Saturday, 30 November 2013 11:54

አርቲስት ስለሺ ደምሴና የሙዚቃ ፍልስፍናው

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(5 votes)

የቱሪዝም ትልቁ ነገር ኢትዮጵያዊነትህን ለሌላው መሸጥ ነው…
“ጋሽ አበራ ሞላ” ይኑርም አይኑርም፣ ጥሩ ኢትዮጵያዊ አባወራ ነው…
ባለፈው ሰሞን ከአርቲስት ስለሺ  ደምሴ ጋር የተገናኘነው ቦሌ ሚሌኒዬም አዳራሽ ግቢ ውስጥ ነው፡፡ ከአጋሮቹ ጋር

በመተባበር ለገና በዓል ‹‹ያምራል አገሬ›› የሚለውን አዲስ አልበሙን በልዩ የመድረክ ትርኢት ለማቅረብ አስቧል፡፡

ከሁለት ወራት በፊት አልበሙ በብሄራዊ ትያትር ሲመረቅ ጋሽ አበራ ሞላ ከ250 በላይታዳሚዎችን ያረካ ትርኢት

አቅርቧል፡፡ ተመሳሳይ ትርኢት በሚጠበቅበት በገናው የሙዚቃ ዝግጅት የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች፤ ሙዚቃ አድናቂዎችና

የክብር እንግዶች የተካተቱበት 12ሺ ተመልካቾች ይታደማሉ፡፡ ከ10 በላይ የሙዚቃ መሳርያዎች የሚጫወቱ

ባለሙያዎችና ከ20 በላይ ዘማሪዎች ያሰባሰበ የኪነጥበብ ቡድንም ያሳትፋል። አርቲስት ስለሺ ደምሴ ከአዲስ አድማስ

ጋር ባደረገው ልዩ ቃለምልልስ ስለታሪክ አዋቂነቱ፤ ስለተረት አባትነቱ ታሪኮችና ተረቶችን ስለሚያገኝባቸው ምንጮቹ

እና ይዘታቸው፤ ምእራባውያን በእጅ አዙር ቅኝ አገዛዛቸው ስላስጣሉን ወይም ስላሳጡን ባህላዊ ትውፊቶች እና ሌሎችም

ጉዳዮች ይናገራል፡፡
በሙዚቃ ባለሙያነትህ የሙዚቃ መሳርያዎችን መጫወት ብቻ ሳይሆን በመስራትና በማስተማርም ትታወቃለህ፡፡ ደግሞም

ታሪክ አዋቂ ነህ፡፡ የተረት አባትም ትመስለኛለህ ፡፡ ለመሆኑ ታሪክና ተረት ከሙዚቃ ጋር ምን ያስተሳስራቸዋል?
ህብረተሰቡ ውስጥ በተረት፤ በምሳሌ፤ በፍልስፍና፤ በምክር፤ በትንቢት መልክ የሚነገሩ ታሪኮችን በአንድ ላይ እና

በተናጠል ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገሩ የቆዩ  አፈታሪኮች ናቸው፡፡ ብዙዎቹ በፅሁፍ የወጡና የቀረቡ አይደሉም፡፡

ከድሮ ጀምሮ በቃል ሲነገሩ የኖሩ ናቸው። እየተወራረደ እና እየተወራረሰ የመጣ ባህል ነው፡፡ ራሱን የቻለ ትልቅ

ማህበረሰባዊ ትውፊት ነው። ስለ አንድ ህብረተሰብ ልዩ ልዩ ታሪኮችን መተረክ ቀደም ሲል የነበረ ነውና አንድም

በተናጠል ራሱን ችሎ ይሄዳል፡፡ በሌላ በኩል  ከሙዚቃ ጋር ተያይዘው  ተረትና ታሪክ የሚሰሩበት ባህልም አላቸው፡፡

ከሙዚቃ ጋር ተቀናጅተው ይሰራሉ፡፡
ምሳሌ ላቅርብልህ፤ ሁለት ሌቦች ናቸው፡፡ ከብት እንስረቅ ብለው አንድ ሃብታም ቤት ይገባሉ፡፡ አንደኛው አዝማሪ

ነው፡፡ አዝማሪው ምድነው የሚያደርገው ሰዎቹን በሙዚቃ ያጫውታል፡፡  ሌላኛው በጓሮ በኩል ሰተት ብሎ ገብቶ

ከብቶቹን ነድቶ ሊያወጣ ነው፡፡ በዚህ  ተስማምተዋል፡፡  ይህ ተረት ነው፡፡ ከጀርባው ሙዚቃ አጅቦት እንዴት ይዘጋጃል

መሰለህ፡፡
በጓሮ ዞሮ የገባው ሰውዬ ከብቶቹን ከበረት እያስወጣ ሲነዳ፣ ግቢው ውስጥ ሃይለኛ ውሻ ስላለች “ውውውውውው…”

ብላ አንዴ ስታናጋው፣ የቤቷ እመቤት በጓሮ በኩል የሆነ ነገር ስለሰሙ፤  ‹ኧረ ምንድነው የከብት ኮቴ ይሰማል› እያሉ

ይናገራሉ፡፡ ይህን ጊዜ ቤት ውስጥ ያለው አዝማሪ ‹‹አሮጊቷ መቼም አትተኛ ፤ ነይ ቡቺ ጥጥጥጥጥጥ” እያለ ያዜማል፡፡

ውሻዋ “ውውውውውው” ማለቷን ስትቀጥል፤ አዝማሪው “ነይ ቡቺ ጥጥጥጥጥ” እያለ ደጋግሞ ሲጠራት ጩኸቷን ትታ

ወደሱ ትመጣለች። አዝማሪው በጨዋታው የቤቱን ሰዎች አዘናጋ ማለት ነው፡፡ ሌላኛው ከብቶችን ዘርፎ ይወጣል። ተረቱ

እንዲህ በሙዚቃ ተውቦ አንድ ላይ ተቀናጅቶ ሊቀርብ ይችላል፡፡ ይህን ተረት እኔ በሙዚቃ ስጫወት መጀመርያ ታሪኩን

እንደተረት እተርከዋለሁ፡፡ ታዳሚው ሁኔታው ፍንትው ብሎ እንዲታየው  ነው፡፡ በዚህ መልክ የሚነገሩ የተለያዩ አይነት

ተረቶች፣ አባባሎች፣ ዘይቤዎች፣ ፈሊጦች ከሙዚቃ ጋር እየተቀናጁ የሚሄዱበት መንገድ ነው፡፡
እነዚህን ታሪኮችና ተረቶችን ከየት ሰበሰብካቸው? ከተለያዩ የህይወት ተመክሮዎች ነው? ከሰዎች ሰምተህ ነው? ታሪክ

አጥንተህ ነው? በፈጠራ ችሎታህስ የሰራሃቸው አሉ?
 ሲነገሩ የነበሩ ታሪኮችን በመስማት ነው፡፡ ቀደም ሲል ከቤተሰቦቼ በተለይ ከአባቴ ብዙ ታሪኮች ይነገረኝ ነበር፡፡ አባቴ

ክራር ተጫዋች፤ ተረት ነጋሪና ታሪክ አዋቂ ነበር፡፡ ብዙ ነገሮች ያውቃል፡፡ በየጊዜው አዳዲስ ነገሮችን እየነገረ ነው

ያሳደገኝ፡፡ ሌላው ምንድነው አብሮ ከሚኖሩ ጎረቤቶች ጋር ቤተሰብ ቡና ሲጠጣ ከነበሩ ወጎች ነው። የድሮ ሰፈሬ

ጃንሜዳ አካባቢ የሚገኘው ቸሬ የተባለ አካባቢ ነበር፡፡ በዚያ ሰፈር ሰዎች ድግስ፣ ሰርግ፣ ለቅሶ እና ተስካር

የምትሰማቸው ብዙ ጨዋታዎች እና ታሪኮች አሉ፡፡ ይገርምሃል እኔ በልጅነቴ አሮጊቶችና አዛውንቶች ተሰብስበው

ሲያወጉ፤ ቡና ላይ የነበሩ ጨዋታዎችን መስማት ልማዴ ነበር፡፡ ብዙ ብዙ ታሪኮችን ሲጫወቱ ዛሬም ድረስ

አስታውሳቸዋለሁ፡፡ ቡና ተፈልቶ ጎረቤት ከተጠራ በኋላ እያንዳንዱ ጎረቤት በራሳቸው የጨዋታ ለዛ የሚያወራቸው

ታሪኮች ነበሩ፡፡ ቡና እስከ ሶስተኛ ይጠጣል፡፡ ሶስተኛ ሳይጠጣ ማንም ከቡናው አይነሳም።  ሲጫወቱም ትዝ ይለኛል፡፡

በሰርግና በሃዘን ህብረተሰቡ በእነዚህ ታሪኮች ፈጠራ ውስጥ ይኖራል፡፡ የአገራችን አባቶች ቋንቋቸው የረቀቀ፤

አመለካከታቸው የዳበረ፤ ፍልስፍናቸው ብዙ የሚያስረዳ ነው፡፡ የእነሱ ታሪኮች እና ጨዋታዎች ከቤተሰብ፤ ከጎረቤት፤

ከማህበረሰብ፤ ከአፈታሪክ ዘመን ከዘመን ሲሸጋገሩ የቆዩ ናቸው፡፡
ሌላው ምንጭ ታሪክ ነው፡፡ ብዙ የኢትዮጵያን ታሪክ የከተቡ መፅሃፍት ደግሞ እዚህ አገር ከተዘጋጀው እና ከሚገኘው

ይልቅ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ተሰብስበው የሚገኙት ይልቃሉ፡፡ በፖርቹጊዝ፣ በስፓኒሽ፣ በጣሊያንኛና በእንግሊዝኛ

ቋንቋ ፀሃፊዎች የተዘጋጁ ናቸው፡፡ በ14ኛው እና በ16ኛው ክፍለዘመን ወደ ኢትዮጵያ እየመጡ ብዙ ጥናት ያደረጉ አሉ፡፡

እነዚህ ፀሃፍት ከኢትዮጵያ ተረቱን፣ አባባሉን፣ ዘይቤውን ወስደው በተለያዩ ቋንቋዎች ፅፈዋቸው ይገኛሉ፡፡ አንድ

በፈረንሳይኛ የተዘጋጀ መፅሃፍ አለ፤ ስለአማርኛ ቋንቋ የተፃፈ ነው፡፡ በዚህ መፅሃፍ በጣም የሚገርምህ አገኘሁ እንግዳ

ስለተባሉ በሐይለስላሴ ጊዜ ስለነበሩ ታዋቂ ሰዓሊ ይናገራል፡፡ በዚያን ጊዜ የነበረውን ብር ምስል የሰሩ ናቸው፡፡

በበጌምድር፣ በወሎና በሸዋ አካባቢዎች የተነገሩ  የድሮ ተረቶችን ከግዕዙ እና ከሰምና ወርቁ እያጣቀሰ፤ ከፈረንሳይኛው

ቋንቋ ጋር እያነፃፀረ ያቀርባል፡፡ በዚህ መፅሃፍ የአገኘው እንግዳ  ታሪክ ምንድነው? ጓደኛሞች ስለነበሩ አንድ በሬና አህያ

የሚተርክ ስዕላዊ ድርሰት ነው፡፡ በሬ እና አህያው በአንድ ሃብታም ቤት ሲያገለግሉ ቆይተው አቅም ሲያንሳቸው በሬው

እንዳይታረድ፤ አህያው ደግሞ እንዳይባረር ሰግተው ሰነበቱ፡፡ አልቀረላቸውም፤ ብዙም ሳይቆይ አባወራው ከቤቱ

ያሰናብታቸዋል፡፡ የኖሩበትን አገር ጥለው በመንገድ ሲሄዱ አንድ ደግሞ ከዶማ በቀር በሬ እና አህያ አይቶ የማያውቅ

የተቸገረ ደሃ ገበሬ ያገኛቸውና…. እንዲህ እያለ የሚቀጥል ደስ የሚል ታሪክ ነው፡፡
ብዙ ታሪካዊ ስብስቦችና ተረቶች በዚህ መልክ በውጭ አገር ተሰባስበው የተዘጋጁበት ነው፡፡ በሙዚቃውም ታሪክ ስብስቡ

በአብዛኛው በፈረንሳውያን፣ በፓርቱጋላዊያን በጣሊያናዊያን እና በሌሎች አገራት ሰዎች የተሰሩ ናቸው።
ከተረቶች እና ከታሪኮቹ ምን ምን ይገኛል?
ለምሳሌ የከበደ ሚካኤልን ታሪክና ምሳሌ ብትወስደው፤ በዚህ መፅሃፍ የሚገርም የጊዜን ምስል ያሳያል፤ የማይረሳ ምክር

ይሰጥሃል፤ ልዩ ልዩ የህይወት ዘዴዎችን ይነግርሃል፤ የተለያዩ አመለካከቶችን ያስገንዝበሃል፡፡ የአኗኗር ዘዴ፤ የአመለካከት

ዘዴ፤ የፈጠራ ዘዴ ትማርበታለህ፡፡ አሁን ለምሳሌ በከበደ ሚካኤል ታሪክና ምሳሌ መፅሃፍ ውስጥ የአንድ አዝማሪ እና

ወራጅ ውሃ ታሪክ አለ፡፡ አዝማሪው ያ ወንዝ በጎርፍ ሞልቶበት በመሰንቆው ለወንዙ፣ ይጫወትለታል፡፡ ከታች ወንዙ

የአዝማሪውን ጨዋታ ሰምቶ ሲያልፍ፣ ከላይ ያልሰማው ይመጣል፡፡ ሰውዬው በሰማ እና ባልሰማ ወንዝ ላይ ሲተክዝ

ታስተውላለህ፡፡ ሰውዬው ይህን ጎርፍ ባዜምለት ችግሬን አይቶ ያቆምኛል ብሎ አስቦስ እንደሆነ ማን ያውቃል፡፡ የሰማው

ሲሄድ ያልሰማው ሲመጣ እያለ ሲያዜም፣ ይህ ትልቅ አመለካከት ነው፡፡ የጠለቀ ነገር ነው። ብዙ እንድታስብ የሚያደርግ

ነው፡፡ አንድ ዋና ከሆነ ነገር የተለያየ አመለካከት መኖሩን የሚያሳይም ነው፡፡ አሁን በከበደ ሚካኤል ታሪክና ምሳሌ

ያለውን ያን አዝማሪ ሞኝ ልትለው ነው፡፡ አዝማሪው ብልህ ነው፡፡ ለዚያ ወንዝ እንደዚያ ብሎ ከልቡ ሲነግረው

አስበው፡፡ ያ ወንዝ ሰምቶ የሚቆም መስሎት እንደሆነስ፡፡ መፅሃፉ እንደሚለው፤ ክርስቶስ በውሃ ላይ ሄዷል፡፡ ከዚያ

በኋላ በውሃ ላይ የሄዱ ሰዎች የሉም፤ አሉ፡፡ የሰው ልጅ ከዚህም በላይ ሊያስብ ሊሰራ ይችላል ብሎ የሚያሳይ ነው፡፡

ከአናኗር ባህል ብልህነት እንደሚገኝ፤ ፈጠራ ሊኖር እንደሚችል የምትማርበት ነው፡፡
በተለያየ  ተፅእኖዎች ሳቢያ እነዚህ የገለፅካቸውን የባህል ትውፊቶች የራቅናቸው፤ የተውናቸው ይመስላል። መቼም ይህ

ሁኔታ ብዙ ነገር አሳጥቶናል አይደል?
ዛሬ በሚሰሩ የሙዚቃ ስራዎች እንዲህ በብቃት የሚታይ ትእይንት የሚሰራበት ሁኔታ ብዙም የዳበረ አይደለም፡፡

ሙዚቃዎች ከህብረተሰቡ ነባራዊ ሁኔታ እና አኗኗር ምንም አይነት ግንኙነት የላቸውም፡፡ ይህ በመሆኑ ከድሮ የባህል

ትውፊቶቻችን ጋር ተለያይተናል። ከኢትዮጵያዊነታችን ጋር የተሳሰረ የነበረው ሁሉ ግንኙነቱ እየጠፋ ቆይቷል፡፡

የመጀመርያው ያጣነው ስነምግባርን ነው፡፡ ስነምግባር ማለት ማክበርን፤ ጎንበስ ብለህ ሰላምታ መስጠትን፤ ተነስቶ

ተቀመጡ ማለትን፤ ማንኛውንም ሰው እንደእድሜው እንደማንነቱ ማክበርን … ዛሬ ቁምነገር አይሰጠውም፡፡ ይህን

በትምህርት ቤት አትማረውም፡፡ አክብሮት ባለማወቅህና ባለመማርህ ለሰው ክብርና ዋጋ አትሰጥም፡፡ ትሳደባለህ፤

ትሳለቃለህ፤ መብትህን ታጣዋለህ፤ ከወገኖችህ አክብሮት ስታጣ ቅሬታ ይሰማሃል፡፡ ማንነትህን ታጣለህ፡፡ ሌላው

የምታጣው ጠቃሚ እና ብልህ የሆኑ ዘዴዎችን ፈጠራዎችን ነው፡፡ አሁን ለምሳሌ ዛሬ ክራር፤ መሰንቆ፤ በገና የሚሰራ

የለም። እነዚህን ባህላዊ ትውፊቶችን ከኛ ተርፎ ለሌሎች መሸጥ የምንችልበት ጊዜ መሆን ነበረበት፡፡ የቱሪዝም ትልቁ

ነገር ኢትዮጵያዊነትህን ለሌላው ዓለም መሸጥ ነው፡፡ አመጋገቡን፤ አለባበሱን፤ ብልህነቱን አኗኗሩን፤ ስራውን

በኢትዮጵያዊ ትውፊት አዳብሮ፤ ራስን መሆን አዳጋች የሆነበት ደረጃ ላይ ደርሰናል፡፡ አሁን እኔና አንተ ኮራጅ ሆነናል፡፡

ከውጭ የሚመጣ ሰልባጅ ለብሰህ፣ ቤትህን አጊጠህ፣ ያልሆነ ነገር ይዘህ ከሌላ ዓለም የሚመጣ ሰው ከአንተ የሚያገኘው

ነገር የለም፡፡ ስለዚህ ማነትህን ስታጣ አገርህን ትጎዳለህ፤ ራስህን ትጎዳለህ፡፡ ቀደም ሲል ስለኢትዮጵያ ሲነገር የነበረውና

የኖረው ቅድመ ስልጣኔው፤ ታሪኩ ፤ፍልስፍናው ፤ዘይቤው የክዋክብት ጥናት በለው፤ ምርምሩ በለው … እነዚህ ሁሉ  አሉ

የሚባሉት ነገሮች ጠፉ ማለት ነው፡፡ እነዚህ የኢትዮጵያዊነት መገለጫዎች ከጠፉ ከውጭ አገር የሚመጣ ቱሪስት ምንም

የሚያገኘው ነገር አይኖርም፡፡ እኛ ቋንቋችንን ብናዳብር፤ መፅሃፍት ብንፅፍ፤ ያሉትን ትውፊቶችን በመፅሃፍ ብናስቀምጥ፤

በሙዚቃ ብናዘጋጅ የሌላው ዓለም ሰው የማያገኘው ልዩ ነገር በመሆኑ ይገዛል፡፡ አንድ የውጭ አር ዜጋ እዚህ አገር ወዳለ

ሙዚቃ መሳርያ መሸጫ ቢሄድ የሚያየው ጊታሩን፤ ኪቦርዱን፤ ሳክስፎኑን ነው እንጂ ኢትዮጵያዊ የሆነ ክራር፤

እምቢልታ፤ ዋሽንትና ከበሮ አያገኝም፡፡
ትልቁ ተፅእኖ በእጅአዙር  ቅኝ አገዛዝ ተቀይሮ የተፈጠረው  ነው፡፡ ሁኔታው በቀጥታ አሽከር አያደርግህም፡፡

በትምህርት፤በአስተዳደር፤ በቋንቋ እና በሁሉም መስክ የእነሱን አካሄድ እንድትከተል በማድረግ ማንነትህን ማጥፋት

ነው፡፡  ዛሬ ዘመናዊ ትምህርት ቤቶች የተባሉት በምዕራቡ ዓለም አስተሳሰብ የተቀረፁ ናቸው። የኢትዮጵያ  ታሪክን

ትተህ የምትማረው ስለ አውሮፓ ሆኗል፡፡ ድሮ  በተማሪ ቤት በእነ“ለማ” በ“ገበያ” ምንባቦች የተማርንበት ጊዜ ላይ

ደርሸበታለሁ፡፡ በእነለማ ገበያ ፈንታ ታድያ ከውጭ እነ ሬድ ፕራይመር፣ እነ ሪደር ዋን፣ እነ ማርች ኦፍ ታይም የተባሉ

መፅሃፍት መጡ። ይገርምሃል እኔ ለማ በገበያ፤ ለማ በትምህርት ቤት የተባሉ መፅሃፍትን እያነበብኩ ነው ያደግሁት፡፡

ህፃናት የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ሲገቡ ለጀማሪ የሚሆን የአፍ መፍቻ ቋንቋ በንባብ የምትማርባቸው የታሪክ

መፅሃፍት ናቸው፡፡ ለማ በእነዚህ መፅሃፍት ውስጥ ባሉ ታሪኮች ውስጥ የሚገኝ ዋና ገፀባህርይ ነው፡፡ ያኔ ገጠርም ሆነ

ከተማ ልጅ አንድ አይነት አስተዳደግ ነው ያለው። ለማ ቁምጣ የሚለብስና ቁንጮ ያለው ትንሽዬ ልጅ ነው።  አሁን

ለምሳሌ “ለማ በገበያ” በሚባለው ታሪክ ለማ ዘወትር በጠዋት ተነስቶ የአባቱን ጥራጥሬዎች በየስልቻው አስገብቶ፣

አባቱን አጫጭኖ፣ ቁምጣውን ለብሶ እና በትሩን ይዞ፣ አባቱን እያገዘ ገበያ ይወጣል፡፡ የተጫነውን የእህል ጆንያ

ያወርዳል፤ ለገበያተኛ ይሰፍራል፡፡ ለማ ጎበዝ ልጅ ነው፡፡ታታሪ ነው … እያለ ታሪኩ ምክሩን ያስተላልፋል፡፡ “ለማ

በትምህርት ቤት” በሚለው ታሪክ ደግሞ ሰኞ ሆነ፤ ለማ በጠዋት ተነስቶ ልብሱን አዘጋጅቶ ወደ ተማሪ ቤት ሄደ፤

ትምህርት ቤት ገብቶ ሲማር ምን ያህል ጎበዝ እንደሆነ ታታሪነቱን  ያወጋል፡፡ “ለማና ዘመዶቹ” በሚለው ታሪክ ደግሞ

ለማ በቤተሰቡ ያለውን ጨዋነት ፤ ስነምግባሩን ሲማር እየተረከ የሚመክር ነው፡፡ የለማ ታሪኮች በየትምህርት ቤቱ

መማርያ መፅሃፍት ሆነው የተዘጋጁ ነበሩ፡፡ ከዚያ በፊት እኔ ትዝ ይለኛል … ትምህርት ቤት ሄጄ የለማን ታሪኰች

ሸምድጄ፣ እቤት ስገባ እናቴ የማገኛት እንጀራ እየጋገረች ይሆናል፡፡ ለማ ጎበዝ ልጅ ነው፤ ለማ ትምህርት ይወዳል

እያልኩ ሳነበንብላት፤ “ጎሽ የተባረከ ልጅ ነው፤ እግዚአብሄር ይስጠው” እያለች ትመርቀው ነበር፡፡ የለማ መፅሃፍት

ከየትምህርት ቤቱ መጥፋት የጀመሩት በ1950ዎቹ መጨረሻ አካባቢ ነው፡፡  ከዚያ በኋላ የውጭ መፅሃፍት መጡ፡፡ ከዚያ

ኋላ ትዝ የሚለኝ ተማሪ ቤቱን ያጥለቀለቁት የእነ ሎንግማንሺፕ ህትመቶች የሆኑ የብሪቲሽ መፅሃፍት ናቸው፡፡ በእነዚህ

መፅሃፍት በትምህርት ቤት ውስጥ ማንነትህን ረስተህ፣ በሌላው አገር ታሪክ መማር የምትገደድበት ጊዜ ሆነ፡፡
የለማ ታሪኮች ከቀሩ በኋላ ሬድፕራይመር የተባለው መፅሃፍ መጣ፡፡ በዚህ መፅሃፍ በቀይ ቀለም በተፃፈ ንባብ በምስል

ድመት አለች፤ ጠረጴዛ ስር ቁጭ ብላለች፤ ከስሩ ‹‹ዘ ካት ኢዝ አንደር ዘ ቴብል ››ይላል ፤ በሌላ ምስል ደግሞ ድመቷ

ጠረጴዛው ላይ ወጥታ ከምትታይበት ስር ‹‹ዘ ካት ኢዝ ኦን ዘ ቴብል›› የሚለው አለ፡፡ መፅሃፉ ገፁ በሙሉ በድመቷ

የተሞላ ነው፡፡ በመፅሃፉ አዲስነት እና ማራኪ አቀራረብ ልጅ ስለሆንን በጉጉት እንሸመድደው ነበር። እኔ እቤት ገብቼ

እናቴ ዛሬ እንግሊዘኛ ተማረ ጎበዝ ትለኛለች ብዬ፤ ‹‹ዘ ካት  ኢዝ ኦን ዘ ቴብል›› ፤‹‹ ዘ ካት ኢዝ አንደር ዘ ቴብል››

እያልኩ ስለፈልፍ ብትሰማኝ ብትሰማኝ ለማ የለም፤ በኋላ ‹‹አንተ ይከትክትህና  መድሃኔያለም፤ ለማ የት ሄዶ ነው ካት

ካት የምትለው›› ብላ በማማሰያ ታባርረኛለች፡፡ እናቴ ይህ የለማ ነገር አንገብግቧት፣ በአይምሮዋ ገብቶ፣ ዣንጥላዋን ይዛ  

ትምህርት ቤት ሄደች፡፡ በአጠቃላይ ለማለት የፈለግሁት ከውጭ የመጣው ይህን የመሰሉት ተፅእኖዎች፣ በአገራችን

ያለውን ትውፊት ማሳጣቱን ነው። ትምህርቱ ብቻ አይደለም፤ በሙዚቃውም ተመሳሳይ ወረራ ነው፡፡ መሰንቆው፣ ክራሩ፣

ዋሽንቱ፤ ከበሮው የተረሳበትና የማያስፈልግበት ነገር ቀጠለ፡፡
በ1960ው በ1970ው በሙዚቃው ያለው ነገር ሁሉም ከምዕራቡ ዓለም መጥቶ ነው፡፡ እናም በእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ

ጭንቅላታችን ተደብድቧል፡፡ ወደን በሰጠነው ፍቃድ በውጭው አገር ባህል ተበርዘናል። ይህም የራሳችንን ታሪክ

እንድንርቅ፣ ባህላችንን እንድንጠላ አድርጎናል፡፡ መማር ማወቅ ማለት የውጭ ስልጣኔ ተባለ። ስልጣኔ የራሱን ቋንቋ፣

ባህል እና ታሪክ አስተወው፡፡ ዛሬ የምታየው ይህ ሁሉ መደነቃቀፍ፤ ይህ ሁሉ ሌላ ሆኖ መተያየት ከዚህ የተነሳ ነው፡፡

ይህ፤ ሰው ወዶ በራሱ እንዴት ባርያ እንደሆነ የሚያሳይ ነው፡፡ እነ ዩኔስኮ እኮ ዛሬ እኮ ቋንቋችሁን አዳብሩ፤ ልብሳችሁን

አትተው፤ ማንነታችሁ እየጠፋ ነው ብለው እየጨቀጨቁ ናቸው፡፡ ለዚህም ነው ዛሬ በኪነት ስሜትን የሚገዛ፤ ማንነትህን

የሚገልፅ አቀራረብ እንደገና ፈልገን እየሰራን ያለነው፡፡ ኢትዮጵያዊ ማንነትን መልሶ ለማምጣት እንደገና ለማስተማር

ነው፡፡ እኔ ወደ ራስ ጉዞን እመኛለሁ፡፡ ፍላጎቱንም እያየሁ ነው፡፡ የሰው ልጅ ትልቁ ነገር ራሱን ማወቅ ነው፡፡ አለበለዚያ

ቀውስ ውስጥ ይገባል፡፡ ከአዲሱ ‹‹ያምራል አገሬ›› አልበም በፊት በመፅሃፍት እና ሙዚቃ መልክ የሰራናቸው፣ ለህፃናት

ማስተማርያ ይሆናሉ ያልናቸው ሁለት ስራዎች አሉን፡፡  ለምሳሌ ስለ እነሶረኔ ስለ እነዳንኪራ፤ ስለ እነ አያጅቦ በሙዚቃ

በማጀብ ብቻ ሳይሆን ህፃናትን ሊያስረዱ በሚችሉ ትእይንቶች ተቀናብረው ተዘጋጅተዋል፡፡ እነዚህን መፅሃፍት፤ የዘፈን

ስብስቦች እና ቪድዮዎች ያዘጋጀነው ለህፃናት፤ ለወጣቱ እና ለአዛውንቱ እንደየእድሜው ነው፡፡ የማህበረሰቡን አኗኗር፣

አመለካከት፣ የፈጠራ ችሎታ ወዘተ የሚያንፀባርቁ ብዙ ታሪኮች ተሰባስበዋል፡፡ ስለባህላዊ የሙዚቃ መሳርያዎች አሰራር

እና አጨዋወት የሚያስገነዝቡ፤ የኢትዮጵያን ታሪኮች የሚያወሱ የመማርያ መፅሃፍት ተዘጋጅተው እንዲሰራጩ ለማድረግ

ከትምህርት እና ባህል ሚኒስቴር መስርያ ቤቶች ጋር በመተባበር ለመስራት ተስማምተናል፡፡
ባህላዊ የሙዚቃ መሳርያዎቻችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተሰሚነት ያገኛሉ?  ተፈላጊ የሚሆኑበት ገበያስ ይኖራቸዋል?
ክራር ዓለም አቀፍ የሙዚቃ መሳርያ አይደለም የሚሉት መጫወት የማይችሉት ናቸው፡፡ ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ፣ ስለ

ኢትዮጵያ ሙዚቃ አያውቁም፡፡ ማወቅ ስላልፈለጉ ወደ ውጭ አለም ገቡ፤ ማንነታችሁን አሳዩ  ሲባሉ የሚቀበላቸው

አጡ፡፡ የኢትዮጵያን ሙዚቃ ለማወቅ ሂድ እስቲ ጋምቤላ፤ ሂድ እስቲ ኢሊባቡር፤  ሂድ ጋሞጎፋ… ዛሬ ጃዝ ብለህ

የምታገኘውን ሙዚቃ እዚያ በየመንደሩ በባህላዊ ሙዚቃዎች ተሰርቶ ታገኛለህ፡፡
እነዚህን አገር በቀል የሙዚቃ ፈጠራዎች በልዩ ሁኔታ አቀናብረህ ለዓለም አቀፍ ገበያ ተፎካካሪ አድርገህ ማቅረብ

ትችላለህ፡፡ የራሳችንን ሙዚቃ አፍረን ትተነው እንጅ ባህላዊ የሙዚቃ መሳርያዎቻችን ስላልተፈለጉ አይደለም፡፡ እኔ

አለሁ አሁን፣ በባህላዊ ሙዚቃ መሳርያዎች እየተጫወትኩ ዓለምን የምዞረው፡፡ ስንት አፍሪካዊ በራሱ ሙዚቃ ባህል

ዓለምን ማርኮ የለም እንዴ፡፡ የዓለም ሙዚቃ መሰረቱ እኮ ከአፍሪካ ነው፡፡ አርቲስት ሙላቱ አስታጥቄ እንዲህ በዓለም

አቀፍ ደረጃ የገነነ የሙዚቃ ባለሙያ የሆነው በኢትዮጵያ ጨዋታ ስልት ነው፡፡ ባሉን ባህላዊ ትውፊቶች ለዓለም አቀፍ

ደረጃ የምንበቃበት ጅማሮዎች አሉ፤ ደረጃ በደረጃ እየታመነበት መጥቷል፡፡ በ“ያምራል አገሬ” አልበም ባህላዊ የሙዚቃ

መሳርያዎችን የምንጠቀመው ለዚህ ነው፡፡ ዋሽንት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ዋና የሚባል የሙዚቃ መሳርያ ነው፡፡ ሰዎች

በእረኝነት በየጫካው በየዱሩ፤ በየአካባቢው እራሳቸውን የሚያዝናኑበት፤ ከእንስሳቱ ጋር የሚጫወቱበት፤ ራሳቸውን

የሚያዩበት … የትንፋሽ መሳርያዎች አንዱ ነው፡፡ ክራርም እንደዚሁ ቅድመ ታሪክ ያለው፣ ስለክር መሳርያዎች ስናወራ

ግንባር ቀደም ሆኖ የሚጠቀስ፣ በብዙ የጨዋታ ስልቶች የዳበረ ትልቅ ሚና ያለው መሳርያ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ባህላዊ

ሙዚቃ ቅኝቶች ከክራር ገመዶች የመነጩ ናቸው። ከበሮዎችም በየሰርጉ፣ በየድግሱ፣ በማህበረሰባዊ ጨዋታዎች

የሚያስፈልግ መሳርያ እንደሆነ ይታወቃል። የሌሎች የሙዚቃ መሳርያዎች ድጋፍ ሳያስፈልግ በከበሮ ጨዋታ ሊደምቅ

ይችላል፡፡ ከበሮ የሌሎች የሙዚቃ መሳርያዎችን አጀብ ሳትፈልግ የምትሰራበት ነው፡፡ መሰንቆ ደግሞ ራሱን የቻለ

እንደክራር ትልቅ ጥቅም ያለው፣ ከአገር ወደ አገር ተሸክመኸው በቀላሉ የምትጓዝበት ነው፡፡ የአዝማሪ ዋና መለያው

መሳርያ ነው። እነዚህንና ሌሎች የሙዚቃ መሳርያዎችን በመጠቀም ታሪኩን ማንነቱን በአንድ ላይ አዋህዶ በማቅረብ

ዓለምን መማረክ አያዳግትም። በባህላዊ ሙዚቃ መሳርያዎች ኢትዮጵያዊ ባህልን ማሳየት ይቻላል፡፡ ባህሉን በባህል

መስራት ነው፡፡ ከታሪክ እና ከማንነት የተዋሃደ አቀራረብ እንጅ ከሌላ በመጣ ባህል ጉራማይሌ መሆን የለበትም፡፡
በዘፈኖችህ ላይ የድምፅ ቅላፄህን በተለያየ መንገድ እና ስሜት ታወጣለህ፡፡ በሌላ በኩል ብዙውን ጊዜ ሙዚቃዎችህን

መድረክ ላይ ስትጫወት የምትጨማምረው ነገር አታጣም፤ ከምን የተነሳ ነው?
የኢትዮጵያ ሙዚቃ ከሌላው አለም የሚለይበት አንዱም ምክንያት፣ የአዘፋፈን ስልቱ እና የድምፅ ቅላፄ አወጣጥ ነው፡፡

ማንሾካሾክ ነው፡፡ ከአፍ ሳይሆን ከሆድ ውስጥ የሚወጣ ማንሾካሾክ ነው፡፡ የድምፅ ሂደቶች አሉ፡፡ በጣም የተኛ፣

ከመሬት ውስጥ ቆፍሮ የሚወጣ የሚመስል ድምፅ አለ፡፡ ለምሳሌ አባይ በሚለው ዘፈን ላይ ስትሰማ፣ በመጀመርያው

ስንኞች ‹‹አባቱ መጀን እናቱ ጣና›› የሚለው ድምፅ ላይ ከስር እንደ እሳተ ጎመራ የሚወጣ ድምፅ አለ፡፡ ነፍስ ያለው፣

ከስሜት ጋር የተገናኘ ድምፅ ነው፡፡ የተለያዩ ሙዚቃ ማጀቢያ ምታዊ ዘዴዎችም አሉ፡፡ እንደማጨብጨብ ፤ እንደጣትን

ማንጣጣት እንደማፏጨት አይነት  ነው፡፡ በማንሾካሾክ እና የተለያዩ ድምፆችን በማውጣት መዝፈን ነው፡፡ በዚህ

መንገድ ሙዚቃዎቼን መስራት ፍላጎቴ በመሆኑ ነው፡፡ ለእኛ አገር ሰዎች የነበረውን አዘፋፈን እና የራሴን ፈጠራ በማከል

የምሰራው ነው፡፡ ድምፆቹ ከመመራመር፤ ታሪኮችን ከመመርመር የሚፈልቁ ናቸው፡፡ ቀስ በቀስ የሚዳብሩ ናቸው፡፡ አሁን

በአገራችን ባሉት ሙዚቃዎች  አዘፋፈን የተለመደው አንድ አይነት ድምፅ ነው፡፡ አንድ አይነት አገላለፅ ነው፡፡ አንዱ

ዘፈን ከሌላው የሚለይበት መልክ የለውም፡፡ እኔ ራሴ የማወጣቸው ድምፆች ግን በየዘፈኑ እንደየመልኩ እና

እንደሁኔታው በፈጠራ የማወጣቸው ናቸው፡፡ የተለያዩ ድምፆችን የማውጣት ጥቅም በሙዚቃው ነገሮችን በተለያየ

አቅጣጫ ማየት ስለሚያስችል ነው፡፡ የኢትዮጵያ የሙዚቃ ቅኝቶች አራት ናቸው ይባላል፡፡ ባቲ፣ አምባሰል፣ አንቺ ሆዬ..  

እየተባሉ የተሰጡ የሙዚቃ ቅኝቶች ስያሜዎች ናቸው። ለእኔ ቃኘ ማለት አየ ማለት ነው፡፡ ቃኘ ማለት አዳመጠ ማለት

ነው። አሁን ድምፅ የምትቃኘው ሰምተህ እንደ አላርም ነው፡፡ ሰማ ማለት አየ፤ አየ ማለት ደግሞ ሰማ ነው። ስለዚህ

ምንድነው…. ሁኔታዎችን በተለያየ መንገድ ማየት መቻል አለብህ፡፡ ጠዋት ተነስተህ ውለህ፣ ማታ ተኝተህ በየቀኑ አንድ

አይነት ነገሮችን የምታደርግ ከሆነ፣ የሰውነት ባህርይ ወይንም የማሰብ ባህርይ እንደ ሰው አይደለም፡፡፡ ማንም ሰው

ነገሮችን በብዙ መንገድ እና በተለያየ ሁኔታ ማየት እና መገንዘብ አለበት፡፡ በያይነቱ መንገድ  ፈልጎ መቃኘት አለበት፡፡

ከሰጭነት ይልቅ ተቀባይነቱ፤ የተሰጠህን ስትቀበል በተለያየ አቅጣጫ ማየት ይኖርብሃል፡፡ የሰጭው ብቻ ሁኔታ መሆን

የለበትም፡፡ አንተ መፅሃፍ ሰርተህ እኔ ሳነበው እኔ በሚሰማኝ ስሜት፤ ከምሄድበት ጎዳና ጋር እያነፃፀርኩ እና

እያመሳከርኩ መጓዝ አለብኝ፡፡ እኔ ያንተን ህይወት ከእኔው ጋር አዛምጄው  የራሴን ግንዛቤ እንድፈልግ ማድረግ ነው፡፡
እኔ በተፈጥሮዬ አስተዳደጌ ላይ ከነበረው ነፃነት፤ ከሰፈር አኗኗር ብዙ የተማርኩት አለ፡፡ ዛሬም ቢሆን እኔ የህብረተሰቡን

አኗኗር እና ሁኔታ ማወቅም መኖርም ስለምወድ የማልገባበት ቦታ የለም፡፡ እኔ ካቲካላ ቤት፤ ጠላ ቤት እገባለሁ፤

ከወገኖቼ ጋር መጫወት ደስ ይለኛል፡፡ አርቲስት ሆነህ የጠላ መጠጫ ሽክናን በእጅህ ካልያዝከው፣ ጠላውን ካልጠጣህ

ስለጠላ ምን ልታወራ ነው፡፡ በሙዚቃዎቼ ያሉት  ሁኔታዎች የማውቃቸው፤ ያደረግኳቸው፣ የለምድኳቸው የማህበረሰብ

ነባራዊ ገፅታዎች ናቸው፡፡ ጥሩ ሙዚቃ ድምፅን እንደ ስዕል በሚያሳይ አገላለፅ የሚቀርብ ነው፡፡ በጥሩ ሙዚቃ ውጥት

ባለ ድምፅ ውስጥ ሃዘኑን፣ ደስታውን፣ ትዝታውን፣ መከራውን፣ ሰቆቃውን ትሰማበታለህ። ግጥሙን ተወው፤ የሰውዬውን

የድምፅ አወጣጥ፣ ቅላፄውን አድምጠህ መረዳት ትችልበታለህ፡፡ ሙዚቃን የሚያዳምጥ ሰው፤ ስሜቱን መግዛት

የምትችለው በተለያየ የድምፅ ሂደት ስትዘፍን እና ስትጫወት ነው፡፡
በሙዚቃዬ ሁሌም እንደአዲስ መስራት መጫወት እፈልጋለሁ፡፡ ዋናው ነፃነቱ ነው፡፡ ኪነት ነፃነት ነው፡፡ ኪነት ከሁሉ

ነገር ነፃ የሚያደርግ ጥበብ ነው፡፡ ለሰው ብለህ አይደለም የምትሰራው፡፡ ስሜትህን ከውስጥ የሚሰማህን ነገር አውጥተህ

በነፃነት መስጠት መቻል አለብህ፡፡ ከብዙ ጊዜ ልምድ በመነሳት ሰው ምን ማወቅ፣ ምን ማየት እንደሚፈልግ በመረዳት

የምታደርገው ነው፡፡ ነገሮችን በይበልጥ እይታ እና ስሜት ውስጥ እንዲገቡ ማድረግ ነው፤ ‹‹ኢምፕሮቫይዜሽን››፡፡ ማንም

ሰው በሙዚቃህ የበለጠ እይታ እና መግባባት እንዲኖረው ማድረግ ያስደስታል፡፡ በዜማ፣ በግጥምና በውዝዋዜ አሻሽለህ

በመስራትና በማዳበር ማዝናናት ትችላለህ፡፡ እንቅስቃሴን እየሰባበርክ ታዳሚህ የበለጠ እይታ እንዲኖረው፣ በፍላጎት

ስትሰራበት የሚያዋጣ ይሆናል፡፡ ይህ ሁሉ ማንም ሰው ሙዚቃውን በጥልቀት እንዲገነዘበው ነው፡፡
ግጥሞችህን እንዴትና በምን አይነት ሁኔታ ትፅፋቸዋለህ?
እኔ ግጥም ቁጭ ብዬ ቃላት በመደርደርና ቤት በመምታት  አልፅፍም፡፡ በመጀመርያ ስሜቴን ነው የማዳምጠው፡፡

መንገድ እየሄድኩ ከሆነ፣ በየአካባቢው ያየሁትን እንድምታ በጭንቅላቴ አስቀምጠዋለሁ፡፡ ከዚያ በኋላ በአዕምሮዬ

የተቀመጠውን ነገር በስሜት እገልፀዋለሁ፡፡ ቃላቶች ቤት እንዲመቱ ብዬ አልጨነቅም፡፡ እይታው ላይ ነው የማተኩረው

፡፡ የተፈጠሩ ሁኔታዎች በአግባቡ መገለፅ አለባቸው፡፡ አሁን ብዙዎች ስለዛፍ ሲያወሩ አስበውት ነው፡፡ እኔ የዛፍን እይታ

በደንብ አዕምሮዬ ውስጥ አስቀምጠዋለሁ፡፡ የዛፍን መንፈስ እና ህይወት በአዕምሮ እንደስንቅ ካኖርከው በኋላ፣ የዛፍን

ጠቀሜታ ካዋሃድክ በኋላ ትተነፍሰዋለህ ማለት ነው፡፡ ትንፋሽህን በፅሁፍ መልክ ወረቀት ላይ ታስቀምጠዋለህ። ለምሳሌ

ልጅ ሲወለድ እንዴት ነው? ፅንስ መጀመርያ የሚፈጠረው ከሁለት ህይወት ውስጥ ነው፡፡ ልጁ የሚመጣው በኋላ ነው፡፡

ከዚያ  በፊት ግን ልጅ ቢኖረኝ ብለህ ሃሳቡን ትፀንሳለህ፡፡ ፅንሱ ተፀንሶ ነው ከዚያ በኋላ ልጅ የሚወለደው፡፡ አንድ

ሃሳብ መፀነስ አለበት። በአዕምሮህ ሳይፀነስ የተገጠመ ሃሳብ ግጥም መስሎ አይታየኝም፡፡ ሃሳብን ፀንሰኸው አርግዘኸው

ስትወልደው እያንዳንዱን ህመም፣ ደስታውን፣ አካሄዱን ስትናገር ለሌላው የሚሰማ ይሆናል፡፡ ያንተን ፅንስ ከዚያ በኋላ

ሌላው ይወልደዋል፡፡ በ“ያምራል አገሬ” አልበም ውስጥ ባሉ ዜማዎች ያሉ የግጥም ሃሳቦች መነሻቸው ስዕላዊ ድርሰት

ነው፡፡ ሰው የኖረበትና የሄደበትን ህይወት የሚያሳዩ ናቸው፡፡ ዘፈኖቹ የተመረጡት ከብዙዎች መካከል ነው፡፡ በሺዎች

የሚቆጠሩ ሙዚቃዎች አሉ፤ የተፃፉ የተቀመጡ ናቸው፡፡ እነዚህ የሙዚቃ ጨዋታዎች የሚያገለግሉት ለምንድነው? አንድ

ራሱን የቻለ ባህል ቀደም ሲል ትውፊቱ  የነበረና ለብዙ አመት ተረስቶ የቆየ፤ እይታው ሁሉ ጠፍቶ የነበረውን እንደገና

እንዲነሳ በታሰበ ዓላማ የተሰሩ ናቸው፡፡ ስለምንትዋብ፤ ስለጋሽ አበራ ሞላ፤ ስለአባይ ስናወራ፣ እነዚህ ሁኔታዎች ጥሩ

እይታ የሚፈጥሩ ይሆናሉ በሚል ነው፡፡ የኢትዮጵያ ባህላዊ ትውፊቶች ደብዝዘው እና ጠፍተው በነበሩበት ሁኔታ ላይ

እነዚህን አይነት ዜማዊ  ስዕሎች በህዝብ አይምሮ ውስጥ እንዲገቡ በማድረግ፣ ከህፃናት አንስቶ እስከ አዛውንት

እንዲሰሙት እንዲነሳሱበት ነው፡፡ ሁሉም ሰው ሲሰማው ማንነቱን ማወቅ ይፈልጋል፡፡
ጋሽ አበራ ሞላ ምን አይነት ሰው ናቸው?
ጋሽ አበራ ሞላን በስብዕናቸው ብገልፅልህ ባህርያቸውን  አርቲስት ስለሺ ደምሴ ራሱ ነው የሚል መደምደሚያ ላይ

ትደርስ ይሆናል፡፡ ጋሽ አበራ ሞላ የሚለው ስሙን ራሱን ተርጉመህ ተንትነው፡፡ ጋሽ የሚለው አክብሮት ነው፡፡ ወንድም

ጋሼ፤ መከታዬ፤ ጋሻዬ ብላ አክብሮትህን ትገልፅበታለህ፡፡ ጥላ፤ ከለላዬ፤ ጥንካሬዬ ብለህ የምትረዳው የሙገሳ ማዕረግ

ነው፡፡ አበራ ብለህ ስትጠራ ደግሞ ብሩህ፤ ብርሃን፤ አንድ ነገር አበራ ስትል እይታ ፈጠረ፤ ተስፋ ፈጠረ ብለህ

የምትገልፀው ነው፡፡ ሞላ ደግሞ የሃሳብህን መሙላት፤ ያሰብከው ስለተሳካ የምትገልፅበት ትርጉም ይኖረዋል፡፡ ስሙ

በእነዚህ ትርጓሜዎች አንድነት የሚገለፅ ነው፡፡ ስለዚህ ጋሽ አበራ ሞላ እንደስሞቹ ትርጓሜ አሳቢ ሰው፤ ብርሃንን ማየት

የሚሻ፤ ተስፋን ማግኘት የሚፈልግ፤ አዋቂ ብልህ መካሪ፤ በህብረተሰቡ ውስጥ የተከበረ፣ አንቱ የሚባል ስብዕና ይኖረዋል

ማለት ነው፡፡ ጋሽ አበራ ሞላ የሚባል በህይወት ይኑርም አይኑርም ጥሩ ኢትዮጵያዊ አባወራ ማለት ነው፡፡

Read 6115 times