2.2 ትሪሊዮን ዶላር ወይም 7 በመቶ ድርሻ ያለው ሲሆን እ.ኤ.አ በ2012 ብቻ ምዕራባዊያን 595 ቢሊዮን ዶላር ከኢንዱስትሪው አግኝተዋል፡፡ ከዚህ የትሪሊዮን ዶላር ገበያ የአፍሪካ ድርሻ ከአንድ ፐርሰንት በታች እንደሆነ የጠቆመው መጽሔቱ፤ አፍሪካ በባህልና ጥበብ ዙሪያ ብዙ መስራት እንደሚጠበቅባት አትቷል፡፡ እንደ ሚሌኒየም አዳራሽ ዓይነት ዝግጅቶች ሳይቋረጡ በዘላቂነት ከቀጠሉ የሥነ ጥበብ ዘርፉ አስደናቂ እመርታ የሚያሳይበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም ይላሉ የዘርፉ ባለሙያዎች፡፡ ነፍሱን ይማረውና የ“አዲስ አድማስ” ጋዜጣ መስራችና ባለቤት በነበረው በአቶ አሰፋ ጐሣዬ ፊታውራሪነት “Addis Art Week” በሚል ርዕስ ተዘጋጅቶ አዲስ አበባን የነቀነቀው የጥበብ ዝግጅት በአርአያነቱ ዘወትር ይጠቅሳል፡፡
የሰሞኑን የጥበብ ትርኢት አስመልክቶ አስተያየቱን የሰጠው ሰዓሊ ዳዊት ገርሱ፤ ዝግጅቱ በዚሁ ከቀጠለ ነገ ትልቅ ደረጃ ላይ እንደሚደርስ ተስፋ አለው፡፡ “አዲስ አርት ፌር በሚቀጥሉት ጥቂት አመታት ውስጥ በምስራቅ አፍሪካና በመላው አፍሪካ እንዲሁም በዓለም ላይ ደምቆ የሚታይ ትልቅ አቅም እንዳለው ያስተዋልኩበት ዝግጅት ነው” ብሏል፤ ሰዓሊው፡፡ የላፍቶ አርት ጋለሪ ኩሬተር ሰዓሊ ኑሩ አበጋዝ በበኩሉ፤ “ይህ የስነጥበብ ትዕይንት፤ የሐገራችንን የስነጥበብ ባለሙያዎች በእጅጉ የሚደግፍና የተዘበራረቀውን የስነጥበብ ገበያ ስርዓት ለማስያዝ የሚያስችል ነው።” ብሎ ያምናል፡፡ አውደርዕዩ በየአመቱ ሳይቋረጥ ይበልጥ እየደመቀ እንደ ሚቀጥልም ያልማል የሥነ ጥበብ ዝግጅቱን ለመጎብኘት የመጡ የክልል ተመልካቾች፤ “አውደርዕይው በሚዲያዎች በደንብ አልተዋወቀም፤ ከሳምንት በፊት ቀድሞ ቢነገር ብዙ የስነ-ጥበብ አድናቂዎች ይመጡ ነበር” ሲሉ አስተያየታቸውን ገልፀዋል፡፡ የጥበብ ትርዒቱ ለተመልካች ክፍት የተደረገበት ጊዜ በጣም አጭር ነው የሚሉ አስተያየት ሰጪዎችም አልጠፉም፡፡ አብዛኞቹ ግን ተመሳሳይ ስጋት ይጋራሉ፡፡ “አዲስ አርት ፌር በየዓመቱ ሳይቋረጥ ይካሄድ ይሆን?” የሚል፡፡
እኔ በበኩሌ፤ ይህ ረጅም ዓላማን ይዞ የተነሣ የጥበብ ዝግጅት፤ ነገ ከኢትዮጵያም አልፎ በአህጉር እና በአለም ደረጃ ትልቅ ስምና በርካታ ክንውኖች ያሉት ዓመታዊ ፕሮግራም እንደሚሆን ትልቅ ተስፋ አለኝ፡፡ የዘንድሮውን ዝግጅት ደፋ ቀና ብለው ለስኬት ያበቁት ሁሉ ምስጋና ሲያንሳቸው ነው፡፡ አሁንም በርቱ እላቸዋለሁ፡፡    

Read 1486 times