Saturday, 12 November 2011 08:28

ቃላትን ዘላለማዊ ማድረግ

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(2 votes)

ተሰማ ሀብተሚካኤል በ1951 ዓ.ም ባሳተሙት ከሳቴ ብርሃን የአማርኛ መዝገበ ቃላት መጽሐፍ መግቢያ ላይ አማርኛ ቋንቋ ግእዝን ተክቶ ለንግግር በብዙኃኑ እየተመረጠ ከመጣ በኋላ ብዙ ዓመታትን ሲያስቆጥር መዝገበ ቃላት የሚያዘጋጅለት በማጣቱ ምክንያት የደረሰውን ጉዳት ሲገልጹ፡- “በልዩ ልዩ የዐምሐራ አገሮች ውስጥ ይነገር የነበረውን ልዩ ልዩ ቃላትና የንግግር ስልት ከወዴት እንደተነገረ እንዲታወቅ መዝገበ ቃላትና፤ የሰዋሰው መጽሐፍ የጻፈለት ሳይኖር፣ በዝርው ቃላት ሲነገር እስካሁን ድረስ ኖረ፡፡

በዚህም ምክንያት በእየአውራጃው ይነገር የነበረው ዐማርኛ እየተረሳ፣ እየተለዋወጠና እየሞተ በርሱ ፈንታ ከነጋዴና ከስደተኛ የሚነገር ባዕድ ቋንቋ እየተተካ በመኖሩ የጥንቱን ዐማርኛ ለማግኘትና፣ ለማወቅ ለሥራውም አስቸጋሪ ኾነ፡፡ ማንኛውም ቋንቋ ከአባቶች ሲወርድ ሲዋረድ መጥቶ በትምህርት ቤት እየተነገረና እየተራባ ርስ በርሱም እየተካለሰና እየተራዘመ ካልሄደ፣ የቋንቋ ባህል፣ ኃይለ ቃል፣ የአገር ልምድም በየጊዜው እየተለዋወጠ ይሔዳል፡፡ ከዚህ በኋላ ሕዝቡ የቀድሞ የአባቶቹንና የአገሩን ታሪክ ወደ አለማወቅ ይደርሳል፡፡” 
በልምድና በትምህርት የፀሐፊነት (ደራሲነት) ሥራ ላይ የተማሰሩ ሰዎች ባለ ውለታ የሚሆኑት እዚህ ላይ ይሆናል፡፡ የሰው ልጅ ከዕለት ማግስት በየዘርፉ የሚያስመዘግበው ለውጥና ዕድገት አለ፡፡ ከዚህ ለውጥ ጋር አብሮ የሚያድገው ቋንቋ በየጊዜው የሚፈጠሩለትን ቃላት ቀጣይነት እንዲኖራቸው፣ እንዳይረሱ ወይም ተመዝግበው ለትውልድ እንዲተላለፉ በማድረጉ ረገድ ፀሐፊያን የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳሉ፡፡
ሀብታም፣ ዲታ፣ ባለፀጋ የሚል ትርጉም ያለው “ሞጃ” የሚለው ቃል በአሁኑ ዘመን የሚጠቀምበት ብዙ ሰው የለም፡፡ ከ30 ዓመት በፊት ግን የአገራችንን ባለፀጎች ለመግለጽ ተመራጩ ቃል ሞጃ ነበር፡፡ ሞጃ ቤተሰቦች፣ የሞጃ ሚስት፣ ሞጃ ሴት … ማለት የተለመደ ነበር፡ እከሌ ሞጃ ይመስላል ከተባለ ትርጉሙ የተመቸው፣ የደላው ወፍራም ነው ለማለት ነው፡፡
የአማርኛ መዝገበ ቃላትን ወይም የቆዩ መፃሕፍትን ስናነብ እንዲህ ዓይነት አገልግሎት ሰጪነታቸውን የተቋረጠ የሚመስሉ ብዙ ቃላት ይገጥሙናል፡፡ ጥሩነቱ በተለይ በመዛግብተ ቃላት ላይ ሰፍረው የሚገኙት ከነትርጉማቸው ስለሆነ የመጥፋትና የመረሳት ዕድላቸው ዜሮ ሆኗል፡፡ ወይም በየዕለቱ ለጽሑፍና ንግግር ሲያገለግሉ ባይታዩም አልሞቱም፡፡
በአገራችን የመዛግብተ ቃላት ዝግጅት ታሪክ ምን እንደሚመስል ሰፋ ያለ መረጃ የሚሰጠው፤ በኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል ተዘጋጅቶ ለመጀመሪያ ጊዜ በ1993 ዓ.ም የታተመው “አማርኛ መዝገበ ቃላት” ሲሆን በአገራችን በግለሰቦችም ይሁን በተቋማት ተዘጋጅተው የቀረቡት መዛግብተ ቃላት አንዳቸውም ቢሆኑ ከጊዜው ጋር እያደጉ፣ አዳዲስ ቃላት፣ ሐረጋትና አገላለፆችን እየጨመሩ መታተም የቻሉ አይመስልም፡፡
በኦክስፎርድ የእንግሊዝኛው መዝገበ ቃላት ላይ እንደሚታየው አዳዲስ ቃላትን፣ ሐረጋትንና አገላለፆችን እየጨመሩ ሁለተኛ፣ ሦስተኛ … እትም በሚል መቅረብ የቻለ የአማርኛ መዝገበ ቃላት መጽሐፍ ያለ ባይመስልም ከዘመንና ከትውልድ መለዋወጥ ጋር አዳዲስ ቃላት መፈጠራቸው አልተገታም፡፡ እነዚህን ቃላት መዝግቦ በማኖሩም በኩል ደራሲያን፣ የመገናኛ ብዙኋን ባለሙያዎችና መድረኩ አዎንታዊ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛሉ፡፡ ጥቂት ማሳያ እነሆ፡፡
የዛሬ 12 ዓመት የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ሲካሄድ የመንግሥት ቃል አቀባይ ሆነው ይሰሩ የነበሩ ሴት ባለስልጣን ከአንድ ጋዜጣ ጋር ቃለ መጠይቅ ሲያደርጉ የቀረበላቸው የመጀመሪያ ጥያቄ “ወይዘሮ ልበል ወይስ ወይዘሪት?” ሲባሉ ጥያቄው መግለጽ የማይፈልጉት የግል ጉዳያቸውን ይፋ የሚያደርግ ስለሆነባቸው ይመስላል፡፡ “ወይዘሮና ወይዘሪትን ቀላቅሎ ወይዝ የሚል ቃል መፍጠር ይቻላል፡፡ ስለዚህ ወይዝ ብለህ ልትጠራኝ ትችላለህ” የሚል ምላሽ ሰጥተው ነበር፡፡
በንግግር ክፍሎች በቅጽል (Pronoun) የሚመደበውና ክብርን መግለጫ የሆነው “ወይዝ” የሚለውን ቃል የፈጠሩት ሴት ከጋዜጣው ቃለ መጠይቅ በኋላ “ወይዝ”ን ለስማቸው ቅጽል በማድረግ ተጠቅመውበታል ወይ? እሳቸውን ተከትሎስ የተገለገለበት ይኖር ይሆን? የጥያቄዎቹ መልስ ምንም ይሁን ምን በአንድ ምክንያታዊ በሆነ አጋጣሚ የተፈጠረው ቃል በየጋዜጣው መዘገብ ስለቻለ ከዓመታት በኋላ በዚህ ገጽ ታወሰ፡፡
የቁርስ፣ የምሳና፣ የራት ሰዓታት ለምን እንደሚውሉ ነጋሪ አይሹም፡፡ ኑሮው ሲመች፣ አቅሙ ሲኖር ደግሞ መቆያ ምግብ ለመመገብ የመክሰስ ሰዓት የሚመድቡም አሉ፡፡ “ቁምሳ” እና “ምራት” የሚሉት ቃላት የምግብ ሰዓትን ገላጭ ሆነው ወደ አማርኛ ቋንቋ ከተቀላቀሉ ጥቂት ዓመታትን አስቆጥረዋል፡፡
ለቃላቱ መፈጠር ምክንያት የሆነው የኑሮ ውድነት ነው፡፡ በመጀመሪያ የመመገቢያ ሰዓት መሆኑ እየተረሳ የመጣው መክሰስ ነበር፡፡ በቀን 3 ጊዜ መመገብ ያልቻሉ ሰዎች በቁርስና በምሳ መሐል የሚመገቡበትን ሰዓት ሁለቱን ቃላት በመቀላቀል “ቁምሳ” ሲሉት የምሳና የራቱን ጊዜ ደግሞ “ምራት” ብለው ሰየሙት፡፡ እነዚህን ሁለት ቃላት በ1994 ዓ.ም የታተመው ”ዘርጋው የአማርኛ መዝገበ ቃላት” መጽሐፍ መዝግቦ ለትውልድ እንዲተላለፉ አድርጓል፡፡
ቃላትን መዝግበው ለትውልድ እንዲተላለፍ በማድረግ ብቻ ሳይሆን አዳዲስ ቃላትንም በመፍጠር በጽሑፍ ሥራ ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች ድርሻ ላቅ ብሎ ይታያል፡፡ በዶ/ር ፈቃደ አዘዘ የአማርኛ መፃሕፍት ላይ የሚታዩትን የቃላት ፈጠራ በምሳሌነት ማንሳት ይቻላል፡፡ “ሳንሱር አድራጊው” ለማለት “ሰንሳሪው”፣ “ኤዲተር” ለማለት “አዳች”፣ “ዲዛይን ሰራች” ለማለት ደዘነች … እያሉ በተለይ የእንግሊዝኛ ቃላትን በተሻለ አገላለጽ ወደ አማርኛ ለማሸጋገር ጥረት እንደሚያደርጉ ይታያል፡፡
የጋዜጠኛና ደራሲ አብርሃም ረታ ዓለሙን ሙከራ እዚህ ላይ በምሳሌነት ማንሳትም ይቻላል፡፡ በ1999 ዓ.ም “አከራይ ተከራይ አካከራይ” በሚል ርዕስ ባሳተመው መጽሐፍ ላይ “አካከራይ” የሚለውን ቃል የተጠቀመው አከራይና ተከራይ አገናኝ/ደላላው የሆነውን ለመግለጽ ነው የሚመስለው፡፡
ገጣሚ ደበበ ሰይፉ “ልጅቱ-የዘመነችቱ” በሚለው የግጥም ሥራ ውስጥ ሱሪዋን ሱርት፣ ጫማዋን ጭምት፣ ቀበቶዋን ቅብትት፣ ጃኬቷን ጅክት … የሚሉ አገላለፆችን በመጠቀም የፈጠራቸውን የሚመስሉ አዳዲስ ቃላት ፈጣሪዎች ብዙ ናቸው፡፡ የወለደ ሰው ዓለምን ሲሰናበት አልሞተም እንደሚባለው፤ በተለያዩ አጋጣሚዎችና በየጥጋጥጉ የሚፈጠሩ ቃላትም በመጽሐፍና ጋዜጣ በመሳሰሉት ቋሚ ቅርሶች የመስፈር ዕድል ሲያገኙ ዘላለማዊ ይሆናሉ፡፡
ቃላትን ዘላለማዊ ለማድረግና በቀጣይነትም አገልግሎት እየሰጡ እንዲቀጥሉ በማድረጉ ረገድ በመዛግብተ ቃላት መፃሕፍት መስፈር የቻሉት ቃላት የተሻለ ዕድል አላቸው፡፡ ይህንን የተረዱ አገራትና ሕዝቦች ከቋንቋቸው ዕድገት ጋር የመዝገበ ቃላት መጽሐፋቸውን እያሻሻሉ በማተም ያቀርባሉ፡፡ ከዚህ አንፃር በእኛ አገር ክፍተት ያለ ይመስላል፡፡ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል የአማርኛ መዝገበ ቃላት በ2001 ዓ.ም ዳግመኛ ሲታተም መጠነኛ ማስተካከያ ተደርጎበታል፡፡ ጅምሩ ቢቀጥል መልካም ነው፡፡ እንዲህም ሆኖ በግለሰቦች ጥረት ብዙ ቃላት የዘላለማዊነት ዕድል ማግኘት ግን ችለዋል፡፡

Read 4630 times